ያልተዘመረላቸው ጀግኖች
የኔሰው ጓንጉል This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
”ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ከሰጪው የተለየ ሀሳብ ላለው ካልተሰጠ መብቱ እርባና ቢስ ነው።”
ሮዛ ሉክዘምበርግ ለሌኒን ከጻፈችው ደብዳቤ
ከሁለት ዓመት በፊት ኢትዮጵያ እያለሁ ከጠዋቶች ሁሉ የሚናፍቀኝ የቅዳሜው ነበር። የእረፍት ቀን ስለሆነ ወይም አርፍዶ ለመነሳት አልነበረም። ቅዳሜ ጠዋት መኪናዬ ውስጥ ቁጭ ብዬ የ”ካልዲ”ን ማኪያቶ እየተጎነጨሁ፤ ለስላሳዋ ጸሀይ እየዳበሰችኝ፤ ደስ የሚል ሙቀት እየፈጠረችብኝ ”አዲስ ነገር”ን ጋዜጣ ለማንበብ ነበር።
በጠዋቱ ካልተነሳሁ ረፈድፈድ ብሎ ለሚነሣ ”አዲስ ነገር” ከጋዜጣ አዟሪዎች ጋር ስትዞር አታገኟትም። የአገር ሳይሆን የወያኔ ደህንነቶች የቻሉትን ያህል ገዝተው አንባቢ እጅ እንዳትደርስ ብዙ ኮፒዎቿን ካራቁት (አቃጥለው ይሁን ቀብረው) ከተረፈችው፤ አንባቢ ለማግኘት በቅዳሜ አርፍዶ የሚነሳ ሰው መሆን አይጠበቅም። የ”አዲስ ነገር” መጨረሻ አካባቢ መስፍን ነጋሽ እየደረሰባቸው ስላለው ጫና የሚጽፋቸው ጽሁፎች መሰነባበቻ ይሆናል ብዬ በፍጹም አልጠበቅኩም ነበር። ”ይህቺ አገር የማናት?” ብሎ ሲጠይቅ ጥያቄ ውስጥ ከቶን የሚለየን አልመሰለኝም ነበር። ይህን ያልጠበቅኩት በ”መንግስታችን” ዲሞክራትነት እምነት ኖሮኝ ሳይሆን፤ ጋዜጣው መንግስት ጉድፉን እንዲያይበት የሚጠቅመው መስታወት ነው ብዬ ስለማምን ነበር። የራሱ መስታወት ባይኖረውም መንግስት የማይዋሸውን መስታወት ይሰብራል ብዬ አልገመትኩም። ጥሩ ገማች ግን አልነበርኩም። መስታወቱ በአንድ ቅዳሜ ተሰብሮ ጠበቀኝ።
እንደለመድኩት ጠዋት ተነስቼ የ”ፍላሚንጎ”ን ማኪያቶ አልፌ ”ሜሞ ክለብ” ፊት ለፊት ያለው ”ካልዲ” ቆሜ ”አዲስ ነገር” እና ሾርት ካፑቺኖ አዘዝኩ። ጋዜጣ ሻጩ ደንበኛዬ ”አዲስ ነገር ጋዜጣ የለችም ጋሼ።” ሲለኝ
”በጠዋቱ አለቀ እንዳትለኝ” አልኩት
”አዪ … ምን ማለቅ ጋሼ። መታተም አቁማለች።”
በድንጋጤ ”እንዴት? … ለምን?” ብዬ ስጠይቀው
”ጋሼ እነዚህ ሰዎች መች ጥሩ ሰው ያሰሩና። የጋዜጣው አዘጋጆች ግማሻቸው ከአገር ወጡ፤ ግማሻቸው መጻፍ አቆሙ ነው የሚባለው። አዲስ አድማስ ይፈልጋሉ?” ሲለኝ ከሀሳቤ ነቃሁ።
”እኔስ ከዚህ ውጪ አዲስ አድማስ አልፈልግም።” አልኩት የአገሬን አድማስ በአይኔ እያሳየሁት
”አረ ያንብቧት ጋሼ።” ብሎ ጋዜጣ ሲሰጠኝ ስለ ”አዲስ አድማስ” ጋዜጣ እንደሚጠይቀኝ ገባኝ።
”አይ አመሰግናለሁ።” ብዬ ጋዜጣውን በእጄ ገፋ አድርጌ በሀሳብ ጠፋሁ። ጋዜጣ ሻጩም አላስጨነቀኝም። ብቻዬን ትቶኝ ሔደ። ደስ የማይል ስሜት ውስጤ ነገሠ። ብስጭት፤ ተስፋ መቁረጥ፤ ስለ ሀገሬ ስጋት፤ እንደገና ብስጭት ደግመው ደጋግመው ስሜቴን ናጡት። ”ምንድን ነው መፍትሄው?” ብዬ ራሴን ጠየቅኩ። መልስ የለም። መልሱ ንዴቴ ብቻ ነበር።
”አዲስ ነገር”ን ከተጀመረች ጀምሮ የማውቃትን ያህል ወደ ኃላ አሰብኳት።
በስደት ከምኖርበት አገር ለእረፍት ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁ ጊዜ ነበር ”አዲስ ነገር”ን የማንበብ እድሉ የገጠመኝ። እንደ አጋጣሚ ሆኖ የተጀመረች አካባቢ ነበር የደረስኩባት። የጋዜጣዋን ሙሉ ገጽ እንደሚጥም ምግብ ጥርግ አድርጌ ነበር የማነባት (ፊደላት ከወረቀት ተነስተው በጉርሻ የማይበሉ ቢሆኑም)። በሁለት ወር የአገር ቤት ቆይታዬ አንድም እትም ሳያመልጠኝ፤ ከእውነት እና መረጃ ተቃመስኩ።ወደ እምኖርበት አገር ስመለስ በአገራችን ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ለምወያየው የስደት ጓደኛዬ ስለ ”አዲስ ነገር” ጋዜጣ ምርጥነት ስነግረው፤ በጣም ቅርባቸው አጠገባቸው ካለ ሰው ሰማሁ ብሎ የነገረኝ አልዋጥ አለኝ። በጆሮዬ ሳይሆን ጮክ ብሎ (በስደት አለም ባለ የነጻነት አወራር) ”እራሳቸው ነው ያቋቋሙት” አለኝ።
እነማን ናቸው ራሳቸው? ብዬ ስጠይቀው
”ወያኔዎች ናቸዋ! ከመስራቾቹ አንዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ነበር የሚሰራው። የደህንነት ጋዜጣ ነች አትመናት።” አለኝ ረገጥ አድርጎ
ጓደኛዬን በብዙ ቁም ነገር ባምነውም እዚህ ላይ ግን ላምነው አልቻልኩም። እንደሡ ለጋዜጣው ቅርብ ከሆነ ሰው የሠማሁት ባይኖርም ጋዜጣዋን ቀረብ ብዬ አንብቤአታለሁ። እነሡን እነሡን የሚል የመረጃ ጣእም ግን አላገኘሁባትም። ከመስጠት ግን አልተቆጠብኩም-ተፈጥሮዬ ስለሆነ።
ቀናት፤ ሳምንታት ሆነው፤ ወራት ደግሞ መንፈቅ ሲሆኑ ቢከፋም ቢለማም ብዬ የቀረችኝን እድሜ አገሬ ላይ ለማሳለፍ፤ ጓዜን እና ጥሪቴን ቀረብቤ ”በሰማዩ ባቡር” ወደ አገሬ ተመለስኩ። ከዘመድ እና ጓደኛ እንዲሁም አንብቤ ከወደድኳት አዲስ ነገር ጋር ዳግም ተገናኘሁ። ”እነሡን እነሡን” የሚል ነገር አድፍጩ ብፈልግባትም አንድም ነገር አጣሁ። ያገኘሁባት ነገር ቢኖር ከዚህ በፊት በፖለቲካችን ባልተለመደ በኩል ቱባ ቱባ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎቻችን ጋዜጣዋ ላይ መጻፍ መጀመራቸው ነው። አቶ ስዬ አብርሃ ደስ ከሚል ፈገግታቸው ጋር ስለ ወቅታዊ ሁኔታ፤ ሀይሉ ሻውል (ኢ/ር) ቆፍጠን ብለው የፖለቲካ አቋማቸውን ሲተነትኑ ማንበብ ደስ የሚል ነገር ነበር። ቅዳሜንም አዲስ ነገር እንድናፍቅ አደረገችኝ። ግን ቅዳሜን መናፈቁ አንድ ጠዋት ላይ አበቃ። ወጣቶቹ ምሁራን እርስበራሳቸው ሳይስማሙ ሣይሆን በግድ ለሚገዛን መንግስት ሳይስማሙ ሲቀሩ እንዲበታተኑ ተደረገ። ለምን? ብሎ ለሚጠይቁ አገሩን የጠቀለሉት ሚኒስትር መልሳቸው ”እኔንጃ! እንሱንም አዲስ ዘመንንም አላውቃቸውም። አይቻቸውም አላውቅም። አነማን ናቸው? ነበር መልሳቸው። - የሌባ አይነደረቅ
አዲስ ነገሮች፤ አዲስ ዘመን አንሆንም አሉ። ይሄኔ ነው ነገር የመጣው። መለስ ዜናዊ ካቢኔውን ብቻ አይደለም ሳይጠፈጥፍ ቅርጽ መስጠት የሚፈልገው። ነጻ ፕሬሱንም ነው። Pliant tools አልሆንም፤ የተፈጠርኩት ያየሁትን፤ የኖርኩትን እንጂ የተባልኩትን የታዘዝኩትን ”ካርቦን ኮፒ” ለማድረግ አይደለም ብሎ ፍርጥም ሲል ለዚህ ጊዜ ያዘጋጁትን ”የሽብርተኝነት ህግ” አውጥተው ልብ ማሸበር ይጀምራሉ። የአርጀንቲናው አምባገነን መሪ ጄኔራል ጆርጅ ራፋኤል ቪዴላ ”አሸባሪነት ሰዎችን በቦምብ መግደል ብቻ አይደለም። ሀሳቡንም ማመንጨት ነው። ሰዎች በዛ ምክንያት ሊታሰሩ ይችላሉ” ብሏል እ.ኤ.አ በ1977። ስልጣን ከያዘ ጀምሮ መለስ ዜናዊ ተመሳሳዩን እያደረገ ነው።
አደኑ ግን እዚህ አላበቃም። ሌላ ሁለት ዓመት ጠብቆ አዳኙ መጀመሪያ የአውራአምባውን አምደኛ (ሸሙጠኛ) አቤቶኪቻውን አስኮበለለ። ”ከምገባ” ወጥቶ አዲሱን የስደተኛ ጋዜጠኖችን ክለብ ተቀላቀለ። አቤ ቶኪቻው ስድስት ወር ሙሉ ወያኔ በፍቅርዋ ልትማልለው ደጁ ብትጠና ልበ-ደረቅ ሲሆንባት ተቆጣች። የስደት ሰለባ አደረገችው። የአቤቶኪቻው አለመማለል ግን እኔን አማሎኛል።
የአውራ አምባ አምደኛ ከመጀመሪያዎቹ እንጂ ከመጨረሻዎቹ አልነበረም-ለመሰደድ። የአለም አቀፍ ጋዜጠኞች መብት ተከላካይ ኮሚቴ የ2003 ዓ. ም. ተሸላሚ ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደም የግፉ (መገፋቱም፤ የግፍ ሰለባ መሆንም) አካል ነበር። ”አውራምቢትም” በጉልበተኞቹ ተንገጫግጫ ለጊዜው ቆመች። ዳዊት ከበደ እንደ ብረት የጠነከረው ያለመሠደድ አቋሙን ለማቅለጥ፤ አቅልጦም ለማጉበጥ፤ ገዢው ፓርቲ ብዙ እሳት ፈጅቷል። ሁለት ዓመት በቃሊቲ ወላፈን ለብልቦታል። ላሽቆ ይወጣል ሲባል ቅርጹን አስተካክሎ፤ በሞራል ጎልብቶ፤ ይበልጥ ጠንክሮ ወጣ። የቃሊቲው ስቃይ መንግስትን እንዲፈራ አላደረገውም። ይበልጥ ተጋፈጠው። ቢገፉት አልገፋ አላቸው። ቢያስጠነቅቁት አልፈራ አላቸው። በሚፈሩአቸው ሲያስመክሩት አልሰማ አላቸው። መጨረሻ ላይ ግን ዝም ሊያሰኙት ተሰናዱ። ቃሊቲ ወይም ማእከላዊ ሊልኩት። እርግጠኛ ነኝ ”ይላኩኝ” ብሎ እንደፈረጠመ አልጠራጠርም። ግን የነሡ ቃሊቲ መሔድ ጠብታ ለውጥ እንደማያወጣ ቀስ ብሎ ሲረዳ ለጊዜው ገሸሽ አለላቸው።
የፍትህ ጋዜጣ አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ እንዳለው፤ የዳዊት ከበደ አባት እና የመለስ ዜናዊ አባት ከአንድ ጅረት የጠጡ ብቻ ሳይሆን የመለስ አባት ሲዳሩ የዳዊት አባት ሚዜ ነበሩ። የእናት ሆድ ብቻ ሳይሆን የአባት ልጆችም በጸባያቸው ለየቅል ነበሩ። ሁለቱ አብሮ አደጎች ለኢትዮጵያ ሁለት የተለያዩ ትርጉም የሚሰጡ ልጆች ነው ያፈሩት።
መለስ ዜናዊ ለአገሩ ብቻ አይደለም ግድ የሌለው። እስትንፋሱ ድንጋይ ላይ ወድቆ ጸጥ እንዳትል ትራስ ሆኖ ላዳነው አረጋዊ በርሔም ግድ አልነበረውም። ከትግል እስከ ድል ላልተለየው የትግል ጓዱ እና የቅርብ ወዳጁ ስዬ አብርሃም ግድ አልነበረውም። ከካድሬ አሰልጣኝነት በአንዴው ወደ ህወሀት መሪነት እሽኮኮ አድርገው ላደረሱት አቦይ ስብሃት ነጋም ግድ አልነበረውም። ሻንጣ ሙሉ ዶላር እና ፓውንድ ቅልቅል (እንደ ጋዜጠኛ ዮናስ በላይ አባባል) ለውድቡ (ህወሃት) የሠጠው ገብረመስቀል ጨርቁን ጥሎ ሲያብድ ግድ አልነበረውም። በሰማእታት አጥንት ብሎ የአዞ እንባ አንብቶ ከስልጣን ላዳነው የህወሃት ካድሬም ግድ የለውም። መለስ ግድ የሌለውን መዘርዘር ከተጀመረ ማብቂያ አይኖረውም። ለነገሩ ለአገሩ ግድ የሌለው ሰው ለምን ግድ ይኖረዋል ብሎ ይታሰባል? … ለራሱ እና ለአዜብ መስፍን- ከፍ ሲል ደግሞ ለልጆቹ።
የኢትዮጵያ ድምጾች አንድ በአንድ ከምድራቸው ተሰደዋል፤ አልያ ወደ ዝነኛው የወያኔ የማይሞላ ቋት ቃሊቲ ተወርውረዋል። አንዲት ድምጽ ቀርታለች። ፍትህ የምትባል። ለፍትህ የምትደክም። በተመስገን ደሳለኝ ሳምባ የምትተነፍስ። 35 ጊዜ በስለት ተወግታ አልሞት ያለች። ቢጮህባት ያልደነገጠች። ብትወዘወዝ ዘመም ያላለች። እንደ አይበገሬው እስክንድር ነጋ የቃሊቲ ወይም የማእከላዊ ቋት ውስጥ ካልተወረወረች በጉልበት ጸጥ የማትል-ፍትህ ፈልጋ የምትጮኸው ”ፍትህ”።
እስክንድር ነጋን የማውቀው ኢትዮ-ሚዲያ ላይ ነው። እኔን አያውቀኝም። አገር ቤት ሆኖ ገዢ ፓርቲው ሊጠጣው የማይደፍረውን እሬት ሲግተው የነበረ ጀግና ነው። ጀግንነቱን ለየት የሚያደርገው ወያኔዎች አፍንጫ ስር ሆኖ መጀገኑ ነው። ጎሹ ወልዴን አገር ቤት ከገባህ እስር ቤት እንልክሃለን ብሎ ያስጠነቀቀው፤ በዳግማዊ ”ህንፍሽፍሽ” ጊዜ ህንፍሽፍሽ ያለው፤ አንዴ ”የነተወልደ ቡድን” ከተባለው ጋር የቆመው፤ ነገሩ አላምር ሲለው ደግሞ ወደ ”ቤተ-መንግስት” ቡድን ጭራውን አየቆላ ”ማረኝ” ብሎ የተቀላቀለው ሀሰን ሽፋ በትግል ቋንቋ ”አንተን ማሰር ሰልችቶናል” እያለው፤ ጠረጴዛ እየደበደበ እሳት እየተፋ ቢያስፈራራው ፍንክች ያላለው እስክንድር ነጋን በጽሁፉ ነበር የማውቀው። አዎ የማውቀው ለሀገሩ ያለውን ፍቅር ነበር። የማውቀው ስለ ዲሞክራሲ፤ ፍትህ፤ ስለ ህገ-መንግስቱ መከበር ያለውን ፍቅር ነው። ስለ ሀይለስላሴ ወይም የደርግ ህገ-መንግስት ሳይሆን እራሱ ወያኔ አስሬ ስለሚጠራው ህገመንግስት መከበር ነበር። ቃላችሁን አክብሩ፤ እዚህ ያደረሳችሁን፤ እንዲህ አቀማጥሎ የሚያኖራችሁን ህዝብ አክብሩ፤ እባካችሁ አክብራችሁን እናክብራችሁ ባለ፤ እንገልሃለን ከአይናችን ራቅ አሉት። ”እንዴት ተደርጎ እምቢየው ወይ ፍንክች ከተወለድኩባት አገር ወዴት?” አላቸው። ተው ልናስርህ ነው፤ እኛን መታገል ከፈለግክ ራቅ ብለህ ቢሉት በፍጹም አለ። ከዚያም ለሚፈልጓት ጊዜ ብለው ያስቀመጡዋትን ”የሽብርተኝነት” ቀይ ካርድ አውጥተው ወደ ”ዝም ማሰኛቸው” ላኩት። ከዚያ በኃላ ነው የእስክንድርን ሰውኛ ባህሪ ለማወቅ የቻልኩት።
ለተመስገን ደሳለኝ የእስክንድር ባለቤት ሰርካለም እንደነገረችው ጀግናው አዛኝም ነው። ለአገሩ እንደሚያዝን እርግጥ እኛም እናውቃለን። የሱ አዘኔታ ግን ከዚህም የዘለለ ነው። ለሚያሳድዱት ”ደህንነቶች”ም ነው የሚያዝነው። ”ተዪአቸው የሚያሳዱኝ እኮ እንጀራቸው ሆኖ ነው። አትፍረጂባቸው።” እያለ ነው መከራውን ለሚያሳዩት የሚያዝንላቸው።- እስክንድር ነጋ-በመከራ አልቀልጥ ያለ ብረት።
ከማንበብና ከመጻፍ ውጪ ምንም ወንጀል ያልፈጸሙትን ጋዜጠኞች የአክሽን ፊልም ድርሰት በሚመስል የክስ ፈጠራ ወህኒ ቤት መወርወር እና ራቅ ያሉትን (A prisoner on leave) ”ቆይ ልያዛችሁ!” ብሎ ማስፈራራት የኢህአዴግ የወትሮ ባህሪው ሆኗል። እንሀ ሀላፊነት የሚሰማቸው ኢትዮጵያውያን ከማንበብና መጻፍ ውጪስ የራሳቸው እና የህዝቡን ህይወት በጥሩ ለመቀየር ቢታገሉ ምን አጠፉ? ወንጀል ነው? ወንጀል ከሆነ ዛሬ የምኒሊክ ቤተመንግስ እንኳን የጠበባቸው እነ መለስ ዜናዊ በ19 አመታቸው አድርገውት የለ? ከከፍተኛ ተቋም ተመርቀው፤ ስራ ይዘው ቢሮክራሲውን ሳያዩት የዘውግ ስርአቱን የተካውን ወታደራዊ መንግስት ዳዴውን ሳይጨርስ፤ ለውጥ በመጣ በአመቱ ነው ጫካ የገቡት። እኒህ ጋዜጠኞች እኮ ለቤተ-መንግስቱ ሰዎቻችን ቢያንስ ሶስት የውሸት ምርጫ እድል (እያንዳንዱ ድፍን አምስት ዓመት ያለው) ሰጥተውታል።
ወያኔ የምትፈራውን ሰው አገር ጥለው እንዲወጡ የተለያየ ጫና ስታደርግ ቢያንስ ከሁለት ነገር እንደምትጠቀም ታውቃለች። አንደኛ ችግር ይፈጥርብኛል ብላ የምታስበው ድምጽ ራቅ ብሎ እንዲጮህና፤ ብሶት አሰሚውም ሲርቅ የህዝቡ ብሶት እንዳይሰማ ይጠቅመኛል ብላ ስለምታምን ነው። ሁለተኛ ሲሰደዱ የቅርብ ተቃውሞአቸው ሲቀርባት ዶላራቸውን ግን በቤተሰብ እርዳታ ሰበብም ይሁን ጓደኛ ለመደጎም ሲለሚላክ ነው። ዌስተር ዩኒየን ይሁን ሌላዊ ህጋዊ ሀዋላ ባይሆንም ወደድንም ጠላንም ብሩ ኢትዮጵያ ሲደርስ፤ የኑሮ ውድነት፤ ስራ ማጣት ያጎሳቆለው ቤተሰብ እና ጓደኛ ተንፈስ እንዲል ይረዳዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ኑሮ ውድነቱ እጅግ ብሶበታል። አንድ ቤተሰብ አንድ ኪሎ ስጋ የመግዛት እድላዊ አቅም ካገኘ ያለው አማራጭ ጥሬውን መብላት ነው። ጥሬ ስጋ የምርጫ ምግብ ሆኖ ሳይሆን የስጋው ማባያ እና መስሪያ፤ ቅቤ፤ በርበሬ፤ ለማብሰያ ጋዝ መግዣ ስጋው ከተገዛበት አልፎ ስለማይተርፍ ነው። አንድ ኪሎ ስጋ እስከ 115 ብር እየተሸጠ ነው። ኢምፖርት ከሚደረጉ እቃዎች እኩል ስጋ እየተሸጠ ነው። ማን ያውቃል ኢህአዴግ እድሜ ከሰጠው ስጋ እንደ ወርቅ በግራም መሸጥ ይጀመር ይሆናል። ያኔ ነጋዴዎች ”ስጋና ወርቅ ቤት” የሚል ሱቅ መክፈት ሊኖርባቸው ነው። ስጋውም ሊበላ ሳይሆን ሊጌጥበት ይሆናል የሚፈለገው። እንደ ጆርጅ ኦርዌል ”1984” መጽሀፍ ለእለት ተእለት ኑሮ የሚያስፈልጉ ነገሮች ኢትዮጵያ ውስጥ የቅንጦት መሆናቸው የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ሊሆን ይችላል-ወያኔ እድሜዋ ከረዘመ።
ኢትዮጵያ ጊዜዋ ብቻ አይደለም እየባከነባት ያለው። ምርጥ ልጆችዋም እየባከኑባት ነው። በምን ቀን ይሆን እኒህ የተረገሙ ልጆችዋ ኩሩዋ አገሬ ላይ እንዲፈነጩባት የፈቀደችው ብዬ ሳስብ፤ አያት ቅድመ-አያቶቼ ወደተቀበሩበት ገረአልታ ተራራ ግርጌ ስር ትዝታ ወሰደኝ።
እንደ ሶስት ሺህ ዘመን የኩራት ታሪካችን ደረቱን ገልብጦ የቆመው የገረአልታ ተራሮችን ማየት፤ ማየት ብቻ ሳይሆን ሚጢጢ ፍጡር ሆኖ ፊት ለፊቱ መቆም ለልብ ግዝፍናን፤ እብጠትን ይፈጥራል። ተራራው አጠገብ የቆምኩት ብቻዬን አልነበረም። እዛው ቦታ ተወልዶ ያደገ፤ ያገባ እና የወለደ የአጎቴ ልጅም አጠገቤ ነው ያለው። እንደ ቀልድ አንድ ጥያቄ ጣል አደረኩለት። ”ታጋይ ነበርክ?” አልኩት። ”እንዲያውም” አለኝ። ”ለምን?” ስለው የፌዝ ሳቅ ስቆ ዝም አለኝ። የፌዝ ሳቁ ውስጥ ማብራራት የማይፈልገው ነገር እንዳለ ቢሰማኝም የወንድሙን ስም ጠርቼ እገሌ ግን ታጋይ ነበር አዲስ አበባ እንደገቡ እኛ ቤት ሲመጣ አስታውሳለሁ ስለው ”እሡ የድል አጥቢያ አርበኛ ብቻ ሳይሆን ስሜታዊ ነበር” አለኝ። ቁጭት በተላበሰ ቅላጼ። ”እንዴት” አልኩት።
ፊቱን ዞር አድርጎ ባለ ግርማ ሞገሱን የገረአልታ ተራራ በጣቱ እየጠቆመ ”ከዚህ ተራራ መልስ ወያኔ ከአስር ዓመት በላይ በስብሳለች። አልገፋ ያላት መሬት ነበር። ልቡ አልሸፍት ያላት ያለ ህዝብ ምድር ነበር የሆነባት። የዚህን ህዝብ ልብ ለማሸፈት ሁለት ሺህዎችን መጨረስ ነበረባት። አደረገችውም። በፕሮፓጋንዳ አልሸፍት ያላትን ህዝብ ግን በቦንብ ጨረሰቸው። ቦንብ ወርውራ ሳይሆን ቦንብ አስወርውራ። ሀውዜንን አስደብድባ..” አለና አጉረጠረጠ። ቁጭት ንዴት ሞልቶታል።
”ስማ …” አለኝና ጸጥ አለ። ትንፋሹን ለመሰብሰብ። ከዚያ ከንፈሩን ነክሶ፤ በእግሩ ወደአሸዋማነት እየተቀየረ ያለውን አፈር እያተረማመሰ፤ በጣቱ ወደ መሬት እያሳየ ”እቺ ምድር ከ1980 በፊት የወየኑ በጣት የሚቆጠሩ ልጆች ነው የነበሩዋት። የሚበዙቱ የደርግ ”አዞ” ሰራዊት አባል የነበሩት ናቸው። ከሀውዜን ድብደባ በኃላ ምን እንደተፈጠረ ሰምተሃል?” አለኝ ጥያቄ በሞላበት እና በንዴት በሚንቀለቀል አይኑ እያየኝ
”አልሰማሁም”
”ሀውዜን ከተደበደበች በኃላ ደረግ በአንድ ቀን ከ15ሺህ በላይ ”የአዞ” ሰራዊት አባል ነው የኮበለሉበት። ከሀውዜን ድብደባ በኃላ ወያኔ መንገዱ አልጋ በአልጋ ሆነላት። ሶስት ዓመት አልፈጀባትም ቀሪውን ለመቆጣጠር። ገረአልታ ከልጆችዋ ጋር ወጥራ ይዛት ነበር። የዋህዋ ገረአልታ ግን በሴራ ተሸነፈች።” ቀጠለ የአጎቴ ልጅ።
”ወያኔ እኛን አታምነንም። ”ነፍጠኛ” ባትለንም ”ነፍጠኛ” ከምትላቸው እኩል ነው የምትፈራን። ፍርሃትዋን ለማወቅ ሀውዜን ወረዳ አስተዳደር ቢሮ፤ ፖሊስጣቢያ፤ ጤና ቢሮ ሒድ። ሀውዜን በልጆችዋ አይደለም የምትተዳደረው። የሀውዜን አስተዳዳሪዎች የወያኔ ልጆች ናቸው። እኛ ደግሞ ወያኔ አይደለንም። በራሳችን ልጆች እንተዳደር ብለን ብዙ ጊዜ ስሞታ አሰማን። ግን ወያኔ ”የነብርን ጭራ አይዙ፤ ከያዙም አይለቁ” ብላ ነው መሰል …” ብሎ ዝም አለ።
ሀውዜንም የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ነው ብላለች። ልማታዊ ጋዜጠኛም አፍርታለች። የነ ብጻይ ስዩምን ጀብድ ለመጻፍ የነስዬን ስም መናድ የፈለገ ታሪክ አጉዳፊ ጋዜጠኛ አብቅላለች። ለሀቅ የቆመ፤ ቀድሞ ሀቅን እና ወያኔን የተጋፈጠ ጋዜጠኛም አብቅላለች።
ሀውዜን ከቀሪው ኢትዮጵያ የተለየች አይደለችም። ከአድዋም፤ ተንቤንም፤ ከጎንደርም፤ ከአዲስ አበባም፤ ከደብረዘይትም፤ ከአዋሳም፤ ከሀረርም፤ ከመላው ኢትዮጵያ አትለይም። እጣቸው አንድ ነው። የቀመሱት ግፍ አንድ ነው። ትግላቸው አንድ ነው። ኢትዮጵያዊ ያደረጋቸው ታሪካቸው ብሳ ሳይሆን መከራቸውም ነው። በአምባገነን መንገላታት፤ መሰደድ፤ መታሰር፤ መሰቃየት፤ መሞት …።
አምባገነንነት ከምን ሊመነጭ ይችላል? የተለያየ ምክንያት ይኖረዋል። ከምክንያቶች አንዱ ሊሆን የሚችለው የሀገር ፍቅር ማጣት ነው። የሚያስተዳድሯት አገር ሙሉ በሙሉ የራሳቸው ያልሆኑ ሰዎች አምባገነንነት ይታይባቸዋል። ለምሳሌ?
ሒትለር ኦስትሪያዊ ነው። ናፖሊዮን ደግሞ ኮርሲካ። የሰርቢያው ነውጠኞች ሚሎዞቪች እና ራዶቫ ካራድዚክ ከሞንቴኔግሮ ናቸው። ኢሳይያስ እና መለስስ? መልሱን ለእናንተ ትቼዋለው።
እርግጥ በጥሩም የሚነሱ አሉ። የቻይናው ናሽናሊዝም አባት የሚባለው ሱን ያን ሴን ከሆንግ ኮንግ ነው። ቼ ጉቬራ አርጀንቲና ተወልዶ፤ ኩባን ነጻ አውጥቶ፤ ኮንጎ ዘምቶ፤ ቮሊቪያ ነው የተገደለው። የቅርብ ጊዜ ጀግናችን ኦባማ ግማሽ ጎኑ ኬኒያዊ ቢሆንም፤ ከዩኒቨርሲቲ ጀምሮ አሜሪካን ያገለገለ የጥቁር ህዝብ መመኪያ የአሜሪካን ፕሬዚዳንት ነው።
ግፉ በዝቷል። ተንዛዝቷል። ነጋዴዎች ተማረዋል። ምሬታቸውን ሲገልጹ ቫት አጭበርብራችኃል ተብለው ይታሰራሉ። ተማሪዎች በቅጡ ባላለቀ እና ባልተሰራ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ለፕሮፓጋንዳ እና ኮታ ፍጆታ ተብሎ ሁለት ዓመት ቀድሞ በተመረቁ ተማሪዎች ይማራሉ። አምስት ሚሊዮን መለዮ ያልለበሰ ፖሊስ ህዝቡን በአይነ ቁራኛ ይጠብቀዋል። ቁርስ ምሳ እና እራት በኑሮ ውድነት ምክንያት ህብረት ፈጥረው ”ቁምራት” በሚል ምህጻረ ቃል ተደራጅተው ህዝቡን በቀን አንዴ እያገለገሉት ነው። ብዙ ያልተጻፉ፤ ያልተሰሙ ግፎች እየተፈጸሙ ነው-ኢትዮጵያ።
ህዝቡም እየጠበቀ ነው። አንድ የሚያደርጋቸውን ብርሃን እየጠበቀ ነው። ህዝቡ መሮታል። ትግሉን 17 ብቻ ሆነው ሳይሆን 17000 ሆነን መጀመር እንችላለን። 17 ዓመት ሳይሆን 17 ወራትም አይፈጅብንም - ከተደራጀን - በአንድ ድምጽ ሆ ብለን ከተነሳን። ምክንያቱም እኛ 99% ነን።
ፕሬዚዳንት ኦባማ ብዙ ጊዜ እንደሚጠቅሱት የዶ/ር ኪንግ አባባል ”With our days become dreary with low-hovering clouds of despair, and when our nights become darker than a thousand midnights, let us remember that there is a creative force in this universe, working to pull down the gigantic mountains of evil, a power that is able to make a way out of no way and transform dark yesterday into bright tomorrows. Let us realize the arc of the moral universe is long but it bends toward justice.”
የኔሰው ጓንጉል
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



