የተከበረው ፍ/ቤት ጥር 15/2004 እኔን 7ኛ ተከሳሽ እስክንድር ነጋን አስመልክቶ የሰጠው ብይን በ3 ይከፈላል። እነዚህም፡-
1ኛ. የአመፅ ተግባርን ለመፈፀም ከሚንቀሳቀሱ የሀገር ውስጥ ፓርቲ አመራሮች ጋር ስለጉዳዩ ተደጋጋሚ ስብሰባ ያደረግኩ መሆኔን፤
2ኛ. የተከበረው ፍ/ቤት የግንቦት 7 ልሳን ነው ብሎ ለጠረጠረው የኢትዮጵያ ሣተላይት ቴሌቪዥን የተለያዩ መረጃዎች የሰጠኹ መሆኔን፤
3ኛ. ሁከትን የሚቀሰቅሱ ፅሁፎችን የፃፍኩና ያሰራጨኹ መሆኔን የሚያስረዱ መረጃዎች እንደቀረቡብኝ የተከበረው ፍ/ቤት በይኗል።
‹‹የአመፅ ተግባርን ለመፈፀም ከሚንቀሳቀሱ የሀገር ውስጥ ፓርቲ አመራሮች ጋር ስለጉዳዩ ተደጋጋሚ ስብሰባ አድርጓል›› ከተባልኹት ልጀምር


ስብሰባዎቹን ከመቃኘቴ በፊት ግን፣ ስብሰባዎቹ ሲደረጉ አጥሎ ስለነበረው ድባብ ለተከበረው ፍ/ቤት ግንዛቤ ማስጨበጥ የግድ ይላል፡ ፡ ድባቡ በስብሰባዎቹ ይዘት፣ ዓላማና ግብ ላይ ቀጥተኛ አንድምታና ተፅዕኖ ነበረውና።


ምንም እንኳን እንደ አንድ ለነፃነቱ ትልቅ ዋጋ እንደሚሰጥ ጋዜጠኛ ከመንግሥት ጋር ያለኝ ተቃርኖ ብዙ ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም፤ በየካቲት 2003 ዓ.ም. በግብፅ እንደድንገት ስኬት ለመሆን በበቃው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ህዝባዊ ለውጥ የተደናገጠው የኢትዮጵያ መንግስት ‹‹እርምጃ እንወስድብሃለን›› ብሎ እንዲዝትብኝም ምክንያት ሆነ። ቀደም ባሉት 4 ሳምንታት፣ ማለትም በወረሃ-ጥር ዓለምን አስደምሞ ስለነበረውና በግብፅ ለተቀጣጠለው ህዝባዊ ተቃውሞ አርአያ የነበረው የቱኒዚያ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን አስተያየት ስሰጥና ስተነትን፣ በጋዜጦችና በኢንተርኔት ደግሞ ፅሁፎች ሳቀርብ ሰነባብቼ ነበር።


እውነቱን ለመናገር፣ በአረብ ሀገራት እንዳየነው ዓይነት ፈጣን፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሂደት በሀገሬም ማየት እንደምሻ በቀጥታ አልናገር እንጂ፣ ልቤም አእምሮዬም በአዲሱ ክስተት ተሸንፎና ተማርኮ እንደነበር መደበቅ አልሻም። ከሚያውቀኝ ህዝብና መንግሥትም የተሰወረ አልነበረም። ማስጠንቀቂያ ያሰጠኝም ይህ እውነታ ነበር። ‹‹ኢትዮጵያ ሰላማዊ የሆነ የዴሞክራሲ ሽግግርና ለውጥ ያስፈልጋታል›› ብዬ ያኔም ሆነ ዛሬ ከልብ አምናለኹ። ሂደቱን ጠብቆ ለተከበረው ፍርድ ቤት እንደማስረዳውም ይህ እምነት የእኔ ብቻ ሳይሆን የብዙሃኑ ኢትዮጵያዊያንም እንደሆነ በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ በተግባር ለማሳየት የጀመርኹት እንቅስቃሴ፣ ውሎ አድሮ ‹‹የማይቆረጠም ባቄላ›› እንዳይሆን በኢህአዴግ በእንጭጩ ተቀጭቶ፣ የህሊና እስረኛ ለመሆን አብቅቶኛል።

 

ለማንኛውም፣ በወረሃ-የካቲት 2003 ዓ.ም. ፒያሳ ከሚገኝ አንድ የኢንተርኔት ቤት በር ላይ በፌደራል ፖሊስ አባላት ተይዤ በመንግሥት የተሰጠኝን ማስጠንቀቂያ በሚመለከት፣ በወቅቱ ለንባብ አብቅቼው ከነበረው ባለ2 ክፍል መጣጥፍ የመጀመሪያውን ክፍል አቃቤ ህግ ለፍርድ ቤቱ አቅርቦታል፤ ምን እንደሚያስረዳለት ለእኔ ግልፅ ባይሆንም። ለፍርድ ቤቱም ያስረዳው ነገር የለም። በእኔ በኩል ግን፣ አሁን ከሳሼ ሆኖ የቆመው መንግሥት ሲዝትብኝና ሲያስፈራራኝ እንደነበር ያረጋግጥልኛል። ይህን ነው በዚህ ክስ ላይ ያጠላው ድባብ የምለው፡፡ የተመሰረተብኝ ክስ ግልፅ የሆነ መነሻ አለው።


መቋጫው እዚህ ፍ/ቤት አድርሶኛል። የመጣጥፉ ርዕስ ‹‹ጄኔራል ጻድቃን፣ ኢህአዴግና የሰሜን አፍሪቃ አብዮት›› የሚል ነው። የተከበረው ፍ/ቤት በአፅንኦት እንዲያነበው አሳስባለኹ።
የተመሰረተብኝ ክስ በሐሰት የተቀነባበረና የበቀል ግብ እንዳለው ግልፅ ቢሆንም፣ የተከበረው ፍ/ቤት ከሀገር ውስጥ ፓርቲ አመራሮች ጋር ስላደረግኳቸው ስብሰባዎች እናድከላከል ባዘዘው መሰረት በክሱ ውስጥ የተካተቱትን 3 ስብሰባዎች በአጭር በአጭሩ እቃኛቸዋለኹ።

 

1ኛ. በአንድነት ጽ/ቤት ስለተካሄደው ስብሰባ

ነሐሴ 29 2003 ዓ.ም. በአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ጽ/ቤት ተደርጎ የነበረውን ህዝባዊ ስብሰባ አቃቤ ህግ ለተከበረው ፍ/ቤት በማስረጃነት አቅርቦታል፡፡ እንደ አቃቤ ሕግ አቀራረብ ከሆነ፣ ስብሰባው በህብዑ የተደረገ፣ የአመፅ ቅስቀሳ የተጧጧፈበትና ተሰብሳቢዎቹ ህገ- ወጥ ተግባር ለመፈፀም ያሴሩበትና የተስማሙበት መድረክ ነበር፡፡


በዚህ ክስ ሂደት አስደማሚ ከነበሩት ክስተቶች መካከል ይህን ህዝባዊ ስብሰባ ‹‹ህብዑ ነበር›› በማለት አቃቤ ህግ የተከራከረው ነው፡፡ እንዳልነበር ግን አሳምሮ ያውቃል፡፡ ምርመራውን ያጣራው ፌደራል ፖሊስ የሚያውቀውን ሐቅ አቃቤ ሕግ አያውቅም ተብሎ ሊጠረጠር አይችልም፡፡


ይጠርጠር ከተባለም የአቃቤ ህግን ሙያዊ ብቃት ጥያቄ ውስጥ የሚከት ከመሆን አያልፍም፡፡ ችግሩ ግን የአቃቤ ህግ ሙያዊ ብቃት አይደለም፡፡ ፖለቲካው ጣልቃ እየገባ ወደማይፈልጉት አቅጣጫ ባይመራቸው ኖሮ፣ አቃቤ ህጋን ማህበረሰባቸውንም ሆነ ሀገራቸውን በብቃት ማገልገል የሚችሉ ናቸው፡፡ ሆኖም፣ በባዶ እጅ ክስ እንዲመሰርቱ ሲገደዱ የሌለን ያለ አስመስለው ከማቅረብ ውጭ አማራጭ የላቸውም፡፡ ይህንን ነው በዚህ ክስ ውስጥ በድግግሞሽ የምንታዘበው፡፡


ለማንኛቸውም፣ ህዝባዊ ስብሰባው ህጋዊ እንደነበር፣ በህብዑ ሳይሆን በሚዲያ ጥሪ ተደርጐ የተከናወነ እንደነበርና ምንም ዓይነት የአመፅ ቅስቀሳ እንዳልተደረገበት በማያሻማ ሁኔታ የሚያስረዱ የፅሁፍና የቪዲዮ ማስረጃዎች ለተከበረው ፍ/ ቤት አቅርበናል፡፡ በዚህ ብቻ ግን አላበቃንም፡፡ ከሚያስፈልገው በላይ ቢሆንም፣ ዛሬና ነገ ደግሞ በሰው ማስረጃዎች ይበልጥ እናጠናክራቸዋለን፡፡


የተከበረው ፍ/ቤት ጠንቅቆ እንደሚረዳው፣ መሰብሰብ ህገ-መንግስታዊ መብት ነው፡፡ ከዚያም አልፎ በህገ መንግስታዊ ድንጋጌ እውቅና አገኘም አላገኘም ተፈጥሯዊ መብትም ነው፡፡ እነዚህ እውነታዎች ግን ከምርጫ 97 በኋላ በአብዛኛው ተጥሰው ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያም የመሰብሰብ መብት በወረቀት ላይ እንጂ በተግባር የማይከበርባት ሀገር ሆናለች፡፡ አንድነት ፓርቲ ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ ፅሁፍ እንዳቀርብ ስጋበዝ ምንም ሳላቅማማ የተቀበልኹት፣ ይህ መብት ምንም ሳይሸራረፍ ሊከበር ይገባዋል ብዬ ስለማምን ነው፡፡ ባለኝ አቅም ህዝብ ተሰባስቦ በሰላማዊ መንገድ ስለሀገሩ ጉዳይ እንዲመክር ለማበረታት አስቤ ያደረግኹት ነበር፡ ፡ ይህ መብት እንዲከበር መታገል ሁሉም ዜጐች ላይ የተጣለ ኃላፊነት ነው፤ ይህንን የተከበረ ፍ/ ቤት ጨምሮ፡፡ በዚህም መሰረት የተከበረው ፍ/ ቤት በዚህ ስብሰባ ዙሪያ የቀረበውን ፍሬከርሲ ክስ ሁሉ ውድቅ በማድረግ ለዜጐች ተፈጥሯዊና ህገ- መንግስታዊ መብት መከበር የፍርድ ቤቶችን ከለላና ጥበቃ የመስጠት አደራና ኃላፊነት አለበት፡፡ ብይኑን ታሪክና ህዝብ በጉጉት ይጠብቁታል፡፡


2ኛ. ከመኢዴፓ አመራር አባላት ጋር ስላደረግዃቸው ስብሰባዎች


የተመሰረተብኝ ክስ አስቂኝና አዝናኝ ምዕራፍ ደግሞ በአንድ በኩል እኔ፣ በሌላ በኩል መኢዴፓ፣ በሌላው ጫፍ ደግሞ ግንቦት 7 የተሳሰርንበት ልብ-ወለድ ትረካ ነው፡፡ በዚህ ልብ- ወለድ ትረካ ግንቦት 7 በዋና ተዋናይነት መመሪያ አውራጃ ሆኖ ቀርቧል፡፡ ድጋፍ ሰጪ ተዋናያንና መመሪያ ተቀባዮች ደግሞ እኔና መኢዴፓ ሆነን ተስለናል፡፡ አስቂኙ ተግባር፣ ድርሰት ፀሃፊዎቹ ወደ ዝርዝር ትረካቸው ገና ከመግባታቸው መነሻ ሃሳባቸውን አፈራርሰውት ማረፋቸው ነው፡፡


እንደልብ-ወለዱ ትርክት ከሆነ እኔና መኢዴፓ በግንቦት 7 የተሰጠንን ተልዕኮ ለማሳካት መጀመሪያ በአንድነት ጽ/ቤት በተደረገው ህዝባዊ ስብሰባ፣ በቀጣይነት ደግሞ በጣይቱ ሆቴል እየተገናኘን እንመክርና እናሴር ነበር፡፡ ዛሬ በቪዲዮ ማስረጃ ለተከበረው ፍ/ቤት እንደምናሳየው፣ ትራጂ-ኮሜዲው የሚጀምረው አንድነት ጽ/ቤት በተደረገው ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ነው፡፡ የግንቦት 7 ወኪልና የመኢዴፓ አመራር አባል ነው የተባለው አበበ ቀስቶ፣ በመስከረም ወር በመስቀል አደባባይ እንዲደረግ በታቀደ ህጋዊ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ተሰብሳቢ እንዲካፈል ጥሪ ያቀርባል፡፡ የስብሰባው ተካፋይ የሆነኹት ሌላኛው የግንቦት 7 ወኪል የተባልኹት እኔ ደግሞ፣ ሰላማዊ ሰልፍ መደረግ የለበትም ብዬ ተቃውሞ በማቅረብ የተሰበሳቢውን ልብ እከፍላለኹ፡፡ አስቂኝም-አዝናኝም ነው፡፡ ወይ ግንቦት ሰባቶች በአስቂኝና አዝናኝ ደረጃ ዝርክርኮች ናቸው፣ ወይ ደግሞ ልብ-ወለድ ትረካው በጀማሪዎች ተቀናብሯል ማለት ነው፡፡


ትራጀ-ኮሜዲው በጣይቱ ሆቴልም ይቀጥላል፡፡ የአቃቤ ህግ ምስክርና የመኢዴፓ መሪ የሆኑት አቶ ዘመኑ ሞላ በዚህ ፍ/ቤት ተገኝተው እንደመሰከሩት፣ በጣይቱ ሆቴል ባደረግነው ውይይት ‹‹ከኢትዮጵያ ውጭ የሚላክ ገንዘብ አትቀበሉ›› ብዬ ምክር ሰጥቻለሁ፡፡ በልብ-ወለዱ ግን ግንቦት 7 ገንዘብ ላኪ ወይም ፋይናንስ ሆኖ ቀርቧል፡፡ እዚያው ጣይቱ ሆቴል መኢዴፓዎች ‹‹ሰልፍ እናደርጋለን›› ሲሉ፣ እኔ ‹‹ተው›› እላላኹ፡ ፡ በዚህ አስቂኝ ትረካ፣ ግንቦት 7 በአንድ እጁ የሚገነባውን በሌላኛው እጁ ያፈርሳል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት አስቂኝ ድራማ የተጠመደ ድርጅት የልጆች እንጂ ፈፅሞ የአዋቂዎች ስብስብ ሊሆን አይችልም፡፡ በፀረ-ሽብርተኝነትም ለመከሰስ ብቃት የለውም፡፡ ይሄ ጉድ ተይዞ ነው የተከበረው ፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ እንዲያስተላልፍብኝ የሚጠብቀው፡፡


3ኛ. በመቋቋም ላይ የነበረው የሲቪክ ተቋም


ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊያን ሰላማዊ ለውጥ እንደሚፈልጉ በተግባር መታየት አለበት ብለን የምናምን 7 ኢትዮጵያዊያን ተሰባስበን ኮሚቴ አቋቁመን ነበር፡፡ ህቡዑ ድርጅት የተቋቋመ በማስመሰል የዚህን ኮሚቴ አንድ ቃለ-ጉባዔ አቃቤ ህግ በማስረጃነት አቅርቦታል፡ ፡ ይህ ኮሚቴ በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ ብቻ የሚንቀሳቀስ እንዲሆን በመስማማት ቃለ-ጉባኤ ይዘን በመፈራረም ይፋዊ እንቅስቃሴ ለመጀመር ተዘጋጅተን ነበር፡፡ ይህን የሚገልፀው ቃለ-ጉባዔ ለፍርድ ቤቱ አይቅረብ እንጂ፣ መኖሪያ ቤቴ ውስጥ በፍተሻ ተገኝቶ በኤግዚብትነት ተመዝግቦ በፖሊስ እጅ ይገኛል፡፡ ቃለ-ጉባዔው በሁለት ኦርጅናሎች ተዘጋጅቶ የተቀመጠ በመሆኑም፣ ሁለተኛውን ኮፒ ለተከበረው ፍ/ቤት በፅሁፍ ማስረጃነት አቅርበናል፡ ፡ ኮሚቴው ፍፁም ህጋዊና ሰላማዊ መሆኑን መንግሥት በመተማመኑም ከእኔ ውጭ ያሉት አባላት ለእስር አልተዳደረጉም፡፡ ከስድስቱ መካከል 2ቱ ዛሬ በሰው ማስረጃነት ቀርበው የነበረውን ሂደት ለተከበረው ፍርድ ቤት ያስረዳሉ፡፡
እዚህ ላይ ቢሆንም፣ አቃቤ ህግ የሌለን ነገር ያለ አስመስሎ ለማቅረብ የተገደደው፣ ‹‹የተቸገረ እርጉዝ ያገባል›› እንዳሉት፣ በእጁ ላይ ምንም ተጨባጭ ማስረጃ ስለሌለ መሆኑን ፍ/ቤቱ ልብ ሊለው ይገባል፡፡


4ኛ. ከኢትዮጵያ ሣተላይት ቴሌቪዥን ጋር አለህ ስለተባልኹት ግንኙነት


የተከበረው ፍርድ ቤት በሰጠው ብይን፣ የግንቦት 7 ልሣን ነው ብሎ ለጠረጠረው ኢሣት የተለያዩ መረጃዎችን መስጠቴን በአቃቤ ህግ ማስረጃ መረጋገጡን አትቷል፡፡ አቃቤ ህግ ባቀረባቸው ማስረጃዎች ውስጥ ግን አንድም ቦታ ላይ እኔና ኢሣት ቴሌቪዥንን የሚያገናኝ ማስረጃ ማቅረቡን አልገለፀም፡፡ በሌላ በኩል ግን፣ ከኢሣት ሬዲዮ ጋር ቃለ-ምልልስ አድርጓል በሚል ከአበበ በለው ጋር ያደረግሁት ቃለምልልስ በማስረጃነት ቀርቧል፡፡ የተከበረው ፍ/ቤት ለኢሣት ቴሌቪዥን የተለያዩ መረጃዎች እንደሰጠሁ አድርጐ የተረዳው፣ የኢሣት የቦርድ አባል ከሆነው አበባ በለው ጋር ያደረግሁትን የተለያዩ ቃለ-ምልልሶች አጣቅሶ ነው ብዬ እገምታለሁ፡፡


ኢሣት በቀጥታ የግንቦት 7 ልሣን ነው ተብሎ መገመቱ ስህተት ነው ብዬ አምናለኹ፡፡ ይህንን ስል፣ የግንቦት 7 አባላት በኢሣት ዝግጅት ክፍልም ሆነ በቦርድ አባላት የሉም ብዬ መከራከሬ አይደለም፤ እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ብዙሃኑ የኢሣት ዝግጅት ክፍልና ቦርድ አባላት ግን የግንቦት 7 አባላት እንዳልሆኑ ጠንካራ እምነት አለኝ፡፡ ለምሳሌ ከቦርድ አባላቱ መካከል በግል የማውቃቸውና የማከብራቸው ወዳጆቼ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም፣ ታማኝ በየነ፣ አበበ ገላው፣ አበበ በለው፣ ሉሊት መስፍንና ለጊዜው የማላስታውሳቸው ሌሎችም የግንቦት 7 አባላት እንዳልሆኑ አውቃለሁ፣ እመሰክራለኹም፡፡ ከሙህራዊ ብቃታቸውና Integrity አኳያም ግንቦት ሰባትም ሆነ ሌላ ማንኛቸውም ድርጅት ከኋላ ሆኖ በዘፈቀደ የሚያሽከረክራቸውና የሚጠመዝዛቸው ሰዎች አይደሉም።


ግንቦት 7 የተባለው ድርጅት ‹‹የግንቦት 7 ድምጽ›› የሚባል ልሣን አለው፡፡ በኢንተርኔት የሚሠራጭ ጋዜጣ ነው፡፡ ‹‹የግንቦት 7 ድምፅ›› የሚባልም ሬዲዮ ጣቢያ አለው፡፡ ከሬዲዮና ከጋዜጣው ባሻገር ቴሌቪዥን ካለውም ‹‹የግንቦት 7 ድምፅ›› ብሎ የማይሰይምበት ምክንያት አይታየኝም፡፡ እንዲያውም፣ ነገሮቹ የፖለቲካ ድርጅቶች ባላደረጉት ደረጃ አዲስ የተቋቋመው ግንቦት 7 የቴሌቪዥን ጣቢያ ባለቤት ለመሆን ከበቃ፣ ግርማ ሞገሱንም ሆነ ተሰሚነቱን የሚያጐላለት በመሆኑ እንዲታወቅለት እንጂ እንዳይታወቅበት የሚፈልግበት ምክንያት ግልፅ አይደለም፡፡


ለማንኛቸውም፣ ለተከበረው ፍ/ቤት ግንዛቤ የኢሣትን ቻርተር በፅሁፍ ማስረጃነት አያይዘነዋል፡፡ ቻርተሩ እንደሚገልፀው ከሆነ፣ ቴሌቪዥን ጣቢያው ከማንኛቸውም የፖለቲካ ድርጅት ጋር ያልወገነ ነፃ ተቋም ነው።


በዚህ ክስ ውስጥ እስከተገለፀበት ጊዜ ድረስ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ኢሣት የግንቦት 7 ልሣን መሆኑን አንድም ጊዜ ተናግሮ አያውቅም፡፡ በዚህም ሳቢያ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በህጋዊና በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች፣ ጋዜጠኞችና ሙህራን ከኢሣት ጋር ተደጋጋሚ ቃለ-ምልልሶች እንዳደረጉ ሀገር የሚያውቀው ሐቅ በመሆኑ፣ ማስረጃ ማቅረብ የሚያስፈልገኝ አይመስለኝም፡፡ የተከበረው ፍ/ቤት በjudicial notice ግምት ውስጥ ሊያስገባው ይችላል። ፍሬ ነገሩ፣ ከኢሣት ቴሌቪዥን ጋር ቃለ-መጠይቅ ማድረግ ከግንቦት 7 ጋር መወገን ወይም ማሴር ነበር ብሎ መደምደም የሚቻልበት Context አልነበረም፡፡ ይህን ስል ግን፣ በኢሣት ውስጥ ያሉት የፖለቲካ ድርጅት አባላት ሚና ሊያሳስበን አይገባም ማለት አይደለም፡፡ ኢሣት ነፃ ተቋም ነኝ እስካለ ድረስ፣ ሊያነጋግረንም ሊያሳስበንም ይገባል። የውይይት መድረኩ ግን ከቶ ፍርድ ቤቶች ሊሆኑ አይገባም።


በመጨረሻም፣ ከአበበ በለው ጋር ስላለኝ ግንኙነት ልናገር፡፡ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቐሺ ገብሩ በሚል ርዕስ የተላለፈ ዶክመንተሪ ፊልም ነበር፡፡ ዋና ማጠንጠኛ የሆነችው ታጋይ በደርግ እጅ ወድቃ ቃለ-ምልልስ ሲደረግላት፣ ‹‹የመንግሥትን ሬዲዮ እንዳናምን ያደረገን የትግራይ ገበሬ በሕወሓት እየተገደደ ለጦርነት ይማገዳል የምትሉት ነው›› ብላ ነበር፡፡ መላ የትግሬ ገበሬ እውነት አለመሆኑን ያውቅ ነበርና፡፡ በተመሳሳይ መንገድም፣ በዚህ ክስ አበበ በለው፣ አበበ ገላው፣ ኦባንግ ሜቶን የመሳሰሉ ታዋቂ ግለሰቦች የግቦት 7 አመራር አባላት ናቸው ተብለው መፈረጃቸው በዲያስፖራውና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ክሱን፣ ሂደቱንና በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ፍትህ ሥርዓት ተአማኒነት የሚያሳጣ ነው፡፡ እንዳልሆኑ ቢያንስ ቢያንስ መላው ዲያስፖራ ያውቃልና፡፡ ከአበበ በለው ጋር ያደረግዃቸው ቃለ- ምልልሶች ሙሉ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ባለ የኤፍ ኤም (በእነሱ ኤ.ኤም) ሬዲዮ ጣቢያ ላይ የተላለፈ ነው፡፡

በሬዲዮ ጣቢያው የሚተላለፈው የአማርኛ ቋንቋ ፕሮግራም ግንቦት ሰባትም ሆነ ኢሣት ከመቋቋማቸው በፊት የነበረ ነው፡፡ መንግስትም ጠንቅቆ የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱን ሆን ተብሎ ለማሳሳት እየተሞከረ የሚገኘው፣ ለቀረበብኝ የፈጠራ ክስ ተጨባጭ ማስረጃ ማቅረብ ስለማይቻል ብቻ መሆኑን ለተከበረው ፍ/ቤትም ሆነ ለማንኛውም ገለልተኛ ተመልካች ሊሰወር አይችልም፡፡


5ኛ. ሁከትን የሚቀሰቅሱ ጽሁፎችን የፃፈና ያሰራጨ ስለተባልኹት


አቃቤ ህግ ያቀረበብኝ የፅሁፍ ማስረጃዎች ሲቃኙ፣ በጋዜጣና በኢንተርኔት የወጡ 6 መጣጥፎች፣ በሀገር ውስጥ ከሚታተሙ ጋዜጦች ጋር ያደረግዃቸው 2 ቃለ-ምልልሶች፣ በአሜሪካ፣ በካናዳና በስዊድን ሀገራት ካሉ ሬዲዮ ጣቢያዎችና ፓልቶኮች ጋር ያደረግዃቸው ቃለ-ምልልሶች ተካተዋል፡፡ በተጨማሪም እንዴት እንደሚመለከተኝ ግልፅ ባይሆንልኝም፣ ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ በስዊድን ሀገር ያደረጉት ንግግርና ይልማ በቀለ የተባሉ ኢትዮጵያዊ ምሁር ያወጡት አንድ መጣጥፍም በማስረጃነት ተቆጥረውብኛል፡፡


እነዚህን ሁሉ በዝርዝር መቃኘት አስፈላጊ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሆኖም፣ For the record በስሜ የወጡት መጣጥፎችና የሰጠኋቸው ቃለ-ምልልሶች የእኔ የሆኑና እስካሁን ድረስ ያለምንም ማሻሻያና መሸራረፍ ሙሉ ለሙሉ የማምንባቸው ናቸው፡፡ ዓላማቸው ብጥብጥ ማስነሳት አልነበረም፡፡ በሀገራችን የህልውና ጉዳይ የሆነውን ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እንዲኖር የሚመክሩ፣ የሚማፀኑ፣ የሚገስፁ፣ የሚለምኑና መንገዱን የሚጠቁሙ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የአውራ ፓርቲ ግንባታ ሙከራ በሀገሪቷ አንድነት ቁማር መጫወት ነው፡፡ እንደአንድ ለሀገሩና ለህዝቡ የሚቆረቆር ዜጋና ጋዜጠኛ ድምፄን የማሰማት ኃላፊነት ነበረብኝ፤ ኃላፊነቴንም ተወጥቻለኹ፡፡ ከዚህ በኋላ ከእኔ የሚጠበቀው የምከፍለው ዋጋ ካለ በፀጋ መቀበል ብቻ ነው።


ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ አንድነትና ፍቅር ለሀገሬና ለህዝቧ እመኛለሁ።


አመሰግናለሁ።

ከፍትህ ጋዜጣ የተወሰደ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ