ኢትዮጵያ እንደ ሩዋንዳ? የዳዎድ ቡድን ባወጣው መግለጫ ላይ
ግርማ ካሳ
መግቢያ
በጄኔራል ከማል ገልቹ የሚመራው ኦነግ «ኦሮሞ የኢትዮጵያ ግንድ ነው። ቅርንጫፍ ከግንድ ይገነጠላል እንጂ ግንድ ከቅርጫፍ አይገነጠልም» በሚል፣ የኢትዮጵያን አንድነት ተቀብሎ፣ ለኦሮሞ ባህልና ቋንቋ መስፋፋት፣ ለዜጎች ሁሉ መብት መከበር፣ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ወንድሙ ጎን በመቆም ትግሉን እንደሚቀጥል ይፋ አድርጓል። ይህ ከኦነግ ዘንድ ይፋ የተደረገው የፖለቲካ አቋም ለውጥ፣ ኦሮሞ ነን የሚሉትን ጨመሮ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ውይይትን ጭሯል።
አንጋፋው የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲን ጨምሮ፣ የበርካታ ድርጅቶች ስብሰብ የሆነው፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ መስራችና የኦሮሞ ፌደራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ የቀድሞ ሊቀመንበር፣ የተከበሩ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ፣ ኦነግ ኢትዮጵያዊነትን ተቀብሎ ይህንን ጠቃሚና ወቅታዊ እርምጃ መውሰዱን አድንቀዋል። «ጄኔራል ከማል ገልቹ ብቻ ሳይሆኑ ሁላቸውም በዚህ ሃሳብ ዙሪያ ቢሰባሰቡ ጥሩ ይመስለኛል» ያሉት አቶ ቡልቻ «ኦነግ እገነጠላለሁ ሲል ነበር። ይሄን እኔ ከድሮ ጀምሮ የምቃወመው ነገር ነው። አሁን ጄኔራል ከማል የተናገሩትን እኔ በደስታ ነው የማዳምጠው። ኦሮሞው፣ አገር ውስጥ ኖሮ፣ በኢኮኖሚ በፖለቲካ በማህበራዊ ኑሮ ሁሉ ተሳተፎ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ አለሁ ብሎ፣ የሚኖር ሕዝብ ነው። የሚሸሽ ወይንም የሚገነጠል ህዝብ አይደለም» ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ሌላ አንጋፋ ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ አባት፣ የተከበሩ አቶ ሮቤል አባቢያ በበኩላቸው፣ የኦነግ አመራሮች የወሰዱት ድፍረት የተሞላበትን አቋም፣ «የተቀደሰ» ሲሉት፣ በታሪክ ትልቅ የጀግንነት ገድል ካላቸው፣ የኦሮሞው ሕዝብ አብላጫ (ማጆሪቲ) ከሆኑት፣ አገር ወዳድና ኩሩ ኢትዮጵያዊ ኦሮሞ ወገኖቹ ጋር፣ ኦነግ መቀላቀሉ እንዳስደሰታቸውም ገልጸዋል።
የኦነግ ኢትዮጵያዊነትን መቀበል የሚቃወመው የዳዎድ ኢብሳ ቡድን
ምንም እንኳን በኦነግ አቋም የተደሰተው ሕዝብ እጅግ በጣም ቢበዛም፣ በተቃራኒው ይህ ታሪካዊ ክስተት ያላስደሰታቸው ጥቂቶች እንዳሉም እየታዘብን ነው። በዳዎድ ኢብሳ የሚመራው የኦነግ አክራሪ ቡድን፣ በሚቆጣጠረው ድህረ ገጽና አንዳንድ የፓላቶክ ክፍሎች፣ በጄኔራል ገልቹ በሚመራው ኦነግ፣ እንዲሁም ከነጄኔራል ገልቹ ጋር በቅርበት በሚሰራው ግንቦት 7 በተሰኘው ድርጅት ላይ፣ የከፈተውን ከፍተኛ የሆነ የፕሮፖጋንዳ ጥቃት እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።
«ግንቦት ሰባት የተሰኘው ድርጅት የኦሮሞን ሕዝብ የነጻነት ትግል ጎራ በማናጋት ላይ አተኩሯል። ድርጅቱ ከኦሮሞ ሕዝብ የትግል ጎራ በጣት የሚቆጠሩ ወንጀለኞችን በጉያው ሸጉጦ እንደ መሳሪያ በመጠቀም፣ የኦነግን ታላቅነት ሊያረክስና የትግሉን አላማም ለመቀልበስ ሲል ደጋፊዎቹን ደቦ ጠርቶ ወደ ዘመቻ ገብቷል» ሲል የዳዎድ ቡድን ይከሳል።
«የኦሮሞ ሕዝብ የሚኖርበትን ሰፊ መሬት የሚያሳየው፣ የኦሮሞያ ካርታም ኢትዮጵያን የሚንድ አደጋ ተብሎ በዚህ ኃይል ዘንድ በጽኑ እየተወገዘ ይገኛል። የኦሮሞ ሕዝብ የራሱን እድል በራሱ ወስኖ፣ ካሻው የራሱን መንግስት መመስረት፣ አልያም ከጎሮቤቱ ሕዝቦች ጋር የፖለቲካ አንድነት የመፍጠር መብቱ፣ ግንቦት 7 ዘንድ እንደ ወንጀል ታይቶ፣ ሰፊ የፕሮፖጋንዳ ጥቃት ተከፍቶበታል። ባጭሩ ለማስቀመጥ ይህ ድርጅት በኦነግ ላይ የተያያዘውን የጥቃት ዘመቻ አድማስ በማስፋት ሰፊውን የኦሮሞ ሕዝብ ወደ ማጥቃት ተሸጋግሯል» ሲልም የግንቦት 7 ንቅናቄ አውግዟል።
ኢሳት እንደ ሚል ኮሊንስ ራዲዮ?
የዳዎድ ኢብሳ ቡድን ጥቃቱን በግንቦት ሰባት ብቻ ላይ በማድረግ አልተቆጠበም። የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን የሆነውን ኢሳትን እንደ ጥላቻ አራማጅ፣ በኦሮሞ ላይ እንዳነጣጠረ ሜዲያ አድርጎም አቅርቦታል። «ኢሳት የተሰኘው ቴሌቭዝኝ እየነዛ ባለው ፀረ-ኦሮሞ ፕሮፓጋንዳ፣ ከራዲዮ ሚል ኮሊንስ ጋር የሚቀራረብ ሚና እየተጫወተ መሆኑን መገንዘብ አስፈላጊ ነው። ኢሳት አሁን በኦሮሞ ሕዝብ፣ በመሪ ድርጅቱ ኦነግና በኦሮሞነት ላይ አነጣጥሮ በተለያዩ ስልቶች እየነዛ ባለው አደገኛ ፕሮፓጋንዳ፣ ነገ ኢትዮጵያ ውስጥ የሩዋንዳ አይነት ቀውስ እንዲቀሰቀስ መሰረት እየጣላ መሆኑን አስቀድመን መጠቆም እንወዳለን» ሲል ኢሳትን ለሩዋንዳ እልቂት ዋና ተጠያቂ ከሆነው ከሚል ኮሊንስ ራዲዮ ጋር አመሳስሎታል።
በምርጫ ዘጠና ሰባት ወቅት የመለስ ዜናዊ አገዛዝ፣ ኢንተርሃሙዌ በሚል በሩዋንዳ ያሉ ሁቱዎች ቱትሲዎችን እንደጨፈጨፉት፣ የተቀረው ኢትዮጵያዊም ትግሬዎችን ሊጨርስ እንደተነሳ አድርጎ በማቅረብ፣ አሳዛኝና ኃላ ቀር የዘር ካርድ በመጫወት፣ በትግሬዎችና በተቀረው ኢትዮጵያዊ መካከል መፈራራት እንዲኖር ለማድረግ መሞከሩ የሚታወስ ነው። ከቅንጅት እንደመጣ በማስመሰል፣ ሕወሃቶች እራሳቸው «ትግሬን ግደሉ» የሚል የጥላቻ መግለጫ እየጻፉ ሲበትኑም እንደነበረ ብዙዎች ይናገራሉ።
እውነቱ ግን ሌላ ነበር።፡ሕወሃቶች የአጋዚን ጦር ልከው፣ የተቀረውን ኢትዮጵያዊ በጥይት አረገፉት እንጂ፣ እነርሱ የጭካኔ የግድያ ድርጊት ፈጸሙ እንጂ፣ አንድም ሰላማዊ ዜጋ፣ ጦር አንስቶ ትግሬ ወንድሙን የገደለበት ሁኔታ አልተከሰተም። አንድም ሰው በትግሬ ጎሮቤቱ ላይ አልተነሳም። ሕዝቡ ትግሬ ላይ ቢነሳ ኖሮ 10 ሺህ የማይሞሉ የአጋዚ ወታደሮች ነበሩ እንዴ፣ ሰማኒያ ሚሊዮን ሕዝብን መክተው ትግሬውን ሊያድኑ ይችሉ የነበረው? ሕውሃቶች የትግሬውን ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ ብቻ፣ ትግሬውን በውሸት ፕሮፖጋንዳ ቢያስፈራሩትም፣ የተቀረው ኢትዮጵያዊ፣ ለትግሬው ወገኑ ፍቅርና አክብሮት እንጂ ጥላቻ ኖሮት አያውቅም። አይኖረውምም። የትግራይ ሕዝብ አሉላ አባ ነጋን፣ አጼ ዮሐንስን የመሳሰሉ ጀግናዎችን ያፈራ፣ ለኢትዮጱያ አንድነትና ሉዓላዊነት አጥንቱን የከሰሰ ኩሩ ሕዝብ እንደሆነ የተቀረው ኢትዮጵያዊ ያውቃል።
እንግዲህ ያኔ ሕወሃት ሲያደርግ እንደነበረው፣ በተመሳሳይ ሁኔታ፣ ከሕውሃት ደብተር በመኮረጅ፣ የዳዎድ ኢብሳ ቡድን ስለ ሩዋንዳ እልቂት እንደገና እየነገረን ነው። «ኦሮሞው ኢትዮጵያዊ ነው ። ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ወንድሙ ጋር በፍቅር በመከባበር ለአንዲት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ አብሮ ይሰራል» ማለት፣ እንዴት ተደረጎ በሩዋንዳ የታየውን አይነት የዘር እልቂት ሊፈጥር እንደሚችል ሊገባኝ አልቻለም። እንዴት ተደርጎ «ተፋቅረን፣ ተከባበረን እንኑር» ማለት በወገንና በወገን መካከል ጥላቻን እንደመንዛት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል?
በጄኔራል ገልቹ የሚመራው ኦነግ፣ ከነዳዎድ ኢብሳ ቡድን ጋር ያለው ትልቁ ልዩነት
ጃዋር ሲራጅ መሃመድ፣ በነጄኔራል ገልቹ በሚመራውና በዳዎድ ኢብሳ ቡድኖች መካከል ብዙ ልዩነት እንደሌለ የሚገልጽ አንድ ጽሁፍ በቅርቡ አስነብቦናል። ወንድም ጃዋር እንዴት ወደዚህ ድምዳሜ እንደመጣ ባይገባኝም፣ ከመግለጫዎቻቸው እንደተረዳሁት ግን፣ በሁለቱ መካከል ትልቅና ቁልፍ የሆነ ልዩነት እንዳለ ነው የሚታየኝ።
የዳዎድ ኢብሳ ቡድን «ኦሮሞው ከኢትዮጵያ ጋር ለመሆን ይወስን። ከፈለገም ኦሮምያን ይዞ መገንጠል መቻል አለበት» ባይ ነው። የዳዎድ ቡድን ስለ አቢሲኒያ ኢምፓየር፣ ስለ ቅኝ ግዛት ያወራል። እነ ጀነራል ገልቹ ደግሞ ከመጀመሪያ ኦነግ ሲቋቋም የነበረው አላማ የመብት ጥያቄ እንጂ የመገንጠል ጥያቄ እንዳልነበረ በመግልጽ «ኦሮሞው ኢትዮጵያዊ ነው፣ ኦሮሞነት ኢትዮጵያዊነት ነው» የሚል ጠንካራ አቋም ወስደዋል። ድብን አድርጎ ትልቅ ልዩነት ነው እንጂ ያለው በሁለቱ መካከል!!!
የኦሮሞነት መመዘኛ ምንድን ነው?
የነዳዎድ ኢብሳን ፖለቲካ እስቲ ዘርዘር አድርገን ሊያስከተል የሚችለውን ነገር እንመርምር። በመጀመሪያ «ኦሮሞው ሕዝበ ውሳኔ ይስጥ» ከተባላ፣ ሕዝበ ውሳኔ ለመስጠት አንድ አይነት ሂደት(ፕሮሰስ) መኖር አለበት። ለምሳሌ መራጮች መመዝገብ አለባቸው፤ የምርጫ ካርድ ሊሰጣቸው ይገባል። እንግዲህ አንዱና መሰረታዊ ጥያቄ « ማን ነው ኦሮሞ ተብሎ የምርጫ ካርድ የሚሰጠው?» የሚለው ነው። ይህ ጥያቄ ቀላል ይመስላል እንጂ እጅግ በጣም የተወሳሰበ ጥያቄ ነው።
ኢሕአዴግ አዲስ አበባ እንደገበ በቀበሌ ደረጃ የክልል ምርጫ ተደረጎ ነበር። ለመምረጥ ወደ ቀበሌ ሄድኩኝ። የዘር ሃረጌን ጠየቁኝ። «ኢትዮጵያዊ» ብላችሁ ጻፉ አልኩ። «አይደለም እርሱማ ዜግነትህ ነው። የጠየቅንህ ብሄርህን ነው» አሉኝ። «ኦሮሞና አማራ» አልኩ። «አንዱን ምረጥ» አሉ። «በጭራሽ፣ ሁለቱን እፈልጋለሁ» አልኳቸው። ጭቅጭቅ ተፈጠረ። ካርድ ሊሰጡኝ ፈቃደኛ አልሆኑም። ሳልመርጥ ቀረሁ። በአገሬ፣ በተወለድኩባት መንደር፣ በመሃይምነት ይጥፋ ዘመቻ ባስተማርኩበት ቀበሌ፣ ጭካ ባቦካሁበት፣ በባዶ እግሬ እግር ኳስ በተጫወትኩበት ሰፈር፣ እንደ ባእድ ዜጋ ተቆጠርኩ። እንግዲህ የዘር ሃረግ ሂሳብ ከተሰላ እንደ እኔ አይነቱ ሰው ምኑ ጋር ነው የሚመደበው?
ኦሮሞው ከአማራው፣ ጉራጌው፣ ከሶማሌው ተደባልቋል። በምን መመዘኛ ኦሮሞውን ከሌላው መለየት እንደሚቻል ግልጽ የሆነ ነገር የለም። የመጀመሪያው ቋንቋ አፋን ኦሮሞ የሆነ ነው ኦሮሞ የሚባለው? ወይንስ አራሱን ኦሮሞ ነኝ ብሎ አንድ ሰው ስለቆጠረ ነው የኦሮሞነትን ሚዛን የሚያልፈው? እንግዲህ አስቡት፣ የዳውድ ቡድን እንደሚፈልገው፣ «ኦሮሚያ ትገንጠል፣ አትገንጠል» የሚል ሬፌረንደም ለማድረግ ቢሞከር እንኳን፣ ምን ያህል ገና ከጅምሩ ሊያስከትል የሚችለውን ጭቅጭቅና ውዝግብ!!!
ኦሮሚያ ከኢትዮጵያ ብትገነጠል እነ ፊንፌኔ/ድረዳዋ/ጂም ከኦሮሚያ ቢገነጠሉስ?
ኦሮምያ እንደምናውቀው ታላላቅ የኢትዮጵያ ከተሞችን የያዘች ክልል ናት። (በነገራችን ላይ ኦሮሚያ የሚባል ክልል በታሪክ ኖሮ አያውቅም። ሕውሃት እና ኦነግ የፈጠሩት ግዛት ነው) ፊንፊኔ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ዋና ከተማ ናት። በኦሮምያ እምብርት ውስጥ ትገኛለች። 99 በመቶ የፊንፊኔ ሕዝብ፣ ከተለያዩ ብሄሮች የተወጣጣ በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምን ሕዝብ ነው። ድረደዋ አማሮች (በዚያ አካባቢ ክርስቲያኖች ናቸው አማሮች የሚባሉት)፣ ሶማሌዎች ኦሮሞዎች ተደባልቀው የሚኖሩባት፣ በኦሮሚያ ውስጥ የምትገኝ ሌላ ሕብረ ብሄር ትልቅ ከተማ ናት። የኦሮሚያ ዋና ከተማ አዳማ/ናዝሬት፣ ጂማ የመሳሰሉ ከተሞች ከ80 በመቶ በላይ አማርኛ ተናጋሪ፣ ዜጎች የሚኖሩባቸው ሕብረ ብሄር ከተሞች ናቸው። በአሁኑ ጊዜ አዲስ አበባ፣ በሰሜን በኩል እሰከ ለገጣፎ፣ በደቡብ እስከ ናዝሬት ተለጥጣለች። ከጥቂት አመታት በኋላ አዲስ አበባ ከናዝሬትና ከደብረ ብርሃን ጋራ መግጠሟ አይቀሬ ነው።
እንግዲህ ኦሮሚያ የምትገነጠል ከሆነ፣ ከደብረ ብርሃን እስከ አዳማ የሚኖረው ሕዝብ ምን ሊደረግ ነው? የጂማ የድሬደዋ እንዲሁም ያልጠቀስኳቸው በርካታ የኦሮሚያ ታላላቅ ከተሞች እንዴት ሊሆኑ ነው? «እኛም ደግሞ በበኩላችን ከኦሮሚያ ተገንጥለን፣ ለብቻችን እንሆናለን» የሚል ጥያቄ ቢያነሱስ? ኦሮሞው ከኢትዮጵያ የመለየት መብት እንደተሰጠው እነርሱም ከኦሮሚያ የመለየት መብት የላቸውም ወይ? አዲስ አበባ፣ ናዝሬትን፣ ደብረ ዘይትን፣ ጂማን ድረዳዋን፣ መቱን ... ወዘተረፈ ጨምሮ በኦሮሚያ ያሉ ከተሞች ለብቻ ሆነው እንዴትስ ነው ኦሮሚያ ልትኖር የምትችለው? ገጠሩ ያለ ከተማው እንዴት ሊሆን ይችላል? ወይንስ በቀድሞ ዩጎዝላቪያ፣ ክሮዬሻዎች ከክራዪና ሰርቦችን፣ ሰርቦች ከባኛ ሉካ ቦስኒያዎቹን በግፍ እንዳባረሩት፣ «ኦሮሞ አይደላችሁም፣ ኦሮሞ ናችሁ» በሚል የዘር ጦርነትና በዘር ላይ የተመሰረተ የሕዝብ ፍልሰት ሊከሰት ነው?
እንግዲህ ስለ ሩዋንዳ እልቂት ከተነሳ፣ በግልጽ ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት፣ በአገራችን የዘር ግጭት እንዲፈጠር ሊያደርግ የሚችለው፣ የዳዎድ ቡድን የሚያራምደው፣ ኦሮሚያ የሚላትን የኢትዮጵያ ግዛት ለመገንጠል የሚደረገው የጥላቻ ፖለቲካ ነው እንጂ፣ ኦሮሞው፣ አማራው፣ ጉራጌው ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት ተካባብሮ፣ ተቻችሎ ለመኖር መወሰኑ አይደለም።
ሁሉም የኢትዮጵያ ምድር ለኦሮሞው መሬቱ ነው!
ከጥቂት አመታት በፊት በመቀሌ አረና ትግራይ በጠራው ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ፣ የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ገብሩ አስራት፣ ሕወሃት በባደመ ጥያቄ ዙሪያ ነደፎ ያስቀመጠውን አምስት የ"ሰላም" ሃሳቦች በመቃወም በአዲስ አበበ መስቀል አደባባይ በተዘጋጀው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ንግግር ማድረጋቸውን በማስታወስ፣ አንድ የሕወሃት ካደሬ «ጠላት ከሆኑት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተገኝተህ ለምን ንግግር አሰማህ?» በሚል ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር። አቶ ገብሩ ሲመለሱ «ኢትዮጵያውያንን እስከሆንን ድርስ ትግራይ መሬታችን ነው። ኦሮሚያ መሬታችን ነው። ደቡብ እና ሶማሊያ መሬታችን ነው። አፋርም መሬታችን ነው። ለነርሱም ትግራይ መሬታቸው ነው። አማራም ትግራይ መሬቱ ነው። ሊኖርበት ይችላል። በዚህ ማመን አለብን። ከዚህ ውጭ የፖለቲካ ተቃዋሚ ድርጅቶችን እንደጠላት ለማስፈራሪያ መጠቀም የሥልጣን እድሜን ማራዘሚያ እሆኑ መታወቅ አለበት። አሁንም በሰላምዊ ትግል ካመኑትና ሕጋዊ ፈቃድ ካገኙት ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር አብረን መሥራት እንቀጥላለን።" በማለት ድርጅታቸው ከሌሎች የተቃውሚ ድርጅቶች ጋር አብሮ እንደሚሰራና በኢትዮጵያ የመከፋፈል ፖለቲካ ቦታ እንደማይኖረው ነበር ያስረዱት።
በርግጥ አቶ ገብሩ እንዳሉት ለኦሮሞው ሁሉም የኢትዮጵያ ግዛት መሬቱ ነው። ባህሉና ቋንቋውን በኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን በሁሉ ክልሎች ሊከበሩለት፣ ደሴ እንደ ደንቢዶሎ፣ አዋሳ እንደ ደደር፣ መቀሌ እንደ ያቤሎ ሊሆኑለት ይገባል። በኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎች ክልሎችም መስራት፣ መነገድ፣ መኖር መቻል አለበት። ሌላውም ኢትዮጵያዊ እንደዚሁ።
ቋንቋ መግባቢያ ነው – የግጭት መንስዔ ሊሆን አይገባውም!
አፋን ኦሮሞ ቋንቋችን ነው። አማርኛም ቋንቋችን ነው። ትግሪኛም ቋንቋችን ነው። ብንችል፣ ሁለት ሶስት ቋንቋ ብንናገር ጥቅም አለው እንጂ ጉዳት የለውም። እናቴ አፋን ኦሮሞ፣ አማርኛ፣ ሶማሌኛ ትችላለች። ጣሊያንኛም ትሞክራለች። በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያስተማሩኝ፣ ነፍሳቸውን መድሃኔዓለም ይማርና፣ የምወዳቸው የአማርኛ አስተማሪ ነበሩኝ። ጉራጌ ነበሩ። ጉራጌኛ፣ አማርኛ፣ ኦሮሞኛን ትግሪኛ ይችሉ ነበር። ታዲያ ይሄ መታደል አይደለም? ቋንቋ የመግባቢያ መሳሪያ እንጂ የልዩነትና የመከፋፈል ምክንያት ሊሆን አይገባም። ብዙ ቋንቋ ማወቁ ጥቅም አለው እንጂ ጉዳት የለውም።
አፋን ኦሮሞ ከአማርኛ ጋር ብሄራዊ የፌደራል ቋንቋ እንዲሆን በአንዳንድ ኦሮሞ አክቲቪስቶች እየተጠየቀ ነው። «አፋን ኦሮሞ የፌደራል ቋንቋ ከሆነ፣ ኦሮሞው በክልልም በፌደራልም ደረጃ ከሌላው ሕዝብ ይነጣል። ቢያንስ አማርኛ ፌደራል ቋንቋ መሆኑ ነው፣ አንድ የሚያደርገንና የሚያስተሳስረን» በሚል ተቃውሞ የሚያነሱ አሉ። «አፋን ኦሮሞ የፌደራል ቋንቋ እንዲሆን ከተደረገ፣ አማርኛም ከአፋን ኦሮሞ እኩል የኦሮሚያ የሥራ ቋንቋ መሆን አለበት» የሚሉም ጥቂት አይደሉም። ግእዝ ብቸኛ አፍሪካዊ ፊደል ከመሆኑም ባሻገር፣በግእዝ መጻፉ፣ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንደመግደል የሚቆጥሩም አሉ። በአንድ ጊዜ የግእዝ ፊደልን በማወቅ፣ አፋን ኦሮሞንም አማርኛንም ማንበብ ስለሚቻል። በተቃራኒው ደግሞ ከግእዙ ፊደል ይልቅ «በላቲኑ ነው አፋን ኦሮሞ መግልጽ የሚቻለው» የሚሉም የአፋን ኦሮሞ ተናጋሪዎች አሉ። ነገሮችን ከተለያዩ ማእዘናት ከማየታችን የተነሳ የሃሳብ ልዩነቶች ሊኖሩ ይችላሉ።
ነገር ግን፣ ከተከባበርን፣ በመሃከላችን ቅንነት ካለ፣ አንዳችን የሌላችንን ስሜት መረዳት ከቻልን፣ ለሁሉም የሚጠቅም፣ በጥናት ላይ የተመሰረተ፣ መተማመን የሞላበት ውሳኔ ማሳለፍ እንችላለን። ለምሳሌ አፋን ኦሮሞ የፌዴራል ቋንቋ እንዲሆን ቢወሰን፣ በኦሮሚያም አማርኛ ከአፋን ኦሮሞ ጋር የሥራ ቋንቋ ቢደረግ፣ በፌዴራል ወይንም በክልል ደረጃ ላቲን ወይን የሳባ ፊደል መጠቀም አለብን» የሚል፣ ከላይ ወደ ታች የሆነ ውሳኔ ከሚተላለፍ፣ ሁለቱም ፊደሎች ለሕዝቡ እንደ አማራጭ ቀርበውለት፣ በወረዳና በዞን ደረጃ ሕዝቡ የሚመቸውን እንዲወስን ማድረግ ቢቻል ለሁሉም የሚቀል ሊሆን ይችላል። አማርኛ ተናጋሪው ከልቡ አፋን ኦሮሞን ለመማርና ለማወቅ ቅናት ካደረበት፣ ኦሮሞውም እንደ አፋን ኦሮሞ አማርኛን ቢማረው፣ አብረን የበለጠ እናድጋለን። በጭራሽ ቋንቋ የመለያየታችን ምክንያት ሊሆን አይገባም።
ማጠቃለያ
እነ ዳዎድ ኢብሳ «ኦሮሚያ የኦሮሞ ብቻ ነው። ኦሮሞው ከፈለገ ይገነጣል» ሲሉን ለኦሮሞ የቆሙ ሊያስመስላቸው ይችል ይሆናል። ነገር ግን አይደለም። የኦሮሞን መብት እያስከበሩ ሳይሆን ኦሮሞውን እየጎዱት ነው። ኦሮሞው በአካባቢ ካሉት ወንድሞቹ ጋር እንዲቃቃር፣ እንዲለያይ ነው እያደረጉት ያሉት።
ሕወሃት በስልጣን ለመቆየት ሲል በትግሬውና በተቀረው ኢትዮጵያዊ ዘንድ የጥላቻ ግንብ ለመገንባት እንደሞከረው፣ የዳዎድ ቡድንም ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በኦነግ ውስጥ ሃሳባቸው ውድቅ ሲሆንባቸው፣ በኦነግ ውስጥ ያላቸውን ቦታ ለመቆናጠጥ ሲሉ በኦሮሞውና በተቀረው ኢትዮጵያዊ መካከል ችግር ለመፍጠር ደፋ ቀና እያሉ ነው። ይህ ቡድን እያሰራጨ ያለው፣ የዘር ጥላቻ ርካሽ ፕሮፓጋንዳ፣ የወጣት ኦሮሞዎችን እንጭጭ አይምሮ እያበላሸ ያለ ወይንም ሊያበላሽ ስለሚችል፣ በሙሉ ኃይል፣ ከሁሉም አቅጣጫዎች ሊመከተና ሊሸነፍ የሚገባው ፀረ-ሕዝብ፣ ፀረ-ኢትዮጵያና ጸረ-ኦሮሞ ፖለቲካ ነው።
እግዚአብሄር ፍቅርና አንድነቱን ይስጠን!
ግርማ ካሳ



