አንዱዓለም ተፈራ
በተደጋጋሚ ትክክለኛ ያልሆነ ነገር ሲያጋጥማችሁ፤ አሁንስ በዛ! ማለታችሁ አይቀርም። እኔም ይኼው ዕጣ አጋጠመኝ። ታዲያ ዝም ማለቱ ወንጀል ሆነብኝና ይኼን ጻፍኩ። እንዲህ ነው የሆነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፤ ላለንብት የፖለቲካ ምስቅልቅል፤ መፍትሔ ፈላጊዎች የሩጫ ፊታቸውን ወደ ታሪክ አዙረዋል።

የወገንተኛው አንባገነን ሕገወጡ መንግሥትና አጨብጫቢዎቹ፤ የሀገራችን ሁሉ ችግሮች ምንጮች፤ የዛሬዎቹም ሆኑ የትናንቶቹ፤ የቀድሞ ነገሥታት ናቸው ሲሉ ራሳቸውን ነፃ አውጥተዋል። አሁን በታጋዩ ወገን ካለነው በኩል ደግሞ፤ አሁን ላለብን ችግር ተጠያቂው ተፈጥሮ፣ ጠባያችን ወይንም የቀድሞ ታሪካችን ነው የሚል ማምለጫ ተደርድሯል። ወዴት! ወዴት? የመጨረሻው እንጥሌን ያረገፈው ጽሑፍ፡ "ስኬታማ ውድቀት (Successful Failure!)" በይሄይስ አእምሮ (አዲስ አበባ) በሚል ርዕስ በየድረገፆች የተለጠፈው ነው።

ይሄይስ አእምሮ የሀገሩን ታሪክ ለማወቅ መጽሐፎቹን ማገላበጡ በጣም አስደስቶኛል። ይህን ሁላችንም ልንጋራው የሚገባ አስፈላጊና ተገቢ ባህል ነው። ታሪካችንን ስናጠና ደግሞ፤ ዓላማ አንግበን መሆን አለበት። ለማወቅ፣ ለመረዳት፣ ለመማር። አለበለዚያ ማንበባችን ትርጉም የለውም። የኛ ዋናው ኃላፊነታችን፤ አሁን ያለንበትን የሀገራችን ሀቅ ለውጠን፤ የተሻለ በማድረግ፤ ለኛና ለመጪዎቹ አጥጋቢ ሁኔታን መፍጠር ነው። ተጠያቂነታችን አሁን ላለንበት እውነታ መሆኑን ተቀብለን፤ የተረከብነውን ሀቅ ደግሞ መመርመርና ጥሩውን አቅፎ፤ ጥሩ ካልሆነው ደግሞ ትምህርት ወስዶ፤ በሂደቱም ይህ የማንነት አካል መሆኑን ሳይገድፉ ፊትን ወደ መጪው ማተኮሩ ነው።

በራስ መኩራት በማንኛውም መለኪያ ቢመዘን ስህተት አይደለም። ራስን ማድነቅ በምንም መንገድ አሉታዊነት የለውም። በእርግጥ ዛሬ የታሪክ ቦታን ይዞ መገኘት ደግሞ ከኛ ከአሁኖቹ የሚጠበቅ ጉዳይ ነው። ታዲያ ላለንበት ሀቅ ወደ ኋላ ተመልሶ ተጠያቂ መፈለጉ አልጣመኝም። ይሄይስ አእምሮ እንዲህ ሲል ጠቅልሎ መልዕክቱን አስተላለፈ፤

የተሣካ ውድቀት ውስጥ መግባት እኛ ኢትዮጵያውያን ብርቃችን እንዳልሆነ ያነበብኳቸው መጻሕፍት ሁሉ በኩራት ይመሰክራሉ። እነዚህም ሆኑ ሌሎች በተለያዩ አጋጣሚዎች የማውቃቸው ታሪኮቻችን የሚነግሩኝ አንድ ነገር ቢኖር እኛ ኢትዮጵያውያን አንድ የሚጎድለን የተፈጥሮ ቅመም መኖሩን ነው። ...

ብዙዎቻችን አዘውትረን እንደውዳሤ ማርያም እንደምንደጋግመው ምቀኝነትና የሥልጣን ጥም በደማችንና በመቅኒያችን የመሸጉብን ስለመሆናቸው የቀድሞና የአሁን ታሪካችን ነጸብራቅ የሆኑ እነዚህን መጻሕፍት በማንበብ መረዳት ይቻላል።

አልጋ ለመቀማት ወይም አልጋውን ላለመቀማት ሲል ንጉሥ አባት ልዑል ልጅን በጦርና በጎራዴና ምግብን በመመረዝ ሣይቀር የሚገድልበት፣ ነገሥታት ከሀገራዊ ልማት ይልቅ ለሥልጣናቸው ሲሉ ለብዙ አሠርት ዓመታት በማያቋርጡ ጦርነቶች ራሳቸውንና ሕዝባቸውን የሚማግዱበት፣ ለሥልጣንና ለሹመት ሲባል አንዱ ሌላውን በመርዝና በሰይጣናዊ መተትና ድግምት የሚጨራረሱበት፣ የሥልጣን አራራን ለማስታገስ ሲባል የገዛ ሚስትን ሳይቀር ለከፍተኛ መሪዎች እያቀረቡ በትዳርና በ"ፍቅር" ጡር የሚሠራበት፣ ኃይማኖትን መሣሪያ በማድረግ ሕዝብ ከእውነተኛ የፈጣሪ መንገድ እንዲወጣና የነገሥታት ባሪያ እንዲሆን የኃይማኖት መሪዎችና ነገሥታት የሚመሣጠሩበት፣ በዕብድና ወፈፌ ነገሥታት የደንቆሮ አገዛዝ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በረባ ባልረባው ሚዛን የማይደፋ ምክንያት እጅ እግራቸው እንዲቆረጥና በ"እኔን ያዬህ ተቀጣ" ለመቀጣጫነት የሚዳረጉበት፣... አሣፋሪ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ውጪ በሌላ ሀገር ስለመኖሩ በበኩሌ አላውቅም።

ይህ ባጠቃላይ የይሄይስ አእምሮ የጽሑፉ ማጠንጠኛ መዕከላዊ ነጥቡ ነው። እንግዲህ ይኼን ታሪክ ላነገበ ሀገር፤ ማን ነው ሀገሬ ብሎ ሊያቅፈው የሚፈልግ? አቶ ይሄይስ አእምሮ በውጭ ያለነው ተመልሰን እንዳንገባ ወይንም ሀገራችን እንድንጠላ ብሎ ጻፈው፤ የሚል ብዥታ የለኝም። በአንድ መንገድ ሆነ በሌላ ለሀገሩ ተቆርቁሮ መሆኑን መገመት አያዳግትም። ነገር ግን የተጠቀመበት መንገድ ወልጋዳ ነው። የደረሰበት ድምዳሜ ተልካሻ ነው። መረጃውን አጠቃቀሙ አሳፋሪ ነው። ለትግል የሚያበረታታ ሳይሆን ተስፋ አስቆራጭና ጨለማ ዘሪ ነው። የተጠቂነት ትልቁ አርማ ነው። ግቡ ምንድን ነው? ሀገራችን ወደፊት አልሄደችም፣ መደረስ ከነበረባት ወደኋላ ቀርታለች ብሎ መቆርቆርና፤ የተፈጥሮ ቅመም ጎድሎናል ማለት፤ የሰማይና የመሬት ያህል የተራራቁ ናቸው። ለምን ይህ ሆነ ብሎ መሠረታዊ ችግሮችን መመርመር አለብን። ይሄ አያጠያይቅም። ነገር ግን አጭር መልስ ፈልጎ በመጣለት መጎመር፤ ካዋቂነት አያሰልፍም።

ችግራን ምን ነበር? አሁንስ ምንድን ነው? ያለንበት የሀገራችን አቀማመጥ ምን ያህል ሌሎች በኛ ላይ ትኩረት እንዲሠጡ አድርጎናል? በኃይማኖት አጣብቂኝ መወጠራችን ምን ያህል በታሪካችን ላይ ተፅዕኖ አድርጎብናል? የአስተዳደር ሂደታችንና የውርስ ግዛት ሁኔታው ምን ያህል ወደኋላ ለመቅረታችን አስተዋፅዖ አድርጓል? የታሪክ አጋጣሚዎች ከላይ ከተጠቀሱት ጋር በመዳመር፤ ምን ያህል ጎድተውናል? ከዚህ ለምን አልወጣንም? እነዚህ መታየት ያለባቸው ጉዳዮች ናቸው።

ይሄይስ የሀገሩን ታሪክ እንዳላጠናው ሁሉ፤ የሌሎች ሀገሮችን ታሪክም አልቃኘውም። ዛሬ እንኳ፤ በዚህ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን፤ በሰሜን ኮሪያ የገዛ አጎቱን ለሥልጣን ይቀናቀኑኛል ብሎ ያረደውን ኪም አልተከታተለም። የእያንዳንዱን ሀገር ታሪክ ለተመለከተ፤ የኛ ሀገር የተለየች አለመሆኗን መረዳት ይቻላል። የኛን ሀገር በተለየ መመዘኛ ላይ መጫን፤ አጉል ለማያውቁት ዘፈን አታሞውን መያዝ ይሆናል። አሁን በመካከላችን ያለው ችግር፤ የትግሉን ምንነት አለመረዳትና የትግሉን ቅደም ተከተል አለማወቃችን ነው። ከዚህ ወጥተን ሀገራችን ከሌሎች ሀገሮች የሥልጣኔ ደረጃ እንድትደርስ መጣር አለብን።

በኔ እምነት፤ አሁን በሀገራችን ያለውን ችግር ለመፍታት፤ በሥልጣን ላይ ያለው ቡድን መወገድ አለበት። አሁን በሁሉም መንገድ አይሎ የሚታየው ቡድን፤ ነገ ሁሉም ተገላብጦ ወደ መጨረሻ ውድቀቱ እንደሚያመራው እምነት አለኝ። ለዚህ መሠረቱ፤ የወገንተኛው አምባገነን ሕገወጡ መንግሥት የፖለቲካ ፍልስፍናውና የአስተዳደር መመሪያው የወራሪ ዓይነት ስለሆነ ነው። እናም ይሄን መቋቋምና ማስወገድ የሚያስችለው የትግል መንገድ፤ ለወገን ደራሽና ሀገርን ነፃ አውጪ ድርጅት፣ ራዕይና ተልዕኮ ሲኖረን ነው።

ለድርጅቱ አወቃቀር መነሻ የሚሆነው፤ የትግሉ ምንነት ነው። ይህ ደግሞ የወራሪ አስተዳደር መኖሩን መቀበልና ይሄን ለመቋቋም ምን ያስፈልጋል የሚለውን ጥያቄ መመለስ ስንችል ነው። ለዚህ ትግል፤ እያንዳንዱ የራሱ ድርጅት፣ የራሱ ራዕይና የራሱ ጦር ካሠለፈ፤ ትግሉ የተመሰቃቀለና የባሰ ነገ ይጠብቀዋል። ድርጅቶች ትርጉም የሚኖራቸው፤ ሕዝቡ ሉዓላዊነቱ ተጠብቆ፤ የበላይነቱና ወሳኝነቱ በተረጋገጠበት የፖለቲካ ሀቅ ነው። አሁን ያለው ትግል ያንን ለማስገኘት ነው። ታዲያ ያን በተግባር ለማዋል በአንድ መነሳት የለብንም? ይህ ድርጅት በኢትዮጵያዊነት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሚሰለፍበት መሆን አለበት። በምን እንሰለፋለን ለሚለው ጥያቄ የሚከተለው አቀርባለሁ።

መሠረታዊ የሆኑ የመሰባሰቢያ ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው፤

ሀ) የኢትዮጵያዊያን አንድነትና ሉዓላዊነት የሚረጋገጥበት፤
ለ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነት የሚጠበቅበት፤
ሐ) በኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት የሚሰፍንበት፤
መ) የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚከበሩበት፤

ሀገር እንድትሆን የሚሉ ናቸው። ይህ ድርጅት ዋናው ኃላፊነቱ በውጭ ያለነውን የኢትዮጵያዊያን ትግል መምራት ነው። ትግሉን ለማካሄድ ሙሉ ኃላፊነት ይኖረዋል። ለዚህ ደግሞ፤ የትግል ማዕከሉን ያረጋግጣል፣ ራዕዩን ያረቃል፣ አስፈላጊ የሆኑ መዋቅሮችን ያበጅና ኢትዮጵያዊያንን ያሰባስባል፣ በአንድ አካል፣ በአንድ ራዕይ፣ በሀገር ቤት የሚካሄደውን ትግል ይመራል።

ይህና ይህ ብቻ ነው በአሁን ጊዜ ያለን አማራጭ መንገድ። ይህ መንገድ፤ እያንዳንዱን ለትግሉ ድጋፍ ሠጪ ኢትዮጵያዊ ያሰባስባል። ይህ ጥንካሬን ያስገኛል።

የዛሬዋ ኢትዮጵያ የዛሬዎቹ የያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን፤ ኃላፊነት ናት።
አንዱ ዓለም ተፈራ
የአስከመቼ አዘጋጅ
ማክሰኞ፤ ጥር ፪ ቀን ፳፻፮ ዓመተ ምህረት - (1/28/2014)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ