Girma Moges ግርማ ሞገስግርማ ሞገስ 

በክፍል አንድ እንዳነበብነው የዝንጀሮዎቹ አምባገነን ጌታ ተርቦ ከመሞቱ በፊት የሚቀልቡት የፖለቲካ ኃይል ምንጮች ነበሩት። የፖለቲካ ኃይል ምንጮቹ መድረቅ ተርቦ እንዲሞት አድርገውታል። እንደ ዝንጀሮዎቹ አምባገነን ጌታ መንግሥትም የፖለቲካ ኃይል ምንጮች አሉት።

 

የአንድ መንግሥት የፖለቲካ ኃይል ምንጮች ከሞላ ጎደል የሚከተሉትን ያካትታል።

(1) መንግሥት ከህዝብ የሚያገኘው የገዢነት ክብር፣ ህጋዊነት፣

(2) መንግሥት ከቢሮክራሲው (ከመንግሥት ሰራተኞች) የሚያገኘው ትብብር መጠን፣

(3) መንግሥት ከሙያተኞች የሚያገኘው የቴክኖሎጂ ክህሎት እና ፕላን የማቀድ፣ የማስተዳደር እና የመሳሰለው ዕውቀት ትብብር፣

(4) የመንግሥት የአገር ኢኮኖሚ (የተፈጥሮ ሃብት፣ የገንዘብ፣ የኢንዱስትሪ፣ የእርሻ፣ የንግድ፣ የትራንስፖርት፣ የኮምኒኬሽን) ባለቤትነት፣

(5) በመንግሥት ስልጣን ላይ የሚገኙ መሪዎች በሚከተሉት ርዕዮተ ዓለም ወይንም በጎሳ ማንነታቸው የሚያገኙት የተወሰነ ህዝብ ክፍል ድጋፍ፣

(6) በመጨቆኛ እና በመቅጫ ተቋም ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራው ፖሊስ፣ ደህንነት እና የጦር ኃይል ለመንግሥት የሚለግሰው ትብብር።

እንደሚታወቀው 200 ያህል የሰላም ትግል ማራመጃ መሳሪያዎች (Weapons) አሉ። እነዚህ መሳሪያዎች በሶስት አብይ ክፍሎች ይከፈላሉ። እነሱም

(1ኛ) ተቃውሞና ማግባባት (Protest and Persuasion)፣

(2ኛ) ትብብር መንፈግ (non-cooperation) እና

(3ኛ) ጣልቃ መግባት (intervention) ይባላሉ። ዛሬ በኢትዮጵያ "እየሞትን ሳንገድል ህገ-መንግሥት እናስከብራለን" በሚል መርህ አንድነት ፓርቲ ከሰኔ ወር 2005 ዓ.ም. ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ ሲያኪያሂድ የነበረው እና መስከረም 19 ቀን 2006 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ የሚያጠናቅቀው "የሚሊዮኖች ድምጽ ለነፃነት" የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች፣ ፊርማ የማሰባሰብ እና ህዝባዊ ስብሰባዎች የማድረግ ዘመቻዎች (1ኛ) ተቃውሞና ማግባባት (Protest and Persuasion) ለሚለው የሰላማዊ ትግል ማራመጃ መሳሪያ ጥሩ ምሳሌ ነው።

የዝንጀሮዎቹ ትብብር መንፈግ (Non-cooperation) ለረጅም ጊዜ የተደላደለውን የዝንጀሮዎቹን አምባገነናዊ ጌታ የገዢነት ስልጣን (የፖለቲካ ኃይል) ምንጭ እንዳደረቀ እና ከትከሻቸው ላይ አሽቀንጥሮ እንደጣለላቸው በክፍል አንድ አይተናል። ስለዚህ የተለገሰን ትብብር መሉ በሙሉ መሳብ (መንፈግ) ይቻላል። በዚህ ክፍል ደግሞ ከፍ ብለው የተዘረዘሩትን የመንግሥት የፖለቲካ ኃይል ምንጮች ለማድረቅ ሰላማዊ ትግል ከሚጠቀምባቸው 200 ያህል የሰላም ትግል ማራመጃ መሳሪያዎች ውስጥ ትብብር መንፈግ (Non-cooperation) ምን ምን አይነት እርምጃዎችን እንደሚያካትት እና አቅሙ ምን ያህል እንደሆነ እንመረምራለን። እግረ መንገዴን (3ኛ) ጣልቃ መግባት (intervention) የተባለውን የሰላማዊ ትግል ማራመጃ መሳሪያ ባጭሩ አቀርባለሁ።

ትብብር መንፈግ ሲባል ፖለቲካዊ ትብብር መንፈግ (Political Non-cooperation) ወይንም ኢኮኖሚያዊ ትብብር መንፈግ (Economic Non-cooperation) ወይንም ማህበራዊ ትብብር መንፈግ (Social Non-cooperation) ወይንም ሁሉቱ ብቻ ወይንም ሶስቱም ማለት ሊሆን ይችላል። ትብብር መንፈግ የመንግሥትን የፖለቲካ ኃይል ምንጮች ለመቆጣጠር እና መንግሥት ለህዝብ ጥያቄ መልስ እንዲሰጥ ለማድረግ ይጠቅማል። አልፎም ትብብር መንፈግ የመንግሥትን የፖለቲካ ኃይል ክምንጩ ለማድረቅ እና መንግሥትን ከስልጣን ለማውረድ መድሃኒት ነው። ትብብር መንፈግ የተባለው የሰላማዊ ትግል ማራመጃ መሳሪያ ማስተላለፍ የሚፈልገው መልዕክት "እኛ (We the People) ከዚህ በኋላ መንግሥትን አንተባበርም!" የሚል ነው።

ትብብር መንፈግ የተባለው የሰላም ትግል ማራመጃ መሳሪያ አብይ ክፍል ሶስት ንኡሳን ክፍሎች አሉት። እነሱም፥ "(1) ማህበራዊ ትብብር መንፈጊያ ሰላማዊ ትግል ማራመጃ መሳሪያዎች (Social non-cooperation Weapons)፣ (2) ኢኮኖሚያዊ ትብብር መንፈጊያ ሰላማዊ ትግል ማራመጃ መሳሪያዎች (Economic non-cooperation Weapons) እና (3) ፖለቲካዊ ትብብር መንፈጊያ ሰላማዊ ትግል ማራመጃ መሳሪያዎች (Political non- cooperation Weapons)" የተባሉት ናቸው። አንድ ትክክለኛ ፕላን ያለው እና እነዚኽን መሳሪያዎች በጥንቃቄ መምረጥ እና መጠቀም የሚችል ሰላማዊ ትግል አምባገነን መንግሥትን ማስወገድ ይችላል። ህዝብ ትብብር የሚነፍጉ ዘመቻ ማድረግ ከጀመረ በመንግሥት የፖለቲካ ኃይል ምንጮች ላይ ቀጥተኛ ጥቃት መፈጸም መጀመሩን አንባቢ ልብ ሊል ይገባል። የትብብር መንፈግን ሶስት ንኡሳን ክፍሎች ባጭር ባጭሩ እንመልከት።

ንኡስ ክፍል አንድ ማህበራዊ ትብብር መንፈግ የሚለው ነው። በህብረተሰብ ውስጥ ማንኛውም ሰው ማህበራዊ ትብብር መንፈግ ይችላል። ከአንድ ሰው ጋር የነበርህን ሰላምታ መለዋወጥ፣ አብሮ ቡና ቤት መሄድ፣ ቤተሰቡ ሲታመም መጠየቅ እና የመሳሰሉትን ማህበራዊ ግንኙነቶች ካቆምህ ለግለሰቡ እና ለቤተሰቹ ማህበራዊ ትብብር ነፈግህ ማለት ነው። በህዝብ ላይ በደል ከሚፈጽሙ አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣኖች ጋር የነበረን ማህበራዊ ግንኙነቶች ማቋረጥ ግለሰቦቹን እና ቤተሰባቸውን እጅግ ሊጎዳ ይችላል። ማህበራዊ ማግለል ከሚያካትታቸው የሰላም ትግል ማራመጃ መሳሪያዎች ውስጥ የሚከተሉት ጥቂቶቹ ናቸው፥ (ሀ) ግለሰቦችን ማግለል (Ostracism of persons)፣ ምሳሌ፥ ለመብቱ በሰላማዊ መንገድ የሚታገልን ሰው የሚገድሉ ፖሊሶች ወይንም ባለሥልጣኖች የቤተ ክርስቲያን ወይንም የመስኪድ ግልጋሎት እንዳያገኙ (Excommunication) ማድረግ፣ ሃዘናቸው እና ሰርጋቸው ላይ አለመገኘት፣ (ለ) ለማህበራዊ ክንውኖች፣ ልማዶች እና ተቋሞች ትብብር መንፈግ ምሳሌ፥ የኢትዮጵያ የስፖርት ክለብ በሰራው ጥፋት ከአፍሪካ ክለብ ጨዋታዎች ቢታገድ፣ የተማሪዎች ትምህርት ማቆም። ይኽ የሰላማዊ ትግል ማራመጃ መሳሪያ ስራ ላይ ሲውል በዘር እና በሃይማኖት ክፍፍል እንዳይበከል የሰላም ትግል ሰራዊት ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት። በዚህ ረገድ ስህተት ከተፈጸመ መንግሥት ህዝብን ለመከፋፈል እና ትግሉን ለማዳከሚያ ፕሮፖጋንዳ ይጠቀምበታል።

ንኡስ ክፍል ሁለት ኢኮኖሚያዊ ትብብር መንፈግ ነው። ይኽ ንኡስ ክፍል ደግሞ በሁለት ይከፈላል። የመጀመሪያው ክፍል የንግድ ግንኙነት በማቋረጥ (የንግድ እገዳ ወይንም እቀባ በማድረግ) ከፖለቲካ ባላንጣ ወይንም ከፖለቲካ ባላንጣ ተባባሪ ጋር አለመገበያየት ነው። ይኽ የሰላማዊ ትግል ማራመጃ መሳሪያ ስራ ላይ ሲውል በዘር እና በሃይማኖት ክፍፍል እንዳይበከል የሰላም ትግል ሰራዊት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማደረግ አለበት። በዚህ ረገድ ስህተት ከተፈጸመ መንግሥት ህዝብን ለመከፋፈል እና ትግሉን ለማዳከሚያ ፕሮፖጋንዳ ይጠቀምበታል። ሁለተኛው ኢኮኖሚያዊ ትብብር መንፈግ ደግሞ ስራ ማቆም (Strikes) ሲሆን 22 ያህል የሰላም ትግል መሳሪያዎች አሉት። ምሳሌ፥ የእርሻ፣ የኢንዱስትሪ፣ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የትራንስፖርቴሽን (የባቡር፣ ያቶቢስ፣ የታክሲ፣ የአየር መንገድ፣ ወ.ዘ.ተ.)፣ የማዕድን፣ የመንግሥት መስሪያ ቤት (ቢሮክራሲ)፣ ወ.ዘ.ተ. ሰራተኞች ለየብቻቸው ወይንም በህብረት የሚያደርጉት የስራ ማቆም። ይኽ ሰላማዊ ትግል ቀጣይነት ካለው መንግሥትን ያደኸያል። ይኽ ከሆነ ደግሞ መንግሥት ለወታደሩ፣ ለጦሩ፣ ለቢሮክራሲው፣ ለካድሬው የሚከፍለው ደሞዝ በማጣት እና እንደቀድሞው መግዛት ያቅተዋል።

ንኡስ ክፍል ሶስት ደግሞ ፖለቲካዊ ትብብር መንፈግ ነው። ይኽ ንኡስ ክፍል 38 ያህል የሰላም ትግል መሳሪያዎች አሉት። ለናሙና ያህል ጥቂት እንመልከት። (ሀ) የፖለቲካ ታማኝነትን ከመንግሥት ነፍጎ ለተቃዋሚ መለገስ (Rejection of authority)፣ ምሳሌ፣ ዜጎች በየድረ ገጹ፣ በየመጽሐፉ፣ በየመጽሔቱ እና በየጋዜጣው ላይ የሚፅፉት የፖለቲካ ትችት፣ ኩነና እና የትግል ቅስቀሳ። የአገር ውስጥ የመንግሥት ወታደራዊ እና ሌሎች ባለሥልጣኖች እንዲሁም በውጭ የሚሰሩ ዲፕሎማቶች ስልጣናቸውን እየለቀቁ ሰላማዊ ትግሉን መቀላቀላቸው። ወ.ዘ.ተ. (ለ) ዜጎች ለመንግሥት የፖለቲካ ትብብር ሲነፍጉ (Citizens' non-cooperation with government)፣ ምሳሌ፣ ዜጎች በምርጫ ወቅት ድምጻቸውን በስልጣን ላይ ለሚገኘው ፓርቲ በመንፈግ ለተቃዋሚ ፓርቲ ሲለግሱ። ዜጎች ነፃነታቸውን አውጀው በሚሊዮኖች ሆነው በአደባባይ መንግሥት ከስልጣን እንዲወርድ ሲጠይቁ። ወ.ዘ.ተ. (ሐ) የመንግሥት ሰራተኞች ለመንግሥት የፖለቲካ ትብብር ሲነፍጉ (Government personnel's non-cooperation with government)፣ ምሳሌ፥ የአስተዳደር ስራ በተገቢ አለመስራት፣ የጸጥታ ክፍል ሙሉ ትብብር ሲነፍግ፣ ፖሊስ ፈልገህ እሠር የተባለውን ግለሰብ እያየ እንዳላየ ሲሆን፣ ፖሊስ ግደል ሲባል ከመግደል ወደ ሰማይ ሲተኩስ ወይንም እንቢ ሲል። ወ.ዘ.ተ. (መ) የአለም አቀፍ መንግሥታት ለመንግሥት የፖለቲካ ትብብር መንፈግ (International governmental action)፣ ምሳሌ፥ አለም አቀፍ ህብረተሰብ በስልጣን ላይ ለሚገኝ መንግሥት ህጋዊ ዲፕሎማሲያዊ እውቅናን ሲያዘገይ ወይንም ሲነፍግ ወይንም ሲገፍ ወይንም ሲያቋርጥ።

ጣልቃ መግባት (intervention) የተባለው ሶስተኛው አብይ የሰላም ትግል መሳሪያ ማራመጃ ክፍል አምስት ንኡሳን ክፍሎች ያሉት ሲሆን በአምስቱ ንኡሳን ክፍሎች ውስጥ ደግሞ ድምራቸው ከ40 በላይ የሚሆኑ ሰላማዊ መታገያ መሳሪያዎች አሉ። እነዚኽ የሰላም ትግል መሳሪያዎች በግልጽ የሚታዩ ናቸው። ለባለሥልጣኖችም የሚደቅኑት ፈተና ቀጥተኛ በመሆኑ ፈጥኖ መልስ የማግኘት እድላቸው ከፍተኛ ነው። ከባለሥልጣኖች የሚሰነዘረው ምላሽ ወከባ እና ቅጣት ሊሆንም ይችላል። ትብብር ከመንፈግ የሰላም ትግል መሳሪያዎች ይልቅ ጣልቃ መግባት የሰላም ትግል መሳሪያዎች አምባገነኖችን ይበልጥ ሊያስቆጣ እና ፈጣን ቅጣት ሊያስከትልም እንደሚችል የሰላም ትግል መሪዎች ሊገነዘቡ ይገባል። ጥቂት ምሳሌዎች እንመልከት፥

(ሀ) ሳይኮሎጂያዊ ጣልቃ ገብነት (Psychological intervention) ምሳሌ፥ የረሃብ አድማ በማድረግ ዲፕሎማቶች የመንግሥት ባለሥልጣኖችን እንዲያስጨንቁ ማድረግ ወ.ዘ.ተ.

(ለ) አካላዊ ጣልቃ ገብነት (Physical intervention) ምሳሌ፥ የካይሮ ሰላም ትግል ሰራዊት ጥያቄው እስኪመለስ ድረስ በነጻነት አደባባይ የድንኳኖች ከተማ መስርቶ መኖሩ (Sit-ins) ድረስ መኖር፣

(ሐ) ኢኮኖሚያዊ ጣልቃ ገብነት (Economic intervention) ምሳሌ፥ የባለሥልጣኖች ገንዘብ እና ንብረት እንዳይንቀሳቀስ ማድረግ፣ ወይንም አማራጭ ገበያ መጠቀም መጀመር፣ ምሳሌ በአላባማ አሜሪካ ሮሳ ፓርክስ በቀሰቀሰችው የሰላም ትግል አፍሪካዊ አሜሪካውያን በህገ መንግሥት የተጻፈው የእኩልነት መብታቸው እስኪከበር ድረስ በመንግሥት አውቶቢስ ከመጓዝ ፈንታ አማራጭ ትራንስፖርት በመጠቀም የከተማው መንግሥት ገቢ ዝቅ እንዲል ማድረጋቸው ወ.ዘ.ተ.

(መ) ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት (Political intervention) ምሳሌ፣ የመንግሥት አሰተዳደር በስራ እንዲወጠር እና የእለት ከእለት ስራውን መስራት እንዳይችል ማድረግ፣ የሰላዮችን ስም ይፋ ማድረግ። የሰላዮች ስም ይፋ ሲደረግ ስህተት እንዳይፈጸም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ትይዩ መንግሥት (Parallel government) መመስረት እና ሌሎች የፖለቲካ ጣልቃ ገብነቶች ማድረግም ይቻላል እንደ አስፈላጊነታቸው። በኢትዮጵያ ምርጫ ሲደረግ መንግሥት ድምጽ ማጭበርበር የለመደበት በመሆኑ ከአሜሪካ እና ከምዕራብ አውሮፓ ብዙ ምርጫ ታዛቢዎች በኢትዮጵያ ምርጫ ጣልቃ እንዲገቡ ማድረግ፣ እንዲሁም የሊቢያ ህዝብ ሰላማዊ ትግል እንደጀመረ ጋዳፊ በሊቢያ ህዝብ ላይ ጦርነት ሲያውጅ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያስተላለፈው ውሳኔ አስፈላጊ የሆነ የአለም ህብረተሰብ ዲፕሎማሲያዊ እና ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ነው። ቀጥለን ለጥቂት ጥያቄዎች መልስ በመስጠት ጥናታችንን እንቋጫለን።

በዚህ ጽሑፍ ሰላማዊ ትግል ብለን የምንጠራው እና የምናጠናው በስትራተጂስቱ ጋንዲ የዳበረው እና ዛሬ ደግሞ እነ ጂን ሻርፕ እና ሌሎች አያሌ የአልበርት አነስታይን የሰላም ትግል ምርምር ተቋም የፖለቲካ ሳይንስ ጠበብቶች ከፍተኛ ደረጃ ያደረሱትን በተግባር የተፈተነ ሰላማዊ ትግል ንድፈ አሳብ እና አፈጻጸም ነው።

አንዳድ ሰዎች ሰላማዊ ትግል እና ትጥቅ ትግል ተደጋጋፊ ናቸው ብለው ሲሰብኩ እንሰማለን። እውነቱ ግን ተቃራኒው ነው። እነዚህ ሁለት የትግል ስልቶች ተደጋጋፊዎች አይደሉም። ሰብዓዊ መብት የሚያከብር ሰላማዊ ትግል እና በግድያ የሚያምን ትጥቅ ትግል እንዴት ተደጋጋፊ ሊሆኑ ይችላሉ? እንዲያውም ትጥቅ ትግል ሰላማዊ ትግልን ስለሚበክል የሰላም ትግል ሰራዊት አደባባይ ሲወጣ የሰው ደም ማፍሰስ የሚያስደስታቸው ወይንም በመንግሥት አረመኔ ተግባር የተበሳጩ የዋሆች ወይንም በትጥቅ ትግል እምነት የተወናበዱ በውስጡ ሰርገው በመግባት በፖሊስ ላይ ግድያ ፈጽመው ሰላማዊ ትግሉን እንዳያስመቱት ጥንቃቄ እንዲያደርግ እንመክራለን። የታጠቁት ግለሰቦች ቀደም ብለው የተዘጋጁበት ጉዳይ ስለሆነ ጥቂት ጥይቶች ተኩሰው በፖሊስ ላይ ጉዳት ካደረሱ በኋላ ሮጠው ያመልጣሉ። ፖሊስ በምላሽ የሚለቀው የጥይት እሩምታ የሚያርፈው ግን በህግ አክባሪው ሰላማዊ ሰልፈኛ ላይ ነው። ሞርሲ ከስልጣን ከወረደ በኋላ በግብጽ በተደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች ያየነው ይኽንኑ ነው። መንግሥት ህግ አክብረው ሰልፍ ለሚወጡ ዜጎች ጥበቃ የማድረግ ህገ-መንግሥታዊ ግዴታ አለበት።

እነዚሁ የትጥቅ ትግል አራማጆች ውስጥ አንዳንዶች በድፍረት ካለምንም ሃፍረት ሰላማዊ ትግል ብቻውን አምባገነን ገዢዎችን ከስልጣን ያወረደበት አገር የለም በማለት ይጽፋሉ። ይሰብካሉ። ሃቁ ግን ተቃራኒው ነው። የግብጹ ሙባረክ፣ ከስልጣን የተወገደው በሰላማዊ ትግል መሆኑን ከመቼው እንደረሱት የሚገርም ነው። ሲጽፉ አውቅወ ረስተውት ይሆናል።

ረቀቅ ያሉት የዚሁ የትጥቅ ትግል አራማጅ ክፍል ሰዎች ደግሞ ዴሞክራሲን በመጨመር ሰላማዊ ትግል ብቻውን አምባገነን ከስልጣን አውርዶ ዴሞክራሲ ያስገኘባቸው አገሮች ሰለመኖራቸው የታሪክ መረጃ ስለመኖሩ እንደሚጠራጠሩ ሲሰብኩ እንሰማለን። እውነቱ ግን ተቃራኒው ነው። ብራዚል ዴሞክራሲ አገር የሆነችው በትጥቅ ትግል ወይንም በከተማ የትጥቅ አመጽ ሳይሆን ዛሬ እነ አንድነት በኢትዮጵያ በሚያካሂዱት ሰላማዊ ትግል አይነት ነው አምባገነን አስወግዳ ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር ያደረገችው። እርግጥ በአቅም ደረጃ የኢትዮጵያው ገና በወጣትነት እድሜው ላይ ነው። ከፍተኛ የአቅም ግንባታ ዘመቻ ይጠበቅበታል። ምስራቅ አውሮፓ አገሮችም አምባገነኖችን አስወግደው ዴሞክራሲ የሆኑት በትጥቅ ትግል አይደለም። ሰርቢያ አምባገነኑን ሞልሶቪች ከስልጣን አስወግዳ ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር ያደረገችው በትጥቅ ትግል አይደለም። የሞሊሶቪች መንግሥት በስልጣን ላይ ሳለ እና ከስልጣን ከተወገደ በኋላ በህብረት ሰለሚያደርጉዋቸው እና መቼ ነፃ ምርጫ እንደሚጠሩ በሚያስማማቸው ፕሮግራም ዙሪያ አስራ ስድስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ህብረት መሰረቱ። በህበረት ህገ-መንግሥት የማስከበር ሰላማዊ ትግል ጀመሩ። ምርጫ ሲመጣ በህብረት ተወዳደሩ። ድምጻቸው ሲሰረቅ ደግሞ በህብረት ሆነው "የህዝባቸውን ድምጽ ያስከበረ" ሰላማዊ ትግል አደረጉ። ደምጽ ለማስከበር ያደረጉት ሰላማዊ ትግል የሞሊሶቪችን መንግሥት የፖለቲካ ኃይል ምንጭ አደረቀ።

የፖለቲካ ኃይሉ በግልጽ ሲደርቅ ያስተዋሉት የቀድሞ ታማኞቹ የፖሊስ እና የጦር ኃይል ሹማምንት ሳይቀሩ ከዱት። ሞሊሶቪች ሽንፈቱን ከመቀበል የተሻለ አማራጭ እንደሌለው አምኖ ሽንፈቱን በሰላም እንዲቀበል አደረጉ። ከዚያ ከምርጫው በፊት በተስማሙት መሰረት ሰርቢያን ለሶስት ወይንም ለአራት አመቶች ያህል ጊዜ በህብረት ከገዙ በኋላ በሰርቢያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነፃ ምርጫ ጠርተው 16ቱ ፓርቲዎች ተፎካከሩ። አብዛኛውን የህዝብ ድምጽ ያገኘው ፓርቲ ገዢ ፓርቲ ሲሆን የቀሩት ተቃዋሚ ፓርቲ በመሆን የፓርላማ ትግል ጀመሩ። የሰርቢያ ዴሞክራሲ አራማጅ ፖለቲከኞች ይኽን ሁሉ ሰላማዊ ትግል ሲያደርጉ አንድም ቀን ስለትጥቅ ትግል ተወያይተውም አያውቁም። እርግጥ የሰርቢያ ተቃዋሚዎች FM ሬዲዮ ነበራቸው። ስለዚህ ሰላማዊ ትግል በፍጹም ከማንኛውም አይነት ትጥቅ ትግል ወይንም የከተማ የትጥቅ አመጽ እርዳታ እና ትብብር እንደማይሻ ከወዲሁ በማክበር እናስታውቃለን። ሰላማዊ ትግላችን በጠብ መንጃ፣ በቦንብ፣ በታንክ፣ በመድፍ እና በመሳሰሉት የግድያ መሳሪያዎች እንዲበከልብን አንፈልግም። ይኽን ልዩነት አንባቢ ሊገነዘብ ይገባል።

በመጨረሻ አንድ መንግሥት ካለ ህዝብ ታዛዥነት (Obedience)፣ ትብብር (Cooperation) እና አሜን ብሎ መገዛት/መገበር (Submission) በስልጣን ሊቆይ እንደማይችል የዝንጀሮዎች ጌታ ማስረጃ መሆኑን ለአንባቢ በማስታወስ የዛሬውን ጥናታችን እንደመድማለን።


ግርማ ሞገስ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ