ቴዲ አፍሮና የቢራው ፖለቲካ
ክንፉ አሰፋ
በጋዜጠኛ ስህተት የወጣች አንዲት ጽሑፍ ምክንያት 18 ሺህ ፊርማ በኢንተርኔት መሰባሰቡን ሰማን። ጽሑፉን ያሳተመው መጽሔት ስህተቱን አረመ። ይቅርታም ጠየቀ። ዘመቻው ግን እንደቀጠለ ነው። ቴዲ አፍሮ ይንን እንዳልተናገረ መግለጫ ቢሰጥም ጉዳዩ እልባት ሊያገኝ አልቻለም። ከቶውንም አንድነታችንን የማይፈልጉ ምዕራባውያን ጭምር ይህችን ምክንያት በመያዝ ጉዳዩን ማራገብ ጀመሩ።
አንድ የዳች ጋዜጣ አጼ ምኒልክን ከሂትለር ጋር አመሳስሎ በመጻፍ ጋዜጣውን በዚህ ሳምንት አሰራጭቷል! ያለ አንዳች መረጃ። "ለነጮች እጄን አልሰጥም!" ብሎ አድዋ ላይ ስላዋረዳቸው ምኒልክን ለማንቋሸሽ ምንም መረጃ አያስፈልጋቸውም።
እልፍነሽ ቀኖ የተባለች የኦሮምኛ ሙዚቃ አቀንቃኝ በአንድ ወቅት በለቀቀችው ነጠላ ዜማ ምክንያት ማዕከላዊ እስር ቤት ታስራ ነበር። ምርመራውን የሚያካሂዱት ሰዎች በመጀመሪያ የዘፈኑ ግጥም ወደ አማርኛ እንዲተረጎም አደረጉ። በግጥሙ ምንም አይነት የወንጀል ነገር ሲያጡ ግጥሙ "የሕግ ትርጉም ይደረግለት" ሲሉ አዘዙ። የሕግ ትርጉሙም ብዙ ስላላስኬዳቸው ለግጥሙ የፖለቲካ ትርጉም እንዲሰጠው አደረጉና ሙዚቀኛዋን "ጥፋተኛ ነሽ" ሲሉ ከሰሱ። የፖለቲካ ትርጉሙ "ይህን ያለችው እንዲህ ለማለት ነው ..." ከማለት ተነስቶ አቀንቃኝዋ በልቧ አስባው ይሆናል የሚለውንም ያካተተ ነበር። በኢትዮጵያ "የፍትህ ሰዎች" የምናስበውንም ያውቁ ኖሯል።
የበደሌ ቢራ አድማ ጠሪዎች ቴዲ አፍሮ በልቡ ያሰበውን የማንበብ ኃይል እንዳላቸው አናውቅም። እሱ ግን የተባለውን ነገር እንዳልተናገረ ገልጾላቸዋል።
አጼ ምኒልክ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ያከሄዱት ጦርነት "ቅዱስ ጦርነት ነው" ወይንም "አይደለም" የሚለውን ሙግት ለግዜው ወደጎን እንተወው። ምክንያቱም የዚህ ውይይት ውጤጥ የኦሮሞ ህዝብ አሁን ላለበት ችግር የሚፈይደው አንዳች ነገር የለም። የህሊና ዓይኖቹን ክፍት አድርጎ ለሚመለከት ሁሉ፤ የዛሬው የኦሮሞ ህዝብ ችግር የበዴሌ ቢራን ከመጠጣት እና ካለመጠጣት የላቀ ነው። ለነገሩ እንጂ 90 በመቶ የሚሆነው የኦሮሞ ህዝብ የሚተዳደረው በግብርና፤ ኑሮውም ከእጅ ወደ አፍ በመሆኑ የበደሌ ቢራን የመጠጣት አቅሙም ሆነ ዕድሉ የለውም። የዚህ ዘመቻ መሪ ተዋንያን የሆነው ጃዋር መሐመድ እንደነገረን ከሆነ ደግሞ 90 በመቶው የኦሮሞ ህዝብ የሙስሊም እምነት ተከታይ ነው። በሙስሊም አልኮል "ሃራም" ነው።
"እስር ቤቱ ሁሉ ኦሮምኛን ይናገራል!" ያለው ማን ነበር? አዎ! የሥርዓቱ ቁንጮ የነበረው ስዬ አብርሃ ነው። ስዬ ሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ከርቸሌ ታስረን የነበርን ጋዜጠኞች የእነ ኦቦ ባይራን ጉዳይ እያነሳን በኦነግ ስም በግፍ ለታሰሩት ስንጮህ የዝሆን ጆሮ ነበር የሰጠን። አቶ ስዬ አብርሃ ዓይኑ የተከፈተውና ጆሮው ኦሮምኛን መስማት የጀመረው እጆቹ የኋሊት ታስረው ቃሊቲ ሲወርድ ነበር። በእርግጥ ማየት ማመን ነው። ያየውንና የሰማውን በመመስከሩ ሊመሰገን ይገባዋል። ልብ በሉ። እስረኛው ሳይሆን እስር ቤቱ ነው ኦሮምኛ እየተናገረ ያለው።
ሂዩማን ራይትስ ዋች ሰሞኑን በለቀቀው ዘገባ፤ በኦሮሞ ወገናችን ላይ እየተፈጸመ ያለውን አስከፊ ስቃይ በድምፅና በምስል ጭምር አሰራጭቷል። ይህንን ስቃይ ለማስቆም የፌስቡክ ታጋዮቹ ስንት ሺህ ፊርማ እንዳሰባሰቡ አልነገሩንም። የበዴሌ ቢራን የኦሮሞ ህዝብ እንዳይጠጣ በ24 ሰዓታት ውስጥ 18 ሺ ፊርማ ተሰብስቧል ብለውናል።
እርግጥ ነው። "ሰብዓዊ መብት ይከበር!" የሚል ዘመቻ ከመጀመር ይልቅ "ቢራ አትጠጡ!" ማለቱ ቀላል ሊሆን ይችላል። በምዕራቡ ዓለም የሚመረተውን ሄነከን ቢራ ራሳቸው እየተጎነጩ ይህንን ቀጭን ትዕዛዝ ሲያስተላልፉ ግን በዚያ ትልቅ ህዝብ ላይ እያሾፉበት መሆኑን የዘነጉት ይመስላል።
የኦሮሞ ልሂቃን ግራ ያጋቡኛል። ይህን ስል ያለምክንያት አይደለም። በአባ ጅፋር ግዛት ተወልጄ በኦሮሞ ባህል ታንጼ ነው ያደግኩት። በደሙ ብቻ 'ኦሮሞ ነኝ' እያለ ከሚመጻደቀው ይልቅ የኦሮሞን ህዝብ ማንነት ጠንቅቄ አውቀዋለሁ። ቋንቋው፣ ባህሉና ስነልቦናው ውስጡ ሰርጎ ሳይገባ በደሙ ብቻ ራሱን እየለካ ከህልም እና ከቅዠት ዓለም ውስጥ ገብቶ የኋሊት ከሚራመደው በተሻለ መንገድ። ... እናም አንድ የኦሮሞ ህዝብ አውቃለሁ። በቋንቋው፣ በባህሉና በታሪኩ የሚኮራ ህዝብ። ታታሪና ሠራተኛ ህዝብ። ከሌላው ጋር ተዋልዶና ተከባብሮ በፍቅር አብሮ የሚኖር ህዝብ። የኦሮሞ ህዝብ ከሌላው ወገኑ ጋር በደም ተሳስሯል። ሐቁ ይህ ነው። ግና ፖለቲከኞቹ ከዚህ ህዝብ በሁለት ሺህ ማይልስ ርቀው በምዕራቡ ዓለም በሚሠሩት ሥራ ይህንን ትልቅ ህዝብ እጅግ ትንሽ የሚያደርግ መሆኑን ያስተዋሉት አይመስለኝም።
በቅርቡ ሳዑዲ ዐረቢያ በወገኖቻችን ላይ የጸመችውን ግፍ ለመቃወም በዓለም ዙሪያ ያለ ኢትዮጵያዊ በጋራ በሚጮህበት ወቅት አንድ እንግዳ ክስተት በኢንተርኔት ላይ ወጥቶ አየን። "ሳዑዲ ዐረቢያ ኦሮሞን አትግደሉ፣ ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ አይደለም፣ ኦሮሞ ወንጀለኛ አይደለም።" የሚል መፈክር የሚያሰሙ ሰዎች ለብቻቸው ሰልፍ ወጡ። እነዚህ ሰዎች የተሰለፉት "ኦሮሞን አትንኩ። ሌሎቹ ግን ወንጀለኞች ስለሆኑ ይገባቸዋል" የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ነበር። መቼም ከማንም ሰብዓዊ ፍጡር እንዲህ አይነት ኢ-ሰብዓዊ አባባል አይጠበቅም። ድርጊታቸው ያሳፍራል። አንገትም ያስደፋል። ይህ አሳፋሪ ድርጊት እኔን እንዲህ ካሸማቀቀኝ፤ አፈር ስንፈጭ ያደግነው በኢትዮጵያዊነታቸው የሚኮሩ የኦሮሞ ልጆች ቢያዩት ምን ሊሉ እንደሚችሉ በምናቤ እስል ነበር። በዚያ ትልቅ ሕዝብ ስም አደባባይ ወጥተው፣ ተግባራቸው ግን ማስተዋል የተሳነው ትንሽ ህዝብ ነበር። ያንን ኩሩ ህዝብ እንዲህ ... እንዲህ እያሉ ሊያሳንሱት አየን።
እ.ኤ.አ. በ1998 ገደማ አቶ ዳዊት ዮሐንስ በሆላንድ ውስጥ ህዝባዊ ስብሰባ ጠርቶ ነበር። ከስብሰባው መሃል አንድ ሰው ከመቅጽበት ተነስቶ 'ለኦቦ ነጋሶ ጊዳዳ የሚያደርሱልኝ ጥብቅ መልዕክት አለኝ' አለ። ስብሰባውን የሚመራው አቶ ዳዊት ዮሐንስም ሰውዬው ተነስቶ መልዕክቱን እንዲናገር ፈቀደለት። ሰውየው ከመቀመጫው ተበሳ።
"ፊንፊኔ መሃል ላይ ያለው የምኒልክ ሐውልት በአስቸኳይ እንዲነሳ ይንገሩልን!" አለ ፊቱን ቅጭም አድርጎ በኩራት እየተናገረ። በስብሰባው የነበርን ሰዎች ግን ለተናጋሪው አፈርን። ያሳፈረን ይህንን መልዕክት ማስተላለፉ አልነበረም። ሰውየው ሊናገር ከመቀመጫው ሲነሳ ሌላ አንገብጋቢ ጉዳይ ያነሳል ብለን ገምተን ስለነበር እንጂ። 'ሰዎች በዘራቸው (በኦሮሞንታቸው) ብቻ የሚታሰሩት፣ የሚሰቃዩትና የሚገደሉት እስከመቼ ነው?' የሚል መልዕክት ነበር የጠበቅነው። ምክንያቱም ወቅቱ በቁጥር 20 ሺህ የሚደርስ የኦሮሞ ተወላጆች የጦር ካምፕ እስረኛ እንዲሆን ካደረጉ በኋላ፤ የኦነግ መሪዎች በባሌ ሳይሆን በቦሌ እየተሸኙ የወጡበት ሰሞን ነበር። የኦነግ መሪዎች ከህወሓት ጋር በጋራ መስርተውት የነበረውን ቻርተር ረግጠው በመውጣታቸው ምክንያት ኦሮሞው ወገናችን የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር ይከፍል የነበረበት ወቅት።
ዳዊት ዮሐንስም አግባብ ያለው ጥያቄ መሆኑን ከተናገረ በኋላ መልዕክቱን ለርዕሰ-ብሔሩ እንደሚያደርስ ቃል ገብቶ ሄደ። መልዕክቱን ለዶ/ር ነጋሶ ያድርስ፤ አያድርስ የታወቀ ነገር የለም። ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በዚያን ወቅት የሀገሪቱ ርዕሰ-ብሔር ነበሩ። እንኳንና የተባለውን መልዕክት ሊያስፈጽሙ፤ እሳቸውም የዛ ሥርዓት ሰለባ ሆነው አየን።
የአጼውን ሐውልት ግን ዛሬ በባቡር ሃዲድ ሥራ ምክንያት ከነበረበት ስፍራ እንዲነሳ አድርገውታል።
የተዛባ ታሪክ ይዘን፣ ጥላቻን ብቻ በምናባችን አርግዘን የት እንደምንደርስ አላውቅም። አሁንም በመፍትሔው ላይ ሳይሆን በችግሮቹ ላይ ተወጥረናል። የምኒልክ ሐውልት ተነሳም አልተነሳ እንደ እንስሳ ለሚታደነው የኦሮሞ ህዝብ ምን ፋይዳ አለው? "በእስር ያሉ ወገኖቼ ይፈቱ!" ለማለት እንኳን ሞራል ሳይኖረን አዕምሯችንን በአፈ-ታሪክ ብቻ ወጥረን አንዲት ኢንች እንኳን ወደፊት መራመድ እንዳልቻልን ለምን አናስተውልም?
አጼ ምኒልክ ኢትዮጵያን ግዛት አንድነት ለማስፋፋት ባደረጉት ጦርነት ወንጀል ፈጽመው ከሆነ አጽማቸው ወጥቶ ለፍርድ ይቅረብ ነው የምትሉት? ወይንስ ይህ ትውልድ የዚያ ወንጀል ውርስ አለበት? ውርስ ካለበትስ ማን ነው ወራሹ? አማራው? ጉራጌው ወይንስ ኦሮሞው? እንደ ዘረኞች፣ ደም መለካት ካለብን እኚህ መሪ ከአማራም፣ ከኦሮሞም፣ ከጉራጌም ይወለዳሉ። ጠለቅ ብለን ከሄድን ደግሞ ራስ ጎበና ዳጬን በዚያ ስዕል ውስጥ እናያለን። ምዕራብ እና ደቡብ ኢትዮጵያን በኃይል የያዙና ያስገበሩ የአጼው የጦር መሪ። ራስ ጎበናን ልንጠላቸው እንችል ይሆናል። ኦሮሞነታቸውን ግን ልንክደው አንችልም። የወንጀል ውርስ በተዋረድ (guilt by association) ውስጥ ከገባን የኦሮሞን ህዝብም በአዕምሯችን ለፈጠርነው ወንጀል ወራሽ ልናደርገው ነው።
የቴዲ አፍሮ "ጥቁር ሰው" አልበም የሚያሞግሰው ኢትዮጵያን ከወራሪ ጠላት የታደጉትን ጀግኖች ነው። እነ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴን እና እነ ባልቻ አባ ነፍሶ። ቴዲ አፍሮ ለነዚህ ጀግኖች ባያቀነቅንላቸውም ከታሪክ መዝገብ ላይ ልንፍቃቸው አንችልም። የታሪክ ተመራማሪዎች ስለነዚህ ጀግኖች የጻፉት አፈ-ታሪክ ወይንም ድርሰት አይደለም። በጀግኖቹ የምንኮራው በዘራቸው ሳይሆን የሠሩት ገድል ነው። በ'ጥቁሩ ሰው' የተመራው ይህ የፀረ-ቅኝ ግዛት ገድል ከኢትዮጵያ አልፎ ለመላው አፍሪካና ለጥቁር ህዝቦች ነፃነት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። ይህ ሊዋጥላችሁ የሚገባ እውነታ ነው። በዚያ ገድል የሚያፍሩ ካሉ የራሳቸው ጉዳይ። መላው የአፍሪካ ህዝብ ግን ይኮራበታል። የዓለም ጥቁር ህዝብም ሲያስታውሳቸው ይኖራል።
ዘር እየቆጠርን ከሄድን ብዙ የሚጎረብጡ ነገሮችን ልናነሳ ነው። በግዛት ማስፋፋቱ ሂደት ግን አንድ ሐቅ አለ። ኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ህልቀ መሳፍርት ኢትዮጵያዊ አልቋል። ይህ ደግሞ የድንበር መስፋፋት፤ እድገት እና ሥልጣኔ ይዞት የሚመጣው ችግር እንጂ አንድን ህዝብ ለመጨረስ ጥናት ተደርጎ የተሠራ እንዳልሆነ ታሪኩን ከስር መሰረቱ ማየቱ ይበጃል። ችግሩ በእኛ ላይ ብቻ ሳይሆን በአያሌ ሀገሮች እንደተከሰተ የታሪክ መዛግብት ይነግሩናል። በ17ኛው ክፍለ ዘመን የተከሰተው የኢንዱስትሪ አብዮት ሳቢያ እንኳን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት የማይተናነስ እልቂት ነበር።
አጼ ምኒልክን ከጀርመኑ ኦቶ ቮን ቢስማርክ ጋር የሚያመሳስሉ ምሁራንም አሉ። እርግጥ ነው ጀርመን አሁን የያዘችውን ግዛት ቅርጽ እንድትይዝ ያደረገው ፕሩሲያዊው ቢስማርክ ነው። ቢስማርክ የጀርመንን አንድ ታላቅ ኤምፓየር ለመፍጠር አንባገነን፣ ኃይለኛና ጦረኛ መሆን ነበረበት። ታዲያ ይህችን ኃያል ሀገር በመመስረቱ ጀርመኖች አልጠሉትም። ይልቁንም የጀግንነት ስያሜ ለግሰውታል። አያሌ የመታሰቢያ ሐውልቶችንም አቁመውለታል።
ቢስማርክ የሕግ ምሁር ነበር። አጼ ምኒልክ ግን መደበኛም ሆነ ዘመናዊ ትምህርት የተማሩ ሰው አልነበሩም። ከታሪክ እንደምንረዳው በአጼ ልብነድንግል ዘመነ መንግሥት፤ የግራኝ አህመድ ወረራን ተከትሎ የነበረውን መከፋፈልና መተላለቅ ለማስቆም መሪዎች ተነሱ። ሀገርን አንድ የማድረጉን ትግል አጼ ቴዎድሮስ ጀመሩት፣ አጼ ዮሐንስ ቀጠሉበት ከዚያም እምዬ ምኒልክ ተረከቡት።
አጼ ምኒልክ ለዓመታት በኦነግ ሰዎች ተወግዘዋል። ውግዘቱ አሁንም እታገልለታለው የሚሉትን ህዝብ ችግር ሲፈታው አላየንም። በ1991 ከህወሓት ጋር ጋብቻ ፈጽመው የምኒልክ ቤተ-መንግሥት ሲገቡ ይናገሩት የነበረውን ሁሉ ረሱት። ከቶውንም ያነሱት የነበረው የኦሮሞ ህዝብ የመብት ጉዳይ ሳይሆን የሥልጣን ጥያቄ ለመሆኑን አረጋገጡልን። የሽግግር መንግሥቱን ቻርተር ሲያጸድቁ "ኢትዮጵያዊ አይደለንም" የሚለውንም ሳያውቁ ዘንግተውት ነበር። ከገዢው ፓርቲ ጋር የጀመሩት ጊዜያዊ ጋብቻ በፍቺ ሲጠናቅቅ የምኒልክ ጠላትነት መፈክራቸውን እንደገና አነሱት።
የዘር ፖለቲካው ስካር ሞቅ ብሎ በነበረበት በዚያን ወቅት እንደቀልድ ይነገር የነበረ አንድ ቁም ነገር አለ። አንድ የምግብ ቤት በር ላይ በላቲን ፊደል "አማራ መግባት ክልክል ነው!" የሚል ጽሑፍ ሰፍሯል። የጽሑፉ ትርጉም ያልገባው አንድ የአማራ ተወላጅ ጎራ ብሎ ምግብ አዘዘ። አስተናጋጆቹ የሰውየው ድፍረት አስደነገጣቸው። ባለሥልጣን ስለመሰላቸው አስተናገደዱት። ዳግም እንዳይመለስም እጥፍ ዋጋ አስከፈሉት። ሰውየው በድጋሚ ሲመጣ ሦስት እጥፍ አስከፈሉት። በሌላ ግዜ ከአምስት ጓደኞቹ ጋር መጥቶ ምግብ አዘዘ። ከተስተናገደ በኋላም አራት እጥፍ ቢል አቀረቡለት። በዚህ ጊዜ ቲፕም ጨምሮ ሰጣቸው። የሆቴሉ ባለቤት በነጋታው "አማራ መግባት ክልክል ነው!" የሚለውን ጽሑፍ አንስቶ "ኦሮሞ መግባት ክልክል ነው!" በሚል ቀየረው።
በአሁኑ ዘመን ከበድ አለ እንጂ፣ ሰዎችን በጎሣ አደራጅቶ ከማሳደም የቀለለ ትግል የለም። ደም ከውሃ ይወፍራል እንዲሉ፤ ሰዎች በጋራ የሚጋሩትን ነገር እያነሱ ሥነልቦናዊ ዘመቻ ማድረግ ስኬት ሊኖረው ይችላል። ዘለቄታ ግን አይኖረውም። የዘር ፖለቲካ ልክ እንደ ስካር ነው። ይሞቃል ከዚያም ይበርዳል። በርግጥ በሞቅታ ግዜ የሚፈጠረው አደጋ ቀላል ላይሆን ይችላል። እ.ኤ.አ. በ1993 በምስራቅና በምዕራብ ኢትዮጵያ የተፈጸመው አሰቃቂ ወንጀል ለዚህ ዋቢ ነው። የኦነግ ልሂቃን የ19ኛውን ክፍለ ዘመን ጉዳይ እየደጋገሙ ያነሱልናል። በ21ኛው ክፍለ ዘመን በራሳቸው እጅ የተፈጸመው ግድያ ግን በብሔራዊ ቴሌቭዥን ጭምር እንድናየው ተደርጓል። ነብሰ-ጡር ሴቶች በጩቤ ሆዳቸውን እየተሰነጠቁ ሲገደሉ አየን። ነብስ ያላወቁ ሕጻናትና የ90 ዓመት አዛውንት ጭምር ከተራራ ላይ እየተወረወሩ ሲጣሉም የዓይን ምስክሮች ነን። እነዚህ ሰዎች የምናስታውሰው ይህን በመሰለ ወንጀል ብቻ አይደለም። ድርጊቱ የቂምና የቁርሾ አሻራ ጥሎ አልፏል።
ይህ ሁሉ በደል በዘመናችን ተፈጸመ። በዳዮቹ ግን አሁንም በቀልን አርግዘው ይጓዛሉ።
የበደሌ ቢራን አለመጠጣት የኦሮሞን ችግር የሚፈታ ከሆነ፤ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ቢራውን መጠጣት ያቁም። የአኖሌን ሐውልት መሠራት ለኦሮሞ ህዝብ ፍትህ የሚያመጣ ከሆነ ደግሞ፤ ሐውልቱ በየከተማው ይገንባ። ግና ይህ ሐውልት ለመጭው ትውልድ ጥሎት የሚያልፈው ቂምና በቀልን እንጂ፤ ለሚታገሉለት ህዝብ የፍትህ ጥያቄ ዋስትናው ምን እንደሆነ ልንረዳው አልቻልንም። አሁን ያለው ትውልድ ያልፋል። ከዚህ ትውልድ በኋላ ለሚወለዱት ልጆች ጥለንላቸው የምናልፈው ቅርስ ጥላቻ፣ ቂም እና በቀል ብቻ ይሆናል።
ከዘመናችን ታላቅ ሰው ከኔልሰን ማንዴላ አንድ ነገር እንማር። ማንዴላ የደቡብ አፍሪካን ብቻ ሳይሆን የዓለምን ፖለቲካ የለወጠ የፖለቲካ ነብይ ነው። ይህንን ሲያደርግ የፖለቲካ ፎርሙላ አልነበረውም። ክፉን ነገር በበጎ ለማሸነፍ ወሰነ። ጥላቻን በፍቅር ለወጠ። ልክ እንደ ክርስቶስ፣ የበደሉትን ሁሉ ይቅር ብሎ በፍቅር አሸነፋቸው። ታሪክ ሠርቶ አለፈ። ስሙም ከመቃብር በላይ ለዘልዓለሙ ይኖራል።