ከአቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ለውጥ ይጠበቃል
ታክሎ ተሾመ
አቶ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያን 21 ዓመት ከገዙ በኋላ ከሚኖሩባት ምድር በሞት ተሰናብተዋል። በሳቸው ሞት ዙሪያ በደጋፊዎቻቸውና በተቃዋሚዎቻቸው መካከል ሳቅና እለቅሶ ሲፈራረቁ መክረማቸው ተሰምተዋል።
ሰው ዘላለማዊ አይደለም። ይፀነሳል፤ ይወለዳል፤ ያድጋል፤ ያረጃል፤ መጨረሻው ሞት ነው። በአገራቺን የእድሜ ባለፀጋ ሆኖ የሚሞት ብዙም አልታየ። ኢትዮጵያዊያን በህይወት የመኖር እድላቸው በአማካኝ 41 እስከ 48 ቢደርስ ነው። በእነዚህ ሂደቶች ውስጥ ጥሩና መጥፎ አጋጣሚዎች መኖራቸው የታሪክ ሃቅ ነው።
ገዥዎቻችን ጨካኞች ናቸው፤ ሕዝብ ገንዘብ እየከፈለ የሚያስተዳድራቸውን ወታደሮች የግላቸው እያደረጉ የራሳቸውን ሕዝብ በጥይት ሳይጨርሱ ያለፉ መንግሥታት በአጋጣሚ እንኳን አንድም አልታየ። እንዲያውም የግድያውን ዓይነት እረቂቅ እያደረጉ የተቀናቃኝ ቁጥር ለመቀነስ በየጊዜው የሚገደለው የሰው ቁጥር አሃዙ ከፍ ያለ ነው። ይህ ወባን፤ ተቅማጥን፤ የሳምባ ነቀርሳንና ርሃቡን ሳይጨምር ማለት ነው።
በአቶ መለስ የግዛት ዘመን የተሰሩ ጥሩና መጥፎ ሥራዎችን በዚቺ አጭር ጽሁፍ ማጠቃለል ጉንጭ ማልፋት ስለሚሆን በዚሁ ማለፍን መርጫለሁ ። ለነገሩ ገዡ የሉም፤ እርሳቸውን ሊተካ የሚችል ጠቅላይ ሚኒስቴር ማግኘት እንዳልተቻለ በኢሕአዴግ ባለሥልጣናት አንደበት በብዙሃን መገናኛ ሲናገሩ መሰማቱ ግን ሌላ ጉዳይ ነው። ይህ ማለት ህወሓት ኢሕአዴግ በአቶ መለስ ዜናዊ ይሁንታ ብቻ እየታዘዘ ይንቀሳቀስ እንደነበር ያመላክታል።
ቀኝም ነፈሰ ግራ አገሪቱ አንድ ጠቅላይ ሚኒስቴር ያስፈልጋታል። በአቶ መለስ ህልፈተ ሞት ምክንያት ኢሕአዴግ የተነፈሰ ጐማ ሆነ። የተነፈሰውን በአየር ለመሙላት እንደማይታሰብ የብዙዎች ግምት ነው። የመንግሥት ባለሥልጣናት በመደናገጣቸው የተነሳ እርስ በርሳቸው አልተማመን ብለው የቡድን ሥራ ፍትጊያ መጀመራቸው የቅርብ ቀን ትውስታ ነው። ም/ጠ/ሚ/ሩ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚ/ር መለስን መተካት አለባቸው የሚሉ ኃይላቸውን እያጠናከሩ ይሞግቱ ጀመር። አሜሪካም እርዳታ ማግኘት ከፈለጋችሁ ም/ጠ/ሚ/ሩ አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስቴር እንዲሆኑ የኢሕዴግን ባለሥልጣናት ያባበሉበት ሰዓትም ተከስቶ ነበር። በሌላ በኩል የህወሓት ባለሥልጣናት የአቶ መለስ የሥራ ድርሻ ከህወሓት እጅ መውጣት እንደሌለበት ደጋፊዎቻቸውን አስተባብረው ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም።
ከኢሕአዴግ ውስጥ የተፈጠረው አዲስ ክህስተት ዱብ እዳ ነው። ተገዥው ሕዝብ መሀል ሆኖ ወይ “የፈጣሪ ያለህ እኛ ያላመጣነው መዓት “በእግዚአብሄር ደርሶ” እርስ በርሳቸው ሊጨራረሱ ነው፤ አገራችን ወደ አላስፈላጊ መንገድ እንዳይከቷት የሚለው የድምጽ ጭምጭምታ ተበራከተ።
የፖለቲካ ድርጅቶች በኢሕአዴግ ውስጥ የተከሰተውን ክፍተት መጠቀም በሚያስችል ዙሪያ ብዙ መስራት እንዳለባቸው የተለያዩ ምሁራን ሲናገሩ ተደምጧል። የፖለቲካ ድርጅቶች ቁጥራቸው የዋዛ ባይሆንም በጋራ የመቆማቸው ጉዳይ ግን አሳሳቢ መሆኑ አልቀረም። ይሁን እንጂ ከአቶ መለስ ሞት በኋላ የሚተካው ማን ነው? በሚለውና ስለአሟሟታቸው በየድረ-ገጾች ጽሁፍ እያወጡ ማስነበባቸው ይታወሳል። አንዳንዶች የሽግግር መንግስት ባስቸኳይ ያሉበት ወቅትም ነበር። ከዚህ አለፍ እያሉ የውጭ መንግሥታት እውቅና እንዲሰጣቸው አሜሪካ ውስጥ የተዋቀረው ሽግግር ምክር ቤት ለአውስትራሊያ ጠ/ሚ/ ር ለአቶ ቦብ የተፃፈውን ዌብ ሳይት ላይ መመልከት ተችሏል።
ጥሩ እውቅናው ባልከፋ ግን የውጭ አገር መንግሥት ቢፈቅዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ካላመነበት ይቀበላቸዋል ወይ? የሚለው በጥሞና የታሰበበት አልነበረም። ምክንያቱም ወሳኙ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነውና ። የዚህ መንግሥት እድሜ ያላጠረው በተቃዋሚዎች የእርስ በርስ መናቆር መሆኑ ግልጽ ነው። አንድነት ቢኖር ኖሮ አቶ መለስ ከሞመታቸው በፊት ጉድ ያዩ ነበር።
አቶ መለስ ዜናዊ 21 ዓመት ብቸኛ የሥልጣን ባለቤት ነበሩ። የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎችም ሆነ ሕዝብ 21 ዓመት ያልደፈራቸውን አቶ መለሰን እግዚአብሄር ባሰበው ቀን “ከምድራዊ የምቾት ኑሮ” አንስቷቸዋል። በሞት መመፃደቅ ባህላችን ስለማይፈቅድ ነፍሳቸውን ይማር ከማለት ውጪ እርማን መጨመር አግባብነት የለውም። በእሳቸው ሞት የሚደሰቱም ሆኑ የሚያለቅሱ የየራሳቸው ምርጫ ይሆናል።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴራችን ከሞቱ በኋላ በምን ዓይነት ይኖሩ ይሆን የሚለው የሚያስጨንቅ አይሆንም። በገዥዎቻችን ከተገደሉ ቤተሰቦቻችን ውስጥ አንዳቸውም ቢሆኑ በምን ዓይነት እንደሚኖሩ ወረድ ብለው የነገሩን ምስጢር የለም። “ሥራ ለሰሪው ሾህ ላጣሪው” እንዲሉ አቶ መለስ ወደፊት በምን ዓይነት ይኖሩ ይሆን የሚለው የሚያስጨንቅ አይደለም።
በዚህ ጠቢብ ሥራ መግባት የራስን ሃጢያት ማብዛት ይሆናል። ሳጥን ውስጥ ፊታቸው ታይቶ አዲስ አበባ ውስጥ ተቀበሩ አልተቀበሩ ሊያሳስበን አይገባም። የተቀበሩበት አካባቢ በወታደር ተጠበቀ አልተጠበቀ የእኛ ችግር አይደለም። የሞቱት ጠቅላይ ሚ.ር እንዲህ ነበሩ በማለት ጊዜ የሚባክንበት ወቅት አይደለም። ጥሩም ሆነ መጥፎ ሰርተው አልፈዋል፤ በቃ።
ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ወደፊት አገሪቱን እንዴት በሰላም መምራት ይቻላል? እንዴት ሥልጣ ከሕዝብ እጅ ይገባል በሚለው ዙሪያ አንዱ ሌላውን ሳይጐሽም በመቻቻል በመመካከር በአገሪቱ ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ብዙ የቤት ሥራ ይጠይቃል።
አቶ መለስ አልሞቱም ብሎ ሕዝብ አልዋሸም፤ አልቅሶ ቀብሯቸዋል። እርሳቸውን ማን ይተካ የሚለው ውዝግብም እልባት አግኝቶ ምክትል ጠ/ሚ/ሩ አቶ ኃ.ማርያም ደሳለኝ የጠቅላይ ሚኒስቴርነት ማዕርግ ማግኘታቸውን ሰማን። እሰየው ከነገር ሰውረን፤ ሹመት ያዳብር በሚል ቀጣዩን እርምጃ መጠበቅ ነው።
አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ምን ዓይነት የሥልጣን ኃላፊነት ይኖራቸዋል የሚለውን ጥያቄ ለራሳቸው እንተወው። አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ሙሉ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደተባሉ በሕዝብ መገናኛ ያሰሙትን ንግግር ስናስታውስ
“ከፊት እናንተ እየመራችሁኝ “ከኋላ እኔ እየተከተልኩ” ከዚህ በፊት አቶ መለስ የጀመሯቸው ሥራዎች ምንም ሳይሸራረፉ፤ ሳይሰረዙ የተጀመሩ ሥራዎችን ተግባራዊ እናደርጋለን ነበር ያሉት። አዎ የተጀመሩ ሥራዎች ተግባራዊ መሆን አለባቸው ጥሩ እንስማማ።
ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ፊት ሆኖ አገርና ሕዝብ ካልመራ እንደ ጂራት ተከታይ ከሆነ ሥልጣናቸው የውስጥ ችግር አለበት ማለት ነው። አቶ መለስ በጠቅላይ ሚኒስትርነት አገር ሲመሩ ከፊት እየተጓዙ ቀደመው ሌላው እየተከተላቸው 21 ዓመት ዘልቀዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለውጥ እንዲመጣለት ድፍን 21 ዓመት ሙሉ ድምጹን ሲያሰማ ቆይቷል። የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስቴራችን አቶ ኃ/ማርያም ከሚፈተኑበት ሰዓት ላይ ናቸው። ሕዝብ ከሳቸው ብዙ ነገር ይጠብቃል። የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶችም እንዲሁ በአገራቸው ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ለማስከበር በተቃውሞ ላይ ናቸው። ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ተመካክረው አገሪቱን ወደ ተሻለ ጐዳና ለማስኬድ ፍላጐታቸውን እየገለጹ ነው። በዚህ ሁኔታ ለውጥ ይመጣ ይሆናል የሚለው የብዙዎች ምኞች ነው።
ይህ ለውጥ በአቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ እጅ ያለ ይመስለኛል። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ቅን አሳቢ መሆናቸውን በተግባር ለማስመስከር በዋናነት መሰረታዊ ችግሮች በሚባሉት ላይ ማተኮር ይጠበቅባቸዋል።
• ካቢኒያቸውን በመሰረቱ በማግስቱ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞችን ሲፈቱ፤
• በአገርም ሆነ ውጪ ከሚኖሩ ፖለቲካ አድርጅቶች ጋር ተስማምቶ አገሪቱን በጋራ ለመምራት እንደተለመደው የይስሙላ ጥሪ ሳይሆን ለተግባራዊነቱ ቅድመ ዝግጅት ማለት መብቶቻቸውን ሲያመቻቹ፤
• በራሱ አገር ላይ ሽብር ሊፈጥር የሚችል ኃይል በሌለበት ሁኔታ ተቃዋሚዎችን ለማጥቃት ሲባል ከዚህ በፊት በህግ የተደነገገውን የፀረ-ሽብር አዋጅ ሲሽሩ፤ ከሁለት የተከፈለው ሲኖደስ ወደ አንድ የሚመጣበትን መንገድ ሲያመቻቹ፤
• በአገዛዙ በደል ውጭ የተሰደዱ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው ተመልሰው በእውቀታቸው ሕዝባቸውን እንዲያገለግሉ ዋስትና ያለው ጥሪ ሲያደርጉ፤
• ሕዝብ ያለ ወታደር ጣልቃ ገብነት የመናገር፤ የመፃፍ፤ የመቃወም፤ የመደገፍ፤ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ወዘተ ሙሉ መብቶች ሳይሸራረፉ ዴሞክራሲን በይፋ ሲያውጁና ለተግባራዊነቱ ዋስትና ሲሰጡ፤
• ነፃ ፕሬሶች በፈለጉት ብዕርና ቋንቋ የመፃፍ መብቶቻቸው ነፃ ስለመሆኑ፤ መገናኛ አውታሮች ከመንግስት ቁጥጥር ነፃ ሆነው እውነተኛ መረጃ ለሕዝብ ማቅረብ የሚችሉ ስለመሆናቸው አቋማቸውን በግልጽ ለሕዝብ ማሳወቅ የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል። ነገር ግን ሁሉን የፖለቲካ እስረኞች ሳይፈቱና ከፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ተግባብተው መቀጠል ካልቻሉ ከወዲሁ የሕዝብ ተቃውሞ ሊገጥማቸው እንደሚችል ነጋሪ ጠንቋይ የሚያስፈልጋቸው አይመስለኝም።
ኢሕዴግ ጥሩም ሆነ መጥፎ ሥራ መስራቱ አይካድም። ያለፈው አልፎ ይቅር ተባብሎ አገሪቱን ወደ ተሻለ ጐዳና ለመምራት ባለሥልጣናት ቀናነትን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል። የህወሓት ደጋፊዎች ጉዳይም በዝምታ የሚታለፍ አይሆንም። በአቶ መለስ ሞት ሳቢያ በጣም የተደናገጡ በየአደባባዩ ታይተዋል። መደገፍና መቃወም መብት ነው። ነገር ግን ለምን እንደሚደግፉና ሌሎችን ለምን እንደሚቃወሙ በውል መለየት ይኖርበታል። ከአገርና ከሕዝብ ጥቅም አኳያ ሲታይ 21 ዓመት አንድ ፓርቲ በሥልጣን ተቀምጦ መሪው በህመም ቢሞት “ነፍስ ይማር” ማለት ሲገባ በየአደባባዩ ሁከት መፍጠር አግባብነት የለውም። ልብ ልንለው የሚገባን ጉዳይ ቢኖር በለቅሶም ሆነ በርግማን እግዚአብሄር የወሰነውን ለማስቀረት አንድም ኃይል አለመኖሩ ነው።
ታዲያ በዚህ እንዲት ሰው ይጣላል? ለማንኛውም ጭፍን ደገፋ አያዋጣም። ለሁላችን የሚበጅ በሰላም እንዴት እንኑር በሕዝብ የተመረጠ ሕጋዊ የሆነ መንግስት እንዴት እናግኝ፤ በሚለው ጊዜ ማጥፋት ሲገባን የከሌ ወገን መባልን ምን አመጣው ? ኢትዮጵያ እኮ የሁሉም እንጅ የተወሰኑ ሰዎች ግኝት አይደለችም።
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስቴራችን መልካም የሥራ ዘመን ይሁንለዎ፤ ሕዝብ ሊመርቀው የሚገባ ሥራ እንዲሰሩ እግዚአብሄር ይርዳዎት
ከዘመኑ ወረርሽኝ ለጉሜ በሽታ ይጠብቀዎ አሜን!
አስተያየት ለመስጠት This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.