ኤርትራ በኤርትራ ተወረረች
ታረቀኝ ሙጬ
እንደማንኛውም ጊዜ ሁሉ የወያኔ ኢሕአዲግን የዜና ማሠራጫዎች - በቀላልና ለሁሉም በሚገባ ቋንቋ የበሬ ወለድ ቱሪናፋ ማራገቢያ ወናፎች ማለትም ይቻላል - እንደአጋጣሚ ሆኖ ከተከታተልኩ ብዙውን ጊዜ ራሴን የምታመምበት አንዳች ነገር አላጣም። በሁለት ሰዓቱ የዛሬ ምሽት ዜና ላይ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ድህነት ከ38.7 ወደ 29.6 በመቶ የመቀነሱን ዜና ስሰማ የወትሮ የለበጣ ሣቄም ሳይቀር ከዳኝ። ኑሮው በየቀኑ እየኮደኮደኝ በምን አቅሜ ልሣቅ? ”እዬዬም ሲደላ (ሲዳላ) ነው” መባሉም እኮ ለዚህ ነው። ሣቅም ሆነ ልቅሶ ድሎትን ይሻሉ ማለት ነው።
ለወያኔና ለአጫፋሪዎቹ እርግጥ ነው ድህነት ቀንሷል ብቻ ሣይሆን ከነአካቴው ጠፍቷል። ከድሃ ቤተሰብ መፈጠራቸውንም ራሱ ረስተውት ከማይምነትና ከጸላኤ-ኢትዮጵያዊነት ጋር የተለወሰ የሀብት ብዛት አናታቸው ውስጥ ከፍተኛ የሞራ ክምችት ፈጥሮባቸው አብደውና ሰክረው በተለይ በአሁኑ ሰዓት ይሠሩትን አጥተዋል። ”ከተራበ ለጠገበ አዝናለሁ” የምንለውን ነባር ብሂል በእነሱ ላይ እየታዘብን ነው። ጥቂት ወያኔዎችና አሽከሮቻቸው ስለጠገቡና እሚሠራቸውን ስላጡ ግን ድህነት ከሀገር ተነቅሎ ወጣ ማለት እንዳልሆነ በብዙ ማስረገጫዎች እውነቱን መግለጽ ይቻላል።
እንደወያኔ ዘገባ ቻይና 10.3 በመቶ ዕድገት እያስመዘገበች ስትሆን ኢትዮጵያ ቻይናን አስከትላ በ11 ከመቶ በላይ በፈጣን ዕድገት ዓለምን እየመራች ናት። ይሄው ግስጋሴዋም በነ”የዐይጥ ምሥክር ድንቢጥ” የግም ለግም ተያይዘህ አዝግም ወሽካቶች የሀሰት ምሥክርነት እየተደገፈ በዕብለት ጎዳና መትመሙን ቀጥሏል።
በዓለማችን ብዙ አስደናቂና አሳዛኝ እውነታዎች እታዘብን ነው። የወያኔ ውሸትና ሕዝብን በሁሉም ረገድ ማጎሳቆል፣ ከንዑሳኑ ጎሣ በልዩ ሥልት በአባቱ አማካይነት ሥልጣን ላይ የወጣውና ”መንበሬን በሰላም ከምለቅ ሦሪያ ከነሕዝቧ እንጦርጦስ ትውረድ” ብሎ የቆረጠው የመለስ የባሕርይ ወንድም የሶሎጉ ባሽር አላሳድ ጭፍጨፋ፣ የፑቲን ቅጥፈት፣ የምዕራባውያን በተለይም የአሜሪካ ትምክህትና ማንአብኝነት፣ የቻይና ማስመሰልና አድርባይነት (opportunism)፣ የኢራን ከማን አንሼ እልኸኝነትና የተጣለባት የኢኮኖሚ ማዕቀብ፣ የሰሜን ኮሪያ ብሔራዊ ኩራትና በዚያም ሰበብ የተከሰተባት ኢፍትሃዊ መገለልና ማዕቀብ፣ የነዳጅና የምግብ ምርቶች የዋጋ ንረት፣ የታሊባን አልሞትባይ ተጋዳይነት፣ የዓለም ሕዝብ ብዛት በአስደንጋች ሁኔታ መጨመር፣ አደጉ በሚባሉ ሀገሮች የሕዝብ ቁጥር እየቀነሰ መምጣት፣ የኔቶ - የአልቃኢዳና መሰል ጉልበተኛ ታጣቂዎች አሸባሪነት (መሣሪያ የያዘ ባብዛኛው ”አሸባሪ” ነው ቢባል ምን ውሸት አለው?)፣ የዓለም ሰላማዊ ሕዝብ ተሸባሪነት፣ የፖለቲከኞች መሠሪነት፣ የኃይማኖት አክራሪነት፣ ኃይማኖት የለሽነት፣ የአምባገነን መሪዎች ዕብሪት፣ የባለሀብቶች መረን የለቀቀ ጥጋብ፣ የሊቢያ፣ የየመንና የግብጽ ውሽንፍር፣ የኃይማኖትና ባህል ዓለማቀፋዊ ዝቅጠት፣ የተፈጥሮ ሀብቶች መመናመን፣ የኦዞን ንጣፍ መሣሣት፣ የደኖች ተመንጥሮ ማለቅ፣ የአፈር መሸርሸር፣ ሆዳምነትና ኅሊናቢስነት መንሰራፋት፣ የዓለም የሙቀት መጠን በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ መሄድ፣ የሰዎች ጭካኔ ከምንጊዜውም በላይ እየጨመረ መምጣት፣ በየሀገሮች መካከል ሊፈነዱ የተቃረቡና ኒኩሌርን በዋናነት ጨምሮ በሌሎች ሕዝብ ጨራሽ መሣሪያዎች (Weapons of Mass Destruction (and Distraction as well) የታገዙ ጦርነቶች ድግስ መጧጧፍ፣ የብዙዎች ወጣቶች ዓላማ ቢስነትና ጨለምተኝት፣ የበርካታ ዜጎች ተስፋ መቁረጥና ከጤናማ ሕይወት እየወጡ ለሱሰኝነትና ለሞራለቢስነት ሕይወት መዳረግ፣ የፍቅርና እምነት መጥፋት - መተሳሰብና ሰብዓዊነት መደብዘዝ፣ የዘረኝነትና ጎጠኝነት ክፉ ይትበሃል እንደወረርሽኝ መስፋፋት፣ አስተዋይነትና ብልህነት በደደብነትና በራስ ወዳድነት መተካት፣ … ከሁሉም ከሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድም ዘመን በቅጡ ሳያርፍ የነዚህ ሠይፎች ዋነኛ ሰለባ ሆኖ ባግባቡ ከኖሩትም ለመኖር ካቆበቆቡትም ጋር ሲጠፋ መመልከት ከጸጸቶች ሁሉ ከፍተኛው ነው። ረጂም ዐረፍተ ነገር እንዴት ያስጠላል እባካችሁ? ባጭሩ ባልቀጨው እኮ ከዚህም ሊረዝም ነበር ማለት ነው።
ስለወያኔ ውሸታምነት እንኳን ዓለምና እኛ ግፉዓኑ ራሱ ወያኔም አሳምሮ ያውቃል። ውሸታምነቱም አልጠቀመውም አይባልም። ጎሣዊ፣ ብሔራዊ፣ ዓለማቀፋዊና ካስፈለገም ከዚያም ባሻገር ያሉ ሞኞችንና የዓላማ ተቆራኞችን ለማታለልም ሆነ ለማስደሰት ይጠቀምበታል። እንጂ እኔ የባለ አራት ሺህ የወር ደሞዝተኛው - በኑሮ ውድነቱና በወያኔ ገንዘብ የመግዛት አቅም መንኮታኮት ሳቢያ ከድራፍት ቤት ተባርሬ ከወጣት ሀገር አልባዎች ጋር ሻሜታና ኮረፌ ቤት እየቆዘምኩ በምገኝበት ሁኔታ እንዴት ነው ድህነት ቀነሰ የሚባለው? እኔ እንዲህ የተሰቃየሁ ከኔ በታች ያሉ የባለ ሁለት መቶና ሦስት መቶ ብር የወር ደመወዝተኞች ምን ይሁኑ? ፍረዱታ አንባቢያን። አታሞ በሰው ዕጅ ታምር ነው ነገሩ።
ለትራንስፖርት እንኳን የማይበቃ ደሞዝ ተብዬ እየተከፈላቸው እሚሠሩ አናውቅም? ”ደመወዝ” እያገኙ፣ የዘመድ ድጋፍ እየተወረወረላቸው … ያ በፍጹም ስለማይበቃቸው እሚለምኑ አናውቅም? በኢምግሬሽን ቢሮ - ጥቁር አንበሣ ሆስፒታል አካባቢ እንደወገብ ዝናር ሦስት አራት ዕጥፍ ለስደትና ለዐረብ ሀገር ግርድና/እሽክርና የሚሠለፈው ሕዝብ ሀብታምነትን ጠልቶ ይሆን? ቆሼ ተራ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕጻናትና ወጣቶች እንደዝንብ የሚተረማመሱት የዕድገታችንን ፍሬ ለመቋደስ ይሆን? ኧረ! ወያኔዎች የኔን የትንሹን ኢትዮጵያዊ ልመና ስሙኝና ትውልዳችሁን ለማዳን ወደኅሊናችሁ አሁንም ቢሆን ተመለሱና ቢያንስ ይህን የሚገማና የሚገለማ አፋችሁን ዝጉ!
መቸገር በኛ አልተጀመረም፤ በአምባገነን ቀጥቃጮች መቀጥቀጥ በኛ አልተጀመረም፤ ወገን ሊሆን በሚችል መሠሪ ጠላት መሰቃየት በኛ አልተጀመረም፤ በዕጅ አዙር ቅኝ ግዛት መንገብገብ በኛ አልተጀመረም፤ ከሥጋዊ ስቃያችን የበለጠ እየጎዳን ያለው ይህ በሚከረፋ የፕሮፓጋንዳ ሥልት የምታደርሱብን የኅሊና በደል ነው። ከዚህኛው ብፌ እባካችሁን ቀንሱልን። በበኩሌ አንገፈገፈኝ። የሥላሤን ዝክር ስጠራ ባልሄድ ምን ነበረበት? ምነው እግሬን በሰበረው! እሰው ቤት እኮ ነው ቲቪ ተከፍቶ ያየሁት።
ድህነት በወሬ ሆነ እንዴ የሚቀንሰው? ትራንስፎርሜሽን በሥራና በጥረት እንጂ በሀሰት ወሬና ቤተ ሙከራ ውስጥ በተጠፈጠፈ የውሸት ዘገባ በጭራሽ አይሳካም። በመጀመሪያ ደረጃ ትራንስፎርሜሽን ብሎ ነገር፣ ህዳሴ ብሎ ነገር የአታጣ ማርያም የመለስ ፍብርክ ነጭ ውሸት እንጂ ወደ እውነትነት ሊገለበጥ የሚችል አንዳችም ቁም ነገር እንደሌለው የታወቀ ነው። መለስ ግን እንዴቱን ያህል ታድሎ ያልታደለ ነው? መታደሉ መላውን ዓለም እያጭበረበረ በአፍዝ አደንግዙ ዐይናችንን አሳውሮና ማሰቢያ አካላችንን አደንዝዞ እስካሁን ሥልጣን ላይ መቆየቱ ሲሆን፤ አለመታደሉ ደግሞ በግብሩ መጠላቱ ነው። በአምስት ዓመት ኢትዮጵያን በዕድገት ከመካከለኞቹ ተርታ አደርሳለሁ ብሎ ስለወሻከተ ያንን ውሸት ለመደገፍ ነው እንግዲህ ድህነት በዚህን ያህል መቶኛ ወረደ ብሎ ያስነገረው። እውነቱማ ባለበት አለ። ይህ ተጨፈኑ ላሞኛችሁ የሞኝ ፈሊጡ የተለመደ ማታለያና የሥልጣኑ አንቲሪትሮቫይራል መሆኑ ነው።
”ሆድን በጎመን ቢደልሉት ጉልበት በዳገት ይለግማል” ይባላል። ከመቶ ሁለትና ሦስት የማይሞላ ሕዝብ አዲስ አበባን ጨምሮ በጥቂት ዋና ዋና ከተሞች በተንደላቀቀ ኑሮ ስለሚገኝ ሚሊዮኖችን ይወክላል ማለት አይደለም። ከፍ ሲል ራሴን በምሣሌነት አቅርቤያለሁ። የኔ ደሞዝ በኢትዮጵያ የደመወዝ እስኬል መሠረት ከሀብታሞች የምመደብ ነበርኩ - በነበር ባይቀር። ነገር ግን የ30 ብር ኩንታል ጤፍ በብር 1500 (ልብ በሉ 50 ዕጥፍ ማለት ነው!) እንድገዛ እየተገደድኩ፣ የ50 ሣንቲም ኪሎ ስኳር በ15 ብር፣ የ75 ሣንቲም ዘይት በ58 ብር (እንቶኔ የተባለውና ከምን እንደተሠራም እንኳን የማይታወቅ በጠባይም ከጓያ ጋር ምስስል አለው እሚባል የዐረብ ዘይት)፣ የ65 ሣንቲም ሊትር ቤንዚን 19.26፣ የ4 ብር ኩንታል ከሰል 160 ብር፣ ምኑ ቅጡ … ስንቱስ ተዘርዝሮ … እንዲያው ለአብነት እነዚህን ጠቀስኩ እንጂ ኑሮማ ሰማይን አልፋ ከነጎደች በትንሹ ሰባት ዓመታት ተቆጠሩ።
ወይ ነዳማ! ምናለበት የ97 ምርጫ ተብዬ ነገር ባይመጣ ኖሮ? ጉድ ሠርቶን ሄደ። መሄዱ ብቻውን ባልከፋ - ጦስ ጥምቡሱ አልለቀን ብሎ የኑሮ ምህዋራችንን ከማናጋቱም በላይ እንደ እስክንድር ነጋና እንደ አንዱዋለም አራጌን የመሳሰሉ የሀገር ተስፋ ወጣቶችንና አለኝታዎቻችንንም ለእሥርና እንግልት ዳረገብን። ይሁን ለበጎ ነው። ያለ መስዋዕትነት የሚገኝ ድል አይጣፍጥም ይባላል - ግን ሸክማቸውን እናግዛቸው። ”ሃምሣ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክም ነው …” እንዲሉ። እንደዶክተር ፍስሐ እሸቱ ከተኛንበት የሰመመን እንቅልፍና ከተጣለብን አንደርባዊ ደንቃራ ነቅተን አንዳች ነገር እናድርግ። በቃ - ባጭሩ ሰው እንሁን ጎበዝ። ኢትዮጵያዊነትን ከማፈሪያነት እንደቀድሞው መኩሪያነት እናድርገው። እርግጥ ነው - ”Better said than done” - ቢሆንም … ቢሆንም …
ቅድም ያ የዐማራው ተወካይና እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በግልጽ ከዚያም በኋላ ከመጋረጃ በስተጀርባ የዐማራው ድርጅታችን የኢሕዲን ማለትም የብአዴን ሊቀመንበር የነበረው በረከት ስምዖን በቪኦኤ ሲናገር ሰማሁትና ርዕሴን በሱው ቅኝት አስኬድኩት። የዐማራው ድርጅት ሊቀመንበር እሚናገረው ልክ እንዳሥመራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ተጠሪ በትግርኛ ነበር። በትግርኛ መናገሩ በራሱ ልማት ካልሆነ ጥፋት የለውም። ለምን በወዳጆቻቸው በቻይናው መንደሪን አይናገርም! ነገር ግን ዐማርኛን ጠልቶ የዐማሮች ድርጅት አለቃ መሆን ከአሥር ሺህ ዓመታት ምናልባት አንዴ የሚገኝ ወርቃማ ዕድል መሆን ያለበት ብፃይ ወዲ ስምዖን ሊያውቀው ይገባል። ግሩም የታሪክ አጋጣሚና ቅንብር - መቼም የማናገኘው የዘመናት ሤራ እውን-ህልማዊ ክንውን። እናም ግና በዚህ ልዩ ቀመር በጣም ተደመምኩ።
መለስ ኤርትራዊ፣ በረከት ኤርትራዊ፣ ስብሃት ኤርትራዊ፣ ጻድቃን (አሁን ከፊት ለፊት ሳይታይ ከኋላ ሥራውን እየሠራ ቢሰለፍም) ኤርትራዊ፣ አያ ዘርፍጤ እንደልቡ ሣሞራ ኤርትራዊ፣ ምን አለፋችሁ ቱባ ቱባው የወያኔ ወሮበላ ሁላ ኤርትራዊ በሆነበት ሁኔታ ማንኛው ኢትዮጵያዊ ባለሥልጣን ነው በኤርትራ ላይ ውጊያ እሚከፍት? እዚያ ማዶ ኤርትራውያን ባለሥልጣናት እዚህ ማዶ ኤርትራውያን ወሮበሎች (ባለሥልጣናት ልል ስል አፌን አንዳች ነገር ያዘኝ) - ምን ዓይነት የታሪክ ዕንቆቅልሽ ነው?
ፕሬዚዳንታችን የተሟረተባቸው ነገር እንደህልም እልም ተቆጥሮ በተሟላ ጤንነት ቢሆኑ ኖሮ የዚህ ዓይነት ቅሌት ውስጥ እንደማንገባ አምናለሁ። ይህችን አጋጣሚ - መታመማቸውን ወይም በሀገር ውስጥ አለመኖራቸውን ተጠቅመው መሆን አለበት ይቺን የቤተሰብ ጨዋታ ለሆነ ዓላማ የፈጠሯት። ሲመለሱ ወይም ባሉበት ሆነው ይታዘቧቸዋል መቼስ። እግራቸው ወጣ ከማለቱ ይህን ዓይነት ሸፍጥ ጥሩ ነው? ያቀባብራል? አሁን በውነቱ ምን የሚያቆራቁስ ነገር ተገኘ? ባገር አማን ከመሬት ተነስቶ መወራከብ አለ እንዴ? ሊያውም ወንድም በወንድም ላይ። እርግጥ ነው የጭቁን ተራ ወታደሮች ሞት ዝምድናን ላያጠይም ይችል ይሆናል። ሰባ ሺህ ዜጎች አልቀውም ግንኙነታቸው አልተቋረጠም። በኤርትራ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የመለስን የንግድ ድርጅቶች … አይ ይህስ ለዛሬ ይቅር። ደግሞም ገና ያላበሰልኩት ጥሬ መረጃ ነው ያለኝ። ግን ”ጠርጥር ገንፎም አለው ስንጥር ነው” ነገሩ። የምታውቁ ብትቀድሙኝ ቅያሜ አይኖረኝም። ቢበቃኝስ …



