ምነው ጠላቶች በዙብን?
ቸሩ ላቀው
እኛ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያዊነታችንና አንድነታችን ኩራታችንና ክብራችን ነው። እንኮራባቸዋለን፣ እንከበርባቸዋለን፣ እናከብራቸዋለን። ስንከበርበትና ስንኮራበትም ኖረናል። አንድ የአበባ ማስቀመጫ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በአበባው ማስቀመጫ ውስጥ የተለያዩ ቀለማት ያሉዋቸው አበቦች ይቀመጣሉ። የተቀመጡት አበቦች ለተመልካቾቻቸው ደስታን ይሰጣሉ። አዕምሮአቸውን ያረካሉ።
ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ተሰባስበው፣ ተከባብረውና ተፋቅረው መኖር ኩራታችን፣ ፀጋችንና ድምቀታችን ነው። የአብሮነት ደስታችንን እያዳበረ የመጣ ሂደት ነው። አበቦቹ በአንድ ላይ በአበባው ማስቀመጫ ውስጥ ሲቀመጡ ቦታ ጠበበን፣ ቀለምህ አላማረኝም፣ ቁመትህ ቀውላላ ወይም አጭር ስለሆነ አንመጣጠንም ተባብለው አይገፋፉም፣ አይነታረኩም፣ አይጣሉም። አብረው ተስማምተው ተቀምጠው በድምቀታቸው ተመልካቾቻቸውን ያስደስታሉ፣ ያረካሉ። የኢትዮጵያ ሕዝብም በጎሣ፣ በዘር፣ በቀለም፣ በፆታ፣ በዕድሜ፣ በክልል፣ በመንደር ሳይከፋፈል አብሮ በፍቅርና በሰላም የኖረ ነው። ይህ አብሮነታችን ለምን ጥላሸት አጠላባቸው?
ኢትዮጵያዊነታችንና አንድነታችን እንደ አጥንትና ሥጋ የተያያዙ ናቸው። አንዱ ሲነካ ሌላውም ይነካል። ሥጋ ያለ አጥንት እንደማይቆም ሁሉ አጥንትም ሥጋ ካልለበሰ ሊኖር አይችልም። አፅም ብቻ ሆኖ ይቀራል። አፅም በየገጹ እንደሚባለው። ወዳጅ መሳይ ጠላቶቻችንና የለየላቸው ጠላቶቻችን ይኸንኑ ኢትዮጵያዊነታችንንና አንድነታችንን ሊያዩ አይፈልጉም። ምክንያቱን ገልጸው ባይነግሩንም በግልፅም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገዶች ግን ከመቦርቦርና ለማፈራረስ ከመጣር ቦዝነው አያውቁም። ለምን?
እንስሳት ሜዳ ላይ ሲተኙ በቡድን በቡድን ሆነው ፊታቸውን ወደ አራቱም ማዕዘናት በማዞር ነው። በማንነታቸውም አንበሶች ለብቻቸው፣ ነብሮች ለብቻቸው፣ ጅቦች ለብቻቸው፣ ከብቶች ለብቻቸው፣ በጎች፣ ፍየሎች፣ ወዘተ ለየብቻቸው ወገናቸውን ለይተው ሲተኙ በአንድነታቸው ደግሞ ጠላቶቻቸውን ለመከላከል እንዲያመቻቸው በቡድን በቡድን ሆነው ለጥበቃው እንዲያመቻቸው ዘዴ ቀይሰው እየተጠባበቁ ይተኛሉ። ኢትዮጵያዊነት የጋራ መለያችን ሲሆን አንድነታችንም የጋራ መከላከያችን ነው። ሁለቱም ባንድ ላይ የተዋኸዱ ስለሆኑ እኛነታችንን ጠብቀው ያቆዩና የሚቆዩ ናቸው።
በኢትዮጵያዊነታችንና (በኛነታችን) በአንድነታችን (በትብብራችን) ፀንተን ከኖርን በቀላሉ ለጥቃት እንደማንጋለጥና እንደማንበገር ስለተገነዘቡ ይኸንን በአለት ድንጋይ ላይ የተገነባ ትስስራችንን ማፍረስ አለብን ብለው በመነሳት ከብዙ ዓመታት በፊት ጀምሮ ሲጥሩ የነበሩ ናቸው። ጦርነት በመጫርና እምነት በማስተማር ሰበብ እየገቡ እየሰረሰሩን ነው። የተፈጥሮ ሀብታችንን ካልወሰድን ብለው ጦር እየሰበቁብን ነው። የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት በቅርቡ ያሰማው ዛቻ የዚሁ ምስክር ነው። ይኸ የዓረቦች እየተቧደኑ መፎከር ለብዙ ዓመታት የቆየ ነው። ራሳቸው መጥተው ውጊያ መክፈትና ሀገሪቷን በቁጥጥራቸው ሥር ማድረጉ በተለያዩ ጊዜያት ሞክረው ሲሳናቸውና ተዋርደውም ሲባረሩ የሀገሬውን ኃይል ሻዕቢያንና ወያኔን አሰልጥነውና አስታጥቀው ከሌሎች ተባባሪዎቻቸው ጋር በመሆን አሰማርተው የጥፋት መንገዱን ተያይዘውታል። ወያኔዎች ግን ኢትዮጵያን አጥፍተው ጨረቃ ላይ ለመኖር ቦታ ተኮናትረው ይሆን?
የሙስሊም እምነት ያስተሳሰራቸው የዓረብ ሀገሮች ኢትዮጵያን አካለው ያሉ ስለሆኑ በሙስሊሙ ሀገሮች መካከል እንደ ደሴት እየታየች መቀመጥ የለባትም ብለው ወደ ሙስሊሙ እምነት ለመቀየር ትግል ከጀመሩ ብዙ ዓመታትን አስቆጥረዋል። ከነርሱም በተጨማሪ በርከትከት ያሉ ዘመን አፈራሽ የእምነት ዓይነቶች የክርስትና እምነት የመጀመሪያ የሆነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጠፍቶ በአዳዲሶቹ ዘመናዊ ኃይማኖቶች መተካት አለበት ብለው ዘመቻ የሚያካሄዱም በርካቶች ናቸው። እነዚህ መጤ ኃይማኖት አስፋፊዎችና ፖለቲኮ-ኃይማኖት ሰባኪዎች በተዘዋዋሪ መንገዶችና በግልፅም እየገቡ በሕዝቡ መካከል ልዩነት እየፈጠሩ የእርስ በርስ ፍጥጫ እንዲፈጠር አድርገዋል።
እያደረጉም ናቸው። የኢትዮጵያ ሕዝብ በእምነቱ የተሳሰረና የሚያስተባብረውም ስለሆነ በእምነቱ ላይ የመጣበትን በሀገሩ ላይ እንደመጡበት፣ በሀገሩ ላይ የመጡበትም በእምነቱ ላይ እንደመጡበት ስለሚቆጥር ሀገሩንና ኃይማኖቱን አጥብቆ ይጠብቃል። በዚሁ የኃይማኖታቸው በጥናት መጠበቅ ምክንያት ኃይማኖታቸውን ከኃይማኖቶች ውዝግብና ከፖለቲካ ቀውሶች ጠብቀው የቆዩ ሲሆን ባሁኑ ጊዜ ግን የሀሩን ሰርዶ ባገሩ በሬ ሆኖ የወያኔ መሪዎች ማፍረስ አለብን ብለው እየፎከሩ ናቸው። ከጠላትም በላይ የእናት ጡት ነካሾቹ ወያኔዎች የወላጆቻቸውን ኃይማኖት ለማጥፋት ሌትና ቀን ሲያሴሩ ዘመነኞቹ ኃይማኖቶች አልተነኩም። እንዲያውም ዳግም ማጥመቁን በስፋት እንዲያከናውኑ በሩ ወለል ተደርጎ ተከፍቶላቸዋል። ይኸው ኃይማኖታችንን አፅንተን መያዛችንና ሌሎች በራዦችን ለማስተናገድ ፈቃደኞች ባለመሆናችን ጠላቶች እንዲነሱብን አድርጓል።
በዓለም ላይ ያሉ የክርስትና እምነት ተከታዮች እውነት የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮችና በክርስትና ኃይማኖት እናምናለን ካሉ ቀጥተኛው የእምነቱ ባለቤት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ነው። ሌሎቹ በኋላ የተመሠረቱና አፈንጋጮችም ናቸው። ይህ መሆኑ እየታወቀ የነርሱ ብቻ መሆን አለበት በሚልና ከኃይማኖቱ ጋር የማይገናኝ አካሄድ እያከሄዱ ከመሆኑም በላይ ፖለቲካውን ስለያዙ ኃይማኖትም የነርሱ እንጂ ሌሎቹ ወደ ገነት አያስገቡም ብለው ያታልላሉ።
ፋሽስት ኢጣሊያ በ1928 ዓ. ም. በሰሜን ኢትዮጵያ በኩል ገብቶ ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሩ ሥር ለማድረግ ወደ መሀል ሀገር ሲገሰግስ የኢትዮጵያን መሬቷን እንጂ ኢትዮጵያውያንን እንደማይፈልግ በግልፅ አስረግጦ ተናግሮ ነበር። የቻለውን ያህል ሕዝቦቿን ጠራርጎ ጨርሶ ሰው አልባ ስትሆን መሬቷን በቁጥጥሩ ሥር አድርጎ የኢጣሊያ ገበሬዎችን አምጥቶ ለማስፈር ዕቅድ ነድፎ ይዞ ነበር። ወያኔም ልክ እንደ ኢጣሊያው የኢትዮጵያን ሕዝብ ፈጅቶ የትግራይ ተወላጆችን ለማስፈር ባቀደው መሠረት በተግባር እያሳየ ነው። በጎንደር፣ በወሎና በአፋር ማስፈሩን ተያይዞታል። የተቸገረው ገድሎ መጨረሱ ላይ ነው።
ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለመያዝ ባቀደውመሠረት ያለመውን ለፍጻሜ ለማድረስ ሦስት ነገሮች ካልተወገዱ እንቅፋት እንደሚፈጥሩበት ወይም እንደሚያጋጥመው ፈርቶ ነበር። ሦስቱ እንቅፋቶች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ዐማራና ዘውድ ነበሩ። በዚያን ጊዜ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ የነበረና ለእምነቱ ቀናዒ ስለነበረ ኃይማኖቱን ሲነኩበት ተጠራርቶ እንደሚነሳ ስለሚያውቁና የቆየም ታሪክ ስለአለ ስጋት ነበረባቸው። ዓፄ ሱሲኒዮስ የካቶሊክ እምነት ሲቀበሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን ከተለያዩ አካባቢዎች ከአንድ ወር በላይ በእግር ጉዞ አድርገው ንጉሡን በማውገዝ ዐዋጁን እንዲሽር አስደርገው ነበር። የሕዝብ ቁጣ ተቀብሎ ዐዋጁን ማንሳቱ በዚያን ጊዜ የነበረው የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ምን ያህል ጠንካራ እንደነበረ ያስገነዝበናል። ኢጣሊያኖች የዚህም ቁጭት ነበረባቸው። ወያኔም በተግባሩ የኢጣሊያው ፋሽስት ውላጅ በመሆኑ ተማሪዎቹ ከመምህራኑ በላይ በመሆን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ኃይማኖትንና ዐማራውን አከርካሪአቸውን መትተናል ብሎ በመፎከር ላይ ነው። የዚህን የኃይማኖትና ዐማራውን ለማጥፋት አቅደው የተነሱት ገና ጫካ በነበሩ ጊዜ መሆኑን ገልጸውታል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፊውዳላዊ አመለካከት ያለባት ስለሆነች መመታት አለባት፣ ዐማራውም የአንድነት ተከራካሪ፣ የሀገር ተቆርቋሪ፣ የሕዝብ አለኝታነትን ተናጋሪ፣ ወዘተ ስለሆነ መጥፋት አለበት ብለው ደደቢት ላይ ወስነው የተነሱበት ዓላማቸው ነው፣ በተግባርም እየገለጹት ነው።
ወያኔ ያገሪቷን አንድነት የሚያንፀባርቁ ድርጅቶች በሙሉ እንደ ጠላት ስለአያቸውና ቤተ ክርስቲያኗ ሕብረ ብሔራዊት ስለሆነች መጥፋት ካለባቸው ድርጅቶች ውስጥ መዝግቦ ያዛቸው። ይኸንኑ ዘመቻውን ለማመቻቸት ካድሬዎቹን ካባ እያለበሰ አብያተ ክርስቲናት ውስጥ መሰግሰግ፣ በትላልቅ ገዳማት መነኮሳትንና ካህናትን ለወያኔ ፀረ ቤተ ክርስቲያን ተገዢ ማድረግና ለዘለቂታው ቤተ ክርስቲያን ለማሽመድመድና በቁጥጥሩ ሥር ለማስገባት የራሱን ካድሬዎች ሲኖዶስና ከፍተኛ አመራር ላይ ማስቀመጥ ጀመረ። ሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላና ገብረ መድኅንን ከሾመ በኋላም ከ40 በላይ ጳጳሳት ሲሾሙ አብዛኛውዎቹ የጫካ ካድሬዎች የነበሩ ናቸው።
ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል እንደሚባለው እኛ ሞፈርና ቀንበሩን ከጫካችን ቆርጠንና አዋሂደን በሬዎቻችን ጠምደን ማረስና ማምረት እንችላለን ስንል እነርሱ አትችሉም፣ አታውቁበትም ይሉና እኛ ቆርጠንና በሬዎቻችሁን ጠምደን ማረስና መጠቀም አለብን ይሉናል። እኛ ደግሞ የምንለው የኛን ለኛ ተውልን ነው። እናንተ እዚያው ሀገራችሁ ሆናችሁ ባላችሁ መሣሪያ እረሱ፣ እኛን ለማስተማር አትጨነቁ ስንላቸው እነርሱ በግድ እናስተምራችሁ እያሉ ሲያሰኛቸው ይለምኑናል፣ አለዚያም ያስፈራሩናል፣ በተዘዋዋሪ መንገዶችም ያስገድዱናል።
የእንግሊዝ መንግሥት በደረሰችባቸው ሀገሮች ሁሉ ቀብራ የምትሔደው ፈንጂ ጊዜውን እየጠበቀ የሚፈነዳ መሆኑ በተለያዩ ሀገሮ የተከሰተ ስለሆነ የብዙዎች ዕይታ ነው። የዚህ ፈንጂ አቀባበር ተንኮሏ ኢትዮጵያን በቀጥታ በቅኝ ግዛት ባትይዝም ኤርትራን ለሰላም አስከባሪነት ተብላ በተቀመጠችባቸው ጥቂት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የቀበረችው ፈንጂ ባገር በቀሉ ጠላት በትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር አማካይነት ፈንድቶ ሀገሪቷን እየለበለባት ነው። በ1940ዎቹ ዓመታት ኤርትራ ክፍለ ሀገር በነበረች ጊዜ በኤርትራ የእንግሊዝ ወታደራዊ አስተዳደር ኃላፊ የነበረው ብርጋዴር ስቲፈን http://www.ethiopianreview.com/forum/viewtopic.php?t=48294&p=278989 ተባለው ወታደራዊ መኮንን ቀይሶ የነበረው ስትራቴጂ የምዕራባውያን አፈቀላጤና ለምዕራባውያን አጎብዳጅና ተላላኪ የሚሆን መንግሥት በአፍሪካ ቀንድ እንዲመሠረት መሠረት ጥሎ ነበር። የዕቅዱ ሰለባ ያደረጋቸው ትግሬዎችን ነበር። የተጠነሰሰውን ሴራ ግን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ኢትዮጵያውያን አያውቁትም ነበር። በሴራው ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የጦሱ ሰለባ እንዲሆኑ የታጩት ሀገሮች የመን፣ ጂቡቲና ሶማሊያም ነበሩ። ሴራውን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ስለሆኑ ከተጀመረ ጀምሮ በሰለባው ቤተሰብ ፈርሷል፣ በበሽታ ተጠቅተዋል፣ በረሃብ አልቀዋል፣ በመጨቆንና በመገፋት ለስደት ተዳርገዋል፣ ወዘተ። የሴራው ዋና መነሻ የትግራይ ትግሪኝ መንግሥት እንዲመሠረት መሠረት መጣል ነበር።
ከዚህም በተጨማሪ የእንግሊዝና የኢጣሊያ መንግሥታት በመተባበር በ1941 ዓ, ም. (እአአ) በቀይ ባሕር ላይና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ጥቅማቸውን ለማስከበር እንዲያመቻቸውና እንዲቦጠቡጡ የፖለቲካ ስትራቴጂ ቀይሰው ነበር። ዘዴውም የትግራይ ፖለቲካና የሸዋ ፖለቲካ ብለው የመከፋፈል ነበር። ይኸ ማለት ትግራይንና ሸዋን ለመከፋፈልና ለማዋጋት መሆኑ ነው። ሁለቱ ወገኖች ጎራ ለይተው ሲጫረሱ አንዳቸው ካንደኛው ወገን ሆኖ ሲያማክርና ወደ ጦርነቱ ሲገፋፋ ሌለኛው ደግሞ ከሌላው ወገን ሆኖ እንደዚያው ያደርጋል። የጦር መሣሪያዎቻቸውን ይቸበችባሉ። ሰዎቹም ተላልቀው ሲዳከሙ እነርሱ የበላይነቱን ይዘው ቁጥጥሩን ይረከባሉ።
የትግራይ ፖለቲካ የምዕራባውያንን መንግሥት የሚደግፉና ታዛዥ የሆኑ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያሉትን የሚያጠቃልል ሲሆን የትግራይ ባላባቶችን በመያዝ እንዲሆን ነበር። በዚህ ዕቅድ መሠረት በመጀመሪያ መደረግ ያለበት የሸዋውን መንግሥት ማዳከምና የኤርትራን መንግሥት መስርቶ ሁለት ወይም ሦስት ቦታዎች መከፋፈል ነበር። ይኸንን ተግባራዊ ለማድረግ ስቲፈን ያቀደው በኤርትራ ውስጥ ትግሬዎችን አሰርጎ ማስገባት ነበር። በስሌቱም መሠረት እነመለስና ስብሃት ነጋ ለኤርትራ መገንጠል ከሻዕቢያ ይበልጥ ሲታገሉ የነበሩና አሁንም ኤርትራን ማንም ሊነካ አይችልም እያሉና እየተሟገቱ ናቸው። ይኸው እንቅስቃሴ ዳብሮ በ1950ዎቹ የትግራይ ትግሪኝ መንግሥት እንዲመሠረት ዕቅድ ተያዘ። ወያኔ በ1968 ዓ. ም. ሲመሠረት ታላቋ የትግራይ ሪፐብሊክ ተብሎ ተሰየመ።
ወያኔ ከጥፋት የማይመለስ አረመኔ ድርጅት በመሆኑ በቀይ ሽብር ወቅት ከፍተኛውን የማስገደል ሚና የተጫወተ እንደነበረ የሚናገሩ ሰዎች አሉ። ባገር ጥፋት ድርጊቱም ወያኔ ከታላላቅ የስለላ መረቦች ጋር ግንኙነት ስለአለው በሳቴላይት የተደገፈ መረጃ ያገኝ ነበር፣ ገንዘብና የጦር መሣሪያም በገፍ ያገኝ ነበር፣ አሁንም ያገኛል። የአፍሪካ ቀንድን እንዲያሸብር በተሰጠው ተልዕኮ መሠረት ስለተላከ ብቻ በማያገባው ገብቶ ሶማሊያን ወርሮ የንጹሃን ዜጎችን ሕይወት በከንቱ አጥፍቷል። ባሁኑ ጊዜም የትግራይ ትግሪኝ መንግሥትን እንመሰርታለን ብለው ሽርጉድ የሚሉት የወያኔ ባለሥልጣናት በሙሉ ልባቸውና ድርጊታቸው እንግሊዝ በ1940ዎቹ እንደተከለችው ዓላማ የምዕራባውያን ሎሌዎች መሆናቸውን በተጨባጭ አስመስክረዋል።
የትግራይና የሸዋ ፖለቲካ ብለው በቀየሱት መሠረት ወያኔ ሥልጣን በምዕራባውያን አዛዦቹ ከያዘ በኋላ በ1940ዎቹ የተቀየሰውን የሸዋን መንግሥት የማዳከምና የመበታተን ዘዴዎችን እየተገበሩ መሆናቸውን ባለፉት 21 የግዛት ዓመታቸው እያየን ነው።
ኢትዮጵያ የራሷን እንደማትሰጥና የሰውንም እንደማትፈልግ የሚገልጽ አባባል አለ። ይኸንኑ የቀየ ዓላማዋን ይዛ በመጓዝ ሌሎችን አትነካም ሲነኳት ግን በዋዛ አታሳልፍም። በዚሁ አትንኩን፣ አንነካችሁም በሰላም ተከባብረን እንኑር በማለታችን ባለመደሰታቸው ይነካኩናል። ጥጋብ የነፋቸው የበለፀጉ ሀገሮች ሁልጊዜ ከበታቻቸው ሆነው የሚሰግዱላቸውን ሰዎች ይፈልጋሉ። ደሃን ማየቱ ያስደስታቸዋል። እኛ ግን ባለማጎብደዳችንና በራሳችን ተማምነን ከመከባበርና በስተቀር እግራቸው ላይ ባለመነጠፋችን ይገረማሉ፣ ብስጭትም ይሰማቸዋል፣ ለምን የሚል ጥያቄም ያነሳሉ።
ማንም ዜጋ የአዕምሮ ዘገምተኛ ካልሆነ በስተቀር ሀብቱ ሲወሰድበት ዝም የሚል የለም። ኢትዮጵያውያንም ከዚህ በሽታ ነፃ ስለሆኑ ሀብታቸውን ላለማዘረፍ ከጥንትም ጀምሮ ሲከላከሉ የነበሩ ናቸው። ማንኛውም የውጭ ሀገር ዜጋ ወደ ሀገር ሲመጣ ቤት ያፈራውን ይጋብዙታል። ግን የሀገራቸውን ምስጢር አይዘከዝኩለትም። የሀገሪቱ ሀብትም እንዲዘረፍ አይመቻቹለትም። ታዲያ እነዚህ ቀምተን እንብላ ባዮች ለምን እንዳንዘርፍ ይከለክሉናል በማለት በመጥፎ ዓይን ሲያዩን ነበር፣ እያዩንም ናቸው። ስለዚህ አንዱ ለጠላትነት ያበቃን ሀብታችንን አናዘርፍም በማለታችን ነው። ዛሬ ግን ለወያኔ ዕድሜ እየለመኑ ዝርፊያውን ተያይዘውታል።
ሀገራችንን ላለማዘረፍ፣ ላለማዋረድ፣ ከጥፋት ለመታደግ ዘብ እንቁም።
ቸሩ ነኝ፣ ቸር ይግጥመን።
ቸሩ ላቀው
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



