"ለመለስ አለቀስኩ፣ ለምን? ቢሉኝ ..."
ኤሎን ሳምሶን
ፓውል ኩልሆ "The Alchemist" በሚለው መጽሐፉ እንዲህ ጻፈ፦
ናርሲስ ተወዳዳሪ የሌለው ቆንጆ ወጣት ነበር አሉ፤ ከውበቱ ጋር ፍቅር ስለያዘው በየዕለቱ ወደ አንድ ሐይቅ እየሄደ መልኩን በውሀው ነጸብራቅ ሲያይ ይውላል። አንድ ቀን አጎንብሶ ሲመለከት አንሸራተተውና ሐይቁ ውስጥ ገብቶ ሞተ።
በማግስቱ የጫካ ንግስት ውሀ ለመጠጣት ወደ ሐይቁ ወረደች፤ ነገር ግን በፊት የምታውቀው የሐይቁ ውሀ ወደ ጨውነት ተለውጦ ለመጠጣት አስቸጋሪ ሆኖ አገኘችው።
የጫካዋ ንግስትም የሐይቋን ንግስት ጠየቀቻት
"ስለምን እንባዎችሽን ታፈሻለሽ? እንባዎችሽ እኮ ውሀውን ጨው አደረጉብን?"
"ምን ላድርግ ብለሽ ነው ናርሲስ እኮ ሞተ"
"አንችም አልቅሽለት፣ እኔ እሱን ለማደን በየጫካው እዞራለሁ፣ እሱ ደግሞ ካንቺ ጎን ተደፍቶ ቁንጅናውን ሲመለከት ይውላል።"
"ናርሲስ ቆንጆ ነበር እንዴ?" ጠየቀች የሐይቋ ንግስት።
"ቆንጆ ነበር ትያለሽ? ስለሱ ውበት ካንች የተሻለ ማን ሊነግረን ይችላል? ካንች አጠገብ አይደለም እንዴ ተንበርክኮ የሚውለው?"
የጫካዋ ንግስት በሀሳብ ተውጣ ለትንሽ ጊዜ ጸጥ አለች።
ቀጠለች "አየሽ የናርሲስን ውበት አንድም ቀን አስተውየው አላውቅም ነበር፤ ነገር ግን እሱ ከጎኔ መጥቶ አንገቱን አዘቅዝቆ ሲመለከተኝ እኔ በእሱ አይኖች ውስጥ የራሴን ውበት መልሼ ስለማየው እደሰት ነበር። ያለቀስኩትም ለዚህ ነው።"
መለስ በተቀበረ በሳልስቱ ኢህአዴግ ደስ ብሎት "ለመለስ ዜናዊ ያነባህ የኢትዮጵያ ህዝብ ልዩ ምስጋና ይገባሀል" የሚል መግለጫ አወጣ።
የኢትዮጵያ ህዝብም እንዲህ ሲል መለሰ "አይ ኢህአዴግ ያለቀስነው እኮ ለራሳችን ነው። መለስ የውበታችን ማሳያ ነበር፤ በእሱ ክፋት የኛን ደግነት፣ በእሱ ጥጋብ የኛን ረሀብ፣ በእሱ ውሸት የኛን እውነት፣ በእሱ ጉራ የኛን ትሁትነት፣ በእሱ ስድብ የኛን ጨዋነት እያየን እራሳችንን እያደነቅን እንጽናና ነበር።"
ኤሎን ሳምሶን (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)



