ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም

(ፍትህ እትም ቁጥር 176 አርብ የካቲት 16 2004 ዓ.ም.)

መንግሥት ለሚባለው ድርጅት የመጨረሻው ተጠያቂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ‹‹መንግሥት ሌቦች›› በአደባባይ ሲናገር ከሌቦች ጋር እየሠራ በመሆኑ እንድናዝንለት ነው? ወይስ ምን እንድናደርግ ነው? ሰዎቹን እንዳንቆጣለት ስማቸውን አልነገረንም፤ ከዚያም በላይ የሚያስፈራው ማፈኛ የሽብርተኛነት ክስ አለ፤ ሰሞኑን በኢንተርኔት የሚሰራጨው ወሬ ታላላቅ ባለሥልጣኖች የሚያሠሩዋቸው ስለተባሉት ታላላቅ ሕንፃዎች ነበር፤ ስደት ለወሬ ይመቻል እንደሚባለው አጉል ጉረምረም መስሎን ነበር፤ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አምርሮ ስለ‹‹መንግሥት ሌቦች›› የሰጠው ምስክርነት ወሬውን ያጠናክረዋል።

 

 

ለመሆኑ ‹‹የመንግሥት ሌቦችን›› ጉዳይ ሊነግረን የሚገባው ማን ነበር? ፖሊሶቹ ‹‹የመንግሥት ሌቦች›› ከተባሉት ውስጥ ይኑሩበት አይኑሩበት የታወቀ ነገር ስለሌለ እንተዋቸው፤ ይህ ጉዳይ ምናልባት የጋዜጦች ዋና ሥራቸው ሊሆን ይችል ነበር፤ ግን በአሁኑ ጊዜ የመንግሥት ሌቦች እየበረከቱ ነው ብለው ቢጽፉ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሌቦች አለቃ አደረጋችሁ ተብለው በሽብርተኛነት ይከሰሱና በማዕከላዊ በኩል ወደቃሊቲ ይጓዙ ነበር፤ አሁንስ ‹‹የመንግሥት ሌቦች›› ከተባሉት ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚከስና ራሱን ከሌብነት ነፃ ለማውጣት የሚከጅል ሰው ሳይኖር ይቀራል እንዴ? በደርግ ዘመን አንድ ጎረምሳ ሻምበል ሎሌ በዩኒቨርስቲ መጣና ፕሬዚደንቱ ዶ/ር ዱሪ መምህራን ሁሉ በራስ መኮንን አዳራሽ እንድንሰበሰብ አስደረገ፤ ካድሬው ተነሥቶ ትንሽ እየተውረገረገ ንግግር አደረገና አንዳንድ ጥያቄዎች ተነሡ፤ በጥያቄዎቹ ያልተደሰተው ካድሬ በራሱ ንግግር ሞቅ እያለው ሲሄድ ‹‹ዱሮውንም ይሄ ዩኒቨርስቲ የአድኃርያን መናኸሪያ መሆኑን እናውቃለን›› አለ፤ እኔ ተነሥቼ በዩኒቨርስቲ ውስጥ ያለው ሰው ቁጥርና በሕዝብ ድርጅት ውስጥ ያለው የሰው ቁጥር መጠን አድኃርያን የሚባሉትን ብናሰላ የአንተ ድርጅት የበለጠ የአድኃርያን መናኸሪያ ሳይሆን አይቀርም፤ ሁለተኛ በእውቀት የምትመራ ሰው ብትሆን ዩኒቨርስቲውን በአጠቃላይ የአድኃርያን መናኸሪያ ከማለት ስም እየጠራህ አድኃርያን የምትላቸውን ማጋለጥ ተግባርህ ነበር አልሁት፤ ተቀለበሰና ማድበስበስ ጀመረ፤ ዛሬስ ቢሆን ከመንግሥት ባለሥልጣኖች ውስጥ ‹‹የመንግሥት ሌቦች ካልካቸው ውስጥ ስሜን አስወጣልኝ፤ አለዚያ እኔ የለሁበትም ብዬ ራሴን አወጣለሁ፤የሚል ሰው አይኖርም እንዴ? የምክር ቤቱ አባሎቹም ቢሆኑ የቀረበላቸውን ተሽዋሚ ሁሉ ሳይመረምሩ እየተቀበሉ በማጽደቃቸው ስሞታው እነሱን ይመለከት ይሆናል፤ አለዚያማ ጠቅላይ ሚኒስትሩ…

 

የኢትዮጵያን ሕዝብ ከወሮበሎችና ከሌቦች ይጠብቃቸዋል ተብሎ ተስፋ የጣለበት መንግሥት እንዲሁ በጅምላ፣ ሾላ በድፍኑ የሌቦች ዋሻ መስሎ እንዲታይ ማድረግ እጅግ ተስፋን የሚያስቆርጥ ነው፤ ተስፋ አስቆራጭ የሚሆንበትም ምክንያት ግልጽ ነው፤ የመንግሥት የበላይ የሆነው ጠቅላይ ሚኒስትር በብስጭት ስለ‹‹መንግስት ሌቦች›› ሲናገር ሌቦቹ ያየሉበትና የተቸገረ ይመስላል፤ ተስፋ የሚያስቆርጠው ለዚህ ነው፤ ‹‹ከሽብርተኞች ሙሰኞች›› ይብሳሉ እስከማለት የደረሰበት ያለምክንያት ነው ብሎ ለማመን ያስቸግራል፤ ለሕዝቡ ግን ትልቁ ችግር የሚሆነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹የመንግስት ሌቦች›› ያላቸውን ያነሣበት ምክንያት ሳይሆን የነዚያ ‹‹ሌቦች›› የተባሉት ሰዎች ሥልጣን ነው፤ ሥልጣኑን የሰጣቸው ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፤ ተጠያቂነትና ኃላፊነት የጠፋበት ሁኔታ ውስጥ መግባታችንን የሚያመለክት በመሆኑ የሚያሳዝን ነው።

 

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ውስጥ ሁለተኛው አስገራሚ ነገር ‹‹የሎጂክ›› ጉዳይ ነው፤ እኔ ሎጂክን ሕገ ኀልዮት እለዋለሁ፤ በትክክል የማሰብ ሕግ ማለት ይሆናል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ መለስ ለምክር ቤት ሲናገር ያንድ ፖለቲካ ድርጅት ስም ጠርቶ አመራሩ በሽብርተኛነት ውስጥ እንዳሉበት ‹‹መቶ በመቶ እናውቃለን›› እያለ ደጋግሞ ገለጠና ሰዎቹ ያልተያዙትና ያልታሰሩበት ምክንያት ‹‹አስተማማኝ ማስረጃ ስለሌለ ብቻ ነው›› ብሎ ተናገረ፤ አቶ መለስ ይህንን የተናገረው በግል ለአንድ ጓደኛው ቢሆን የሚታለፍ ነበር፤ ግን የተናገረው በአደባባይ ብዙ የአገር ውስጥና የውጭ ምስክሮች ባሉበት፣ ሕግ አስከባሪዎች የሚባሉት ሁሉ (ፖሊሶች፣ ደኅንነት የሚባሉት፣ በየቡና ቤቱና መጠጥ ቤቱ የሚርመሰመሱት ሰላዮች፣ ዓቀብያነ ሕግ የሚባሉት፣ ዳኞች ተብለው የሚሰየሙት) እነዚህ ሁሉ አቶ መለስ ‹‹የመንግሥት ሌቦች›› ያላቸውን ጨምሮ ሰምተዋል፤ እንግዲህ አቶ መለስ ለወንጀለኛነታቸው መቶ በመቶ እርግጠኛ የሆነባቸውን ሰዎች ለመያዝና ለማሰር፣ ምስክሮችን በማሠልጠን ማስረጃ ለማዘጋጀትና አስፈላጊውን ፍርድ ለመስጠት የሚሸለሙበትን ሥራ ከአሁኑ አልጀመሩም ለማለት ይቻላል? አቶ መለስ ማስረጃ ቸግሮታልና አዘጋጅቼ ላቅርብለት ብለው የሚያስቡ ሰዎች የሉም ለማለት እንችላለን? በቅርቡ ርዕዮት ዓለሙና ሌሎችም አሥራ አራት ዓመት እስራትና ሠላሳ ሺህ ብር ቅጣት ሲፈረድባቸው አይቻለሁ፤ ምን አድርገው? በእኔ ግምት አደረጉ የተባለው ሁሉ ከወሬ አያልፍም።

 

አቶ መለስ ሎጂክ የሚለውን ቃል ይወደዋል፤ ግን አይተዋወቁም፤ ቢያውቀው ይበልጥ ይወደው ነበር፤ ከመጀመሪያ ደረጃ ሎጂክ ውስጥ አንዱና ዋናው የቅራኔ ሕግ የሚባለው ነው፤ ይህ ሕግ የሚለው አንድ ነገር በአንድ ጊዜ መሆንም አለመሆንም አይችልም ነው፤ ይህንን የቅራኔ ሕግ መጣስ ወፍራም የአስተሳሰብ ግድፈት ነው፤ የመድረክ መሪዎች በአንድ ጊዜ ሽብርተኞች ሊሆኑና በማስረጃ አለመኖር ምክንያት ሽብርተኞች ላይሆኑ አይችሉም፤ አቶ መለስ ደጋግሞ መቶ በመቶ እርግጠኛ ነኝ የሚለው ይህንን ነው፤ የመድረክ መሪዎች መቶ በመቶ የተረጋገጠ ሽብርተኞች ናቸው፤ ግን ማስረጃ ስለሌለ ሽብርተኞች አይደሉም!

 

አቶ መለስ በእምነትና በእውቀት መሀከል ያለውን ድልድይ ብዙ ተመልካቾች ባሉበት ሳተው፤ ምናልባት በመንፈስ ቅዱስ የሚገለጥ እውነት ይዞ ይሆናል፤ ‹‹እግዚአብሔር ወልድ ከእግዚአብሔር አብ ቅድመ-ዓለም ያለእናት ተወለደ፤ እግዚአብሔር ወልድ ድኅረ-ዓለም ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለአባት ተወለደ፤›› ይህ ከእምነት የሚመጣ እውቀት ነው፤ ማስረጃ አይጠየቅበትም፤ ወደ እውቀት ዓለም ስንገባ ማስረጃ የለኝም እንጂ መቶ በመቶ አውኘቃለሁ ብሎ በአደባባይ መናገር ከእምነት ውጭ ምንም አላውቅም ማለት ነው፤ በተጨባጩ ዓለም እውቀት (ሳይንስ) ያለምንም ማስረጃ መቶ በመቶ እርግጠኛነት በጭራሽ፣ በፍፁም፣ በየትኛውም ዓለም፣ በማንኛውም ጊዜ አይታለምም፤ የሂሳብ ነገር ወዲህ ቢሉት አራት፣ ወዲያ ቢሉት አራት ነው፤ የብልጠት አቋራጭ መንገድ የለውም፤ የእድገቱ መመዘኛ እንደሽብርተኞች መመዘኛ ከሆነ ዘፋኙ ሁሉም ዜሮ ያለው ደረሰ ማለት ነው።

 

መቶ በመቶ እርግጠኛ ባልሆንም አቶ መለስ ሀኪም የመሆን ምኞት ነበረው ሲባል የሰማሁ ይመስለኛል፤ እውነት ከሆነ እግዚአብሔር በጥበቡ ሕመምተኞችን ለማዳን መንፈስ ቅዱስን ልኮ አቶ መለስን ከዩኒቨርስቲ ወደጫካ አስወስዶታል ማለት ነው፤ አለዚያ መቶ በመቶ እርግጠኛ ሆኖ ያዘዘው መድኃኒት የመጡለትን ሕመምተኞች ሁሉ ለዘለዓለም እንዳያማቸው እያደረገ ያሰናብታቸው ነበር! የማሰናበቱ ሥልጣን በጠቅላይ ሚኒስትርነትም አለ፤ ፕሮፌሰር ዓሥራትና ዶ/ር ታየ የአርበኞች ግንባር መሪዎች መሆናቸው መቶ በመቶ ‹‹እውነት መሆኑ ታውቆ›› ታሰሩና ማስረጃው ስለጠፋ ከመንገድ እየተያዙ በማዕከላዊ ለምስክርነት ሠልጥነው ፍርድ ቤት በቀረቡ ጊዜ ተናግረዋል፤ በጊዜው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ እነዚህ በማዕከላዊ የሠለጠኑ ምስክሮች በፍርድ ቤት የሰጡትን ቃል በይፋ በአማርኛም፣ በእንግሊዝኛም አውጥቶታል።

 

አቶ መለስ በምክር ቤት ለሚቀርቡለት ጥያቄዎች መልስ ሲሰጥ በጠያቂዎቹ ላይ ከማተኮርና እነሱን ለማሸማቀቅ ከመጣር ይልቅ ጉዳዩን በቀጥታ ቢያስረዳ ከብዙ የሚመዘገቡ ግን አላስፈላጊ ስሕተቶች ይድን ነበር፤ እግዚአብሔር እሱንም እኛንም ይርዳን።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ