ግርማ ካሳ

የጦርነት ነጋሪት እየሰማን ነው። ገዢውን ፓርቲ የሚደግፉ በሰሜን አሜሪካ የሚገኘው የትግራይ ተወላጆች ማህበር አባላት፣ እንደ አይጋ ፎረም ያሉ ድህረ ገጾች፣ ሕወሃት/ኢሕአዴግ በኤርትራ ላይ ጦርነት እንዲከፍት ከፍተኛ ግፊት እያደረጉ ነው።

እነዚህ ወገኖች፣ ከኤርትራ ጋር ጦርነት ቢከፈት በቀላሉ አስመራ መግባት የሚቻል ሳይመስላቸው አይቀርም። ትክክል ሊሆኑ ይችላሉ። የኤርትራ ጦር ተዳክሟል። ወታደሮቹ መዋጋት አይፈልጉም። በተባበሩት መንግስታት እቀባ ስለተደረገባትም፣ ኤርትራ በቂ መሳሪያ ላይገባላት ይችላል። በአቶ ኢሳያስ ላይም ሕዝቡ ያለው ጥላቻ በጣም ስር የሰደደ ነው። በመሆኑም በቀላሉ የኢትዮጵያ ጦር፣ በኤርትራ ሕዝብ ድጋፍ አስመራ ያለውን መንግስት ሊያስወገድ ይችላል።

ከታሰበውና ከተጠበቀው ውጭም፣ የኤርትራ ጦር ጥንካሬ አሳይቶ፣ ጦርነቱም ረዝሞ፣ እንደ ባድመው ጦርነት በሁለቱም ወገኖች፣ ከሰባ ሺሆች በላይ ወንድሞቻችን የሚያልቁበት ሁኔታ ሊፈጠርም ይችላል። ለሁሉም የሚያዋጣው ግን፣ የተሻለው አማራጭ፣ ወደ ጦርነት ከመጀመሪያውኑ አለመሄድ ነው። ጦርነት አይጠቅምም። ችግርን በጦርነት መፍታት ለነአሜሪካም አልበጀም።

ለዚህም ነው አቶ መለስ ዜናዊ በኤርትራ ጉዳይ ላይ ለፓርላማ በቅርቡ የሰጡትን ምላሽ በአዎንታዊነት የምቀበለው። ችግሮችን በሰላምና በውይይት መፍታት እንደሚጠቅም ነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት። «ከኤርትራ መንግስት ጋር ቢሆን የመጀመሪያ ምርጫችን ጉዳዩን በሰላም መፍታት ነው። ሁለተኛው ምርጫችን በሰላም መፍታት ነው። ሶስተኛው ምርጫችን በሰላም መፍታት ነው» ሲሉ ለሰላም አለኝ ብለው የሚያስቡትን ቁርጠኝነት ይፋ አድርገዋል።

ከአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በየትኛው ቦታ፣ በማንኛውም ጊዜ፣ በማንም አደራዳሪነት፣ አደራዳሪ ካላስፈለገም ያለ ማንም አደራዳሪ፣ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ለመወያየት ዝግጁ እንደሆኑ የገለጹት አቶ መለስ፣ በተለይም በአይጋ ፎረም አዝማችነት እየተቀጣጠለ ያለውን የጦርነትና የጀብደኝነት መንፈስ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ከልሰውበታል።

ብዙዎቻችን፣ ምን አልባት ሁለት የተለያዩ መንግስታት ስላሉ ኢትዮጵያን እና ኤርትራን የተለያዩ አገሮች አድርገን ልንወስድ እንችላለን። ነገር ግን እውነትና ታሪክ የሚያሳያን የኤርትራ ሕዝብ ወንድማችን እንደሆነ ነው። «የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ሕዝብ፣ የኤርትራን ሕዝብ እንደ ወንድሙ አይቶ የሚያስተናገድ ነው። አሁን ብዙ ስደተኞች ነው እየመጡ ያሉት ከኤርትራ። ስደተኛው ሲመጣ ባእድ አገር ውስጥ እንደገባ ሆኖ አይሰማውም። የኢትዮጵያ ሕዝብም የሆነ ባእድ እንደመጣ አድርጎ አይደለም የሚያየው» ሲሉ አቶ መለስ በጥሩ ሁኔታ ከመረብ ባሻገርና ከመረብ ወዲህ ያለው ሕዝብ አንድ ሕዝብ እንደሆነ አስረድተዋል።

ብዙዎች አቶ መለስ ዜናዊ በእናታቸው የአዲ ቋላ (ኤርትራ) ሴት እንደነበሩ ይናገራሉ። በዚህም ምክንያት አቶ መለስ ዜናዊ ለኤርትራ ፍቅር እንዳላቸው ተደርገው ይታማሉ።

እኔም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ለኤርትራ ፍቅር አለኝ። ትውልዴ አዲስ አበባ ነው። «ከአዲስ አበባ ቀጥሎ ሌላ የት ከተማ መኖር ትመርጣለህ» ብባል ድሬደዋ፣ አዋሳ፣ መቀሌ፣ ባህር ዳር ምርጫዬ አይሆኑም። ምርጫዬ አስመራ ነው የሚሆነው። የኤርትራን ሕዝብ ከትግራይ ህዝብ፣ ከጎንደር ህዝብ ከጎጃሜው፣ ከወለጋው ለይቼ አላየውም።

ለዚህም ነው ሳልፈራ አቶ መለስ ዜናዊ ለኤርትራውያን መቆርቆራቸው «ጠቃሚ ነው፤ መልካም ነው። ኢትዮጵያዊ ተግባርም ነው» የምለው። የተባረሩ የኤርትራ ስደተኞች እንዲመለሱ መደረጉ፣ በስደት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የኤርትራ ተማሪዎች በኢትዮጵያ ከፍተኛ ተቋማት እንደሌላው ኢትዮጵያዊ እንዲማሩ መወሰኑ አስደስቶኛል። የሚገነባ ነው። የሚያንጽ ነው። የሚያቀራርብ ነው። በዚህ አቶ መለስ ዜናዊ ሊወቀሱ የሚገባ አይመስለኝም።

በርግጥ ከኤርትራ ጋር ያለውን ችግር እነ አይጋ ፎረም እንደሚሉት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍታት ያስፈልጋል። አሁን ባለንበት ሁኔታ ልንቀጥል አንችልም። ነገር ግን በጦርነት ሳይሆን በሰላምና በውይይት ችግሩን በአስቸኳይ መፍታት ለሁሉም የሚበጅ ነው።

ሌላው ለማንሳት የምፈልገው ነጥብ ቢኖር፣ አቶ መለስ ዜናዊ በፓርላማ ካደረጉት ንግግር በሌሎች ተቃዋሚዎች ላይ ያንጸባረቁትን የንቀትና የጥላቻ አስተያየት ነው።

አቶ መለስ ዜናዊ ከኤርትር ጋር ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ፣ ያላቸውን ልዩነቶች ለመፍታት፣ ሲወስኑ ከአንድነት ለዲሞክራሲን ለፍትህ ፓርቲ እንዲሁም መድረክ ጋር በምንም መልኩ፣ የስነ ምግባር ኮድ የሚባለውን ሰነድ ካልፈረሙ በቀር፣ ለመነጋገር ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ነው የገለጹት። እንግዲህ አስቡት ስለኤርትራ በተናገሩበት፣ ስለ ሰላም ባወሩት አፍ ነው ይህን የሚሉት። ይሄ ምን ማለት ነው? የሰላምና የእርቅ እጅ ለአንዱ ተዘርግቶ ለሌላው የሚከለከልበት ምክንያቱ ምንድን ነው?

በአፋር ለተፈጠረው ችግር፣ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፣ አቶ ኢሳያስን ተጠያቂ አድርጓል። እንደዚያም ሆኖ ግን አቶ መለስ የኤርትራን መንግስት ሽብርተኛ መንግስት አላሉት። «አተራማሽ» ነው ያሉት። እንግዲህ አተራማሽ ባሉት ቡድን ላይ የኃይል እርምጃ እንደማይወስዱ፣ ችግሮችን በሰላም ለመፍታት እንደሚሞክሩ በአንድ በኩል እየተነናገሩ፣ በሌላ በኩል የአገሪቷን ሕገ መንግስት አክብረው፣ በሰላም የሚንቀሳቀሱ እንደ አቶ አንዱዋለም አራጌ፣ በቀለ ገርባ ያሉ የመድረክ አመራር አባላትን፣ እንደ አቶ እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ ያሉ አንጋፋ ጋዜጠኞችን «ሽብርተኞች ናቸው። ኢሳያስ አፈወርቂ ይረዳሉ ...» ብለው የኃይል እርምጃ መውሰዳቸው፣ ወህኒ እንዲወርዱ ማዘዛቸው የሚያስተዛዝብ ነው።

አቶ መለስ ለሰላም ቆሜያለሁ የሚሉ ከሆነ፣ ሁሉ ነገር የሚጀመረው ከቅርብ ነው። ለአስመራ ያውለበለቡትን ነጭ ባንዲራ ለኛም ሊያውለበልቡልን ይገባል። ለፍርድ ቤት ቀጥተኛ ትእዛዝ በመስጠት በግፍ ያሰሯቸውን ንጹሃን ዜጎች በአስቸኳይ መፍታት ይኖርባቸዋል። የሰላም እጃቸውን ለኤርትራውያን ብቻ ሳይሆን ለተቀረውም ኢትዮጵያዊ ሊዘረጋ ይገባል።

በአገር ውስጥ በሰላም የሚታገሉትን ብቻ አይደለም። በውጭ አገር የአመጽ/ትጥቅ ትግል እናደርጋለን ከሚሉ፣ ከነ ኦነግ፣ ኢሕአፓ፣ ከመሳሰሉ ድርጅቶች ጋር፣ ለአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ እንዳደረጉት፣ ያለ አንዳች ቅድሜ ሁኔታ ለመነጋገር ዝግጁ መሆን ይኖርባቸዋል።

ደግሜ እናገራላሁ። አዲስን ነገር ያድርጉ አይደለም የምለው። ለአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ያላቸውን ቅን አመለካከት ለተቃዋሚዎችም ያሳዩ ነው የምለው።

አቶ መለስ ለአቶ ኢሳያስ የከፈቱትን የሰላም በር ለተቀረው ኢትዮጵያዊም የማይከፍቱ ከሆነ፣ ብሄራዊ እርቅና መግባባት እንዲፈጠር የማይሰሩ ከሆነ፣ አጉል የፀረ-ሽብርተኛ ሕግ እያሉ ዜጎችን ማሸበር የማያቆሙ ከሆነ፣ በርግጠኝነት የምነግራቸው ነገር ቢኖር አወዳደቃቸው፣ የርሳቸው ብቻ ሳይሆን የደጋፊዎቻቸውም ሳይቀር እጅግ በጣም የከፋ እንደሚሆን ነው።

ጆሮ ያለው ይስማ፣ ልብ ያለው ያስተውል!

ግርማ ካሳ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ