ከብዕር ስም ጀርባ

ብስራት ኢብሳ (ሆላንድ)

ድሮ የምደግፈው የነአበበ ጉርሙ የመቻል እግር ኳስ ቡድን ከጠፋ ከዓመታት በኋላ በትላንቱ ምሽት ለመጀመርያ ጊዜ የተከታተልኩትን፣ በደቡብ አፍሪካ፣ ብሔራዊ ቡድናችን ባሳዛኝ ሁኔታ በቡርኪና ፋሶ ተሸንፎ ጨዋታው ሲያልቅ፣ ተደብሬ የቴሌቭዥኑን መስመር ከኢሮ-ስፖርት ወደ ደች የዜና መስመር ቀይሬ ከባለቤቴ ጋር የዓለም ዜና ማዳመጥ ጀመርን።

 

በአፍሪካ አህጉራችን፣ ማሊ ውስጥ ፈረንሳይ “የአልካሂዳን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር” በሚል ርዕስ ዙርያ፣ ፈረንሳይ ሁሌ ለዚህ አይነት ተግባር የምታሰማራቸውን፣ ቅጥረኛ (ፈረንጆቹ ሜርሲነሪ የሚሉት) ወታደሮቿን እንደላከች በምስል በተቀረጸ ፊልም ካሳዩ በኋላ፣ አንድ ሆላንዳዊ ድሮ በእንደዚህ አይነት ውትድርና ተቀጥሮ የነበረ፣ ስለ ቅጥረኛ ወታደር ልምዱን ለተመልካችና አዳማጭ እንዲያካፍል ጋዜጠኛው አቀረበው።

 

እንደ ጀብደኛው የቀድሞ ቅጥረኛ ወታደር አገላለጽ፣ ለእንደዚህ አይነት ውትድርና መቀጠር የሚፈልጉ ሰዎች፣ የተለያየ የግል ችግር ያለባቸው፣ ዓላማ የሌለው ጀብዱ መስራት የሚወዱ፣ ለገንዘብ የሚሞቱ...ወዘተ ዘርዝሮ፣ የስልጠናው ክብደት፣ ያሰልጣኞቹን ኢ- ሰባዊ የጭካኔ አያያዝና፣ ኮርሱን ጨርሰው ከተልዕኮዋቸው በህይወት የሚመለሱበት ዕድል ምን ያህል የጠበበ እንደሆነ በጣም ሰፋ አድርጎ ልምዱን አካፈለ።

 

ከረዥም ልምዱ በተለይ ቀልቤን የሳበው፣ ሲቀጠሩ አዲስ የውሸት ስም እንደሚወጣላቸና፣ ትክክለኛ ስማቸውን የያዘ ፓስፖርታቸውን፣ የባንክ ካርዳቸውን፣ መንጃ ፍቃዳቸውን ... ወዘተ ማንኛውም ከእውነተኛ ማንነታቸው ጋር የተያያዘን ዶክሜንት እንደሚያቃጥሉና፣ አዲሱን ስማቸውን ብቻ የሚገልጽ መታወቂያ ተሰርቶ እንደሚሰጣቸው የተናገረው ነበር።

 

ይህንን የሚያደርጉበት ምክንያትም፣ ቅጥረኞቹ የሚላኩበት ሃገር እንዲሰሩ የሚታዘዙት፣ በሃገሩም ሆነ በዓለም አቀፍ ሕግ የተከለከለና፣ ኢ-ሰብዓዊ የሆነ ድርጊት እንደሆነ ቀድመው ስለሚያውቁት፣ የግል ኃላፊነትን ላለመውሰድና ከተጠያቂነት ለመሸሽ እንደሆነ አስረዳ።

 

ፕሮግራሙ ሲያልቅ፣ ስለሰማሁት እያብሰለሰልኩ፣ ዘወትር ዓርብ ማታ፣ ወደ መኝታዬ ከመሄዴ በፊት፣ እንደ ድሮ ካዛንቺስ ወይም ባንቢስ፣ ሦስቱ በር፣ አምስቱ በር፣ አድዋ መደዳ የመዝናኛ ስፍራዎችን የሚያካክስልኝ፣ አዲሱ የሽማግሌ የመዝናኛ ስፍራዬ የፓልቶክ መደዳ ጎራ ብዬ አንድ ሁለቱ ዘንድ ሃዘን ተቀምጠው ስለደረስኩኝ፤ ዘግቼ፣ የኢሜል መልዕክት እንዳለኝ ስፈትሽ አንድ በብዕር ስም የተጻፈ፣ በግለሰብ ስብዕና ላይ የሚያተኩር ዘገባ አየሁ። ፀሐፊው የራሳቸውን ስም ሸሽገው፣ የሚወቅሱትን ግለሰብ ስም ፀሐይ ላይ አስጥተውታል። እኚህ ፀሐፊ እንደ አተናተናቸው፣ ለሃገር ተቆርቋሪ፣ ረዥም ዓመታት በሆላንድ የኖሩ፣ ብዙ ውጣ ውረድ ያዩ ናቸው። ፀሐፊው ማን ሊሆን እንደሚችል ለማወቅ አልሞከርኩም። ምክንያቱም ፀሐፊው ሲጽፉ ሊያስጠረጥሩ የፈለጉት ሰው ስላለ፣ እሳቸውን መተባበር አልፈለኩም። በትክክለኛ ስማቸው በማይጽፉ ተቺዎችም ይሁን አስተያየት ሰጪዎች፣ እንኳን አቅዋም ለመውሰድ፣ ላለማንበብ ከወሰንኩኝ ስለሰነበትኩኝ፣ እንደዚህ አይነት፣ ስም የለሽ ደብዳቤዎች ሲመጡ፣ በቀጥታ የምልካቸው ወደ የቁሻሻ ማጠራቀሚያ ቅርጫት ነበር።

 

ይህ ምሽት ግን በኳሱ ብስጭትና፣ በቅጥረኛው ወታደር ታሪክ እየተገረምኩኝ ሳላስበው የእኚህን የብዕር ስም ትችት ግማሹን ካነበብኩ በኋላ ነበር፣ ማንበብ እንዳልነበረብኝ ከሃሳቤ የነቃሁት። ግማሽ ቃሌንም ቢሆን ለማክበር ጽሁፉን ማንበብ አቋርጬ፣ እንደተለመደው ወደ ቆሻሻ ቅርጫት ስፍራው ሰድጄው ወደ መኝታዬ ሄድኩኝ።

 

ነገር ግን እንደተመኘሁት ያቺ በስህተት ያነበብኳት እንደ አቦል ቡና እንቅልፍ ነስታኝ መገላበጥ ጀመርኩኝ። ድሮ እኔም በስሜ መጻፍ ከመጀመሬ በፊት በግለሰብ ዙርያ ሳይሆን በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ እጽፍ ስለነበር፣ የብዕር ወይም የውሸት ስም መቼና እንዴት? እንደተጀመረ፣ ለምን? ማን እንደጀመረው ለማወቅ ማሰላሰሌን ተያያዝኩት። እኔን እንደዚህ በጨረፍታ ያነበብኩትን እንቅልፍ የነሳኝ፣ የሚጻፍባቸው ግለሰቦችንና፣ ፀሐፊው እራሱ እንቅልፍ አጥቶ በዚህ የስፖርት ግርግር ለዚህ ጉዳይ ጊዜውን ያጠፋው ምን ያህል የተጎዳና፣ እርዳታ የሚያስፈልገው ሰው ይሆን? ወይስ እንደተለመደው የወያኔ ተላላኪዎች? እያልኩኝ እያሰላሰልኩኝ እንቅልፍ አሸለበኝ።

 

ይህንን እንቅልፍ የነሳኝን የብዕር ስም አመጣጥ ቅድመ ታሪክ ለማወቅ ዛሬ ጠዋት ከቁርስ በኋላ ባለቤቴን ወደገበያ ብቻዋን ልኬ፣ የተለመደ ጉግሌንና፣ ዊኪፒዲያን አገላበጥኩኝ። የደረስኩበትንም ማሰርያ ለአንባቢዎቼ አካፍዬ ለመገላገል ወሰንኩኝ። ስለዚህ ይህ መልዕክት በብዕር ስም ስለተላከልኝ መልዕክት አስተያየት ለመስጠት፣ ወይም የብዕር ስምን በደፈናው ለማውገዝ አይደለም።

 

ከላይ እንደጠቀስኩት ፈረንሳዮች ለቅጥረኛ ወታደር ብቻ ሳይሆን፣ ለመደበኛ ወታደሮቻቸውም፣ ከፈረንሳይ አብዮት በፊት ጀምሮ፣ ከሙሉ ስማቸው መጨረሻ፣ ኒክ ኔም፣ ተደጋጋሚ ስሞችን ለመለየት፣ ወታደሩ ከመጣበት አካባቢ መንደር፣ መንገድ፣ ተራራ ስም ጋር የሚያያዝ፣ ወይም በሰውየው ሰውነት ላይ ከሚታይ የተለየ ነገር በማያያዝ ተቀጥላ ስም ያወጡለት ነበር። በሃገራችንም ጀብዱ የሰሩ ጀግናዎች ከፈረሳቸው ስም ጋር (ታጠቅ፣ ገስግስ፣ አባ ቦራ፣ ወዘተ) እንደሚባለው ማለት ነው። በተረፈ ከተወሰነ ሙያቸው፣ ባህሪያቸው፣ ከሚወዱት ነገር፣ ከሚያዘወትሩት፣ መርሳት ከማይፈልጉት፣ ... ወዘተ ጋር በተያያዘ የሚወጡ ብዙ አይነት፣ የብዕር፣ የመድረክ፣ የስክሪን፣ የኃይማኖት፣ የተልዕኮ፣ ... መዘርዘር እስከሚሰለቸን ብዙ አይነት የተለያዩ (ፔሱዶኒም፣ ኒክ) ስሞች መጠቀም በዓለማችን የተለመደ ነው።

 

እንዲሁ በፖለቲካውም ከአስራ ስምንተኛውና፣ አስራ ዘጠነኛው ዘመን ጀምሮ፣ ለህቡዕ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለቀስቃሽ ጋዜጦች፣ ለህቡዕ እንቅስቃሴዎች፣ ለካድሬ ስሞች የብዕር ወይም የድብቅ ስም ተጠቅመዋል። ለምሳሌ ሌኒን፣ ስታሊን፣ ትሮትስኪ ... ወዘተ የካድሬ (የፖለቲካ) ስማቸው እንጂ፣ ትክክለኛ ስማቸው ሌላ ነው። ብዙዎቹ ቀሪውን ዕድሜያቸውን ከትክክለኛ ስማቸው በላይ የሚታወቁበት ወይም የሚጠሩበት በአንድ ወቅት፣ ለሆነ ምክንያት ወይም ችግር ባወጡት ስማቸው ነው። በኛም ሃገር በባህላችን በስማችን ላይ፣ እንደ ቅጽል፣ ከምግባር፣ ወይም ከድርጊት ጋር በተያያዘ ምክንያት እንጨምር ነበር። ከዚህ ባሻገር፣ እንደ ውጪው ሃገር የብዕር ስም መጠቀም የተጀመረው፣ ይኔ ትውልድ ሥርዓቱን መታገል ከጀመረና፣ የግራው ፖለቲካ ወደ ሃገራችን ከገባ በኋላ፣ እራስን ከአገዛዙ የፖሊስና የጸጥታ አፈና ላለማጋለጥና፣ ፍልስፍናውን እንደፈጠሩት የቀደምት ፖለቲከኞችን መንገድ እንደፋሺንም ጭምር በመከተል ነበር።

 

ሆኖም በአንድ በተወሰነ ወቅት፣ ይህ እራስን ከአንባገነኖች አፈና ተደብቆ የማታገያና የመታገያ ዘዴ፣ ሌሎችም፣ እንደ ማፍያ አይነት ወንጀለኛ ድርጅቶች ለመጥፎ ተግባር መጠቀም ጀመሩ። ከላይ ቅጥረኛው ወታደር እንደ ነገረን፣ በፖለቲካውም ሆነ በማፍያው ዓለም፣ ስማቸውን እየደበቁ በማስፈራራት በመዝረፍ፣ ስም እያስጠፉ እራሳቸውን ለመጥቀም፣ ለማበልጽግና በኋላም እራሳቸውን ከኃላፊነትና፣ ከተጠያቂነት ለማምለጥ የብዕር ስምን መጠቀም ቀጠሉ።

 

ባጠቃላይ የብዕር ስም ሌላውን አጥቅቶ ለመደበቂያ፣ ለወንጀል ተግባር፣ ሌላውን ለማስጠርጠር፣ ለመከፋፈል፣ ስም ለማጥፋት አይሁን እንጂ፣ ማንም የብዕር ወይም የውሸት ስም የመጠቀም መብትም አለው። በሚወዳት ፍቅረኛው፣ በምታደንቀው ጀግና ስም፣ በምንወደው መፈክር ... ወዘተ፣ የብዕር ስም መጠቀም ተንኮልና ሴራ እስከሌለው ድረስ፣ ችግር የለውም። ወይም በአገዛዙ ላይ ለህይወታቸው የሚያሰጋ ትችት የሚያቀርቡና፣ ሃገር ውስጥ መግባትና መውጣት የሚፈልጉ እስከሆኑ ድረስ፣ በበኩሌ ችግራቸው ይገባኛል።

 

በተረፈ እዚሁ እንደ ከሳሾቹ ከሃገሩ ለተሰደደ፣ በግልጽ ማንነታቸውን አሳውቀው የመተቸትም ሆነ የመቃወም መብት የተጠበቀበት ነጻ ሃገር ቁጭ ብለው፣ የሚጽፉትን በእውነት የሚያምኑበት ከሆነና ሌላ የተደበቀ ተንኮል ከሌለበት?፣ ወይም ተገዶ በተጽዕኖ፣ አሊያም ገንዘብና ስልጣን አታሎት ካልሆነ በስተቀ፣ የሚተቸውን ሰው ስም እየጠቀሰ የራሱን ስም የሚደብቅበት ምክንያት የለም።

 

(በእርግጥ አንዳንድ የሌላውን ቀልብ ለመሳብ፣ የውይይት ማዕከል ለመሆንና ለሚቀጥለው ተንኮላቸው ሽፋን ለመጠቀም፣ ሌላ ሰው እንደጻፈ አስመስለው በራሳቸው ላይ የሚጽፉ እንዳሉ፣ በተለያዩ መጻሕፍት ያነበብናቸውና፣ “ተደራራቢ ስብዕና” ፈረንጆቹ “መልቲፕል አይደንቲቲ” የሚሏቸው የግለሰብ ባህሪዎች መኖራቸውንም አንዘነጋ።)

 

ወደ ጀመርኩት ልመለስና፣ እንዲያውም በቅርቡ የተጀመረው፣ “በአንድ ጠጠር ሦስት ወፍ” እንደሚባለው፣ ስምን መደበቅ ብቻ ሳይሆን፣ ጻፈ አስኝተው ለማሳጣት የሚፈልጉትንም ሰው አይነት የአጻጻፍ ዘዴ፣ የፊደሉ አመራረጣቸው፣ የአርስት አሰጣጣቸው፣ ቅንፍና ኮማ ሳይቀር ሊያስጠረጥሩ እንደሚፈልጉት ሰው አድርገው መጻፍ ጀምረዋል። በዚህ ዘዴ የሚፈጽሙት ደባ ሊያጠቁ የሚፈልጉትን አስጠርጥረው ያስነጥሉታል፣ ያስጠሉታል። የሚሰድቡትንም በዚህ አይነት ስሙን ያጠፋሉ። በሁለቱ ግለሰብ፣ ወይም ድርጅት ወይም ... ወዘተ ቅራኔ ፈጥረው ያተራምሳሉ። ይህ አይነት የተቀነባበረ ሴራ ደግሞ፣ በግለሰብ የሚሰራ፣ ወይም አንድን ሰው ለመጥቀም ሳይሆን፣ ከኋላው ወፍራም መዳፍ ያለበት ወያኔያዊ ወይም ሻዕቢያዊ ተልዕኮ ብቻ ሳይሆን ከተቃዋሚም ሰፈር አካባቢ ከሆነ፤ በጣም አደገኛ በታታኝ ሴራ ስለሆነ፤ የድረ-ገጽ ኃላፊዎች፣ እንደዚህ አይነት ዝቅ ያለ ደረጃ ወርደው ለሚከፋፍሉን፣ ትግሉንም ሆነ ታጋዮችን ስለሚያዳክም መተባበር የለባቸውም።

 

ትችት ተገቢ ነው። አንድ ተቺ ስለ ግለሰብ የሚጽፈውን የሚያምንበት ከሆነ እራሱን መደበቅ የለበትም። የማያምንበት ወይም የሚፈራ ከሆነ አርፎ መቀመጥ ይችላል። ነገር ግን እሱ ማንነቱን ማሳወቅ ፈርቶ፣ የሚከሰውን ሰው ስም እየጠቀሰ፣ ያልጻፈን ሰው እያስጠረጠረ የሚደበቅ ሰው የሚመሳሰለው፣ ከኋላ አድፍጦ ከሚተኩስ ፈሪ ሰው ጋር ብቻ ነው።

 

ስለዚህ የኢንተርኔት ድረ-ገጽ ኃላፊዎች፣ እንደነዚህ አይነት ኃላፊነት የማይሰማቸው፣ እንደ ቅጥረኛው ወታደር ከተጠያቂነትና፣ ከኃላፊነት ለማምለጥ፣ ተደብቀው በብዕር ስም ደባ የሚሰሩትን፣ ድረ-ገጾቻችሁ ላይ ለማውጣት አትተባበርዋቸው። በማንኛውም ኃይማኖት፣ ሞራል፣ ኤቲክስ፣ ጤነኛ አዕምሮ ያለው ይህን አይነት አሰራር፣ አይከተልም። (በእርግጥ በአንባቢ እጦትና፣ በራሳቸው ምርጫ ስሜታዊ አሉባልታዎችን በማስተናገድ ድረ-ገጾቻቸውን በዚህ አይነት ጽሁፍ ለማጨናነቅ ከወሰኑት በስተቀር) ማንም ለፍትህና ለዲሞክራሲ የሚታገል፣ የኢንተርኔት ድረ-ገጽ ኃላፊ፣ ከአርዕስቱ ወጥቶ በግለሰቦች ስብዕና ላይ በሃሰት ስም ጀርባ ተደብቀው የተንኮል ድራማ ዘመቻ ለማስነበብ የሚፈልጉትን ተንኮለኞች እንደማይተባበሩ ተስፋ አለኝ።

 

በተረፈ በኳሱ ጨዋታ ትናንት ብንሸነፍም፣ ከኳሱ ጀርባ ተከፋፍለን እንድንቆም ተዘጋጅቶ የነበረውን ድራማ፣ አብዛኛው ወገናችን ነቅቶ፣ ከብሔራዊ ቡድናችን ጎን በመሰለፍ የተዘጋጀውን ወጥመድ በማክሸፉና፣ በአንድነት ቆሞ ለወገኑ ድጋፉን መስጠት በመቻሉ፣ ሌላ የሕብረትና፣ የፀባይ ድል ስለተጎናጸፍን፣ በደቡብ ያጣነውን ኳስ፣ ከደቡብ እስከ ሰሜን፣ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ተያይዘን አንድነታችንን የደረስንበትን አዲስ ክስተትና፣ ድል እንደተፈጠረ ሳንረሳ፣ ይህንንም እያዳበርነው፣ እያቀጣጠልነው ወደፊት እንቀጥል በማለት የሽማግሌ ምክሬን አስተላልፋለሁ።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ከከፋፋዮች ይጠብቃት!! እኛም እንተባበረው!!

ብስራት ኢብሳ (ሆላንድ) 26-01-2013

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ