ቸሩ ላቀው

በመንግሥት አመራር ላይ የተቀመጡ ቡድኖችና በኃይማኖት አመራር ላይም የተቀመጡ የኃይማኖት መሪዎች በየፊናቸው የሕዝብን አደራ በኃላፊነት ተቀብለው በሀገሪቱ ባለው ሕገ መንግሥትና በኃይማኖቱ ሕግ መሠረት በሐቅና ለሕቅ ብለው ምለውና ተገዝተው ሕዝብን ለማገልገል የተቀመጡ ናቸው።

 

እንደ አንዳንድ የዋሃን አባባልና እምነት ሁለቱም ቡድኖች ከፈጣሪ ተቀብተው የተላኩ ሳይሆን በሚያገለግሏቸው ዜጎች ተመርጠው የተቀመጡ እንደኛው ሰዎች ናቸው።

 

እነዚህ የሕዝብ ኃላፊነት የተሸከሙ ሁለት አካላት በየፊናቸው ከታች እስከ በላይ አካላት ድረስ መዋቅራቸውን ዘርግተው በመንቀሳቀስ ተግባሮቻቸውን ይተገብራሉ። ተግባሮቻቸውም ይለያዩ እንጂ ተከታዮቻቸው ሁለቱም መዋቅሮች ውስጥ አሉ። አማኞቹ በሀገራቸው መንግሥት ሥር የሚተዳደሩ ስለሆኑ የሀገራቸውን ሕገ መንግሥት አክብረው ይተዳደራሉ፣ ይኖራሉ። መንግሥትም የእምነታቸውን ተግባር ለነርሱ ትቶ በሕገ መንግሥቱ ተከልለው የሚኖሩ መሆናቸውን ያረጋግጣል። ይህ ሕዝቡ በሁለቱም ውስጥ መኖሩና ቢንቀሳቀስም በመንግሥታዊ አስተዳደር ውስጥ የሚካሔደው እንቅስቃሴና በእምነቱ በኩል በኃይማኖት ዘንድ የሚደረገው እንቅስቃሴ ይለያያል።

 

ሰዎች ኑሮአቸውን በትክክለኛው መንገድና የተረጋጋ አዕምሮአቸውን በተስተካከለ መንገድ ለመምራት እንዲያመቻቸውና እንዲያስችላቸው በየቀኑ 8 ሰዓት መሥራት፣ 8 ሰዓት ማረፍና 8 ሰዓት መተኛት አለባቸው። በመሆኑም ግለሰቦች መንግሥት የዜጎቹ ኑሮ እንዳይናጋ ወይም እንዳይዛባ በየቀኑ 8 ሰዓት መሥራታቸውን ያረጋግጣል። ከዚያ ውጭ ያለው ጊዜ የግለሰቦቹ ስለሆኑ ለመዝናናት፣ ለመጸለይ፣ ወዘተ የነርሱ ጊዜ ነው። መንግሥት ሊቆጣጠራቸው አይችልም፣ ተገቢም አይደለም። መንግሥት ለሀገር ደህንነትና ለዜጎቹም ጥበቃ ስለሚያደርግ ወንጀል እንዳይሠራ ይጠብቃል። ግለሰቦችም በዜግነታቸው ባላቸው ኃላፊነት መሠረት ሕገ መንግሥታዊ መብቶቻቸውን ከማስከበር በተጨማሪ የሀራቸውን ደህንነትም የመጠበቅ ኃላፊነት ስለአለባቸው ከወንጀል የፀዱና ወንጀልም ሲሠራ ሲያዩ  ለሕግ አስከባሪዎች የማመልከትና የማስታወቅ ግዴታ አለባቸው። ይህ መንግሥትና ሕዝብ የሚያደርጉት መተባበር ለሀገር ሰላምና ደህንነት ዋስትና ናቸው። ልማትና ዕድገትን ያስከትላሉ። ከዚህ ውጭ ግን ያለመተማመን ከተፈጠረ በኃይማኖትም ሆነ በሌሎች መስኮች ችግሮች መከሰታቸው አይቀርም።

 

ባሁኑ ጊዜ በርካታ የእምነት ተከታዮች የኃይማኖት መሪዎች እምነቱ ከሚያዘው ውጭ በመውጣት በተቃራኒው ለፖለቲካ መጠቀሚያ ሆነዋል እያሉ ናቸው። ከሚያነሷቸው ነጥቦችም መካከል ለሀብታሞችና ለጦርነት መጠቀሚያ መሆናቸው፣ ለበለፀጉ ሀገሮች ጥቅም ማስከበሪያ፣ ማስጠበቂያና የበላይነት መገለጫ አፈቀላጤ መሆናቸውና የመሳሰሉትን ይዘረዝራሉ።

 

ኃይማኖትና ፖለቲካ አንድ ላይ መጓዝ አይችሉም። የሁለቱም አካሔድ ይለያያል። ኃይማኖት የሰው ልጅ ክቡር ስለሆነ መታሰር፣ መገረፍ፣ መሰቃየት፣ መገደል የለበትም፣ በአጠቃላይም ሰብአዊ መብቱ መጣስ የለበትም ብሎ የሰው ልጆች ተፋቅረው፣ ተዋደውና እጅ ለእጅ ተያይዘው በመጓዝ አብረው በሰላምና በፍቅር መኖር አለባቸው ብሎ ያምናል፣ ያስተምራልም። ፖለቲከኞች ደግሞ ለሥልጣናቸው ስለሚጓጉ ቀና ብሎ የተመለከታቸውንና የተቃውሞ ሐሳብ ያቀረበባቸውን ሁሉ ያስራሉ፣ ይገርፋሉ፣ ያሰቃያሉ፣ ይገድላሉ። በአጠቃላይም ሰብአዊ መብትን የሚገፍና የሚረግጥ ተቋም ነው። ስለዚህ የአመለካከትና የአካሔድ መንገዳቸው የተለያየ ስለሆነ አንድ ላይ ባንድ መስመር ላይ ሆነው መጓዝ አይችሉም። ቢሆንም ግን አንዱ በሌላው ላይ ተፅዕኖ ሳያደርግ በየፊናቸው መንቀሳቀስ አለባቸው። ሁለቱም በየፊናቸው ይንቀሳቀሱ ሲባል ተኳርፈው እንደ ጠላት እየተያዩ ድርጊቶቻቸውን ያከናውናሉ ማለት ሳይሆን የሚያገናኛቸው ላይ ይወያያሉ፣ በሰላም አብረው ይጓዛሉ። ግን አንዱ በሌላው ላይ ተፅዕኖ የማድረግ ስሜት ማሳየት የለበትም። ፖለቲከኛው ሕዝቡ ለርሱ ለጥ ፀጥ ብሎ እንዲገዛለት፣ እንዲታዘዝለትና እንዲሰግድለት አስገድድልኝ፣ ገዝትልኝና የመሳሰሉትን መጠየቅና በጉልበቱም አስደርግ ብሎ ማዘዝ የለበትም። የኃይማኖት መሪውም ሕዝቡ በሙሉ የርሱን እምነት ተቀብሎ  እንዲከተለው መንግሥት እንዲያዝለት፣ እምቢ ካለ እንዲቀጣለት የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ማቅረብ የለበትም። ነገር ግን የእምነቱ ተከታዮች ከመንግሥት ጋር የሚያገናኛቸው ብዙ ነገሮች ስለአሉና መንግሥትም የሕዝቡ አገልጋይ ስለሆነ በሰላምና በፍቅር እጅ ለእጅ ተያይዘው ይጓዛሉ።

 

ወያኔ ሕገ ወጥ ስለሆነ በእምነትም ጣልቃ ገብቶ ሕገ ወጥ ተግባር መፈጸም የለበትም። መጀመሪያ ራሱን አርሞ ወደ ኢትዮጵያዊነት ይመለስ። ሁሉንም አጥፍቼ ልጥፋ የሚለውን መፈክሩን ያንሳ። የርሱ ተግባር የመንግሥትን ተግባራት በአግባቡ መፈጸም እንጂ በማያገባው ገብቶ እርሱ የሚሰጣቸውን እምነት እንዲቀበሉ፣ እርሱ የሚሰጣቸውን ወይም የሚሾምላቸውን የኃይማኖት መሪዎች ተቀበሉ ብሎ ጣልቃ መግባት የለበትም። የኃይማኖት ሥራ የመንግሥት ሥራ አይደለም።

 

እምነት የያንዳንዱ ዜጋ የግሉ አመለካከት ስለሆነ ሊያምን፣ ላያምን፣ በዛፍ፣ በውሃ፣ በእንስሳት ሊያመልክ፣ በምንም ላያመልክ መብቱ ነው። ያ ስለሆነ ኢትዮጵያዊ ዜጋ አይደለም ማለት አይደለም። ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ዜጎቿ ሀገር ስለሆነች ግለሰቦችም ሆኑ መንግሥት ሊከለክሏቸው አይችሉም። ሁሉም ዜጋ ለሀገሩ ተቆርቋሪ ስለሚሆንና ስለሆነም ሀገሩን ዘብ ቆሞ ይጠብቃል። አይሸጥም፣ አያሸጥም፣ አይዘርፍም፣ አያዘርፍም። መንግሥትም እነዚሁኑ ዜጎቹን በማስተባበር፣ በሰላምና በፍቅር አብረው እንዲኖሩ በማድረግ ሀገሩን ያስጠብቃል። ከዘራፊዎች፣ ከቀማኞችና ከሻጮች ይጠብቃል፣ ያስጠብቃል። ዜጎች አብረው ካልሠሩ አንድ ስንዝር ብቻውን ጠመንጃ ስለአነገተ ብቻ መጓዝና ደህንነቱን መጠበቅ እንደማይችል ሕዝቡ ትምህርት እየሰጠው ቢሆንም በዕብሪት የተወጠረ ስለሆነ ሊገባው አልቻለም። ንገረው፣ ምከረው እምቢ ካለ መከራ ይምከረው ሆነና የመከራዋን ቀን እየተጠባበቀ ነው።  

 

ቸሩ ነኝ በቸር እንገናኝ! 

 


ቸሩ ላቀው

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!