አቶ ስዬ አብርሃንና ፕ/ር መረራ ጉዲና በሚኒሶታ ከተማ Siye Abreha and Prof. Merera Gudina public meeting in Minnesotaያሬድ አይቼህ

በሚኒሶታ ከተማ የአቶ ስዬ አብርሃንና የፕ/ር መረራ ጉዲናን ንግግሮች ፓልቷክ ዱቅ ብዬ ሰማሁ። ሁለቱም የዴሞክራሲ ታጋዮች ያቀረቡዋቸው ነጥቦች ግሩም ናቸው። በተለይ አቶ ስዬ ከስብሰባው ታዳሚዎች አንዱ ከነበሩት ከአቶ ጌዲዮን የቀረበላቸውን ጥያቄ አስከትለው ያነሱዋቸው ጉዳዮች እጅግ በጣም ማረኩኝ። ለካስ የበሰሉ የፓለቲካ ታጋዮች ኢትዮጵያ አፍርታለች! አቶ ስዬ አብርሃ በአንድ ጎኑ ብቻ የበሰለ ሰው አይደሉም። አቶ ስዬ በሁለቱም ጎኑ ተገላብጦ እንደበሰለ አንባሻ ናቸው።

 

በአገራችን ፓለቲካ ጥልቀት ያለው፣ አርቆ የሚያስብ፣ ነገሮችን ከሁሉም አቅጣጫ የሚመለከት፤ የጦርነትን አስከፊነት፣ የአምባገነናዊነት ስርዓትን ፍርደገምድልነት፣ የደርግን ፋሽስትነት በግል ከቀመሱ ኢትዮጵያውያን አንዱ አቶ ስዬ ናቸው።

  

“የዛሬ 40 ዓመት የተከሰተው ላይ ስንወዛገብ አሁን ፊታችን ያለው አጋጣሚ አያምልጠን ፥ ድርድር ከምትወደው ሰው ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ከምትጠላውም ሰው ጋር ነው” እያሉ አቶ ስዬ ሲማጸኑ ሰምቼ መንፈሴ በጣም ተጠገነ።

  

አርቀው ሚያስቡ፣ የአገራችንን አክሳሪና የዜሮ ድምር ፓለቲካዊ ባህል በግል የቀመሱ፣ ነገር ግን የፓለቲካ ባህላችን መንፈሳቸውን ያልሰበረው፣ ጽናታቸውን ያልሸረሸራቸው እንደ አቶ ስዬ አይነት ፓለቲከኞች መኖራቸው ለአገራችን ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋና ትልቅ ጸጋ ነው።

  

በአገራችን አባባል “የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል” ይባላል፤ ፓለቲካችን እርጋታ አንጂ ግርግር አይጠቅመውም፤ የሰከነና አርቆ የሚያስብ አስተሳሰብ እንጂ ቂም፣ ቁርሾ እና በቀል አይጠቅመንም።

 

የአገራችን የዋጋ ንረት 21% በመቶ በሆነበት ወቅት፤ ኢህአዴግ እረኛ የሌለው መንጋ ሆኖ በደቦ በሚመራበት ዘመን የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች አንዱ አንዱን የማዳከም ዝንባሌ፣ አምባገነኑን ኢህአዴግን መጥቀም ነው። ወቅቱ የሚጠይቀው ትብብር እና ትኩረት ነው። እንተባበር፣ እንደጋገፍ።

 

አቶ ስዬ፦ ከወጣትነት ጀምሮ እስካሁን ለከፈሉት ክቡር መስዋዕትነት፤ ለግል መርሆ ላለዎት ታማኝነት፤ በመከራ ለመጽናትዎ፤ ለዘለቄታዊና አገራዊ መፍትሄ ሲሉ ለቁርሾና ለቂም በቀልነት ላለመንበርከክዎ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ወንድሞ ከልቤ አመሰግናለሁ!! ይበርቱ! ይቀጥሉ! ይግፉ!


ያሬድ አይቼህ (ኦክቶበር 3 ፥ 2012)

አድራሻዬ፦ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ