የሹክሹክታው ክፍል ሁለት ገፅታ
ከዚህ ቀደም ‹‹ሹክሹክታው ምንድርነው?›› በሚል ርዕሰ ጉዳይ አንድ ፅሁፍ ፅፌ ነበር። የፅሁፉ ጭብጥ የሚያጠነጥነው የአረብ ሀገራት የተሳካ አብዮትን ተከትሎ በኢትዮጵያም ሁለት ዓይነት ሹክሹክታዎች ነፍስ መዝራታቸው ላይ ነበር።
በገዢው መደብ እና በተገዢው መደብ ወይም ‹‹ስልጣን በቃችሁ›› እና ‹‹እንዴት ተደርጎ! ከዚህ በኋላም አርባ እና ሃምሳ አመትበስልጣን መቆየት እንፈልጋለን›› በሚሉ ኃይሎች መካከል ማለቴ ነው። በእርግጥ ሁለቱም በቂ ምክንያት አላቸው፡፡ ለምሳሌ የኢህአዴግ አመራር ከነጀሌዎቹ ‹‹ህዝቡ ይነሳብን ይሆን? ይጮኽብን ይሆን? መራራ ጉዲና የተራበ ህዝብ የሚበላው ሲያጣ መሪውን ይበላል የሚለው ይህ አይነቱን ተቃውሞ ይሆን?...›› የሚሉ የድንጋጤ ሹክሹክታ ቢያንሾኳሹክ አይፈረድበትም። ሁለተኛው ደግሞ በተገዥው መደብ ያሉ የጭቁን ኢትዮጵያውያን ሹክሹክታ ነው። ፍሬ ሃሳቡም ‹‹መቼ ይሆን እንደቱኒዚያውያን ወይም ግብፃውያን በሀገራችን ታላላቅ አደባባዮች በኩራት የምንጎማለለው? የምናምንበትን ሃሳብ የምናንፀባርቀው? በመረጥነው መንግስት የምንተዳደርበት ቀንስ እየመጣ ይሆን? የመንግስት የዘራፊነት እና የአስፈራሪነትስ ጀንበር እየጠለቀች ይሆን?…››› የሚሉ ተስፋ የሰነቁ ሹክሹክታዎችን ቢያናፍሱ ለዘመናት የናፈቁት ነውና ምክንያታዊ ነው። ዛሬ ደግሞ የሹክሹክታውን ሁለተኛ ክፍል ወይም የዕድገት ደረጃ በደምሳሳው እናየዋለን፡፡
ስለሹክሹክታው ከወደታች እመለስበታለሁ። በዚህ አጋጣሚ ምንአልባትም ድርጊቱ ተደጋግሞ የሚቀጥል ከሆነ ይውደም!፣ ይገደል! ያልነውን ‹‹አናርኪዝም››ን ሊያሰፍን ስለሚችል አንድ ጉዳይ ላንሳ። ፍትሃዊ ስላልሆነ ዳኝነት፡፡ መቼም ህግ የለም ካልን መንግስትም የለም ማለታችን እንደሆነ ግልፅ ነውና፡፡ ዳሩስ የፍትህ መፈክር ራሱስ ‹‹ፍትህ የአንድ አገር የማዕዘን ድንጋይ ነው›› አይደለምን? እናም የማዕዘኑ ድንጋይ ፈርሶ ከማለቁ በፊት ብንነጋገርበት ምን ይለናል?
…ዕለተ ሰኞ ሚያዝያ 22 ቀን 2004 ዓ.ም. በከፍተኛው ፍርድ ቤት 3ኛ ወንጀል ችሎት የአራት ወር እስራት ወይም የ2000 ብር ቅጣት ተፈርዶብኝ፤ ሁለተኛውን አማራጭ ተቀብዬ ለሰዓታት ከቆየሁበት በተለምዶ ‹‹የአንበሳ ቤት›› ከሚባለው ማረፊያ ቤት ተለቀኩ። በቅድሚያ ለምን ተከሰስኩ? ለምን ተፈረደብኝ? የሚል ቅሬታ እንደሌለኝ አስገነዝባለሁ። ምክንያቱም ቅሬታዬ ክሱ ላይ ሳይሆን ዳኝነቱ ላይ ነውና። ነገሩም እንዲህ ነው ሚያዝያ 11 ቀን 2004 ዓ.ም. አቃቤ ህግ ‹‹ከላይ በተጠቀሱት በከሳሽና በተከሳሾች (የፌዴራል ዓቃቤ ህግ እና እነአንዷለም አራጌ) መካከል በተከበረው ችሎት እየታየ ያለውን የወንጀል ክስ አስመልክቶ በፍትህ እና ነጋድራስ በተባሉ ሳምንታዊ ጋዜጦች እየወጣ ያለውን የተዛባ የችሎት ዘገባ አስመልክቶ የቀረበ አቤቱታ ነው›› በሚል ርዕስ የፃፈው ቅሬታ ደረሰኝ፡፡ ልብ በሉ ዓቃቢ ህግ ያቀረበው ክስ አይደለም አቤቱታ ነው። እናም ዓቃቤ ሕግ አቤቱታውን ከዘረዘረ በኋላ በመጨረሻም ከችሎቱ የሚፈልገውን ዳኝነት እንዲህ ሲል ጠየቀ ‹‹የተከበረው ችሎት ለወደፊቱ ከተመሳሳይ ድርጊት እንዲቆጠቡና ያወጡትንም ፅሁፍ የአንድ ወገን መረጃን ብቻ የያዘ መሆኑ ታውቆ ማስተባበያ እንዲሰጡበት እንዲደረግ በአክብሮት እናመለክታለን››
እንግዲህ የፍትህ ምላሽም በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ተገድቦ ነው የቀረበው። ፍርድ ቤቱም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ። በተለወጠው የቀጠሮ ዕለትም ፍርድ ቤቱ አቃቤ ሕግ አቤቱታውን ካቀረበባቸው የአራት ሰዎች ፅሁፍ ውስጥ አንዱ የሆነው ክንፈ ሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) በችሎቱ ፊት ቀርቦ ፅሁፉ የእርሱ መሆኑንና አለመሆኑን እንዲያረጋግጥ ትእዛዝ ሰጠ። በእርግጥ የአቃቤ ሕግ አቤቱታ ውስጥ ‹‹ፅሁፉ የተከሳሾቹ የራሳቸው መሆን አለመሆኑ ላይም ጥርጣሬ አለኝና ይጣራልኝ›› የሚል ነገር ባለመኖሩ፣ እንዲሁም ከአራቱ ተከሳሾች በግሉ ጠበቃ ማቆም ያልቻለው (ሌሎቹ ጠበቃ ቀጥረዋል) አበበ ቀስቶ ብቻ እንዲቀርብ መታዘዙ ግራ ቢገባኝም በቀጠሮው ቀን አበበ ቀስቶ ቀርቦ ‹‹ፅሁፉ የራሴ ነው። የአዘጋጀሁትም እዚሁ ፍርድ ቤት በንባብ ላቀርብ ነበር። ሆኖም ስላልቻልኩ ለጋዜጣው ላኩት›› ሲል መሰከረ። እኔም ከአሁን አሁን አቤቱታው ውድቅ ሆኖ፣ በነፃ ተሰናብቼ ተግሳፅ ለአቃቤ ሕግ ይሰጣል ብዬ ብጠብቅም ሌላ ቀጠሮ ተሰጠ። እንደተለመደው በዚህም ቀን ቀረብኩ። ችሎቱም ‹‹ትእዛዝ›› ለመስጠት (የቅጣት ውሳኔ አይደለም ያለው ትዕዛዝ ነው። በትእዛዝ እና በቅጣት ውሳኔ መካከል ልዩነት መኖሩን ልብ ይሏል) የግድ አበበ ቀስቶ መቅረብ አለበት አለና የእለቱ ችሎት ለከሰዓት በኋላ ተቀጠረ። ከሰዓት በኋላም አበበን ጨምሮ ሁላችንም በችሎቱ ተገኘን። ፍርድ ቤቱም ትእዛዝ ሰጥተናል አለና ጉዳዩን በሶስት ከፍሎ እንዳየው ገለፀ፡፡
የአንዱአለም አራጌ እና የእስክንድር ነጋ ፅሁፍ ላይ አቃቤ ህግ ያቀረበውን አቤቱታ ውድቅ አድርገናል አለ። የናትናኤል መኮንን እና የክንፈ ሚካኤል ደበበ ፅሁፎች ላይ የቀረበው አቤቱታ ደግሞ ተገቢ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ እንዳመነበት ከገለፀ በኋላ በዚሁ ጉዳይ ላይ ‹‹ፍርድ ቤት ቀርበህ መስክር›› የተባለው አበበ ቀስቶ በዚሁ በመሰከረበት ጉዳይ ‹‹ችሎት በመድፈር›› ጥፋተኛ ተባለና የ8 ወር እስራት ተፈረደበት። በእኔ ላይ ደግሞ የአራት ወር እስራት ወይም የ2 ሺህ ብር ቅጣት እንደተወሰነ የመሀል ዳኛው በአክብሮትና በትህትና ገለፁ፡፡ የናትናኤል መኮንን ፅሁፍ ችሎት መድፈር መሆኑን ፍርድ ቤቱ አምኖበት እንደሆነ የተገለፀ ቢሆንም ስለናትናኤል ግን የተባለ ነገር የለም፡ ፡ መጠየቅ አለበትም የለበትምም አልተባለም። ሁለት ተመሳሳይ ጥፋት ካጠፉ ሰዎች መካከል አንዱ ተለይቶ የሚቀጣበት አካሄድ ለእኔ ግልፅ አይደለም። (ምንአልባት አበበ ቀስቶ ‹‹ፅሁፉ የእኔ አይደለም›› ብሎ ክዶ እኔን እንዲወነጅል ተፈልጎ ስላልተሳካ ይሆናል አበበ ከናትናኤል ተለይቶ የተቀጣው የሚል ክፉ ጥርጣሬ የለኝም። ሆኖምይህ ሁኔታ ማብራሪያ ያስፈልገዋል)
ትልቁ ስጋቴ በፍርድ ሂደቱ ላይ የተስተዋሉ ሁለት ግዙፍ ነገሮች ናቸው፡፡ የመጀመሪያው አቤቱታ አቅራቢ አቃቤ ሕግ እኔን ወደፍርድ ቤት ያስጠራኝ ‹‹ማስተባበያ›› አወጣለት ዘንድ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ እንዲሰጥ ነው፡፡ በግልፅ በደረሰኝ የመጥሪያ ደብዳቤ ላይም ‹‹ማስተባበያ እንዲሰጡ ይደረግልኝ›› ሲል ገልፆአል፡፡ ነገር ግን አቤቱታ አቅራቢው ከጠየቀው ዳኝነት በእጅጉ የተለየ የቅጣት ውሳኔ ነው የተወሰነብኝ። ለእኔ እንደሚገባኝ ‹‹የእጅ ¬ጥብቅ ዋስ ይጥራልኝ›› ብሎ አቤቱታ ላቀረበ ሰው የቅጣት ውሳኔ እንደማስተላለፍ አይነት ሆኖ ነው። ሌላው ቀርቶ የቅጣት ውሳኔ የሚሰጥ እንኳን ከሆነ በየትኛውም ፍርድ ቤት ካለው አካሄድ አንፃር አቃቤ ሕግም ሆነ እኛ ተከሳሾች የቅጣት አስተያየት ልንጠየቅ ይገባ ነበር። ይህም አልተደረገም። የተደረገው ምንድን ነው? በደፈናው ‹‹ትዕዛዝ እንሰጣለን›› ተባለ፡፡ የተነበበው ግን ትእዛዝ ሳይሆን የቅጣት ውሳኔ ነው። ይህም ለፍትህ ስርዓቱ ቀጣይነትና ተቀባይነት አደጋ ይመስለኛል።
ሌላው በእጅጉ አስገራሚ የሆነው ጥፋተኛ የተባልንበት አንቀጽ ነው። ፍርድ ቤቱ ‹‹የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀጽ 449/1 ላይ የተገለፀውን ተላልፋችኋል›› ብሎ ነው ፍርድ የሰጠው። ሆኖም ለአንባቢያን እና ለሚመለከተው አካል ግልፅ ይሆን ዘንድ አንቀፁ የሚለውን እንየው፡-
አንቀጽ 449 -ፍርድ ቤትን መድፈር
1. ማንም ሰው በፍርድ ቤትምርመራ በሚደረግበት ወይም የፍርድ ሥራ በሚከናወንበት ጊዜ፡-
ሀ. ፍርድ ቤቱን ወይም የዳኝነት ስራ በማከናወን ላይ ያለውን ዳኛ በማናቸውም መንገድ የሰደበ፣ ያወከ ወይም በነዚሁ ላይ ያፌዘ ወይም የዛተ እንደሆነ ወይም
ለ. የፍርድ ቤቱን ሥራ በማናቸውም ሌላ መንገድ ያወከ እንደሆነ፤ ከአንድ አመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከሶስት ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል ይላል።
እንግዲህ በእኔም ሆነ በአበበ ቀስቶ ላይ ዓቃቢ ህግ ያቀረበው አቤቱታ በዚህ አንቀፅ እንደተብራራው የፍርድ ቤት ምርመራ በሚደረግበት ወይም የፍርድ ስራ በሚከናወንበት ጊዜ ‹‹ችሎት ደፈራችሁ›› የሚል አይደለም። ከችሎት ውጭ በጋዜጣ ላይ ችሎቱን ደፈራችሁ የሚል ነው። የወንጀለኛ ህጉም ይህንን አይነት ጥፋት የሚዳኘው በአንቀጽ 449/1 ሳይሆን በአንቀጽ 449/2 እንደሆነ በግልፅ እንዲህ ሲል ይደነግጋል፡-
አንቀጽ 449/2 ‹‹ወንጀሉ የተፈፀመው ከችሎት ውጭ ሆኖ ዳኛው ሥራውን እያከናወነ ባለበት ጊዜ ከሆነ፣ ቅጣቱ ከስድስት ወር የማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከአንድ ሺህ ብር የማያበልጥ መቀጮ ይሆናል››
ታዲያ የተከበረው ፍርድ ቤት፣ ያውም ከፍተኛው ፍርድ ቤት፣ ያውም ሶስት ዳኞች የተሰየሙበት፣ ሌላው ቀርቶ ዜጎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ክስ ቢመሰርቱ እንኳ በታማኝነት በተገቢው የህግ አንቀፅ እውነተኛ ፍትህን ይሰጣል የሚባለው ፍርድ ቤት፤ ከጥፋታችን ጋር የማይገናኝ አንቀፅ ጠቅሶ ሲቀጣ በህግ አውጭው ላይ ብቻ ሳይሆን በህግ ተርጓሚውም ላይ እምነት ባንጥል በማን ይፈረዳል?
የሚመለከታችሁ ሀላፊዎችም ‹‹ባልተጣሰ አንቀፅ›› የመቅጣቱ ሁኔታ ምንአልባት በእኔ እና በአበበ ቀሰቶ ብቻ የደረሰ ላይሆን ስለሚችል የዳኝነት አሰራሩን ደግማችሁ ደጋግማችሁ እንድትፈትሹት የሚያደርግ ነው ብዬ አስባለሁ።
መቼም የአጠፋሁት ጥፋት 449/2 ላይ የተጠቀሰው ሆኖ ሳለ ከዚህ የሚበልጥ የቅጣት መጠን ያለው አንቀፅ ተፈልጎ ባላጠፋሁበት አንቀፅ የተቀጣሁት ሆን ተብሎ ወይም በደካማ የህግ እውቀት የተመራ ዳኝነት ነው ብዬ ስለማላስብ ስህተቱ እንደሚታረም ተስፋ አደርጋለሁ። የዚህ ፅሁፉም አላማ ‹‹የቅጣት ውሳኔ የሚወስነው አጥፊውን ለማስተማር ነው›› በሚለው የፍትህ መርህ የተቀኘ መሆኑን በቀናነት ትረዱታላችሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
አሁን ደግሞ ወደ ሌላው አጀንዳችን እንሸጋገር ወደ ሹክሹክታው።
በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በፓርላማ ተገኝተው ተቃዋሚዎች በመንግስታቸው ላይ ህገ-ወጥ በሆነ መልኩ እያሴሩ እንደሆነ ገልፀው ‹‹መንግስት ማየት የተሳነው፣ መስማት የተሳነው›› አይደለም ብለው ነበር። በቅርቡም በዛው ፓርላማ የመምህራኖችን ተቃውሞ ሲያጣጥሉ ‹‹አመፁን የቀሰቀሱት አስተማሪዎች ከዚህ ቀደም ወላጆች እና መምህራኖች ብቃት የላቸውም፣ ስነምግባር የላቸውም አባሩልን ሲሉ አልሰማ ያልናቸው ናቸው›› አሉን። ይህን ከቅን እሳቤ ተነስተን እውነታቸውን ሊሆን ይችላል ብለን እናስብ (በግሌ ግን ፍፁም እውነት እንዳልሆነ እርግጠኛ ነኝ)
ነገር ግን ዜጎችን ሽብር ላይ የሚጥለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት ምን ጊዜም የሚሰማው ድምፅ ለስልጣናቸው የሚያሰጋውን ለይቶ ብቻ መሆኑን ያመላክታል። ባለፉት 21 የጭቆና አመታት እንዲህ የሚሉ የኢትዮጵያውያን ድምፆች ነበሩ፡- ‹‹…የመሬት ፖሊሲያችሁ ለህዝብ አይጠቅምምና ቀይሩት፣ የህገ-መንግስቱ አንቀፅ 39 ሀገሪቱን የሚበታትን ነውና አውጡት፣ የኤርትራና የአሰብ ጉዳይ የህዝብ እንጂ የፓርቲ ጉዳይ ስላልሆነ ብቻችሁን አትወስኑ፣ ምንም እንኳን አሸናፊዎች ብትሆኑም ከ50 አመት በላይ ሲገነባ የቆየውን የኢትዮጵያ ሰራዊት አትበትኑ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የቤተሰብ አስተዳዳሪዎችን ያቀፈውን ህንፃ ኮንስትራክሽን አታፍርሱ፣ በቋንቋ ላይ የተመሰረተው የፌዴራል ስርዓታችሁ ለአንድነታችን ፀር ነው፣ ከኤርትራ/ሻዕቢያ ጋር ያላችሁ ግንኙነት ከሌሎች ጐረቤት ሀገራት ጋር ባለን ግንኙነት መሰረት ይሁን፣ ምርጫ አታጭበርብሩ፣ የህግ የበላይነት ይስፈን፣ በተለያየ ጊዜ በጎዳና ላይ ለተገደሉ ዜጎች ተጠያቂው ለፍርድ ይቅረብ፣ የኢትዮጵያ ጦር ወደ ሱማሊያ አይዝመት፣ በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አትግቡ፣ ሀገሪቱን በሙሉ የፓርቲ አባል ለማድረግ የሚደረገው ሩጫ ጎጂ ነው፣ ኑሮ ተወደደ፣ የሸቀጦች ዋጋ አሻቀበ፣ ያልተጠና የዋጋ ማስተካከያ ከማረጋጋት ይልቅ ያባብሳል፣ ሃያ አንድ አመት አንድ ፓርቲ እና አንድ ሰው በስልጣን ላይ መቆየታቸው አምባገነንነት ነው….›› ወዘተረፈ ሰሚ ያላገኙ ወይም የባከኑ ድምፆች ናቸው፡፡
እነሆ ዛሬ ዛሬ ከሞላ ጎደል እነዚህ ድምፆች ከሹኩሹክታ ያለፉ ቢሆኑም ማየት ያልተሳነው፣ መስማት ያልተሳነው መንግስት ማየትም መስማትም አልቻለም። ለዚህም ነው የቱኒዚያ ህዝባዊ ተቃውሞ ተቀስቅሶ ከተሳካ በኋላ የኢትዮጵያውያኖችን ቀለብ በፍጥነት ሊስብ የቻለው፡፡ ይኽንንም ተከትሎ መሽቶ በነጋ ቁጥር ‹‹ሰላማዊ ለውጥ››ን ተስፋ ያደረጉ አንሾካሻኪዎች ድማፃቸውን ጎላ ማድረግ ጀመሩ።
በእርግጥም ሃያ አመት በከሸፈ ርዕዮተ- አለም፣ በጉልበተኛ ፓርቲ፣ በአምባገነን መሪ ስር መቆየቱ አሰልቺ ብቻ ሳይሆን አስከፊም ነው። ለዚህም ይመስለኛል የማንሾካሾኪያው የጊዜ ገደብ አልፎ ልክ እንደቱኒዚያዊው ጀግና ራስን በቤንዝን በማቃጠል ድምፅን በአሰቃቂ ሁኔታ ማሰማት ደረጃ ላይ የተደረሰው። ከወራት በፊት ከአዲስ አበባ በብዙ መቶ ኪሎ ሜትር በምትርቀው የዳውሮ ዞን መምህር የእኔሰው ገብሬ ‹‹ፍትህ የለም፣ ልማት የለም፣ ዴሞክራሲ የለም›› ሲል የዞኑ አስተዳደር ቅጥር ጊቢ ድረስ በመሄድ ራሱን በራሱ አቃጠለ። ሆኖም መንግስት የእኔሰውን የበላውን የእሳቱን ወላፈን ሊያየው አልቻለም፤ የሰቆቃና የስቃይ ድምፁንም ሊሰማው አልፈቀደም። ምንአልባት ዳውሮ ከአራት ኪሎ ቤተመንግስት ብዙ እርቀት ላይ ስለሚገኝ ይሆን ይሆናል፡፡ ይህን የሚያውቀው ‹‹መስማትና ማየት አልተሳነኝም›› የሚለው መንግስት ብቻ ነው፡፡
ሰሞኑን ደግሞ ከአራት ኪሎ ቤተመንግስት አንድ ኪሎ ሜትር በማይሞላ ዕርቀት ላይ የሀገሪቱ እምብርት በሆነው የፒያሳ አደባባይ ዳዊት ለንዳሞ የተባለ የፌዴራል ፖሊስ አባል የነበረ ሰው ‹‹የምበላው አጣሁ፣ ኑሮ ተወደደ›› ሲል ራሱን በማቃጠል ድምፁ ይሰማ ዘንድ መስዋዕት ሆነ። መቼም ዳዊትን የበላው እሳት ወላፈንም ሆነ ጢስ ከቤተ መንግስቱ ቅጥር ሆኖ ላንጋጠጠ ማየት አይሳነውም። የግድ ቤተ መንግስቱ ውስጥ ገብቶ ካልተቃጠለ ‹‹አንሰማም፣ አናይም›› ካልተባለ በቀር።
የሆነ ሆኖ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ መንግስታቸው የሀዘን ብሶት እየሰማ ‹‹ጆሮ ዳባ…›› እንደሚል አረጋግጦልናል። ‹‹ወላጆች እና ተማሪዎች እነዚህ አስተማሪዎች (ያመፁትን ማለታቸው ነው) ችሎታና ስነ ምግባር የላቸውም ሲሉን ሰምተን ዝም ማለታችን ነው›› ብለውናልና። መቼም ይህ ብሶት ለአቶ መለስ ጆሮ በመድረስ የመጀመሪያው አይመስለኝም። የሌሎቹ ችግሮች ድምፅ እንደ መምህራኖቹ በተደራጀ ሁኔታ የስራ ማቆም አድማ በማድረግ ባለመታጀቡ ለመንግስቴ ስጋት አይደለም ብለው ይመስለኛል። አሊያማ ብንጮኽ፣ ብንጮኽ፣ ብንጮኽ… ‹‹አይሰማም›› ሲሉን የከረሙት አቶ መለስ ራሳቸው በአደባባይ ‹‹ሠምተን ዝም አልን›› ባላሉንም ነበር፡፡ ግና አሉን፡፡ የእምነት ቃላቸውን ሰጡን፡፡ የመልሳቸው መንፈስ የሰረፀው የመምህራኑ አድማ ቀጣይ ከሆነ ከሌሎች የሀገሪቱ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ጋ ተደምሮ ‹‹ለመንግስቴ ጦስ ጥንቡሳስ›› ይሆናል ከሚል ስጋት ነው።
ምክንያቱም ሌላው ቢቀር ‹‹መምህራኖቹ ይባረሩልን›› ብሎ ወላጅ እና ተማሪው ከጠየቀ፣ የስነ ምግባርና የክህሎት ችግር ከነበረባቸው ለህዝብ የሚነገረው ከደሞዝ ጭማሪ ጋር የተያያዘ አገር አቀፍ አመፅ ሲያደርጉ ሳይሆን በወቅቱ ነው። ህግ ባለበት ሀገር እየኖርን ወንጀለኛ ከተበራከተ ‹‹መንግስት አልባ ወይም ህገ-መንግስት አልባ ናቸው እያልን ከምንሳለቅባቸው ሀገራት ከምን ተለየን?
በእርግጥ ኢህአዴግ ሃያ አንድ ዓመት ሙሉ መፍትሄ እንዲሰጥ ሲጠየቅ ለነበረው የህዝብ ችግር፤ እግር በእግር እየተከተለ ማስቀየሻ ሲፈጥርለት ነው ዛሬ ላይ የደረሰው። የመምህራኑ ጥያቄ ግን አንድም ድንገት ሆነበት፤ ሁለትም ከወትሮ የማስቀየሻ ስልቶች ገፍቶ ወጣ። እናም አዲስ ማስቀየሻ አልተበጀለትምና ጥሶ የመጣበት ቀዳዳ በርካታ የታፈኑ እውነታዎችን እንዲህ ዘርግፎ አወጣ።
እዚህች ጋ ግራ የሚያጋባው መምህራኖቹ ስነ ምግባር የጎደላቸውና ክህሎት የሌላቸው ከሆነ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት በተዋረድ የሾማቸው ሀላፊዎች እንዴት መፍትሄ ሊሰጡት እንዳልቻሉ ነው። ምክንያቱም ከመምህሩ በላይ ዩኒት ሊደር፣ አስተዳደር እና ዳይሬክተር የሚገኙበት የበላይ መዋቅር አለ። ከእነዚህ አቅም በላይ ከሆነም የክፍለ ከተማው ትምህርት ቢሮ መፍትሄ መስጠት ነበረበት። ከእሱም አቅም በላይ ከሆነ የአዲስ አበባ ወይም የየክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች አሉ። እነሱም ካልቻሉ ትምህርት ሚኒስትር ምን ይሰራል? ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹ሰምቼ ዝም አልኩ›› እስኪሉ ድረስ? ወይስ…
በአጠቃላይ ኢህአዴግን እስከምናውቀው ድረስ የመሬት ፖሊሲውን ለውጥ ‹‹በመቃብሬ ላይ ካልሆነ ወይ ፍንክች››፤ ህገ-መንግስቱ ይሻሻል ‹‹ሞቼ ነው ቆሜ›› ሲል ይሰጥ የነበረው ‹‹ተፈታታኝ›› ምላሽ በአዲስ ታሪክ እየተቀየረ ነው ወይስ አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሰሙት ድምፅ በአድማ እና አመፅ የታጀበን ብቻ ነውን?... ይህ የእኔ ብቻ ጥያቄ አይመስለኝም።
ሹክሹክታዎችም ቀስ በቀስ ወደ አደባባይ ጩኸቶች የሚቀየሩት በሁለት ሁነቶች ተዛምዷዊ ክስተት ነው። የመጀመሪያው በቀስታ የሚያጉረመርሙት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሄዱ ነው። ለሹክሹክታው መነሾ የሆኑት አምባገነንነት እና የኑሮ ውድነት እየገነገኑ መሄድ የሹክሹክታውን ተሳታፊዎች ቁጥር እየናረው ይሄዳል። የሹክሹክታው መስፋፋት ወደ አደባባይ ድምፅነት እንዲቀየር ግን አገዛዙን መሸከም ያንገፈገፋቸው ዜጐች ‹‹የእኛው መስቀል አደባባይ ከታህሪሩ አደባባይ ምን ያህል ይርቃል?›› የሚል ጥያቄ ሲያነሱ ሁለተኛው አስገዳጅ ምክንያት ይፈጠራል። የየእኔሰው ገብሬና የዳዊት ለንዳሞ ዘመነኞችም ከቡዓዚዝ ትውልድ በባሰ አምባገነንነትን የሚሸከም ትከሻ እንዴት ሊኖራቸው ይችላል? አቶ መለስ ሊሰሙት ባይፈቅዱም ትውልዱ ግን ወደ ታህሪር መመልከት ጀምሯል?
ፍትህ ጋዜጣ (አዲስ አበባ)



