Happy Ethiopian Newy Year! መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልዎ!

ትዕዝብት አድማሱ

ሰሞኑን የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ስከታተል ሶስት ድራማዎች ጎን ለጎን ሲካሄዱ ታዝቤአለሁ። አንደኛው ድራማ የመከላከያ ሠራዊት ሳምንት በሚል እየተካሄደ ያለው ሰልፍና ኤግዚቪሽን ነው። ሁለተኛው ድራማ ጅሃዳዊ ሐራካት ፊልም በሚል ተደጋግሞ የቀረበው አስቂኝና አሳዛኝ ድራማ ነው።


ሶስተኛው ድራማ ደግሞ የህወሓት 38ኛ በዓል የትግራይ ህዝብ ልደት ነው እየተባለ በውጭና በሀገር ቤት ሲከበር ማየቴ ነው። በኔ አመለካከት ሶስቱም አላማቸውና ግባቸው አንድ ዓይነት ሆኖ ነው ያገኘሁት። አላማቸው በርዕደ መሬት እየተናወጠ ያለው ቡድን በህዝብ ፊት ሀይል (ጡንቻ) ያለው መንግስት መኖኑን ለማሳየት ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ የአንድ ሞኖፓላዊ ድርጅት ጠባቂና ተከላካይ የሆነው የህወሓት ሠራዊት እየተባለ የሚነገርለትን መከላከያ መልኩንና ቀለሙን በመቀያየር ኢትዮጵያዊ ሠራዊት መስሎ እንዲታይ እየተደረገ ያለው ጥረት ነው። ወጣም ወረደ የሶስቱም ድራማዎች ግብ የኢትዮጵያ ህዝብ ለመብቱ እንዳይተጋል በሀይል በማስፈራራት ከነሱ ውጭ በኢትዮጵያ ምድር ሌላ ተቀናቃኝና ለነፃነቱ የሚታገል እንዳይበቅል አንገቱን ለማስደፋት የተወጠነ ነው። ይህን ዓይነቱ የኮሚኒስት ምትሃታዊ ተንኰል የወለደው የፈጠራ ተውኔት ደግሞ ባዶና ውሸት መሆኑን ኢትዮጵያዊ ቀርቶ ሌላም ጠንቅቆ ያውቀዋል። "ውሸት ሲደጋገም ሓቅ ይመስላል" ይላልና ስንክሳር መፅሐፋቸው።

 

ወደ ተነሳሁበት ወደ ጥያቄዬ ልግባ፡- 10 ጥያቄዎች ናቸው። ልብ ብላችሁ ተከታተሉ፦

1. ሠራዊቱ "የሕገ መንግስት ዘብ ነው" እየተባለ በተደጋጋሚ ሲነገርለት እንሰማለን። ለመሆኑ የተኛው ሕገ መንግስት ነው?። እውነት መከላከያ ሠራዊት የሕገ መንግስት ዘብ ቢሆን ኖሮ የህዝብ ድምፅ በኃይል ሲነጠቅ፣ ሕገ መንግስቱ ለአንድ ሰው ብሎም ለአንድ ድርጅት መጠቀምያና መገልጊያ ሆኖ ሲቆር፣ የፍትሕና የዳኝነት ተቋማት ነፃነታቸውንና ውሳኔያቸውን በጥቂት መሪዎችና ካድሬዎቻቸው በግልፅ በአቋራጭ ሲነጠቅ ሲደፍርና ሲጣስ ለማን ነው አቤት የሚባለው? የመከላከያ ሠራዊቱ ዘብነትና ህዝባዊነትስ የቱ ላይ ነው? ለመሆኑ ይህቺን ሚስኪን ሀገራችን ባለቤትዋ ማን ነው? እናንተ የሠራዊት አባላት የታጠቃችሁት መሳሪያም ሆነ የምታገኙት ጥቅምና ደመወዝ ከመሪዎቻችሁ ኪስ የወጣ ሳይሆን የህዝብ ገንዘብና የሀገሪትዋን አንጡራ ሀብት መሆኑን ትዘነጋላችሁ የሚል ጥርጣሬ የለኝም። ነገር ግን የመሳሪያችሁ አፈ ሙዝ ያነጣጠረው በማን ላይ ነው?

 

2. አሁን ያለው ሠራዊት ካለፉት ስርዓቶች የተሻለና ለሀገሩ ሉዓላዊነትና ለህዝብ ልዕልና የቆመ ነው እየተባለ ነጋ ጠባ ሲነገርለት እንሰማለን። ለመሆኑ ይችን ሀገር ከባዕዳን ወራሪዎች እየተዋጋ ክብርዋን በደሙ ጠብቆ ያቆያት ማን ነው? በአንፃሩ የሀገሩን ብሄራዊ ጥቅም፣ ዳር ድንበሩንና የባህር በሩን መጠበቅ አቅቶት የሻዕቢያ ባለሟል በመሆን መሬቱን ለባዕዳን አሳልፎ በመስጠት ሽባ ሀገር ያወረሰን የሃፄ ሀይለስላሴ ሠራዊት ነውን? ሌላ ቀርቶ የአውሮጳ ቅኝ ገዢዎች እንኳን ያን ያህል ያልደፈሩን በአሁኑ ዘመን ግን ከባዕድ ሀይል (ከሻዕቢያ) ጋር ተመሳጥሮ ህዝባችንን ያስደፈረና ያስገደለ የሃፄ ኃይለስላሴ ሠራዊትና መንግስት ነውን?

 

3. የመከላከያ ሠራዊት ከህዝብ አብራክ የወጣ፣ የህዝብና የሀገር ፍቅር ያለው የድል ሠራዊት ነው ሲባል እሰማለሁ። ባንድ በኩል ያስቀኛል በሌላ በኩል ደግሞ ያሳዝነኛል። የሚያሳዝነኝ ባድመን ነፃ ታወጣለህ ተብሎ የዘመተው ሀይልና የተከፈለው መስዋእትነት ከንቱ ሆኖ መቅረቱ ነው። ጉዳዩ እስከ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ይድረስ እንጂ የመጨረሻ አሸናፊ ሆኖ የተገኘው ሻዕቢያ ነው። ሻዕቢያ ያሻነፈበት ምክንያት ደግሞ ሀቅ ስለያዘ ሳይሆን እናት ሀገራችን በፅናት የሚከራከርላት ቁርጠኛ ኢትዮጵያዊ ልጅ በማጣትዋ መሆኑን ማንም ይገነዘበዋል። ታዲያ የኛ መከላከያ እውነት የሀገርና የህዝብ ፍቅር ያለህ ሠራዊት ከሆነክ ባድመ የማን ነው የሚል ጥያቄ አንስተህ ታውቃለህን? ከጥዋቱ ባድመ የኤርትራ መሆኑን የሚታወቅ ከሆነ ለምን ያን ያህል ደም እንዲፈስ ተደረገ? ብለህ መሪዎችህን ጠይቀህ ታውቃለህን?

 

4. የኤርትራ መገንጠል ሰላም ያመጣል ሲባል ነበር። ነገር ግን ባሰበት እንጂ አልበረደም። ሰሜኑ አሁንም የጦርነት ቀጠና ነው። እስካሁንዋ ደቂቃ ድረስ ህይወት እየተቀጠፈ ይገኛል። ይህ ትራጀዲ መቋጫው መቼ ነው ብለህ ትገምታለህ? በሰሜኑ ክፍላተ ሀገራችን አሁንም በየቀኑ በሻዕቢያ ታጣቂዎች እየታፈኑ የሚወሰዱትን በሽዎች የሚገመቱ ዜጎቻችን የት እንደደረሱ የሚታወቅ ነገር የለም። ዜጎቼ ናቸው ብሎ ጥብቅና የሚቆምላቸው አስታዋሽ ኢትዮጵያዊ መንግስትም ገና አልበቀለም። ታዲያ እናንተ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በዳር ድንበሩ አካባቢ በቀበሮ ጉድጓድ በምሽግ ተቀምጣችሁ በፍርድ ያለቀለትና የሞተ መሬት እየጠበቃችሁ መኖሩ ትርጉሙ ምንድን ነው? የራሱን ህዝብና ሀገር ድህንነትና ሰላም መጠበቅ ያልቻለ ሠራዊት የድል ሠራዊት ነው ሊባል ይችላል ወይ? በራሱ መሬት ላይ ዘላቂ ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ ያቃታው ሠራዊት የሌላ ሀገር ህዝብ ሰላም መጠበቅና ለፍትሕ መቆም ይችላልን?

 

5. የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገርና የህዝብ ፍቅር አለው የሚለው አባባል ከነአቶ በረከት ስምዖን፣ አቶ ቴድሮስ ሐጎስ እና ሌሎች የአቶ መለስ ራዕይ ወራሾች ነን ከሚሉት መሪዎች አመለካከትና ፓሊሲ ጋር የሚቃረን አይሆንም ወይ?። አቶ በረከት "በሰላሳ ዓመት ዕድሜ ክልል ያለው ወጣት ስለ ዳር ድንበርና የባህር በር ጉዳዩ አይደለም ረስቶታል" የሚሉ ናቸው። ሠራዊቱም በነሱ ራዕይና ፓሊሲ የቀረፁትና የሚመሩት እነዚህ ናቸው። ታዲያ የሠራዊቱ የሀገርና የወገን ፍቅሩ የቱ ላይ ነው?

 

6. የመከላከያ ሠራዊት የልማት ምንጭና የዕድገት ተምሳሌት ነው እየተባለ ሲነገርለት እንሰማለን። በአፈ ሙዝ የሚገነባ ሀገር ቢኖር ኖሮ ሰሜን ኰሪያን በቀዳሚነት ልትጠቀስ ትችል ነበር። ነገር ግን አልሆነም። መሆንም አይችልም። በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ መከላከያ የሙሱናና የዝርፊያ ተምሳሌት እንጂ የልማት ምንጭ መሆን አልቻለም ብለው በጭብጥ መረጃ እያስደገፉ የሚናገሩ ብዙ ናቸው። በትግራይ አካባቢ በህዝቡ ዘንድ መከላከያ ማለት "ዱባይ ወይም ጅዳ" ተብሎ እንደሚጠራም ጓደኞቼ ነግረውኛል። ምክንያቱም በመከላከያ አካባቢ ወፍራም ዘመድ ያለው ሰው በአንድ ጊዜ ሚሊዮነር ሊሆን ይችላል የሚል ትዕዝብት ስላላቸው ነው። ስለሆነም መከላከያና ህወሓት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅ በሆኑበት ሁኔታ በየከተማው ፎቅ የሌለው ጀነራልና ኰኔሬል የለም ቢባል ውሸት አይደለም። ታዲያ ወገኖቼ የሀገር ልማትና ሌብነት አብሮ ይሄዳል ወይ?

 

7. በየዓመቱ በመቶ ሽዎች የሚገመቱ ወጣቶች ከየትምህርት ተቋማቱ እየተመረቁ በየቀኑ ስራ ፍለጋ ሲንከራተቱ ይታያል። ስራ አገኙ ከተባለ ደግሞ ከኰብል ድንጋይ ያለፈ አይደለም። ካላገኙ ደግሞ ወደ ስደት በመጉረፍ የባዕድ ሲሳይ ሆነው የሚቀሩ ወጣት ምሁራንና ባለሙያዎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። በአጠቃላይ በሀገሪትዋ ሙሱና ከኤይድስ የባሰ የሰደድ በሽታ በሆነበት ወቅት መከላከያ ብቻውን የልማት ምንጭ የሚሆንበት መመዘኛ ምንድን ነው? ሌላው ባለሙያ እየበተኑና እያመከኑ መከላከያ የልማት ማእከል እንዲሆን የሚደረግበት ሚስጢርስ ምን ይሆን?

 

8. ሌላው የታማኝነት ጥያቄ ነው። እርግጥ ነው አምባ ገነኖች ሠራዊቱን ሲቀርፁና ሲያዋቅሩ በአምሳላቸው ስለሆነ ከሀገርና ከህዝብ በላይ የመሪዎቹን ስልጣንና ድህንነት እንዲጠብቅና እንዲንከባከብ ይገደዳል። የኢትዮጵያ መከላከያ በተመሳሳይ በነፃነትና በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ታንፆ ያደገ ሳይሆን በአቶ መለስ ዜናዊ አመለካከትና ለአንድ ድርጅት ፍላጎትና አላማ መገልገያ ተብሎ የተቀረፀ መሆኑን ራሳቸው የመከላከያ ሰዎች እየተናገሩ ይገኛሉ። እውነታቸው ነው። ዛሬ ከኢትዮጵያ ካርታ ይልቅ የአንድ ግለ ሰብ መሪ ፎቶ ግራፍ የበለጠ ክብር የተሰጠበት ሁኔታ ይታያል። ዛሬ መለስ እንደ መሪ ሳይሆን እንደ ፈጣሪ የሚታይበት ጊዜ መሆኑን በግልፅ እየታየ ያለ ጉዳይ ነው። ታዲያ ሀቁ ይህ ከሆነ የሠራዊቱ ታማኝነት ቅድሚያ የሚሰጠው ለማን ይሆን? የሰሜን ኰሪያና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መሰረታዊ የባህሪይ፣ የአቋም፣ የአደረጃጀትና የደክትሪን ልዮነት አላቸው ብላችሁ ታምናላችሁን?

 

9. የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ገለልተኛ ነው ሲባል ይሰማል። ገልተኛ ማለት ደግሞ በሀይማኖት፣ በፓለቲካ አመለካከት፣ በነፃ ዳኝነት፣ በፍትህ አካላትና በዜጎች የግልና የቡድን ነፃነት ላይ ጣልቃ የማይገባ ማለት ይመስለኛል። ሀቁ ይህ ከሆነ የአንድ ፈላጭ ቆራጭ የፓለቲካ መሪ ፎቶግራፍ እንደ ታቦተ ፅዮን ተሸክሞ የሚሄድና የሚያመልክ ሠራዊት ገለልተኛ፣ የህዝብ ወገንተኛ፣ ነፃ የፍትሕና የልማት ሠራዊት መሆን ይችላል ብላችሁ ታምናላችሁን?

 

10. የመጨረሻ ጥያቄ ለህወሓት ታጋዮች፣ ካድሬዎች፣ ደጋፊዎቻቸው ነው። በራሳቸው አንደበት "እኛ ህወሓቶች ኤርትራን ከኤርትራውያን በላይ ታግለን ያስገነጠልናትና ነፃ ያወጣናት እኛ ነን" ብለው በማያሻማ መልኩ በሚያምኑት በአቶ ስብሓት ነጋ መሪነት የተፈጠረው የትግራይ ነፃ አውጪ ድርጅት (ህወሓት) ዛሬ በመከላከያ ሠራዊት ታጅቦ 38ኛው የልደት በዓሉን እያከበረ ይገኛል። ይህ በዓል ደግሞ ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜው ሳይሆን የትግራይ ህዝብ ልደት ነው እየተባለ በአደባባይ መከበር ከጀመረ እኖሆ ግማሽ ምእተ ዓመቱን ሊያስቆጥር ጥቂት ዓመታት ነው የቀረው። እንዲያውም በዓሉ የአንድ ፓለቲካ ድርጅት መታሰቢያ ቀን ከመሆን አልፎ በትግራይ ህዝብ ዘንድ እንደ አንድ ቅዱስ ቀን ተቆጥሮ በፍትሃተ ፀሎትና በድግስ እንዲያከብረው እየተደረገ ቆይቷል። ዛሬም በተመሳሳይ ደራማ በውጭም በሀገር ውስጥም ሲከበር እያየን ነው። ነገር ግን ጥያቄው የካቲት 11 የማን ልደት ነው? የበረከት? የስብሓት? የቴድሮስ? የመለስ? የጥቂት ካድሬዎች? ወይስ በስሙና በደሙ እየተነገደበት ሳይወድ በግድ የኤርትራ ነፃነት ማዳበሪያና የጥቂት ከሃዲ መሪዎች የስልጣን አገልጋይና መሳል ሆኖ እንዲኖር እየተደረገ በሁለት አለንጋ እየተገረፈ የሚገኘው ህዝብ ልደት ነውን?

 

የትግራይ ህዝብ በጀግኖች አባቶቹ የሰማእታቱ መቃብር ላይ ቆሞ የህወሓትን ልደት በጭፈራና በዳንኬራ የሚያከብርበት ዋና ምክንያት ምን ይሆን? እውነት በደሙ ራሱ የገነባትን ሀገር ተመልሶ ራሱ በማፍረስ ዛሬ ባህር አልባ የሆነች ሽባ ሀገር ይዞ በመቅረቱ ደስ ብሎት ይሆናል ብላችሁ ታምናላችሁን?

 

የትግራይ ህዝብ የህወሓት ልደትን የሚያከብረው ባድመ የኛ ነው፣ መሬትህ በባዕድ ተደፍረዋል፣ ዛሬም እንደ ትናንቱ ተነስ!! ክተት!! ተብሎ የከፈለውን መስዋእትነት ከንቱ ሆኖ በመቅረቱንና መሬቱን ተሸንሽኖ ለባዕድ በመሰጠቱ ምክንያት ደስተኛ ስለሆነ ነው ብላችሁ ታምናላችሁን?

 

"አትረፍ ያለው በሬ ቆዳውን ለከበሮ ይውላል እንዲሉ" ህወሓት የትግራይን ህዝብ ሁለት ጊዜ ገድሎታል። አንድ ኤርትራን ነፃ ለማውጣት በአስር ሽዎች የሚቆጠሩ ለጋ ወጣቶች በሳህል በረሃ የአምራ ሲሳይ ሆነው እንዲቀሩ አድረጓል። ሁለተኛ ደግሞ ህዝቡ አድኑን እያለ ሲጮህ ጆሮ ዳባ በመስጠት አሳልፎ ለጅብ በመስጠት ዳግም በሻዕቢያ ወረራ እንዲቀጠቀጥና እንዲደማ አድርገዋል። ለዚህም ነው ደደቢት የጥቂት ከሃዲዎች በዓል እንጂ የትግራይ ህዝብ ልደት አይደለም የምንለው። ዛሬ ጥቂት ሙሰኞቹን በዊስኪ እየተራጨን የምናጅብበት ጊዜ ሳይሆን ህዝብና ሀገር ማእከል ያደረገ አጀንዳ ይዘን ለመብታችን የምንታገልበት ወቅት ነው።

ትዕዝብት አድማሱ

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!