ኢብሮ ከጀርመን This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

ንጉሥ ኃይለሥላሤ፣ ረሃብና ድርቅ፣ ድህነት አሁን አሁን ደግሞ ሩጫችን እዚህ በጀርመን አገር ጥሩ መታወቂያችን ናቸው። በቃ ኢትዮጵያ ለነሱ እንደዚህ ናት። የኛ መለያ! እኔ ግን እላለሁ የዲሞክራሲ ቸነፈርን አትርሱብኝ!

 

 

የዲሞክራሲ ድርቅ አብሮን የተፈጠረ እስኪመስል ድረስ ሊለቀን አልቻለም። ከተጠቀለልንበት ሼል ውስጥ ሰብሮ በመውጣት ከዲሞክራሲ የሚገኘውን የውሀ ጥም ለማርካት ያለን ፍላጎት ሁሌም ከፍተኛ ነው። ለዚህም ምክንያቱ ለሰው ልጅ ነጻነት፣ፍትሕና ብልጽግና መሠረት መሆኑን ስለምንገነዘብ ይመስለኛል።

 

በዲሞክራሲ ቸነፈር መመታታችን ሳያንሰን አገር አልባ ለመሆን በተቃረብንበት ወቅትና ማንነታችን ጥያቄ ውስጥ በገባበት ጊዜ ዲሞክራሲን መናፈቃችን ብቻ ትፈጥሮአዊ አያደርገውም።ተፈጥሮኣዊ የሚያደርገው በተፈጥሮ ያገኘነውን ነጻነት በተግባር ስናስጠብቅ ነው።

 

የዲሞክራሲ ሥርአት የተራበውን ሕዝብ ተስፋው እውን እንዲሆን በሚደረገው የትግል ሂደት ቅጥተኛ ተሳታፊ የሚሆነውና ትግሉን የሚመራው በልሒቃን በመሆኑ፣ የዲሞክራሲ ባህሎችን ለሕዝቡ በማስተማርና እራሳቸውም በመተግበር ከፍተኛ ሚና ይጠበቅባቸዋል።በመሆኑም

 

የዲሞክራሲን ሥርአት በአገራችን ለመትከል የወያኔን ሥርዓት መጣል ብቻ እንደ ግብ መታየት የለበትም።

 

ያለፈው የፖለቲካ ታሪካችን የሚያሳየን በተለያዩ ወቅት የነበሩት መንግስታት በሚያራምዱት ሥርዓት ምክንያት የዲሞክራሲ ባህል እንዳይኖር ጥሩ አድርገው ሠርተዋል። በዲሞክራሲ ስም እየተማለ መሬት ላይ ግን ምንም በሌለበት ሁኔታ እነሆ ካለን የረዥም ጊዜ ታሪክ አኳያ ልናገኘው የሚገባንን ዕድገት ሳናገኘው ያለችንንም ጠብታ ደግሞ ፍጹም እያጣን እንድንሄድ ተደርገናል። በመሆኑም የወያኔን ሥርዓት በመታገልና በማስወገድ ጎን ለጎን ከወዲሁ የዲሞክራሲ መሠረቶችን በውስጣችን በመጣል በአገራችን ዕውን አንዲሆን ለምንፈልገው ዲሞክራሲ በስነልቦናም ይሁን በተግባር ዝግጁ መሆን ይጠበቅብናል።

 

ትግሉን የበለጠ ፈታኝ የሚያደርገው ደግሞ አሁን ያለው የወያኔ ሥርዓት ካለፉት ሥርዓቶች በተለየና በከፋ ሁኔታ በሚያራምደው የጎሳ ፖለቲካውና ለዚህም ዋስትና የሆነው የጠበቀ ድርጅታዊ አሠራሩን እስከታች በማውረድ በሕዝቡ ውስጥ ትልቅ ፍራቻ በማንገስ በስልጣን ላይ ለመቆየት የሚያደርገው መሯሯጥ ለዲሞክራሲ የቆሙትን ኃይሎች የሚከፍሉትን መስዋትነት ከፍ እንዲል ያደርገዋል።

 

የዚች ታሪካዊ አገርን ችግሮች ጠንቅቆ በማወቅ የሕዝቡን ሰቆቃ እንዲያበቃ ጠንክሮ መሥራትን፣ ባለራዕይ መሆንን፣ ከምንታገለው ወያኔ እጅ ላይ ኳሷን እንዴት መንጠቅ እንዳለብን በስትራቴጂ መንቀሳቀስንና የመሳሰሉትን አላማዎች ወደ ተግባር የምንለውጣቸው ለዲሞክራሲ በቆሙ ኃይሎች ውስጥ ያለው ለዲሞክራሲ ሥርዓት መሰናክል የሚሆኑትን ኢዲሞክራሲያዊና የዲሞክራሲ ሥነምግባር የማይንጸባረቅባቸውን ድርጅታዊ አሠራሮች ሲወገዱ ነው።

 

ዲሞክራሲያዊ ሥነምግባሮች የፖለቲካና የሥነምግባር መርህ ብቻ ሳይሆኑ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጥርጊያ መንገድ የሚያመቻቹ እንደመሆናቸው በነዚህ ሥነምግባሮች ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ድርጅት አመራር የሕዝቡን ጥያቄ አንግቦ እስከመጨረሻው የሚጓዝ ለመሆኑ ምንም ጥያቄ የለውም።

 

እስከአሁንም እንደሚታየው ግን ለዲሞክራሲ ቆመናል በሚሉ ኃይሎች ውስጥ እራስን ኃይለኛ፣ የማይደፈር፣የፈለገውን ለማድረግ የማንንም ሀሳብ የማይሻ አድርጎ ማቅረብ፤ የተሰጣቸውን ሀላፊነት ከመወጣት ይልቅ ሀብት ለማግኘት በፖለቲካ ሥም መነገድ፤ የቤተሰብ ማህበር እስኪመስል ድረስ የፓርቲን አመራር በጥቂት ሰዎች ቁጥጥር ሥር በማድረግ የሚታዘዛቸውንና የሚመሳሰላቸውን እየጎተቱ ማስገባት፤ ዝርክርክ አሰራሮችና ሙስና አንኳር ችግሮቻችን ሲሆኑ የነዚህ ውጤት ግን አንድ ድርጅት ዕራይ ባለው ጠንካራ የሰው ኃይል ጎልብቶ እንዳይወጣ፣ ተተኪ የሚሆኑ ወጣቶችን አለማዘጋጀትና ማግለል፣ የርስ በርስ ሽኩቻ በመጠመድ ጊዜን በከንቱ እንዲጠፋ ማድረግ፣ተክለ ሰውነትን በመትከል ላይ ማተኮር እንደምሳሌ ሊጠቀሱ የሚችሉ ቢሆኑም ባጠቃላይ ግን የፖለቲካ ኃይሎች ለፖለቲካ ሥነምግባራዊ ባሕል አለመገዛት እንመራሀለን የሚባለውንና የዲሞክራሲ ርሀብተኛ የሆነውን ሕዝብ ለለውጥ ያለውን የተነሳሽነት ሥሜትና ተስፋ ከመጉዳቱም በተጨማሪ ትውልድን ለባርነት አሳልፎ መስጠት ነው።በጥቅሉ በማንኛውም ሚዛን ብንመዝነው ከየትኛውም አቅጣጫ ብንመለከተው በተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች ውስጥ የሚፈጠረው ችግር በዋነኝነት ለፖለቲካ ሥነምግባራዊ ባህል ካለመገዛት የሚመነጩ ናቸው። ለዚህ ዓይነት ሥነምግባር የማይገዛና ተግባራዊ ያልሆነ ሰው የዲሞክራሲን ሥርዓት ለማምጣት ይችላል የሚል ዕምነት የለኝም።

 

በፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ የዲሞክራሲ ሥነምግባር ባህል እንደ አንድ ተቋም ሊታይ ይገባል። ሰዎች ወደ ተቋም ገብተው ተምረው እንደሚወጡ ሁሉ ተቋሙም መሰረቱ ጸንቶ ሌላውን ተረኛ እያነጸ ያወጣል። በንደዚህ አይነት ባህል የታነጸ ማንኛውም የፖለቲካ ሰው የፖለቲካ ባህል ዕሴቶችን ያከብራል፤ ህሊናዊና አካላዊ ግዴታዎች ስለሚጠይቁት ሀላፊነቱን በሚገባ ሊወጣ ይችላል።

 

የዲሞክራሲን ሥርዓት በተግባር በሚክተሉ አገሮች ምንያህል ለዲሞክራሲ ባህል ተገዥ እንደሆኑ ሊያሳየን የሚችልና ሁሌም የምደነቅበት የቀድሞውን የጀርመን ፕሬዝዳንት ሆርስት ኮለር እንደ ምሣሌ ማንሳት ተገቢ ይሆናል። በ 2010 እራሱን ከፕሬዝደንትነት ያገለለው ሆርስት ከስልጣኑ ለመልቀቅ ያበቃው ምክንያት በአፍጋኒስታን የሚገኙ የጀርመን ወታደሮችን በመውቀሱ ነበር። ይህ ሥልጣንን ለመልቀቅ እንደምክንያት ለመቀበል ቢቸግርም እሱ ግን የሰጠው ምላሽ "የእኔ በስልጣን ወንበር መቆየት ያዳበርነውን የፖለቲካ ዲሞክራሲያዊ ባህልን ይጎዳል፤ ሕዝቡም በፖለቲካ መሪዎች ዕምነት አይኖረውም" የሚል የበሰለና አስተማሪ የሆነ አባባል ነበር።

 

ወደ አገራችን ጉዳይ ስንመለስ ግን ዶ/ር ብርሐኑ "የነጻነት ጎህ ሲቀድ" በሚለው መጻሕፉ እንዳስቀመጠው "ለዲሞክራሲ የቆሙ ኃይሎች ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን በመገንባት ሂደት ውስጥ ለአንባገነኖች የሚመች ስነልቦና ከማሕበረሰቡ ውስጥ አውልቆ መጣል ለዲሞክራሲ ሥርዓት ምስረታ ማረጋገጫ መሆኑን" ኣስቀምጧል። የሁን እንጂ የፖለቲካ ኃይሎች አስተሳሰብና ስነልቦና ከወዲሁ መቀየር ትግሉን ወደ አንድ አቅጣጫ ከመውሰዱም ባሻገር ለዲሞክራሲ የሚደረገውን ጉዞ አስተማማኝ ያደርገዋል።

 

የሰሜን አፍሪካውና የአረቡ ዓለም የለውጥ ምሳሌ አገር ውስት ላለው የመረረ የሕዝብ ብሶት ተጨማሪ ግበአት በመሆን በኢትዮጵያችን ለውጥ አይቀሬ መሆኑ ግልጽ እየሆነ መቷል። ወያኔን ከመታል ባሻገር ላለው ሥራ ከወዲሁ እንዘጋጅ!

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!


ኢብሮ ከጀርመን

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ