ግርማ ሠይፉ ማሩ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሦስተኛ ዓመት ሁለተኛው ዓመት አጋማሽ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ መለስ ዜናዊ በሞት መለየት መንስዔ ከገባበት የሀዘን ድባብ ተላቆ ከወትሮ በተሻለ መነቃቃት እየታየበት እንደሆነ ይታመናል። ይህ እውነት ቢሆንም አንዳንዶች ምንም አዲስ ነገር የለም ይላሉ (የአዲስ አድማስን "ፓርላማው ጥርስ አወጣ" ዘገባን ልብ ይሉዋል።) አዲስ ነገር መኖሩ ግን እየታየ ያለ አውነት ነው።

 


በምክር ቤት አባላት ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትሩ የቀረቡት ጥያቄዎች እንዲሁ በዋዛ የሚታዩ አልነበሩም። ይህ ሁሉ ሆኖ ምክር ቤቱ በሰኔ 13 ውሎው በቀኝ በኩል በአማራ ክልል ተወካዮች አማካኝነት ሲያጠቃ ውሎ ግብ ማስቆጠር ግን ሳይሆንለት ቀርቶዋል። ሙከራው ግን አበረታች ነው።

 

የ1999 የህዝብ ቆጠራ ብዙ አከራካሪ ነጥብ የነበረው ቢሆም የአማራ እና የአዲስ አበባ የህዝብ ቁጥር ከቅድመ ግምት ያነሰ መሆኑ አንዱ ነበር። የአማራ ክልል ህዝብ ቀድሞ ከነበረው ቅድመ ግምት በሶስት ሚሊዮን ገደማ ማነሱ ይህ ሁሉ ህዝብ የት ደረሰ ለሚለው ጥያቄ መልስ መስጠት አስፈላጊ የነበረ ሲሆን፤ መልሶቹ የአንድን ክልል የህዝብ ቁጥር ሊቀንሱ የሚችሉትን ዋና ዋና ኹነቶች ሶስት ሲሆኑ፤ እነርሱም ፍልሰት፣ ሞት እና የውልደት ምጣኔ እንደሆኑ ይታወቃል። ለነዚህ ጉዳዮች በየተራ የቀረበው ሙግትና የተሰጠው ማብራሪያ የሚከተለው ነበር።

 

ፍልሰት
የፍልሰት ዋነኛ ተቀባይ የሆነችው አዲስ አበባ እንኳን ሶስት ሚሊዮን ከአማራ ልትቀበል፤ የራሷን ነዋሪ ሶስት ሚሊዮን እንዳልደረስ የሚታወቅ ነው። ስለዚህ ለአማራ ክልል ሕዝብ መቀነስ ፍልሰት በተለይ ወደ አዲስ አበባ የማይታሰብ ስለነበር በ2001 ሪፖርት ሲቀርብም እንደ ምክንያት የቀረበ አልነበረም። ዳርዳርታው ግን ነበር።

 

ሞት
ሁለተኛው ምክንያት ሞት ነው። የአማራ ህዝብ የሞት ምጣኔ ከሌላው ህዝብ በተለየ ሁኔታ እንዲሞት የሚያደርግ የተፈጥሮ ወይም ሰው ሰራሽ አደጋ ካለመኖሩ ጋር ይህ ጉዳይ ብዙ የሚባልለት ባይሆንም በብዙ የምክር ቤት አባላት ለመጥቀስ ፈራ ተባ ሲሉ አንደኛው የምክር ቤት አባል ግን ደፍረው፤ የአማራ ክልል ህዝብ በተለየ ሁኔታ በኤድስ ሞቶዋል መባሉ ትክክል ስለአልሆነ ይቅርታ መጠየቅ ሲከፋም በኃላፊነት መጠየቅ አስፈላጊ መሆኑን ሞግተዋል።

 

የውልደት ምጣኔ
የውልደት ምጣኔ በመላው ሀገሪቱ ዝቅ እያለ የመጣ ቢሆንም፤ በአማራ ክልል በተለየ ሁኔታ ዝቅተኛ ነው ማለት እንደማይቻል ይልቁንም በክልሉ በስፋት ካለው ያለ ዕድሜ ጋብቻ እና አንድ እናት ብዙ ልጆችን መውለድ አንፃር ሲታይ ይህም ተቀባይነት እንደሌለው በምክር ቤቱ ሞጋች ሆኖ ነበር።

 

የእነዚህ ሶሰት ጉዳዮች ድምር ውጤት የሆነው የህዝብ ዕድገት ምጣኔ 1.73 በመሆኑ ምንም ተቀባይነት እንደሌለው የተከራከሩ ሲሆን፤ በሴንሰስ ማዕከል (በአምስት ዓመት) የተደረገው ጥናትም ያሳየው ሐቅ የአማራ ክልል የህዝብ ዕድገት ምጣኔ ከፍ ብሎ 2.3 በመቶ እንደሆነ ይፋ ሆኖዋል።

 

የምክር ቤት አባላት በዚህ ስህተት ምክንያት የአማራ ክልል ህዝብ ቁጥር "አንሷል" በሚል ላለፉት አምስት ዓመታት ከዘጠኝ እስከ አስር ለሚሆን ወረዳ የሚሆን በጀት እንዲያጣ ተደርጓል። ከዚህም በላይ የአማራ ክልል ህዝብ ተገቢ ባልሆነ መልኩ በኤድስ ሞቶዋል የሚለው ጉዳይ ይቅርታ ሊያስጠይቅ ብሎም በኃላፊነት ሊያስጠይቅ ይገባል የሚል አቋም በስፋት ሲቀርብ ነበር። በዚህ መስመር በቀኝ ክንፍ ሲያጠቃ የዋለው ምክር ቤት በመጨረሻ ግብ ማስቆጠር አልቻለም። ይቅርታውንም ሆነ ተጠያቂነትንም ማረጋገጥ አልቻለም።

 

እንደ ግብ ይቆጠር የነበረው የአማራ ህዝብ በተለይ በኤድስ ሞቶዋል የሚለውን የ1999 የህዝብ ቆጠራ ውጤት ማብራረያ እና የአማራ ህዝብ የህዝብ ዕድገት ምጣኔ ከሀገሪቱ አማካይ በታች እንዲሁም ከአንድ አንዴ አውሮፓ ሀገራት ጋር በሚመጣጠን ሁኔታ 1.73 በመቶ ነው የሚለው ትክክል ያለመሆኑን በአማራ ክልል የተለየ የህዝብ ፍልሰት አለ የሚለውን ሁኔታ አስረግጦ መልስ መስጠት ባለተቻለበት ሁኔታ ነው። መታወቅ ያለበት አንዱ ሐቅ ግን ከ1999 በፊት የነበረው ቆጠራ ልክ ከነበረ የዕድገት ምጣኔው 1.73 ልክ ካልሆነ የ1999 ዓ.ም.ቱ 17.1 ሚልዮን ልክ አይደለም።

 

የምክር ቤት አባላቱ ይቅርታ ከመጠየቅ እስከ መጠየቅ የሚል ሃሳብ ቢያቀርቡም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለወደፊት ተሞክሮ መውሰጃ ተደርጎ መታየት አለበት በሚል አረጋግተው፤ አፈ ጉባዔው ደግሞ ድምፅ ሳያሰጡ በስምምነት በሚል እንዲፀድቅ አድርገውታል። የምክር ቤቱ አባላት ከወትሮ በተለየ በመረጃ በተደገፈ ሲሞግቱ ቢውሉም የአማራ ህዝብ ቁጥር በቃ እንደተቆጠረው ነው ተብሎ የታለፈ ሲሆን፤ ከ1999 በኋላ ግን በ2.3 በመቶ እንዲያድግ ተደገርጎ የ2004 የአማራ ቁጥር 19.2 ሚልዮን ሆኖዋል ተብልዋል።

 

መታወቅ ያለበት ስህተቱ የቅድመ ግምት እንጂ የቆጠራ ያለመሆኑን፣ የግምት ስህተት ለአማራ ክልል በዚያን ያህል ርቀት ለምን? የሚለው ያልተመለሰ ጥያቄ ሲሆን፤ እያከራከረ እንደሚቀጥል ይጠበቃል። ይህ ጉዳይ በአዲስ አበባም ተመሳሳይ ነው።

 

በዚሁ አጋጣሚ ኢቲቪ የ2001 የህዝብ ሪፖርት ቆጠራ ተከትሎ የአማራ ህዝብ በስነ ተዋልዶ ያመጣውን ስኬት በማሳየት በወቅቱ የተገለፀውን የ1.73 በመቶ ዕድገት ለማስረዳት የደከመው ድካም ሲታይ ግን አሁን ምን ሊል እንደሚችል መጠየቅ አስፈላጊ ይመስለኛል። አሁንም ቢሆን የአማራ ህዝብ ዕድገት ምጣኔ 2.3 በመቶ ነው የተባለው በዋነኝነት የአማራ ህዝብ ፍልሰትም ከሌላው በተለየ ከፍተኛ በመሆኑ ነው የሚል ማብራሪያ ተሰጥቶዋል። ተቀባዩ አዲስ አበባ ነው የሚል ይመስላል አዲስ አበባ ግን በዚያው ልክ ቁጥሩ እየጨመረ አይደለም። ነገሩ ግራ የገባው ግራ ዓይነት ነው።

 

አዲስ አበባን በሚመለከት አንድ አንድ መረጃ ልስጣችሁና ይህን ጦማር ላብቃ። የአዲስ አበባ ባለ አደራ መስተዳድር ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ዶ/ር ውብሸት የአዲስ አበባ ህዝብ 4 ሚልዮን እንደሚገመትና የአዲስ አበባ ውሃ ሽፋንም ሰባ አምስት በመቶ እንደሆነ ገልጸው ነበር። በዚህ ስሌት የአዲስ አበባ ህዝብ 2.7 ሚልዮን ከሆነ የአዲስ አበባ የውሃ ሽፋን ከመቶ በላይ እንደሆነ መገመት ይቻላል። አሁንም ቢሆን የአዲስ አበባ ህዝብ ቁጥር በቃ ሶስት ሚልዮን ገደማ ነው ተብልዋል። ብዙ መስሎ የሚታየው ውሎ ገብ ነው የሚል ሆኖዋል።

 

ጎበዝ አሁን መንግሥት ለመስራት ባቀደው የቤት ምዝገባ 1.3 ሚልዮን ቤት ፈላጊ ዕድሜው ከአስራ ስምንት ዓመት በላይ የሆነ ነዋሪነቱ አዲስ አበባ የሆነ ብቻ ይመዘገባል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ ማለት አዲስ አበባ አሁን ምንም የመኖሪያ ቤት የላትም ወደሚል መደምደሚያ የሚወስድ ነው። ቴሌ ኮሚኒኬሽን በአዲስ አበባ ከ2.5 ሚልዮን በላይ ሞባይል እንዳሰራጨ ይናገራል። ስለዚህ የአዲስ አበባ ነዋሪ የሞባይል ሽፋን መጣራት ያለበት ነው። ህፃናቱ ሁሉ ሞባይል ይዘዋል ማለት ነው? የአዲስ አበባ ሕዝብ ቆጠራ በመጽሐፍ ቅዱስ አቆጣጠር ይሆን እንዴ? ያስብላል። ሴቶችና ሕፃናትን ሳይጨምር።

 

መቼም በቁጥር እንኳን ላለመተማመን የተስማማን ይመስላል። ኧረ የምናምነው የመንግሥት ተቋም ስጠን ብለን እንፀልይ። በተጨማሪም ሲያጠፋ ይቅርታ የሚጠይቅ እና ላጠፋው ጥፋትም ተጠያቂ የሚሆን - አሜን!


ከአዘጋጁ የተከበሩ ግርማ ሠይፉ ማሩ ብቸኛው የፓርላማ አባል መሆናቸው ይታወቃል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ