መኢአድና አንድነት ከሰማያዊ ጎን ቆሙ
ግርማ ካሳ
ዜጎች ሃሳባቸውን በነፃነት የመግለጽ፣ የመሰባሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ሙሉ መብት አላቸው። ይሄንን መብት በመጠቀም አገር ቤት የሚንቀሳቀሰው የሰማያዊ ፓርቲ፣ በአፍሪካ ሕብረት ፊት ለፊት ሰላማዊ ሰልፍ ይጠራል። ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት፣ ለባለስልጣናት ሰልፍ እንደተጠራ ማሳወቅ ብቻ ስለሚያስፈልግ፣ የፓርቲው አመራር አባላት ማስታወቂያ ለማስገባት ወደ አዲስ አበባ አስተዳደር ይሄዳሉ።
የአስተዳደሩ ሃላፊዎች ግን ሊያናግሯቸውም ሆነ ማስታወቂያውን ሊቀበሏቸው ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀረ። ተደጋግሞ ሙከራ ቢደረግም፣ በሕጉ መሰረት የሰማያዊ ፓርቲን ማስታወቂያ ተቀብለው፣ አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ የነበረባቸው የኩማ ደመቅሳ ሰራተኞች ግን ዜጎችን ማንገላታት መረጡ።
ዜጎች ሰልፍ በሚጠሩበት ጊዜ ለባለስልጣናት የሚያሳውቁት፣ ፍቃድ ለመጠየቅ ሳይሆን፣ የትራፊክ መጨናነቅ፣ የኮንስትራክሽን ግንባታዎች የመሳሰሉ ችግሮች ካሉ፣ አስፈላጋዊውን ዝግጅት ማድረግ፣ ያም ካልተቻለም ደግሞ ሰልፉ የሚደረገበትን ሌላ አማራጭ ቦታ ወይንም ጊዜ በመግለጽ፣ እንዲተላለፍ መጠይቅ ይችሉ ዘንድ ነው።
በአዲስ አበባ አስተዳደር እንግልት የደረሰባቸው የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አባላት፣ በፓስታ ቤት፣ በሬኮመንዴ ሰልፍ እንደሚያደርጉ የሚገለጸውን ደብዳቤ ይልካሉ። ከአስተዳደሩ ግን ምንም አይነት ምላሽ አሁንም ሳይገኝ ይቀራል። የዚህን ጊዜ ሰልፍ ለማድረግ ማሳወቅ እንጂ ከማንም ፍቃድ መጠየቅ እንደሌለባቸው ጠንቅቀው ያወቁት ብሉዎች፣ ሰልፉ በተባለው ቀን (ግንቦት 17) እና ቦታ እንደሚደረግ ያሳውቃሉ። የዚህን ጊዜ፣ በሰማያዊ ፓርቲ ውሳኔ ግራ የተጋቡትና የጨነቃቸው የአዲስ አበባ አስተዳደር ባለስልጣናት፣ በርካታ የውጭ አገር መሪዎች በአዲስ አበባ በመኖራቸውና ከፍተኛ መጨናነቅ በመኖሩ፣ ሰልፉ ከአንድ ሳምንት በኋላ እንዲደረግ ይጠይቃሉ። ሕግን የሚያከብረው ሰላማዊው የሰማያዊ ፓርቲ፣ በቀኑ መለወጥ ተስማምቶ፣ ሰልፉ የፊታችን እሁድ ግንቦት 25 ቀን 2005 ዓ.ም. እንደሚደረግ ይገልጻል።
እንግዲህ ይሄ ሁሉ የሚያሳየው፣ ለመብት፣ ለእኩልነትና ለነፃነት የሚደረገው ትግል ስር እየሰደደ መምጣቱን ነው። በዚሁ በሰላማዊው ትግል እንቅስቃሴ ዙሪያ ከፍተኛ የሆነ የኢትዮጵያውያን መሰባሰባና መተባበር እየታየ ነው። ይሄም በራሱ ትልቅ ድል ነው።
የመኢአድ ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበር የተከበሩ አቶ ወንድሙ፣ ድርጅታቸው መኢኣድ፣ ሰማያዊ ፓርቲ በጠራው ሰልፍ ላይ አባላቱና ደጋፊዎች እንዲገኙ ጥሪ እንዳቀረበ፣ ከፍተኛ የማስተባበር ሥራ እንደሚሰራም አስረድተዋል። የአንድነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ፣ የተከበሩ አቶ ዳንኤል ተፈራ በበኩላቸው፣ የአንድነት ፓርቲ የሰማያዊ ፓርቲን ጥሪ ከልብ እንደሚደግፍ፣ አባላቱም ከብሉ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር ሆነው ድምጻቸውን ለማሰማት እንደተዘጋጁ ገልጸዋል። ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር የአንድነት አመራር አባላት የቅርበት ግንኙነት እንዳላቸው የገለጹት ሌላው የአንድነት ከፍተኛ አመራር አባልና የውጭ ጉዳይ ሃላፊ፣ የተከበሩ አቶ ተመስገን ዘውዴ "የሰማያዊ ፓርቲ ያናሳቸው ጥያቄዎች የአንድነት ጥያቄዎቹ ናቸው። በአዲስ አበባ በሚገኙ 23 ወራዳዎች ባሉት ሴሎችና ጽ/ቤቶቹ አማክኝነት፣ የቅስቀሳ ሥራ ጀምሯል" ሲሉም የሰላማዊ እንቅስቃሴውን ግለት ለማሳየት ሞክረዋል።
ከመኢአድና ከአንድነት ፓርቲ በተጨማሪ የባላራዩ የወጣቶች ማህበር የተስኘው የሲቪክ ማህበርም በሰልፉ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ የገለጸ ሲሆን፣ የአመራር አባላቱ ከሰልፉ ጋር በተገናኘም ከወዲሁ ከፍተኛ እንግልት እየደረሰባቸው ነው። የባላራእዩ ወጣቶች ማህበር የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ፣ ወጣት ተክለ ያሬድ በአሁኑ ወቅት በአገዛዙ ፖሊሶች ተይዞ በእሥር ቤት ይገኛል። ይሄም የሚያሳየው ምን ያህል በአገር ቤት ያሉ ወገኖቻችን ከፍተኛ መስዋእትነት እየከፈሉ እንዳለ ነው።
ወደ ውጭ አገር ስንመጣ ደግሞ ኢትዮጵያውያን በሚሰባሰቡበት በርካታ የፓልቶክ ክፍሎች ከመቼውም ጊዜ በላይ፣ ከቅንጅት ጊዜ ጀምሮ ታይቶ ያልታወቀ፣ አገር ቤት እየተደረገ ላለው ትግል ትልቅ ድጋፍ እየተሰጠ ነው። ትላንት የተለያየ መስመር ይዘው እርስ በርስ ሲላተሙ የነበሩ፣ የቃሌ ክፍል፣ ከረንት አፌር፣ ደብትራው፣ ሲቪሊቲ ... የመሳሰሉ ክፍሎች እየተግባቡ፣ እየተቀራረቡና ለአንድ አላማ በአንድ ላይ እየተሰባሰቡ ነው። ሁሉም ትኩረታቸውን አገር ቤት አድርገው፣ እየተደረገ ላለው ሰላማዊ ትግል ድጋፋቸውን እየለገሱ ነው። እንደ ኢሳት፣ ኢትዮጵያ ሪቪው፣ ዘሃበሻ፣ አቡጊዳ፣ ኢኤምኤፍ ያሉ ሜዲያዎችም፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፊ ዘገባ እያቀረቡበት ሲሆን፣ ተስፋ ቆርጠው፣ በነበሩት መከፋፈሎች አዝነው፣ ዝምታን መርጠው የነበሩ ሁሉ እየተነቃነቁ ነው።
በውጭ አገር ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶችን ካየን ደግሞ፣ በባህር ዳር ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንዳደረገ በኢሳት የተዘገበለት የሽግግር ምክር ቤት የተሰኘው ድርጅት፣ እንዲሁም ኢሕአፓ-ዴ፣ የሰማያዊ ፓርቲ ለጠራው መኢአድና አንድነትን ለተቀላቀሉት የሰላማዊ ሰልፍ ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል። በስምንት የፓልቶክ ክፍሎች፣ በፌስቡክና ትዊተር በመተላለፍ ወደ 10 ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ተከታትለውታል በተባለው፣ ግንቦት 17 እና 18 2005 ዓ.ም የሲቪሊቲ ክፍል ባዘጋጀው የአለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን ኮንፍራንስ ላይ፣ የተገኙት የሽግግር ምክት ቤቱ ዋና ጸሃፊ የተከበሩ ዶር ፍስሐ እሸቱ፣ ድርጅታቸው በአገር ቤት ለሚደረገው ሰላማዊ ትግል ሙሉ ድጋፍ እንዳለው አረጋግጠዋል። "ትግሉ ያለው አገር ቤት ነው። አገር ቤት የሚታገሉትን መርዳት አለብን" ሲሉ ነበር ዶር ፍስሐ ለአገር ቤቱ ትግል ያላቸውን ጠንካራ ሶሊዳሪቲ የገለጹት።
ይሄ ሁሉ እንግዲህ የሚያሳያው ጸሎታችን እየተሰማ እንደሆነ፣ እንደ ሕዝብ ለመብታችን፣ ለአገራችን አንድነት መከበር፣ ለእኩልነት፣ ለፍትህ መስፈን፣ ለሕግ የበላያነት፣ ለመታገል በአንድ ላይ እየተሰባሰብን መሆኑን ነው።
ሁለት ነጥቦች ጣል አድርጌ ላቁም። በጣም መሰረታዊና ሊሰመርባቸው የሚገባ ነጥቦች!
አንደኛ - የፊታችን ቅዳሜ ግንቦት 24 ቀን የሚደረገው ሰልፍ ጅማሬ እንጂ ፍጻሜ አይደለም። ቀጣይነት ያለው፣ የተደራጀ፣ የተጠና ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ይቀጥላሉ። በዘጠና ሰባት በግፍ የተገደሉትን፣ እነ ሽብሬ ደሳለኝ፣ ለማስታወስ፣ የአንድነት ፓርቲ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ለማድረግ ዝግጅት ላይ እንዳለ የፍኖት ጋዜጣ በቅርቡ መዘገቡ ይታወሳል።። ለአንድነት ቅርበት ያላቸው እንደገለጹልኝ፣ የሚደረጉትን ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች፣ ሰላማዊ ሰልፎችን የሚያካትቱ ሲሆኑ፣ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በማቀናጀት የሚሰራ እንደሆነም ለመረዳት ችያለሁ። መኢአድም እንደዚሁ የሚያደጋቸው ይኖራል። በአጭሩ ተከታታይ እንቅስቃሴዎች በሁሉም መስክ ይኖራሉ።
ሁለተኛ- የፊታችን ቅዳሜ ግንቦት 24 የሚደረገው ሰልፍ፣ ሰማያዊ ፓርቲ ቢጠራውም፣ የመኢአድ፣ የአንድነት፣ የሽግግር ምክር ቤቱ፣ የኢሕአፓ-ዴ፣ የባላራዩ ወጣቶች ማሕበር፣ ሰልፉን የምንደግፍ ዜጎች ሁሉ ሰልፍ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰልፍ ነው። ሰማያዊ ፓርቲ ለኮሰ። የተለኮሰውን ማቀጣጠል የእያንዳዳችን ነው። በድርጅቶች የሚጠሩት እንቅስቃሴዎች ውጤት የሚያመጡት እያንዳንዳችን ስንተባበር ብቻ ነው። አገር ቤት ያለነው ወደ ሰልፉ መሄድ ይጠበቅብናል። ሰልፉ ሰላማዊና በሕግ የተፈቀደ ነው። "መብታችን ተረገጠ፣ ድህነት በዛ፣ ዘረኝነት በዛ፣ በአገራችን ባርያ ሆንን መኖር መረረን፣ ፍትህ ጎደለ፣ ቀንበርና ግፍ በዛ" የምንል ካለን፣ እንግዲህ ጊዜው አሁን ነው። ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንነሳ። እንጩህ። ድምጻችን እንደ ነጎድጓድ ያስተጋባ። አንፍራ።
በውጭ አገር ያለነው ደግሞ፣ ስልክ እንደውል፣ ኢሜል እንላክ። ዘመድ ወዳጆቻችንን እናበረታታ። ደብረጽዮን የስልክ መስመሩን እና ኢንተርኔቱን ሊዘጋው ይችላል። ግድ ይለም። መስመሮቹን እንዲዘጋ ማስደረጋችን በራሱ ትልቅ ድል ነው።
ያኔ ኢትዮጵያም በልጆቿ ትኩራለች!
ግርማ ካሳ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ግንቦት 22 ቀን 2005. ዓ.ም.