የኢሳት መንፈስና የኢሳት ሸክም
የኔታ ተክሌ - (ቶሮንቶ-ካናዳ)
ከዲሲ ማርያም እስከ ቶሮንቶ ማርያም
በሳን ሆሴ (ዜ) ያየሁትም በዚያ በኮለምበስ እንዳየሁት ነው። በኮምበስ ያዩሀት በአትላንታ እንደመሰከርኩት እንደሆነው ማለቴ ነው። በርግጥ በነዚህ ከተሞች ያየሁት በቶሮንቶ ወይንም በዲሲ ቅድስት ማሪያም እንዳየሁት አይሆንም። የዛሬ ወር ከግማሽ አካባቢ ነው፤ ባንድ እለተ-ሰንበት፤ በዲሲ ቅድስት ማሪያም ከረፈደ ተገኝቼ፤ ያው ከረጅሙ የኛ ቤተክርስቲያን አገልግሎት በሁዋላ፤ ቄሱ በዚያ ሳምንት ለህንጻ ማሰሪያ የተዋጣውን ገንዘብ መዘርዘር ጀመሩ። አንዳንድ ግዜ የመዋጮውን ብዛት ሳስበው፤ የዛሬ አራት ወር የሰማሁትን እየደገሙት ነው ወይስ አዳዲስ መባእ ነው ያስብለናል።
አባታችን ቀጠሉ … አንድ ስሙ እንዲገለጽ ያልፈለገ ሰው፤ 600 ዶላር ሰጥቷል። ስሜን እመቤታችን ታውቀዋለች ያሉ ሴት 1200 ዶላር አስገብተዋል። እልልልልልል። እመቤታችን ስለቴን ነግሬያት ሰምታኛለች፤ ያሉት ወለተሚካኤልና ባለቤታቸው ክንፈገብርኤል፤ 4300 ዶላር አምጥተዋል። ይሄ በዲሲ ማርያም ነው። የዲሲ ገብርኤልን አላነሳውም። በዚያ ሰሞን በነበረው ግርግር የተነሳ ቢቀጭጭም፤ እዚያም የምሰማው የመዋጮ መኣት የአስተዋጽኦ ትርኢት የትየለሌ ነው።
እነሆ ከዚያ መልስ ነው ወደቶሮንቶ ማርያም ስመጣ ተመሳሳይ ድምጽ የሰማሁት። አልፎ አልፎ ህንጻ ግንባታ ላይ አተኩረው፤ ባንዳንድ ከተሞች ህዝብ ሲፈርስ ፈጣን እርምጃ ባለመውሰዳቸው ብወቅሳቸውም፤ እኛን የመሰለ አስቸጋሪ ህዝብ አንድነት ጠብቀው በሚገነቡት ካቴድራል ህንጻ የማደንቃቸው፤ ቆፍጣናውና አገር ወዳዱ የቶሮንቶው ደብር አስተዳዳሪ፤ የሲኖዶሱ ቃል-አቀባይ፤ ሊቀካህናት ምሳሌ እንግዳ የሚሰጠውን ገንዘብ ብዛት ያነባሉ። አቶ በድሉና ባለቤታቸው ወለተማሪያም አንድ ሺህ ዶላር ቃል ገብተዋል (ስሞች በሙሉ ተለውጠዋል)፤ ዶ/ር እንቶኔም ከባለቤታቸው አስካለማሪያም ጋር በመሆን አንድ ሺህ ብር (ዶላር) ሰጥተዋል። ባለመቶ ብሮቹን ተዋቸው። ሊቀካህናት ደከማቸውና ሊቀዲያቆኑ ቀጠሉ። ….. ይገርማል። አዲሱን የቅድስተ ማርያምን ቤ/ክ ለመገንባት ወደ አምስት ሚሊዮን ዶላር ካዋጡ በሁዋላ፤ እንደገና አሮጌውን ለማፍረስ ደግሞ ወደስልሳ አምስት ሺህ ዶላር ገንዘብ ያስፈልግ ኖሮ ባንድ ቀን የቅዱስ ሚካኤል ንግስ ነው 45 ሺህ ምናምን የተሰበሰበው።
ታቦታትን የተካከል ክስተት፡ ኢሳት
ዲሲ ማርያም፤ ቶሮንቶ ማሪያም፤ ቅድስት ማርያምና ኢሳትን ምን አገናኛቸው? በነዚያ በኢሳት የገንዘብ ማሰባሰቢያ ምሽቶች ላይ የማያቸው ክስተቶች፤ ኢሳትም የታቦታትን ያህል ገነነ እንዴ አሰኝቶኝ ነው። ኢሳት በሁለት አመት የቅድስት ማርያምን ያህል ገንዘብ እንዲስብ ባንገምትም፤ ከቅዱሳን ባላነሰ መልኩ የሰውን ኪስ፤ የህዝብን ጭንቅላት፡ የትውልድን ልብ እየማረከ ያለ ተቋም ነው። ኢሳት። በያካባቢው ወዳሉ የኢሳት ገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች ስሄድ የምሰማው ሁሉ የሚደንቅ የኢሳት ፍቅር ነው። የኢሳት ወረርሽን። አትላንታ ልውሰዳችሁ። እመት አረጋሽ ሲሳይ ልጃቸውን ሊያርሱ መጥተው እዚሁ የቀሩ ባልቴት ናቸው። ኢሳት ተመችቷቸዋል። መደበሪያቸው እንዲሁም መዝናኛቸው እንዲሁም የቤት ስራቸው ሆኗል። እለት እለት አያመልጣቸውም። አማቻቸው የኢሳትን ገንዘብ ሲያሰባስብ፤ ለኔስ እንዴት ዝም አልከኝ ብለው ከመንግስት ከሚያገኟት ገንዘብ ላይ ካልሰጠሁ ብለው ግብግብ ገጠሙ። ወ/ሮ እመቤት በልሁም እንዲሁ በኦታዋ አካባቢ እንጀራ በመሸጥ ቤተሰባቸውን የሚደጉሙ ትልቅ ሴት ናቸው። ዘወትር ጠዋት ላይ እንጀራቸውን እያሰፉ በኪሳቸው ስልካቸውን ይዘው የኢሳት ዝግጅት መጫን አለመጫን ይጠብቃሉ። የሳቸውማ የሚገርም ነው። እንደው አንዳንድ ቀን፤ የቴክኒክ ችግር ተፈጥሮ በሰዓቱ ሳይጫን ቢቀር፤ አላስችል እያላቸው፡ ስልክ ደውለው “ምነው ተክልዬ፤ እንደው ዛሬስ የላችሁም?” ይሉኛል። “ተክልዬ” ሲሉ፤ የኦታዋውን አቡነ ተክለሀይማኖትን የሚጠሩ ነው የሚመስለው። እኚህ እናትም፤ ከሚሸጡት እንጀራ ገቢ ላይ በባላቸው በኩል ገንዘብ ይልካሉ።
ኦሀዮ የሆነውም የሚያስደስት ነው። ለምሳሌ፤ ይሄ ለምሳሌ ብቻ ነው፤ የዛሬ ሶስት ወር አካባቢ፤ አቶ ፍቅሬ ከነልጆቻቸውና ባለቤታቸው የኢሳትን ቀን ድግስ ሲደግሱ ሲያሳልፉና ሲያስተባብሩ ውለው አምሽተዋል። ኮለምበስ ያየሁትን የኢሳት ፍቅር፤ የኢሳት ልክፍት ብለው ይሻለኛል። ኮለምበስን ካነሳን አይቀር ግን፤ አንድ የማይያያዝ “ነገር” ልወርውር፤ ልክ ኢሳት የቅድስት ማርያምን ያህል ሚሊዮናት እንዲስብ የማንጠብቀውን ያህል፤ በሌሎች አካባቢ የምንገኝ ኢትዮጵያዊያን፤ በገንዘብ አሰባሰብ ረገድ፤ ከወልቃይቴዎች የምንማረው ነገር አለ። አንድ ግዜ እዚያው ኮለምበስ ኦሀዮ የሆነውን ሲነግሩኝ፤ አንድ ወልቃይቴ ታሞ ይሁን ታክሞ ወደ አገሩ ይግባ ሲባል፤ ያንን ሰው ወዳገሩ ለመሸኘት፤ ስልሳ የሚሆኑቱ አንዳንድ ሺህ ሰብስበው፤ ስልሳ ሺህ ነው የሰጡት። ወልቃይቴዎች ጋር በርዳታ ቀልድ የለም። ይረዳሉ።
ወደሳንሆሴ ልመልሳችሁና በቶሮንቶ አጠቃልላሁ
በሳን ሆሴ፤ በተካሄደው የገንዘብ ማሰባሰብ ውሎ ላይ፤ የነበረው መተሳሰብ፤ የሰዉ ምክክርና የሰዎ መከባበር፤ ያስቀናል። በዚያው አጋጣሚ፤ የቀድሞ የኬንያ የስልክ ወዳጄን ጋሽ ግርማ በቀለን ከ11 አመት በሁዋላ አግኝቼ ለማመስገን እድል አገኘሁ። እነጋሽ ግርማ ስራብ አላበላችሁኝም፤ ስሰደድ አልተቀበላችሁኝም የሚለው የመጽሀፉ ቃል የገባቸው ናቸው። በ2001/2 ኬንያ በስደት በነበርንበት ወቅት፤ ያኔ አሜሪካ ያሉ ኢትዮጵያዊያን የቸሩንን ከ10 ሺህ ብር በላይ እርዳታ አስተባብረው ልከውልናል። እነሆ ከ11 አመት በሁዋላ የኢሳት ዝግጅት ላይ ሳገኛቸውም ደግነታቸው እንዳለ ነው። ለጫረታ የቀረበውን የአጼ ምኒሊክ የ1899 ጠገራ ብር፤ በአንድ ሺህ ዶላር ገዝተዋል። ባንድራም አብሮ ተበርክቶላቸዋል። ሳን ሆሴ ሌላው ያስደሰተኝኝ የሴቶቻችን ተሳትፎ ነው። ወ/ሮ ኮኒ፡ የሁለት ልጆች እናት ናቸው። የአበበ ገላውን ነጻነት ነጻነት የሚል ምስል በ2400 ዶላር አካባቢ አሸንፈው ገዙት። የዛኑ እለት፤ ከታች ሳን ሆሴ ሲያደምቀው፤ ሲያትልም ከሰሜን ቀውጢ ያደርገው ነበር። ልክ ቅዳሜ ቶሮንቶ ሲቀውጠው፤ እሁድ ዲሲ እንደሚያቀልጠው ማለት ነው። ሲያትሎች ወደሀያ ሺህ ዶላር አካባቢ ሰብስበዋል።
ኢሳት ጾታና እድሜ፤ ብሄርና ሀይማኖት ሳይገድበው ብዙዎችን የማረከና የሳበ ተቋም ሆኗል። እነሆ አሁን ደግሞ ተራው የቶሮንቶ ነው። በዚህ ቅዳሜ፤ ጁን 30 ቀን ከምሽቱ 1 ሰዓት ጀምሮ በ71 Gough መንገድ ላይ፤ በፔፕና ዳንፎርዝ መጋጠሚያ አጠገብ፤ ተሰናድተን እየጠበቅናችሁ ነው። የቶሮንቶን የኢሳት ድጋፍ ሰጪ ስብስብ አባላት ስመለከት፤ ስለኢትዮጵያ ያለኝን ተስፋ ያለመልመዋል። የ17 አመቶቹ የ”ሰብሰብ በሉ” ወጣቶች ከባለ 80ዎች እነግርማ ቸሩ ጋር፡ እድሜና ጾታ ሳይለያቸው የሚሰሩበት ስኬታማ ስብስብ ነው። በዚህ ካናዳ ውስጥ በሸበትኩበት ሰባት አመት ውስጥ፤ ብዙ የሚለያዩን የሚያጨቃጭቁንና አንዳንድ ጊዜ የሚያኮራርፉን ስራዎች አይቻለሁ። አመልና ስስት ሆኖባቸው ከሚያውኩት በስተቀር፤ በሄድኩባቸው ሁሉ ብዙዎቻችንን የሚያስማማ፤ የሚያስተባብርና የሚያስተሳስር ተቋም ቢኖር ግን ኢሳት ነው። ያ ማለት ግን ችግር የለም ማለት አይደለም። በተለይ በኢሳት አስተዳደር በኩል ብዙ መታረም ያለባቸው ነገሮች አሉ።
ነገሩ እንዲህ ነው፤ የህዝብን ቀልብና ልብ ማግኘት ከባድ ነው። ያንን ጠብቆ ማቆየት ደግሞ እጅግ በጣም ከባድ ነው። ኢሳት በከፍተኛ ትጋትና ጥረት የህዝብን ልብ እያገኘ ነው። ይሄንን ልብ ለማግኘት ደግሞ፤ ስቱዲዮን መኖሪያቸው፤ ላፕቶፕን ትራሳቸው፤ ምንጣፍን ፍራሻቸው ያደረጉ ከአምስተርዳም እስከ ዲሲ የመሸጉ በሳልና ትንታግ ልጆች ተሳትፈውበታል። ኢሳት ይሄንን የህዝብን ልብ የራሱ አድርጎ ለመቆየት ግን የበለጠ ትጋት ይጠይቃል። እኔ ራሴ ካለፍኩበት፤ ከየአካባቢው በደረሱኝና፤ እኔው በታዘብኳቸው እንዲታረሙ በተደጋጋሚ ቢነገርም፤ ባለመታረማቸው ምክንያት፤ እስካሁን ባለው ሁኔታ ብዙ ሰውን ያለስቀየሙ፤ ወደፊት ግን የህዝብንና የደጋፊን ልብ ሊያሳጡ በሚችሉና ኢሳት ሊያርማቸው በሚገባቸው አስተዳደራዊም ይዘታዊም ነገሮች ላይ ከቶሮንቶው ድግስ በሁዋላ እጽፋለሁ። ኢሳት በዜናውና በዝናው ብቻ ሳይሆን፤ በአሰራርም በአስተዳደርም ለሰዎች ቅርብ መሆን አለበት። የዜና ጥራትም ሊታሰብበት ይገባል። ዝርዝሩ ይመጣል።
እስከዚያው ግን፡ ዛሬ ቅዳሜ፡ ጁን 30፤ በቶሮንቶ፤ ኢትዮጵያዊያን መንገዶች ሁሉ ወደኢሳት ቀን ያመራሉ። እሁድ በዲሲ ወደ ሰራተን እንደሚያመሩት፤ በሳምንቱ ቅዳሜ፡ ጁላይ 7ተም በዳላስ ወደኢሳት ዝግጅት እንደሚያመሩት ማለት ነው። ይሄ ባንድ ዝግጅት ላይ ዘጠኝ ተናጋሪ እንግዳ የመደርደር ልማድን ግን አልተው ብለናል። ጎበዝ፡ ላንድ ከሰዓት ዝግጅት፤ 9 ተናጋሪ እንግዳ መደርደር ትክክል አይደለም። አንዳንድ ግዜ መምረጥ ሊኖርብን ይችላል። አንዳንድ ግዜ ደግሞ መደጋገምም የለብንም። አምና ያንደኛው አመት በዓል ላይ መሰለኝ 9 እንግዶች ተጋብዘው፤ አረ ጎበዝ ላንድ ሰዓት ዝግጅት ይሄን ሁሉ እንግዳ አታንጋጉ ብል የሚሰማኝ አጣሁ። የእሁዱ የሁለተኛው አመት ዝግጅት ላይ 4 እንግዶች አሉ፤ አሁን ደግሞ ዳላስ መልሰው 9 ሰዎች። ኡ። በዝቷል። አንዳንዴ ዝግጅቶቻችን መዝናኛም ይብዛባቸው እንጂ። መዝናኛ የማይወደው፤ የኔቢጤው፡ ዞሮ ዞሮ 9ኝም እናቅርብ 19 ይመጣል። አሁን መስራት ያለብን ግን “ፈን” እና “ዘፈን” የሚወደውን መሳቡ ላይ ነው። የዳላስ ዝግጅት ግን ፈን አይመስልም። “ገን” እንጂ።
ያው እኔው ነኝ፡ የኔታ ተክሌ፡ ሰኔ፡ 2004/12



