አደገኛና የተቀነባበረ የዘር ማጥፋት ሴራ-ክፍል 2 (ዳኛቸው ቢያድግልኝ)
ክፍል 2. መሪ የሌለው ሕዝብ እረኛ እንደሌለው መንጋ ነውና መሪዎቹን ከሕዝቡ መነጠልና ከሀገር ማስወጣት
ከእለት ተዕለት ኑሮው ጋር እየኖሩ፣ ደስታውንና ሀዘኑን እየተጋሩ በየቀኑ የሚያድገው አስተሳሰብ ከሚፈጥረው እውነታን ገላጭ ቋንቋ ጋር ተሳስረው የሚኖሩ ምሁራን፣ ጋዜጠኞች፣ መምህራን፣ የኪነጥበብ/ስነጥበብ ሰዎች፣ ተማሪዎችና ሌሎችም ህብር ነው የአንድን ማሕበረሰብ ጠንካራ ቁርኝት የሚገልጹት። እንዲህ ያለ ጠንካራ ትስስር ያለው ማሕበረሰብ ውስጥ የሚፈጠሩ መሪዎች ደግሞ በቀላሉ በችግሮቹ ዙርያ መወያየትና መፍትሄ መፈለግ ይችላሉ።
‘መሪ የሌለው ሕዝብ እረኛ እንደሌለው መንጋ ነውና ተቃዋሚውን ከሕዝቡ በመነጠል ከሀገር ማስወጣት’ የሚለው የወያኔ መርህ በስንቶቻችን ጆሮ እንደሚጮህ አላውቅም። ግን ተገፍተን አገር ለቀን ስንወጣ ከዋናው የትግል መስክ ገሸሽ ተደርገናል። መታሰርና ቆሞ መሞት መለኪያው ነው ለማለት ሳይሆን ካገር ከወጣን ወደ ትግል እስክንገባ ድረስ ያንድ ሰሞን ወሬ ነን። ስንታሰር ግን እስከምንፈታበት ጊዜ ድረስ ትኩሰ ዜና ስለምንሆን ማታገያና ማሰባሰብያ ለሌሎችም አርአያ እየሆንን ተተኪ ታጋዮችን እናፈራለን።
ለሕዝብ የማያስብ መንግስት ይልቁንም የአጥፊ ተልዕኮ ይዞ የሚንቀሳቀስ የመለስ አይነቱ ገዢ ግን ይህንን ቁርኝት አጥብቆ ይፈራዋል። ስርዓቱ በርሱ ቢጤ ከሀዲዎች ሲያዝ መፍትሄው ሁሉ ብቅ ያለውን መግደል ይሆናል። ይህን ሲያደርገው የነበረ ቢሆንም አሁን ባለበት ሁኔታ ታዋቂ ሰዎችን መግደል እምብዛም አያዋጣውም። ታዋቂ ቢሆኑ አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ የሚያስባቸውን ነው ከስር ከስር የሚያጠፋው። ይህንን እያደረገ ግን ክሕዝቡ ጎላ ብለው የሚታዩትን መምህራን፣ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና ጋዜጠኞችን ቢቻል አስፈራርቶ ካልሆነም እያሰረና እየፈታ የመውጫ ኮሪደሩን መክፈት ነው። በስውር የሚሰራው ግፍ ደግሞ አብዛኛውን ተስፋ ቢስ ስለሚያደርገው ስደትን የመጨረሻ አማራጭ እንዲያደርገው ይገፋፋል። ያኔ ሀገሪቱን በግላጭ ለመዝረፍ ይመቻል ማለት ነው።
ድህነት ደግሞ ለስደት ሌላው ምክንያት ይሆናል። መታሰርና ከስራ መባረር ካለ ለታጋዮች ወጪያቸውን ሸፍኖ በቆራጥነት እንዲታገሉ ለማስተባበር የተደራጀና በገንዘብ አቅሙ ጠንካራ የሆነ ሀይል ከውጪ ባለመኖሩ የሀገር ቤቱን ቆይታ እጅግ አስቸጋሪ ያደርገዋል።በርካታዎቹ ታጋዮች ኑሮአቸው ከእጅ ወደ አፍ ነውና ችግሩ የከፋ ይሆናል።
ስደት ደግሞ አስኪለመድ የራሱ ጣጣ አለው። ወደ አዲስ ኑሮ ውስጥ ሲገባና ለእለት ጉርስ ሩጫ ሲጀመር ብዙ ነገር ማድረግ አይቻልም። በዚህ መካከል ከሀገር ቤት ጋር ያለ ቁርኝት እየቀነሰ ግንኙነትም እየላላ ሲሄድ መረጃም እያነስ ይመጣል። የብዙዎቻችን አእምሮ ተቀርጾ የሚኖረው ሀገር ቤት በነበርንበት ወቅት የነበረው ሁኔታ ነው። ለዚህም አንዳንዶቻችን ከሀያ አመት በፊት የወጣን ከሆነ ትውስታውና አዘውትረን የምናወራው በዚያን ወቅት በነበረው ጉዳይ ላይ ይሆንና ከዚያ በሁዋላ ያለውን ለውጥ ለማጣጣም ያስቸግረናል። ምክንያቱም የትግል ልምዱ የሚመነጨው ከነበረው ተለምዶ ነውና ነው።
ሌላው የስደቱ ጣጣ እጅግ ተቀራርበው መስራት የሚችሉና አንዳቸው ለሌላኛው ብርታት የሚሆኑ ሰዎች በጣም የተራራቀ ቦታ መኖር ይገደዳሉ። ከዐይን ሲርቁ ከልብም ይርቃሉ ነውና አብሮነት የሰጣቸውን ጉልበት ስደት ያደክመዋል ይሰብረዋልም። በተለያየ አጋጣሚና የጊዜ ልዩነት የመጡ ደግሞ ልክ እንደ ትውልድ ልዩነት የአስተሳሰብና የቅራኔ አፈራረጅ ልዩነትም አላቸው። መመሳሰል እስኪቻል ድረስ ዘመናት ይነጉዳሉ። ስለዚህ ሁሉም ከቢጤውና ከመሰሉ ጋር መደራጀትን ይመርጣል። ሁሉም ባለድርጅት ግን ያልተቀናጀና አንዳንዴም የማይተዋወቅ ይሆንና ውጤቱ የሚያመረቃ አይሆንም።
ይህ መሰሪ የሆነው የወያኔ የብተና ስራ የአመት አምስት አመት ሳይሆን ቶሎ ካልተያዘ ሀገር የማጥፋት ነውና ትግሉ ፈጣን ቀልጣፋና ውጤታማ እየሆነ ሊጓዝ ይገባዋል። ይህንን ጉዳይ መተንተኑ ለቀባሪው አረዱት ሊሆን ስልሚችል ከዘር ማጥፋት ወይም ትውልድ ከማቀጨጭ ጋር ለማያያዝ የፈለግሁት ካንገቱ ቀና ብሎ የሚሄድ ትውልድ እንዳይኖር ከተደረገና ሁሉም መዳን በስደት ነው ብሎ በልቡ ከሸፈተ ሀገር ለቀማኞች የተተወ ያንድ ጎሳ ወይም ጎጥ የበላይነት ይልቁንም የውጭ ኢንቨስተሮች ገነት ሆነ ማለት ነው።
ሕዝቡ ለባርነትና ለስደት እየተዳረገ ሲቀጭጭ ማለትም ባህሉ፣ እምነቱ፣ ቋንቋውና የአኗኗር ዘይቤው ያለ ፈቃዱ ሲለወጥ አገሩ እየተነጠቀ ሞቱን ሲጠብቅ አገር እየሞተች ነው ማለት ነው። ለዚህም ነው ጉዳዩን ከዘር ማጥፋት ጋር ሊያያዝ የሚገባው። በአሜሪካ አንድ ከተማ ያሉ የሕክምና ዶክተሮች በአገሪቱ ካሉት በቁጥር የሚበልጡ ከሆነ ሀገር ቤት ውስጥ ሕክምና በማጣት የሚሞተው የዚሁ ስርዐት ሰለባ ነው ማለት ነው። እንዲህ እየተባለ ብዙ መተንተን ይቻላል። የዚህ ጽሁፍ አላማ በዚህ ለመቆም ሳይሆን ይህንን ችግር ወደ ውጤታማ መንገድ መውሰድ እንችላለን ግን እንዴት? በሚለው ጉዳይ ላይ ሀሳብ ለማንሳት ነው።
• ከሀገር ያወጣንን ስደት ፋይዳ ወዳለው ህብረት እንዴት?
የችግሩን መጠነ ሰፊነትና አደገኛነት መግለጹ እንደማሳሰብያ ቢሆንም ትልቁ ነገር መፍትሄ ሊሆን የሚችለው ጉዳይ ላይ ትኩረት መስጠቱ ነው። እንደ እኔ እምነት ያለውን ጥቂት ሀብት በአግባቡ መጠቀም፣ በእውቀት የጎለመሱ ዜጎችን ማፍራት እንዲሁም በሀገር ቤት የሚደረጉትን ትግሎች ማበረታታትና ድጋፍ መስጠት፣ በሀገራችን እየሆነ ያለውን ለሌሎች ማሳወቅ። የደነገጡ፣ የበረገጉ፣ ያኮረፉ፣ ግራ የተጋቡ ወገኖችን ማሰባሰብ መቻልና ለትግሉ ጉልበት እንዲሆኑ ማድረግ አስፈላጊው ስራ ይመስለኛል።
ያለንን የሰውና የገንዘብ ሃይል በአግባቡና ለውጤትም በመጠቀም (ወደ አንድ ጉልበት መለወጥ እንኳን ቢከብድ) ለተመሳሳይ አላማና ለተመሳሳይ ውጤት ሀብታችንና ጉልበታችን እንዳይባክን ማድረግ አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ በይዘታቸው በጣም ተመሳሳይ የሆኑ ብዙ ድህረ ገጾች አሉ። አንዳንዶቹ እንዲያውም ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል ከሌሎች ድህረገጾች እየገለበጡ የሚለጥፉ ናቸው። ነገር ግን እኒሁ ድህረ ገጾች በየተቋቋሙባቸው ሀገራት ያሉትን አገር ነክና ፋይዳ ያላቸው ዓለምአቀፋዊ ወሬዎችን ቢያቀርቡ፤ በየሀገራቱ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ስራና ሕይወት ቢያስተዋውቁ የበለጠ የሚያቀራርቡና የሚያዋድዱ ሊሆኑ ይችላሉ። የትምህርት አምድ ቢኖራቸውና ኢትዮጵያውያንም ይሁን በየሀገራቱ ያሉ ምሁራን ትምህርት እንዲሰጡ ማድረግ። አንዳንዴም የሚያቀርቡትን ትምህርት በቀላል አቀራረብ ወደ አማርኛ በመመለስ ታዳሚውን በ እውቀት ማነጽ ቢችሉ መልካም ነው። የድህረ ገፅ አዘጋጆች የግድ ይህ ሁሉ እውቀት እንዲኖራቸው አይጠበቅም። ይልቁንም ሌሎችን የማሳተፍ ልምድና ችሎታቸውን ነው ሊያሳድጉ የሚገባው።
በተጨማሪም በየሀገራቱ ተበትነናልና ልጆቻችንም አፍ የሚፈቱት በተለያየ ቋንቋ ነው። እኒህ ድህረ ገጾች የጀርመኑ ከጀርመንኛ፣የእንግሊዙ ከእንግሊዝኛ፣ የደቹን ከደች ወዘተ እያስማሙ ኢትዮጵያዊነትንና የመግባቢያ ቋንቋውን ቢያስተምሩበት ተተኪው ትውልድ የሚግባባበትን መንገድ እየፈጠርን ኢትዮጵያዊነትን እያስከበርን መኖርን እንቀጥላለን። የወንድማማች ልጆች በተለያየ አገር ቋንቋ አፍ ፈተው ኢትዮጵያ ለጉብኝት በመጡ ጊዜ መግባባት ያለመቻላቸውን ሰምቼ አዝኜ ነበር። እንደ ሀገር ስናስበው በአንድ ቋንቋ ተናግረን ያልተግባባን የመጪው ትውልድ ደግሞ ምን ይጠብቀዋል ብሎ መዘጋጀት ተገቢ ንወ። የወያኔን በደልና ከዚያም በፊት የነበረውን እየቆጠርን በቃላት መጠዛጠዙ ብቻውን አገር አያድንም። ስለምንኖርባቸው ሀገራት ታሪክ ማወቅና ለኛ ተሞክሮ የሚጠቅመውን ማሳወቅም አንድ ትልቅ የልምድ መቅሰሚያ መንገድ ነው። ለዚህ ግን አዘጋጆች ማንበብ፣ መመርመርና እውቀት ማዳበር የግድ ያስፈልጋቸዋል። ባሉበት እየረገጡ ወደፊት ሂድ ማለት የመለያየት መጀመርያው ነው።
ፖለቲካው ላይ ብቻ ማነጣጠር ፋይዳም የለውም። ለሀገር የሚያገለግል ደግሞ የግድ የፖለቲካ ድርጅት አባል ሊሆንም አይገባም። እንዲያውም የፖለቲካውን አቅጣጫ የሚቀርጸው ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ስነልቦናዊ ትስስር ነው። ይህንን በማጎልበት፣ ከድክመታችን ይልቅ ጥንካሬያችንን የሚገልጹ፣ ከተሸናፊነት ይልቅ አሸናፊነትን የሚያበስሩ ከክስና እርግማን ይልቅ ሽልማትና ምርቃትን የሚዘክሩ ነገሮችን ብንሰራ ቢያንስ ጠላት ደስ አይለውም። እንደተፈለገው ኢትዮጵያ መሞት ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ባሉበት ሁሉ ኢትዮጵያ እንድትወደስ ማድረግ ይቻለናል። ያኔ በመጥፎ ነገር የተሳቀቀው ልባችንና አእምሮአችን በደስታና በተስፋ በሳቅና በፍቅር ይሞላል። ይህም እውነት ነው Posititve thinking እና Emotional Intelligence እየተባለ የሚነገረው። ሀዘን ሀዘንን፣ ክስ ክስን፣ ወቀሳ ወቀሳን ይወልዳሉ መጥፎነታቸው ደግሞ እንደ ተላላፊ መሆናቸው ነው። ዐየሩ በዚህ ከተሞላ ሁሉም ይታመማል። ለዚህም ነው በርካታዎቹ ተቋሞቻችን በመፋረስ በሽታ እየተሰቃዩ ያሉት ማለት ይቻላል።
ይህንን ቀዳዳ ለመድፈን ደግሞ የወገንን የቋንቋና የእወቀት ደረጃ ከግምት በማስገባት መሰረታዊ የሆኑ ትምህርቶችን በተለያዩ የመገናኛ መድረኮች ማሰራጨትና መወያየት እንዲቻል ማድረግ። ለምሳሌ ስለ ዲሞክራሲ፣ ስለ ነፃነት፣ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ሰለ ጎሳ ፌዴራሊዝም፣ ስለ ማህበራዊ ኑሮ፣ ሰለ ውጪው አለም ኑሮና ራሳችንን ስለማዘጋጀት፣ ስለ ባህል፤ ስለ ጤና፣ ስለ ስብሰባ አመራርና ውይይት፣ ስለ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች፣ ስለ መንግስት መማማር መቻል የበለጠ ዝግጁ ያደርገናል። አስፈላጊው እውቀት ከሌለን እንደ ሕዝብ ዘለቄታ ያለው መፍትሄ ልናመጣ አይቻለንም። አስፈላጊው አውቀት ብዙሀኑ እንዲኖረው ካልተደረገ ጠንካራና አስተማማኝ ድጋፍም መጠበቅ ስህተት ነው የሚሆነው። በእውቀት የተገነባን ከሆንን ጠንካራና መሰረታዊ ጥያቄዎችን የምንጠይቅና መንገዱንም የምናመላክት ከሆንን ለመምራት የሚነሱ ሁሉ በቅጡ የተዘጋጁ ይሆናሉ። መሪ መፍጠርም ከባድ አይሆንም። ስለዚህ ምሁራኑ ፊታቸውን ወደ ወገን በመመለስ ብዙዎችን ልንደርስበት በምንችለው ቋንቋ በመጠቀም የአስተሳሰብ አድማስን ማስፋት አንገብጋቢው ጉዳይ ነው። ሁነቶችን ተከትለን መተንተን ብቻ ሳይሆን እኛው ራሳችን ሁነቶቸን የመፍጠር አቅም እንዲኖረን አድረገን ካልተዘጋጀን መከተል እንጂ መቅደምና ማሸነፍ የሚችል አቅም አይኖረንም።
ይቀጥላል ...
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!
ዳኛቸው ቢያድግልኝ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



