ዶ/ር ብርሃኑ ነጋና አውራምባ ታይምስ
ግርማ ካሳ
ከዶ/ር ብርሃኑ ጋር አንድ ወቅት፣ የቅንጅት አመራር አባል የነበሩ ጊዜ በጣም ወዳጆች ነበርን። ላለፉት አምስት አመታት ግን ተራራቅን። አለመስማማት በመካከላችን ተፈጠረ። እርሳቸው አንድ መንገድ ያዙ። የጦርነት መንገድ! ከማይመቹን ቡድኖች ጋር ማበር ጀመሩ። በተለያዩ ጊዜያት የሚመሩት ድርጅት የሚያራምዳቸውን ፖሊሲዎችን መንቀፍ ጀመርን። የፖለቲካ ልዩነት ባህል ብዙ ያልገባቸው የርሳቸው ደጋፊዎች ተነሱብን። "ግንቦት ሰባትን ለምን ትናገራላችሁ?" በሚል ወያኔ ተባልን።
ከጅምሩ ቅንጅቱን በይፋ ሳይለቁ፣ የቅንጅት አመራር የነበሩ ጊዜ ነበር ዶ/ር ብርሃኑ ስለ ጠመንጃ ትግል ማውራት የጀመሩት። የቅንጅት ድጋፍ ድርጅቶች የሰላማዊ ትግሉን የሚደግፉ እንደመሆናቸው፣ በድጋፍ ድርጅቶች ስብሰባ ላይ ስለጠመንጃ መወራቱ አላስደሰታቸውም። ዶ/ር ብርሃኑን ማስተናገድ አቆሙ። የዚህን ጊዜ ግንቦት ሰባት የተሰኝ ድርጅት አቋቋሙ። ይኸው በግንቦት ሰባት ውስጥ መንቀሳቀስ ከጀመሩ አምስት አመት ሆናቸው።
በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ አገኙ። "አገር ቤት የሚደረገው ትግል ዋጋ የለውም። የሰላማዊ ትግል ኢትዮጵያ ውስጥ አደርጋለሁ ማለት ቅዠት ነው" እያሉ አገር ቤት ያሉ ታጋዮች የሚያገኙትን ድጋፍ ለማራቆት ከፍተኛ ዘመቻ አደረጉ። አገር ቤት የነበሩ እንደ አውራምባ ታይምስ ያሉ ጋዜጦችም፣ አገር በት ያሉ እንደ አንድነት ፓርቲ የመሳሰሉትን ወደ ጎን እየገፉ፣ በስፋት እርሳቸው የሚመሩትን ድርጅት፣ የግንቦት ሰባትን እንቅስቃሴ መዘገብ ጀመሩ። ከአቶ አንዳርጋቸውና ጽጌና ከእርሳቸው ጋር የተደረገ ሰፊ ቃለ ምልልስ በዚህ ጋዜጣ ላይ ወጥቶ አነበብን። የእናት አገር ፍቅር ሰርተፊኬት እየተሰጠ ብዙዎች አምስት መቶ፣ አምስት መቶ ዶላሮች አዋጡ። ብዙ ገንዘብ ተሰበሰበ። እኛ በመርህ ላይ ተመርኩዘን ተቃውሟችንን ቀጠልን። "ትግሉ ያለው አገር ቤት ነው። ከውጭ ሆኖ ዘራፍ ማለት ውጤት የማያመጣ ፖለቲካ ነው። ዳግመኛ ኢሕአፓ መሆን ነው" ብለን ተከራከርን። ብዙ ተሰሚነት አላገኘንም።
አንድ አመት አለፈ። ሁለት ተባለ። ምንም ነገር የለም። "በአጭር ጊዜ ውስጥ ወያኔን አፍንጫውን ብለን እናስወግደዋለን፤ እኛ በሩን ማንኳኳት ሳይሆን ሰብረን ነው የምንገባው ..." በሚል የተሰጡን ተስፋዎች ተስፋ ብቻ ሆነው ቀሩ። ድንገት ሳናስበው የግንቦት ሰባቱ ዋና ጸሃፊ፣ ቲራቮሎ አስመራ አይሮፕላን ጣቢያ ኮቴያቸው አረፈ። ግንቦት ሰባት፣ እንደ ኦነግ፣ ኦብነግ የመሳሰሉቱ፣ ከሻእቢያ ጋር ተወዳጀ። የአፍሪካ ኪም ኢል ሱንግ ከተባለው፣ በአስመራ ያሉ ወገኖቻችን እያረደ ካለው፣ እብድና በሽተኛ ሰው ጋር ግንቦት ሰባቶች ተቃቀፉ። የፖለቲካ ክስረት ይሉታል ይሄ ነው!
ሻእቢያ ውስጥ ውስጡን ከወያኔ/ኢሕአዴግ ጋር እንደሚገናኝ ይታማል። በምንም አይነት ጠንካራ ኢትዮጵያዊ ኃይል እንዲኖር አይፈልግም። ኦነግ፣ የአርበኞች ግንባር ... ለሃያ አመታት አስመራ ተክለው አንድ ቀበሌ ማስለቀቅ አለመቻላቸው አንዱ ምክንያት፣ ወያኔ/ኢሕአዴግ ጠንካራ ስለሆነ ሳይሆን፣ ሻእቢያ የተቃዋሚ ግንባሮች ትንሽ ጠንከር ሲሉ ስለሚመታቸው መሆኑ በግልጽ የታወቀ ነው። (ሻእቢያ፣ አስቀድሞ ለወያኔ/ኢሕአዴግ ነግሮ፣ ከሶት ሺሆች በላይ የኦነግ ወታደሮችን በሱዳን በኩል በማስገባት፣ አንድ በአንድ በጥይት እንዲለቀሙ ማድረጉን አንድ የደምቢ ዶሎ ልጅ በምሬት ነግሮኛል።)
ይሄንን አሳዛኝ ወታደራዊ እውነታ እየተናገርን፣ የግንቦት ሰባት አመራሮች ከሻእቢያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲበጥሱ ጥሪ ማቅረቡን ቀጠልን። በተለይም እነ ጄነራል ከማል ገልቺ የቁም እስረኛ መሆናቸውን ኢትዮጵያ ሪቪው ከዘገባ በኋላ፣ ግንቦት ስባት ከአምስት አመታት በኋላ አንዳች ውጤት ያላመጣበትን፣ የሌለና የውሸት የጠመንጃ ትግል የሚለውን ትቶ፣ ከአስመራ ጥገኝነት ተላቆ፣ ከብሄራዊ የሽግግር ምክር ቤት፣ በቅርብ ከተቋቋመው ከኦሮሞ ዴሞክራሲአይዊ ግንባር፣ ከሸንጎ፣ እንዲሁም በአቶ ኦባንግ ከሚመራው የኢትዮጵያ ሶሊዳሪቲ ንቅናቄ ጋር በመሆን፣ የተደራጀ፣ ውጤት የሚያመጣ የዲፕሎማሲ ሥራ የሚሰራ፣ አገር ቤት ያለውን ትግል የሚደግፍ፣ አንድ ትልቅ የኢትዮጵያውያን የተባበረ ኃይል እንዲመሰርቱ፣ በዚያም ትልቅ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ በመገልጽ ውስጥ ውስጡን ትልቅ ግፊት አደረግን።"እባካችሁ የሌለ ጀብደኝነት እያወራችሁ አገር ቤት ያሉትን ሰላማዊ ታጋዮች እንዲያጠቃ ለአገዛዙም ሰበብ አትስጡ" እያልን ጮህን።
የኢሳቱ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ዶ/ር ብርሃኑን ቃለ መጠይቅ ባደረገ ጊዜ "አምስት አመታት ሙሉ ምን ተሰራ? ለምን እርስዎ ጫካ አልሄዱም? ..." የሚሉ መሰረታዊ ጥያቄዎች አቀረበ። ዶክተሩ መልስ የላቸውም። አራያና ቆቦ፣ የማይገናኙና የማያሳምኑ አረፍተ ነገሮችን ወረወሩ። ኢሳት የግንቦት ሰባት ጥገኛ አለመሆኑንም በዚህ አጋጣሚ አሳየ።
በአምስተኛው የግንቦት ሰባት ጠቅላላ ጉባኤ፣ ውስጥ ውስጡን፤ላደረግናቸው ግፊቶች አዎንታዊ መልስ ስንጠብቅ፣ የሚያሳዝን ዜና እንደገና ሰማን። በጉባያቸው ምንም ውጤት እንዳላመጡ ቢያምኑም፣ ላለፉት አምስት አመታት ሲያራምዱት የነበረውን ግን ለመቀየር አልተዘጋጁም። የድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊው አቶ ኤፍሬም ማዴቦ እንደገና በይፋ ከሻእቢያ ጋር ያላቸውን ትብብር አረጋገጡ።
በዚህ ሳምንት ደግሞ አንድ አስገራሚ ኦዲዮ አደመጥን። ግንቦት ሰባት ከግብጽ ግማሽ ሚሊዮን ዶላር እንደተረዳ አውራምባ ታይምስ ዘገበ። አውራምባ ታይምስ ያቀረበው ዘገባ የፈጠራ ዘገባ አይደለም። አንድ ጋዜጠኛ እውነትን ሲዘግብ ሊመሰገን እንጂ ሊወቀስ አይገባም። ለቀረበው ሪፖርት የሰለጠነ መልስ ከመስጠት ይልቅ ግን፣ ዶ/ር ብርሃኑ የአውራምባ ታይምስን ኤዲተር በበረከት ስም የተላከ ወያኔ እንደሆነ በመግልጽ መክሰስን መረጡ።
አቶ ዳዊት ከርሳቸው ጋር በቃሊት የታሰረ ነው። አቶ ዳዊት የድርጅታቸውን እንቅስቃሴ በአገር ቤት ውስጥ ሆኖ ሲዘግብ የነበረ ነው። ያኔ አቶ በረከት ነበር እንዴ፣ የርሳቸውን ቃለ መጠይቅ አውራምባ ታይምስ እንዲያወጣ ትእዛዝ ሲሰጥ የነበረው? የምንፈልገው ሲጽፍ ወዳጅ፣ የማንወደውን ሲጽፍ ጠላት አድርጎ ማየቱስ ተገቢ ነውን?
ከጅምሩ በግለሰብ ደረጃ ሳይሆን በሚያራምዱት ፖለቲካ ከግንቦት ሰባት ጋር ያሉኝን ልዩነቶች ገልጫለሁ። የአውራምባ ታይምስ ኤዲተር አቶ ዳዊት "ለግንቦት ሰባት ትልቅ ድጋፍ እየሰጠ፣ በወቅቱ ያኔ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ይመራ በነበረው የአንድነት ፓርቲ ላይ ጠንካራ ትችቶች ይሰነዝራል" የሚል ቅሬታ ነበረኝ። ከዚህም የተነሳ እንደ አንድነት ደጋፊ ቅሬታዬን አሳውቄያለሁ። እንደምሳሌ በተለያዩ ጊዜ ከተጻፉ ብዙ ኢሜሎች መካከል፣ ከአራት አመታት በፊት ለአውራምባ ታይምስ ከጻፍኩት ቀንጥቤ የሚከተለውን አቅርቤያልሁ።

አውራምባ ታይምስ በአንድነት ፓርቲ ላይ ጠንካራ ትችት ሲያቀርብ፣ ደጋፊዎችም ሆነ የአንድነት አመራር አባላት፣ ባንስማማም፣ አቶ ዳዊትን፣ "ወያኔ፣ ካድሬ፣ የበረከት ተላላኪ" እያልን ወደ ስድብና ተራ የስም ማጥፋት ዘመቻ አልሄድንም።
አቶ ዳዊት ከበደ ጋዜጠኛ ነው። እንደ ማንም ባለሞያ ስህተቶች ሊሰራ ይችላል። በሰለጠነ መልኩ ስህተቶች ማረም ሲቻል፣ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ካለመፈለግ የተነሳ፣ አንገብጋቢ ጉዳዮችን ወደ ጎን ጥሎ ግለሰቦችን ማጥቃት ግን የስድሳዎች እንጂ በ2005 ሊኖር የሚገባው የሰለጠነ ፖለቲካ አይደለም።
ዶ/ር ብርሃኑ በኦዲዮ የተሰማውን የተናገሩት ከግንቦት ሰባት አባላት ነው። ለነ በረከት ስምኦን አይደለም የተናገሩት። ይህ ኦዲዮ የተገኘው ከበረከት ስምኦን ሳይሆን ከግንቦት ሰባት አመራር አባላት ነው። ከግንቦት ሰባት ውስጥ ነው። አውራምብ ታይምስ፣ ከግንቦት ሰባት አባላት ከራሳቸው የደረሰውንና ይፋ ያደረገው ኦዲዮ፣ ዶ/ር ብርሃኑ ግማሽ ሚሊዮን ዶላር ከአንድ ካልተጠቀሰ አገር እንደተቀበሉ በግልጽ ያሳያል። ከሌሎች ሶስት ጓዶቻቸው ጋር ወደዚያ አገር ይሄዳሉ። በዚያ ያሉ ባለስልጣናትን ያነጋግራሉ።
ሻእቢያ ከራሱ አውጥቶ ዶላር እንደማይሰጥ፣ ዶ/ር ብርሃኑም አስመራ እንዳልበረሩ የሚታወቅ ነው። ስለዚህ "የት አገር ነው የሄዱት?" ለሚለው ቀጥተኛ መረጃ የለም። አውራምባ ታይምስ ግብጽ እንደሆነ ይናገራል። ይሄን የአውራምባ ታይምስ ዘገባ ግን "ውሸት ነው" በማለት ዶ/ር ብርሃኑ ለማስተባበል ፍቃደኛ አልሆኑም። ይሄም ገንዘቡ ከግብጽ ለመገኘቱ አንድ ሰርከምስታንሻል ማስረጃ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
እንግዲህ እውነታው ይሄ ነው። ጥያቄውና ትኩረቱ መሆን ያለበት አውራምባ ታይምስ ላይ፣ የበረከት ስምኦን ማንነት ላይ ሳይሆን፣ የተነሳው ጉዳይ ላይ ነው። ጥያቄውና ጉዳዩ የኢትዮጵያ ጥቅምን የሚነካ ጉዳይ ነው።
የአንድነት ፓርቲ፣ የሰማያዊ ፓርቲ እንዲሁም መድረክ ከአንድ ኢትዮጵያዊ ድርጅት የሚጠበቅ መግለጫዎች በማውጣት፣ ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝን የመጠቀም ሙሉ መብት እንዳላት በማረጋገጥ፣ ለግብጽ ፖለቲከኞች፣ የሚያኮራ ኢትዮጵያዊ መልስ ሰጥተዋል። "እነርሱ (ግብጾች) ከአባታቸው አይበልጡም፤ እኛም ከአባቶቻችን አናንስም" በማለት ነበር እንደውም ሰማያዊ ፓርቲ በተዘዋዋሪ መንገድ የጉራን እና የጉንደትን ድል በማውሳት ለግብጽ የፀብ ጫሪነት ፕሮፖጋንዳ ምላሽ የሰጠው።
ለኢትዮጵያ ጥቅም ቆመናል ከሚሉ ድርጅቶ እነ ሰማያዊ የሰጡት አይነት ምላሽ ይጠበቃል እንጂ "አባይን ለማፍረስ የተቃዋሚ ድርጅቶች በመርዳት በኢትዮጵያ ቀውስ እንፍጠር" እያሉ ከዛቱ ግብጾች እርዳታ መቀበል አይጠበቅም። ትልቅ ታሪካዊ ስህተት ነው እየተሰራ ያለው።
አሁንም ለግንቦት ሰባት አመራሮች ወንድማዊ ምክሬን እለግሳለሁ። ዶ/ር ብርሃኑ በኮንግረስ የሰጡትን አስተያየት ብዙዎቻችን አድንቀናል። በቅንጅት ጊዜ የምናውቃቸው ዶ/ር ብርሃኑን አስታወሰን። ይህ አይነቱን የሰለጠነ፣ ሰዎችን በማሳመንና በማግባባት ላይ የተመረኮዘ የሰላም ትግል ማድረጉ ነበር የሚበጃቸው። ከሻእቢያ ቀሚስ ስር መተኛት አዋርዶ ያጠፋቸዋል። ከግብጾች ጋር መስራት ከሕዝብ ጋር ለመጨረሻ ጊዜ ያቆራርጣቸዋል። አስቸኳይ የአቋም ለውጥ እንዲያደርጉ፣ ከሻእቢያ ጋር ግንኙነታቸውን እንዲበጥሱ፣ ከግብጽ የወሰዱትን ገንዘብ እንዲመልሱ፣ አገር ቤት የሚደረገውን ትግል እንዲደግፉ፣ ከሽግግር ምክር ቤት፣ ከሶሊዳሪቲ ንቅናቄ፣ ከኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባርና ከሸንጎ ጋር ሆነው አንድ በጋራ፣ በአንድ ድምጽ የሚናገር የዲፕሎማሲ ኮሚቴ እንዲያቋቁሞ ጥሪ አቀርባለሁ።
አልሰማም ካሉ፣ ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ የሚበጀውን እርምጃ ለመውሰድ ከተቆጠቡ፣ የግብጽና የሻእቢያ ጀሌዎች ከሆኑ፣ እንደነ በረከት ስሞን ግትርነትን ከመረጡ፣ በማንኛው መስክና ቀዳዳ የምንታገላቸው መሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል። እናከብራቸዋለን። ከዚህ በፊት ለከፈሉት መስዋእትነት ምስጋና እናቀርባለን። ነገር ግን ከሁሉም በላይ የአገራችንን ጥቅም እናስቀድማለን።
እንደለመዱት፣ ምክራችንን ከመስማት፣ በዳዊት ከበደ ላይ የሚያደርጉት አይነት "ግርማ ካሳ ወያኔ ነው" የሚል ክስ ሊጀምሩ ይችላሉ። ያን ቢያደርጉ አልደነቅም። አንዳንድ ድህረ ገጾችም አስተያየታችንን ላያስተናግዱ ይችላሉ። ነገር ግን እኛን መስደብና ማውገዝ፣ ድህረ ገጾች እንዲያግዱንም በነርሱ ላይ ግፊት ማድረግ፣ የተነሳውን አንገብጋቢ ጉዳይ አያጠፋውም። እርግጠኛ ነኝ ኢትዮጵያውያን፣ በተለይም ኢንፎርሜሽን በሽ በሽ በሆነበት ዘመን ሁሉንም በትክክል እንደሚገነዘቡ።
በመጨረሻ ኢሳትን በተመለከተ አንድ ነገር ጣል አድርጌ ላቁም። ከዚህ በፊት በኢሳት ላይ ብዙ ጠንካራ ተቃውሞዎችን አሰምተናል። ኢሳት ማሻሻያዎች እንዲያደርግ ግፊት አድርገናል። "የአገር ቤቱ ትግል ለምን በስፋት አይዘገብም?" እያለን ከሰናል።
ላለፉት ጥቂት ወራት ግን ነገሮች ተቀይረው፣ ለሰላማዊ ትግሉ ትልቅ ትኩረት ኢሳት ሰጥቶ፣ በአገር ቤት ዘጋቢዎች አሰማርቶ፣ ለሕዝቡ ትልቅ አገልግሎት እየሰጠ ነው። ይሄንን አደንቀናል። እንደግፋለንም። በዚህ አበራታች አሰራር ከቀጠለም ኢሳት ለትግሉ አሁን ከሚያደርገው የበለጠ ትልቅ ሚና ሊጫወት ይችላል ብዬ አምናለሁ። ኢሳት የኢትዮጵያውያን እንጂ የሌላ ሊሆን ስለማይገባውም፣ ኢትዮጵያውያን ልንደግፈውና ልንከባከበው ይገባል ባይ ነኝ።
ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ ከግብጽ ከተቀበሉት ግማሽ ሚሊዮን፣ 200 ሺህ ዶላር ለኢሳት እንደተመደበ ይናገራሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢሳት ማብራሪያ ጠይቂያለሁ። የተሰጠኝ መልስ በጣም አርክቶኛል። ኢሳት ከኢትዮጵያውያን እና ከዴሞክራቲክ የምእራባውያን አገሮች ብቻ እርዳታ እንደሚቀበል፣ እውነትን ለመዘገብ፣ በተቻለው መጠን የኢዲቶሪያል ፖሊሲውን በጠበቀ መልኩ እንደሚሰራ፣ ስህተቶች ካሉ ከአድማጮች የማሻሻያና የወቀሳ አስተያየቶችን እንደሚያስተናግድ፣ የማንም ድርጅት አገልጋይ እንዳለሆነ ነው የተገለጸልኝ። በመሆኑም ዶ/ር ብርሃኑ "ለኢሳት ተመድቧል" ያሉት ገንዘብ፣ እርሳቸው ማብራሪያ ይስጡበት እንጂ ከኢሳት ጋር ግንኙነት የለውም። በተሰጠኝ መልስ መሰረት፣ ኢሳት ከግብጽም ሆነ ከሻእቢያ ዱዲ አልተቀበለም። አራት ነጥብ።
ግርማ ካሳ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ጁን 23 ቀን 2013



