ነሀሴ 26ን በደቦ ሸኝተን፤ 2006 ዓ.ምን በተስፋ
አርኣያ ጌታቸው
የዘንደሮ ክረምት ከቀደምቶቹ በጥቂቱ ጠንከር ያለና ብዙዎችን በተለይም አዲስ አበቤዎችን እያማረረ ነው። ሌላው "በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ" የሚያስብለው ደግሞ የከተማዋ መንገዶች በአብዛኛው ጥገና ላይ መሆናቸውና በዚህም ሳቢያ የበርካቶች መኖርያና የንግድ ሱቆቻቸው መፍረሳቸው ነው።
ይህንን ሁኔታ በምናብ ለማየት ለምትፈልጉ ቅዳሜ ነሀሴ 4 ቀን 2005 ዓ.ም በወጣቺው ፋክት መጽሔት ላይ ፕ/ር መስፍን እንዲህ ሲሉ ገልጸዋታል "አዲስ አበባ በመሬት መናወጥ ፈራርሳ በመጠገን ላይ ያለች ከተማ ትመስል የለም እንዴ"። ብቻ ክረምቱም ወደማለፉ እየተቃረበ አዲሱንም ዘመን ለመቀበል ሽርጉዱ ተጀምሯል።
ምን ክረምቱ ብቻ ፖለቲካውም ክረምቱን ተከትሎ ከ8 ዓመታት በኋላ እሱም ጠንከር ያለ ይመስላል። ላለፉት ጥቂት ዓመታት በሀገር ውስጥ ሲደረጉ የነበሩት የፖለቲካ ፓርቲ እንቅስቃሴዎች በአመት ውስጥ እንኳ አንድ የሚረባ ለዜና የሚሆን ስራ ሳይሰሩ በውስጥ ጉዳያቸው ተጠምደው፤ የሀገሪቷን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ከሕብረተሰቡ እኩል ተመልካች መስለው ነበር። ምንም እንኳ የአሁኑ የፖለቲካ ጡዘት መነቃቃት የፈጠረው ግንቦት 25 በአዲስ አበባ የተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ነው ብንልም፤ ላለፉት 2 ዓመታት ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መልኩ ሰላማዊ ትግሉን በጽናት ሲያካሄዱ የቆዩት የሙስሊሞቹን እንቅስቃሴ ለአፍታም ሳንዘነጋ መሆን ይኖርበታል።
ወደዋናው የጽሁፌ ዓላማ ስመለስ፤ "የፊታችን ነሀሴ 26 ቀን 2005 ዓ.ም (ሴፕቴምበር 1 ቀን 2013 እ.ኤ.አ.) በሰማያዊ ፓርቲ አዘጋጅነት የሚካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ከመድረሱ በፊት ከኛ ምን ይጠበቃል?" የሚለውን መነሻ ሀሳብ ለማቅረብ ነው። ከዚህ ቀን ቀደም ብሎ አንድነት ፓርቲ ከአዲስ አበባ ውጪ የሚያደርጋቸውን በርካታ ሰላማዊ ሰልፎችን እና ስብሰባዎችን ሳልዘነጋ ነው። ይህ የነሐሴ 26ቱ ግን በይዘቱም፣ በጥያቄዎቹም፣ እንዲሁም በቦታውም ለየት ያለ በመሆኑ የተለየ ትኩረት ይሻል። በመጀመሪያ በፓርቲው የተነሱት ጥያቄዎች በቀጥታ ከድርጅቱ የተገኛኙ ሳይሆኑ አጠቃላይ ድርጅቱ እታገልለታለሁ ያለውን ሕብረተሰብ የሚወክሉ በመሆናቸውም ጭምር ነው።
የተነሱት አራት መሰረታዊ ጥያቄዎች ለማስታወስ ያህል፦
- የመጀመሪያው "ለፍትህና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መስፈን የሚታገሉ ጋዜጠኞችን፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችንና አባላትን በአሸባሪነት ስም ማሰርና ማሰቃየትን አጥብቀን የምንቃወም መሆኑንና እስረኞችንም እንዲፈታ"
- በሁለተኛ ደረጃ የተነሳው ደግሞ "የዜጎችን ሰብዓዊና ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን በመጣስ ለዘመናት ከኖሩበት ቦታ ኢሰብዓዊ በሆነ ድርጊት በታጠቁ ኃይሎች እንዲፈናቀሉ ማድረግ የዘር ማጥፋት ወንጀል በመሆኑ የድርጊቱ ፈፃሚዎች ለፍርድ እንዲቀርቡና የተፈናቀሉት ዜጎችም በአስቸኳይ ወደየመኖሪያቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ በመንግሥትም ሆነ በግብረ ሰናይ ድርጅቶች አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግላቸው"
- ሦስተኛው ጥያቄ "መንግሥት በኃይማኖታችን ጣልቃ አይግባ፣ የእምነት ሥርዓታችንና የኃይማኖት መሪዎቻችንን እምነታችን በሚፈቅደው ብቻ እናከናውን ያሉ የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮችን በአሸባሪነት ወንጀል በመክሰስ በእስር እንዲማቅቁና ሰብዓዊ መብታቸው እንዲጣስ መደረጉ እንዲቆምና ያነሷቸውም የእምነት ነፃነት ጥያቄዎቻቸው እንዲከበሩ"
- በአራተኛነት የተነሳው "የኑሮ ውድነትን፣ የሥራ አጥነትን እና በሙስና የተዘፈቁ የመንግሥት ሌቦችን የሚቆጣጠርባቸውን መንገዶችና ፖሊሲዎች በማውጣት ሀገራችንን ከቀውስና ዜጎችንም ከሰቆቃ እንዲያወጣ"
የሚሉ ናቸው። እነዚህ ጥያቄዎች በአብዛኛው የሥርዓቱ ተቃዋሚዎችን የሚወክል በመሆኑ፤ እንዲሁም ይህንን ጥያቄ ለመደገፍ እና ለዚህ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ድጋፍ ለማድረግ የማንንም የፖለቲካ ፍልስፍና ወይም አቋም የማይጻረር፤ ሰማያዊ ፓርቲም የራሱን የፖለቲካ ፍልስፍናም ሆነ አቋም ለመጫን ያልሞከረበት፤ በአጠቃላይ የእያንዳንዱ ሀገር ወዳድ ዜጋ መሰረታዊ ጥያቄዎች ናቸው ብዬ ስለማምን ነው።
ምንም እንኳ ፓርቲው ለነዚህ ጥያቄዎች ከመንግሥት መልስ እንዲሰጠው ለ3 ወር ጊዜ የሰጠው ቢሆንም፤ ሥርዓቱ ግን ይባስ ብሎ አፈናውን በማጠናከር ከማሰርና ከማፈናቀል በዘለለ ንጹኀን ዜጎችን አንድ ተራ ሽፍታ እንኳ የማይፈጽማቸውን በሕጻናት እና በእናቶች ላይ ተኩስ መክፈትና መግደል ጀምሯል።
ይህ ምናልባት ለኢህአዴግ መራሹ መንግሥት አዲስ ታሪኩ ባይሆንም፤ ከ20 ዓመታት በላይ ድርጅቱን በፍጹም አምባገነናዊነት የመሩት የአቶ መለስ ሞትን ተከትሎ ተስፋ ላደረጉ ጥቂቶች የሥርዓቱን መበስበስና የማይቀየር መሆኑን አሳይቷቸዋል። ይህንን ሥርዓት ከሕብረተሰቡ ጫንቃ ላይ ለማንሳት የሚደረገው የሰላማዊ ትግልም ከዚህ የሥርዓቱ ባህሪ አንጻር ፍጹም መራርና ከባድ መስዋዕቶችን ሊያስከፍለን እንደሚችል መገመት አያዳግትም።
ከነዚህ የሰላማዊ ትግሎች ውስጥ ግንቦት 25 ቀን 2005 ዓ.ም. የተጀመረው የሰማያዊ ፓርቲ እንቅስቃሴ አንዱ ነው። ፓርቲው ከሰልፉ በኋላ ሲያደርጋቸው የነበሩት እንቅስቃሴዎችም የሚቀጥለው እንቅስቃሴው ከሰልፍ በዘለለ የሰላማዊ ትግል መርኾችን እየተከተለ መሆኑን ያሳያል። ከዚሁ ጋርም ተያይዞ ነሐሴ 26 (ሴፕቴምበር 1) የሚደረገው ሰልፍ አዲስ አበባ ላይ መሆኑ፤ የሰልፉ ስኬታማነት አንድነት ፓርቲ በክልሎች ከጀመረው የማንቃት ስራ ጋር ተዳምሮ ለመላዊ የሀገሪቱ ህዝብ ትልቅ መነቃቃትንና ቁርጠኝነት ሊፈጥር ይችላል፤ "አዲስ አበባ ላይ ያካፋው ክልል ላይ ይዘንባል" እንዲሉ።
እንግዲህ ለዚህ ሰልፍ ወደ 15 ያህል ቀናት ይቀሩታል። በነዚህ በተቀሩት ቀናቶች የዚች ሀገር የቁልቁለት ጉዞ የሚያሳስባችሁ በተለይ ለኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች፤ ለድረ ገጽ ባለቤቶች እና ለማኅበር ድረ ገጽ አክቲቪስቶች ይህንን የነሐሴ 26ቱን ሰልፍ፤ ከግንቦት 25ቱ ሰልፍ ላቅ ባለና የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ጥያቄ ያካተተ ይሆን ዘንድ ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በተለየ መልኩ ያለባችሁን ኃላፊነት ከቡድናዊ ስሜት ወጥታችሁ በሀገራችን በአሁኑ ሰዓት ያለውን የሚዲያ ክፍተት በመሙላት የተጀመረውን ትግል አንድ እርምጃ ወደፊት እንድትገፉ በኢትዮጵያዊ ዜግነቴ እጠይቃለሁ። እንደምታውቁት በአዲስ አበባ ከሌሎቹ ከተሞች በተለየ የተሻለ የኢንተርኔት ስርጭት ያለበት በመሆኑ በዚህ ከተማ የሚገኘውን ማኅበረሰብ ለመቀስቀስና ለማስተማር ማኅበራዊ ድረ ገጾች የፈረጠመ አቅም አላቸው።
የዚህን ክረምት ድብታ ከፖለቲካ ድብታችን ጋር ነሐሴ 26ን ሸኝተን የሚቀጥለውን 2006 ዓ.ም. በተስፋ እና በመነቃቃት እንጀምረው ዘንድ የሁላችንንም ያላሰለሰ ጥረት ይጠይቃል። በድጋሚ የሚቀጥሉትን 15 ቀናት ሁላችንም በትጋት እንስራ።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
አርኣያ ጌታቸው
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ነሐሴ 2005 ዓ.ም.