ተነጠፈስ፥ ቀረ የአውራ ዶሮ ቁርበት

ዳዊት ፋንታ

እ.ኤ.አ. በ2012 ከተሠሩ ምፀታዊ ኮሜዲ ምርጥ የሆሊውድ ፊልሞች መካከል በሳሻ ባሮን ኮህን እና አሌክ በርግ ተፅፎ በሌሪ ቻርለስ ዳይሬክተርነት የተተወነው ''ዲክታተሩ'' /The Dictator/ የተሰኘው ፊልም በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው።


በዚህ ፊልም ላይ ዋና ገፀ-ባህርይ ሆኖ የሚተውነው አድሚራል ጄነራል አላዲን በኦሎምፒክ የ100 ሜትር ሩጫ ላይ ተሳታፊ የነበረ ሲሆን፣ የውድድሩን መጀመር የሚያበስረውን ሽጉጥ ራሱ በመያዝ የተወሰነ ሜትር ብቻውን ከሮጠ በኋላ ውድድሩን ያስጀምራል። በቅርብ ርቀት የተከተለውን ሯጭ ተኩሶ ከውድድሩ ያሰናክለዋል። እንዲሁም በመግቢያው መስመር ላይ ሪባን ዘርግተው የቆሙትን ሰዎች በፍርሃት በማሸማቀቅ ሪባኑን ይዘው ግማሽ መንገድ ያህል ወደ አላዲን እንዲመጡ በማድረግ ''አሸናፊነቱን'' ያረጋግጣል።

በእርግጥ ከዚህ ፊልም ጋር በይዘት ተመሳሳይ የሆነ የምርጫ ድራማ የአድሚራል ጄነራል አላዲን ተምሳሌት በሆነው ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ በየጊዜው ይሰራል፤ እንዲሁም በፊታችን ሚያዚያ በሚደረገው የአካባቢ ምርጫ ላይም ተመሳሳይ ነገር እየተሰራ ይገኛል።

ህወሃት ወደ ስልጣን ከወጣ ጀምሮ የአካባቢ ምርጫ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው በሽግግር መንግስቱ ወቅት እ.ኤ.አ በ1992 አጋማሽ አካባቢ ሲሆን እስከ ምርጫ-97 ድረስ ባለው ጊዜ ሌላ ተጨማሪ የአካባቢ ምርጫ ተደርጓል። ይሁን እንጂ ''ቀን እባብ ያየ፥ሌሊት በልጥ በረየ'' እንደሚባለው እ.ኤ.አ. በ2005 በተካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ (ምርጫ-97) የደረሰበትን ሽንፈት በፀጋ መቀበል የተሳነው ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ምድር ህወሃት እስካለ ድረስ የስልጣን ምንጩ አፈ-ሙዝ እንጂ ህዝብ እና የምርጫ ሳጥን የሚሆንበትን ምዕራፍ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በአምባገነናዊ ክንዱ አተመው!!!

ይህንንም አምባገነናዊ አካሄድ ለማጠናከር አንዳንድ መሠረታዊ ለውጦችን /Ground Works/ እስኪያጠናቅቅ ድረስ በተያዘለት የጊዜ ሠሌዳ መሠረት እ.ኤ.አ. በ2006 መካሄድ የነበረበት የአካባቢ ምርጫ እስከ 2008 እስኪራዘም ተደርጓል።

በዚህ ወቅትም የመወዳደሪያ ሜዳውን ለወያኔ/ኢህአዴግ ብቻ እንዲመች የሚያደርጉ ድንጋጌዎች ተግባራዊ ተደርገዋል። ከነዚህም መካከል የምርጫ ህግን ማሻሻል፣ የምርጫ ቦርድን እንደገና ማዋቀር የሚሉት ሲገኙበት በቀበሌና ወረዳ ምርጫ ላይም የተመራጮች ቁጥር ቢበዛ 24 የነበረው ወደ 300 እንዲያድግ ተደርጓል። በቀበሌና ወረዳዎች ላይ የተደረገው የተወካዮች ቁጥር ማሻቀብ በእርግጥ ወያኔ/ኢህአዴግ እንደሚለው የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ታስቦ ሳይሆን (1ኛ) የኢትዮጵያን ህዝብ ንብረት ለፓርቲው አገልግሎት ከሚያውለው ወያኔ/ኢህአዴግ አንፃር የተቃዋሚ ፓርቲዎች አቅም ውስን በመሆኑ በየቀበሌው 300 ተወካዮችን ለምርጫ ማቅረብ ባለመቻላቸው ወያኔ ይህንን የቁጥር የበላይነት እንዲጠቀምበት ሲሆን (2ኛ) በተግባር እንደታየው ወያኔ/ኢህአዴግ በየቀበሌው የሚያደርገውን የ5ለ1 አደረጃጀት በአግባቡ ለመምራትና ለመቆጣጠር በርከት ያለ የሰው ቁጥር በማስፈለጉ ነው።

በፌደራል ስርዓት ውስጥ የአካባቢ ምርጫ ከፍ ያለ ሚና ሲኖረው በተለይ አሸናፊው ፓርቲ ከህዝብ ጋር የቀጥታ ግንኙነት ስለሚኖረው ፓርቲዎች በማህበረሰቡ ውስጥ ዘልቀው በመግባት ለሀገር አቀፍ ምርጫ መሠረት እንዲጥሉ ያስችላቸዋል። ነገር ግን ፍትሀዊ የሆነ የመንግስት ሚዲያ አጠቃቀም በሌለበት፣ የመንግስት ንብረት ለገዢው ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ እየዋለ ባለበት፣ አፋኝ የሆኑ የምርጫ ህጎች ባሉበት፣ ገለልተኛ የምርጫ ታዛቢዎች ባልተጋበዙበት እንዲሁም ነፃና ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ፣ የፖሊስ ኃይልና ፍርድ ቤቶች በሌሉበት ሁኔታ በምርጫ ለመሳተፍ ማሰብ በእርግጥም የህዝብን የስልጣን ምንጭነት በኃይል ጨፍልቆ በአፈ-ሙዝ እያስተዳደረ ላለው አፋኝ ስርዓት ይሁንታን መስጠትና ለአምባገነናዊ ተግባሩም መተባበር ይሆናል። ለዚህም ይመስላል በቅርቡ ቁጥራቸው ከ33 የማያንስ ፓርቲዎች ከሚያዚያው የአካባቢ ምርጫ ራሳቸውን ያገለሉት።

በእርግጥ አሁን ባለው ሁኔታ እነዚህ ፓርቲዎች ተሳተፉም አልተሳተፉም በኢትዮጵያ ላለው የፍትህ፣ የዴሞክራሲ፣ የእኩልነት እና የመልካም አስተዳደር እጦት ብሎም በህዝቦች የሥልጣን ባለቤትነት ላይ ለተጋረጠው ችግር የሚያመጣው መፍትሔ የለም። በሌላ በኩል ነፃና ፍትሃዊ የመወዳደሪያ ሜዳ የሌለበት፣ የህዝብ የስልጣን ባለቤትነት ያልተረጋገጠበት የወያኔ ምርጫ ተካሄደም አልተካሄደም ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚያመጣው አንዳች ለውጥ የለም። ተነጠፈስ ቀረ፥ የአውራ ዶሮ ቁርበት እንዲሉ።

ይልቁን ወያኔ/ኢህአዴግን በሚገባው የኃይል አሰላለፍ ተደራጅቶ አንድም ወደ ድርድር ማምጣት አልያም ከኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ የሚወገድበትን መንገድ መከተል ከላይ ላነሳናቸው ችግሮች መፍትሔ ሊያመጣ ይችላል። ቸር እንሰንብት!!!
ዳዊት ፋንታ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ