የመሪዎቻችን መልእክት፡ ለዚህ ሰዓት ይመጥን ይሆን?
አለቃ ተክላይ - ካናዳ
ጠቅላይ ሚኒስትሩና ጠቅላይ ተቺው፡
ይሄንን ጽሁፍ የምጽፈው፤ በተወለድኩኝ በ36ኛው አመቴ ዋዜማ ላይ ነው። ሰው በኔ እድሜ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ፤ 21 አመት ሊገዛ ይመቻቻል፤ እነሆ እኔ ደግሞ ጠቅላይ ተቺ ለመሆን ኮምፒውተሬን እስላለሁ። ደግሞ ወገንን። የራስን ወገን፤ የራስን ጎራ፡ መተቸት ይከብዳል። በተለይ አብረው የበሉትን፡ አብረው የጠጡትን፡ አብረው የተሰለፉትን፤ እንዳቅምም ቢሆን የሚችሉትን ለመስራት ደፋ ቀና የሚሉትን። ግን ደግሞ ካልተተቻቸን አናድግም። አንሰለጥንም። ጠላትን የመተቸቱንና የመዘልዘሉን ስራ ሌሎች ሄደውበታል። ስለዚህም፤ እኔ የራስን ጎራ የመተቸቱን አስቀያሚ ሀላፊነት ልወስድ ፈቀድኩ። የዲባቶ ብርሀኑን ቃለምልልስ።
ግን የአቶ አያልሰው ደሴን ቃለምልልስም ሰማሁት፤ ያው ነው። ትንሽ የጄኔራል ከማል ገልቹ ይሻላል። እርግጠኛ ነኝ ዲባቶ ብርሀኑም ይሁኑ አቶ አያልሰው በትችቴ አይከፋቸውም። እንዲያውም ከሚያሞግስ ድምጽ ይልቅ የሚያወግዝ ድምጽ የሚወዱ ይመስለኛል። ባሳለፉት ረጅም የትግል የትግል አመታት፤ ብዙ ዘለፋ፤ አያሌ ትችትና አፍ እላፊ እየተሰነዘረባቸው ኖረዋልና፤ በኔ በታናሹ ብላቴና ትችት ይቀየማሉ ብዬ አላምንም። ለነገሩ መሪ ቆዳው ወፍራም መሆን አለበት። ልክ እንደኔ። ሌሎቻችንም ብንሆን ደግሞ፤ አንዳንድ ግዜ፤ የማይጥመነንም ነገር ለመስማት መዘጋጀት አለብን። ስለዚህ የማይጥመንን ነገር ወደመስማት እንዝለቅ።
የኢትዮጵያ ሁኔታ እንደምትሰሙት ነው። የእስልምና እምነት ተከታዮች ተቃውሞና የመብት ጥያቄ እየጦዘ ሲሆን፤ የአቶ መለስን ከእይታ መጥፋት ተከትሎ የተፈጠረው ውዥንብርና ውጥረት እንደቀጠለ ነው። በአቶ መለስ ሁኔታና በሙስሊሞቹ ንቅናቄ ላይ ብዙ የምለው የለም። ዜናውን ትከታተሉታላችሁና። ይሁን እንጂ ወቅቱ ከፖለቲካ ድርጅቶቻችን ጠንካራ የአቅጣጫና የአካሄድ መመሪያ መስማት የምንፈልግበት፤ በርግጥም ፖለቲካ ድርጅቶቻችን ስራ እየሰሩ ነው ወይስ ዝም ብለው ነው የሚያደርቁን የሚለውን የምንፈትሽበት፤ ወቅት ነው። እንዳለመታደል ሆኖ ግን፤ በቅርቡ የግንቦት ሰባቱ ሊቀመንበር ዲባቶ ብርሀኑ ነጋ ያደረጉት የሁለት ሰዓት ቃለምልልስ፤ http://www.youtube.com/watch?v=vnEKc7gbN5Q&feature=BFa&list=PL0F3368BE320E79BE፤ እንዲሁም አቶ አያልሰው ደሴ በኢሳት ላይ ያደረጉት ቃለምልልስ፤ ጠላትን የሚያስደነግጥ፤ የወደፊቱን አቅጣጫ የሚጠቁም፡ ስለምንከተለው መንገድ የሚያስራዳ ሳይሆን፤ ማንም የኔ ቢጢ ተራ ሰው ሊናገረው በሚችለው ነገር ላይ ያተኮረ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ሁለቱም፤ አመራር ሰጪ ሳይሆን፤ አስተያየት ሰጪ ነው የሆኑት። እንዲያውም ሁላችንንም አስተባብሮ ወደፊት ይመራናል፤ ጠላትን አፍንጫውን በቡጢ ያነግልልናል፤ ያልኩትን ግንቦት ሰባት እንድጠራጠር፤ በርግጥም ይህቺ አገር ቀውስ ውስጥ ብትገባ፡ “ተተክቶ የሚመራ አስተማማኝ ድርጅት አላትን?” የሚለውን ያንዳንድ ሰዎች አስተያየት እንደገና እንዳስብበት አድርጎኛል። ያም ብቻ አይደለም፤ በዚህ ቃለምልልስ የተነሳ፤ ግንቦት ሰባትና ጥምረቱ፡ የኢህአፓና የሸንጎ መሳቂያ መሳለቂያ ሊያደርጉን ነው ብዬ ተሸማቅቄያለሁ።
ቃለምልልሳቸው፡ ከኛ ይልቅ ለጠላት ይጠቅማል፡
በቃለ ምልልሱ፤ ዲባቶ ብርሀኑ ነጋ በተለይ በዚህ በታሪክ አጋጣሚ በመጣ ወሳኝ የውጥረት ሰዓት፤ ግንቦት ሰባትን ተከትለን እንድንጓዝ የሚወሰውስ ውይይት አላደረጉም ባይ ነኝ። “በዚህ በኩል ሄደን በዚያ በኩል ተጉዘን፡ በዚህ በዚህ መልኩ፤ እምቢ ያሉትን እንጨርሳቸዋለን፤ የተሸነፉትን እንማርካቸዋለን፤ እሺ ያሉትንም እንቀበላቸዋለን” እንዲሉ ሰንጠብቅ፤ እንደውም፤ ልክ እንደባእድ ተንታኝ፤ መለስ ቢሞት ሊፈጠር ስለሚችለው የተለያየ ሁኔታ መላምት መስጠቱ ላይ ማተኮራቸው አናዶኛል። የኢሳት ጋዜጠኞች ሲያስተዋውቃቸው እንደድርጅት መሪዎች ሳይሆን እንደ ምሁር ቢሆን ባልከፋኝ። ነገር ግን ዲባቶ ብርሀኑ የቀረቡት ባሁን ሰዓት በንጽጽር ከሌሎች ሁሉ የተሻለ ነው ብለን በምናስበው ድርጅት መሪነት ነውና፤ ከአመራር ይልቅ ትንታኔ ማብዛታቸው አብሽቆኛል። ፖለቲካዊ መላምት ከፖለቲካ መሪ ይልቅ በፖለቲካ ምሁራን ይሻላል። ካለበለዚያ እነ ሙልጌታ ሉሌ፤ ጃዋር ሙሀመድ ምን ሰርተው ይብሉ? ከዲባቶ ብርሀኑ ነጋ፤ ይሄንን ማድረግ አለብን የሚል የልበሙሉ መሪ ንግግር ሳይሆን፤ “ያው የሚሆነውን እንጠብቅ ነገር” ነው ያስተዋልኩት። “ያው ሰውየው (መለስ ማለት ነው) አንድ ነገር ይሆናል … ምናልባት ሰዎቹ (የመለስ ባልደረቦች) ማሰብ ይጀምራሉ … የያዙትን ለመብላት ሲሉ ይስማማሉ ….. ወይንም ጥገናዊ ለውጥ አድርገው ሊጓዙ ግድ ይላል… እስኪ እንያቸው” ይመስላል። በንግግራቸው፤ ከዚያም ባሻገር እንዲሄዱ ተመኝቼ ነበር። ንግግራቸው፤ “ይህቺ አገር እንዲህ ልትሆን ስለምትችል፤ እኛ ይሄንን እያደረግን ነው፤ የሆነ ነገርም እናደርጋለን፤ ህዝቡም ይከተለን፤ ይተባበረን” የሚል መልእክት አለማስተላለፉ ዋጋውን አውርዶታል።
ያው እንደነገርኳችሁ፤ የራስን ቡድን ማቀፍ እንጂ መንቀፍ ይከብዳል። በነዚህን ሰዎች ቃለምልልስ ያልተደሰትኩበት ሌላው ምክንያት፤ ድርጅቶቹ ራሳቸው በፈጠሩት ሳይሆን ሌሎች የሚፈጥሩትን፤ ወይንም በእግዜር እጅ የተያዙት አቶ መለስ የወደቁበትን አዲስ ነገር ተንተርሶ የተደረገ ትንተና ስለሆነ ነው። ቃለምልልሱ ተነተነው እንጂ፤ “ኮማ” ውስጥ የገባውን የመለስ አገዛዝ ስለመጨረስ ምንም አልተናገረም። ቀድሞ ነገር፤ የቃለምልልሱ አስፈላጊነቱም አልታየኝም። በቃለ ምልልሱ ላይ፡ ዲባቶ ብርሀኑ፡ ድርጅታቸው እየሰራ ስላለው ስራ በግልጽ ቋንቋ አላስረዱም፤ ህዝቡም፡ ደጋፊዎቻቸውም፡ ሌሎች ድርጅቶችም፡ ኢትዮጵያውያንም በዚህ ሌላ ወሳኝ ወቅት ሰዓት ማድረግ ስላለባቸው ነገሮች አልተናገሩም። ሕወሀትን ስለመጣል ተአምራዊና መለኮታዊም ባይሆን፤ አንዳንድ ልንከተለቻው ስለሚገቡ አካሄዶችም ይመክሩናል ብዬ ነበር። ያንን ግን አላገኘሁም። ምስጥራዊ፤ ድርጅታዊና ስልታዊ ነገሮች እንደተጠበቁ ሆነው፤ “አቶ መለስ ቢሞቱና ሕወሀት ቢከፋፈል፤ እንዲሁም ስልጣን የሚረከብ ወይንም የሚቀማ ሀይል ቢያስፈልግ ዝግጁ የሆነ ሀይል አለ ወይ?” የሚለውን ጥያቄ በተዘዋዋሪ መልሰውልናል። መልሱ አያስደስትም። ግንቦት ሰባት ለዚህ ወቅት የተዘጋጀ አይመስልም። ኢህአፓና ኢዴፓ፤ መኢአድና መድረክ እንዳልተዘጋጁ ስለምናውቅ፤ ባጠቃላይ የእኛ (የተቃዋሚው) ጎራ ለወቅቱ እንዳልተዘጋጀ አርድተውናል። ይሄ ቃለምልለስ ለኛ ከሰጠን ጥቅም ለጠላት የሰጠው ይበልጣል። ለጠላት መረጋጋትን የሚፈጥር ቃለምልልስ ይመስለኛል። ምክንያቱም፤ የሕወሀት ባለስልጣናት ይሄንን ቃለምልልስ አይተው፤ “አይ ምንም የሚያሰጋን ነገር ስለሌለ፤ ተረጋግተን መተካካታችንን እናድርግ” የሚሉ ይመስለኛል። የዲባቶ ብርሀኑ ቃለምልልስ ፉከራና አመራር፡ ወኔና ቁርጠኝነት ያንሰዋል።
የቃለምልልሱ ክፍል ሁለትም ያው ነው። በክፍል ሁለትም፤ ዲባቶ ብርሀኑ ነጋ ፖለቲካዊ ንግግር ሳይሆን፤ ምሁራዊ ትንታኔ የሰጡት http://www.youtube.com/watch?v=uRr_FNzS8pI&list=UU2AvdK6_3mGgyky6T82QBMQ&index=9&feature=plcp ሲሆን፤ አንዳንዱ ምሁራዊ ትንታኔም ግልጽና ለህዝብ የሚገባ አይደለም። ለምሳሌ ስለአብዮታዊና መሰረታዊ ለውጥ ሲያስረዱ፤ ልዩነቱ ሊገባኝ አልቻለም። ዲባቶ ብርሀኑ፤ አብዮታዊ ለውጥን ቢሸሹትም ስሙን በመሰረታዊ ለውጥ ቀይረው አምጥተውታል። የሁሉም አብዮት ባህርይ፡ አሸናፊ ሀይሎች ሁሉንም ነገር ከአዲስ እንዲጀምሩ ማድረጉ ነው ብለዋል። ኢህአዴግና ደርግ ያደረጉት ያንን ነው። ሁለቱም ወደስልጣን መጡ፤ ከዚያ ከነሱ የቀደመውን እንዳለ አፈራረሱት። የኢህአዴግን መውደቅና አወዳደቅ ተከትሎ ስለሚፈጠረው ነገር ላይ ግን፤ ዲባቶ ብርሀኑ፤ ኢህአዴግ መደምሰስ እንዳለበት፤ ሁሉም ነገር ግን መፈራረስ እንደሌለበትም የሚገልጽ አሻሚ ሀሳብ ተናግረዋል። ጥገናዊ ለውጥ ሳይሆን፤ መሰረታዊ ለውጥ ያስፈልጋል ብለዋል። ግን ደግሞ “ሕብረተሰቡን የማያናጋ” የሚል ነገር አክለውበታል። ወያኔ መወገድ አለበት፤ ነገር ግን አብዮታዊ ለውጥ መምጣት የለበትም አይነት ነገር ነው። ግልጽ አይደለም። ይሄ ሁሉ መድበስበስና አሻሚ አካሄድ የመነጨው ምሁራዊነትንና ፖለቲካ መሪነትን አዋህዶ ከመሄድ ነው። እንደግንቦት ሰባት መሪም እንደፖለቲካ ምሁርም ስለተናገሩ ነው። ባሁኑ ሰዓት ደግሞ የሚያስፈልገን፤ ብዙ ምሁርነት ሳይሆን፤ ቆራጥ መሪነት ነው።
የምሁራንና የፖለቲከኞች ልዩነት፡ አንዱ ይተነትናል፤ አንዱ ይመራል
ምሁራን ጽንሰሀሳብን ማብራራት ላይ ያተኩራሉ። መሪዎች ግን ይመራሉ። ይወስናሉ። ይቆርጣሉ። ምሁር አይቆርጥም። ተማሪው ወይንም አድማጩ እንዲቆርጥ ነው የሚተወው። ለምሳሌ፤ በዚህ ቃለ ምልልስ ላይ የተነሳው አንዱ ጉዳይ፤ በህወሀት አገዛዝ ዘመን ስለተፈጠረው ጥላቻና፡ ህወሀት ቢወድቅ ስለሚፈጠር የብቀላ እርምጃ ነው። የዲባቶ ብርሀኑ ትንተና እንደአብዛኛው ሰው አይነት ትንተና ነው። ለውጡና ያለው ጥላቻ ምን ሊያመጣ እንደሚችል አናውቅም፤ ስለዚህ እንጠብቅ አይነት ነገር። ግን የፖለቲካ መሪ ቢያንስ እሱና ድርጅቱ እስከሚያውቀው ድረስ እርግጠኛ መሆን ወይንም በርግጠኝነት ማድረግ ስለሚገባው ነገር ማወቅ አለበት። “ሕወሀት/ኢህአዴግ ቢወድቅ፤ ቢከፋፈል፤ ደም መፋሰስ ይኖራል?” ለሚለው ጥያቄ፤ ግንቦት ሰባት መልሱን ማወቅ ወይንም መገመት አለበት። ካለበለዚያ ያ በሳልና ሀላፊነት የሚሰማው ድርጅት አይደለም። አለማቀፍ ተቋማትና ሀይላትም ሊተማመኑበት አይችሉም። ያው እንደማንኛውም የሽግግርና የአብዮት ወቅት የተወሰነ መራበሽና ግጭት ይኖራል። ከዚያ በተረፈ ግን፤ ሀላፊነት የማይሰማው ደደብ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ፖለቲከኞች ካልቀሰቀሱት በስተቀር፤ ሕወሀት/ኢህአዴግ ቢወድቅ ህዝቡ ደም የሚፋሰስበት ምክንያት አይታየኝም። የፖለቲካ ድርጅቶቻችንም ያ አይነቱ ሁኔታ እንዳይፈጠር መመኘትና መጸለይ ብቻ ሳይሆን፤ ተግቶም መስራት ይጠበቅባቸዋል።
በቃለምልልሶቹ ላይ፤ “ምንድነው የምንፈልገው? እንዴትስ ነው የሚመጣው? ያንን ለማምጣትስ ምንድር ነው የምናደርገው?” የሚሉት በቅጡ አልተመለሱም፤ ዴሞክራሲያው ስርአት ከሚለው ድፍን መልስ ውጪ። ትንታኔው በእውነቱ ግልጽና ተጨባጭ ነገር ላይ የተመረኮዘ አይደለም። እዚያች “ዴሞክራሲያዊት” ኢትዮጵያ ላይስ ለመድረስ የትኛውን መንገድ ነው መከተል ያለብን?” የሚለው በበቂ አልተብራራም። በተለይ ዲባቶ ብርሀኑ ልክ እንደ ባእድ ተንታኝ ወይንም እንደሰብአዊ መብት ተሟጋች ነው የተናገሩት። እንደ ጆርጅ አይቴ፤ ወይንም እንደ ሌዝሊ ለፍኮው። በፖለቲካው ውስጥ፤ ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ፤ ቢያንስ ለአስር አመት በሰላማዊ ታጋይነት፡ ለአምስት አመት ደግሞ ሰላማዊ ባልሆነ ታጋይነት እንዳሳለፈ ሰው አይደለም የተናገሩት። ለምሳሌ፤ መምረጥ ያለብን በተቻለ መጠን ብዙ ጥፋት የሌለበትን መንገድ ነው ብለዋል። “ያ መንገድ ግን የትኛው ነው?” የሚለው በደንብ አልተብራራም። የሙስሊሞቹን መነሳሳት ተንተርሰው፤ የተዋህዶ ገዳማትን መደፈር ተደግፈው፤ የመለስን ከፖለቲካና/ምድር ገጽ መጥፋት አልመው፤ ህዝቡን “ተነስ፤ ብዙ እድሎች አመለጡን፤ ይሄ ወሳኝ እድል እንዳያመልጠን፤ እኛ ዘመቻችንን በዚህ አድርገናል፤ አንተም በዚያ አግዘን” የሚል አዋጅ መንገር ነበረባቸው። የሁለት ሰኣት ቃለምልልስም ረዘመ። 45 ደቂቃ በቂ ነበር። ነገሮችን ቁጭ ቁጭ ማድረግ።
በርግጥ፤ ትችት ላይ ማተኮሬ፤ ጥሩው ያው ጥሩ ነውና ብዙ መደጋገም አያስፈልገውም ብዬ ስለማስብ ነው። እንጂ፤ እሳቸው፤ ስለዴሞክራሲና እድገት ዝምድና ወይንም ግንኙነት፤ ስለምእራባዊያን እርዳታ መርህ፤ ኤርትራን ስለመጠቀም ያነሱት ይበል የሚያሰኝ ነው። ወደነዋል። ይሁን እንጂ፤ “ሰዎቹ ቢገረሰሱ ምን ይፈጠራል? የሚገረስስ ስራስ እየሰራን ነው ወይ?” የሚለው ላይ ተስፋ ቆርጫለሁ። ያኔ በየመድረኩ እንደጨቀጨቅኩት ኤርትራ መሽገን ቢሆን ኖሮ፤ ይሄን ግዜ መሰስ ብለን አራት ኪሎ ገብተን ነበር። ምክንያቱም እንደምንም ትግራይን ከተሻገርን፤ ጎንደርና ጎጃም፤ ወሎና ሸዋ ሕወሀትን ጠልቶታልና፤ መንገዳችን አልጋ ባልጋ ነበር። ቢያስቸግረን ወለጋ ነው፤ ወለጋ ደግሞ እነ ከማል ገልቹን ባይቀበልም፤ እነሌንጮ ለታና ዲማ ነገዎ የነከማል ገልቹን አጀንዳ ትንሽ ቀየር አድርገው ይይዙታል። ምን ዋጋ አለው፤ ሰሚ አጣሁ። በዚህ በውጭ አገር ዲባቶ ብርሀኑና ነጋና ድርጅታቸው ግንቦት ሰባት/ጥምረት የመሪነቱንና የማስተባበሩን ስራ ይወስዳሉ ብየ እኔ ራሴ ልከተል አሰፍስፌ ነበር። ለጊዜው አልሆነም። ከማጠቃሌአው በፊት ግን …
ለእሳቱ ኢሳትና ለትንታጉ ሲሳይ
በዚህ ቃለምልልስ ላይ፡ ኢሳት ወይንም ሲሳይም ደክሞ ታይቷል። አንደኛ ነገር፤ ቃለምልልሱ በትኩሱ አልታየም። በርግጥ ከኢሳት ጋር አብሮ በመስራት እንዳየሁት፤ ከሰው ሀይልና አቅም እጥረት የተነሳ፤ ቃለምልልሶች ብዙውን ግዜ ታርመውና ተስተካክለው እስኪቀርቡ አንድም ሁለትም ሳምንት ይፈጃሉ። ይሁን እንጂ እንደዲባቶ ብርሀኑ ያለ የድርጅት መሪ፤ በንደዚህ ያለ ቀውጢ ሰኣት ሲናገር ቃለምልልሱ ቶሎ መቅረብ ነበረበት። ምክንያቱም ነገሮች ቶሎ ቶሎ (ወይንም እንደታማኝ በየነ “ተሎ ተሎ”) ስለሚለዋወጡ፤ ቃለምልልሱ በአፍላው ካልቀረበ፡ ይቆረፍዳልና። ይሄ ቃለምልልስ የቀረበው ቃለምልለሱ በተደረገ በሁለት ሰምንቱ ነው። በዚህ 15 ቀን ውስጥ ደግሞ ብዙ ነገር ተከስቷል። አቶ መለስ ታመዋል ከሚለው ወደኮማ ገብተዋል እንደውም ወደቤልጂየም ተወስደዋል እንደውም ሞተዋል፤ እንደውም ወደአገርቤት ተመልሰዋል፤ ወደሚለው አድጓል። ስለዚህ የዶ/ር ብረሀኑ ቃለምልልስ ወቅታዊነቱ ቀንሷል። በንደዚህ ያለ ሰዓት ኢሳት፤ የፖለቲካ መሪዎችን በትንሽ በትንሹም ቢሆን፤ ሲሆን ሲሆን በሰዓታት ልዩነት ካለበለዚያም በሁለት በሶስት ቀን ማቅረብ ነው ያለበት። እንጂ ንግግራቸው ቋንጣ ከሆነና በሌላ ክስተት ከተዋጠ በሁዋላ መሆን የለበትም። ያ የኢሳት ችግር ነው።
ወደወዳጄ ሲሳይ አጌና ልለፍ። እለት እለት ወደኢሳት የሚመልደው፡ ኢሳት ውሎ ከሞላ ጎደል ኢሳት የሚያድረው፤ በኢሳት ስራ ከመጠመዱ የተነሳ፤ አንድ አመት ከምናምን ቨርጂኒያ ሲቆይ፤ እዚያው አምስት ደቂቃ ወረድ ብሎ ያለውን የዲሲ የከተማ ባቡር እንኩዋን ለማየት ያልቻለው፤ ትጉውና እረፍት የለሹ ትንታግ ጋዜጠኛ፤ ወዳጄ ሲሳይም፡ ዲባቶ ብርሀኑ ለደቂቃዎች ያለ ተከታይ ጥያቄ ሲናገሩ በዝምታ ለቋቸዋል። ሲሳይ በቃለምልልሱ ላይ፤ ዲባቶ ብርሀኑን ብዙ አላስጨነቃቸውም። እንዲያውም መሪ ጥያቄዎችን እየሰጠ እሳቸው እስኪበቃቸው እንዲናገሩ ፈቅዶላቸዋል። ሲስ፤ የወትሮውን አይነት የጋዜጠኛ ስራ አልሰራም። በቃለምልልሱ ላይ ሲሳይ እጁን አጣጥፎ ነው የተመለከተው ብል ይቀላል። አንዳንድ ግዜ ተከታይ ጥያቄ እያስፈለገ ዝም ብሏል። ለምሳሌ ከኤርትራ ጋር በተያያዘ ዲባቶ ብርሀኑ ኤርትራን አለመጠቀም የዋህነት ብቻ ሳይሆን፤ ጅልነትም ነው ብለዋል። ለኔ የምፈልገውን ነው ያሉት። ሲሳይ ግን ጥያቄውን እዚያ ጋር ማቆም አልነበረበትም። ግንቦት ሰባት ከኤርትራ ጋር እስካሁን ምን እያደረገ እንደሆነ ወይንም ምን እያሰቡ እንደሆነ መጠየቅ ነበረበት። በተጨማሪም፤ ያንን ሀሳብ የሚቃወሙትን ሀይሎች አቋም ተመርኩዞ ተከታይ ጥያቄ ማስከተል ነበረበት። በተረፈ ሲሳይ፤ አሁን የምንፈልገው የሚተነትን ወይንም የሚተች ፖለቲከኛ ሳይሆን፤ የሚመራ፡ የሚያሰራ፤ የሚያሰልፍ እንዲሁም የሚያጣድፍ የፖለቲካ መሪ ነው። እንጂ ትንተናውንማ አንተም አለህ። እኔም አለሁ። ሌሎችም አሉ። ስለዚህ እንደድሮህ አፋጥ።
በዚህ ቃለምልልስ ላይ፤ ሲሳይ ተከታይ ጥያቄዎችን ያለመጠየቅ ብቻ ሳይሆን፤ አንዳንድ መነሳት የነበረባቸውን ጥያቄዎች አልጠየቀም። ለምሳሌ የእስልምና እምነት ተከታዮችን ጥያቄ ይመለከታል። በርግጥ፤ ቃለምልልሱ ከተካሄደ በሁዋላ ነው የአወሊያ መስጊድ ሁኔታ የተባባሰው። ይሁን እንጂ በዚህ ላለፉት ስድስት ወራት ከአንድ መስጊድ ጉዳይ ወጥቶ ወደአገር አቀፍ የእስላሞች ጥያቄ ያደገው የሙስሊሞቹ ጉዳይ በቃለ ምልልሱ አልተነሳም። ከተነሳም ዲባቶ ብርሀኑ በደንብ አልሄዱበትም። ወዳጄ ሲሳይ አንዳንዴ ያዝ ማድረግም አለበት። ለማፋጠጥና መልስ ለማሳጣት ብቻ ሳይሆን፤ የተሻለ መልስ ለማግኘት፤ ተመልካቾች የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ ብዙ መጎርጎር ነበረበት። በቃለምምልሱ ላይ ብዙ ግዜ እሳቸው የሚሉትን ብቻ እንደ ሙሉ መልስ እየወሰደ ተጉዟል። ያም ይታረማል ብዬ አምናለሁ። ለዛሬ በቃኝ።
ባጠቃላይ፤ የዲባቶ ብርሀኑም የአቶ አያልሰውም ቃለምልልስ ዘራፍ፤ ጎበዝ ተነስ፤ እንግዲህ ይህ እድል እንዳያመልጥህ የሚልና፤ እነሱም ሌሎች መንግስታትን የሚሞግቱበት፤ ምእራባዊያን መንግስታት በኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ስርአት ገንዘብና ቀለብ በመስጠት እድሜውን ማርዘም ብቻ ሳይሆን፤ ከተቃዋሚ ሀይሎች ጋር ተባብሮ እንዲሰራና እውነተኛ ተሀድሶ እንዲያደርግ እንዲገፋፉ የሚሞግት የሚያሳስብ ሳይሆን፤ የመልካም ስሜት/ምኞት መግለጫ ነው የሚመስለው። ድርጅቶቻችን፤ እባካችሁን፤ ይሄም እድል እንዳያመልጠን አሰሩን። ምሩን። እንደሰላሙ ግዜ ዘና ብላችሁ ሳይሆን፤ እንደመከራ ሰዓት ኮስተር ቆጣ ብላችሁ ቀስቅሱን። አሰልፉን። ባማርኛም፤ በእንግሊዘኛም፤ በኦሮምኛም፤ መግለጫዎችንናና መመሪያዎችን ልቀቁብን። ለአለሙም ሁሉ ልቀቁበት። ወይም ተዉን። እንጂ የጠገብነውን የመለስን/የሕወሀትን አምባገነንት ደጋግማችሁ አትንገሩን።
ያው እኔ ነኝ፤ አለቃ ተክላይ፤ በጁላይ፡ ቶሮንቶ፡ 2012



