ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም Dr. Tewodros Adhanom

ግርማ ካሳ

ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖምን ጨምሮ በርካታ የኢሕአዴግ ባለስልጣናት፣ በተለያዩ የአሜሪካና የአውሮፓ ከተሞች በመዘዋወር፣ ለአባይ ግንባታ ገንዘብ ለማሰባሰብ ሞክረዋል። ነገር ግን በበርካታ ከተሞች፣ ከዚህ በፊት ከነበረው በተለየ ሁኔታ፣ ጠንካራ ተቃውሞ የደረሰባቸው ሲሆን፣ አንዳንድ ከተሞችም፣ ተቃዋሚዎች ስብሰባውን ሙሉ ለሙሉ እስከመቆጣጠር የደረሱበት ሁኔታም እንደነበረም ታዝበናል።

በሚነሱ ተቃውሞዎች ዙሪያ፣ በዋሺንግተን ዲስ አስተያየት የሰጡት ዶ/ር ቴዎድሮስ "በሃሳብ አለመስማማት በጣም ጤነኛ ነገር ነው። ነገር ግን እንደ ሰው ማመን የሚከብደኝ፣ ድህነትን ከአገራችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያደርገውን የልማት እንቅስቃሴ በመቃወም፣ ሳይሰለቻቸው የሚጮሁትን መታዘብ ነው" ሲሉ በሚነሱ ተቃውሞዎች ላይ ያላቸውን ንዴት አዘል ዘለፋ አሰምተዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ አምባሳደር ግርማ ብሩ፣ በሂውስተን ቴክሳስ፣ ባደረጉት ንግግር፣ የአባይን ግድብ ለመገንባት ለምን እንዳስፈለገ የሚያስረዱ ነጥቦችን ካስቀመጡ በኋላ፣ ወደ ንግግራቸው መጨረሻ ላይ ድህነትን ከአገራችን ለመቅረፍ የሚረዳ ፕሮጀክትን መቃወም ከ"ጸረ-ኢትዮጵያዊነት" ተለይቶ እንደማይታይ በማሳሰብ ነበር፣ በተቃዋሚዎች ላይ ጠንካራ ትችት ያቀረቡት።

ለአባይ ግንባታ ያለኝን የጸና ድጋፍ፣ በተለያዩ ጊዜያት በጽሁፍ ይፋ አድርጊያለሁ። ወደፊትም ይሄንን አቋሜን ከማንጸባረቅ ወደ ኋላ አልልም። አባይን መገንባት ይቻል ዘንድ፣ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ ማሰባሰብ እንደሚያስፈልግ፣ ኢትዮጵያውያንን ለማሰባሰብ ደግሞ፣ በፖለቲካውና በሰብአዊ መብት አከባበር ዙሪያ ለውጥ መደረግ እንዳለበትም አሳስቤ ነበር። ከዚህ በፊት ኢሕአዴግ ማሻሻያዎችን እንዲያደርግ የቀረበለትን ጥሪ ተቀብሎ ለብሄራዊ እርቅ ተዘጋጅቶ ቢሆን ኖሮ፣ ዳያስፖራው እነ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖምን በተቃውሞ ሳይሆን በአክብሮት ይቀበላቸው ነበር።

አምባሳደር ግርማ ብሩም ሆኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ ያጡታል ብዬ አላሳብም፤ ካጡት ግን እንዲገነዘቡ የምፈልገው ነጥብ አለኝ። እርሱም አባይ እንዳይገነባ የሚፈልግ ማንም ኢትዮጵያዊ እንደሌለ ነው። ጥያቄው አባይን የመገንባት አስፈላጊነት ላይ አይደለም። ኢትዮጵያውያን "አባይ አይገንባ" የሚል መፈክር አላሰሙም። ጥያቄው የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የዲሞክራሲና የመብት ጥያቄ ነው። "አባይ ይገደብ። ግን ከአባይ በፊት ዘረኝነት ይገደብ" ነው እየተባለ ያለው። የሪፖርተር አባባልን ልዋስና "አባይን የመገደብ ሥራ ዴሞክራሲን ባለመገደብ ይታጀብ " የሚል ነው አንዱና ዋነኛው የኢትዮጵያውያን ጥያቄ።

አባይ የሚገነባው እኮ ሕዝብን ለመጥቀም ነው። አሁን እየሆነ ያለው ግን ኢሕአዴግ አባይን፣ ተቃዋሚዎችን ለማጥቃት የሚጠቀምበት መሳሪያ እያደረገው፣ ለፖለቲካ ፍጆታና ጥቅም እየተጠቀመበት እንደሆነ ነው። አባይ ለሕዝብ መሆኑ ቀርቶ፣ ሕዝብ ለአባይ፣ አባይ ደግሞ ለኢሕአዴግ እየሆነ ነው። ከፈረሱ በፊት ሰረገላው እየቀደመ ነው። አንድ በሉ።

"አቶ መለስ ሞተዋል። የርሳቸውን ነገር ለታሪክ እንተወው። ከልብ የሚወዷቸው ደጋፊዎቻቸውን ላለማስከፋት፣ ለእርቀ ሰላም በሩን እናመቻች" በሚል ሃሳብ ነው እንጂ ዝም የምንለው፣ ወደ ኋላ ተመልሰን ነገሮችን መምዘዝ ከፈለግን እኮ፣ ብዙ ስለ አቶ መለስ ግፍና ወንጀል መዘርዘር እንችላለን። ኢሕአዴጎች ግን ዝምታችንን እንደ ሞኝነት ቆጥረውት ነው መሰለኝ፣ መለስ ዜናዊን "አምልኩት" ለማለት እየከጀላቸው ነው። የአባይንም ግድብ እንደመሳሪያ በመጠቀም የአቶ መለስን "ጀግንነት"፣ "ሕያውነት" በአይምሯችን ውስጥ ሊቀርጹ ይፈልጋሉ። አባይን ብሎ የሚመጣው ሰው ሁሉ የአቶ መለስን ምስል ተሳልሞ እንዲመለስ ነው መሰለኝ፣ በዊውስተን ቴክሳስ በተደረገው የአባይ ግድብ ስብሰባ፣ አምባሳደር ግርማ ብሩ ንግግር ያደርጉበት ከነበረው መድረክ በስተቀኝ፣ ትልቅ የአቶ መለስ ዜናዊ ምስል እንደ ታቦት ተቀምጦ ያየነው።

እንግዲህ ሁለተኛው የሕዝብ ጥያቄ "አባይን የፕሮፖጋንዳ መሳሪያ ለምን ታደርጉታላችሁ?" የሚል ነው። "አቦ ሰለቸን። ሱካርም ሲበዛ ይመራል! አባይ አባይ፣ መለስ መለስ እያላችሁ አታደንቁርን" እያለ ነው ሕዝቡ። ሁለት በሉ።

ኢሕአዴግ ለአቶ መለስ ዜናዊ ቀብር ስነ-ስርዓት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮች አቃጥሏል። ወደ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ አባላት አሉት። አብዛኞቹ አንድ ለአምስት በሚለው አሰራር፣ ሌላ ሥራ የሌላቸው፣ ሕዝብን የሚሰልሉና የሚያስጨንቁ ካድሬዎች ናቸው። በርካታ የኢሕአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣናት ዶላር እየከፈሉ፣ ልጆቻቸውን እጅግ በጣም ውድ በሆኑ ውጭ አገር ባሉ ኮሌጆችና ትምህርት ቤቶች ያስተምራሉ። የአዲስ ፎርቹኑ ጋዜጠኛ ታምራት ወልደ ጊዮርጊስ እንደዘገበው፣ ለአባይ ግድብ ከሚያስፈልገው ወጭ ሁለት እጥፍ የሚሆን፣ ወደ ስምንት ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ፣ ከኢትዮጵያ በሚስጥር ተዘርፎ ወጥቷል። መቼም ወደ 99.9 በመቶ የሚሆነው ድሃው ሕዝባችን ዶላር በእጁ ይነካል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው። በአብዛኛው ለአባይ ግድብ ገንዘብ የሚሰበስቡ የኢሕአዴግ መሪዎች፣ አባላትና ደጋፊዎቻቸው ናቸው ዶላር ወደ ውጭ አገር የሚያሸሹት።*

እንግዲህ አንድ፣ እነዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የዘነጉት ነገር ቢኖር፣ የተቃዋሚዎችና የአብዛኛው ሕዝብ ሌላው ጥያቄ፣ በአባይ ግድብ ላይ ሳይሆን፣ "ለአባይ ግንባታ ብላችሁ፣ ከሕዝብ የምትሰበስቡት ገንዘብ፣ ለአባይ ጥቅም ሳይሆን ወደ ባለስልጣናቱ ካዝና አለመግባቱ ምን ማረጋገጫ አለን?" የሚል መሆኑን ነው።

እነ ዶ/ር ቴዎድሮስ፣ በዚህ ጉዳይ ሊጠይቋቸው የሚችሉ፣ እንደ አቶ እስክንድር ነጋ፣ ርዮት አለሙ፣ ውብሸት ታዬ ያሉ ጋዜጠኞችን በሽብርተኝነት ወንጀል ከሰዋቸዋል። በሕዝቡ ፊት የኢሕአዴግ ባለስልጣናትን ቻሌንጅ ሊያደርጉ የሚሞክሩ እንደ አቶ አንድዋለም አራጌ፣ አቶ ናትናኤል መኮንን፣ አቶ በቀለ ገርባ ያሉ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን አስረዋቸዋል። እንደ ፍትህ፣ ፍኖት ያሉ ነጻ ጋዜጦችን ዘግተዋል። ሶስት በሉ።

ዶ/ር ቴዎድሮስ በዋሺንገትን ዲሲ የተናገሩት፣ አንድ የምጋራላቸው አባባል አለ። "የሃሰብ ልዩነቶች መኖራቸው በጣም ጤነኛ ነገር ነው" ባሉት እስማማለሁ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ በሃሳብ ከሚለይዋቸው ጋር ለመነጋገርና ለመመካከር ፍቃደኛ የሆኑም ይመስለኛል። የሃሳብ ልዩነቶች ሊያጣሉን፣ ሊለያዩንና ሊያቃቅሩን አይገባም። ነገር ግን፣ አንድ መረሳት የሌለበት ነጥብ ቢኖር፣ የሃሳብ ልዩነትን የማያክብረው፣ ቅድመ ሁኔታ እያስቀመጠ፣ አገር ቤት በሰላም ከሚታገሉ የፖለቲክ ድርጅቶች ጋር አልነጋገርም በማለት ግትር የሆነው፣ ለወንድማማችነትና ለብሄራዊ እርቅ በር የዘጋው፣ "ለምን ተቃውሞ ተነሳብኝ ? " ብሎ ዜጎችን የሚያስረውና የሚያስጨንቀው፣ የርሳቸው ድርጅት ኢሕአዴግ መሆኑን ነው።

የሃስብ ልዩነቶች የሚንሸራሸሩባት፣ የመቻቻል፣ የመቀባባል ባህል የሰፈነባት ኢትዮጵያን ማየት የሚሹ ከሆነ፣ ዶ/ር ቴዎድሮስ በቀዳሚነት ድርጅታቸውን ይፈትሹ ዘንድ እመክራቸዋለሁ። እርሳቸውና ጓዶቻቸው፣ የሚነሱ ተቃውሞዎችን ለማውገዝ ከሚቸኩሉ፣ ተቃውሞዎች ለምን እንደሚነሱ ቆም ብለው ቢመረምሩ፣ እንደ ከፍተኛ አመራር አባል ለሚነሱ ጥያቄዎች መፍትሄ ቢፈልጉ መልካም ነው እላለሁ።

እንደውም እውነት እንነጋገር ከተባለ የአባይ ጉዳይ እንደ ጉዳይ መነሳትም አልነበረበት፤ የለበትምም። አባይ የፖለቲክ ጉዳይ ሳይሆን የአገር ጉዳይ ነው።

ዶ/ር ቴዎድሮስ ሃሳብ ሊገባቸው አይገባም። እርሳቸውና ድርጅታቸው በነርሱ በኩል ማድረግ ያለባቸውን ካደረጉ፣ እርግጠኛ ነኝ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነትና በጋራ አገሩን ለማልማት፣ አባይን ለመገንባት ይነሳል። ኢትዮጵያውያን በአባይ ጉዳይ ቀሳቀሽና አስታዋሽ አያስፈልጋቸውም። እንኳን፣ አንዱን አባይ፣ አሥር የአባይ አይነት ግድቦች የመስራት አቅሙና ጉልብቱ አላቸው። የሚያስፈልገው ይሄንን የሕዝብ ኃይል ማዳመጥ፣ ማክበር፣ ለሚያነሳቸውም መሰረታዊ የመብት ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ብቻ ነው። አለቀ። ጆሮ ያለው፣ ይስማ፣ ልብ ያለው ያስተውል።

በተለይም የሚከተሉትን በማድረግ፣ ኢሕአዴግ ግልጽ የሆኑ የፖሊሲ አቅጣጫ ለውጦች ከወሰደ፣ እጅግ በጣም በርካታ የአገራችን ችግሮችና እንቆቅልሾች መፍትሄ ያገኛሉ ብዬ አምናለሁ።

1. እስክንድር ነጋ፣ አንዱዋለም አራጌ፣ ርዮት አለሙ፣ ውብሸት ታዬ፣ ናትናኤል መኮንን፣ በቀለ ገርባ የመሳሰሉ የሕሊና እስረኞች ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ይፈቱ። እነዚህን ወገኖች ሽብርተኞች ናቸው ብሎ ፈርጆ ማሰር፣ አስቂኝ ከመሆኑ ባሻገር፣ አሳፋሪና አሳሪዎቹንም ምን ያህል የጫካ አስተሳሰብ ያላቸው፣ ያነሱ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው።

2. እንደ ምርጫ ቦርድ፣ ሜዲያ፣ ፍርድ ቤቶችን የመሳሰሉ ተቋማት፣ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ማድረግ የሚቻልበትን መንገድ ለመመካከርና፣ ስር የሰደዱ የፖለቲካ ችግሮችን ለመፍታት ይቻል ዘንድ፣ ከተቃዋሚዎች ጋር ድርድር/ውይይት ይጀመር። ኢትዮጵያ ቻይና አይደለችም። ተቃዋሚዎችን በመርገጥና በማፈን ብቸኛ አውራ ገዢ ፓርቲ ሆኖ መቀጠል አይቻልም።

ይሄን አባባሌን አንዳንድ ኢሕአዴጎች ላይስማሙ፣ በጡንቻቸው ተማምነው፣ "ባለህበት ቀጥል" ሊባባሉ ይችላሉ። ነገር ግን እነርሱ ውስጥ ያሉ፣ ብስለት ሊኖራቸው የሚችል ጥቂቶች፣ የ"ባለህበት ቀጥል" ፖለቲካ እንደማያዋጣና ኢሕአዴግ በሰብአዊ መብቶች መከበርና በዲሞራሲያዎዊ ለውጦች ዙሪያ ትልቅ ማሻሻል ማድረግ እንደሚገባ ያጡታል ብዬ አላስብም።

3. የአባይ ግድብ ፕሮጀክት፣ የ"ኢሕአዴግ ፕሮጀክት" ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ፕሮጀክት ይሆን ዘንድ ከኢሕአዴግ እንዲሁም ከተቃዋሚዎች የተወጣጡ ባለሞያዎች ያሉበት፣ ገለልተኛ የሆነ፣ የግልጽነትና የተጠያቂነትን አሰራር ያለው፣ ኮሚሽን እንዲመራ ይደረግ።

ያኔ፣ በአባይ ግድብ ዙሪያ በሚደረጉ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች ላይ የሚነሱ ተቃውሞች አይኖሩም። ያኔ ገንዘብ ለማሰባሰብ ብዙ ዝግጅቶችም ማድረግም አያስፈልግም። በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ የሚያስፈልገውን አራት ቢሊዮን ዶላር፣ አገር ቤት ያለው ድሃ ሕዝባችን የአንድ ወር ደሞዝን እንዲከፍል ታንቆ ሳይገደድ፣ ዳያስፖራው ብቻ፣ በራሱ አነሳሽነት ሊሸፍነው ይችላል።

እንግዲህ ዶ/ር ቴዎድሮስም ሆነ ጓዶቻቸው ልብ ይላሉ ብዬ አስባለሁ። የሚነሱ ተቃውሞዎችን አናንቀው፣ ለኢትዮጵያውያን መሰረታዊ የመብት ጥያቄ ችላ ብለው የሚቀጥሉ ከሆነ ወደፊት የተወሳሰበ ሁኔታ ላይ ሊወድቁ እንደሚችሉ አሳስባለሁ። የሕዝብ መብት እየተረገጠ የሚደረግ የልማት እንቅስቃሴ ዘለቄታ አይኖርም። ምናልባት እድሜ ዘመኑን በጫካ ያሳለፈ ጠባብና እንጭጭ የኢሕአዴግ አመራር አባል፣ ይሄን ላይረዳ ይችላል። እንደ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ አቶ ደምቀ መኮንን ያሉ፣ የተማሩ፣ በሳልና ትሁት ምሁራን የኢሕአዴግ አመራር አባላት ግን ይረዱኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።


* Over $8bn Flee Ethiopia in Two Decades (Fortune newspaper)


ግርማ ካሳ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ሚያዚያ 21 ቀን 2005 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ