እንኩዋን ደስ ያላችሁ! አዲስ ምዕራፍ፣ አዲስ ፈተና

ኢህአዴግ የቅንጅትንና የኢትዮጵያን ትግል ቆዳውን ሊልጠው ትንሽ አቆሰለው እንደሁ እንጂ፡ ውስጡንና ጉዞውን አልቀላውም አይቀላውምም። እነሆ በአዲስ ወኔ፡ በአዲስ ሞራል፡ በአዲስ ስም፡ ነገር ግን በቆየው ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርአት የመመለስ ተልእኮ ጠቅላላ ጉባኤያችሁን ልታደርጉ መሆኑን ሰማን። የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ የኢትዮጵያም ድህነት የተቀበረው እዚያው ኢትዮጵያ ውስጥ ነውና በውጭ አገር ህይወት ሳትማረኩ ተመልሳችሁ ከህዝቡ መካከል ለመታገል ወስናችሁ የምታደርጉትን ውጣ ውረድ ሁሉ እናደንቃለን። “ወደፈተናም አታግባኝ” ተብሎ በሚጸለይበት ዓለም እናንተ እያወቃችሁና ሊደርስባችሁ የሚችለውን አደጋ ተረድታችሁ፡ ወደፈተናና ወደፈተና ለመግባት መሰለፋችሁ እለት እለት ያስደምመናል።

 

ሀሳባችሁ ሁሉ ይሳካ ዘንድ ምኞታችን፡ ፈጣሪም ለኢህአዴግ እንደሚያዳላ በአባ ጳውሎስ አይተነው ለረጅም ግዜ የተውነውን ጸሎታችንም ከናንተ ጋር ነው። መቼም በጸሎት ብቻ የሚሆን ነገር የለምና እንደሰው የፈራነውን እንደሰው የሰጋነውንም ልንጠቁማችሁ ደፈርን። አስር ዶላር ወረወርን ብለን የመቶ ዶላር ትችትና የምክር ናዳ ልናወርድባችሁ አንደፍርም። ይሁን እንጂ በዚህ በጠቅላላ ጉባኤያችሁ ሰሞን፡ ብታስቡባቸው፡ እንደ ክታብም ብታስሯቸው ብለን እነዚህን የታናሽ መሰንዘር መረጥን። ከጠቀሙ ያዟቸው። ካልጠቀሙም ያዟቸው። የሚጠቅሙበት ዘመን ይመጣልና።

 

ላለፈ ስርየት ነው፡ ለሚመጣው ግን እቅበት

 

የተገፋችሁ እለት፡ በገፏችሁ ላይ የውግዘት ቃል፡ መልካም የሰራችሁ እለት ስለመልካም ስራችሁ የድጋፍ መግለጫ፡ የተሳሳታችሁ የመሰለን እለት ደግሞ በስህተታችሁ ላይ የተቃውሞ መልእክት፡ አስተላልፈናል። በኢህአዴግ እስር ከርማችሁ ስለመከራችንና ፍዳችን የተሸከማችሁት የሁለት ዓመታት የእስራት መስቀል ከጫንቃችሁ ሲወርድም፡ የአፈታታችሁ ምስጢር የምንኮራበትና የምንፎክርበት ባይሆንም ደስታችንን ገልጸናል። ለዚህም ነው አትላንቲክን አቋርጣችሁ ልትጎበኙን ስትመጡ ኪሎሜትሮችን አቋርጠን እናንትን የዴሞክራሲ አርበኞች ልንሳለማችሁ የገሰገስነው። ሲያንሳችሁ እንጂ አይበዛባችሁም። የዚያኑም ያህል ጥቂት ውስጥ-በቀል አምባገነኖችና ጋሻዣግሬዎቻቸው ባስነሱት ሁካታ ምክንያት በመካከላችሁ በተፈጠረውና ደጋፊን ባሸበረው ክፍፍል ተሸማቀን ነበር። እኛስ ግድየለም፡ ከዚህ ከሞቀ አገር ነው ያለነው፡ ያ ከናንተ ጋር የተቆራመተ የተገፋ ህዝብ እንዳዘነ በየመስኩ ሰምተናል። ስለህዝብ መቆራመትና መገፋት ከናንተ በህዝቡ ጉያ ካላችሁት የተሻለ ብንቆረቆር፡ ከመምሩ ደቀ መዝሙሩ ይሆንብናል፡ አንሞክረውም። በመከፋፈላችሁ ግን፡ የድፍረትና የዘለፋ ሾተል አንስተው ከኢትዮጵያ እስከ አሜሪካ ከአውሮፓ እስከ ካናዳ ከደቡብ አፍሪካ እስከ አውስትራሊያ የወጓችሁ፡ የዘረጠጧችሁ፡ ያነጓጠጧችሁ አያሌ ናቸው። ያ ሁሉም አልፎ፡ አብዛኞቻችሁ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳችሁ በተነጠቃችሁት ስምና ክብር፡ መብትና ነጻነት ሳትሸነፉ የናንተንም የኢትዮጵያንም ትግል ወደፊት የሚያራምድ ድርጅትና ስም አዋቅራችሁ ወደፊት ልትገሰግሱ መሆኑን ዜና ስንሰማ፡ የኢትዮጵያ ትግል እዚያው ኢትዮጵያ ውስጥ እንደተቀበረና እናንተም በምንም መልኩ መረዳት እንዳለባችሁ የምናምን ስደተኛ ኢትዮጵያዊያን እጅጉን ኮርተንባችኋል።

 

ይሁን እንጂ

 

ከቅርብ ግዜ ወዲህ ውስጥ ውስጡን የምንሰማቸው፡ ንቀን ልናልፋቸው የጣርናቸው ጥቃቅን የሚመስሉ፡ ነገር ግን በየጊዜው የኢትዮጵያን ህዝብ ሞራልና ሰሜት የጎዱ ሽኩቻዎች በመካከላችሁ እንደተፈጠሩ ስንሰማ፡ ቀድሞም በቅጡ ያላጠገገ መሸማቀቃችን አገርሽቷል። ስለዚህም፡ ዝም ብለን በአሉባልታና በሰቀቀን ከምንታሽ፡ በጸሎትና በምኞት ብቻ የሚሆን ነገር የለምና፡ ለመጪው ጠቅላላ ጉባኤያችሁ አካሄድ ያግዝ እንደሆነና የምታልፉበትን አስቸጋሪ ሂደት በንቃት የምንከታተልና ውጤቱንና ስኬቱንም በጉጉት የምንጠብቅ መሆኑን ለመግለጽ፡ ለዚህም ለኛ በወዳጅ አገራት ጥበቃ ስር ለምንንደላቀቅ ጥቂቶች ስትሉ ሳይሆን፡ ለብዙሀኑ መጠጊያ ላጣ፤ ቀደም ሲል በኑሮ ውድነት፡ አሁን ደግሞ በረሀብም ጭምር ለሚንገላታና ለክፍለዘመናት ለውጥ ለናፈቀው፡ በሚሌኒየሙ ባዶ የተስፋ ዳቦ ለተመገበው ብዙሀን ስትሉ፡ አካሄዳችሁ ሲሆን ሲሆን የመስማማት፡ ባይሆን ደግሞ ያለመባላት እንዲሆን ይህቺን አጭር መልእክት ማስተላለፍ ሻትን። ይህንን መልእክት ለማስተላለፍ፡ ልጆቻቸው ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ በተሰዉ ወላጆች መካከል፡ ቤተሰቦቻቸው በኢህአዴግ አፈናና የቅንጅትን ድል ለማስጠበቅ በተደረገ ትንቅንቅ በተፈናቀሉ ኢትዮጵያዊያን አጠገብ በረሀብና በጭቆና እለት እለት ከሚረገጥ ህዝብ ውስጥ ከምትኖሩ ደፋር የአንድነት/ቅንጅት መሪዎች የላቀ የሞራልም የእውቀትም ብቃት የለንም። እንደው በኋላ ከማማትና ከማውገዝ የበኩላችንን በማዋጣት በሀሳብ ለማገዝ ያህል ብቻ እንጂ። በመሆኑም በመጪው ጉባኤያችሁም ይሁን ከዚያ በኋላ፡ እነዚህን አብይ ጉዳዮች ከግምት ታስገቧቸው ዘንድ እንማጸናለን።

 

ዴሞክራሲን አደራ፡ ያለፈውን እንዳትደግሙ

 

ከናንተ መካከል የተሻለ፡ እሱ መሪ ይሁን። የተሻለውን ደግሞ የሚያውቅ እሱ የሚመርጠው ነው። የተሻለው የባሰ ቢሆንም እንኩዋን፡ አግባብ ባለው አካሄድ እስከተመረጠ ድረስ፡ በአብላጫው ድምጽ የተመረጠውን ተቀበሉ።

 

ቀደም ሲል በነበረው የቅንጅት ሂደት የተፈጸመ ዲሞክራሲን የተጣረሰ ስህተት ከነበረ፡ በምንም መልኩ ያለፈውን ስህተት እንዳትደግሙ። ኢህአዴግን በፍትሀዊ ምርጫ አለመኖር ከወቀስነው፡ እኛ በዚያ ላለመከሰስ መጣርና መጠንቀቅ አለብን።

 

ከተድበሰበሰና ከተሸፋፈነ አካሄድ መጽዳት ያስፈልጋል። የተድበሰበሰና የተሸፋፈነ አካሄድ ምን ያህል እንደጎዳን ከቅንጅት ተምረናል። አቶ ሀይሉ ሻውልን በላያችን በላያችሁ እንዲፈነጩብን ያደረገው ከሁላችሁም የተለየና የላቀ ችሎታቸው ሳይሆን፡ የተድበሰበሰና የተሸፋፈነ፡ አትንኳቸው አትናገሯቸው አሰራር ነው።

 

የራሳቸው የግል ፍላጎት ያነገቡ እንጂ፡ ራእያቸው የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊያን፡ ህልማቸው የህዝቡ የሆነ ሰዎች ግፋ ቢል በሀሳብ የሚለያዩበት እንጂ የሚጋጩበት ምክንያት አይታየንምና ግጭታችሁን ብንሰማ ለኢትዮጵያ ሳይሆን ለራሳችሁ የግል ፍላጎት እንደተቋሰላችሁ እንገምታለን።

 

የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም ያስቀደመ ሰው ከሱ ለሚበልጡትንና ለተሻሉት መንገድ ይለቃል እንጂ፡ እኔ እበልጣለሁ ብሎ የስልጣን ሽሚያ ውስጥ አይገባም። የሚበልጡትን እንጂ የሚበልጣቸውን አያስብም። ያም ባይሆን፡ አግባብ ባለው መልኩ ለስልጣን መታገል መልካም ነውና፡ ውድድር ውስጥ ከተገባም፡ ውሳኔያችሁንና ስልጣን ድልድላችሁን ሁሉ በድምጽና በምርጫ ታደርጉት ዘንድ አደራ።

 

በምርጫ ሳይሆን በኮታ ይገባኛል ብሎ ስልጣን የያዘን ሰው ማውረድም ማረቅም አስቸጋሪ መሆኑን በዚህ ሁለት ሶስት ዓመት በአቶ ሀይሉ ሻውል አይተነዋል። ታስረው እንኩዋን አምባገነንነታቸው እስር ጥሶ ወጥቶ ሲያምሰን እንደነበረ የቅርብ ግዜ ትዝታችን ነው። እብሪታቸው ጣሪያ ከመንካቱ የተነሳ፡ አብራችሁ የታሰራችሁትንና የተሰቃያችሁትን፡ እናንተን ገመና ሸፋኝ ጓዶቻቸውን “የቁጥር ዶክተሮች ናቸው” ብለው ዘርጥጠዋል። በእውኑ አሜሪካ ሲታከም የከረመ የፖለቲካ መሪ እንዲህ ካለ ፖለቲካዊ ደዌ ይፈወሳል እንጂ፡ ብሶበት ይመጣልን?

 

ተንኮለኞችንና ነገረኞችን አትታገሱ። በግልጽነትና በነጻነት ወስኑ። መቼም የተከፋና የተገፋ ህዝባችን፡ ሌላ ንትርክና ሽኩቻ፡ ሌላ መከፋፈልና ሌላ መጠላለፍ የሚሰማበትና የሚመለከትበት ጉልበትም አንጀትም የለውምና፤ የሚያጣላችሁ ወይም የሚያጋጫችሁ ነገር ቢኖር፡ ራሳችሁን በድላችሁ፡ ላገራችሁ እንጂ ለራሳችሁ ክብር ሳትጨነቁ፡ ለመወሰን ወስኑ።

 

እነሆ ቅዳሜ እና እሁድ መልካሙን ሁሉ እንጠብቃለን። ከቅዳሜና ከእሁድ ባሻገርም ጉዟችሁን አንጋጠን እናያለን።

 

ሰኔ 2000 ዓ.ም.

ኢትዮጵያዊያን ካናዳዊያን፡ ከአገረ ካናዳ

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ