ግርማ ካሳ

በምርጫ ዘጠና «ይህ ሕዝብ የሚፈልገው የመጣህበትን መሰረት አይደለም። የመጣህበትን ብሄር አይደለም። የምትሰራለትን ስራ ነው» የሚለው፣ አቶ በረከት ስምኦን ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ካደረጉት ቃለ ምልልስ የተቀነጨበ ግሩም አባባል ነው። ከአንድ ከኢሕአዴግ አመራር አባል ብዙ ጊዜ የማንሰማው አባባል!!!

ከአንድ አመት በፊት ለሶስት ሳምንታት አሜሪካን ለመጎብኘት የመጣ፣ አንድ ሰው በወቅቱ ያስደሰተኝ፣ አንድ ወሬ አወጋኝ። አቶ መለስ የሚመሩት የኢሕአዴግ ማእከላዊ ኮሚቴ ይሁን ጠቅላላ ጉባኤ፣ ስብሰባ አድርጎ በነበረ ወቅት የሆነ ነገር ነው። ከስብሰባው መካከል ከዚህ በፊት ተነስተው የማያውቁ ጥያቄዎች መጠየቅ፣ ቀርበው የማያውቁ አስተያየቶች መሰጠት ጀመሩ። «ለምን የብሄር ብሄረሰብ እና የዘር ነገር ላይ እናተኩራለን? ሕዝቡ ይሄን አይፈልግም። አንድነትን ነው የሚፈልገው? ለምን የስራ ሃላፊነት በሞያ ብቃት ሊሆን ሲገባው በዘር ይሆናል? ለምን ብቃት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ከዚህ ብሄር አይደላችሁም ተብለው በአንዳንድ ክልሎች እንዳይሰሩ ይታገዳሉ? ይሄን ኢሕአዴግ ማስተካከል አለበት …ወዘተረፈ » የሚሉ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ነበሩ ሲቀርቡ የነበሩት።

ታዲያ አሁን አቶ በረከት «ይህ ሕዝብ የሚፈልገው የመጣህበትን መሰረት አይደለም። የመጣህበትን ብሄር አይደለም። የምትሰራለትን ስራ ነው» ሲሉ ገረመኝ። «ከአንድ አመት በፊት የደረሰኝ መረጃ ትክክለኛ ነበር ማለት ነው?» ብዬ እራሴን ጠየኩ።

ይሄ ብቻ አይደለም። የአቶ መለስ ወዳጅ እና ልዩ አማካሪ የነበሩ፣ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ለኢሕአዴግ ተሟጋችና «ጠበቃ» ተብለው ይቆጠሩ ከነበሩ ጥቂት ግለሰቦች መካከል በቀዳሚነትና በዋናነት የሚጠቀሱ አሜሪካዊው ፖል ሄንዚ ነበሩ። እኝህ ሰው በምርጫ ዘጠና ሰባት ወቅት በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ኢሕአዴግን የመከሩት አንዳንድ ምክሮች ነበሩ።

«ከ1991 በሁዋላ የተፈጠረው የፖለቲካ ስርዓት ብዙ ያልተጠና (Ad Hoc) እና ደርግ ሲወድቅ የነበረውን ሁኔታ ያንጸባረቀ ነበር። ነገር ግን የማይቀየርና የማይሻሻል ተደርጎ ሊወሰድ አይገባውም። ለምን ብዙ ጠቃሚ ያልሆኑ ሁኔታዎች እንዲከሰቱ አድርጓል» በማለት ነበር ፓል ሄንዝ የጻፉት።

ጠቃሚና አላስፈላጊ ካሉዋቸው ነጥቦች መካከል፣ በኢሕአዴግ ስርአት ከመጠን ያለፈ ጊዜና ጉልበት ለብሄር ብሄረሰቦች በደልና ብሶት መሰጠቱ እንዲሁም የትኩረት አቅጣጫው ከልክ ባለፈ መልኩ በብሄር ብሄረሰብ ወይንም በዘር ላይ መሆኑ ይገኙበታል።

በዚህም ምክንያት ፕል ሄንዝ፣ ኢሕአዴግ በዘር ላይ ከማተኮር በአንድነት ላይ ማተኮር እንዳለበት፣ በዘር ላይ የተመሰረቱ ድርጅቶች ግንባር መሆኑ ቀርቶ፣ የኢትዮጵያውያንን በሙሉ ጥቅም ለማስጠበቅ የቆመ አንድ ሕብረ ሄራዊ ፓርቲ ቢሆን መልካም ሊሆን እንደሚችል ነበር የገለጹት።

"If a majority of EPRDF leadership agrees that the entire party structure of Ethiopia should be changed, they would be well advised to pre-empt Kinijit by announcing the transformation of EPRDF into a party with a new name and new character. Among names that could be considered most appropriate might simply be "Ethiopian Democratic Party (EDP)" which would declare adherence to a platform for protecting the unity and integrity of the country, furthering its development and modernization in all respects with a firm commitment to democracy." ነበር ያሉት እኝህ ምሁር።

በፕል ሄንዝ አስተያየት ላይ የራሳቸውን ተጨማሪ አስተያየት የሰጡት በውጭ አገር የሚኖሩ አቶ ሳሙዔል ገብሩ ሲጽፉ «The notion of placing one's ethnic affiliation above one's status as being an Ethiopian has plagued the country's political development. Ethiopians tend to declare each other as either "the oppressed" or "the oppressor" without recognizing that at one point in our history we were all oppressed and oppressors » በማለት የአቶ ፖል ሄንዚ አስተያየቶች ይጋራሉ።

ኢሕአዴግ፣ ከአራት በዘር ላይ የተደራጁ ድርጅቶች ስብሰብ መሆኑ ከበፊትም እንደማይዋጥላቸው የገለጹት አቶ ሳሙኤል «I would rather have the EPRDF as a political party and that be it. Too much concentration on one's ethnicity further divides Ethiopia's unity» ሲሉ ኢሕአዴግ ማሻሻያዎች እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበውም ነበር።[1]

እንግዲህ ኢሕአዴግ በምርጫ ዘጠና ሰባት የተመለከተውን የሕዝቡን ስሜት አስተውሎ፣ ኢትዮጵያውያን የተዋለዱ፣ የተደባለቁ፣ ለመቶ አመታት ተከባብረው ተዋደው የኖሩ መሆናቸውን ተረድቶ፣ እንዲሁም እንደ ፖል ሄንዝና እና አቶ ሳሙኤል ገብሩ ያሉ ያቀረቡትን አስተያየቶች ከግምት በማስገባት፣ ደረጃ በጠበቀ መልኩ ኢትዮጵያውያንን በሚያስተሳሰርና በሚያቀራረብ አጀንዳዎች ዙርያ መስራት ብዙ ይጠበቅበታል።

እርግጥ ነው እንደምንሰማው በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሕወሃት፣ ኦህዴድ፣ የአማራውና የደቡብ ድርጅቶች እንደሚዋሃዱ ነው። ነገር ግን ከአራት ድርጅቶች ግንባርነት ወደ አንድ ፓርቲ መዞር በራሱ መሰረታዊ ለውጥ ሊሆን አይችልም።

መሰረታዊ ለውጥ ማለት እነ ፓል ሄንዚ እንደመከሩት ኢሕአዴግ የአገሪቷን በዘር ላይ ያተኮረ ሕገ መንግስት እንዲሻሻል በማድረግ ዙሩያ ቀዳሚ በመሆን እንቅስቃሴዎች ሲጀምር ነው።

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስተር ኃይለማሪያም ደሳለኝ፣ አቶ መለስ ዜናዊ የነበራቸውን ፖሊሲዎች እንደማይለውጡ እየነገሩን ነው። እርግጥ ነው በሶማሊያ በሱዳን የሚደረጉ የኢትዮጵያ ጥረቶችን፣ አባይን በመገንባት እንዲሁም ሌሎች በርካታ የልማት እንቅስቃሴዎችን በማስፈጸም ዙሪያ የአቶ መለስን ጅማሮዎች መቀጠሉ ተገቢ ነው።

ነገር ግን፣ የአቶ መለስን ዜጎችን በፍርደ ገምድልነት የማሰርና ዜጎችን በሽብርተኝነት የመፈረጅ፣ ነጻ ጋዜጦችን የመዝጋት፣ የዴሞክራሲ ተቋማት በአንድ ፓርቲ ቁጥጥር ውስጥ እንዲሆን የማድረግ የመሳሰሉ የአቶ መለስ የተሳሳቱ ፖለቲካዎችን እና አሰራሮችን መቀየርና መለወጥ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ እነ ፕል ሄንዚ እንደመከሩት ጠቃሚ የፌዴራልም ሆነ የክልል ሕገ መንግስቶች ላይ ማሻሻያዎች ማድረግ ይኖርባቸዋል።

እርግጥ ነው አቶ በረከት እንዳሉት «ይህ ሕዝብ የሚፈልገው የመጣህበትን መሰረት አይደለም። የመጣህበትን ብሄር አይደለም። የምትሰራለትን ስራ ነው»። የዚያኑ ያህል ደግሞ ይህ ሕዝብ የሚያገለግለውና የሚያከብረው መሪና ደርጅት ነው የሚፈልገው። አዲሱ የአቶ ኃይለማርያም ኢሕአዴግ የአቶ መለስ ኢሕአዴግ የጀመራቸውን ጥሩ ስራዎች ያዝ፣ ጎጂ የሆኑትን ደግሞ ጣል አድርጎ ሕዝቡ የሚፈልገውን አይነት ድርጅት ቢሆን፣ ለኢሕአዴግም ለኢትዮጵያም የሚጠቅም ነው ባይ ነኝ።

እንግዲህ እግዚአብሔር አራት ኪሉ ላሉቱ ማስተዋልና ልቦና ይስጣቸው!

[1] http://smgebru.blogspot.com/2008/06/ethiopia-henzes-views-on-eprdf.html#!/2008/06/ethiopia-henzes-views-on-eprdf.html


ግርማ ካሳ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ