ግርማ ደገፋ ገዳ

ኢሜይል አስጠላፊ፣ ገዢውን ማኳኳያ ራዲዮ አየር ባለቤት፣ የማወናበጃ መጽሔት አዘጋጅ፣ የተዘረፈ ዶላር አስተላላፊ፣ የፕሮፓጋንዳ ለቅላቂ፣ የሚሰረቅ እቃ ኤክስፖርተር፣ በልማት ስም የዘረፋ አማካሪ፣ የራቁት ዳንስ ቤት ባለቤት፣ የጸጥታ ሰራተኛና ወሬ አመላላሽ ሆነው ኢሕአዴግን ከሚያገለግሉት መሃል፤ አብዛኛዎቹ ሚሊዮነር ናቸው። እነዚህ ሰዎች፣ በሕዝብ ስም ተለምኖ ከሚመጣው ገንዘብ ላይ ድርሻቸውን ለማፈስ ብለው፤ ኮቴያቸው ባሪያ እንዲሆን ፈቅደዋል። በዛሬው ጽሁፌ፣ የዘረፋ ጥቅማቸውን እያስጠበቁ መንግሥትን ስለሚያኳኩሉ፣ ስለዘራፊው መንግሥትና የፍትህ ሥርዓቱ ውስጥ ተወሽቀው ስለሚያሾፉ ዳኞች በጥቂቱ የምለው ይኖረኛል።

ሁሉም የዝርፊያ ገንዘብ ወደው፣ በየተመደቡበት ሙያ ኢሕአዴግን ማሽሞንሞን ነው ስራቸው። ወደው የሸጡትን የራሳቸውን ነጻነት፣ ሌላውም እንዲቸበችበው ይሰብካሉ። ሽንጣቸውን ይዘው የሚታገሉት፣ የሥርዓቱ የሌቦች ክንፍ መዘውር ከመሆናቸው አንጻር፣ የገንዘብ ቁልላቸው እንዳይደረመስ ነው። በሃገሪቱ እየተስፋፋ ያለውን በሃብት ያለመመጣጠን ለማዳበር፣ በደሃና በሃብታም መካከል ያለውን ክፍተት ለማስፋትና መካከለኛ ገቢ ያለው መደብ የሚባል እንዳይኖር፤ ከንጋት እስከ ምሽት ስለ ኢሕአዴግ ቁንጮ ሰዎች አርቆ አሳቢነት መለፍለፍ፣ ለነሱ ትርፍ የማግበስበሻ ‘ሃይ! ሃይ!’ ለሌላው ‘ዋይ ዋይ!’ ነው።

እነዚህ ሰዎች፣ ጥቅማቸው ከቀረባቸው፣ ‘እናልበዋለን’ የሚሉትን ኢሕአዴግን አንድ ቀን እንኳ በነጻ ሊያገለግሉ የማይችሉ፤ በገንዘብ እንደሸቀጥ የተገዙና ገንዘብ እስከጎረፈላቸው ድረስ ብቻ ከኢሕአዴግ ካድሬዎች በላይ ራሳቸውን ካድሬ ያደረጉ ናቸው። ኢሕአዴግ፣ ‘ደምተዋል፣ ቆስለዋል፣ ተጠምተዋል፣ ተርበዋል፣ መከራ አይተዋል፤ ያለነሱ እልህ አስጨራሽ ትግል ዛሬ መንግሥት ሆኜ አራት ኪሎ ውስጥ ተቀርቅሬ አልቀርም ነበር’ ከሚላቸው ታጋዮቹ በላይ፤ አንቀባሮ የያዛቸው እነዚህን ግንባራቸው ላይ የመሸጫ ዋጋቸውን ሞቅ አድርገው የለጠፉትን የሰው ሸቀጦችን ነው። ምክንያቱም፣ ኢሕአዴግ እነዚህ ሸቀጦች ከግዝገዛው ቅርንጫፍ ውስጥ ተለቅመው ከወጡበት፤ ምን ማድረግ እንዳለበት የማያውቅ፣ ራቁቱን አደባባይ ላይ ቆሞ የሚቀርና ዜጋው ሁሉ የሚያላግጥበት ድርጅት እንደሆነ፣ ራሱን ከወያኔ ማህጸን ሲፈጥር ጀምሮ አሳምሮ ያውቃል።

ራሳቸውን ነጻ ለማውጣት ባልፈቀዱና እጅ እያወጡ የተሻለ ባሪያ ለመሆን በሚሽቀዳደሙ ባሮች ድጋፍ ጭምር ነው የመንግሥት የእለት ተእለት ተግባር በመላ ሃገሪቱ የሚካሄደው። ወፍ ዘራሽ አዳዲስ ሚሊዮነር ከመሆናቸውም ባሻገር፣ ታንክ ስላልታጠቁና ‘ብርጌድ’ የሚባል ወታደራዊ ክፍል በይፋ ስላልተሰጣቸው ‘ሲቪል’ ይባላሉ እንጂ፤ የገንዘባቸውን ምንጭ ለመከላከል የማያደርጉት ምንም ነገር የለም። የአብዛኛውን ዜጋ ሆድ በአንዲት ጉርሻ አቅበው፣ እነሱ መንግሥትን እስካልነኩ ድረስ፤ የፈለጋቸውን ሁሉ ማድረግ እንዲችሉ ልዩ መብት የተቸራቸው ልዩ ዜጎች ሆነዋል። በእንደዚህ ዓይነት ባሮች በተሞላ መንግሥት ውስጥ ነው ዜጎች ያለጥፋታቸው ጥፋት እየተፈበረከባቸው የሚታፈኑት።

እነዚህ ኮቴያቸውን ባሪያ ያደረጉ ፍጡሮች፣ ከባህርማዶ ለጉብኝት ሲመጡም ‘ኢትዮጵያ በጣም አድጋለች ....ሞባይል ስልክ የሌለው የለም!’ ይሉናል። የአሜሪካን እርዳታ፣ የሕንድና የቻይና ብድር ከሃገሪቱ ዓመታዊ ባጀትም ይሁን ሰብአዊ ጉዳዮች ላይ ተጎትቶ ከወጣ፤ መንግሥት እንደ መንግሥት ቆሞ ሊሄድ የሚችልበት ምንም ሁኔታ እንደሌለ አይናገሩም። ዜጋው ሳይሆን መንግሥት ራሱ የድርቅ ምስል ሊሆን እንደሚችል፤ ታይምስ መጽሔትም እንደፈረደበት ‘ያመቱ ረሃብተኛ መንግሥት’ ብሎ የፊት ገጹ ላይ በትልቁ እንደሚለጥፈው ሊነግሩን አይፈልጉም።

እነሱ ተናገሩም አልተናገሩም፣ ኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት የኢትዮጵያን ሕዝብ እዳ በእዳ አድርጓል። ሕዝቡ፣ መቼም ሊከፍለው በማይችለው ከሁለት መቶ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ብድር ተውጧል። በአንድ ወቅት አንድ የኢሕአዴግ ባለስልጣን የሃገሪቱን ብድር በተለከተ አስተያየት ሲሰጡ፣ ‘ምነው አንድ የአሜሪካ ስፖርተኛ ብዙ ሚሊዮን ብድር አለበት አይደለም እንዴ!’ የመሰለ ነገር ሲሉ ተደምጠዋል። በሁለት ምክንያቶችም ይህ ሁሉ ገንዘብ ለሃገር ጥቅም የዋለ ነው ማለትም አይቻልም። አንደኛው፣ በአገዛዙ የዘረፋ መዋቅር አማካይነት በየዓመቱ ወደ ውጭ የወጡ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮች እንዳሉ የተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች ከበቂ ማስረጃ ጋር በተለያዩ ወቅቶች ሲገልጹ ነበር። ሁለተኛው ምክንያት፣ ቁንጮ ቁንጮ ባለሥልጣናቱ በባለቤትነት የያዙትና ኢፈርት የሚባለው ድርጅት፤ በቢሊዮን የሚቆጠር ሃብቱን በገልተኛ የኦዲት መስሪያ ቤት ያስመረመረበትና ለሕዝብ ያሳወቀበት ጊዜ የለም። በመሆኑም፣ ኢፈርትን የሚመሩ ሰዎች የመንግሥትንም ከፍተኛ ሥልጣን የጨመደዱ ናቸውና፤ የመንግሥትን ብድር አስመልክቶ የሚያወጡትን ሪፖርት፣ ራሳቸውን ነጻ ለማውጣት ያልፈቀዱና እጅ እያወጡ የተሻለ ባሪያ ለመሆን የሚሽቀዳደሙ ባሮች ያምኗቸው እንደሆን እንጂ፤ ሕዝቡ በእንደዚያ ዓይነት ግልጽነት በጎደለው ሪፖርት አይታለልም።

ኢሕአዴግ ይህን ሁሉ የትውልድ እዳ በሕዝቡ ላይ የሚዘፈዝፈው፣ የድርጅቱ መሪዎች እና በትምህርትና ሥልጠና ላይ የሚገኙት ግልገል አምባገነኖቹ፤ በኢኮኖሚ ሊመጣጠናቸው የሚችል ኃይል በሃገሪቱ ላይ እንዳይኖር ካላቸው የቅርብና የሩቅ እቅድ በመነሳት ነው። በነሱ እምነት፣ ያንን ማድረግ ከቻሉ ብቻ ነው ከወደፊት ተጠያቂነት ሊያመልጡ የሚችሉት። የሚቆልሉት ሃብት ምሽግ ሆኖ ሊያገለግላቸው እንደሚችል ምንም ጥርጥር የላቸውም። ድርጊቱን የሚፈጽሙትም፣ የጠመንጃ ኃይል የበላይነት ስላላቸውና የተሻለ ባሪያ ለመሆን የሚሽቀዳደሙ ባሮች ከጎናቸው ቆመውና ሽንጣቸውን ይዘው ስለሚከራከሩላቸው ብቻ እንጂ፤ እንደምክንያት ሊጠቀስ የሚችል ሌላ ምንም ምስጢር ወይም ምሁራዊ ትንታኔ የለም።

ጠመንጃ ስላላቸው ዴሞክራት፣ ጠመንጃ ስለተደገፉ የልማት ሰዎችና ጠመንጃ አቅፈው ስለሚተኙ ዜጋው ሁሉ አባሪያቸው የሆነ ይመስላችዋል። ጠመንጃውና ኮቴያቸው ባሪያ እንዲሆን የፈቀዱ ስግብግቦች ዞር ሲሉ፤ ተያይዘው ‘ዘጭ!’ እንደሚሉ ጠመንጃቸውን ለቀናትም ቢሆን ገለል አድርገው ታይተዋል። የመሸነፍ ዓይነት አለው፤ እነሱ በሚያስጠላ ሁኔታ ነበር ተያይዘው የተደፉት። አፍሪካ ውስጥ፤ መሸነፍ ምን፣ ምን እንደሚል ማማሲያውን ነክሶ እንደእነሱ ያጣጣመ ያለ አይመስለኝም። የሚይዙትና የሚጨብጡት፣ የሚደበቁበትና የሚሸሸጉበት እስኪያጡ ድረስ ናላቸው ዞሮ ነበር። በሞትና በሕይወት መካከል ሆነው፤ ከዚህም ጋር ከዚያም ጋር ‘እንደራደራለን’ እያሉ ሲቀላብዱ የነበሩት እነሱ ናቸው። የነበረውን ማፍረስ እንጂ የማነጽ ሕልም ያልነበራቸው ግለሰቦች፣ ግድብ የመገደብ ሃሳብ የፈለቀላችሁ ያኔ ነው። አናታቸው በሽንፈት አርጩሜ ሲጠበጠብ፤ አስፋልቱ፣ ድልድዩ፣ ፎቁ፣ ዶዘሩና ግሬደሩ ወለል ብሎ ታያቸው። እነሱ “ኢትዮጵያን ከእንቅልፏ አነቃናት!” ይላሉ እንጂ፤ ራሳቸው ናቸው በመሸነፍ ኩርኩም ብዛት ከእንቅልፋቸው ደንብረው የባነኑት። ያ ወርቃማ የሽንፈት ጊዜ ባይኖር ኖሮ፣ ቁንጮዎቹ የኢሕአዴግ መሪዎችና ቱባ ቱባ ባለሥልጣናቱ፤ እንደለመዱት ተኝተው ስለ ቦናፓርቲዝም ሥርዓት አስፈላጊነት ወረቅት ሲያባዙ፣ በላያቸው ላይ ትላልቅ የወንዝ ዳር ዋርካዎች አድገው ባየን ነበር።

ከቱኒሲያው የቀድሞ መሪ ቤን አሊ፣ ቤቱ ከሚገኘው መደርደሪያ ላይ ብቻ፣ ከሃያ ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው እንደ አጃክስ ሳሙና ተከምሮ የተገኘው። በየባንኩ ያለውን፣ አዲሱ የቱኒሲያ መንግሥት ሌላ ‘ዶላር ቆጣሪ’ ካልቀጠረ በስተቀር፤ ቆጥሮ የሚጨርሰው አይመስለኝም። ዜጎቹ መንገድ ዳር ፍራፍሬ እንኳ መሸጥ ተከልክለው፤ ደፈር ካሉት ነጋዴዎች ላይ የፍራፍሬ መደርደሪያቸው እየተወረሰና እየተገነጣጠለ፤ እሱ ያንን ሁሉ አዳዲስ ዶላር መደርደሪያው ላይ ከምሮ ይኮምክ ነበር። እንደ ኢትዮጵያው የፓርላማ ጌታ፤ ስለ ዴሞክራሲ፣ ሰብአዊ መብቶች፣ የኢኮኖሚ እድገት፣ ስለሰላም አስፈላጊነትና ስለሙስና መጥፎነት፤ በፓርላማው ተገንቶ ለቱኒሲያ ሕዝብ አስተምሯል። ያላስተማረው የትምህርት ዓይነት የለም። እናንተም እንደ ቤን አሊ ስለሁለት ዲጅት እድገትና ፍትህ መስፈን በፓርላማ ውስጥ ድራማ እየሰራችሁ ሕዝቡን ከምታሰለቹ፤ መጀመሪያ መደርደሪያችሁ ላይ ስንት ሚሊዮን ዶላር እንደ አጃክስ ሳሙና ቆልላችኋል? ለምን ለሕዝቡ ያንን አትነግሩትም? ከሁለት መቶ ቢሊዮን ብሩ ላይ ስንት፣ ስንት ቀንጭባችሁ መደርደሪያችሁ ላይ በአደራ አኑራችኋል?

ኢትዮጵያ ውስጥ፤ ይህ ሁሉ ሥርዓት አልበኝነት፣ የዝርፊያ ሸፍጥ፣ በሥልጣን መባለግ፣ ሥልጣን ላይ መሰፋት፣ ሠራዊቱን ለጭቆና ማራዘሚያ መጠቀም፣ የፍትህ ተቋማትን የግል በትር ማድረግና ዜጎች ላይ መጫወት በሃገር ደረጃ ፊት ለፊት ሲፈጸም፤ የሃገሪቱ ዳኞችም እንደ ፊልም እያዩ ነው። የፍትህ መዋቅር ውስጥ ተመድበው የሚያገለግሉ የዳኝነት ባለሙያዎች፣ ይህንን ግልጽና ግዙፍ ብሔራዊ ጉዳይ፤ ምንም እንዳልተፈጠረ ቆጥረው የተለመደ ኑሯቸውን ቀጥለዋል።

አንድም ቀን አንድን ዜጋ ‘ነፃ ነው’ ብለው አሰናብተው የማያውቁ ዳኞች ብዙ ናቸው። መንግሥትን ለማስፈንደቅ ብቻ፤ 10፣ 16፣ 20 ዓመትና እድሜ ልክ ከመፍረድ ውጭ ምንም የማያረካቸው! ያን ከፈረዱ በኋላ፤ ቤታቸው ሄደው ልጆቻቸውን የሚያጫውቱ፣ ጥሩ ራት የሚበሉ፣ ቴሌቪዥን የሚያዩና ከዚያም የሚተኙ! ጥፋተኛ ባልሆነ ዜጋ ላይ የሚፈርድን ዳኛ፣ ትራሱ እንዴት ተመችቶት እንቅልፍ እንደሚወስደው አምላክ ይወቀው! .....ሲነጋ፣ ሰው ናቸውና እንደሰው ፊት አላቸውና እንደሰው ፊታቸውን ይታጠባሉ። ንጹህ ልብስ ይለብሳሉ፣ ጥሩ ቁርስ ይበላሉ፣ ኃይለኛ ማኪያቶ ይጠጣሉ፣ በሰው ላይ በጭካኔ የሚፈርደውን ዶክመንት የያዘ ቦርሳቸውን ያዘጋጃሉ፣ እንደ ጥሩ ሕግ አዋቂ ቦርሳቸውን ያዝላሉ፣ አቆራርጠው ፍርድ ቤት ይደርሳሉ፣ ሰዉን እየገላመጡ ከግቢው ይገባሉ፣ የተከበረውን ፍርድ ቤት ለማርከስም ወንበር ስበው ይቀመጣሉ። በጉዟቸው መጨረሻም፣ መንግሥትን ለማስፈንደቅ፤ 10፣ 16፣ 20 ዓመትና እድሜ ልክ የፈርዳሉ። አንዳንዴ ሳስበው፣ የደሞዝ ጭማሪና የደረጃ እድገት የሚያገኙት በግፍ በሚፈርዱባቸው ንጹሃን ዜጎች ቁጥር ብዛት ብቻ የሚሆን ይመስለኛል።

የሕግ ትምህርትን በሰርተፊኬት፣ በዲፕሎማ ወይም በድግሪ ፕሮግራም ተምሮ የተመረቀ ሰው፤ የፈለገ ፖለቲከኛ ቢሆን፣ የሚማረው ስለፍትህ ነው። የሕግ መጽሐፍቶቹ፣ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ገጻቸው ድረስ የሚተነትኑት፤ ስለ ፍትህ ነው። በበዳይና በተበዳይ ወይም በከሳሽና በተከሳሽ መካከል ያለውን ችግር ከበቂ ማስረጃ ጋር ስለመመልከት እና ያንን ተከትሎ የሃገሪቱን ሕግጋት መሰረት አድርጎ ፍትህ ስለመስጠት ነው። ተምረው የሚመረቁት ያንን ነው፤ ወይም እኔ የሚመስለኝ እንደዚያ ነው። የፖለቲካ አመለካከታቸው ወደ አንዱ ፓርቲ ስላጋደለ ብቻ፣ 20 ዓመት እንደቀልድ ለመፍረድ አይደለም። ለሃገሪቱ መሪዎች 20 ዓመት 20 ቀን የሆነባቸው እንደሆን፣ በግፍ እስር ቤት 20 ዓመት እንዲበሰብሱ ለሚፈረድባቸው ዜጎች፣ 20 ዓመት 20 ቀን የሚሆንበት ምንም ምክንያት የለም። 20 ዓመት፣ የሙሉ ዕድሜያቸው ግምሽ፤ ገፋ ካለም አንድ ሶስተኛ ነው። በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ከሚለመነው ገንዘብ ያሻውን እየወሰደ፣ ያንን ሁሉ ዕድሜ ገደል ውስጥ ገፍትሮ ቲቪ ላይ የሚተከልና ማኪያቶ የሚያንቃርርን የሕግ ባለሙያ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በትእግስት የሚያይበት ምንም ዕዳ የለበትም።

እንደቀልድ፣ ‘መንግሥት ማስረጃ አቀረበ፣ ያቀረበው ማስረጃም አሳበደን፣ ከዚያም 20 ዓመት ፈረድን’ የሚሉ አሉ። ተከሳሾች፣ የተከሰሱበት ክስ 20 ዓመት አይደለም 20 ሠዓት ሊያሳስራቸው እንደማይችል የሚያቀርቡት ቁልል ማስረጃ፤ እነዚያን ዳኞች አያሳምናቸውም። ማተሚያ ቤት በእጁ ያለው መንግሥት፣ የፈለገውን ሰነድ እየሰራና የተጭበረበረ ማኅተም እየመታ የሚያመጣውን ፎርጅድ ማስረጃ የማጣራት ሙሉ ሥልጣን ያላቸው ዳኞች፤ ያንን ፎርጅድ ሰነድ እንደበቂ ማስረጃ ተቀብለው እንደ ቀልድ 20 ዓመት ይፈርዳሉ። ‘መትረየስ ከቤቱ አገኘን’ የሚል የቪድዮ ማስረጃ ሲቀርብላቸው፣ ቪድዮው እንዴት እንደተቀረጸና ደራሲው ማን እንደሆነ እያወቁ፣ ‘ማስረጃው አእምሯችንን አሳበደው’ ብለው 20 ዓመት ይፈርዳሉ። የተማሩበት ትምህርት ቤት ያሉ አስተማሪዎችም ሆኑ መጽሐፍቱ፣ ሕግን እንዲያ በግላጭ እንዲጫወቱበት አይደለም የነገሯቸው፤ ወይም ያስተማሯቸው።

አንዳንዶቹ፣ ‘የባለሥልጣናት ተጽእኖ አለብን’ ሲሉም ይሰማሉ። ያንን ለመሰለው ምክንያት መፍትሔው ቀላል ነው። ከተቻለ፣ ፍትህ እንዲሰፍን ከሚታገሉ ጋር ተቀላቅሎ ፍትህ አልባ እንድትሆን የምትጎተትን ሃገር ለማዳን መሞከር። ካልሆነ ቦታውን በሰላም አስረክቦ ከሙያው ጋር ተቀራራቢነት ያለው ሥራ ሰርቶ በሰላም ማደር። ለምንድ ነው በልጆቻቸው ላይ ሃጢያት የሚከምሩት? እነዚያ 20 ዓመታት ተደማምረው፣ አንድ ቀን በልዩ ልዩ መልክ ወደ ራሳቸው መምጣታቸው አይቀርም። በዚያ ቀን፣ ስልክ እየደወሉ ‘20 ዓመት ፍረድበት! አንተን እኛ እንጠብቅሃለን!’ የሚሉ የዛሬው ባለሥልጣናት ላይኖሩ ይችላሉ። ሥልጣን ላይ ተራራ ይመስል ለዘላለም የተተከለ ሰው የለም። አጼ ቴዎድሮስ፣ አጼ ዮሀንስ፣ አጼ ምኒሊክ፣ ልጅ እያሱ፣ ንግስት ዘውዲቱ፣ አጼ ኃይለ ሥላሴ እና ኮሎኔል መንግሥቱ ሥልጣን ነበራቸው። ዛሬ ሥልጣን የላቸውም፤ ሥልጣኑን ትተው የሚሄዱበት ሄደዋል። የዛሬዎቹም ሰዎች እጣቸው ያ ነው፤ ሰዎች እንጂ ከረባት ያሰረና መነጽር ያጠለቀ ዋርካ ስላልሆኑ ወደዱም ጠሉም ከሥልጣናቸው መፈንገላቸው አይቀርም። ዓለም፤ ከአሮጌው ሂትለር፣ ሙሶሎኒ፣ ስታሊንና ሞቡቱ ከጸዳች ብዙ ጊዜዋ ነው። አዳዲሶቹም አምባገነኖች አሮጌዎቹን እንደሚከተሏቸው መጠርጠር አያስፈልግም።

አንድ ዜጋ ‘በመንግሥት በደል ደርሶብኛል’ ብሎ መንግሥትን ሲከስ፣ ፍትሃዊ የሆነ ውሳኔ መስጠት የሚያቅታቸው ወይም ለመስጠት ፍላጎት የሌላቸው ዳኞች፤ በያቅጣጫው አሉ። መሬቱን ከአግባብ ውጭ በሆነ መንገድ የተቀማን ዜጋ ሮሮ መስማት አይፈልጉም። የፍትህ ሥርዓት መስመር ይዞ በሚሄድበት ሃገር፤ አንድ ዜጋ፣ መንግሥትን ከሶ ማሸነፍ የሚችልበት ሁኔታ ብዙ ነው። ዳኞች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ስለሚያውቁ፣ የስልክ ትእዛዝ አይጠብቁም። መንግሥት ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ፣ መንግሥትን ጥፋተኛ አድርገው አንድን በመንግሥት የተበደለን ዜጋ በፍትህ ያስደስታሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ዳኞች ግን፣ ሥራቸው ሁሉ የተገላቢጦሽ ነው። ኩንታል ሙሉ ማስረጃ ቢኖር፣ በምንም ምክንያት መንግሥት እንዲሸነፍ አይፈለጉም። ዳኝነታቸው፣ መንግሥት በየጊዜው ለሚያጸድቀው ሕግ ሳይሆን፤ መንግሥትን ከዜጋው ለመከላከል የጨቋኙን መንግሥት ጉልበት ሕጋዊ ሽፋን መስጠት ነው። መንግሥት በጉልበት ሊያጸድቀው ካረቀቀው ሕግ ውስጥ፣ መጽደቅ የሌለበትን መዘው በመቃወም የራሳቸውን ሙያዊ ጥረት ስለማድረጋቸው ተሰምቶ አይታወቅም። 20 ዓመት ማከናነብ እንጂ ያንን’ማ አይሞክሩትም። ‘ዳኛ’ የሚባለውን የተከበረ ስም በዚያ መልክ ለምን እንደሚቀልዱበት ግራ ነው የሚገባው። ፍትህ እንዲያሸንፈው የማይፈልገው መንግሥትም፣ በነዚህ ሰዎች አማካኝነት፤ ጥፋተኛ ባልሆኑ ዜጎች ላይ የጭካኔ ፍርድ ሲከምር፣ ለነገ አይልም። ያለ የሌለ ወንጀል ይደርስና፣ ያለ የሌለ ፍርድ ይደፈድፋል።

ሃገር ሙልጭ አድርገው የሚዘርፉትን ፍርድ ቤት አያውቃቸውም። ሃገር የሚያዘርፉትን ፍርድ ቤት አያውቃቸውም። ሰላማዊ ዜጎች የፈጁ የመንግሥት ታጣቂዎች ፍርድ ቤት አይቀርቡም። ለማስፈጀት ትእዛዝ የሰጡ ፍርድ ቤት አይቀርቡም። መሬት የሚቀሙ ባለሥልጣናት ፍርድ ቤት አይቀርቡም። ቤት ያፈረሱ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ፍርድ ቤት አይቀርቡም። እንድምንም ቢቀርቡ እንኳ፣ የሌለ የዋስትና መብት ይፈጠርላቸውና ዳግም ፍርድ ቤት አይቀርቡም። ሰው ያልገደለ ግን ጋዜጣ ላይ የጻፈ፣ አንገቱን ተይዞ ፍርድ ቤት ይቀርባል። ሰው ያልገደለ ግን ‘እከሌ በታጣቂ ተገደለ’ ብሎ የጮኸ ይጠፈነጋል። ‘አትንኩን!’ ሆኗል። ‘የፈለግነውን እናደርጋለን ምን ታመጣላችሁ’ ነው። ‘ፍርድ ቤቱ፣ ወታደሩ፣ ጄኔራሉ፣ ፖሊሱ፣ ደህንነቱ፣ ባንኩ፣ መሬቱ፣ አስፋልቱ፣ ቪላው፣ እስር ቤቱ፣ የጭነት መኪናው.... ሁሉ ነገር የኛ ነው’ አርፋችሁ ተቀመጡ ነው። ‘ማንም ከልካይ የለንም! አፍሽን ዝጊ’ ነው ታሪኩ። ‘ገና የምንወስደው ነገር መዓት ነው፤ ዝርዝሩን አልጨረስንም’ የሚሉ ነው የሚመስለው። መንግሥት እንዴት የራሱን ሃገር ይዘርፋል? አንደኛውኑ በአዋጅ ቢሆን’ኮ፣ ዜጋው የፍትህ ሥርዓት እንደሌለ አውቆ አይንከራተትም፤ ወይ አርፎ ቤቱ ይቀመጣል ወይም ድርሻውን ለመውሰድ ይሞክራል።

‘ፎቁን ወሰዱት፣ እርሻውን ወሰዱት፣ መብራቱን ወሰዱት፣ ስልኩን ወሰዱት፣ ፋብሪካውን ወሰዱት፣ ወርቁን ወሰዱት፣ ሁሉንም ወሰዱት’ ማለት ብቻ ዋጋ የለውም። ‘ትላልቅ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ምርጥ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች፣ ኢንዱስትሪዎችና ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያዎችን በ20 ዓመት ውስጥ በራሳቸው ክልል ውስጥ ገንብተዋ። አንድም የሌላ ብሄረሰብ አባል በወያኔ ዙሪያ ወይም በወያኔ ክልል ውስጥ ሚሊዮነር የሆነ የለም’ ብሎ ማልቀስ መች ነው የሚቆመው? እንዳይወስዱትና ላለማንባት ምን ይደረግ? ቁጭ ብሎ ማየት? .....ስንት ዓመት? 20 ዓመት’ማ አለፈ። .....30 ዓመት? 40 ዓመት? 50 ዓመት? .....እንዲያ ከሆነ እሺ ተጣጥፈህ ተቀመጥ! .....ይመችህ አቦ!

በምንም ተአምር አትታለሉ፤ ኢሕአዴግ በምንም ሁኔታ ሥልጣኑን አሳልፎ ለማንም አይሰጥም። ከተለያዩ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የፈለገ ዓይነት ስምምንነት ቢያደርግ፣ ሥልጣኑን ያጋራል ማለት አይደለም። ቁራሽ ሥልጣን ጠብቃችሁ ከሆነ ዳግም ተሞኝታችኋል። ኢሕአዴግ ሃብትና ሥልጣን አያጋራም። ሁሌም የበላይ ሆኖ ሌሎችን መምራትና መቆጣጠር ብቻ ነው የሚፈልገው። ሌሎቹ እሱን እንዲያጅቡት ነው እቅዱ። ለሚቀጥሉት ብዙ ዓመታትም ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ለመታየት የሚያስችለውን እርምጃ ሁሉ ከመውሰድ አይመለስም። ኢሕአዴግ ገንዘብ ያላቸውን ዓለም አቀፍ ዘራፊዎች የሚሰበስበው፣ ከትላልቅ ሃገራት የጸጥታ ድርጅቶች ጋር የሚሰራው፣ ገንዘብ እየረጨ በየመንደሩ የራሱን ሚሊዮነር የሚቀፈቅፈውና ሰራዊትቱን የሚያንጸው ለሃገር ብሎ አይደለም። ለአንድ ግልጽ ዓላማ ነው፤ ሥልጣኑን ላለማጋራት፤ ሥልጣን አጠገብ ማንንም ላለማድረስ! .....ያ መታመን ያለበት እውነት ነው።

ከኢሕአዴግ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የጠበቃችሁ፤ ከኢሕአዴግ ሥልጣን መጋራት የፈለጋችሁ፤ ከኢሕአዴግ የእምነት፣ የፕሬስና የሃሳብ ነጻነት የጓጓችሁ፤ ‘ከኢሕአዴግ ጋር ተስማምቶ መሥራት ይቻላል’ የምትሉ፤ ተስፋ ቁረጡ። እንኳን አብሮ ለመሥራት ለመወዳደር እድል የማይሰጥ ፈሪ ድርጅት መሆኑን በይፋ አረጋግጧል። ከኢሕአዴግ ጋር አንድ ነገር ብቻ ነው የሚቻለው፤ ከኢሕአዴግ በታች ሆኖ መሥራት። ጫማ እየላሱ ‘ጌታዬ!’ ማለት። ያንን የሚመርጥ የፖለቲካ ድርጅት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደፈለገ መንቀሳቀስና መሥራት ይችላል። ጥሩ ቢሮ ይሰጠዋል። ግዙፍ ባጀት ይመደብለታል። ዓመታዊ ጉባዔውን ሼራተን መደገስ ይችላል። በየምክንያቱ ቤተመንግሥት መግባት መብቱ ይሆናል። የመገናኛ ብዙሃን ችግር አይገጥመውም። እስር፣ ዛቻና ወከባ ሕልም ሆነው ይቀሩለታል። ‘ባሪያ የተቃዋሚ ድርጅ’ እየተባለም ይወደሳል።

የታደለ መንግሥት ያላቸው ሃገራት፣ ከሌላ ሃገር ነው የሚዘርፉት። ከሌላ ሃገር ዘርፈው ሃገራቸውን ያበለጽጋሉ። ዜጎቻቸው እንዳይራቡ፣ እንዳይጠሙ፣ እንዳይታረዙ፣ እንዳይደነቁሩና እንዳይታመሙ፤ ብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቀው ተጉዘው፣ ያገኙትን ሁሉ አግበስብሰው ወደ ሃገራቸው ያመጣሉ። የኛ ሃገር ባለሥልጣና የራሳቸውን ሕዝብ እየሰደቡ፣ እየገደሉና እያሰሩ፤ የራሳቸውን ሃብት ነው የሚዘርፉት። ከአንዱ አቅጣጫ ወደ አንዱ አቅጣጫ ያግዙታል። ከጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉልና ኦሮሚያ ወደ ሌላ ሃገር ይልኩታል። ኢሜይል አስጠላፊ፣ ገዢውን ማኳኳያ ራዲዮ አየር ባለቤት፣ የማወናበጃ መጽሔት አዘጋጅ፣ የተዘረፈ ዶላር አስተላላፊ፣ የፕሮፓጋንዳ ለቅላቂ፣ የሚሰረቅ እቃ ኤክስፖርተር፣ በልማት ስም የዘረፋ አማካሪ፣ የራቁት ዳንስ ቤት ባለቤት፣ የጸጥታ ሰራተኛና ወሬ አመላላሽ የሆኑት ደግሞ፤ የተለመደውን ትብብራቸውን እየለገሷቸው፣ አንድ ላይ ይዝቁታል። የተቀረው ዜጋም አርፎ አልተኛም፣ የ20 ዓመት ‘ዋይ ዋይ!’ አልበቃ ብሎት፤ ለሚቀጥለው ረጅም ‘ዋይ ዋይ!’ እየተሰናዳ ነው። ግን 20 ዓመት ስንት ነው?

(ጸሐፊውን በዚህ ኢሜይል ሊያገኙት ይችላሉ፦ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ