ቸሩ ላቀው
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገሮች ቀደምትነት ያላት ሀገር መሆኗን ራሳችንን ከፍ ከፍ ለማድረግና ለመመጻደቅ ሳይሆን ታሪክ የመሰከረላት ናት።


ቀደም ያሉ ታሪኮቿ እንደሚመሰክሩትላት ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገሮች ከወርቅ፣ ከብርና ከነሓስ የተሠሩ የገንዘብ ሽርፍራፊዎች በመጠቀም የመጀመሪያዋ ሀገር የሆነች፣ ኃይማኖቷን ከኃይማኖቶች ውዝግብና ከፖለቲካ ቀውሶች ጠብቃ የቆየች፣ በአፍሪካ የመጀመሪያዋ የሥልጣኔ ጮራ የፈነጠቀባትና መንግሥት ለመመስረት የመጀመሪያዋ የሆነች፣ ከአፍሪካ ሀገሮች ብቸኛ የሆነውን አፍሪካዊ የግዕዝ ቋንቋ ባለቤትና ለጽሑፍም ያበቃች፣ በታሪክም ከሁለት ሺህ ዓመታት በላይ ያስመዘገበችና እንደ ሉሲ የመሳሰሉ የሰው ዘር መገኛ ቅሪተ አካል የተገኘባት ሀገር ናት። ለምን? ለምን ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች አልፈጸሙም? ኢትዮጵያውያን ከአፍሪካውያን የተለዩ ናቸው? ዘራቸው የተለየ ነው? ወይስ የያዙት ቦታ የተለየ ነው? እነዚህና መሰል ጥያቄዎች ናቸው ሀገሪቷን በውጭ ሀገራት ዕይታ ውስጥ የከተታትና በተለያዩ ዘዴዎች እየገቡ ሊበታትኗትና ሊቦጠቡጧት የሚፈልጉት።


የግብርና ክንውኖች በኢትዮጵያ መተግበር የጀመሩት ቀደም ካሉ ጊዜት ጀምሮ እንደነበር ታሪክ ሲያስረዳ በ1520ዎቹ ዓመታት ኢትዮጵያውያን በመስኖ በመጠቀምም ጥሩ ምርት ያመርቱ እንደነበር መረጃዎች ይመሰክራሉ። ይኸ መረጃ የሚመሰክረው የግብርናን ተግባር የጀመሩት ከዚያ በጣም ቀደም ብለው መሆኑንና ተደላድለው መኖር በመጀመራቸውም አፈሩ የተፈጥሮ ለምነቱ እየቀነሰ በመምጣቱ ወይም የአንድ ወቅት ዝናምን በመጠቀም አንድ ጊዜ ብቻ ከማምረት በዓመት ውስጥ ሁለት ጊዜ ማምረት እንደሚቻል በመረዳታቸው የወንዝ ውሃን እየጠለፉ መጠቀም መጀመራቸውን ነው።


ኢትዮጵያውያን ውጭ ሀገራትን መጎብኘት ከጀመሩ ረዘም ያለ ጊዜ ያላቸው ቢሆንም ጣሊያንን መጎብኘት የጀመሩት ግን ከ1306 ዓ. ም. (እአአ) ጀምሮ ነበር። ከኢጣሊያ ወገን ግን የኢጣሊያ ተወላጅ ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ የጎበኘው ፒትሮ ሮምቡሎ ሲሆን ጊዜውም ከኢትዮጵያውያኑ ጉብኝት ከአንድ መቶ ዓመት በኋላ በ1407 ዓ. ም. (እአአ) ነበር። ጉብኝት አድርገው የነበሩት ኢትዮጵያውያን ብዛታቸው 30 ሲሆን በጉብኝታቸው ወቅት ንጉሣቸው ፕሪስተር ጆን ይባል እንደነበረ፣ የሀገሪቷም ፓትሪያርክ ይኸው ንጉሥ እንደነበረና ከርሱ ሥር 127 ኤጲስቆጶሳት እንደነበሩ ለኢጣሊያው መሪ ገልጸውለት ነበር። ኤጲስቆጶሳቶቹም እያንዳንዳቸው 20 ጳጳሳት የነበሩዋቸው ሲሆን በጠቅላላው 2540 ጳጳሳት ነበሩ ማለት ነው። ፕሪስተር ጆን ንጉሠ ነገሥት ሆኖ በሥሩ 74 ንጉሦች ነበሩት። ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ልዑላንና ልዕልቶችም ነበሩ።


ፕሪስተር ጆን ዛሬ ካለነው በጣም የላቀ የሀገር ስሜት የነበረው ንጉሥ መሆኑ ከሚመሰከርለት አንዱ የዓባይ ወንዝ ችግር በዚያን ጊዜም የነበረ ስለሆነ የውሃው ተጠቃሚዎች ነን ባዮች ችግር የሚያመጡ ከሆኑ የውሃውን ፍሰት አቅጣጫ እንደሚለውጥ አስጠንቅቆ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ የዓባይ ወንዝ ጣጣ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የቆየ መሆኑን ነው።


ነጮች አፍሪካን ከተቀራመቱና ሀብቷን መጥጠው ከጨረሱም በኋላ ለቀው ለመውጣት የሞት ሽረታቸውን ከነፃ አውጪዎቹ ጋር ሲዋጉና ከለቀቁም በኋላ የአፍሪካ ታጋዮችንና መሪዎችን ሲወጉ፣ ሲማርኩ፣ ሲያሰድዱና ሲገድሉ ነበር። ኢትዮጵያዊው ዳግማዊ ምኒልክ ግን በተለየ መልኩ ሕዝባቸውን አቅፈውና ደግፈው እንዲሁም በሕዝባቸው ታቅፈውና ተደግፈው ለነጮች አልተንበረከኩም ነበር። ይባስም ብለው ኃያሉን የኢጣሊያ ወራሪ ሠራዊት አዋርደው መልሰዋል። የኢጣሊያ መሸነፍና መዋረድ ለአውሮፓ ሀገሮችም ውርደት መሆኑን በጊዜው ጽፈውታል፣ ተጸጽተዋልም። ይኸም በመሆኑ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ መሪዎችና ሕዝቦች ምን ቢያገኙና ቢሰማቸውስ ነው የማይንበረከኩት በማለት ለአያሌ ዓመታት ሲያሴሩና ሲያደቡ ነበር፣ ናቸውም። John Reader Africa በተባለው መጽሐፍ፣ በገጽ 208፣ 210፣ 265፣ 350-351፣ 583-585 ላይ ከላይ የተዘረዘሩትን መረጃዎች በማቅረብ አትቷል።


እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ታሪካዊ መረጃዎች የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያውያንን ማንነት በጉልህ የሚገልጹ ናቸው። ኢትዮጵያውያን የሆንና በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነታችን የምናምን ከሆን ይኸንኑ ስሜታችንን የምንገልጸው ኢትዮጵያን ስንወዳትና ስንሞትላት እንጂ ስናስማማት፣ ስንሸጣት፣ ስንጠላት፣ ስንገላትና ስናስገድላት አይደለም። መውደድ በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር መገለጽና መታየትም አለበት። ወላጆቻቸውን የሚወዱ ግለሰቦች በወላጆቻቸው ላይ ለሚደርሰው ችግር ሁሉ ቀድመው መድረስና መከላከል መቻል የልጅነት ግዴታቸው እንደሆነ ሁሉ ኢትዮጵያ ሀገራቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ለሚወዷት ሀገራቸው ዘብ በመቆም ከማንኛውም ችግሯና አደጋ የመጠበቅና የመከላከል ግዴታና ኃላፊነትም አለባቸው።


አንዳንድ ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል እንኳ መጥራት የሚጠየፉ፣ ስሟን ከዓለም ካርታ ላይ ለመሰረዝና ለማስሰረዝ ትግል የሚያደርጉ ያሉ ሲሆን በስሟ ደግሞ ሲነግዱና ሲጠቀሙ ይታያሉ። ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ሀገራት ሲወጡ በኢትዮጵያ ስም የተሠራና በኢትዮጵያ መንግሥት ማኅተም የታተመበት የይለፍ ወረቀት (ፓስፖርት) ይዘው ይወጣሉ፣ በዓለም ሀገራት ይሽከረከራሉ፣ ይጠቀሙበታል፣ ይከበሩበታል። በእንቅስቃሴአቸው ወቅት ደግሞ ኢትዮጵያን የሚያጠፋ ሴራ ሲጎነጉኑና ሲሸርቡ ይታያሉ፣ ይሰማሉ። ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለያይቶ ማስቀመጥ አይቻልም። ኢትዮጵያን የሚወዱ ኢትዮጵያዉያን ናቸው። ኢትዮጵያን የማይወዱ ደግሞ ፀረ ኢትዮጵያ ስለሆኑ ኢትዮጵያውያን ሊባሉ አይችሉም።


ኢትዮጵያ ስትጠራም ኢትዮጵያዊ የሆኑ በርካታ ቅርሶች አሉዋት። እነዚህ ቅርሶች በኢትዮጵያዊነታቸው ለሚያመኑ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ማንም ሊከለክላቸው የማይችል ሀብታቸው ናቸው። ለአንተ ይኸንን ያህል፣ ለአንተ ደግሞ ይኸንን ያህል ተብሎ በመጨመርና በመቀነስ የሚደለደል ሳይሆን ለሁሉም እኩል የሆነ ድርሻ አላቸው። ቅርሶቹም ለዛሬዎቹ ትውልዶች ብቻ ሳይሆኑ ለሚመጡት ትውልዶችም የሚተላለፉ እንጂ የሚሸጡና የሚለወጡ አይደሉም። የአክሱም ሐውልቶች፣ ባሁኑ ወቅት ላገሯ ሳይሆን ለሌላ ሀገር ገቢ እንዲታስገኝ የምትሽከረከሯ ሉሲ ቅሪተ አካል፣ ሶፎማር፣ ብርቅየ አዕዋፋትና እንስሳት፣ ተራሮችና ሸንተረሮች፣ የእህል ዘሮች፣ ቡና፣ አበቦች፣ የመሳሰሉ ማንም በግል የማያዝባቸው ሳይሆኑ የሁላችን የጋራ ሀብታችን ናቸው።


ቸሩ ላቀው ነኝ። ወላጅ አባቴን ላቀውን የማልወደውና የማልፈልገው ከሆነ የልጅ ከሃዲ ነኝና በላቀው መጠራት የለብኝም። በራሴ ስም ብቻ አባት አልባ ሆኜ መጠራት አለብኝ። በማልወደው አባቴ ከተጠራሁ ወንጀለኛ ነኝ። ሁላችንም ኢትዮጵያን የማንወድና በኢትዮጵያዊነታችን የማናምን ከሆነ በኢትዮጵያ ቅርሶች ላይ ያለን መብት የተሰረዘ ስለሆነ በማንኛውም የኢትዮጵያ ቅርሶች ስም የመጠቀም መብታችን የተሰረዘ በመሆኑም መጠቀም አይቻልም። ኢትዮጵያ እንደ ሆቴል፣ ቡና ቤት፣ የንግድ ድርጅት በመሳሰሉ ለንግድ መጠቀሚያ መዋል የለባትም። ሊጠቀሙ የሚችሉት ልጆቿና ወገኖቿ ናቸው። ለምሳሌ ሉሲ፣ አክሱም፣ ላሊበላ፣ ግዮን፣ ዓባይ፣ ኒያላ፣ አደይ አበባ፣ አዲስ አበባ፣ ከፋ፣ ጂማ፣ ወለጋ፣ ሐረር፣ ድሬዳዋ፣ አዋሳ፣ አሰላ፣ ባሮ፣ ባሌ፣ ዲላ፣ ጎሬ፣ ጎንደር፣ ወሎ፣ ላኮ መልዛ፣ መቀሌ፣ ትግራይ፣ ጎጃም፣ የመሳሰሉ ስሞችን ከኢትዮጵያውያን ገንዘብ ለመሰብሰብ ሲባል መጠቀም የለባቸውም። ኢትዮጵያን የሚወዱና በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑና የሚኮሩ ቢሆኑ ኖሮ እግረ መንገዳቸውን ሀገርን ማስተዋወቅ ስለሆነ በተደገፈ ነበር። ግን ዓላማውና ዒላማው የማይገናኝ ስለሆነ ከማታለል ውጭ ሌላ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም።


ኢትዮጵያን የምንወድ ሁሉ ከመበታተን፣ ከማፈራረስ፣ ከማስማማትና ከመሸጥ ተቆጥበን ለእናት ሀገራችን ዘብ እንቁም። የበጎ ሥራ ተምሳሌት ሆነን ፀንተን በመቆም ሀገራችንን እንጠብቅ።
ቸሩ ላቀው ነኝ። ቸር ይግጠመን!
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ