ይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ

ሉሉ ከበደ (ጋዜጠኛና ደራሲ)

ከሀያ አንድ ዓመታት የሸፍጥ፤የውሸት፤የተንኮል እና የጭካኔ አገዛዙ በሗላ በኢትዮጵያ ህዝብ እንቢ ባይነትና በሟቹ አንባገነን “እኛ እንጂ የሚገዛችሁ የለም” የተግባርና የስነልቡና ጦርነት፤በአሜሪካኖች፤ በእንግሊዞች ወይም ደሞ በኔቶ ያየር ድጋፍ ሳይሆን በእግዚአብሄር ጣልቃ ገብነት፤መለስ ዜናዊ የፈጀውን ፈጅቶ ገና ሳይበቃው፤ ያን ሁሉ በህዝብ ላይ የተሸከመውን ንቀት፤ ያን ሁሉ በአማራ ላይ ያረገዘውን ጥላቻ፤ ያን ሁሉ ለዛ የሌለው ንግግር እንደተጫነ፤ የልቡን እስከመጨረሻው ሳያደርስ ኢትዮጵያን ሳይበትንና የትግራይን መንግስት በይፋ ሳያውጅ እንደወጣ በዚያው ቀረ። የእግዚአብሄር ፍርድ ይግባኝ የለውም። እሱ የፈረደባቸው የእስር ግዜያቸውን ሳይጨርሱ፤ ሞት የፈረደባቸውም ተራቸውን በመጠበቅ ላይ እንዳሉ፤ ለምን እንደቀደማቸው የሚታወቅ ነገር የለም።ቀደማቸው።ይገርማል።

 

ወያኔ ማንን ይተካ ይሆን የሚለው ብዙ ካሳሰበና ካስጨነቀ እነሱንም በዝግ ቤት ብዙ ካነጋገረ በሗላ በገመቱትም ባልገመቱትም የሀሳብ ልዩነት ላይ አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ የአስተዋዩ መሪ ሙሉ ስልጣንና ወንበር ተመረቀላቸው ተባለ። ሆነም። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም እንኳን ደስ ያለዎት።

 

ከዚያ በሗላ ሌላ ነገር ይገመት ጀመር እየተገመተ ነው። እኒህ ሰው እግዚአብሄርን የሚያመልኩ ናቸው። በእግዚአብሄር የሚያምኑና የሚተማመኑ ናቸው። ለውጥ ያመጣሉ። ጀግና መሆን አለባቸው። እግዚአብሄን ካመነ ሰው የበለጠ ጀግና የለም። ለእውነት ይሞታሉ። ስለዚህ አቶ ሓይለማሪያም የሚያምኑትን ጌታ ይዘው በኢትዮጵያ ታሪክ ይሰራሉ። የሚለው ወገን እንዳለ ሆኖ ሌላው ደሞ ሰውየው አድርባይና አይተነው ጊዜን(ኦፖርቹኒስት) ባይሆኑ ይህን ያህልም ከወያኔ ጋር አይቆዩም ነበር። መለስ ሄደ ሀይለማሪያም ተተካ ለውጥ ከወያኔ አይጠበቅም። ከግራም ከቀኝም ከፊትም ከሗላም ከታችም ከላይም ወያኔ በሀይለማሪያም ዙሪያ አሰፍስፎ እሱን ለምልክት አስቀምጦ ስራውን ይሰራል እንጂ የመወሰኑን ስልጣን ሊሰጠው አይችልም። ለውጥ አይመጣም።

 

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እኔም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ የራሴ የሆነ ህልም አለኝ። “አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ እራሳቸውን ሆነው ብቅ ይላሉ።” ይለኛል ህልሜ። የሚወዱት መጽሀፍ ቅዱስ የሚያመልኩት ጌታ የኢትዮጵያን ህዝብ ከመከራ ሊያወጣ የተላከ የክርስቶስ ወታደር ያደርግዎታል ብየ አስባለሁ።

 

ከዚያ በፊት ግን እኔና እርሶ የማንጣላበትን እውነታ ልናገር ግድ ይለኛል።ላለፉት ሀያ አንድ ዓመታት ወያኔን አጅባችሁ እነሱ ሲሰርቁ፡ አነሱ ሲዘርፋ፤ እነሱ ሲገሉ፤ እናንተ በዙሪያቸው ተጋርዳችሁ ስትከልሏቸው፤ ግደሉ ሲሏችሁም እየገደላችሁ፤ ያንዘር ይህንዘር አባሩ ሲሏችሁም እያባረራችሁ፤ ያማራ ተወካይ ነን፤ የኦሮሞ ተወካይ ነን፤ የደቡብ ተወካይ ነን እያላችሁ ወያኔ ይንን ሁሉ ግድያ ጭፍጨፋና ዘረፋ በሀገርና በህዝብ ላይ ሲያካሂድ በመተባበራችሁ፤ ለማይረባ ስልጣንና ጥቅማጥቅም ህሊናችሁን ሸጣችሁ የጥፋት ተካፋይ መሆናችሁ የሚያነጋግር ጉዳይ አይደለም። እርግጥ ነው በሬ ካራጁ ሆኖባችሁም ሊሆን ይችላል። ስልጣንና ጥቅም ስትቀላውጡ፤ስላስጠጓችሁ፤ስለፈጠሯችሁ፤ ሊያጠፏችሁ ስለሚችሉ ወይም ደግሞ ከላይ እንደጠቀስኩት የማይረባው ስልጣንና ጥቅም አጓግቷችሁ ወያኔ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ለፈጸመው ወንጀል ሁሉ ተካፋይ ሆኗችሗል። ራሳችሁን ለህሊና ባርነት ዳርጋችሁ ህዝቡንም ባርነት ስር አውላችሁታል።

 

አቶ ሀይለማሪያም፤ ዛሬ ግን በምንም መልኩ ይሁን ባንድ አጋጣሚ ዋናው የስልጣን ቁልፍ ከወያኔ እጅ ወቶ እናንተ ጋ ደርሷል። የአማራ ነን፤ የኦሮሞ ነን፤ የደቡብ ነን ለምትሉት የወያኔ ፍጡራንና አጃቢዎች ሁሉ ነው መልክቴ። ባለፈው ስህተታችሁ ተጸጽታችሁ፤ የተገነዛችሁበትን የፍርሀት ከፈን ቀዳችሁ፤ እንቢ ለሀገሬ እንቢ ለህዝባችን በሉ። ከወያኔዎች ጋር እኩል ሰው መሆናችሁን በድፍረት ንገሯቸው። ተጋፈጧቸው። አንድ ሁኑባቸው። ለኢትዮጵያ ህዝብ እንጂ ለወያኔ አንታዘዝም፤ አንታመንም በሏቸው።

 

ባልታሰበ ጊዜና ሁኔታ ሊያጠፋችሁ የሚችለው ሰው ዛሬ እስከወዲያኛው አሸልቧል። እነስብሀት ነጋ እነበረከት ስምኦንና ሌሎቹም የወያኔ እብዶች የሚያመጡባችሁን እናንተ በህብረት መመለስ ከተሳናችሁ አሁንም የቁም ሙታን ናችሁ። ከንግዲህ የጌታና የሎሌ ግንኙነታችሁ መቆም አለበት። የኢትዮጵያ ህዝብም ከጎናችሁ አንደሚቆም ጥርጥር የለውም።

 

የአማራን የበላይነት ነው የተዋጋን የምትሉ ሰዎች፤ የትግራይ ህዝብ የማይፈልገውን፤ ያልጠየቀውን፤ ያላሰበውን፤ እነመለስ ዜናዊና እነ ስብሀት ነጋ ባለፉት ሀያ አንድ አመታት የትግሬን የበላይነት ገንብተው፤ ኢትዮጵያዊን ሁሉ ቁልቁል ማየት ሲጀምሩ፤ ይህንን ሁሉ የወያኔ ደናቁርት ጥጋብና ትምክህት እንዴት ቻላችሁት? የትግራይ አርሶ አደር የማይመኘውን ህዝቡ የማይሞክረውን የትግራይ ወንበዴዎች ከናንተ ጋር ተጋግዘው እየገነቡት ያለውን የበላይነታቸውን ለመሸከም ጫንቃችሁ እንዴት ቻለ? ከንግዲህ በሗላ ግን ከወያኔ ጋር አየተባበራችሁ ወይም ደሞ በነሱ እየታዘዛችሁ መለስ ዜናዊ ጀምሮ ያልጨረሰውን ጥፋት እንቀጥላለን ካላችሁ የኢትዮጵያ ህዝብ ራሱን ለማዳን ይነሳል።

 

አቶ ሐይለማሪያም ደሳለኝ የመለስ ዜናዊን አነጋገርና ቋንቋ እንደትያትር ተማሪ እያጠኑ  እስካሁን ባሰሙት ንግግር ላይ በመለማመድ ላይ ናቸው። እንደበቀቀን እየደገሙ እየደገሙ ሲናገሩ ተሰምተዋል። ይህንን እኔ የምመለከተው ባንዲት ጀንበር ሰው ተነስቶ አርበኛ አይሆንም። አቶ ሀይለማሪያምያ ጠላት የሚናገረውን የሚወደውን ቋንቋ መናገር ቀጥሎ ለሚወስዱት እርምጃ መንገድ ሊከፍት ይችላል።ግን “የሱን ምኞትና ህልም ከግብ አደርሳለሁ” የሚሉት ነገር ባርነቱን በርሶና በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ሊያጠብቁ መዘጋጀትዎን የሚጠቁም በመሆኑ የጤናና የእየሱስ ክርስቶስ ልጅ ስራ ሊሆን አይችልም።

 

እኔ ያንን ሳይሆን ህልሜ የሚያደርጉትን ሲያሳያየኝ እንዲህ ይለኛል።

ብሄራዊ እርቅ ይጠራል። ባለፉት ሀያ አንድ አመታት ወያኔ ሆን ብሎ ዘርን ከዘር በማጋጨት የራሱንም ጦር በማሰማራት ይህ ነው የማይባል እልቂት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ አድርሷል።ወያኔ እንደጠበቀው በከፋ መልኩ ባይሆንም ወገን በወገን ላይ ቅሬታ አድሮበታል። የትግራይ አርሶ አደር ልጆች አንዋጋም ብላችሗል ተብለው፤ ተጨፍጭፈዋል። በወያኔ ሚሊሺያ አኙዋክ ተጨፍጭፏል። አማራ ኦሮሞ ሶማሌ የደቡብ ህዝብ እያንዳንዱ የህብረተሰብ ከፍል ደሙ ያላግባብ ፈሷል። የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች አባላት ጋዜጠኞች ታስረዋል፤ ተገለዋል።ከሀገር ተባረዋል።ተሰደዋል። ሰላማዊ ሰልፈኞች ኢሰብዓዊ በሆነ ሁኔታ ተጨፍጭፈዋል። ይህ ሁሉ ጠባሳ ሊሽር የሚችለው ብሄራዊ እርቅ ሲጠራ ብቻ መሆኑን ጠቅላይሚንስትር ሀይለማሪያም ያምናሉ።

 

በእስር ላይ ያሉ ጋዜጠኞች፤ የፖለቲካ መሪዎች፤ ባጠቃላይ የህሊና እስረኞች ባስቸኳይ ተፈተው ወደመደበኛ ተግባራቸው ይሰማራሉ። የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ያለምንም ሳንክና መሰናክል በነጻ ሜዳ ላይ ይፎካከራሉ። የሸፍጥ ፖለቲካ ያንድሰውና ያንድ ቡድን የድሜልክ አገዛዝ ሟቹን የወያኔ መሪ ተከትሎ ይሞታል። የግል መገናኛ ብዙሀን ህግና ስርዓትን እየጠበቁ አንደቀድሞው የሚያኮራ ተግባራቸውን ይቀጥላሉ። እውነተኛውን ህግ ካልተላለፉ አይከሰሱም። አይታሰሩም። ሐሰት ከተናገሩ፤ ሐሰት ከጻፉ ይከሰሳሉ። በህግ ይዳኛሉ። የመንግስትን ጥንካሬና ድክመት፤ የፖለቲካ ድርጅቶችን ጥንካሬና ድክመት፤ የህዝብን ሮሮና ብሶት ወደ መንግስት ከመንግስት ወደህዝብ ከህዝብ ወደህዝብ ነጻ ኢንፎርማሽን ማቀባበላቸውን ይቀጥላሉ።

 

ከእንግዲህ በሗላ ውሸት በኢትዮጵያ የመንግስት የስራ ቋንቋ መሆኑ ያከትማል። ፈጣሪውን ተከተሎ ከርሰመቃብር ይወርዳል። ባለፉት የወያኔ አገዛዝ ዓመታት ውሸት  የመንግስት ብሄራዊ የስራ ቋንቋ ሆኖ እስካሁን እየተሰራበት ይገኛል። በኢትዮጵያ ለታሪክ የሚነገረው የመጨረሻ የመንግስት ውሸት “መለስ ዜናዊ አልሞተም። እረፍት ላይ ነው፤ በስልክ እየሰራ ሀገሪቱን እየመራ ነው፤ ደቡብ ሱዳንን እያስታረቀ ነው ወዘተ…..” ሲባል ተከርሞ “ ትላንታ ማታ በኢንፌክሽን ሞቷልና ወታችሁ ሬሳውን ተቀበሉ…..” የውሸታሞች መንግስት ለዘለዓለሙ ይቀበራል።…ኢትዮጵያ።

 

የመንግስት መገናኛ ብዙሀን ከንግዲህ የውሸት ፋብሪካ መሆናቸው፤ ጋዜጠኞቹም የሀሰት ዜና አምራቾች መሆናቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ያስተዳደር ዘመን ያከትማል ብየ አልሜአለሁ። አስባለሁ።

 

የፍትህ ተቋማት ከሁሉም በፊትና በላይ ራስ ገዝ ይሆናሉ። ሙሉ ነጻነታቸውን አሁኑኑ ይቀዳጀሉ። መንግስትን የሚቃወሙ ዜጎችን ለማሰቃየት ለመግደል፤በወህኒ ለማማቀቅ፤ የሀሰት ክስ መተወኛ መድረክ መሆናቸው፤ የሀሰት ምስክር ማስልጠኛና መስሚያ ተቋማት መሆናቸው ዛሬ ላይ ያቆማል።ዜጎች፤ ህጋዊ ሰውነት ያላቸው የፖለቲካም ሆነ የስቢል ድርጅቶች፤ የመንግስት ተቋማትና አካላት ባለስልጣናት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በኢትዮጵያ ሁሉም ሰብዓዊ ፍጡር ከህግ በታች ይሆናሉ። አንድ ተራ የቀን ሰራተኛና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህግ ፊት እኩል ናቸው። ሁለቱም እኩል ዳኞች ፊት ለፍርድ ይቆማሉ።

 

ዩኒቨርስቲዎቻችንና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትምህርት ቤቶች ከወያኔ ሰላዮች፤ ካድሬዎች እና ጆሮ ጠቢዎች ይጸዳሉ። መምህራንና ተማሪዎች የአካዳሚክ ነጻነታቸውን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ይቀዳጃሉ። መምህራንና ተማሪዎች በሀገራቸው የፖለቲካ የ ኢኮሚና ማህበራዊ ጉዳይ በሁሉም አቅጣጫ በሀገሪቱ መፃኢ እድል ላይ ነጻና ትምህርታዊ ውይይት ያደርጋሉ። በመንግስት ውሳኔዎችና እርመጃዎች ላይ ይነጋገራሉ። ቅሬታቸውን ይገልጻሉ። ገንቢ ሀሳቦችን አማራጮችን ያቀርባሉ። ሀገርን የሚጎዳ አደገኛ ፖሊሲ ወቷል ካሉም ህዝቡን የማወያየት የመቀስቀስ ነጻነት ይኖራቸዋል። ወጣቶች በነጻነት ተምረው በነጻነት ሊያገለግሉ ወደህብረተሰቡ ይቀላቀላሉ።

 

ሕገመንግስቱ አስቸኳይ ጥገናና ለውጥ ይደረግለታል። አንቀጽ 39 መገንጠልን  የሚያረጋግጠው የመለስ ዜናዊ አንቀጽ ፈጣሪውን ተከትሎ ይሞታል።ይሰረዛል።  ወያኔ የገነባው የዘር ግርግዳ ባዋጅ ይፈርሳል። “ብሄር ብሄረሰቦች” የሚለው የወያኔ ቋንቋ “ኢትዮጵያውያን” እና “ዜጎች” በሚሉ ቃላት ይተካሉ። በኢትዮጵያ ህዝብ መታወቂያ ወረቀት ላይ “ዘር” ወይም “ብሄር” በሚለው መስመር ላይ “ዜግነት” የሚለው ቃል ይተካል። ኢትዮጵያውያን ድፍን ኢትዮጵያ ጥንታዊት ሀገራቸው መሆኗ ይረጋገጥላቸዋል። ዘረኞቹ ስልጣኑን ከተቆጣጠሩበት ጊዜ በፊት እንደነበረው ሁሉ፤ ማንም ኢትዮጵያዊ ወደፈለገው ክፍለሀገር ሔዶ መኖር ትዳር መመስረት፤ ሀብት ማፍራት መብቱ ነው።አሜሪካ፤ ካናዳ፤ አውስትራሊያ ወዘተ.. ከሄደ መኖር እንደሚችል ሁሉ በተፈጠረባት ምድር ውስጥም መኖር  አብሮት የተፈጠረ መብቱ ነው። በህግ እንዲኖር ከተፈቀደለት የባእድ ባእድ ሀገር ምንም ወንጀል ያልፈጸመ ኢትዮጵያዊ ሀብትና ንብረትህን አስረክበህ ውጣ ተብሎ እንደማያውቅ ሁሉ፤እትብቱ በተቀበረባት ምድር እናት ሀገር ኢትዮጵያ ውስጥ የተነፈገውን ይህንን መብት፤በስቸኳይ መልሶ መቀዳጀት አለበት።በኢትዮጵያም ከንግዲህ ዜጎች ከክፍለሀገር ክፍለሀገር ዘራቸው እየተለየ ሀብታቸውን እየተቀሙ የሚባረሩበት ወያኔ ወለድ ወንጀል እስከመጨረሻው ይቆማል። ቤተሰብ አይበተንም።እስካሁን ለተፈጸሙት ኢሰብዓዊ ወንጀሎች አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በሞተው የወያኔ መሪ ስም ኦፊሴላዊ ይቅርታ ይጠይቃሉ። የዘረኛው መሪ እርምጃ ሰለባ የሆኑ ሁሉ አስቸኳይ ካሳና እርዳታ ተደርጎላቸው ወደ ተባረሩበት መንደር ይመለሳሉ። ሀብታቸውን ቤታቸውን ይረከባሉ።

 

የዘር ቆጠራ ፖለቲካ በጠቅላይ ሚኒስትር ሓይለማሪያም ያስተዳደር ዘመን በህግ የሚያስቀጣ ወንጀል ይሆናል። ሕጻናት አፍ በፈቱበት ቋንቋ ይማራሉ። ዜጎች በሚናገሩት በሚገባቸው ቋንቋ ይዳኛሉ። አንድ ብሄራዊ የስራ ቋንቋም ይኖራቸዋል።

 

የኢትዮጵያ ህዝብ የኔ የሚለው ጦርሰራዊት የለውም። ሳንወድ በግድ የወያኔን የጥፋት ሚሊሺያ ተሸክመን እዚህ ደርሰናል። ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም የመከላከያ ጦር ሰራዊት ጠቅላይ አዛዥ፤ የወላይታ፤ የከንባታ፤ የሀዲያ የሌላውም ሁሉ ልጅ የጦር መኮንን መሆን አይችልም አልነበረም ያለ ማነው? የኦሮሞ ልጅ የአማራ ልጅ በኢትዮጵያ ውስጥ የሰማንያ ብሄረሰብ ልጆች የጦር አዛዥ፤ የጦር መኮንን አይሆኑም አልነበሩም ያለ ማነው? በኢትዮጵያ ውስጥ የጦር አዛዥነትና ተዋጊነት ለትግሬ ልጅ ብቻ የተፈቀደ ነው ያለ ማነው? ነፍሱ እንደስራው ትዳኝና መለስ ዜናዊ በብዙ መቶዎችና ሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ የአማራ እናም የሌሎች ብሄር ልጆችን ከሰራዊቱ በአንዲት ቀን ጀንበር እያባረረ፤ የራሱን ዘሮችና ታማኞች በጦሩ ውስጥ ይሰገስግ እንደነበር ያውቁታል። አሁን ክቡርነትዎ የሚያደርጉት ነገር የወያኔን የጦር አዛዦች ሁሉ ከስራ እያሰናበቱ ጦሩ በህብረብሄር መኮንኖች አንዲታዘዝ ማድረግ፤ ይህ እርምጃ በፖሊሱም በደህንነቱም ውስጥ ጊዜ ሳይሰጠው እንደሚከናወን ተስፋ አደርጋለሁ።

 

ወያኔ በህብረተሰቡ ውስጥ የገነባው የስለላ መረብ ይወገዳል። የስለላና የደህንነት ተቋማት የሀገርንና የህዝብን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ስራ ላይ ይውላሉ እንጂ፤ ህዝብን በማፈንና በማስፈራራት፤ ተቃዋሚዎችን በመከታተልና በማፈን፤ የገዢ ግለሰቦችን ስልጣን ለመጠበቅ አገልግሎት መስጠታቸው ያከትማል።

 

ሕውሀት በትግራይ ህዝብ ላይ በተለይ ያነጣጠረ ልዩ የመቆጣጠር ተግባር፤ ህዝቡን ከሌላው ኢትዮጵያዊ የተለየ ለማድረግ፤ አስፈላጊ በሆነ ጊዜና ሁኔታ ሁሉ ሌላውን የ ኢትዮጵያ ህዝብ ተቃርኖ ሊቆም በሚችለበት አቋምና እምነት ላይ ለማኖር የሚደረገውን የውስጥ ፕሮፓጋንዳ ስራ ባስቸኳይ ያቆማል። በዘር፤ በህዝብ ልዩነት ላይ የተመሰረተ አሉታዊ ቅስቀሳና ትምህርት፤ በህግ የሚያስቀጣ ተግባር ይሆናል።

 

መላውን የሀገሪቱን ንግድና ምርት አጠቃላይ ኢኮኖሚ እንዲቆጣጠሩ የተፈቀደላቸው የወያኔ የንግድ ድርጅቶች በአዋጅ ወደ ህዝብ ንብረትነት ይዛወራሉ። መንግስትም ሆነ የፖለቲካ ድርጅቶች በነጻ የገበያ ኤኮኖሚ ስም፤ አግባብ ባልሆነ የንግድ ፉክክር የዜጎችን መብትና የስራ እድል አይጋፉም። የፖለቲካ ድርጅቶች በማናቸውም አይነት የንግድ እንቅሰቃሴ ውስጥ አይሳተፉም። የወያኔ ድርጅቶች ከብሄራዊ ባንክ ከመንግስት ባንኮች የተበደሯቸውን ገንዘቦች በሙሉ ባስቸኳይ ይመልሳሉ።

 

በሞተው የወያኔ መሪና የቅርብ ተባባሪዎቹ በጎ ፍቃድ ያለ ሕዝብ ምክርና ዝክር በመሬት ቅርምቱ የተሳተፉ የውጭ ባለሀብቶች፤ በሕዝቡ ምክርና ፍላጎት ላይ የተመሰረተ አዳዲስ ውልና ግዴታ ይዘጋጅላቸዋል። ሕዝቡ በአየር፤ በአፈር፤ በውሀና በደን እንዲሁም በዱር አራዊት ጥበቃ ረገድ፤ ባዕዳኑ በለሀብቶች የሚያደርጉትን በጥንቃቄ ይከታተላል። ጥፋት ሲፈጽሙ በሕግ የተደገፈ እርምጃ ይወስዳል። ምሳሌ፤ በድብቅ የኢንዱስትሪ ዝቃጭ ከውጭ አስገብተው በኢትዮጵያ ምድር ለመቅበር ቢሞክሩ፤ ሕዝቡ ያን ከደረሰበት፤ ፈጥኖ በማስቆም ጉዳዩ ከሚመለከተው የመንግስት ባለስልጣን ጋር በመሆን ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋል።

 

በመሬት ቅርምቱ ምክንያት ከንብረታቸው፤ ከይዞታቸው፤የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን፤ ሙሉ ካሳና ሙሉ መጠለያ፤ የምግብ እርዳታ፤ አስተማማኝ የኑሮ ዋስትና ያለው ስራ ይፈጠርላቸዋል። የትምህርት፤ የጤና፤ አገልግሎት፤ የመንገድና ትራንስፖርት አገልግሎት በአስተማማኝ የሚያገኙበት ሁኔታ በስቸኳይ ተግባር ላይ ይውላል። መንግስት ከባለሀብቶቹ ጋር ተነጋግሮ ይህንን ማሟላት ካልቻለ፤ ባለሀብት መሬት ከኢትዮጵያ ሊያገኝ አይችልም።

 

ሕጋዊና ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ የአሰብን ወደብ ጉዳይ ከኤርትራ ገዥ ቡድን ጋር ንግግር ይጀመራል። በሰላማዊ ድርድር ኢትዮጵያ የወደብ ባለቤትነት መብቷን ማረጋገጥ ካልቻለች፤ ኢትዮጵያውያን የህግ ባለሙያዎች በኮሚቴ ተዋቅረው ጉዳዩ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንዲታይ ስራ ይጀመራል። የሚደረገው እንቅስቃሴ በየደረጃው እድገቱ ለሕዝብ ይፋ ይሆናል። የመፍትሄ ሀሳብና አማራጭም ከህዝቡ ይጠየቃል።ሕዝቡ የሚወስነውም ሁሉ ይፈጸማል።ደረጃ በደረጃ የተበላሸውን ስርዓት የማስተካከሉ ስራ ይቀጥላል።

 

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

መልካም የስራዘመን ለጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ