ይኸነው አንተሁነኝ

“መካብ ሲያቅት ማፍረስ ሥራ ይሆናል” - ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም

ወያኔ ላለፉት 21 ዓመታት የሀገራችንን ታሪክ ለማፈራረስና ለመቀየር የቻለውን ሁሉ ሞክሯል። የሕዝባችንን የአልደፈርም ባይነት ወኔ ለመስለብና ለማኮላሸት ያልቆፈረው ጉድጋድ አልነበረም። ሃይማኖታዊ ስርአታችንንና ወጋችንን ለመናድ ብዙ መንገድ በመጓዝ ደክሟል። አብሮ በመቻቻል የመኖር ወጥ ባህላችንን ለመጨፈላለቅና ለማጥፋት ሞክሯል።

 

በኢኮኖሚ የወያኔ ጥገኛ እንድንሆንና የመብት ጥያቄ እንዳናነሳ ፀጥ ብለን እንድንገዛ ለማድረግ ሲጥር ከርሟል። ለወገናችን ጠብ ባላለው ልማት ስም ስንቶችን ከመኖሪያ ቤታቸው ከእርሻ ማሳቸው አፈናቅሏል። አሻፈረኝ ያሉትንም አስሯል ገድሏል። ራሱ የማያከብረውን የይስሙላ ህግም አስከብራለሁ እያለ የስንቶችን መብት ረግጧል። ወያኔ ከሳምንት እስከ ሳምንት ስገቴ ናቸው የሚላቸውንና ያላማሩትን ሁሉ አቅሙ እስከ ቻለ ተጉዞ በስደት ዓለምም ቢሆን ያፈናና የግድያ ሙከራ ከማድረግ ቦዝኖ አያውቅም። በዚህ የክፋት ድርጊቱም ጥቂት የማይባሉ ወገኖቻችን ላይመለሱ ክቡር ሂዎታቸውን ገብረዋል። ወያኔ ዛሬም ቢሆን በዓለም ዙሪያ እኩይ ስራውን አላቆመም።

 

በሀረር ከ30 ዓመታት በላይ በባለቤትነት ያስተዳደሯቸው ሱቆች ሊፈርሱ እንደሆነ የታወጀበትና በአዲስ አበባ መኖሪያ ቤታቸውን በማፍረስ ሽዎችን ለልመናና ለጎዳና ተዳዳሪነት የዳረገው የወያኔ ራዕይ ሳያባራ አሁን ደግሞ ጉዳዩ ወደ ክልል ከተሞች ወርዶ የአላማጣ ነዋሪዎችን እያስለቀሰ ይገኛል። ህጻናት፣ አዛውንትና አቅመ ደካሞችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ቤቶቻቸው እየፈረሱ በመሆናቸው መፍትሄ ለማያመጣ የተቃውሞ ሰልፍ ለመውጣት ተገደዋል።

 

ወያኔ በህግ ስም ህግን እየረገጠ እንደገና ራሱ ቀድሞ እየጮኸ፤ በልማት ስም ያሻውን እየገፋ የውድቀት ራዒዉን እያሰፋ የፈለገውን እያስፋፋ ሀገር እያጠፋ ቀጥሏል። መብታችን ይከበር ለሚለው ጥያቄ መብት እንደገፈፈ እንዳሰረና እንደገረፈ አለ። በማይመለከተው ይመለከተኛል በማያገባውም ያገባኛል እንዳለና ሕዝባችንን እንዳመሰ ባጅቷል። ለአንድ ዓመት ሳይቋረጥ ለቀጠለው የሙስሊም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የመብት ጥያቄ አሉታዊ መልስ ሲሰጥ የከረመው ወያኔ በራሱ መንገድ መሪዎቻቸሁ እነዚህ ናቸው ብሎ አስቀምጧል። ለመብት የሚደረገው እንቅስቃሴ ባለመብረዱም በገርባ ቀበሌ የፈጸመውን ግድያና አረመኔያዊ ጭፍጨርፋ ገና ሳንረሳ አሁን ደግሞ በሀረር ገና ላቅመ አዳም ያልደረሰ ከ10 እስከ 12 ዓመት እድሜ የሚገመት ህጻን ባደባባይ በመግደልና ጥቂት የማይባሉትንም በማቁሰል ማንነቱንና ትክክለኛ ራዕዩን አሳይቶናል። በኦርቶዶክስ እምነት ላይም እየደረሰ ያለው አፈናና እኔ አውቃለሁ ባይነት ቀጥሎ ወያኔ የፈለገውን ፓትሪያርክ በአባ ጳውሎስ ቦታ ለማስቀመጥ የሚያደረገው ሩጫ የተበላ እቁብ ያህል እርግጠኛ ወደ መሆን ተቃርቧል።

 

ሰላሳ ሶስት የምርጫ ፓርቲዎችን ያካተተው ሰብስብ የወያኔ ምርጫ ቦርድ ለምርጫ ህጉ ይገዛ፣ ከምርጫ በፊት የመሮጫ ሜዳው ይስተካከል፣ ጥያቄዎች አሉንና እንወያይ በማለታቸው “በባለቤቱ የተማመነ …” እንደሚባለው የወያኔው ምርጫ ቦርድ ሁሉንም ፓርቲዎች ከወያኔ የወረዳና የአካባቢ ምርጫ ውጭ አድርጓል።

 

የመሰብሰብ፣ የመናገር፣ የመጻፍና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትን አስከብሬያለሁ እያለ ለዓለም የሚለፈው ወያኔ አንቱ የተባሉ ጋዜጠኞችን በእስር ከማማቀቅ ቀሪዎችንም ከማሰደድ ከማስገረፍና ከማሰሩም በተጨማሪ እንደ ባለራዕይ ወጣቶች አይነት ደፋር ለሀገር አሳቢ ማህበር ድንገት ብቅ ሲል ደግሞ ምክንያት እየፈጠሩ ከሕዝባቸው ጋር እንዳይገናኙና ዓላማቸውን እንዳያሳውቁ ከማስፈራራትና ጉሸማ አንስቶ ለእንደ አዲስ አበባ ወጣቶች ፎረም አይነቶች የተፈቀደውን የስብሰባ ቦታ ከመከልከሉም በላይ በራሳቸው ተሯሩጠው ካገኙት የስብሰባ አዳራሽ ድረስ ካድሬዎቹን አስርጎ በማስገባትና የመሰብሰብ መብታቸውን በመጋፋት ዓላማቸውን እንዳያሳውቁና ወደ ሕዝባቸው እንዳይደርሱ ለማድረግ ስራ በዝቶበት ከርሟል።

 

 

በጋምቤላና በአፋር በኢንቨስትመንት ስም የአካባቢውን ኗሪ አርሶ አደርና አርብቶ አደር ለዘመናት ከኖረበትና እጅጉን ካለማው የእርሻ ማሳው በሃይል በማፈናቀል በሰፈራ ስም ወደ ቦዳ መሬቶች የማዛወሩ ስራ አርሶ አደር ወገኖቻችን ላይ የፈጠረው ቀውስ ሳይስተካከል ዛሬ ይኸው ተግባር በሱሪ በከፋ መልኩ ቀጥሏል። በሱሪ የቀጠለው አርሶ አደሮችን የማፈናቀሉ የወያኔ እኩይ ስራ እጅግ ተካሮ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሱሪዎች ያሰቃቂ ግድያ ምክንያት ሆኗል። ምስኪን ሱሪዎች የእርሻ መሬታቸውን ተነጥቀው በሀገራቸው የመኖር መብታቸውን ተገፈው ባንድ ጉድጓድ ሰላሳ ሰባው እንዲህ እንደሰሞኑ እጅግ ሲከፋም እስከ አንድ መቶ ሃምሳ እየተቀበሩ ይገኛሉ። የወያኔ ራዕይም በሀገራችን በዚህ መልኩ ሳይበረዝና ሳይከለስ ተስተካክሎ ቀጥሏል።

 

በሕዝባችን ላይ እያደረሰ ያለው የሀገር ውስጡ ግፍና መከራ ሳይበርድ በምስራቅ አፍሪካ እንደልቡ የሚወጣውና የሚገባው ወያኔ በቀጠናው ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በስደት ዓለም ሌላ ስደት ለመሆን መከራውን እያየ ይገኛል።

 

ኢትዮጵያዊያን በጅቡቲ ይታፈናሉ ተላልፈውም ለሀገር ውስጥ እስርና ከዚህም ሲከፋ ለግድያ ይዳረጋሉ። በኬንያ የሚኖሩ ወገኖቻችን ያፈና ስጋት አለብን ሲሉ እየጮሁ ነው። በሱዳን በተለይም በደቡብ ሱዳን በቀድሞው የወያኔ ወታደር ያሁኑ ነጋዴ የይስሙላው ጀነራል ፃድቃን አቀነባባሪነት ወገኖቻችን የመታፈንና ወደ ሀገር አስር ቤት የመመለስ፣ ባሉበት የመገደል ወይም ወደ ሌላ ሶስተኛ ሀገር እንደገና የመከራ ስደት ለመጀመር በጭንቅ ላይ መሆናቸው ይሰማል። በሶማሊያ የወገኖቻችን ኑሮ የጭንቅ ነው። ወያኔ በእርግጥ ሰላም የማሳጣት ስራ በዝቶበት ከርሟል። ባንድ ጊዜ ሁሉም ላይ ለመገኘትና ጥቃት ለመሰንዘር እየሞከረ ይገኛል። ሁሉም ላይ ባንድ ጊዜ ለመገኘት መሞከር ግን አንዱንም ለመከወን አለመቻልን ሊያስከትል እንደሚችል የተረዳ አይመስልም። ኢትዮጵያዊያንን ለማጥመድ እጅግ በጣም ርቆ የብስና ውቅያኖስን አቆራርጦ ሲክለፈለፍ ከአሜሪካ የደህንነት ወጥመድ እንደዶለው የሰሞኑ ውርደቱ፤ አንድ ቀን እጅግ የከፋው የወያኔ እኩይ እንቅስቃሴ ወያኔን ላይመለስ ወደ መቃብር እንደማይከተው ምን ማረጋገጫ አለ … ምንም።

ይኸነው አንተሁነኝ

ጥር 19/2013 እ.ኤ.አ.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ