ዳዊት ዋስይሁን

የተከበረና ጀግናው አበበ ገላው የአቶ መለስን አንገት ካስደፋቸው አንስቶ የሰውየው ስም በየትኛውም ጎራ ባለ የመገናኛ አውታርም ሆነ የማህበራዊ መረብ እስከ አሁን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በሪኮርድ ማለት ይቻላል በየለቱ የመወያያና የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ እንደሚገኝ የየለት ትዝብት ነው።

 

ጉዳዩን ልዩ የሚያደርገው በየወቅቱ የሚፈጠር አዳዲስ ክስተት ሲሆን፣ በሚገርም ሁኔታም አንዱን ተነጋግረንና አንሸራሽረን ሳንጨርስ ሌላ አዲስ ነገር ይወለዳል። ይኽው እስካሁን አለን ስንባትል፣ በአገር ቤትም በውጭም በሁሉ ቦታ የደራ የሞቀ መነጋገሪያ ሆኖአል። እንደውም ከሰሞኑማ አገር ቤት ያሉ ሥርዓት አደር የእምነት ተቋማት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ለተፈጠረው ሁኔታ ሱባኤ ሊገቡ እያሰቡ እንዳለ የሚያሳዩ ምልክቶች እየታዩ ነው። እንግዲህ ይህ ነው እኔንም ብዕሬን እንዳነሳ ያረገኝ።

 

መነጋገር መደማመጥና መቻቻል የአደገ ማህበረሰብ መገለጫዎች ሲሆኑ፤ እኛም ይህንን በትዕግስት አደረግነው ማለት ወደ አንድ ደረጃ ከፍ ማለታችንን ያሳያል እንደውም እንዲበዛልንና እንዲያድለን ተግተን ልንመኘው ልንለማመደው ያስፈልጋል፣ ነገር ግን በዚህ ሒደት ውስጥ በተለይ የአቶ መለስ ሁኔታ በፈጠረው ጉዳይ ላይ ጠንቀቅ ልንል ያስፈልጋል። ምክንያቱም ትግልን ያማከለና ውጤትን ያነጣጠረ ሥራ መሰራት ስላለበትና በ1997 የታጣው የህዝብ ጥያቄ ድጋሚ አሁንም በወያኔዎች ጮሌነት እንዳያመልጠን የሚነፍሰውን ንፋስ ለይተን ትግላችንን እንድንመራ ከማሰብ ነው።

 

ይህንን ስል እየታገልነው ያለው ሥርዓት ክፋትን፣ ሸርን፣ ተንኮልን፣ መርዘኝነትን፣ ዘረኝነትን፣ መከፋፈልን እንዲሁም በተለይ ትውልድን ባተሌ ማድረግ ለ21 ዓመት በአገራችን ፖሊሲ ነድፎ ያዋቀረና የተከለ ስለሆነ፤ የምንሰማውን ወይም የሚፈጠረው አዲስ ነገር ሁሉ ልንደርስበት ካሰብነውና ካለምነው ለሰከንድ እንኳን ሊያጓትተን አይገባም። እንዲሁም መጠቀም ያለብንን እውቀት፣ ጉልበትና ሃብት አላስፈላጊ ቦታ ላይ እንዳናፈሰው መጠንቀቅ አለብን።

 

በተለይ ዋናውና ኃይለኛው የወያኔ ብልሃት ትውልድን ባተሌ ማድረግ ነው። ይህ ስልት ከዚህ በፊት ያለፉ፣ አሁንም ያሉ፣ ወደፊትም የሚመጡ አስከፊ አምባገነኖች ሁሉ የሚጠቀሙበት ኃይለኛው መሳሪያቸው ነው። ህዝብን የወሬ ሥራ መስጠት፣ ማባተል፣ ህዝብ እንዲምታታ እዚህም እዚያም የተዘበራረቀ መረጃ መልቀቅ፣ የህዝብን የአስተሳሰብ ማዕከላዊነት መበጥበጥ፣ በአንድ መረጃ ላይ ህዝብ ወጥ የሆነ አቋም እንዳይዝና እንዳይፈታተናቸው የመዋከቡን ሥራ ለሰፊው ህዝብ መተው በዚህ ሰዓት እነሱ ለተንኮላቸውና ለዕቅዳቸው መተንፈሻ ጊዜ ስለሚያገኙ የተነሱ ማናቸውንም አይነት አስተሳሰቦችና የለውጥ እንቅስቃሴዎች በእንጭጩ ማፈንን ይችላሉ።

 

ስለዚህ እንግዲህ እዚህ ጋር ነው የኔ ፍርሃት፤ ጠዋት ወዳጆቼን ሰላም ስል አፋችንን የምንከፍተው የበረከት ስምኦን እና የደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ቢሮ በፈጠረልን ሥራ እንጠመዳለን። ሰውየው ሞተ፣ አገር ቤት ገባ፣ ከሳ፣ አበጠ፣ ጀርመን ነው ያለው አይደለም ቤልጅየም … ትክክል ልንነጋገርባቸው ይገባል። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በጀግናው አበበ ገላው ተለኩሶ እየተቀጣጠለ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ በዝባዝንኪ ብትቶ ወሬ ተጠምደን ዕድሉ ሊያመልጠን አይገባም። እንደውም በምንም መስፈርት እነኝህ የጉዳያችን ዋና አጀንዳ ርዕስ ሊሆኑ አይችሉም። ወያኔ በተወናበደና በተምታታበት ሰዓት በተጠናከረና በተቀናጀ መንገድ ለለውጥ ወደፊት ማየት ይገባናል። አሁን ሰዓቱ የበለጠ የሚታሰብበትና ብረቱ እንደጋለ የሚቀጠቀጥበት ወቅት ነው።

 

ስለዚህ በፊት ለፊታችን ሁለት አማራጮች አሉ። አንደኛ በአሁኑ ሰዓት ወያኔ ያላሰበው ትልቅ ክስረት ገጥሞታል። ተምታቶበታል፣ ተርበትብቷል፣ ምን እደሚያረግ ግራ ገብቶታል፣ በትክክል እስከዛሬ ህዝብን እያባተለበት ያለው መንገድ በውስጡ ፈንድቷል። ምክንያቱም አስፈሪው የሥርዓቱ ማዕዘን ተመትቶ የማያስፈራ ደረጃ ላይ ደርሷል። ስለዚህ አሁን ህወሓት በቀን ቅዠት ላይ ነው ያለው፣ ራሱ የፈለፈላቸው ብአዴን፣ ደኢሕዴን፣ ኦሕዴድ፣ … ነገ ምን ሊያረጉ እንደሚችሉ ስለማያውቅ ይፈራቸዋል። ሆድ አደር አባላቱን ይፈራል፣ ከመሬት ያፈናቀላቸው ገበሬውን ይፈራል፣ ህዝቡን ይፈራል፣ እራሱን ይፈራል፣ የውስጥና የውጭ ተቃዋሚዎችን ይፈራል። እንግዲህ እውነታው ይህ ነው።

 

በተቃራኒው ህዝቡ አዲስ ነገር ይጠብቃል፤ ተስፋም ያደርጋል። ለዚህ ሰዓት መፍትሄ የሚሆን የለውጥ እርሾ ይፈለጋል። አዲስ ራዕይ ይዞ ወደዚህ ህዝብ ሄዶ ህዝቡን ወደትግል ለመምራት ከተቃዋሚዎች አንድ መሆንን እና ቁርጠኝነት ይጠበቃል። እስከ ዛሬ ”ደካማ”፣ ”የተከፋፈሉ”፣ ... እያለ ሲያሾፍና ሲቀልድ የነበረው ወያኔ አሁን ግን ይህ በሽታ ከመቅስፈት አጥቅቶታል። ስለዚህ ይህ ታሪካዊ ወቅትና አጋጣሚ ድጋሚ እንዳያመልጠን ሁላችንም ልዩነታችንን ወደኋላ ትተን ለአንዴና ለመጨረሻ በህዝባችን ጠላት ላይ እንነሳ።

 

ወይም ሁለተኛው ምርጫችን እጃችንን ሰጥተን ወያኔ በሚሰጠን የቤት ሥራ እየባተልን ከነሱ ጋር ሆነን የቀጣዩን አልጋወራሽ እንምረጥ። ለእነሱ በተባባሪነት እየሰራንላቸው እኮ ነው፤ ለለውጥ ማሰብ እና መነቃቃት ሲገባን እንቁ የሆነ ጊዜያችንን ስለዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም ወይም ኃይለማርያም ደሳለኝ አነጋገስ ላይ እየለፋን እንገኛለን።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

 


ፀሐፊውን ለማግኘት This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

 

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ