ለስፖርት ባለሙያዎቻችን እንከብካቤ
ከ. ኃይሌ
በስፖርት ዓለም ማሸነፍና መሸነፍ የሚፈራረቁ ጉዳዮች መሆኑ እየታወቀ ስፖርተኞቻችን ሲሸነፉ ለጥረታቸው መመስገን ሲገባ ነቀፋ ሲዘነዘርባቸው ይሰማል። እንዲሁም ለታወቁ የስፖርትና አርቲስት ባለሙያዎች/ግለሰቦች ታምመው የመታከሚያ ገንዘብ ስላጡ ለእነሱ የዕርዳታ ገንዘብ ለመሰብሰብ በአገር ቤትና በውጭው ዓለም በሚገኙት ሬዲዮ አማካይነት የዕርዳታ ጥያቄ ማሰማት እየተለመደ መጥቷል።
ይህንን ርዕስ ለመጻፍ ያነሳሳኝ በስፖርት ባለሙያዎቻችን ላይ ስለተሰነዘረባቸው ወቀሳና የዕርዳታ ጥያቄ ለማውሳት ሳይሆን አገሪቱ በኢኮኖሚ ደካማ ስለሆነችና አቅመ ደካሞችን ለመርዳት መንግሥት ስላልተደራጀ ወላጆችንና ደካሞችን የሚንከባከቡ ልጆቻቸው ነበሩ። ሆኖም አሁን የወጣቱ ባህርይ ተቀይሮ እራስ ወዳድ ሀኗል። እንዲሁም ልጆቻቸው እያደጉ ወይም ከጭንቀት ብዛት ጥለዋቸው ሲሄዱና ስራ አጥ ከሆኑ እንደሌላው አገር ከሆነ መሰል ዕርዳታ ፈላጊዎችንን መንከባከብ የመንግሥት ሌላው የሥራ ድርሻው አይደለምን። የስፖርት ባለሙያዎች በስፖርት ሙያ ተሰልፈው ባስገኙት ከፍተኛ ውጤት አገራችንን ያሳወቁ፤ ታሪካችንን ያስጠሩና ለአገራችን ክብር ያመጡ፣ ጀግኖቻችንን ሆነው ሳለ ተገቢው እንክብካቤና ትኩረት ሊሰጣቸው ሲገባ በጤንነት ጉድለትና በእድሜ መግፋት ሳቢያ አቅማቸው ለደከሙ ስፖርተኞቻችን እርዳታ አጥተው ለልመና ሞያቸው መጠቀሱ ለሰሚው የሚያስገርም ጉዳይ መሆኑን ለመጠቆም ነው።
በመሠረቱ አትሌቶቻችን ባስገኙት ውጤት የሚያገኙት ገንዘብ ለመታከሚያ ያህል አያጡም ነበር። አሁን አሁን ካላቸው ገንዘብ ላይ ለመጦሪያ እያለ ገንዘባቸውን መዋለ-ነዋይ ላይ ማዋል ወይም ማስቀመጥ ጀምሩ እንጂ ቤተሰባቸውንና ዘመድ አዝማድ እየረዱ ስለሚኖሩ ችግረኛ ናቸው። በመሆኑም ሲታመሙ በአነስተኛ ወጪ ለመታከም ወደ መንግሥት ሃኪም ቤቶች ሲሄዱም ህዝብ እንዲያገለግሉ የተቀጠሩት ሃኪሞች እዚያው ተፈላጊውን ህክምና መስጠት ሲገባቸው ወደ እራሳቸው ወይም አገር ወስጥ ገብተው ደሃውን ህዝብ ወደሚበዘብዙ የውጭ አገር ባለሃብት ክሊንክ ሄደው እንዲታከሙ ሲታዘዙ ያለ የሌላቸውን ገንዘብ ለመጠቀም ስለሚገደዱ ነው። ኢትዮጵያውያን ሃኪሞች በልዩ ልዩ ምክንያት ወደ ውጭ አገር ለመሰደድ ስለበቁ የሃኪም እጥረት ስለተፈጠረና የመቆጣጠሪያ ስልት ስለሌለ የግል ክሊንኮች በሸተኛውን በሚገባ ስለማያክሙ ሃብት ያለው ወደ ደቡብ አፍሪካና ወደ ኤዥያ አገሮች እየሄዱ መታከም አዲሱ ፋሽን ሆኗል። ከፍተኛ ወጪ ወጥቶበት ተሄዶም ነፍሱ ተርፎ አካሉ ተቆርጦ የሚመለስው ህመምተኛው ቁጥር ጥቂት አይደለም። ገንዘብ የሌለው ባህላዊ መድሐኒት ተጠቃሚ ህመምተኛ ስለበዛ የባህል መድህኒት ሰጪ ሃኪም ቤት በያካባቢው ተከፍቷል። ከፊሉም በሸተኛ ወደ ፍልውሃ እየሄደ በፈላ ውሃ መዘፍዘፍ ሌላው አማራጭ መንገድ ሆኖ ስላገኘው በአሁኑ ጊዜ ፍልውሃ የገላ መታጠቢያ ሥፍራ ብቻ መሆኑ ቀርቶ የበሽታ መፈወሻ ድርጅት ሆኖ ታይቶ የመንግሥት አንዱ የገቢ ምንጭ ማፍሪያ ሆኖ ተቆጥሯል።
እነዚህ ዜጎች በህይወት ሲኖሩ፤ ሲደክሙና ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ታሪካቸው አብሮ ሊታማ፤ ለወቀስ፤ ለመታመምና መቀበር የለበትም፤ ሲደክሙ መንከባከብ ማክበር ሲያሸንፉም ሆነ ሲሸነፉ ላደረጉት ጥረት ሁሉ ማመስገን እንደደረጃቸው መሸለም ሌሎችን ወደ ስፖርት ጎራ ለመጋበዝ የሚረዳ ድርጊት ነው። ሲሸነፉ መውቀስና ሲደክሙ ያለመንከባከብ በስፖርት ሞያ ላይ ለመሰለፍና እነሱን ለመተካት የሚፈልጉ ግለሰቦችን ስለሚያሳዝን ነገ በእኔ ላይ ቢደርሰ እንዲህ እሆናለሁ እያሉ በአዕምሮአቸው ውስጥ ስለሚጉላላ ወደ ስፖርት ዓለም ለመግባት እራሱን ያጨው ዜጋ እንዲያሸገሽግ፤ አገር ጥሎ እንዲኮበልልና የባዕድ አገር አገልጋይ እንደሚያደርገው ለማንም ሰው ግልጽ ነው።
ታመው የአልጋ ቁራኛ ከሆኑም እነሱ ይሳተፉበት የነበረውን ስፖርት ጊዜው ሲደርስ የእነሱን ታሪክ በማስታወስ ለህዝብ ማሰማት ለተተኪው ትውልድ እራሱን የቻለ ሞራልና ለተሳታፊዎች ደግሞ ንቃተ ህሊናቸውን የሚክብ ጉዳይ ነው። እንኳን እነሱን ከተቻለም ልጆቻቸውንና ቤተሰባቸውን ጭምር ጤንነታቸውን ለመንከባከብ የሚያስችል የአመራር ስልት ሊኖር በተገባ።
የአገር ስም ለማስጠራት የታገሉት ስፖርተኞች በስተኋላ በሸታ ላይ ሲወድቁ ወይም ሲደክሙ ለአገር ክብር ያመጡት ዝና ዘለዓለም እየታሰበ መኖር ስለሚገባው በሚያገለግሉበት ድርጅት የመተዳደሪያ መመሪያ ውስጥ ተጠቃልሎ በሌላ ሞያ ውስጥ ለአገልግሉ ባለስልጣኖች ክብር ከሚሰጣቸው ግለሰቦች በእኩል ደረጃ ለመታየት ከበቁ ይበልጥ ለመሥራት ያነሳሳቸዋልና። ላበረከቱትም መልካም ተግባር በአገር አቀፍ ደረጃ ዋጋ መስጠት አለበት። ሲጫወቱ ብቻ በጩኸት ማጀብና መልካም መመኘት ሲያሸነፉ መሸለም ብቻ በቂ አይሆንም። ጤንነታቸውን፤ ጉልበታቸውን ጊዜያቸውን ሰውተው ከሚወዷቸው ቤተሰባቸው እየተለዩ ልምምድ በማድረግ ለአገርና ለህዝብ ዝናና ክብር ለማምጣት ለታገሉ ስፖርተኞቻችን ተገቢው ዕውቅና ሊያገኙበት ይገባል። ከህዝብ የሚሰበስብላቸው ጊዛዊ ችሮታ ዘላቂ መፍትሄ ስለማይሆን በህጋዊ መንገድ እንክብካቤ የሚያገኙበትን መንግድ መንግሥት መቀየስ ይኖርበታል።
ሰው ናቸውና ይሳሳታሉ ከስህተት ይማራሉ፤ ተግባራቸውም ሁለትዮሸ ነው። ህዘቡ በተሰለፉበት ስፖርት እንዲያሸንፉ እንደሚፈልጋቸው ሁሉ እነሱም ህዝብ እንዲያከብራቸው ይሻሉ። ከዚህ ባነሰ ለማንም ሰው አይዋጥም፤ ተቀባይነትም የለውም። በቆይታቸው ሊደሰቱ ስለሚገባቸው ቃል የተገባላቸው በታሰበው ጊዜ ውስጥ ሊፈጸምላቸውና ከበሬታ ሊሰጣቸው ይገባል።
ልምድ ያካበቱ ኢትዮጵያውያን የስፖርት አሰልጣኞችና ተጫዋቾች እያሉ የውጭ ዜጋ አሰልጠኞች የውጭ ምንዛሬ እየከፈሉ ቀጥሮ ማሰራት ተቀጣሪውን የውጭ ዜጋ ግለሰብ ለመርዳት ካልሆነ በቀር ድርጊቱ የባለሙያዎችን ቅስም የሚሰብር የአገሪቱን የውጭ ምንዛሬ የሚያዳክም ተግባርና ውሳኔ ነው። ስለዚህ ጤንነት በምግብ ብቻ ለመከላከል በቂ ስለማይሆን እንዲህ ያለ ሙያ ያላቸውን ብርቅዬ ስፖርተኞችን በአካባቢያቸው በሚገኝ ስፖርት ክበብ ውስጥ እያሳተፉ በጉልበታቸው በእውቀታቸውና በልምዳቸው ጭምር ህዝቡን እያገለገሉ ተሳትፎ ማድረግ ለጤንነታቸው ደህንነት፤ ሞራላቸውን ለመጠበቅና ለሌላውም ምሳሌ ለመሆን ከመብቃታቸውም ባሻገር የአገሪቱን የገንዘብ ወጪ ይቀንሳል።
ሲሸነፉ የተሸነፉበትን ምክንያት መገምገምመና ድክመታቸውን ለማሻሻል አስፈላጊውን ማድረግ ሲገባ፤ ተሸነፉ ተብሎ ችላ ከማለት ሞራላቸውን ለመጠበቅ በአገሪቷ አቅም መሠረት የሚቻለውን ከማድረግ መታቀብ ትክክል አሰራር አይመስልም። ታዋቂነታቸውን በአገር አቀፍ ማሳወቅ፤ በጡረታ ሲገለሉም ሆነ በበሸታ ሲጠቁ ያገለገሉበት መ/ቤት ግንኙነት ሳያቋርጥ ልምዳቸውን መጠቀም ስማቸው በታሪክ መዝገብ ውስጥ እንዲሰፍር ማድረግና ላበረከቱት ተግባር ማድነቅ በሌሎች ላይ የስፖርት ፍቅር ያሳድራል። ላስገኙት ትንሽም ሆነ ትልቅ ውጤት ብሄራዊ እውቅና መስጥት ያሻል እንጂ ሲሸነፉ የሚወቀሱ ከሆነ ሌላው ከወቀሳ ለመዳን ለስፖርት ፍላጎት ያለውን ህዝብ ስሜት ይቀንሳል። አሸንፈው ሲመጡ ማድነቅ ተሸንፈው ሲመለሱ ማግለል አመራር ላይ ያሉትንም ትዝብት ላይ ይጥላል። ከሙያቸው ማግለልና ከተግባራቸው ጋር የማይመጣጠን አስተያየት መስጠት በስፖርት አፍቃሪው ላይ የሚያሳድረው መልዕክት የከፍ እንደሚሆን ከወዲሁ መገመት አያስቸግርም።
በእርግጥ ህዝብ አቀፍ አስተዳደር በአፍሪካ ሀገራት ውስጥ አይሰራም። ይሁን እንጂ ያለንበት ክፍለ ዘመን ህዝብ የነቃበት ጊዜ ስለሆነ መንግሥትም ወቅቱን የተከተለ አመራር ይዞ ካልሄደና በአጠቃላይ የህዝቡን ጤንነት ካልጠበቀ፤ ህዝቡ የተሟላ አምራች ዜጋ ሊሆን ስለማይችል የህዝቡ ጤንነት እንዲጠበቅ ማስተማር፤ ንቃተ ህሊናውን ማሳደግና መንከባከብ መንግሥት ሙሉ ኃላፊነት አለበት።
ዛሬ በአገራችን እንክብካቤ የሚፈለግ ቁጥር ህዝብ በፍጥነት እየጨመረ መሄዱን አሃዞች ያመላክታሉ። የጤንነት መጉደል በአቅመ ደጋፊዎችና በእድሜ የገፉ ሰዎች ቁጥር ሲጨምር በበሸታ ስለሚጠቁ በህክምና ግልጋሎት ላይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ለደህንነት ምግብና የተጣራ ውሃ ወሳኝነት ስለአለው ህዝቡ በገቢው ተመጣጣኝ ዋጋ ገዝቶ ለመመገብ እንዲችል በአቅርቦት ላይ መንግሥት ኃላፊነቱን መውሰድ ይኖርበታል። ስለሆነም በስፖርቱ ዓለም ዝናችን እንዲቀጥል ካስፈለገ የሚመለከተው መ/ቤት ጥናት እያካሄደ የረጅም የመካከለኛና የአጭር ጊዜ እቅድ ወይም ፖሊሲ ነድፎ በማውጣት ከአገሪቱ ኢኮኖሚ አቅም አኳያ የሚራመድ ስራ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ለዚህም ህዝቡ በቂ ተሳትፎ እንዲያደርግ በመንግሥት በኩል የሚፈለገውን አሟልቶና ምሳሌ ሆኖ መገኘት ወሳኝነቱ አያጠራጥርም።
ከ. ኃይሌ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.