አንድነትና የሚሊየንም ድምፅ ለነፃነት ንቅናቄ
አማኑኤል ዘሰላም
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር፣ አቶ ይልቃል ጌትነት፣ በውጭ ሀገር የሥራ ጉብኝት እያደረጉ እንደሆነ በስፋት እየተዘገበ ነው። ታዲያ "ስለ ሰማያዊ ብዙ እየሰማን፣ የአንድነት ፓርቲ ድምፅ ግን ምነው ጠፋ።
የሚሊየነሞች ድምፅ ለነፃነትስ ወዴት ገባ?" ብለን የምንጠይቅ ልንኖር እንደምንችል አስባለሁ። በዚህም ረገድ በአንድነት ፓርቲ ዙሪያ አንዳንድ ሃሳቦች ለአንባቢያን ለማካፈል እሞክራለሁ።
በቅድሚያ አንድ መረዳት ያለብን ነገር አለ። የአንድነት ፓርቲና እና ሰማያዊ ፓርቲ፣ ሁለቱም ተመሳሳይ የፖለቲካ ፕሮግራም ቢኖራቸውም፤ ሁለቱም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለውጥ ለማምጣት ቢታገሉም፤ የአሠራር ልዩነቶች አሏቸው። የአንድነት ፓርቲ፣ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ የትግሉ አካል እንደሆነ ቢያውቅም፣ መሰለፍ ብቻ በራሱ ምንም ሊያደርግ እንደማይችል ጠንቅቆ የተረዳ ደርጅት ነው። በዚህም ምክንያት ግብታዊ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን ከማድረግ ብዙ ይቆጠባል። ሰልፎችም ሆነ ማናቸውም አይነት ሰላማዊ እንቅስቅሴዎች ተጠንተው፣ በጥንቃቄና ውጤት በሚያመጣ መልኩ መደረግ አለባቸው ብሎ ያምናል። ካለፈው የቅንጀት ስህተቶች ብዙ የተማረ ነው።
በመሆኑም ሰልፍ አልተደረገም ማለት እንቅስቃሴ የለም ማለት አይደለም። የአንድነት ፓርቲ በአሁኑ ወቅት እያደረጋቸው ያላቸውን አራት በጣም አስፈላጊና መሰረታዊ ጉዳዮች እንዳካፍል ይፈቀድልኝ፤
1. አንድነት፣ ከሰኔ እስከ መስከረም የተደረገውን የሚሊየኖችም ድምፅ ለነፃነት እንቅስቃሴዎች፣ እንዲሁም የፓርቲው ጠቅላላ ሥራዎች፣ ወደ ኋላ ተመልሶ ግምገማ እያደረገ ነው። "የቱ መስተካከል አለበት? የቱ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት? ..." እየተባለ፣ ጠቃሚ ትምህርቶችን ለማሰባሰብ እየተሞከረ ነው። ዝም ብሎ መሮጥ አይደለም። ቆም ብሎም ማሰብና እራስን መመርመር፣ ካለፉትን ተግባራት መማር ያስፈልጋል።
2. ፓርቲው በቅርቡ የአመራር አባላትን ይመርጣል። አብዛኞቹ ሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ድርጅቶች አንድ መሪ ነው ለዝንተ ዓለም የሚመራቸው። የአንድነት ፓርቲን መጀመሪያ ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ከዚያም ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው፣ ከዚያም ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ መርተዋል። አሁን ደግሞ ዶ/ር ነጋሶን ለመተካት ሦስት እጩዎች የምረጡኝ ዘመቻ ላይ ናቸው። እነርሱም የፓርላማ አባል የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ፣ ቀድሞ ፓርቲውን ሲመሩ የነበሩትና በበርካታ አባላት እንደገና እንዲወዳደሩ ግፊት እንደተደረገባቸው የሚነገረው፣ አንጋፋው ኢንጂነር ግዛቸው እንዲሁም ኮንሴንሰን ቢልድ በማድረግና በአስተዋይነታቸው የሚታወቁት፣ በአሁኑ ወቅት ፓርቲውን በፋይናንስ ኃላፊነት የሚመሩት፣ አቶ ተክሌ በቀለ ናቸው። ይህ በአንድነት ውስጥ እየተደረገ ያለው ፉክክር፣ በማንም የሀገራችን ድርጅቶች ያልታየ ዴሞክራሲያዊ ፉክክር ነው።
3. እርግጥ ነው ከአሁን ለአሁን ሕብረት ያስፈልጋል ተብሎ፣ ወደ ኋላ ከሚጎትትና ሥራን ከማያሠራ ድርጅት ጋር ሕብረት አይፈጠርም። ሕብረት ሲፈጠር ለውጤት መሆን አለበት። በዚህም ረገድ አንድነት ከዚህ በፊት አካል ከሆናቸው እንደነ መድረክ ካሉ ስብስቦች ጋር ያለውን ግንኙነት እየፈተሸ ነው። በአንጻሩም ደግሞ ፓርቲውንም ሆነ ትግሉ ወደፊት እንዲሄድ ሊረዱ የሚችሉ፣ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር፣ የላይ ላይ ትብብር ሳይሆን የውህደት እንቅስቃሴ እያደረገ ነው። ከዚህ በፊት እንደ ብርሃን ፓርቲ ያሉ ድርጅቶች ከአንድነት ጋር መዋሃዳቸው ይታወቃል። አሁን ደግሞ አንድነት ፓርቲ ከአንጋፋው መኢአድና በአሁኑ ወቅት አስደሳች እንቅስቅሴ በሜዳ ላይ እያደረገ ካለው ከአረና ጋር ለመዋሃድ ትልቅ ሥራ እየሠራ ነው።
4. ሰላማዊ ሰልፍ ሆነ ሌላም ሌላም እንቅስቅሴዎች እንዲሁ በግብታዊነት አይሠሩም። ጥናት፣ ጥንቃቄ፣ ዝግጅት ያስፈልጋል። የስሜት ትግል የትም አያደርስም። ትግሉ የሰከነ፣ የበሰለና ውጤት የሚያመጣ መሆን አለበት። የአንድነት ፓርቲ የሚሊየነም ድምፅ ለነፃነት በሚል ስም የጀመረው እንቅስቃሴ ክፍል ሁለት፣ ከአመራር አባላት ምርጫ በኋላ፣ ይታወጃል። ይህ እንቅስቃሴ አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን፣ በመላ ሀገሪቷ ያተኮረ፣ ትግሉን አንድ እርምጃ ወደፊት የሚወስድ እንቅስቃሴ ይሆናል። ለዚህም እንዲረዳ አባላት በሰላማዊ ትግል ዙሪያ የተለያዩ ሥልጠናዎች እየወሰዱ ናቸው።
እንግዲህ ሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ለምትኖሩ ኢትዮጵያዊያን እንዲህ እላለሁ። በሀገራችን ሙስና የመስፋፋቱ፣ ዘረኝነት የመብዛቱ፣ የሕግ ሥርዓት ያለመኖሩ፣ የኑሮ ውድነቱ፣ የሰብዓዊ መብት ረገጣው፣ ኢትዮጵያ ለብዙኀኑ ሲዖል፣ ከገዢው ፓርቲ ጋር ግንኙነት ስላላቸው ብቻ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሚሊየነር ለሆኑት ለጥቂቶች ገነት ለመሆኗ ምክንያቱ የፖለቲካው ችግር ነው። የፖለቲካ ችግርን ለማስተካከል ደግሞ የፖለቲካ ትግል ይጠይቃል። የአንድነት ፓርቲ ይህ ለሰላምና ለፍትህ የሚደረገውን የፖለቲካ ትግል ለመምራት እየሠራ ነው።
የአንድነት ፓርቲ ከሁለት ወራት በፊት ባደረጋቸው ሀገረ ሰፊ፣ የሚሊየም ድምፅ ለነፃነት እንቅስቃሴዎች፣ በአዲስ አበባ፣ በመቀሌ፣ በጎንደር፣ በባህር ዳር፣ በደሴ፣ በጂንካ፣ በአርባ ምንጭ፣ በወላይታ ሶዳ፣ በባሌ/ሮቢ፣ በፍቼና በአዳማ ሰላማዊ ሰልፎች አድርጓል። በመቀሌ ሰልፉ ሊደረግ አንድ ቀን ሲቀረው የህወሓት ባለሥልጣናት "እንኳን አንድነት፣ ቅንጅትም መቀሌን አልደፈረም" በሚል የቅስቀሳ መኪናዎችን እና ማይክራፎኖችን በማገታቸውና የአመራር አባላትን በማሰራቸው፣ ከአሥራ አምስት ቀናት ቅስቀሳ በኋላ ሰልፉ ሊሰረዝ ችሏል። በባሌ/ሮቢ፣ ኦሕድዶች ሰልፉ ከመደረጉ አንድ ቀን በፊት፣ "ሰልፉን ካደረጋችሁ ከፍተኛ ደም መፋሰስ ይሆናል" የሚል ዛቻ በመሰንዘራቸው፣ ሕዝብን አደጋ ላይ ላለመጣል ሲባል፣ ሰልፉ ሳይደረግ ቀርቷል።
የአንድነት ፓርቲ በአዋሳ፣ በጋምቤላ፣ በወሊሶ፣ በድሬዳዋና በአሶሳም ሰልፎች ለማድረግ እቅድ ነበረው። ነገር ግን በገንዘብ ማነስ ምክንያት እነዚህ ከተሞች ሰልፍ ማድረግ ሳይቻል ቀርቷል።
አሁንም ፓርቲው የተቻለውን ለማድረግ የወሰነና የቆረጠ ቢሆንም፣ ፓርቲው የሕዝብ ድጋፍ ከሌለው ሊያደርግ የሚችለው የተወሰነ ነው። በተለይም የገንዘብ አቅም ላይ ትልቅ ትኩረት መስጠት እፈልጋለሁ። እንዲሁ ለውጥ ስለተመኘን ለውጥ አይመጣም። ሀገር ቤት ያሉ ኢትዮጵያውያን በጓዳና በሹክሹክታ ብሶታችንን መግለጽ ማቆም ይኖርብናል። ትግሉ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊን ተሳትፎ ይጠይቃል። ጠንካራ ፓርቲ ሲመጣ መቀላቀሉ ሳይሆን፣ አሁን ያሉትን፣ እንደ አንድነት ፓርቲ አይነቶችን ጠንካራ እንዲሆኑ ማድረጉ ይበጃል።
ውጭ ሀገር ያለነው፣ ምን እንኳን የመገደል፣ የመታሰር፣ የመዋከብ አደጋ ባያገኝንም፣ ቢያንስ ሥራችን እና አፋችን መገናኘት ያለባቸው ይመስለኛል። "ሀገር ቤት ካሉት ድርጅቶች ለውጥ ለምን አያመጡም" ብለን መናገርና መጠየቅ ሳይሆን፣ ለውጥ እንዲያመጡ የነርሱ አካል ሆነን ድጋፋችንን መስጠት ይጠበቅብናል። ሕዝቡ ካልተነሳና ካልተነቃነቀ በምንም ሁኔታ ለውጥ ሊመጣ አይችልም። ሕዝቡ እንዲነሳ ሕዝቡ መሃከል ሆኖ ትልቅ ድርጅታዊ ሥራ መሥራት ያስልጋል። ይህን አይነት ድርጅታዊ ሥራ ለመሥራት፣ ሕይወታቸውን ለዚህ ሥራ አላልፈው ከሰጡ ሀገር ቤት ካሉ ጀግኖች ጎን መቆም ይኖርብናል።
እንግዲህ ለሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት እንቅስቃሴ ክፍል ሁለት ከወዲሁ ሁላችንም እንዘጋጅ። ፓርቲውን በገንዘባችን እንደግፍ። በገንዘብ ለመርዳትና ከሚሊዮኖች አንዱ ለመሆን የሚፈልጉ ከሆነ የሚከተለውን ድረ ገጽ ይጎብኙ! http://www.andinet.org/
አማኑኤል ዘሰላም
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ታህሳስ 15 ቀን 2006 ዓ.ም.