የESFNA ፈተናና ገመና፤ ምን ያለበት ዝላይ አይችልም
ከተለያዩ ቡድኖች በተወጣጡ አባላት የተጠናቀረ ጽሁፍ
በውጭ አገር በሚገኙ ኢትዮጵያዊ የሀይማኖት ወይም ማህበራዊ ወይም ፖለቲካዊ ድርጅቶች ውስጥ፤ አስተዳደራዊ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲኖር ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎችን፤ በወያኔነት መፈረጅ የተለመደ ባህል እየሆነ መጥቷል፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት አቶ አለማየሁ ከተማ የተባሉ ሰው፤ በብእር ስም ይመስላል፤ “በESFNA ላይ የተጋረጠው አደጋ” በሚል ርእስ፤ አንድ ጽሁፍ አስነብበውናል፡፡ በፌደሬሽኑ ላይ የተጋረጠው አደጋ፤ ጸሀፊው እንደሚሉት የሰርጎ-ገብ ወያኔዎች አደጋ ሳይሆን፤ ስር የሰደደ ሙስናና ሌብነት ነው፡፡ ይሄ ወያኔ የሚለው ካርድ ተጠያቂነትን የሚያነሱ ሰዎችን በጠላትነት የመፈረጅ፤ የብልጣብልጦች አይን ያወጣ የቁማር ጫዋታ ነው፡፡ በዚህ ጽሁፍ፤ በፌደሬሽኑ ላይ የሚነሱትን ፍትሀዊ ጥያቄዎች በሙሉ ከወያኔ ጋር ማያያዝ ለምን እንደተፈለገ በማስረጃዎች በማስደገፍ እናሳያለን፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ በፌደሬሽኑ አመራርና ቦርድ ውስጥ፤ ከአመት አመት የማለወጥ፤ በአመታት ሙስና የተዘፈቀ የማፊያ ቡድን አለ፡፡ ያ የማፊያ ቡድን ሊጋለጥ ሆነ፡፡ ስለዚህም፤ ሕዝቡ ገና ለገና ወያኔ ሊወስደው ነው ሲባል ከጎናችን ይቆማል በሚል ብልሀትና ከዋናው ጥያቄ ለማምለጥ፤ ማፊያው ቡድን፤ በተጋፈጡት 16 ቡድኖች ተወካዮች ላይ ይሄንን የወያኔነት ካርድ ሊጫወት መዘዘ፡፡ እዚህ ውስጥ ወያኔ የለበትም፡፡ ጥያቄ የሚያነሱትን ወያኔ ብሎ መፈረጅ፤ ፌደሬሽኑ ያሉበትን ውስጣዊ ችግሮች ከመፍታት ይልቅ በችግሮቹ እንዲበሰብስና እንዲፈርስ ወይም የተፈራው እንዲደርስ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ስለዚህም ይሄ ችግር እንዲታረም በሚል፤ ይህንን መልስም አስተያየትም መስጠት ወደድን፡፡
ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ፤ 16ቱ ቡድኖች፤ በፌዴሬሽኑ ፕሬዚደንት ላይም ይሁን በስራ አስፈጻሚው የሚያነሷቸው ጥያቄዎች፤ ምንም አይነት ፖለቲካዊ ተልእኮ የላቸውም፡፡ ጥያቄዎቹን ፖለቲካዊ በሆነ መልኩ የመፈረጅ ስልት፤ ሆን ተብሎ ፍትሀዊ ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎችን አንገት በማስደፋት ከተጠያቂነት ለማምለጥ የሚደረግ ጥረት ነው፡፡ ጸኀፊው የብዙ ቡድኖችን ስም ሲያጎድፉ፤ ብዙ ነገሮችን ነካክተው፤ ያማስረጃና ውሀ በማይቋጥሩ አሉባልታዎችም ጭምር ነው፡፡ ለምሳሌ፤ የሜሪላንዱ ዝግጅት እንዳይሳካ ጣሩ ብለው የከሰሱት ክስ መሰረተ ቢስ ብቻ ሳይሆን፤ እውነታው ተቃራኒው ነው፡፡ የ2013ቱ የ30ኛው ሜሪላንዱ ዝግጅት የAESAONE ሸፍጥ በፈጠረው እልህ የተነሳ ብዙ ሺህ ህዝብን የሳበ ቢሆንም፤ በፕሬዚዳንቱና ተባባሪዎቻቸው በኩል በታየ ዝርክርክነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሰራር የተነሳ ገቢው ከቀደሙት ዝግጅቶች ያነሰ ሆኗል፡፡ በሜሪላንዱ ዝግጅት የተገኘው ህዝብ ብዛት በብዙ ሺህ ቢጨምርም፤ የ2013 ጠቅላላ የገንዘብ ገቢ በፌደሬሽኑ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ከነበረበትና የ2008ቱ ገቢ በ300 ሺህ ዶላር የማነሱ ጉዳይ አሁንም ድረስ ምስጢር ነው፡፡ ለዚያውም የ2013 የትኬት ዋጋ ከ2008ቱ የትኬትና የቬንደሮች ዋጋ በ20 ከመቶ ጭማሪ ኖሮት ማለት ነው፡፡
አሁንም ከዚሁ ከሜሪላንዱ ዝግጅት ጋር ሳንርቅ፤ መነሳት ያለበትና አንዱ ዋንኛው የፌድሬሽኑን ችግር ገላጭ ተሞክሮ፤ የፕሬዚዳንቱ የአቶ ጌታቸው ተስፋዬ፤ የሰለጠነ አሰራርንና ህግን፤ የፌዴሬሽኑንም ደንብ የሚጥስ ስራ ነው፡፡ የጥቅም ግጭት (Conflict of interest) እንዳይፈጠር፤ ስልጣን/ሀላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች፤ ቤተሰባዊ ወይም የቅርብ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ጋር የሚኖራቸው የስራ ግንኙነት፤ በህግ የተገደበና ጥንቃቄ የተሞላው መሆን አለበት፡፡ ወደፊት መደገም የማይኖርበት ነገር፤ በሜሪላንድ በተደረገው ውድድር ላይ የመግቢያ ትኬቶቹ ፕሮፌሽናል በሆኑና በታወቁ ድርጅቶች፤ ለምሳሌም ቲኬት ማስተር፤ ለቁጥጥር በሚመች መልኩ እንዲታተሙ ተደጋጋሚ ጥያቄ ብናቀርብም፤ ትኬቶቹ ለሙስና በሚያጋልጥና ለቁጥጥር በማያመች መልኩ በመንደር አታሚዎች ከመታተማቸውም በላይ፤ ፕሬዚዳንቱ አቶ ጌታቸው ተስፋዬ፤ ያለስራአስፈጻሚው ወይንም ቦርዱ ፈቃድና እውቅና የቤተሰባቸውን አባላት፤ ማለትም ልጆቻቸውንና ባለቤታቸውን በገንዘብ ተቀባይነት መመደባቸው የጥቅም ግጭት ያለመፍጠር ግዴታቸውን የጣሰ ነው፡፡ የፌዴሬሽኑ ዋና ጸሀፊም ከስራቸው ውጪ የቶምቦላ አሳታሚነት ውስጥ መነከራቸው ምን አይነት የጥቅም ግጭት እንደፈጠረ ከታች እናሳያለን፡፡ ይህንን ስህተት ለመንቀስም ወያኔ መሆን አያስፈልግም፡፡ ይሄንን ስህተት ያነሱትንም ወያኔ ብሎ መፈረጅ ስህተትን ለመሸፈን የሚደረግ ሩጫ ነው፡፡
በመሰረቱ በፌደሬሽኑ ላይ የሚቀርቡት ጥያቄዎች የሚነሱት፤ ለፌደሬሽኑ እድገትና ኣላማ መሳካት ላለፉት ሰላሳ አመታት ከተጉና የፌደሬሽኑን ግማሽ ወይም 16 ቡድኖችን ከሚወክሉ ሰዎች ነው፡፡ በጽሁፉ ውስጥ የተገለጹት “ተላላኪዎች፤ ስውር አጀንዳ፤ ከበፊቶቹ ጠላቶች ጋር ተጋፍጠዋል፤ ለማገልገል ቆርጠው ለተነነሱበት የወያኔ ፖለቲካ ድርጅት፤ በጥቅም ተገዝተው፤” የሚሉት ሀረጎች አሳፋሪና ከዋናው ጥያቄ ጋር የማገናኙ ሆነው አግኝተናቸዋል፡፡ ከታች እንደምናሳየው፤ አንዳንድ የፌደሬሽኑ ቦርድና ስራአስፈጻሚ አባላትም ይሁኑ ፕሬዚደንቱ፤ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ፤ እንዲህ ላለው ፕሮፓጋንዳ ተባባሪዎች ሆነዋል የሚል ጥርጣሬ አለን፡፡ ለዚህም ነው ይሄ መልስ በነሱም ላይ ያነጣጠረው፡፡ በመሰረቱ ፕሬዚዳንት ጌታቸው ተስፋዬ በተለያዩ አጋጣሚዎች በተደጋጋሚ እንደገለጹት፤ ይሄ ፌደሬሽን የኢትዮጵያዊያን ሁሉ እንጂ የዚህኛው ወይም የዚያኛው ፖለቲካ ድርጅት አይደለም፡፡ ስለዚህ ፌደሬሽኑን የተቃዋሚዎች ብቻ ስብስብ አድርጎ ማስብ፤ እንዲሁም በፌደሬሽኑ ላይ አስተዳደራዊ ጥያቄ የሚያነሱትን ደግሞ የኢህአዴግ ደጋፊዎች አድርጎ መሳል የተሳሳተና የደከመ ሀሳብ ነው፡፡
በአደባባይ ከሚደረጉ ክርክሮች ጋር በተያያዘ፤ ጸሀፊው ያነሱት ክርክርም የተሳሳተና ያልተሟላ ነው፡፡ ጸሀፊው ካሉት በተቃራኒ፤ ፕሬዚዳንቱም ይሁን ሌሎች ሀላፊነት የሚሰማቸው የፌደሬሽኑ አመራሮች በአደባባይ ከሚደረግ እሰጥ አገባ የተቆጥቡ አይደሉም፡፡ ይሄ ከራሳቸው ከፕሬዚዳንቱ ሀሳብና ስራ ጋርም ቃረናል፡፡ ለምሳሌ በኢሳት ቴሌቪዝን ላይ ቀርበው ፌደሬሽኑን የሚከፋፍል ሀሳብ የሰጡት ራሳቸው ፕሬዚዳንቱ ሲሆኑ፤ ቃለምልልሱ ተላልፎ ብዙም ሳይቆይ፤ በቃለምልሱ የሰጡት አስተያየት ስህተት መሆኑን አምነው፤ የሚከተለውን የይቅርታ ኤሜል ለቦርድ አባላት ልከዋል፡፡
The ESFNA EC discussed extensively my interview and comments on ESAT last night. We believe it went too far in airing our internal workings and disagreements. This is a mistake and I own it … For this mistake, I sincerely apologizes to the entire Board and all ESFNA supporters … Again, sincere apologies for what was said and to those that were offended.
እኛን በመገናኛ ብዙሀን ጥላሸት ከቀቡ በኋላ የሰጡትን የይቅርታ ሀሳባቸውን በፌደሬሽኑ ድረገጽ ላይ ለመለጠፍ እምቢኝ ብለዋል፡፡ በዚህ ረገድ ለኛም እድሉ እንዲሰጠንና አቋማችንን እንድናስረዳ ኢሳትን ጠይቀን፤ ህዝቡን ይከፋፍላል በሚል ምክንያት እድሉን ተነፍገናል፡፡ በዚህ ረገድ ኢሳትም ይሁን ሌሎች መገናና ብዙሀን፤ እንዲህ ያሉ ህዝባዊ ጉዳዮች ሲነሱ ሁሉንም ወገን አቅርቦ ማነጋገር እንጂ፤ አንዱን ወገን ብቻ አቅርቦ ህዝብን ይከፋፍላል በሚል ምክናት ነገሩን አድበስብሶ ማለፍ የለባቸውም፡፡ የሆነ ሆኖ፤ ፕሬዚደንቱ በአንድ በኩል አንድ ነገር ይላሉ በሌላ በኩል ደግሞ ሌላ ነገር ይላሉ፡፡ አንዱ የፌደሬሽኑ ችግርም እንዲህ ያለው ርስ በርሱ የሚቃረን አመራር ካናቱ መኖሩ ነው፡፡ ፕሬዚደንቱ የአምባገነንነት ባህርይ ያላቸውና ቦርዱን ለሁለት ከፋፍለው፤ በሀሳብ የሚደግፏቸውን በጥቅም በመግዛት፤ የሚቃወሟቸውን ደግሞ ልክ እንደኢህአዴግ በላያቸው ላይ ተለጣፊ የቦርድ አባላት በማበጀት ስራ የተጠመዱ ናቸው፡፡ ተለጣፊ ቦርድ አባላት ከማበጀት ጋር በተያያዘ፤ ከታች የላስቬጋስን ምሳሌ እንጠቅሳለን፡፡
አንባቢያን ሆይ፤ በፌደሬሽኑ ላይ የተጋረጠው ችግር፤ በማናቸውም ድርጅት ውስጥ የሚፈጠር አስተዳደራዊ ችግር እንጂ፤ ምንም አይነት ፖለቲካዊ ይዘት የለውም፡፡ ችግሩን ፖለቲካዊ ቀለም የሚቀቡት፤ ከላይ ከመግቢያው እንደጠቀስነው ሀሳብን በሀሳብ ማሸነፍ ያቃታቸውና በአቋራጭ ማሸነፍ የፈለጉ ደካሞች ናቸው፡፡ ድርጅቱ በውጭ/ገለልተኛ የሂሳብ ባለሙያ ኦዲት ይደረግ፤ ዴሞክራሲያዊ አሰራር ይተግበር፤ ተጠያቂነት ይስፈን፤ ግልጽነት ይዳብር፤ የፌደሬሽኑን አሰራር የሚጣረስ አካሄድ ይታረም ማለት ወያኔ ካሰኘ፤ በርግጥም ወያኔዎች ነን፡፡ ነገር ግን እነዚህ ነገሮች ሲነሱ ተጠያቂ ልንሆን እንችላለን ብለው ያሰቡ ሰዎች፤ ቀድመው ወያኔ የሚል ታግ ለጠፉብን እንጂ፤ እኛ ምንም አይደለንም፤ ኢትዮጵያዊያን እንጂ፡፡ ከላይ ከጠቀስናቸው ችግሮች በተጨማሪ፤ ለናንተ፤ ለአንባቢያንና ለፌደሬሽኑ አፍቃሪያን ግንዛቤ ይረዳ ዘንድ፤ በ16ቱ ቡድኖች ከተነሱት ጥያቄዎች ውስጥ የተወሰኑትን አለፍ አለፍ እያልን እናስፍራቸውና፤ እናንተው ፍረዱን፡፡
አንዱ በመካከላችን አለመግባባትን የፈጠረው ችግር፤ ከAESAONE ጋር የተደረገው ድርድር ነው፡፡ ፌደሬሽኑ በፍርድቤት ክረክር እያሸነፈ ቢመጣም፤ ፕሬዚደንቱ ያለቦርዱ ፈቃድና እውቅና በራሳቸው ጉዳዩን በጎን ከፍርድቤት ውጪ በድርድር መጨረስን መርጠዋል፡፡ ከሰላሳ ድምጽ ውስጥ የቀረበውን የእርቅ/ድርድር/የስምምነት ሀሳብ የደገፉት ዘጠኝ ብቻ ቢሆኑም፤ እርሳቸው ግን በድርድሩ ገፍተውበት ጉዳዩን በድርድር ጨርሰዋል፡፡ ያም ይሁን፤ ሌላው አሳዛኝ ነገር የምስጢር ጥበቃ ውሉ ነው፡፡ ከስምምነት ነጥቦቹ አንዱ፤ ቦርዱ ወይም የቦርድ አባላት የድርድር/ስምምነቱን ይዘት ከማናቸውም ቡድን ወይም ከህዝብ ጋር እንዳንደራደር የሚያግድ መሆኑ ነው፡፡ በዚህም ሳያበቃ፤ ፕሬዚዳንቱ አሁንም ቦርዱን ሳያማክሩ፤ ከAESAONE ጋር በጥቅምት/ኦክቶበር የፍርድቤት ክርክርና ፍጥጫ እያለ፤ ግንኙነት ኖርማላይዝ ማድረግ በሚል ምክንያት፤ ለአቶ አብነት ገብረመስቀል ስልክ እንደደወሉላቸው በምስጢር ውስጣዊ ድርድር ለማድረግ ስለመሞከራቸው የነገሩን መርዶ አስደንጋጭ ነበር፡፡ በዚህ ውስጣዊ ድርድረ መሰረት፤ አቶ አብነት ገብረመስቀል 25 ሺህ ዶላር ከፍለው፤ ጉዳዩ ለህዝብና ለመገናና ብዙሀን ድብቅ ሆኖ እንዲቀመጥ ተመቻችቶ አስገዳጅ የስምምነት ውል እንዲፈረም ነበር፡፡ ፕሬዚደንቱ ለዚህ ስህተታቸው እስካሁንም ተጠያቂ አልተደረጉም፡፡
ከAESAONE ጋር በተደረገው የፍርድቤት ክስ ብናሸንፍም፤ ፌደሬሽኑ ከአቶ አስፋው ጋር በገባበት ክስ ጋር በተያያዘ (Asfaw v. ESFNA)፤ አሁንም በፕሬዚደንቱ ችኮነትና ከአቶ አስፋው ጋር የግል ቆርሾ ባላቸው ሶስትና አራት የማይበልጡ የቦርድ አባላት መንቻካነት የተነሳ፤ ፌደሬሽኑ የ8 ሺህ ዶላር ስምምነት እምቢ ብሎ፤ በፍርድቤቱ የ125 ሺህ ዶላር ፍርድ ተፈረደበት፡፡ በዚሁ ቢምረን ጥሩ ነበር፡፡ ጉዳዩ ግን እዚያ ላይ አላበቃም፡፡ በተወሰኑ ቅን ሰዎች ሸምጋይነት የአቶ አስፋው የጠበቃ ወጪ ተሸፍኖ በ60 ሺህ ዶላር ጉዳዩን ለመቋጨት ስምምነት ላይ ቢደረስም፤ አሁንም ፕሬዚደንቱና የግል ቂም ያላቸው እፍኝ የማይሞሉ የቦርድ አባላት እምቢኝ በማለታቸው ስምምነቱ ከሽፏል፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ግን፤ ፌደሬሽኑ በታችኛው ፍርድቤት ለሽንፈት የዳረገውን ጠበቃ ምክር ተከትሎ የ125 ሺህ ዶላር ፍርዱ ላይ ይግባኝ ማለቱ ነው፡፡ ይሄንን ይግባኝ 14 ቡድኖች ደግፈውታል ቢባልም፤ የደጋዎቹ ቡድኖች ስምዝርዝር ግን እስካሁን ይፋ አልሆነም፡፡
ግልጽነት የሚጎድላቸው፤ አለም የተቀበላቸውን መርሆችም ይሁን የፌደሬሽኑን መተዳደሪያ ደንቦች የሚጥሱ ዝምድናን መሰረት ያደረጉ አሰራሮች፤ ፕሮፌሽናሊዝም የጎደለው አሰራር፤ ግልጽ ያልሆነ ጨረታና የመሳሪያ ኪራይ፤ የቬንደሮች መብትና አያያዝ ጉዳይ፤ ነጻና ገለልተኛ የሆነ አካል ምርመራ ወይም ኦዲት ያለመኖሩ ሌሎች የሚጠቀሱ ችግሮች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ዋጋ ለመቀነስ ወይንም ለሌላ ስውር ጥቅማጥቅም ሲባል፤ ደረጃው የወረደ የሙዚቃ መሳሪያ መከራየት የተለመደ አሰራር ሆናል፡፡ በዚህም ምክንያት፤ ባለፈው አመት በሜሪላንድ በነበረው ዝግጅት ያን ሁሉ ሰው ያሳዘነ የድምጽ ማጉያ መሳሪያዎች ጥራት ጉድለት ነበር፡፡ በዚህ ረገድ፤ የፌዴሬሽኑ የቀድሞው የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የነበረው አቶ ዮሀንስ ላስበላ አልሻረክም በማለቱ የደረሰበት ባንድ ወገን ተቃዋሚ ነው በሌላ ወገን ደግሞ የወያኔ ደጋፊ ነው የሚለው አሉባልታ ጥሩ ማስረጃ ነው፡፡ ሌላው ምሳሌ፤ የኦዲት ጉዳይ ነው፡፡ ፌደሬሽኑ ላለፉት 10 አመታት በውጪ ኦዲተሮች ተመርምሮ አያውቅም፡፡ ይሄንን በውጭ ኦዲተር የመመርመር አካሄድ በተለይ በቦርድ አባልነት የቆዩት ሰዎች አይደግፉትም፡፡ ምክንያት፤ በፌዴሬሽኑ ውስጥ የተንሰራፋውን ሙስና የሚያጋልጥና ለረጅም ግዜ በርስትነት የያዙትን ስልጣን የሚያሳጣቸው ስለሚመስላቸው፡፡ ብዙዎቹ ኦዲትን ከመጥላታቸው በላይ፤ ያለቦርዱ ፈቃድ፤ በፕሬዚደንቱ ውሳኔ በቤተሰብ አባል ሌላ አዲስ ቡድን በመመስረትና በመመዝገብ ታማኝ ሆነው ይቀጥላሉ፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የኦስትን ቡድን ነው፡፡
ለነገሩ በኢትዮጵያ ውስጥም ይሁን ከኢትዮጵያ ውጪ፤ በኢትዮጵያዊያን ተቋማት ዘንድ ለረጅም ግዜ ስልጣን ባለመልቀቅ የሚታማው መንግስት ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ፌዴሬሽኑ ራሱ የዚህ ችግር ሰለባ ነው፡፡ የስራ አስፈጻሚ አባል ሆነው የቆዩ ሰዎች ግዜያቸውን ሲጨርሱ ርቀው ሳይሄዱ የቦርድ አባል ሆነው ይሰነብቱና፤ መልሰው የስራ አስፈጻሚ አባል ሆነው ይመጣሉ፡፡ ስለዚህ ላለፉት 20 እና 30 አመታት ስልጣን ላይ የቆዩት የቦርድ ወይም ስራአስፈጻሚ አባላት፤ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ አንዱ ስልጣን ላይ ሙጭጭ የሚሉበት ምክንያት ለአመታት የዘለቀ ሙስናና የጥቅም ግጭት ሊጋለጥ ይችልብናል የሚል ስጋት ነው፡፡ ስለዚህ ብዙዎቹ ኦዲቱን አይወዱትም፡፡ በርግጥም ፌዴሬሽኑ ኦዲት ቢደረግ፤ አላግባብ የባከነ ወይም የት እንደደረሰ የማይታወቅ ገንዘብ በብዛት ይገኝ ነበር፡፡ አንዱ የዚህ ለአመታት የዘለቀና የተቀጣጠለ ሙስና ማሳያ ጥሩ ምሳሌ፤ የቶምቦላ ሽያጭ ነው፡፡ ለምሳሌ፤ በሜሪላንዱ ውድድረ በቶምቦላ ሽያጭ የተገኘው 80 ሺህ ዶላር ሲሆን፤ የመኪናው መግዣና መሰል ወጪዎች 30 ሺህ ቢሆንም፤ በገቢ መመዝገብ የነበረበት በገቢ የተመዘገው ግን 40 ሺህ ዶላር ብቻ ነው፡፡ በ2012 በዳላስም እንዲሁ፤ 80 ሺህ ዶላር ገቢ መመዝገብ ሲገባው፤ የተመዘገበው 40 ሺኅ ብቻ ነው፡፡
ከገንዘብ አያያዝና አወጣጥ እንዲሁም ከኦዲት አለመደረግ በተጨማሪ፤ በክብር እንግዶች አመራርጥ ላይ፤ ከቡድኖች ጋር ባለ ግንኙነት፤ በተጫዋቾች አያያዝና መድህን ጉዳይ ላይ፤ በስብሰባ አጠራርና አካሄድ፤ በዝግጅት ከተማ አመራረጥ ጉዳይ ላይ፤ ፌደሬሽኑ ከፍተኛ ችግሮች ይስተዋልበታል፡፡ ለምሳሌ ከተጫዋቾች ጋር በተያያዘ፤ ባንድ ሆቴል ክፍል እስከ ስምንት ተጫዋቾች እንዲተኙ የሚደረግበት አካሄድ ስህተት ነው፡፡ ተጫዋቾች ቢሰበሩ፤ ቢጎዱ፤ ቢታመሙ በቂ የህክምና መድህንና ዋስትና የላቸውም፡፡ ሌላው፤ የዚህ አመት ከተማ አመራረጥ ላይ፤ የፌደሬሽኑን የገንዘብ አቅም፤ ያለበትን ሁኔታ፤ ባለፈው አመት የተሰራውን ስህተት የማረም እድል፤ ፌደሬሽኑ ሊያገኝ የሚችለውን ገቢ፤ አቶ አለማየሁ በጽሁፋቸው እንደገለጹት ከAESAONE ጋር ባለው ፉክክርና ፈተና ራሱ፤ የዘንድሮውን ዝግጅት በዋሽንግተን ዲሲ ማድረግ የተሻለ እንደነበር ማንም የማይስተው ሀቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ፤ በፌደሬሽኑ ቋሚና ዘላቂ ጥቅም ላይ ሳይሆን በጓደኝነትና ደጋፊ ማሰባሰብ ላይ የተጠመደው አመራር፤ ዝግጅቱን ሳን ሆዜ እንዲሆን አደረገ፡፡
ሌላው በጣም ያሳዘነንና ባንድ በኩል ፕሬዚዳንቱም ይሁኑ ደጋፊዎቻቸው የተቃወሟቸውን በወያኔ ደጋፊነት እየፈረጁ፤ እነሱ ግን አሳፋሪ ስራ የሰሩበት አጋጣሚ በሳኡዲአረቢያ ከተጎዱ ኢትዮጵያዊያን ጋር በተያያዘ ያደረጉት ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ በህጉ መሰረት እስከ 3000 ዶላር በራሳቸው ፈቃድ ማውጣት ቢችሉም፤ ይሄንን የሚያህል ብሄራዊ ውርደትና የዜጎቻችንን ስቃይ በፕሬዚዳንቱ ፍቃድ ብቻ በሚደረግ የ3000 ዶላር ልገሳ መገላገል አይቻልም ብለን ብዙዎቻችን የቦርድ አባላት እናምናለን፡፡ ፌደሬሽኑ ከዚህ በፊትም፤ በተለያዩ አጋጣሚዎች ለተጎዱ ኢትዮጵያዊያን የገንዘብና የቁሳቁስ እርዳታ አድርጓል፡፡ ለምሳሌም በድሬዳዋ በጎርፍ ለተጠቁ ኢትዮጵያዊያንና በድርቅ ለተጠቁ ወገኖቻችን ለያንዳንዳቸው ያደረገው የ25 ሺህና 30 ሺህ ዶላር እርዳታ ይጠቀሳል፡፡ ከ3ሺሁ ከፍ ቢልም፤ ለሳኡዲ ተጠቂዎች 5 ሺህ ዶላር ብቻ መርዳት አሳፋሪ ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ ይሄንን ጉዳይ ለቦርዱ አቅርበው፤ ጠቀም ያለ ገንዘብ ከአባላትና ከየቡድኖች ለማዋጣት ፍላጎትና ጥሪ የነበረ ቢሆንም፤ በፕሬዚዳንቱ ቦርዱን ያላማከረና ያላማከለ ውሳኔ ምክንያት ርዳታው 5 ሺህ ዶላር ብቻ እንዲሆን ሆኗል፡፡
የፌዴሬሽኑ ህግ በግልጽ እንደ ቴክሳስና ዋሽንግተን ያሉ ከሁለት በላይ ቡድን ያላቸው ከተሞች ተጨማሪ ቡድን እንደማያገኙና ለሌሎች ቡድን ለሌላቸው ከተሞች እድሉ እንዲሰጥ ቢደነግግም፤ አሁንም ፕሬዚዳንቱ በመጪ ውሳኔዎች ላይ ድምጽ ብልጫ ለማግኘት በሚል ሰበብ ብቻ ህጉን በተጻረረ መልኩ በቴክሳስ ሀገረግዛት የሚገኘው የኦስትን ቡድን ወደፌደሬሽኑ እንዲገባ አድርገዋል፡፡ ይሄ ውሳኔ የመነጨው ከትውውቅ ወይንም ከጓደኝነት እንጂ ከንጹህ አሰራር አይደለም፡፡ አሁንም ፕሬዚደንቱ የቡድን ተዋካዮች ወይም የቦረድ አባላት ከሳቸው ጋር ሳይስማሙ ሲቀሩ፤ ወደቡድኖቹ በመውረድ የሚፈጥሩት የሚፈጥሩት ብጥብጥና ክፍፍል የማይታለፍ ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው የላስ ቬጋስ ቡድን ነው፡፡ የፌደሬሽኑ ችግሮች ከዚህም ይከፋሉ፡፡ የላስ ቬዳስንም ይሁን የኦስትንን ምሳሌ የጠቀስነው በፕሬዚደንቱ አካሄድ ላይ የተስተዋሉትን ህግንና ስርአትን የሚጻረሩ ስህተቶችን ለመጠቆም እንጂ፤ ከነዚህ ቡድኖች ጋር ምንም አይነት ፐርሰናል ችግር የለብንም፡፡ ለወደፊቱ አካሄዳችን የሚጠቅም ከሆነ የፕሬዚደንቱንም ይሁን የፌደሬሽኑን ችግሮች በቀጣይ ጽሁፎች እንዘረዝራቸዋለን፡፡
እውነታው ይሄ ሆኖ ሳለና፤ የ16ቱ ቡድኖች ተወካዮች ተቃውሞ ወይንም ጥያቄ የመነጨው ተጠያቂነትንና ግልጽነትን ከማዳበር እንዲሁም ሙስናን ከመዋጋት አንጻር ሆኖ ሳለ፤ በፕሬዚደንቱና በዋና ጸሀፊው፤ እንዲሁም ባንዳንድ የቦርድ አባላት አበረታችነት፤ ይሄንን ጥያቄ ባነሳነው ሰዎች ወይም ተወካዮች ወይም ቡድኖች ላይ የቀረበው የወያኔ ተላላኪዎች፤ ስውር አጀንዳ አራማጆች ምናምን የሚለውን ክስ አሳሳችና፤ የማይጠቅም ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በፌዴሬሽኑ ውስጥ ያለው ጦርነት የሌባና ፖሊስ ጦርነት ነው፡፡ ለአመታት የዘለቀው የሌብነት ሂደት በዚህም አመት በሳን ሆዜ እንዲቀጥል የሚፈልግ ቡድን አለ፡፡ ለምሳሌ የቲኬት ህትመት ጉዳይ አሁንም ግልጽ አይደለም፡፡ የውጭ ኦዲተርና ለቁጥጥር የሚመች እንደ ቲኬት ማስተር ያለ አሰራር የማይወዱት ግለሰቦች፤ ያለቦርዱ እውቅና አዲስ የገንዘብ መቀበያ/ማስከፈያ ሲስተም እንደሚኖርም ተነግረዋል፡፡ የዚህ ፌደሬሽን ባለቤት የሆነው ህዝብ፤ በአሁኑ ሰዓት ሞያውን፤ ገንዘቡን፤ ጉልበቱን ሳይሰስት መስዋእት በማድረግ፤ ለ23 አመታት አገራችንን በጉልበት እየገዛ ያለውን አምባገነን የኢህአዴግ መንግስት ከስልጣን ለማውረድና፤ በምትኩ በዘር በሀይማኖት ሳይለይ የሰው ልጆች መብት የሚከበርባትና ፍጹም ሰላምና ዴሞክራሲ የሰፈነባትን ስርአት አምጥቶ ለመተካት ርብርቦሽ የሚያደርግበት ሰኣትን ተገን በማድረግ፤ የግላቸውን ጥቅም ለማሳካት የሚሮጡ ማፊያዎች፤ ያልተገነዘቡት ነገር ግን፤ ለጊዜው እንጂ፤ ወያኔ በሚል ካርድ ከእይታ አምልጠው አይቀሩም፡፡
ስለዚህም፤ የዚህ የአመታት ትግል ውጤት የሆነው ፌደሬሽን ደጋፊዎች፤ የቦርድ አባላት፤ የቡድን መሪዎች፤ እነዚህ ከላ የጠቀስናቸውም ይሁኑ ሌሎች የፌዴሬሽኑ ችግሮችና ድክመቶች እንዲፈቱ የበኩላችሁን ጥረት እንድታደርጉ ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡ የተነሱት ጥያቄዎች ወያኔ ከመሆን አለመሆን ጋር የሚያገናኛቸው ምንም አይነት ነገር የለም፡፡ ዛሬም ነገም ወደፊትም የፌዴሬሽኑ ማእከላዊ ተልእኮ ኢትዮጵያዊነትን ማክበርና ማስከበር እንደሆነ እናምናለን፡፡ ለዚህም ዓላማ እንታመናለን፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ግን ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲኖር እንታገላለን፡፡ ይሄንን ትግላችንን የወያኔነት ስም በመስጠት ለማደናቀፍ የሚሞክሩ ሰዎች ካሉ፤ በመረጃ እንፋለማቸዋለን፡፡
ለማንኛውም ትግላችን ይቀጥላል፤ ሳን ሆዜ እንገናኝ፡፡
ሰኔ፤ 2006/2014



