የመንግሥትን ስም ማጥፋት ማለት የክቡርነታቸውን…?
ፕ/ርመሰፍንወልደማርያም
ስም ምንድን ነው? መታወቂያነው፤ መጠሪያነው፤ ስም ማጥፋት ሲባል ስም አለ ማለትነው፤ ከስምም አልፎ የገነነ ስም አለ ማለት ነው፤ ስለዚህም ሊጠፋ የሚችለው የገነነ ስም ሲኖር ብቻ ነው ማለት ነው፤ ደራርቱ ቱሉ፣ ፋጡማ ሮባ፣ ኃይሌ ገብረሥላሴ የገነኑ ስሞች ናቸው፤ አንድ ሰው እነዚህን የገነኑ ስሞች አጠፋህ ቢባል ሊገባን ይችላል፤ ዘለቀ ወርዶፋ፣ አየለ ተከስተ ስማቸው ጠፋ ቢባል፣ መጀመሪያ የሚቀርበው ጥያቄ እነማን ናቸው? ዱሮስ የገነነ ስም ነበራቸው ወይ? የሚል ይሆናል፤ ስለዚህ መሰላሉን ያልወጣውን ሰው ውረድ ቢሉት ትርጉም የለውም።
ኃይሌ ገብረሥላሴ ስምነው፤ ዘርፈ ሽዋል ማናለብህ ስም ነው፤ ክቡር ፕሬዚደንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ስም ነው፤ ታደሰ ክፍሎም ስምነው፤ ደራርቱ ቱሉ ስምነው፤ ውቢቱ ማስረሻ ስም ነው፤ አዜብ መስፍን ስም ነው፤ ቴዎድሮስ ካሣሁን ስም ነው፤ አበበ ቶላ ስም ነው፤ ሚካኤል በላይነህ ስምነው፤ ሐጎስ በየነ ስም ነው፤ … እነዚህ ሁሉ ስሞች በመሆናቸው አንድ ቢሆኑም ከእያንዳንዳችን ጋር ባላቸው ግንኙነት ይለያያሉ፤ አንዳንዶቹን እናውቃቸዋለን፤ በተለያዩ መንገዶችም ቢሆን ከኑሮአችን ጋር የተያያዙ ስለሆኑ፣ ያስደስቱናል ወይም ያስከፉናል፤ ስለዚህም ሲያስደስቱን እናወድሳቸዋለን፤ ሲያስስከፉን እንወቅሳቸዋለን፤ ዋናው ጥያቄ የሚመጣው እዚህ ላይ ነው፤ ውቢቱ ማስረሻ፣ ዘርፈ ሽዋል ማናለብህ፣ ታደሰክፍሎም፣ አበበ ዋቅቶላ ማንእንደሆኑና ምንእንደሆኑ አላውቅም፤ ስለዚህ የነሱን ስም አንሥቼ የምደሰትበትም ሆነ የምከፋበት ምክንያት የለኝም፤ የኔአይደሉም፤ የሚያስደስቱኝና የሚያስከፉኝ የኔ የምላቸው ናቸው፤ የኔ የምላቸው እነማን ናቸው? ወድጄም ሆነ ተገድጄ ጭንቅላቴ ላይ በእግራቸው የቆሙ ሰዎች አሉ፤ እኔ የኔ ባልላቸውም እነሱ የራሳቸው፣ ዕቃቸው አድርገውኛል፤ የምነቅፋቸው ምራሳቸውን የኔ ሳያደርጉ እኔን የነሱ ስላደረጉኝ ነው፤ ስለዚህም የኔ የሆኑት ሁሉ ሳወድሳቸው አይከፍሉኝም፤ ስወቅሳቸውም አይከሱኝም፤ ሳወድሳቸው ደስ የሚላቸውና የሚኩራሩት ስወቅሳቸው ለምን ይቆጣሉ? የማወድሳቸውም ሆነ የምወቅሳቸው የራሴን ጥቅም እያሰብሁ መሆኑን ሳይ ገነዘቡት ቀርተው ነው? ወደ አራት ዓመት ግድም ሲሆነኝ ገና ጣልያን ሳይገባ አንዲት እግራቸው የማይንቀሳቀስላቸው አሮጊት ጎረቤት ነበሩ፤ ጠዋት ተሸክመው በር ላይ ያስቀምጧቸዋል፤ እንደ ልባቸው ሲለፈልፉ ይውሉ ነበር፤ በደንብ የማስታውሰው ‹‹ሠይፉ ዘለቀ … ተለቀለቀ! መስፍን ስለሺ ይበቃል ለሺ!›› እያሉ በየዕለቱ ይጮሁ ነበር፤ መስፍን ስለሺ የአራዳ ዘበኛ ሀነው በፈረስ ይታዩ ነበር፤ ሠይፉ ዘለቀ በድቅድቂት የሚሄዱነበሩ፤ በኋላ አንደሰማሁትና ትንሽ ትንሽ እንደማስታውሰው ለጣልያን ገብረው ውርደት ደርሶባቸው ነበርና የአሮጊትዋ ትንቢት የያዘ ይመስላል፤ ለማናቸውም ሴትዮዋ ተከሰሱ ሲባል አልሰማሁም።
ከስድሳ ዓመታት ያህል በፊት በኒውዮርክ አንድ ሰው በስም ማጥፋት ክስመሠረተ፤ ፍርድ ቤቱ ከሱንሲመረምር ከሳሽ ፖሊስ መሆኑን ተረዳ፤ ፖሊስ የሕዝብ አገልጋይ ነው፤ ስለሆነም በፖሊስ ላይ ከተገልጋዮቹ ሰዎች ትችት ቢቀርብበት የስም ማጥፋት አይሆንም፤ በተጨማሪም ዜጎች ሁሉ የማይገረሰስ ሀሳብን የመግለጽ መብት ስላላቸው፣ የሕዝብ አገልጋይ የሆነው ፖሊስ ስም እንዳይጠፋ ተብሎ ሕገመንግሥታዊውን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መገደብ አይቻልም በማለት የኒውዮርኩ ፍርድ ቤት በየነ፤ ፍርድ ቤቱ በብይኑ ላይ አንድ መሠረታዊ ሀሳብን አስገነዘበ፤ ስም ማጥፋት የሚባለው በተራሰው ላይ ወይስ በሕዝብ አገልጋይ ላይ የተፈጸመ መሆኑን መለየት እንደሚያስፈልግ አመለከተ፤ በአገራችንም አጼቴዎድሮስ ወንድምዋን የገደሉባት ሴት በሄዱበት ሁሉ እየተከተለች ንጉሠ ነገሥቱን ስትሰድብ፣ በሆነ ባልሆነው ሁሉ ገደል የሚጨምሩትና በእሳት የሚያቃጥሉት ንጉሠነገሥት ይቺን በንዴት የተቃጠለች ሴት ምንም አላደረጓትም! አጼምኒልክንም አሞካሽቶ ገጣጣ ያላቸው ምንም የደረሰበት አይመስለኝም፤–
በሰማይ የሚጠድቅ በምድር ያስታውቃል፤
ከከንፈሩ ተርፎ ጥርሱ ጣይ ይሞቃል፤
በአጼኃይለሥላሴ ዘመን በያመቱ በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ውስጥ ንጉሠነገሥቱ በግጥምም በመፈክርም በጣም ይሰደቡ ነበር፤ አንድም ተማሪ በስም ማጥፋት ሲከሰስ አላየሁም፤ በሌላ መንገድ ቀጥተዋቸው እንደሆነም አላውቅም፤ ግን ብዙዎቹ ተመርቀዋል።
ከላይ የተገለጹት ሁሉ ስለግለሰቦች ነው፤ ሕጉ በግለሰቦች ላይም ቢሆን በኒውዮርኩ ፍርድቤት ውሳኔ እንዳየነው፣ በኢትዮጵያም የወንጀል ሕግ አንቀጽ 612 የማያስቀጡ ትችቶችና ንግግሮች በሚል ርእስ ስር ተደንግጓል፤ በኒውዮርኩ ፍርድ ቤት የምንገነዘበው የከሳሹን የመክሰስ መብት የሚገድብ ሲሆን፣ በወንጀለኛ መቅጫው ሕግ ደግሞ የምንገነዘበው ሊከሰስ የታሰበውን ተከሳሽ ያለመከሰስ መብት የሚገልጽ ነው፤ ሁሉም በግለሰብ ደረጃ መሆኑን ልብ እንበል።
የመንግሥትን ስም ማጥፋት የሚባል የሌለ ነገርነው፤ ካለማወቅ የመጣ የሥልጣን ድፍረት ነው፤ ከላይ እንደተገለጸው በስም ማጥፋት ክስ ለመመሥረት ከስምም የገነነ ስም ያስፈልጋል፤ መንግሥት ምን ስም አለውና ስሙ ይጠፋል? የአጼ ኃይለ ሥላሴስም ይጠፋል፤ የመንግሥቱ ኃይለማርያም ስም ይጠፋል፤ የመለስ ዜናዊ ስም ይጠፋል፤ የመንግሥት ስም የሚጠፋው እንዴት ነው? ሦስቱም የተጠቀሱት ስሞች በአለፉት ሰባና ሰማንያ ዓመታት ውስጥ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በተከታታይ የሚያያይዛቸው ሁኔታ ነበረ፤ ወይም ባህላዊ የፈረስስም እየሰጠናቸው ብንሄድ አባጠቅል፣ አባገልብጥና አባሰንጥቅ ልንላቸው አንችል ይሆናል፤ ፈረሱ አንድ ነው፤ ጋላቢዎቹ የተለያዩ በመሆናቸው እያንዳንዳቸው እንደ የፍላጎታቸው ወይም እንደ የተግባራቸው ለጋላቢዎቹ የወጣላቸው ስም ይለያያል፤ አባ ገልብጥ ከርፋፋ ነው ብንል በስም ማጥፋት ለመክሰስ የሚችለው ጋላቢው ነው ወይስ ፈረሱ? አባ ሰንጥቅ ተንጋሎ የተፋለ ራሱ ከፋ አንደሚባለው ያለጅልነት ያለበት ነው ብንል ከሳሹ ማን ሊሆን ነው?
ሕግን የጭቆና መሣሪያ ማድረግ የተጀመረው በወያኔ ዘመን ነው፤ ዓይን ባወጣ ውሸት ‹‹ሕገ መንግሥቱን ሕገ አራዊት በሏል›› በማለት ፍርድ ቤትን አሳምኖ (ለፍርድ ቤት አስረድቶ አይደለም) በሐሰት ማስፈረድ የተቻለው በወያኔ ዘመን ነው፤ ሕጋዊ የፖሊቲካ ፓርቲ ስብሰባዎችን ‹‹መንግሥትን በኃይል ለመገልበጥ መዶለት›› ተብሎ እንደ ማስረጃ በግልጽ የተሠራውን ቪዲዮ ለፍርድ ቤት አቅርቦ ማሳመንና ማስፈረድ የተቻለው በወያኔ ዘመን ነው፤ በሰላማዊና ሕጋዊ የፖሊቲካ ትግል መንግሥትን ለመለወጥ መሞከር መንግሥትን በኃይል እንደ መገልበጥ ተደርጎ የታየውና ክስ የተመሠረተበት በወያኔ ዘመን ነው።
አንድ ነገር በጋዜጣ ተጽፎ አደባባይ ሲወጣ ከሦስት ነገሮች አንዱ ወይም ሁሉም ይከሰታሉ፤ አንዱ የተጻፈው ሐሰት ነገር ሊሆን ይችላል፤ ሁለተኛ አስተያየቱ የማይወደድ፣ ብዙ ሰዎች የማይቀበሉት ይሆናል፤ ሊሆን ይችላል፤ ሦስተኛ አንድ ግለሰብን በሰብእናው ወይም በሥራው የሚጎዳ ሊሆን ይችላል፤ እንግዲህ የተባለው ነገር ሐሰት ከሆነና ሐሰት ነው የሚለው ሰው እውነትን ይዞ ከሆነ ሐሰትን ለማጋለጥ ከባድ አይሆንም፤ ሐሰቱን ከእውነቱ ጋር አጋፍጦ ቀልጦ እንዲጠፋና እውነቱ ጎልቶ እንዲታይ ማድረግ ነው፤ ትክክለኛ ዳኛ ካገኙ እውነትና ሐሰት በማስረጃ ይሸናነፋሉ፤ እውነቱ ከታወቀ በኋላ አደባባይ በወጣው ሐሰት ጉዳት ደርሶብኛል የሚለው ተራ ዜጋ ከሆነ ካሣ የመጠየቅ መብት ይኖረዋል፤ የሕዝብ አገልጋይ ከሆነ ግን ሆን ተብሎ ለመጉዳት በክፋት እንደተጻፈበት ማስረጃ ማቅረብ ይኖርበታል፤ አንደኛው በዚህ ያልቃል።
ሁለተኛው የተነገረውን ወይም የተጻፈውን የአንድ ሰው አስተያየት በሕግ ወይም በግድ ማስለወጥ አይቻልም፤ በሕገመንግሥቱ የተደነገገው ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የግልአስተያቱን ወይም እምነቱን ለገለጸው ሰው ይመክትለታል፤ የእኔ አስተያየት ከአንተ አስተያየት ወይም የእኔ እምነት ከአንተ እምነት ይሻላል ብሎ በሕግ ክርክር ለማሸነፍ አይቻልም፤ ከመቶሃምሳ ዓመታት በፊት ሚል የሚባል የእንግሊዝ ፈላስፋ እንዳለው የዓለምሕዝብ በሙሉ ተሰብስቦ አንዱን ሰው አስተያየትህ ወይም እምነትህ ትክክል አይደለም ብሎ ሊረታው አይችልም።
ሦስተኛ የተባለው ነገር ግለሰብን በሰብእናው ወይም በሥራው ግልጽ በሆነ መንገድ ከጎዳውና ጉዳቱ ከተረጋገጠ፣ የተባለው ጎጂ ነገር በአደባባይ የተነገረው ሆን ተብሎ ለመጉዳት መሆኑ፣ ወይም ባለማወቅ፣ ወይም በስሕተት መሆኑ ተለይቶ መረጋገጥ አለበት፤ ካሣውም ሆነ የወንጀል ጥፋቱ ከዚያ በኋላ የሚወሰን ይሆናል።
ይህንን ሁሉ ከአልን በኋላ የመንግሥትን ስም ማጥፋት ወደሚለው ስንመለስ ከባድ የአስተሳሰብ ችግር ይገጥመናል፤ መንግሥት ከሕዝብ የተለየ ህልውና እንደሌለው አያከራክርም፤ በአንድ መንግሥት ስር የሚተዳደረው እያንዳንዱ ሰው ወደደም አልወደደም፣ ተቀበለውም አልተቀበለውም በዚያ መንግሥት ስር በመሆኑ የመንግሥቱ አካል ነው፤ ባዕድ አይደለም፤ ስለዚህም ግለሰቡ በመንግሥት ላይ የሚያቀርበው ነቀፌታም ሆነ ሐተታ ጉዳት ያስከትላል የሚባለው ለማንነው፤ አገር የሚባለው ውስጥ ግለሰቡ አለ፤ ሕዝብ የሚባለው ውስጥ ግለሰቡ አለ፤ መንግሥት የሚባለው ውስጥ ግለሰቡ አለ፤ ስለዚህም የመንግሥትን አመራር የሚነቅፈው ግለሰብ የመንግሥትን ስም አጠፋ ማለት ድርብርብ ስሕተቶችን ያሳያል፤ በመጀመሪያ ነገር መንግሥት ከግለሰቡ የተለየ ህልውናም ሆነ ስም እንደሌለው አለመገንዘብ ነው፤ ሁለተኛም ግለሰቡ መንግሥትን፣ ሕዝብን፣አገርን ከዚህም ሁሉ ጋር ራሱን ለማሻሻል በበጎ ፈቃድ ለበጎ ዓላማ የሚፈጽመውን ተግባር ወደ ክፋት መለወጥ አግባብ የለውም፤ ሦስተኛ የመንግሥት ስም ማጥፋት ብሎ ክስመመሥረት አንድ መንግሥትን ዘለዓለማዊ አድርጎ በመገመት ክፉስሕተት መፈጸም ነው፤ በደርግ ዘመን የአጼኃይለሥላሴ መንግሥት ይሰደብ ነበር፣ ዛሬ ደግሞ በወያኔ ዘመን የአጼኃይለሥላሴና የደርግ አገዛዞች ይሰደባሉ፤ መንግሥት ዘለዓለማዊ አይደለም፤ ባለመሆኑም ይወቀሳል፤ ይነቀፋል፤ይለወጣል፤ ይህንን ማድረግ የመንግሥት ባለቤት የሆኑ ትዜጎች መብትና ሥልጣን ነው።
የመንግሥትን ስም ማጥፋት የሚለው የስጋት መግለጫ ዘዴ የአምባ-ገነን አገዛዞችና ሎሌዎቻቸው የሚያቀነቅኑት ማታለያና ማደናገሪያ ነው እንጂ ሕጋዊ መሠረት የለውም፤ በማኅበራዊ ጉዳይ የእውነት ምንጩ ሕዝብ እንጂ መንግሥት አይደለም።
ግለሰቡ ራሱን ለመጉዳት አስቦ ጉዳት የሚያደርሰው በራሱ ላይ ነው ማለት ዋናውን ዓላማ መሳት ነው።