ወላጆችና መሪዎች
ቸሩ ላቀው
ለዚህ የተቀደሰ ተግባርና ከባድ ኃላፊነትን ለሚጠይቅ ሥልጣን መታጨት ያለባቸው የሀገር መሪዎች ማሟላት ያለባቸው መመዘኛዎች በርካቶች ቢሆኑም በኔ እይታ አንዳንዶቹን ከወላጆች ጋር እያስተያየሁ ለመጠቃቀስ እፈልጋለሁ።
- በአንደበታቸው ሳይሆን ሙሉ በሙሉ በሁለመናቸው የኢትዮጵያዊነትን ፀጋ የተጎናጸፉ መሆን አለባቸው። በኢትዮጵያዊነታቸው ኩራት የሚሰማቸው ከሆኑ ለሀገራቸው ለኢትዮጵያ በሙሉ ልባቸው ለማገልገል የተዘጋጁ ይሆናሉ።
- በንዋይ ፍቅር ያልታወሩና ከሙስና የፀዱ መሆን አለባቸው።
- በአጎት፣ በአክስት፣ በሚስት፣ በባል፣ በዘመድ አዝማድ ከውጭ ሀገራት ጋር ንኪኪ የሌላቸውና ለተላላኪነት ያልተሰለፉ መሆን አለባቸው። ባልም ሆነ ሚስት ሙሉ ኢትዮጵያውያን ተወላጆችና ዜጎች መሆን አለባቸው።
- ሕዝብን የሚያምኑና የሚያከብሩ፣ በሕዝብ የታመኑና በራሳቸው የሚተማመኑ መሆን አለባቸው።
- ሀገርንና ሕዝብ ለመሸጥ ያልተነሱ ወይም የማያስቡ፣
- ለሀገር ልማትና ዕድገት አሳቢ፣
- የአመራር ብቃት ያላቸውና ሀገራዊ ርእይ ያላቸው፣
- ከአድሎ የፀዱ መሆን አለባቸው።
ገበሬዎች ለዘሩት ሰብሎቻቸውና ለአረቧቸው እንስሶቻቸው ያስባሉ፣ ይጨነቃሉ። የተዘራውን አዝርዕት በተገቢው አርመው፣ ኮትኩተው፣ አጭደው፣ ከምረው፣ ከአዕዋፋትና አራዊት ጠብቀውና ወቅተው እጎተራቸው እስኪያስገቡ ድረስ ይለፋሉ፣ ክምራቸው በእሳት ቃጠሎ እንዳይወድምባቸው ይጠብቃሉ፣ ጎተራ ከገባ በኋላም ከዘራፊዎች ይጠብቃሉ። እንስሳት የሚያረቡና በአትክልትና ፍራፍሬ አምራችነትም የተሰማሩት እንዲሁ ድካማቸው ቀላል አይደለም። ወላጆችም ልጆች ወልደው በሚገባው ደረጃ አሳድገው ለቁምነገር እስኪበቁላቸው ድረስ የአካሎቻቸው ክፋይ ለሆኑት ልጆቻቸው ያስባሉ፣ ይጨነቃሉ። እንዳይራቡ፣ እንዳይታረዙ፣ ጤንነታቸውና ትምህርታቸው እንዳይጓደል ይለፋሉ። የኢትዮጵያ መሪዎችም ኢትዮጵያውያንን ለመምራት ሲሰለፉ ሙሉ ኢትዮጵያዊ ሆነው ለወገኖቻቸው በሙሉ ልብ የሚሠሩ መሆን አለባቸው። ወንዱም ሆነ ሴቷ ከጥንዶቻቸው ጋር በትውልድም በዜግነትም ሙሉ ኢትዮጵያውያን መሆን አለባቸው። ያ ሲሆን በኢትዮጵያዊነታቸው ኢትዮጵያውያንን ከሰሜን ድንበር እስከ ደቡብ ድንበርና ከምሥራቅ ድንበር እስከ ምዕራብ ድንበር ያሉትንና የሚኖሩትን ኢትዮጵያውያንን በጎሣ፣ በዘር፣ በብሔር ሳይከፋፍሉ ይንከባከባሉ፣ ያከብራሉ፣ በእኩልነት ዓይን ይመለከቷቸዋል፣ አድሎ አይፈጽሙም።
እነዚህ መሪዎች በሚስት ወይም በባል በኩል ከውጭ ዜጎች ጋር ጋብቻ የፈጸሙ ከሆኑ ለሀገር ደህንነት ስለማይበጅ ባይመረጡ ይመረጣል። ይበጃል ብቻ ሳይሆን ፈጽሞ መመረጥ የለባቸውም። ምክንያቱም ሁለቱም ሲሠሩ የዋሉትን ማታ በጨዋታ መልክ ሐሳብ ለሐሳብ መለዋወጣቸው ስለማይቀር የሀገር ምስጢር ሊባክን ይችላል። የውጭ ሀገራትም ሰርስሮ ለመግባት ያመቻቸዋል። ወላጆች ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያውያን ካልሆኑ የተወሰኑት ካንደኛው ወገን በመሆን ወደ ወጪው ሲያደሉ የቀሩት ደግሞ ከኢትዮጵያዊው ጋር በመሆን ወደ ሀገር መመልከት ይጀምራሉ። ስለሆነም ቤተሰቡ ለሁለት የተከፈለ ሐሳብ ላይ ይሆናል።
ከውጭ ሀገራት ጋር ንኪኪ የሚፈጥሩና ለተላላኪነት ራሳቸውን የሚያዋርዱ ግለሰቦች በሀገር ላይ ምን ያህል ችግር እንደሚፈጥሩና ለሀገር ጠንቅ ትተው እንደሚያልፉ ቀደም ባሉት ጊዜያት ከተከሰቱት ምሳሌ እንዲሆነን አንድ የተፈጸመ ክስተት እንመልከት።
የሰባተኛው ቀን አክባሪ የአሜሪካ የሃይማኖት ድርጅት ነው። ቀደም ሲል እግራቸውን ተክለው የነበረው በአሥመራ ከተማ ነበር። ከዚያም ወደ መሀል ኢትዮጵያም ሰርገው በመግባትና አንዳንድ ሆድ-አደር ሰዎችን መልምለው ሁለተኛ ጥምቀት አጥምቀው አገልጋዮቻቸው አደረጓቸው። የዚህ ሃይማኖት ተከታይ ነን ባዮችና ከባሕር ማዶ የመጡ ፖለቲኮ-ሃይማኖት ሰባኪዎች የያዙት መጽሐፍ ቅዱስ የማይፈቅደውን የሐሰት ተግባር በመፈጸም የማጭበርበር ተግባር ፈጽመዋል። ይኸውም ቀደም ሲል ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ የቤተ ክርስቲያ አለቃ ለነበሩት ለአለቃ ዘካሪያስ በተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ እንዲያስተምሩ የተሰጣቸውን ማስረጃ አሰርቀው በመውሰድ የአለቃ ዘካሪያስ ተከታዮችና አስተማሪዎች ነን እያሉ በመዞር የራሳቸውን ስብከት ቀጠሉ። መንግሥትም ምስጢሩን ባለማወቁ ደብረ ታቦር ቦታ ሰጥቶአቸው ሠፈራቸው አደረጉ።
ትምህርት ቤትና የሕክምና መስጫ ክሊኒክም ከፈቱ። ይኸ ሁሉ ሲሆን ሕዝቡ የሚያውቃቸው የአለቃ ዘካሪያስ ተከታዮች ናቸው ብሎ እንጂ ሰርጎ ገብ ሃይማኖት ማስተማራቸውን አያውቁም ነበር። ትምህርት ቤት መክፈታቸውና ክሊንክ ማቋቋማቸውም የአካባቢው ሕዝብ በትምህርት ታንጾ እንዲወጣ፣ ጤንነቱም እንዲጠበቅ አስበውና ተጨንቀው ሳይሆን ከሕዝቡ ጋር የመገናኛ ድልድይ እንዲሆናቸው ነው። ሕዝቡ ለሕክምና ሲሔድ ይሰብኩታል። ልጆቹ አስኳላቸው ገብተው ሲማሩ ይሰብኩአቸዋል፣ ዳግም ጥምቀት ይጠምቁአቸዋል። ዛሬም ወያኔ ይኸንኑ ፈለግ በመከተል የፖለቲካ ስብከቱን ይግታቸዋል። ቀበሌ ስንዴ፣ ስኳር፣ ጤፍ፣ ወዘተ መጥቷልና ኑ ውሰዱ ብሎ ይለፍፋል። ጭቁኖቹ ለመግዛት ሲሔዱ ኢሕአዴግን ለመምረጥ ፈቃደኛ ለሆኑት ብቻ ነው እያለ የመምረጫ ካርድ እንዲወስዱ በተዘዋዋሪ መንገድ ያስገድዳቸዋል። ሌሎችንም የቡና መጠጫ እያለ ገንዘብ ይሰጣቸውና የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ ይገፋፋቸዋል። የሀገር ተወላጆች ነን ብለው የማጭበርበርና የማፊያ ሥራ መሥራታቸው ነው።
ቀጥሎም የአድቬንቲስት ሰባኪያኑ በተዘዋዋሪ መንገድ ባገኙት የመንግሥት ድጋፍ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በአቃቂና በሻሸመኔ ኩየራ በተባለ ቦታ ትምህርት ቤቶችና የሕክምና መስጫ ክሊኒኮች አቋቋሙ። የመንግሥት ድጋፍ የተገኘበትና እንቅስቃሴአቸው እንዲሳካ የተደረገውም በቤተ መንግሥት አካባቢ ከሚሠሩ ባለሥልጣናት መካከል አንዳንዶቹ ልጆቻቸው በነዚህ አድቬንቲስት ሚሲዮን ትምህርት ቤቶች የተማሩና እምነቱን የተቀበሉ ስለነበሩ በነዚህ ልጆች ወላጆች አማካይነት በንጉሡም ዘንድ ተቃውሞ አልደረሰባቸውም። ሌላው ደግሞ ኃይለ ሥላሴ በመንግሥት ስም ተቃውሞ እንዳያነሱ ግፊት ካደረጉት መካከል የግላቸው ወጥ ቤት ሆና ስታገለግላቸው በኖረችው ወይዘሮ ሐንሰን ነበር። ሐንሰን በአዲስ አበባ የአድቬንቲስቶቹ ትምህርት ቤት ሥራ መሪ የአቶ ሐንሰን ባለቤት የነበረች ናት። ሴትዮዋን እቴጌ መነን በጥርጣሬ ዓይን ይመለከቱአቸው እንደነበረም ከውስጥ በተገኘ መረጃ ተገልጿል።
ከሌሎች ተባባሪዎች መካከልም የንጉሡ እንደራሴና አማካሪያቸው የነበሩትና የፀረ-ኢትዮጵያዊነትና የፈረንጅ አምላኪነት ዝንባሌ ይታይባቸው የነበሩት ፊታውራሪ ገብረ ሕይወት ወልደ ሐዋሪያት አንዱ ናቸው። ራስ አሥራተ ካሣ ሌላው ሲሆኑ እርሳቸውም በአስተዳደጋቸውና በአኗኗራቸው፣ እንዲሁም በአስተሳሰባቸውም ሳይቀር የእንግሊዛዊነትን ጠባይ በገሃድ እያሳዩ በዘውዱ ተቀናቃኝነታቸውም ለርዕሰ ብሔርነቱ ሥልጣን ራሳቸውን ከማዘጋጀታቸው ጋር ወደ መጨረሻው ዘመን የቤተ ሕዝቡ (ፓርላማ) የበላይ ተጠሪ የነበሩት አስተዋፅኦ እንደነበራቸው ተጠቁሟል። ጸሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድም ፈረንሣዊት ሚስት አግብተው እንደ ኢትዮጵያዊ ሳይሆን እንደ ፈረንሳዊ ኑሮ ይኖሩ የነበሩ ሲሆን በሚስትዮዋ በኩል የምስጢር መባከን እንደሚኖር እሙን ነበር ተብሎ ኢትዮጵያ የዓለሙ መፋረጃ በተባለ መጽሐፍ ታትቷል (ንቡረ ዕድ ኤርምያስ ከበደ ወልደ ኢየሱስ፣ 1993፣ 300-306)።
መሪዎች ከአንገት በላይ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ብቻ ኢትዮጵያውያን ነን ማለት ሳይሆን በሙሉ ልባቸው መሆን እንዳለባቸው ከላይ ተጠቅሷል። ኢትዮጵያዊነት ሲባልም ለአንድ ጎሣ፣ ዘር፣ ብሔር የተሰጠ ልዩ ፀጋ ሳይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚኖሩ ዜጎቿ ሁሉ የተሰጠ ነው። ትግሬዎች፣ ዐማሮች፣ ኦሮሞዎች፣ አፋሮች፣ ሶማሌዎች፣ ወላይታዎች፣ አኙዋኮች፣ ወዘተ፣ ለመንግሥት ሥራም ሆነ ለተለያዩ ጉዳዮቻቸው ከኢትዮጵያ ወደ ሌሎች ሀገሮች ሲሔዱ የይለፍ ወረቀት (ፓስፖርት) መያዝ የግድ ነው። በይለፍ ወረቀቱ ላይ ዜግነት ሲጻፍ ኢትዮጵያዊ ወይም ኢትዮጵያዊት ተብሎ በኢትዮጵያዊነታቸው በኢትዮጵያ ስም ነው። ተቀባይ ሀገሮችም ከኢትዮጵያ የመጡ የኢትዮጵያ ዜጎች መሆናቸውን ነው የሚያውቀውና የሚያረጋግጠው፣ የሚያስተናግዳቸውም። ያ ሲባል ትግሬነታቸውን፣ ዐማራነታቸውን፣ ኦሮሞነታቸውን፣ ሱርማነታቸውን፣ ሶማሌነታቸውን፣ አፋርነታቸውን፣ ወላይታነታቸውን፣ አኙዋክነታቸውን፣ የምነታቸውን፣ ከፍቾነታቸውን፣ ጉራጌነታቸውን፣ ደራሼነታቸውን፣ አገውነታቸውን፣ ወዘተ ተነጠቁ ማለት አይደለም።
አንድ ግለሰብ ማዕድ ላይ ቀርቦ በቂ ምግብ ቀርቦለት እየተመገበ በሌብነት በሽታ የተለከፈ ካልሆነ በስተቀር ወደ ጓዳ ገብቶ የሚሰርቅበት ምክንያት የለውም። የዚህ ዓይነት በሽታ ካለበት ሠራተኛ ከሆነ የመሥሪያ ቤቱን ካዝና እየገለበጠ ይስረቅ፣ ሥራ አጥ ከሆነም ቤት ሰብሮ ገብቶ ይስረቅ፣ ጉድጓድ ሰርስሮ ገብቶ ይስረቅ፣ ማጅራት እየመታ ይቀማ፣ ኪስ ያውልቅ እንጂ እንኳን ለመሪነት ለየትኛውም የሥራ ቦታ ሊታጭ፣ ሊመረጥና ሊሰማራ አይገባም። ወላጆች ከልጆቻቸው አይሰርቁም። የመንግሥት ሥልጣን ይዞ ሀገር እመራለሁ የሚልም ከሚያስተዳድረው ሕዝብና ከሚመራው ሀገር መስረቅ የለበትም። የሚሰርቁትን መከላከል አለበት እንጂ። ወላጆች የቤተሰቡን ሀብት ከዘራፊዎች ይጠብቃሉ፣ ይከላከላሉ እንጂ እየሰረቁ አይሸጡም። እንዲሰረቅም አይተባበሩም። መሪዎችም እንዲሁ።
ወላጆች በአቅማቸው ያፈሩትን ሀብት ጠብቀውና ተንከባክበው ለልጆቻቸው እንዲሆን ያቆያሉ እንጂ አይሸጡባቸውም። ከሌሎች ጋርም ተባብረውና ተመሳጥረው አያስወስዱም። መሪዎችም የሀገራቸውን ሀብት ከዘራፊና አባካኝ ይጠብቃሉ፣ ያስጠብቃሉ እንጂ ከዘራፊዎች ጋር ተመሳጥረው የጥቅሙ ተካፋይ በመሆን አያስዘርፉም።
ወላጆች በራሳቸው ይተማመናሉ። ለልጆቻቸውም ይኸንኑ ያስተላልፋሉ። ልጆቻቸውን አይፈሩም። ያከብራሉ፣ ይከበራሉ። ልጆቻቸው እያሉ ማንም ኃይል መጥቶ አይተናኮላቸውም። ጠባቂዎቻቸው እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ ልጆቻቸው ናቸው። የመንግሥት መሪዎችም በራሳቸው የሚተማመኑና ሕዝባቸውን የሚያምኑ ከሆኑ የሌላ ኃይል ጠባቂ አያስፈልጋቸውም፣ የሚያከብሩትና የሚተማመኑበት ሕዝብ ይጠብቃቸዋልና።
ወላጆች ልጆቻቸውን ለክፉ ነገር አይዳርጉም። ለጥቅም አሳልፈው አይሰጡም፣ አይሸጡም፣ አይለውጡም። መሪዎችም የዚህ ተግባር ፈጻሚ መሆን አለባቸው። የአንድ ሀገር ሀብቷ ሕዝቧ ነው። ሕዝብ ከሌለ ሌላው ሀብት ዋጋ የለውም። የከበሩ ድንጋዮች ቢኖሩ ሕዝብ ከሌለ ድንጋይ እንደሆኑ ይቀራሉ። ሕዝብ ካለ ግን ማዕድንነታቸው ጠርቶ ይወጣል። ሕዝብ ተጠቃሚ ይሆናል።
ወላጆች በወለዷቸው ልጆቻቸው ላይ የክህደት ተግባር አይፈጽሙም። ስለሆነም ልጆቻቸውን ምንም ከባድ ችግር እንኳ ቢያጋጥማቸው ልጆቻችን አይደሉም፣ አናውቃቸውም፣ አያውቁንም፣ አንተዋወቅም ብለው አይክዷቸውም። መሪዎችም የሚመሩትን ሀገር ሕዝብ አናውቃቸውም ብለው የክህደት ተግባር አይፈጽሙም። አሳልፈው ለሌላ ወገን አይሰጡም። (መሸጥ የለመደ እናቱን ያስማማል።) እንደተባለው ገንዘብ ለማግኘት ሲባል ብቻ ሕዝብ አይሸጥም። ትልቅና ከባድ ወንጀል ነው። እዚህ ተቀምጣችሁ አትነዝንዙን ተብለው ከሀገር እንዲባረሩ አይደረጉም። የተሰደዱት እንኳ ቢኖሩ እንዲመለሱ ይደረጋል እንጂ ዜጎች እንዲሰደዱ አይባረሩም።
ወላጆች ከልጆቻቸው መካከል እየለዩ የማቅረብና የማራቅ አድሎ አያደርጉባቸውም። መሪዎችም በሀገር ውስጥ ያሉትን የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍል እየከፋፈሉ ለይተው ወርቅነህ፣ ፋንዲያ ነህ፣ ዝንብ ነህ፣ ተረፈ - ሕዝብ ነህ፣ ኮካኮላ ነህ፣ እንደ ጣሳ ቂጣ ተጋግረው የተሠሩ ናቸው፣ የተከዜ እስስቶች ናቸው፣ ወዘተ ብለው አይከፋፍሉም። ሁሉንም ሕዝብ በእኩል ዓይን ማየትና ማስተናገድ አለባቸው። ሁሉም ሕዝብ በኢትዮጵያዊ ዜግነቱ ያልተሸራረፈ እኩል መብት አለው።
ወላጆች እንደ አቅማቸው ተጣጥረው ልጆቻቸውን በማስተማርና በመንከባከብ አሳድገው ለቁም ነገር እንዲበቁ ይለፋሉ። ራሳቸውን ችለው የሚኖሩበትንም ሁኔታዎች ይፈጥሩላቸዋል። መሪዎችም ሀገር ለምታና በልጽጋ፣ ሕዝቡ እንዲሻሻል ለሀገር ልማትና ዕድገት ሌት ተቀን ይለፋሉ። ሕዝቡን በየደረጃው በማስተማርና በመቀስቀስ፣ በማስተባበር ለሥራ ያነቃቃሉ። ከሕዝብ ጋርም ተባብረው ሠርተው ያሠራሉ። ከ1880 እስከ 1883 ዓ.ም. ተከስቶ በነበረው ታላቁ ረሃብና በሽታ ብዙ ሕዝብና እንስሳትም አልቀው ነበር። ወቅቱ ሲያልፍ ገበሬው የሚያርስበት በሬ አጣ። ዓፄ ምኒልክ የዘየዱት ዘዴ በዶማ መቆፈር ስለነበር ራሳቸው በዶማ እየቆፈሩ መኳንንቶቻቸውም ሠርተው እንዲያሠሩ አድርገው በቂ ምርት ተገኝቶ ሕዝቡ ሊያገግም ችሎ ነበር። ስለዚህ መሪዎች ሠርተው የሚያሠሩ አርኣያ መሆን አለባቸው። በዚህም የአሠራር ብቃታቸውና ሀገራዊ ርእይ ያላቸው መሆናቸው ይታወቃል። ይመሰገኑበታል እንጂ አይዋረዱበትም። ዓፄ ምኒልክ ሠርተው በማሠራታቸውና አብረው ከሕዝባቸው ጋር ይበሉ ስለነበር "እምዬ ምኒልክ" ተሰኙ እንጂ አልተሰደቡም፣ አልተረገሙም፣ አልተዋረዱም።
ኢትዮጵያን ለማዳን ሁሉም የድርሻውን ይወጣ!
ቸሩ ነኝ፣ ቸር ይግጠመን!
ቸሩ ላቀው
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



