ነጻነት ዘገዬ

ባልና ሚስት ነበሩ። ሚስት ጣም እልኸኛ ናት። ባልዬው ታጋሽ ነው። እርሱዋ ሁል ጊዜ ተቃራኒ ናት። ባልዬው እንብላ ሲላት እስዋ እንሂድ ትላለች፤ እንሂድ ሲላት እንቀመጥ ትላለች፤ በዚህ መልክ እየተዳረቁ ይኖራሉ - ኑሮ ካሉት መቃብርም እንደመሞቁ። በአንድ አጋጣሚ አሳድሩኝ ባይ አንድ የወንድ እንግዳ ወደቤታቸው ይመጣል። ይሄኔ የሚስቱን ጠባይ የዘነጋ ባል ምን ይላል፤ ‹እኔና እንግዶ መደቡ ላይ እንተኛለን፤ አንቺ ከልጆችሽ ጋር እግገኑ ላይ (የገጠር ቤት ሣሎን ማለት ነው) አንጥፋችሁ ተኙ›። ሚስት ሆይት ባል ተናግሮ ሳይጨርስ ካፉ ቀለብ ታደርግና ‹ እንዴት ተደርጎ? ሞኝህን ፈልግ! አንተና ልጆችህ እግገኑ ላይ እኔና እንግዶ እመደቡ ላይ ነው እምንተኛ› ትልና ዘራፍ ትላለች።

 

በዚህ መልክ ትዳሩም ትዳር ሳይሆን እንደኛው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት እንዲሁ እንደተምበጫረቀ ጥቂት ዓመታትን ይዘልቁና ሞት መቼም ለማንም አይቀርም ሴትዮዋ ውሃ ልትቀዳ ወንዝ በወረደችበት አጋጣሚ በዚያው ጎርፍ ይዟት ጥርግ ይልና ትሞታለች። መንደርተኛው ሁሉ ታዲያ ተጠራርቶ ሬሣዋን በመፈለግ ላይ እንዳለ ባልዮው ሁሉም እንዲያዳምጠው ድምጹን ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ይናገራል፤‹ ወንድሞቼና እህቶቼ አድምጡኝማ አንደዜ! ሚስቴ ነገረ ሥራዋ ከሰው ስለማይገጥምና ሁለ ነገሯም ተቃራኒ ስለሆነ ከወንዙ ወደላይ እንጂ ከወንዙ ወደታች እንዳትፈልጓት፤ የርስዋ ነገር የተገላቢጦሽ ስለሆነ ጎርፉም ወደታች ሳይሆን ወደላይ ነው ይዟት እሚሄድ› አለና በሀዘን መሀል ሕዝቡን አስፈገጋቸው ይባላል። እንዲህ ያለ እልኸኛ መንግሥት ማለቴ ባል ወይ ሚስት (ሰው) አያጋጥማችሁ። በእውነት እኮ አይጣል ነው፤ ሚስትና ባልንስ በፍቺ ትገላገይዋለሽ - የወያኔን ዓይነት የጅል ፍቅር በምን ይገላገሉታል? በግድ እወዳችኋለሁ ብሎ ሩብ ክፍለ ዘመን ያህል ሀገርና ሕዝብ ጫንቃ ላይ ቁጢጥ? ‹የሞኝ ፍቅር ሆድ ይገትር› አሉ?

 

ኤፍሬም ማዴቦ ሰሞኑን “Get out, you don’t belong here” በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ ያወጣውን ጽሑፍ በጉጉትና ቶሎ እንዳያልቅብኝ በስስት ነው ያነበብኩት። እጁን ቁርጥማት አይንካብኝ። ‹ሰው ማለት ሰው እሚሆን ነው ሰው የጠፋ ዕለት› ሲል የሰማሁት መሰለኝ ደበበ እሸቱን - በአንድ ቀደም ባለ ወቅት የተደመጠ ማስታወቂያ ላይ። አዎ፣ ኤፍሬም በማለፊያ ቋንቋ ክሽን አድርጎ ያቀረበውን መጣጥፍ ያነበብን ብዙ ተምረንበታል። ግን ‹በጥባጭ ሳለ ማን ጥሩ ይጠጣል› እንደሚባለው የአእምሮ ስንኩላንና በጥቅምና በዓላማ ቁርኝት ወይም በጎጠኝነትና በዘረኝነት ልክፍት ወይም በድንቁርናና በማይምነት ፈውስ የለሽ ደዌ ወይም ከነዚህና ከሌሎችም መሰል አሉታዊ አመለካከቶችና ሥነ ልቦናዊ ህመሞች የተነሳ እንደጋሪ ፈረስ ዐይናቸው ሌላ ነገር እንዳያይ የተጋረደባቸው ወገኖች ይህን ወርቅ ጽሑፍ ሲያብጠለጥሉ ማየት በጣሙን ያሳዝናል። ለርሱ ምስጋናየን፣ ለአእምሮ ድኩማኑ እርግማኔን ላስተላልፍ ነው እንግዲህ አሁን ብዕር ያነሳሁት። አንዴውን ሲኸለቅ ተወላግዶ የተፈጠረ አእምሮን ማስተማርና ማቃናት የማይቻል ወይም የሚከብድ መሆኑ ቢታወቅም ቢያንስ እንደዚህ ዓይነቶች በእናታቸው ማኀፀን ውስጥ ውሃ ሆነው ቢቀሩ የሚሻላቸው ወገኖች ሌላን ሰው እንዳይበክሉና ንፍጣቸውን እንዳይለቀልቁ መከላከል ከሁላችን ይጠበቃል - በተለይ ከድረ ገፆች ማኅበረሰብ አካባቢ። አንድ ሰው ጥሩ ነገር ሲያደርግ ያን ሰው ከማመስገንና ‹ይበል ነው፤ ይልመድብህ፤ ቢስ ዐይይህ› ከማለት ይልቅ ማሳደድ ባህላችን ሆኖ የዘለቀ ቢሆንም አሁንና ከአሁን ወዲያ ግን እየመረረንም ቢሆን ይህን መጥፎ ነቀርሣ ማስወገድ ባሕርያችንንም ማሻሻል ይኖርብናል። በስድብና በዘለፋ የእንካስላንትያ ውርጅብኝ እየተወራወሩ መኖር ይብቃን፤ ያንዳችን ደግ ሥራ ለሌላኛችን የኀልውና ሥጋት ሆኖ እንዲታየን የሚያደርገን አባዜና ፀላኤ ሠናያት ሊወገድ ወቅቱ ግድ ይለናል። በመናቆርና በከንቱ በመተቻቸት ያጠፋናቸው በርካታ ዓመታት ሊቆጩን ይገባል። እንዳንግባባ በመሀከላችን የተበተነው መስተፃልዕና የድግምት ሥራይ መፍትሔ ሊፈለግለት ይገባል። ባጭሩ ልብ ልንገዛ ይገባል።

 

አንድ ማኀበራዊ እምነት አለ። መቼም ከፍየል ሥጋ ጋር በተገናኘ በማኀበረሰቡ እሚባለውን ነገር አንረሳውም። ፍየል የማትበላው ቅጠል የላትም ይባላል። ከእንስሳት ዝርያ እንኳን እባብን ሳይቀር አናቱን ፈጥፍጣ በመግደል ቅርጥፍ አድርጋ ነው እምትበላ። መርዙ እንዳይጣላት ታዲያ በድብቅ ሮጣ ሄዳ የምትበላው ፀረ የእባብ መርዝ አብነት - ቅጠል - አላት አሉ። የማትበላው ነገር ባለመኖሩ የተነሳ የፍየልን ሥጋ የሚበላ ሰው የሠራ አካሉ እንደሚበረበርና በሽታው ሁሉ እንደሚቀሰቀስበት ስለሚታመን ፍየልን የማይበሉ ብዙ ሰዎች አሉ። ብዙዎች ደግሞ ፍየልን እሚበሉት ከምግብነቷ በተጓዳኝ ሥጋዋ በሚሰጠው የመድሓኒነት መፍትሔ እንደሆነም ይነገራል። ምን ለማለት ፈልጌ መሰላችሁ ፡- አንዳንድ መጣጥፎችና የሚዲያ ዝግጅቶች የፍየል ሥጋ ናቸው ለማለት ያህል ነው። የፍየል ሥጋ የበላተኛውን የሠራ ጅስም እየበረበረ በሽታውን ከተደበቀበት እንደሚቀሰቅስና እንደሚገልጥ ሁሉ(ሊያስጎራም ይችላል - እንደበሽታው ዓይነት) አንዳንድ መጣጥፎችም የወያኔን አጋንንታዊ ደዌ እየቀሰቀሱ ምድረ ወያኔንና ምድረ ጥቅመኛ ቅጥረኛ ባንዳን በተለይ የአስተያየት መስጫ ቦታ ባላቸው ድረ ገፆች ሥር አለመላው እንዲበሻቀጡ ሲያደርጉ እናስተውላለን። እነዚህ የጊዮርጊስን መገበሪያ እየገለበጡ እሚኖሩ ጭንቅላት ብሎ ነገር ያልፈጠረባቸው ዜጎች አንድ ሰው ስለሀገሩ መቆርቆሩን የሚገልጽበት አጋጣሚ ሲፈጠር ደርሰው ቀንድ ቀንዱን ለማለትና ከተቻላቸውም ተስፋ አስቆርጠው ዝም ለማሰኘት የማይቆፍሩት ጉደጓድ የለም - ይግቡበትና፤ እንዴ አላበዙትም እንዴ አሁንስ? እዚህ ላይ የፍየልንና የበግን ተምሣሌታዊ የመጸሐፍ ቅዱስ ትርጓሜን ማስታወስ አይከፋም። (ፍየል የርኩስ መንፈስ ማለትም የሰይጣን፣ በግ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ማለትም የእግዚአብሔር ወልድ የክርስቶስ ተምሣሌቶች ናቸው)

 

ለነገሩ ‹አፍ ሲከፈት ጭንቅላት ይታያል› እንዲሉ ማንነታቸውን ለማወቅ ይቻለን ዘንድ የፈለጉትን ቢቀባጥሩ ምንም ማለት አይደለም፤ የፍየሉ ሥጋ - ግዴለም - ይሆኑትን እያሳጣ ያስቀበጣጥራቸው። ደግሞም ውሻ በበላበት መጮሁ እንግዳ ነገር አይደለም። እናም ዝልበዳቸውን ይቀጥሉና በውጤቱም በወያኔው መንደር ይሾሙ፤ ይሸለሙ። የውሸቱ ንጉሥ ወያኔም በሃሰተኛ ደቀ መዛሙርቱ አማካይነት እጅ እግር የሌለውንና እርስ በርሱ እሚላተም ቱሪናፋውን ይዘላብድ። በነገራችን ላይ ዱሮ ዱሮ ሰዓት ለመሙላት ስንፈልግ ኢቲቪን እየከፈትን እንጠቀም ነበር፤ አሁን ግን ሰዓቱንም በትክክል መናገር አቁመዋል። ‹ፕሮግራሞቻችን ሁሉ ውሸት ከሆኑ ሰዓቱንስ አስተካክለን ብንናገር ማን ያምነናል?› ብለው ይመስለኛል እሱንም ሆን ብለው እሚያሳስቱት፤ እስከ አሥር ደቂቃ እኮ ይደርሳል የሚስቱት። እናም ሙያ በልብ ነውና በውሸቶቻቸው መናደድ አይገባንም፤ ለመዋሸትማ እኔስ እዋሽ የለም? አሁን ማን ይሙት ቢስቱ ቢስቱ አሥር ደቂቃ ይስታሉ? ካለበት የተጋባበት አሉ። በሕይወት ዘመኔ ኢቲቪ እውነት ሲናገር ለመስማት ካበቃኝ ለቁልቢ ገብርኤል አንድ ዣንጥላ፣ ለአንዋር መስጊድ ደግሞ የዣንጥላውን ግምት በጥሬ ገንዘብ እሳላለሁ። አይ ኢቲቪ! እንዲህ መጫወቻ እንደሆነ ይቅር?

 

በውነቱ በነዚህ አስተያየቶች የማይነበብ ዝግንትል የለም። ወተቱን እሚያጠቁሩ፣ ማሩን እሚያመርሩ(ሰሞኑን በአንድ ጦማር ያየሁትና በፊትም እማውቀው አገላለጽ ነው) እውነትን ሽምጥጥ አድርገው እሚክዱ፣ ነጭ ውሸት እሚዘሩ(ይታያችሁ - ወያኔዎች በርሀብና በድርቅ እንዲሁም በማዳበሪያ ዕዳ በነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ የሚንጠራወዝ ገበሬን ‹ሚሊዮኔር ሆነ› እያሉ በድሆች እሚያላግጡ እኮ ናቸው!)፣ ሀፍረት እሚባል ጭራሽ ያልፈጠረባቸው ዐይናቸውን በጨው አጥበው ለመዋሸት የተሠለፉ ኮኬዎችን … ብዙና ብዙ የሚያስደምሙ ስብዕናዎችን በነዚህ አስተያየቶች እናያለን፤ እየሳቅንም እናነባለን(‹ባ›ን ጠበቅ!)። የአንዳንዱ አስተያየትማ ‹ለመሆኑ እንዲህ ያ ሰውም አለ እንዴ?› እስክንል ድረስ የመጻፍና የመነበብ ዕድሉን ስላገኘ ብቻ የሚነፋፈጥብን አለ። ብዙው የወያኔ ውሸታም ‹የፍየል ሥጋው› ገና ሲሸተው የቆዩትንም ሆነ በአዲስ መልክ የተለጠፉትን ጽሑፎች ሳያነብና ለማንበብም ፍላጎት ሳያሳይ ርዕሶችን ብቻ እየተመለከተ ወደአስተያየት መስጫዎች በጥድፊ እሚወርድ፣ የክት የስድብ ቃላትን ከጨለማው የአንጎሉ ክፍል እየመዘረጠ እንዲሁ በሰው ላይ እሚያቀረሽ አለ። ይህን ዓይነቱን ቅርሻታምና ድፍን ቅል ራስ ይዘን ነው እንግዲህ የነጻነቱን አቀበት ተያይዘን እምንገኘው። የእናት ሆድ ዥንጉርጉር አይደል? ግዴለም ይሁን። ምን ቸገረን፤ አይለጠፍብን!

 

ኤፍሬም የዘነጋትን ሴት በመግቢያዬ ገልጫታለሁ። ኤፍሬም በመጣጥፉ ላይ የዘመኑን መንግሥታ‹ኣችን›ን ግራ አጋቢ ጠባይ ሲገልጥ የወያኔዎች ነገረ ሥራ እንደሴትዮዋ በሁሉም ነገር የተገላቢጦሽ መሆኑንና እንዲያውም የምንወደውን እንዲወድልን የምንጠላውን እንደምንወድ አድርገን መግለጽ እንደሚገባን ጠቁሟል። እውነቱን ነው። የወያኔ ተፈጥሮ መቃወም ብቻ ስለሆነ በተለይ የሚጠላቸው ወገኖች የሚሉትን ሁሉ በጅምላ እንደተቃወመ ዕድሜውን ፈጀ። እንደግርምቢጧ ሴትዮ ወደላይ ሲሉት ወደታች፣ ወደቀኝ ሲሉት ወደግራ እንዳለና ለገላጋይ እንዳስቸገረ ይሄውና ከሦስት አሠርት ዓመታት በላይ ላይመለሱ የኋሊት ነጎዱ። ከእኛና ከሀገራችን ወርቃማ ዕድሜም ያንኑ ያህል ዘመን በከንቱ ጋዬ። አሁንና ወደፊትስ? የኛ ጉዳይ ነው። የወያኔ ጉዳይ እስካመቸው ድረስ እየዋሸና እየቀጠፈ ይህን ግፈኛ አገዛዙን በተቻለው መጠን ማቆየት ነው። እኛ በአወንታዊ መልኩ ከተለወጥን ግን ዘመኑን የሁላችን ማድረግ እንችላለን - የወያኔውም ጭምር። በአንድነት ስንበረታ ጠላት ይፈራናል፤ በየተናጠል ስንልፈሰፈስ ጠላት መጫወቻው እንዳደረግን ይዘልቃል። የኛ በጎራዎች ተቧድኖ መቆራቆስ ለወያኔ ሠርግና ምላሽ ነው።

 

የፍየል ሥጋ ከተነሣ አይቀር ጥቂት ልበልና ላብቃ። ግንቦት ሰባት የፍየል ሥጋ ነው። ኢሕአፓ የፍየል ሥጋ ነው። ኦነግ የፍየል ሥጋ ነው። ኢትዮጵያውያን ድረ ገፆች የፍየል ሥጋ ናቸው። መኢአድ የፍየል ሥጋ ነው። አንድነት የፍየል ሥጋ ነው። እነዚህ የፍየል ሥጋዎች ወያኔን በምናባዊ ፍርሀት እሚያምበጨብጩ የፍየል ሥጋዎች ናቸው። ትልቁ ክፋት እነዚህ በስም የተጠቀሱና ያልተጠቀሱ የፍየል ሥጋዎች ለወያኔ ብቻ ሳይሆን አንዳቸው ለአንዳቸውም (እርስ በርስ) የፍየል ሥጋ መሆናቸው ነው። ወይ ነዶ! ይህ ሁሉ በውጪም በውስጥም ያለ ኃይል ያለውን የገንዘብ የዕውቀት የልምድና ችሎታ በጠቅላላው ሁሉም አቅሙ እሚፈቅድለትን እምቅ ጉልበት አሰባስቦ - ትዕቢትንና ትምክህትን አስወግዶ መከባበርንና መተማመንን ፈጥሮ -ከኢትዮጵያዊ የቆዬ የምቀንነት ይትበሃል ነጻ ወጥቶ ለእውነተኛ ሕዝባዊ ዓላማ ቢሰለፍ እኮ እውነቱን ለመናገር ነጻነታችን ከተረጋገጠ በጥቂቱ የሃያ አንድ ዓመታት ወርቃማ ጊዜ ሊያልፍ በቻለ ነበር። ግን አንዱ ለአንዱ የበግ ሥጋ ከመሆን ይልቅ የፍየልና የአህያ ሥጋ እየሆነ ላለመቀራረብ ለመነጣጠል እየዛተ፣ ላለመተባበር ለመለያየት እየተፈራረመ፣ ላለመዋደድ ለመጠላላት እየፎከረ፣ ላለፈ ክረምትም ቤት እየሠራና በዱሮ በሬም እያረሰ(ምርቱ ላያምር ላያጠግብም) ይሄውና ዘመን አልፎ ዘመን ተተካ። ፍቅርና መተሳሰብ ማንን ገደለ? ለነገሩ ብሂላችን ‹ዕውቀት እሚገኝ ባምሳ ገንዘብ እሚገኝ በሠላሳ› ነበር እሚል፤ አሁን ይህን ብሂል ምን በላው ይባላል?

 

… ‹ሀ›፣ ‹ለ› ፣ ‹‹ሐ›እና ‹መ› ‹ወ›ን አይወዱትም። ለ‹ወ› ትልቁ ፌሽታ ‹ሀ›፣ ‹ለ›፣ ‹ሐ›እና ‹መ› ዐይንና ነጫ ሆነው በደምና ለደም ሲፈላለጉለት መሆኑን አራቱ ካልገባቸው አንድም ቂሎች ናቸው አለዚያም ‹ወ›ን ለይስሙላ ካልሆነ በስተቀር ከልባቸው አይጠሉትም፤ የዓላማና የድርጊት አንድነት በግልጽ ባይኖራቸውም ሥነ ተፈጥሮኣዊ የባሕርይ ተስስር እንዳላቸው ግን መጠርጠር ይቻላል፤ በቃኝ እባካችሁን፤ ሁሉን ቢያወጉት ሆድ ባዶ ይቀራል። ወይ ነዶ!


ነጻነት ዘገዬ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ