ተከብሮ ያላስከበረ ሕገ-መንግሥት
ይድነቃቸው ከበደ
ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም ሕገ-መንግሥቱ የፀደቀበት ቀን ነው። ይህንንም ተከትሎ በመንግሥት አሳሳቢነት እልፍ ሲልም አስገዳጅነት ህዳር 29 በየዓመቱ ከተለያዩ ጎሳ የተወጣጡ ሰዎች ተሰባስበው በመንግሰት ሹማምንቶች ፊት በአደባባይ ከበሮ የሚደለቅበት ቀን ነው።
ይሁን እንጂ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊያን መልካም ፍቃድና ተሳትፎ ባልታየበት የፀደቀው ሕገ-መንግሥት በብዙሃን ዘንድ ተቀባይነቱ ጥያቄ ውስጥ የገባ ነው። በዚህም መሠረት ከቃሉ አጠቃቀም ጀምሮ እስከ አከባበሩ ክብረ በዓል አብዛኛው ሰው እኔንም ጨምሮ ግድ አይሰጠንም።
"ይህ ሕገ-መንግሥቱን የመነዳ ተግባር ነው!!!" ከገዢው መንግሥት ተደጋግሞ የሚሰማ ለመፈረጅ ወይም ለመከሰስ የሚጠቀሙበት ቃል ነው። አንድ ወዳጄ እንዲህ አለኝ "ይህ ሕገ-መንግሰት ዝም ብሎ የተደረደረ ብሎኬት ነው እንዴ የሚናደው?" በማለት ሲተች ሰምቸዋለው። በመናድ እና ደግፎ በማቆየት ላይ የተመሠረተሁን ሕገ-መንግሥት እጅግ በጣም ብዙ ነገር ተብሎለታል።
እየተንገዳገደ ያለው ሕገ-መንግሥት ከአፀዳደቁ ጀምሮ የሚቀሩት ድንጋጌዎች መኖራቸው ለማንም ግልፅነው። ቢሆንም ፀድቆ በተግባር ላይ የሚገኘው ሕገ-መንግሥት ዋጋ እንዳይኖረው እያደረገ ያለው የገዢው መንግሥት አካሄድና ተግባር መሆኑ በአጭሩ ለማሳየት እሞክራለው።
1ኛ. መንግሥት በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፤ ኃይማኖትም በመንግሥት ጣልቃ አይገባም የሚለው በሕገ-መንግሥት አንቀጽ 11 ንዕሱ አንቀፅ 3 ተደንግጎ የሚገኝ ነው። ይሁን እንጂ ገዢው መንግሥት በኃይማኖት ላይ ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት እየፈፀመ ይገኛል፤ ለዚህም ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በእስልምና አይማኖታ እየተፈፀመ ያለው በደል ነው። በደሉ በይፋ የወጣ ሲሆን በተለይ ለእምነታችን እንቢኝ ያሉ ለሞት፣ ለእስርና ለእንግልት ተዳርገው ይገኛሉ። በተጨማሪ በኦርቶዶክስ እምነት ውስጥም ጣልቃ ገብነቱ እንደተጠበቀ ነው። ገዳማትና አድባራት በልማት ስም ፈርሰዋል የተቀሩት ቦታቸው ተጎምዶ ተወስዶል በዚህም ምክንያት የኃይማኖት አባቶችና ጥቂት የማይባሉ የእምነቱ ተከታዮች ለእስርና ለእንግልት ተዳርገዋል።
ከምንም በላይ ደግሞ በሁሉም በተለይ በኦርቶዶክስና በእስልምና የኃይማኖቱ መሪዎች (አባቶች) ሹመታቸው ከሚያመልኩት አምላክ እና ከምዕመናኖ የመነጨ ሳይሆን በመንግሥት ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት የተፈፀመ ነው።
2ኛ. የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልፅ በሆነ መንገድ መከናወን አለበት፡፤ በሕገ-መንግሥት አንቀጽ 12 ንዕሱ አንቀፅ 1 ተደንግጎ የሚገኝ ነው። ቢሆንም ከታችኛው የስልጣን እርከን ከሆነው ከቀበሌ ጀምሮ እስከላይኛው የመንግሥት ባለስልጣናት አማከኝነት የሚከናወኑ የመንግሥት አሰራሮች ግልፅነት እጅግ በጣም ጠባብ ነው። በመሆኑም ህብረተሰብ በአገሩ ጉዳይ ቀጥተኛ ተሳታፊ በመሆን በመንገስት አሠራር ላይ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አልተደረገም።
በዚህም ምክንያት የመንግሥት አሠራር ለሙሱና የተጋለጠ ነው፤ ሙሱና በአሁን ወቅት በአገራችን ህጋዊ እስከመሆን ደርሷል። በመሆኑም ማናኛውም የመንግሥት ኃላፊ ኃላፊነቱን ወይም ስልጣኑን መሠረት አድርጎ ሲበድል እንጂ ለበደሉ ተጠያቂ ሲሆን አልታየም። ስለዚህም የመንግሥት አሠራር በየትኛውም ደረጃ ለህዝብ ግልፅ አይደለም ይህ ደግሞ የሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው።
3ኛ. ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነትና የነፃነት መብት አለው። ተብሎ በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 14 ተፅፎ ይገኛል። ነገር ግን የሰው ደህንነትን ለመጠበቅ የተቋቋመው የደህንነት መስሪያ ቤት በየደኑና በየጫካው የስንቱን ሰው ህይወት እንዳጠፋና የአካል ጉዳት እንዳደረስ የሚያውቀው ያውቀዋል። በተጨማሪ ይህ የነፃነት መብት ገዢው መንግሥት በችሮታ ወይም በፍቃዱ የሰጠን እንጂ ሰው በመሆናችን ያገኘነው መብት እንዳልሆነ በሚያሳብቅ መልኩ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነትና የነፃነት መብት በገዢው መንግሥት መልካም ፍቃድ ላይ የተመሠረተ እስከሚመስል ደረስ ተደርሷል።
4ኛ. ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት፣ ኢሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት አለው። የሚለው በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 18 ላይ ይገኛል፤ ይህ የሕገ-መንግሥት ድንጋጌ መሸራረፍ ሳይሆን መገርሰስ የሚጀምረው በሕገ-መንግሥቱ በተቋቋመው በህግ አስፈጻሚው አካል ነው።
በመሆኑም ክብርን ለማወረድና ጭካኔን ለማሳየት የሰለጠኑ አሰቃዮችና ማሰቃያ ቦታዎች መኖራቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው። ነገሩን ለማነፃፀር እንዲረዳ ፖለቲከኛ ወይም በህግ ጥላ ስር ያለ ሰውን ይቅርና ስታዲዮም እግር ኳስ ለመመልከት ወራፋ የሚጠብቅ በወረፋ ምክንያት ለተነሳ አለመግባባት ፖሊስ እንዴት አድርጎ እንደሚቀጠቅጥ ዱላውን የቀመሰ ያውቃል።
5ኛ. በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸውን በሚጠብቅ መልኩ የመያዝ እና ከሰዎች ወይም ከጠያቂዎቻቸው የመገናኘት መብት አላቸው። በማለት በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 21/1እና2 ተፅፎ ይገኛል። ይሁን እንጂ ነፃ ጋዜጠኞች እና የፖለቲካ እስረኞች አያያዛቸው ክብርን ከመንካት አልፎ በህይወታቸው ላይ አደጋ የሚያስከትል ነው። በተጨማሪ ከቤተሰብ፣ ከወዳጅ መጠየቅ የማይሞከር ነገር ነው፤ የመጠየቅ እድል ያላቸው እስረኞች እድላቸው በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ነው።
6ኛ. ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የአመለካከት እና ሐሳብን በነፃ የመያዝና በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ የመግለፅ ነፃነት አለው። የሚለው በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 29 ተፅፎ ይገኛል። በእርግጥ ይህ መብት ገደብ ሊጣልበት እንደሚችል በሕገ-መንግሥቱ ላይ ተገልፆ የተቀመጠ ሲሆን ገደብ ግን መሠረታዊ የሆነውን መረጃን የመስጠት እና የማግኘት እንዲሁም አስተሳሰብ ላይ ወይም አመለካከት ላይ ውጤት እንደማይኖረው በሕገ-መንግሥቱ ተገልፆ ይገኛል።
ይሁን እንጂ አሳብን በነፃ ማሰብና ማንሸራሸር በአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ እጅግ አዳጋች ነው። ነፃ አሳብ የሚንሸራሸርባቸው ነፃ ጋዜጦችና መፅሔቶች ምን ያህል አሉ? እርግጥ ነው ገብያውኑ መሰረት ያደረጉ መዝናኛ ላይ ያተኮሩ መፅሔትና ጋዜጣ ለቁጥር በዝተው ይሆናል። ግን ሁሉ ነገር በአገር ነው የሚያምረው! ታዲያ ስለ አገር በነፃ አሳብ የሚንሸራሸርበት መፅሔትና ጋዜጣ ምን ያኸል ነው? ጋዜጠኞችን በማሰቃየት፣ በማሰር እና እንዲሰደዱ በማደረግ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ መጥፎ ሪከረድ አስመዝግባለች። መንግሥትን ተችቶ የፃፈና ፁሁፉ የወጣበት ጋዜጣ ወይም መፅሔት ጨምሮ ሁሉም ተጠራርጎ ቃሊቲ የሚገባበት ወይም አደገኛ ዛቻና መስጠንቀቂያ የሚሰጥበት ደረጃ ላይ ተደርሷል።
7ኛ. ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሣሪያ ሳይዝ ሠላማዊ ሠልፍ እና ስብሰባ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው። ተብሎ በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 30/1 ላይ ይገኛል። ለዚህ ማሳያ የሚሆን የቅርብ ጊዜ አይን ያወጣ የሕገ-መንግሥት ጥሰት ማቀረብ ይቻላል። በሳውዑዲ በሚገኙ ወገኖቻችን ላይ እየተፈፀመ ያለው ግፍና በደል ይቁም፣ ይህንንም የፈፀሙ ለፍርድ ይቅረብ በማለት አቤቱታ ለማቅረብ የተጀመረው ሠላማዊ ሠልፍ በፖሊስ ዱላ እና እስራት ነው የተጠናቀቀው። በተጨማሪ በመንግሥት እየታየ ያለው የአስተዳደር ብሉሹነት ለማመልከት እና ምላሽ ለማገኘት የተጠሩ የተለያዩ የተቃውሞ ሰልፎች እና ስብሰባዎች በመንግሥት ቀጥተኛ ትእዛዝ ተከልክሏአል። ሠላማዊ ሰልፍ ማድረግ እና አቤቱታ ማቅረብ መብት ነው! በማለት ክልከላውን ወደ ጎን በመተው አደባባይ ለመውጣት የሞከሩ ለእስርና ለድብደባ ተዳርገዋል። በመሆኑም የተቃውሞ ሠልፍና ስብሰባ በማድረግ አቤቱታ በኢትዮጵያ ማድረግ የሞት ሽረት ትግልና ጥያቄ ከሆነ ሰንብቷል።
8ኛ. የዳኝነት አካል ከማንኛውም የመንግሥት ባለስልጣን ሆነ አካል ተፅዕኖ ነጻ በመሆን በሙሉ ነፃነት ከህግ በስተቀር በሌላ ሁኔታ አይመሩም። በማለት በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 79 እና በተከታዮቹ ንዑስ አንቀፅ ሰፍሮ ይገኛል። ይሁን እንጂ በየትኛውም ደረጃ የሚገኙ ዳኞች የመንግሥት አስፈፃሚ አካል ከሆነው ነው ሹመታቸውን የሚያገኙት። በመሆኑም ከመንግሥት ጋር ቀጥተኛ ግኝኙነት ያላቸው የፍርድ ውሳኔዎች ምንያኽሉ በህግ እና በህሊና ላይ የተመሠረቱ ናቸው? በተለይ የህሊናና የፖለቲካ እስረኞች የፍርድ ሂደታቸው ምን ይመስል ነበር? እነዚህን እና መሰል ዳኝነቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት በሕገ-መንግሥቱ የሰፈረው ነጻ ዳኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው።
9ኛ. የሀገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት የጎሳዎች ሚዛናዊ ተዋጽኦ ያካተተ ይሆናል። ተብሎ በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 87/1 ተደንግጎ ይታያል። ነገር ግን በየድንበር እና በተልኮ ጭዳ ከሚሆነው ውጪ አብዛኛው የሠራዊቴ አባል እና አዛዥ የአንድ ጎሳ ስብስብ ነው። ስለዚህም ሠራዊቱ የማነው የኢትዮጵያ ወይስ ወደሚል ጥያቄ እያመራ ይገኛል።
10ኛ. በየደረጃው ትክክለኛ ምርጫ እንዲካሄድ ከማንኛውም ተጽእኖ ነፃ የሆነ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ይቋቋማል። የሚለው በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 102 ላይ ይገኛል። ይሁን እንጂ የምርጫ ቦርድ ሃላፊዎች ሹመታቸው ከመንግሥት መልካም ፍቃድ የመነጨ ሲሆን አሰራራቸውም ለገዥው መንግሥ በእጅጉ በጣም ያደላ ነው። ስለዚህም ምርጫ ቦርድ ሕገ-መንግሥቱን መሠረት አድርጎ ነጻ እና ገለልተኛ ነው ለማለት ከበድ ድፍረትን የሚጠይቅ ነው።
በመሆኑም እነዚህ እና መሰል የሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌዎች ጥሰት ወይም በእነሱ ቋንቋ የመንድ ተግባር እየተፈፀመ ያለው በሕገ-መንግሥቱ በየወንዙ ዳር የሚማማለው ገዥው መንገስት ነው። ሕገ-መንግሥት የበላይ ህግ ነው። ማንኛውም ህግ፣ ልማዳዊ አሰራር እንዲሁም የመንግሥት ባለስልጣን አሰራር ከሕገ-መንግሥቱ የሚቃረነረ ከሆነ ተፈፃሚነት አይኖረውም። የሚለው አንቀፅ 9 ንዑስ አንቀፅ 1 የገዥው መንግሥት ደራሽ ውሃ ጠራርጎ ወስዶታል። ስለዚህም የብሔሮ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የሚለውን መጠሪያ ስም በመስጠት ከበሮ ተይዞ የሚደለቅለት እና የሚከበረው ሕገ-መንገሥት መልሶ ካላስከበረ ፌሽታው እና ቀረርቶው ከምን የመነጨ ነው?
ይድነቃቸው ከበደ (የሰማያዊ ፓርቲ የሕግ ጉዳይ ኃላፊ)