“ሠላማዊ ትግልን ያልፈቀዱ አመጽን ይጋብዛሉ” ጆን ኤፍ ኬኔዲ
ጽናት ፍቅሩ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)
የታላቋ አሜሪካ መሪ የነበሩት ጆን ኤፍ ኬኔዲ “those who make peaceful revolution impossible will make violent revolution inevitable” ብለው ነበር። በግርድፉ ስተረጉመው “ሠላማዊ ትግልን ያልፈቀዱ የአመጽ ትግልን ይጋብዛሉ” የሚል ስሜት ይሰጣል። አባባላቸው እውነት ነው። የአመጽን መንገድ መከተል በጣም ቀላል ነው። እጅግ ከባዱ ሠላማዊ ትግልን መከተሉ ነው። በተለይ እንደ አፍሪካ ባለ አህጉር ሠላማዊ ትግል ብዙ መስዋዕትነትን ያስከፍላል።
የአፍሪካ መሪዎች ከሰው ዘር የተፈጠሩ አይመስሉም፤ የሰው ልጅ የያዘውን ርህራሄ መያዛቸውን እስክንጠራጠር ድረስ ዜጎቻቸውን ይገድላሉ። ከኢትዮጽያ ብንጀምር የመለስ ዜናዊ መንግሥት በግንቦት ዘጠና ሰባት ምርጫ ከሁለት መቶ ያላነሱ ወጣቶችን መግደሉ በመረጃ ተረጋግጧል። የኬኒያው ምዋይ ኪባኪም መንግሥት ከአንድ ሺ አምስት መቶ በላይ ሰዎችን ገድሏል። የሙጋቤም መንግሥት በተራው እየገደለ ነው። እነዚህ መሪዎች የሠላማዊ ትግልን ጠቀሜታ ገደል የከተቱና የአመጽ ትግልን የጋበዙ ናቸው።
ታላቁ የነፃነት አርበኛ ኔልሰን ማንዴላ፣ በሠላማዊ ትግል አገሩንና ህዝቡን ነፃ ማውጣት ሳይችል ሲቀር ወደ አመጽ መንገድ አቀና። ሌሎች የሠላማዊ ትግል አርበኞች የሚባሉት ማርቲን ሉተር ኪንግ እና ማህተመ ጋንዲ በአጋጣሚ ይታገሏቸው የነበሩት ኃይሎች የሰብዓዊ መብትን የሚያከብሩና ምክንያታዊ ክርክር የሚገባቸው ሆነው ስለተገኙ በሠላማዊ ትግል እምነታቸው ጸንተው በመቆየት ለድል በቁ። የበርማዋ ታጋይ አሳንሱቺ እስካሁን ድረስ በቁም እስር ላይ ስትገኝ የቅንጅት መሪዎች የነበሩትም እንዲሁ ለሁለት ዓመት ዘብጥያ ወረዱ።
ወደ ቤታችን ስንመጣ፣ የቅንጅት መሪዎች ከነበሩት መካከል አንዳንዶቹ “ሠላማዊ ትግል ወይም ሞት” ብለው የእነማርቲን ሉተርን መንገድ ለመጓዝ ወሰኑ፤ ሌሎች ደግሞ የማንዴላን መንገድ የተሻለ ሆኖ አገኙት። የማንዴላን መንገድ ለመሄድ የወሰኑት ግንቦት ሰባት የተባለ ድርጅት ማቋቋማቸውን ይፋ አድርገዋል። ሁለቱም ጎዳናዎች አቀበት እና ቁልቁለት የበዛባቸው እንደሚሆኑ እገምታለሁ። የትኛው መንገድ ከታሰበው ቦታ በፍጥነት እንደሚያደርስ ባላውቅም፣ በሠላማዊ ትግል ትንሹ የለውጥ ማምጫ ጊዜ ቢያንስ አምስት ዓመት መሆኑን አውቃለሁ። ለውጥ ለማምጣት በየአምስት ዓመቱ ምርጫ እስከሚደረግ ድረስ መጠበቅ ግድ ይላል። በምርጫው ካላሸነፉ ዕድሜን እየቆጠሩና ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ነኝ እያሉ መጓዝ ነው። ከታሰበው ግብ ለመድረስ የሚያስችል መተማመኛ በእጅ ላይ የለምና።
የአመጽ ትግልም እንዲሁ ቁርጥ ያለ ቀን አይሰጥም። በደንብ ከታገሉ በአንድ ቀን ወይም በአንድ ዓመት ለውጥ ሊመጣ ይችላል፣ አልያ ደግሞ አስር ዓመትም ሊወስድ ይችላል። የአመጽ ትግል ጥሩነቱ የጊዜ ሰሌዳው በታጋዩ እጅ መሆኑ ነው። የትግሉን ዕድሜ የሚያሳጥረውም ሆነ የሚያጓትተው ራሱ ታጋዩ ነው። ጥሩ መታገልና ህዝብን ማታገል ከተቻለ ከታሰበበት ዓላማ በአጭር ጊዜ መድረስ ይቻላል። በርግጥ ታሪክ የሚመሰክረው የአምጽ ትግል ረጅም ጊዜ የሚወስድ መሆኑን ነው።
እዚህ ላይ ትንሽ ቆም ልበልና ስለዚህ ጽሑፍ እድገት ልናገር። ጽሑፉን ያዘጋጀሁት በግንቦት 7 ድረ ገጽ እንዲወጣ አስቤ ነበር። በኋላ ግን ኩችዬ የተባሉ ብዕረኛ “’ሠላማዊ ወይስ ትጥቅ?’ - እንካ ስላንቲያዎቹ!” በሚል ርዕስ በሚጣፍጥ ቋንቋ በግንቦት 7 ዓላማና በመሪዎች ባህሪ ላይ ጥያቄ የሚጭር ጽሑፍ ስላቀረቡ፣ ለእርሳቸው በቀጥታም ባይሆን በዘወርዋራው መልስ ሊሆናቸው ይችላል በሚል እምነት በኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ላይ እንዲወጣ ልኬዋለሁ። ብዙም ባልቀይረው መጠነኛ ለውጥ አድርጌበታለሁ።
ፀሐፊው (ኩችዬ) በግንቦት 7 መሪዎች ላይ ስላላቸው ጥርጣሬ በገለጹት ላይ ብዙም የምለው ነገር ባይኖረኝም፣ ከልቤ ልገልጽላቸው የምፈልገው (ካመኑኝ) አንድ ነገር አለ። በግንቦት 7 የተሰባሰቡ መሪዎች በየትኛውም መስፈርት ቢታይ በሌሎች ድርጅቶች ካሉ መሪዎች በብዙ መቶ እጅ የተሻሉ ናቸው። ከዚህ ድምዳሜ ላይ የደረስኩት ለአለፉት ሁለት ዓመታት በተቃዋሚነት ጎራ የተሰለፉትን መሪዎች በአብዛኛው አብሬያቸው እያደርኩ ከአጠናሁዋቸው በኋላ እንጂ እንዲያው በጭፍኑ አይደለም።
የግንቦት 7 መሪዎች ወደ አመጽ ትግል ሲገቡ ፀሐፊው ያነሱዋቸውን ጥያቄዎች ሳይወያዩባቸው ቀርተው አይደለም። ከዚህም እጅግ ከባድ የሆኑ ጥያቆዎች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል። የግንቦት 7ትን አመሰራረትና እድገት ቀረብ ብለው ቢከታተሉ ኖሮ ከኦነግ ወይም ከሌላ ሕብረ-ብሔራዊ ዓላማ ከሌለው ድርጀት ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት እና ስለአጠቃላይ ችግሮች በደንብ ማወቅ ይችሉ እንደነበር አስባለሁ። ማንዴላ ኡምክሆንቶ ዊ ስዝዌ የተባለውን ጦር የመሰረተው አፓርታይድ አሁን በቅንጅት መሪዎች ላይ ወያኔ የሚጫወተውን ጨዋታ ሲጫወት ስለነበር ነው።
የአመጽ ትግል ከቀዝቃዛው ጦርነት ማክተም በኋላ ተቀባይነት አጥቷል ሲሉ የገለጹት በመረጃ ያልተደገፈ ድምዳሜ ይመስለኛል። በሱዳን፣ በፍልስጤም፣ በኢራቅ፣ በሶማሊያ፣ ... ወዘተ የሚደረጉትን ትግሎች ሳይመለከቱ አንዳንድ የንድፈ ሃሳባዊያን ፀሐፊዎች የሚሰነዝሩትን ሃሳብ ብቻ ይዘው የተናገሩት ይመስለኛል። እባክዎት ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ በአሜሪካ ድጋፍ የሚደረጉ ጦርነቶችን ዘ ሮግ ስቴት ከሚለው መጽሐፍ ያንብቡ። ወያኔ “የአመጽ ትግል ያረጀ ፋሽን ነው” በሚለው አባባሉ ስነልቦናችንን አደንዝዞት ካልሆነ በስተቀር፣ ሁሉም ነገር በዕቅድና በንጹኅ ዓላማ ከተተገበረ ይቻላል። ዋናው ይቻላል የሚለውን ስሜት በጽናት መያዙ ላይ ነው።
ወደ ድምዳሜዬ ልምጣ፣ ብዙዎቻችን ሳንወድ በግድ ከሠላማዊ ትግል ሜዳ ወጥተን ወደ አመጽ ትግል እየገባን ነው። ትግላችን የአመጽ ትግል ይሁን እንጂ የምንታገለው ሠላማዊ ትግል በአገራችን እንዲመጣ ነው። የአመጽን መንገድ ብንከተልም፣ የአመጽን መንገድ ቅዱስነት ለማሳየት አንፈልግም። በኢትዮጽያ የሥልጣን ሽግግር መደረግ ያለበት በሠላማዊ ትግል ብቻ ነው ብለን በጽኑ እናምናለን። የእኛም ትግል በኢትዮጵያ ታሪክ የመጨረሻው የአመጽ ትግል ሆኖ እንዲመዘገብ እንፈልጋለን።
ጽናት ፍቅሩ - This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



