አቶ በረከት ምን ነካቸው? ለካስ ጉድ ሳይሰማ የፈረንጆች ገናም አይመጣም!
አቤ ቶኪቻው
የፈረንጆች ገና መጣ። እንንኳን መጣ! የእኛም በቅርቡ ይመጣል። እስከዛው ግን እንኳን ለፈረንጆቹ ገና አደረሰን እንባባል። ያው እንደሚታወቀው አነዚህ ፈረንጆች ገናቸውን ባከበሩ በሳምንቱ አዲስ አመታቸውን ደግሞ ያክብራሉ። ታድያ ይሄኔ እነርሱ አመት ባል ባመትባል ሲደራርቡ እና እረፍት በእረፍት ሲብነሸነሹ ፈረንጅ የያዘው ዶሴ ተሸፈፍኖ መተኛቱ ነውና፤ ከፈረንጅ ጉዳይ ያለው ሰው ቻል ማድረግ ይገባዋል ማለት ነው።
አነሳሴ እንኳ ስለ ዶሴ ለማውራት አልነበረም። ነገር ግን አሁን የፈረንጆች አዲስ አመት ሊገባ ሲል በኛ አዲስ አመት ዘወትር የሚነገር አንድ አባባል ትዝ ብሎኝ ነው። ምን መሰልዎ…?
“ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም!” እንግዲህ መስከረም አዲስ አመታችን ነው። ብዙ ተስፋ የምንሰንቅበት፣ ብዙ የምናቅድበት፣ ብዙ የምንፎክርበት… አዲስ አመት። ታድያ ይህም ሆኖ መስከረም ከመጥባቱ በፊት የሚደመጡ “ጉዶች” አይጠፉም። ከዚህ ጋር ተያይዞ ነው ተረቱም መተረቱ! እናልዎ ሰሞኑን የሰማዋቸው አንዳንድ ነገሮች ለካስ የእኛ ብቻ ሳይሆን የፈረንጆችም አዲስ አመት ጉድ ሳይሰማ አይጠባምና! ብዬ እንዳስብ አደረጉኝ። ትዝ ሲለኝ ደግሞ ነገሩን የሰማሁት ከአዲሱ አመትም ከገናውም በፊት ነበርና ርዕሴን “ጉድ ሳይሰማ የፈረንጆች ገናም አይመጣም!” አልኩት። ጉዱ ምንድነው? ካሉኝ ልብ ለማንጠልጠል ያደረግሁት ሙከራ ተሳክቶልኛል ማለት ነው። ምን መሰለዎ…? አይቸኩሉዋ… እንደውም አዲስ መስመር ላይ እንገናኝ…
የአቶ በረከት ስሞን መፅሀፍ መታተሙን ሰሙልኝ? ጉሽ! ከሰሙ ይበቃል ለማንበብ እንዳይጓጉ። እንኳንስ እርስዎ እና መፅሀፉን ያሳተሙላቸው ሼክ መሀመድ አላሙዲ እንኳ “አላነበብኩትም ነገር ግን ለወደፊቱ ትውልድ ዲሞክራሲ መማሪያ የሚሆን ነው!” ብለው ነው የተናገሩት ታድያ ጉደኛቸው ሼክ መሀመድ ካለነበቡት እርስዎ በምን እዳዎ… ያነባሉ? ዝም ብለው አስተያየት መስጠት እና መስማት እየቻሉ።
ማሳሰቢያ፦ ከላይ ባለው አንቀፅ ሼኩን ጓደኛቸው ብዬ መፃፍ ሳያቅተኝ “ጉደኛቸው” ሼክ መሀመድ ያልኩት ሆነ ብዬ መሆኑን ለማሳወቅ እወዳለሁ።
እናልዎ ወዳጄ… አንድ የተባረከ ወዳጄ ከመፅሐፉ የተወሰነ ቅምሻ ይሆንሃል ብሎ “ስካን” አደርጎ በኢሜል ልኮልኝ ነበር። ታድያ አንብቦ ሳይጨርሱ አስተያየት መስጠት በእኔ አልተጀመረምና፤ ለግዜው ጉድ ያሰኘኝን ነጥብ አነሳለሁ።
ቆይ ቆይ አቶ በረከት ስሞን መፅሐፋቸው ለምን ውጪ ሀገር ታተመ? ምንአልባት የኢትዮጵያ መንግስት እንደ እስክንድር ነጋ መፅሐፍ አታሚዎቻቸውን “ይህንን መፃፍ ታትሙ እና የእንጀራ ገመዳችሁ ይበጠሳል!” ብሎ አስፈራርቶባቸው ይሆን እንዴ? ይሄን ግዜ እርስዎ “ፈቃጅ ከልካዩ እርሳቸው አይደሉ እንዴ!?” ብለው በአግራሞት ይጠይቁኝ ይሆናል፤ እኔ ያነበብኳትን ገፅ ቢያነቡ ግን ሌላም ነገር ይጠራጠራሉ።
የምር ወዳጄ፤ አቶ በረከትን ጠረጠርኳቸው! ብሎት ያምኑኛል? እንዴት ይበሉኛ…! እንዴት ማለት ጥሩ ጥያቄ ነው። ሰውየው ስለ አዲስ ነገር ጋዜጣ በመፅሐፋቸው ገፅ 250 ላይ እንዲህ ይላሉ፤ “አዘጋጆቹ በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው ሀገራችን ሀሳብን በነፃነት ለመግለፅ የሚያስችል መብት አለ!” ካሉ በኋላ ገበያቸው በአንዴ ቀዘቀዘ!” አሉ። ይህንን ሳነብ በእውነቱ አቶ በረከት ምን ነካቸው? ብዬ እጅግ ተደንቄያለሁ። ይህንን ንግግር “የኢትዮጵያ ከረንት አፌርስ” ወይም “ኢትዮ ሚዲያ” ወይ ደግሞ “ኢትዮጵያን ሪቪው” አልያም ሌላ ገለልተኛ አስተያየት ሰጪ ወይም ተንታኝ ቢናገረው አይገርመኝም ነበር። ከአቶ በረከት ግን የምጠብቀው “ልጆቹ በኢቲቪ ቀርበው ዲሞክራሲ አለ ብለው ከተናገሩ በኋላ ገበያቸው ጨመረ።” የሚል ንግግር ነበረ። ለካስ ሰው በኢቲቪ ሲቀርብ ህዝቡ “አይንህ ላፈር!” እንደሚለው አቶ በረከት ያውቃሉና? ጉድ አይሉልኝም?
እውነትም በተለይ አሁን አሁን የአገሬ ህዝብ አንድ ሰውን በኢቲቪ ሲመለከተው ጠንቋይ ቤት ያየው ያህል ነው የሚጠየፈው ብልዎ ያምኑኛል? አያምኑኝም። ምክንያቱም እርሱ ያጋንናል ብለው ስለሚጠረጥሩኝ አያምኑኝም። እውነቱ ግን ሰዉ ከኢቲቪ ደስ ብሎት “እሰይ መጣልኝ” ብሎ የሚመለከተው “ሰው ለሰው” እና “ገመና” ድራማን ብቻ ነው። አኪልዳማንስ? ብለው ቢጠይቁኝ በሳቅ መሞቴ ነው!!!
በርግጥ አቶ በረከት ይህንን እንደሚያውቁ እኔም አውቃለሁ። ነገር ግን ደፍረው፤ ሊያውም ታሪክ ሆኖ በሚቀመጥ መፅሐፍ ላይ እንዲህ ይናገራሉ ብዬ አስቤም አላውቅም ነበር። እንዴ እኛን ሁሉ ስለ ኢቲቪ ቅድስና እንድንናገር አድረገውን ሲያበቁ ዛሬ “ኢቲቪ ላይ ቀረቦ ዴሞክራሲ አለ፤ ያለን ሰው፣ ህዝቡ ይጠየፈዋል” ብለው ማለታቸው የንስሀ ዘመናቸው ደርሶ ይሆን? ያሰኛል ኮ! አሁን አሁን ሳስበው በተለያየ ጊዜ የመንግስትን መግለጫዎች፣ ማብራሪያዎች፣ እና ማረሪያዎች ይዘው ምክትላቸው አቶ “ሼም የለሽን” የሚልኳቸው ለካስ “ህዝቡ እስከ አሁን የደበርኩት ይበቃኛል። አሁን ደግሞ እስቲ አንተ ሂድ” እያሉ ነውና…! ጉድ ሳይሰማ የፈረንጆች ገናም አይመጣም ማለት ይሄኔ አይደለም?
ለአቶ በረከት አንድ ጥያቄ አለኝ። አዲስ ነገሮች አንድ ቀን “ኢቲቪ ላይ ሲቀርቡ ህዝብ አይናችሁ ላፈር ብሏቸዋል” ብለው በድፍረት ተናግረዋል። እንዲህ ከሆነ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና አጠቃላይ ፓርቲው ላለፉት ሃያ አመታት የቴሌቪዥኑ “ስክሪን ሴቨር” ሆነው ያያቸው ህዝብ ምን የሚላቸው ይስልዎታል? “ሳንፈልጋቸው ሃያ አመታቸው” እያለ ይዘፍናል ካሉ በትክክል መልሰዋል።
እውነቱን ለመናገር ግን አቶ በረከት ኢቲቪን ለማዋረድ ፈልገው ካልሆነ በስተቀረ፤ የአዲስ ነገር ደንበኞች ብቻ ሳይሆኑ “ደመኞችም” ጭምር አንድ የተስማሙበት ሀቅ አለ። የአዲስ ነገር ጋዜጣ ተወዳጅነት እና ጥልቀት ያለው ትንታኔ አሰጣጥ መንግስትን “ክው” አድርጎታል። ጠላትዎ ክብ ይበል! (እዚች ጋ ይቅርታ አድርጉልኝና አንድ ግዜ ቅንፍ ውስጥ ይዣችሁ ልግባ (እኔ የምለው መንግስት በሀገሪቱ ውስጥ አንድ ነገር “አሪፍ” ሲሆን ለምንድነው አይኑ ደም የሚለብሰው? የፕሪስ ተቋማት፣ የሙያ ማህበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ትንሽ ብቅ ብቅ ሲሉ እና በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ሲጀምሩ “ሰይጣን የሆነ” ኩርኩም እየኮረኮመ በአጭር ያስቀራቸዋል። ምክንያቱ ምን ይሆን…? እኒያ የቦረና ሰውዬ ለካስ ወደው አይደለም “አሁን አሁን ሳስበው እኛን የሚገዛን ጣልያን ነው እንዴ? እላለሁ!!!” ብለው የተናገሩት። ሰው ለሀገሩ ጥሩ ነገር ሲመጣለት በራሱ ህዝብ ላይ ምቀኛ ይሆናል? ብሎ ማሰብ ከባድ ነው!))
የሆነ ሆኖ አዲስ ነገር ጋዜጣም ህዝቡን ፍቅር እንዳስያዘው መንግስታችን ሲረዳ ተሸበረ። ያኔም አዘጋጆቹን በአሸባሪነት ሊከስ ማማሟቅ ሲጀምር ግዜ “ነቄዎቹ” አዲስ ነገሮች ላጥ አሉበት። እነሆ በሌሉበትም ተከሰሱ “አሸባሪ” ተባሉ። ዛሬም ጭምር የአዲስ ነገር አዘጋጆች መንግስትን እያሸበሩት ይገኛሉ። ህዝቡም እንዲህ ነው እንጂ እያላቸው ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ተሻምቶ ያነባቸዋል።
እናልዎ ወዳጄ አቶ በረከት ኢቲቪን ሊሞልጩት ፈልገው ካልሆነ በስተቀረ “አዲስ ነገሮች በኢቲቪ ስለቀረቡ ህዝቡ ጠላቸው” የሚል ገለፃ ከእርሳቸው አይጠበቅም። በስርአቱ ተፀፅተው ሊያሸሙሩ ፈልገው ነው ብለን እንዳናስብ “ኢሂአዴግ ገና አርባ አመት ይገዛል” ብለዋል። እኔ የምለው እንዲህ ርስ በርሱ የሚጣረስ ነገር የሚያወሩት ሰውየው ያ የራስ ህመማቸው አልተሻላቸውም እንዴ? ሼኩ መፅሐፉን ቢያነቡት ኖሮ አንጠልጥለው ወደ ህክምናቸው ያደርሱልን ነበር።
ይልቅ ወዳጄ የሼኩ ነገር አልገረምዎትም “በረከት ህክምናውን አቋርጦ ሲመጣ አንጠልጥዬ እወስደው ነበር።” ብለው ተናግረዋል። በነገራችን ላይ አቶ በረከት ስሞን የሚያማቸው ራሳቸውን ነው። “ጨለፍ” የሚያደርገው ይሁን አይሁን እንጃ እንጂ ችግሩ ግን ጭንቅላታቸው ላይ እንደሆነ ሰምቻለሁ። የዚሁ አይነት ህመም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንም አለባቸው አሉ። (አረ በኔ እና በርሶ ብቻ ይቅር እንጂ እርሳቸውማ አንዳንዴ በሰላም ሀገር “ጠብ” ያደርጋቸዋል ሲባል ሰምቻለሁ።) ይሄ ነገር የቤት ጣጣ ነው እንዴ? ብሎ መሳለቅ ነውር ነው። ሌሎችም የኢህአዴግ አባላት በተለይ የላይኞቹ የሚያደርጉትን ልብ ብለን አይተናል የሚሉ አንዳንድ ወገኖች፤ “እንዲህ አይነቱ ህመም ሁሉም ሳይኖርባቸው አይቀርም” እያሉ እያወጉ ነው። ታድያ ይሄኔ እኒያ ሼክ ሁሉንም እያንጠለጠሉ ወደ ሀኪም ቤት አልያም ወደ “ዱአ” ቤት ቢወስዱልን ጥሩ ነበር ሲሉ ሰምቻለሁ።
ለማንኛውም ወዳጄ የአቶ በረከትን መፅሐፍ አንብቤ አልጨረስኩትም በቅርቡ ከተባረኩት ወዳጆቼ መካከል አንዱ ሙሉ መፃፉን ልኮልኛል እናም አንብቤ የሚወራ ካለው እናወራበት ይሆናል። ሌሎች ጨዋታዎቻችንን በመጨረሻም ላይ እናውጋቸው
በመጨረሻም
ፍትህ
ተወዳጇ እና አንድ ለናቱ የሆነችው ፍትህ ጋዜጣ ሰሞኑን መከራዋ በዝቶ ሰንብቷል። አዘጋጆቹ ሲገቡም ሲወጡ፣ ሲበሉ ሲጠጡ፣ ሲቆሙ ሲቀመጡ ያደረጉትን ሁሉ አብረዋቸው የሚያደርጉ ደህንነቶች ተመድበውላቸዋል። ጋዜጣዋም ባልታወቀ ምክንያት ቅዳሜ ትወጣ የነበረውን ዘላ እሁድ በሰንበቱ ወጥታለች።
እኔ የምለው ግን መንግስት እንዲህ ለእያንዳንዳችን ደህንነት መድቦ ይችለዋል? ብዬ ስጨነቅ የሰማኝ አንድ ወዳጄ ምን አለኝ መሰልዎ? “መንግስት በአምስት አመቱ ስትራቴጂ ውስጥ ከነደፋቸው ነገሮች አንዱ የሚቃወሙት ለመሰለውን በሙሉ በቂ የሆነ ደህንነት እና ድህነት መስጠት ነው አለኝ!” ጉድ እኮ ነው!
በመጨረሻም
ጎንደር
በጎንደር ዩኒቨርስቲ ባለፈው ግዜ ተማሪዎች በተበላሸ ምግብ እና ውሃ ሳቢያ ታመው በትምህርታቸው ምትክ ሆስፒታል ተኝተው አሳልፈዋል። “እንዲህ አይነት ነገር ነውር ነው!” ያሉ ተማሪዎችም በትምህርት ቤቱ ላይ ቁጣቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል። ታድያ ሰሞኑን ከጎንደር ዩኒቨርስቲ አካባቢ አንድ ዜና ተሰምቷል።
“ምግብ እና ውሃ ብክለት ማጋጠሙ አዎ ትክክል ነው! ያሉት የትምህርት ቤቱ ተወካይ ነገር ግን “የተበላሸም ቢሆን፤ ተበላሸ ብሎ መቆጣት አግባብ ባለመሆኑ ቁጣ ሲያሰሙ ከነበሩት መካከል “ቀንደኞቹ” ለአንድ አመት ከትምህርት ገበታቸው እንዲገለሉ ተደርጓል” የሚል መግለጫ ሰጥተዋል። ይሄኔ አንድ ነገር አስታወሱኝ
ነገሩን ዳኛ ብርቱካን ሚዴቅሳ ስታወራው ነበር የሰማሁት። “የመንግስታችን ትልቁ ችግር መበደሉ ብቻ አይደለም ተበደልኩ ብለህ ስትጮህ መከልከሉ ነው!” ስትል ሰምቻት አውቃለሁ። እውነቷን ነው። የዚህ አይነት ጨዋታ ከዚህ በፊትም ተጫውተናል። እየደበደቡ አታልቅስ ብሎ መቆጣት የጤና ነው? ጉድ እኮ ነው!
በመጨረሻም
ርዕዮት አለሙ
መምህርት እና ጋዜጠኛ የነበረችው ርዮት አለሙ “አሸባሪ” ተብላ ከታሰረች ቆየች። ሰሞኑን ታድያ ፍርድ ቤት ቀርባ ነበር። ፍርድ ቤት ስትቀርብ ጠበቆቿ ካሰቡት የመከላከያ ምስክሮች ውስጥ “ኤክስፐርት” የሚባሉ ምስክሮችን ማቅረብ ነበር። አንዲት እሳት የላሰች የህግ ባለሞያ ወዳጄ እንደነገረችኝ ከሆነ፤ (መሆኑም አይቀርም) ኤክስፐርት የሚባሉት ምስክሮች ሙያዊ ምስክርነት የመስጠት ብቃት ያላቸው ናቸው። በሌላው ሀገር እንዲህ አይነቱ ምስክርነት የተለመደ ነው ባይ ናት። ምስክሮቹ ረዳት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እና ዶክተር ያዕቆብ ሃይለማርያም ነበሩ። ፐሮፌሰሩ ከፖለቲካ አንፃር የርዮት ክስ የማያስኬድ መሆኑን የሚያስረዱ ሲሆኑ፣ ዶክተሩ ደግሞ ከህግ አንፃር ክሱ ውድቅ መሆኑን ለአቃቤ ህግ ሊያስረዱ ነበር… ምን ዋጋ አለው! ፍርድ ቤቱ “አረ ባካችሁ… ልታሳምኑኝ ነው? ወይስ ልታሳምሙኝ?” ብሎ እንቢ አለ (አሁን አሉ በሉልኝ)
ይህንን የሰማ አንድ ወዳጄ ታድያ ምን አለኝ መሰልዎ፤ “ኢህአዴግ እኮ ሀገሪቷን ከቆጣጠረ ቀን ጀምሮ (ከተቆጣጠረ ማለቱ ነው!) ኤክስፐርቶች ሲደውሉለት ስልኩ ጥሪ አይቀበልም” አለኝ። ለምን ይሆን ስለው… “ስልኩ የቻይና ነው!” አለኟ! የተቀበራቸሁ የኢህአዴግ አመራሮች ሆይ ይህ ነገር እውነት ነውን? ጉድ እኮ ነው!
ይበሉ ወዳጄ ለዛሬ ይበቃናል! ያወጋነውን ለፍሬ ይበለው! እስከ ሳምንት…
አማን ያሰንብተን!
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



