አቡ ዘኪያ ከምድረ-አናቶሊያ

ኢሕአዴግ በሀገራችን ዴሞክራሲ ማስፈኑንና ሕገ-መንግሥታዊ ስርዓት መዘርጋቱን ሌት ተቀን ይተርክልናል። እውነታው ግን ሀገራችን በ81 ዓመት የሕገ-መንግሥት ታሪኳ ውስጥ አንድም ጊዜ እደግመዋለሁ አንድም ጊዜ ሕገ- መንግሥታዊ ስርዓት ለማየት አልመታደሏ ነው። የኢሕአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ፀረ-ዴሞክራሲ አብዮት ነው። ኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥቱን የወረቀት ላይ ነብር አድርጎታል። ተቃዋሚዎችን በፀረ-ሕገ መንግሥታዊነት የሚነቅፈው ኢሕአዴግ የሕገ-መንግሥቱ ቀንደኛ ባላንጣ ነው ...

 

 

ሀገራችን በፈርጀ ብዙ ችግሮች እየተናጠች ነው። ሕገ-መንግሥቱ እርባና ቢስ ወረቀት ሆኗል። ፍትሕ የለም። ዜጎች በጅምላ ይታሰራሉ ይገረፋሉ አልፎ ተርፎም በጠራራ ፀሐይ በፀሐዩ መንግሥት ታጣቂዎች ይረሸናሉ። ነጻው ፕሬስ ታፍኗል። ሙስና ነግሷል። የዘረኝነት፣ ዘውገኝነትና ወንዘኝነት ዥረት እርስበርሳችን እያላጋን ነው። ሀገሪቱ የጥቂት ሰርቆ አደር-ጠግቦ አደሮችና የብዙኃን ሠርቶ አደር-ጦም አደሮች ምድር ሆናለች። አንድ ሺህ አንድ ችግሮች ሕዝባችንን እግር ከወርች ጠፍንገው እያሰቃዩት ነው። ችግሩን ለይቶ ማወቅ ወደ መፍትሄ የሚወስደውን ጎዳና እንደ ማጋመስ ይቆጠራል። ነገር ግን ችግሩን አስመልክቶ ችግር አለ። ብዙዎቻችን ያተኮርነው የችግራችን መንስኤዎች ላይ ሳይሆን ምልክቶቹ ላይ ነው። የበሽታው ምልክቶች ስለተወገዱለት በሽተኛው ሙሉ በሙሉ ከበሽታው ሊፈወስ አይችልም። ለተሟላ ፈውስ የበሽታውን ሰንኮፍ መንቀል የግድ ነው።

 

በእኔ እምነት የፍትሕ፣ የሥራ እና የምግብ እጦት፤ሙሰኝነት፣ ዘውገኝነት፣ ጎጠኝነትና ዘረኝነትን መሰል ተውሳኮች በሙሉ የበሽታችን ምልክቶች እንጅ መንስኤዎች አይደሉም። እነዚህን የሀገር ነቀርሳ ምልክቶችን በማስወገድ ከተጠናወተን ደዌ ሙሉ ለሙሉ እንፈወሳለን ብየ አላምንም። አንድ ሺህ አንድ ተውሳክ ተጠናውቶናል ስል አብዛሃኞቹ ተውሳኮች የትላልቆቹ ደዌዎች ውላጆች መሆናቸውን ለማስገንዘብ እወዳለሁ። ቀንደኞቹን ደዌዎቻችንን በማስወገድ ችግራችንን ከነ ጓዙ ከነ አበጋዙ ማስወገድ እንችላለን።

 

አሉ የምንላቸውን ችግሮች ለማስወገድ ከመሞከራችን በፊት ችግሮችን እንደ ክብደታቸው መጠን በቅደም ተከተል ዘርዝረን ማስቀመጥ ይገባናል። እርግጥ ነው የችግሮቹ ምንነትም ሆነ ቅደም ተከተል እንደ አመለካከታችን ሊለያይ ይችላል። እኔም እንደመሰለኝ ሀገራዊ ችግሮቻችንን በአስር አበይት ክፍሎች በመክፈል አጠር አጠር አድርጌ ለማሳየት እሞክራለሁ።

 

እንደኔ ለእኔ የሀገረ ሐበሻ አበይት ደዌዎች እና ተውሳኮች የሚከተሉት ናቸው፦

1. የሕገ-መንግሥት ጥሰት

2. የሦስቱ የመንግሥት አካላት ነጻነት መሸርሸር

3. የባለስልጣናት እብሪተኝነት

4. የዜጎች መሰረታዊ መብቶች መነፈግ

5. ሙስና

6. ቅጥ ያጣ የሀገር ኃብት አጠቃቀም

7. የጥቂቶች የበላይነት

8. የሀገሪቷን ታሪክ ጠንቅቆ አለመረዳት

9. የተዛባ የመረጃ ፍሰት

10. እጅግ ኋላቀርና ደካማ የትምሕርት ስርዓት

 

ሀገራችን ባለፉት 81 ዓመታት አምስት ሕገ-መንግሥቶችንና አንድ የሽግግር መንግሥት ቻርተርን አይታለች። የመጀመሪያው ሕገ-መንግሥታችን በ1924 የታወጀው ሲሆን። ሁለተኛው ደግሞ በ1948 ተሻሽሎ የወጣው ሕገ- መንግሥት ነው። ሦስተኛው ሕገ-መንግሥታችን ለሕዝብ ይፋ ሳይሆን በጅምር የቀረው የአስራ ዘጠኝ ስድሳ ስድስቱን ሕዝባዊ አብዮት ተከትሎ በልጅ እንዳልካቸው ካቢኔ የተረቀቀው ረቂቅ ሕገ-መንግሥት ነበር። መስከረም 2 ቀን 1967 የሕዝብን አብዮት በኃይል ነጥቆ ዙፋን ላይ ጉብ ያለው ወታደራዊ ጁንታም በፖለቲካ ሕይወቱ የመጨረሻ ሳምንታት ማለትም በ1979 አንድ ሕገ-መንግሥት ቢጤ እንካችሁ ብሎን ነበር። የጁንታውን ፍጻሜ ተከትሎም በሰኔ 1983 የሽግግር ወቅት ቻርተር የተሰኘ የመተዳደሪያ ደንብ ታወጀልን። የሽግግር ወቅቱ ቻርተርም በ1987 ለዛሬው ሕገ-መንግሥታችን ስፍራውን ለቀቀ።

 

ከላይ የዘረዘርኳቸውን ሕገ-መንግሥቶችና የሽግግር መንግሥቱን ቻርተር የመገምገም እድል ገጥሞኛል። አሁን ያለው ሕገ- መንግሥታችን ከነ ክፍተቶቹ ከቀደምቶቹ የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ነው ብየም አምናለሁ። ችግሩ ያለው በአብዛሃኛው አፈጻጸም ላይ ነው። ኢሕአዴግ በሀገራችን ዴሞክራሲ ማስፈኑንና ሕገ-መንግሥታዊ ስርዓት መዘርጋቱን ሌት ተቀን ይተርክልናል። እውነታው ግን ሀገራችን በ81 ዓመት የሕገ-መንግሥት ታሪኳ ውስጥ አንድም ጊዜ እደግመዋለሁ አንድም ጊዜ ሕገ-መንግሥታዊ ስርዓት ለማየት አልመታደሏ ነው። የኢሕአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ፀረ-ዴሞክራሲ አብዮት ነው። ኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥቱን የወረቀት ላይ ነብር አድርጎታል። ተቃዋሚዎችን በፀረ-ሕገ-መንግሥታዊነት የሚነቅፈው ኢሕአዴግ የሕገ-መንግሥቱ ቀንደኛ ባላንጣ ነው። ባለፉት ዓመታት ኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥቱን በርካታ ጊዜ ጥሷል። ለአብነት ያህል አፋኙን የፀረ-ሽብር ሕግ፣ የዜጎችን ንብረት የማፍራት፣ የመሸጥና የመለወጥ መሰረታዊ መብቶችን የሚጥሰውን የሊዝ አዋጅ፣ በጥበቃ ስር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸው ሊጠበቅ ይገባል የሚሉትን የሕገ-መንግሥቱን አንቀጽ 20(3) እና አንቀጽ 21(1) ድንጋጌዎችን በመተላለፍ ትናንት በአቶ አንዷለም አራጌ ላይ ዛሬ ደግሞ በሙስሊሙ ማሕበረሰብ ወኪሎች ላይ በእስር ቤት የደረሰውንና እየደረሰ ያለውን ግፍና የሰሞኑን የተጨማሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሹመት መጥቀስ ይቻላል።

 

ሁለተኛው ቀንደኛ ሀገራዊ ደዌና የበርካታ ችግሮቻችን መንስኤ የሦስቱ የመንግሥት አካላት ነጻነት መሸርሸር ነው። እንደ ሌሎች ሀገራት ሁሉ በሀገራችንም ሦስት የመንግሥት አካላት አሉ። እነዚህም ሕግ አውጭ(የተወካዮች ምክር ቤት) ሕግ አስፈጻሚ(ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ እስከ ታች ድረስ ያለው የስራ አስፈጻሚ አካል) እና ሕግ ተርጓሚ(ፍርድ ቤቶች) ናቸው። እነዚህ ሦስት አካላት እርስበርሳቸው ትስስር ያላቸው ቢሆንም ቅሉ አንዳቸው ከአንዳቸው ነጻ ሆነው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው በሕገ-መንግሥቱ ተደንግጓል። ይሁን እንጅ በእነዚህ አካላት መካከል መናበብ አይስተዋልም። ግልጽነትና ተጠያቂነት ህልም ሆነዋል። የአንድ አካል ማለትም የሕግ አስፈጻሚው አምባገነንነት ገኖ ይታያል። ሕግ አስፈጻሚው ሕግ አውጭውንና ሕግ ተርጓሚውን ሲጫናቸው ይስተዋላል። ሕግ አውጭው ያወጣቸውን ሕጎች መተግበር አለመተግበራቸውን የሚቆጣጠርበትና የሚገመግምበት አቅም አጥቷል። ሕግ ተርጓሚው ከሕግ አስፈጻሚው አካል በሚደርስበት ጫናና ጣልቃ ገብነት እጅግ ተዳክሟል። በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ያሉ ፍርድ ቤቶች በሕገ-መንግሥታዊው ድንጋጌ መሠረት ራሳቸውን ችለው በነፃነት መንቀሳቀስ የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ፍትሕ ራሱ የፍትሕ ያለህ እያለ ነው። ፍትሕ አልባ ሰላም ፍትሕ አልባ ልማት አለን?

 

ይህ ጥያቄ ወደ ሦስተኛው ሀገራዊ ደዌ ይመራናል። .የባለስልጣናት እብሪተኝነት...እብሪተኝነት የኢሕአዴግ ባለስልጣናት መለያ ከሆነ ውሎ አድሯል። በችሎታ ሳይሆን በውለታ በብቃት ሳይሆን በቅርበትና በታማኝነት በስልጣን ላይ ለመቀመጥ የታደሉትና ከሕግ በላይ ከሞራል በታች የሆኑት የኢሕአዴግ ሹመኞች የሕዝብ አገልጋይ ሳይሆኑ በሕዝብ ተገልጋይ ናቸው። ለሕዝብ የቆሙ ሳይሆኑ ሕዝብ ላይ የቆሙ ናቸው። እብሪታቸው ከእብሪት በላይ ነው። ባጭሩ የኢሕአዴግ ባለስልጣናት ፀረ-ሕገ መንግሥትና ፀረ-ሕዝብ ተውሳኮች ናቸው።

 

ሕገ-መንግሥቷ በየእለቱ በሚጣስባት ሕግ አውጭውና ሕግ ተርጓሚው በሕግ አስፈጻሚው ስር በዋሉባትና በእብሪተኛ ባለስልጣናት በምትተዳደር ያልታደለች ሀገር ውስጥ ዜጎች መሰረታዊ መብቶቻቸውን መነፈጋቸው ሙስና መስፋፋቱ የሕዝብ ኃብት መመዝበሩ የጥቂቶች የበላይነት መንገሡ ወዘተ አያስደንቅም። ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው የሀገሪቱ ዋነኛ ደዌዎች ከተራ ቁጥር 1 እስከ ተራ ቁጥር 3 ያሉት ናቸው። እነዚህ ሦስት ዋና ዋና ደዌዎች 75% የሚሆነው የሀገሪቱን ችግር ይሸፍናሉ ብየ እገምታለሁ። በመሆኑም የመጀመሪያዎቹን ሦስቱን በመፍታት ቀሪዎቹን ችግሮች ማስወገድ ይቻላል። ለምሳሌ ደዌ ቁጥር 1ን በመፈወስ ተውሳክ ቁጥር 4 እና 7ን ማስወገድ ይቻላል። የደዌ ቁጥር 3 መፈወስ የተውሳክ ቁጥር 5 እና 6 መወገድ ማለት ነው።

 

ለማጠቃለል የመጀመሪያዎቹን ሦስቱን ደዌዎች በማስወገድ ሌሎችን ተውሳኮች ማስወገድ ወይም ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስወግዱ ማድረግ እንችላለን። በመሆኑም ሀገራችንና ሕዝቧ ያሉበትን አሳሳቢ ሁኔታ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በተቃዋሚም ይሁን በደጋፊ ጎራ ወይም ደግሞ በእኔ ምን አገባኝ ሰፈር የሰፈርን ሰፋሪዎች በንጹህ ህሊና በእውነት ለእውነት ስለእውነት በአንድነት በመቆም ሀገራችንና ሕዝቧን ከተጠናወቷቸው ደዌዎች እንታደጋቸው ዘንድ ጥሪየን አቀርባለሁ!

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ