ዮሃንሰ ደሳለኝ (ጋዜጠኛ)

ወዲህ የሁለት ክርስቲያን ወዲህ ደግሞ የሁለት ወገን ደም እንዳይፈስ ቅዱሳን አባቶቻችን በፀሎትና በሽምግልና የተጉበት ጉዳይ ፍሬ አፍርቶ ከዛግዌ ሥርዎመንግሥት ወደ ሰለሞናዊ ሥርዎመንግሥት በሰላም ተሸጋገረች።ያለ ጠብታ ደም ይህ ከሆነ ስምንት መቶ ዓመታት ተቆጠረ። ከዚያ ወዲህ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ህዝብ እንደናፈቀው ገዥዎች እንደተሳለቁበት እነሆ ወያኔ ደራሲው አዘጋጁና ተዋናዩ የሆነበት "ምርጫ" ከፊታችን ቆሟል።

ምርጫው እየተቃረበ በመጣ ቁጥር ከገዢው ፖርቲ ባልተናነሰ ተቃዋሚዎች፣ ህዝቡና አለምአቀፉ ማህበረሰብ በዉል የሚያዉቁትን ሐቅ ወደጎን ገሸሽ አድርገው ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እንደሚካሄድ ለማስመሰል ድራማውን በአጃቢ ተዋናይነት ተቀላቅለዋል።

ግን ከዚህ "ምርጫ" ምን ይጠበቃል? ሁሉም ያውቁታል እያወቁም ውጤቱን በጉጉት ይጠብቁታል። የኢህአዴግ ደጋፊዎችና አባላትማ በማን ይመረጥ ይሆን ቀልባቸው ተንጠልጥላ ልባቸው ሊፈነዳ ደርሷል! ወይ ስላቅ።

ኢሕአዴግ ይመረጣል የተበላ ዕቁብ ነው በእርግጥ ትክክለኛው ቃል "ይመረጣል " ላይሆን ይችላል ግን ይመረጣል።

ወያኔ ኢህአዴግ ከሚመረጥባቸው ምክንያቶች አንዱና ዋናው ፖለቲካዊውን በልኲ እየሰፉ የሚሰጡት ምዕራባውያን አሁንም ከጐኑ መሆናቸውና ሌላው ራሱ የሰራው ኃጥያት ነው፣ (ወንጀል የሚለው ቃል አንሶብኝ ነው)

"የወጋ ቢረሳ" እዚህ ጋር አይሠራም ኢሕአዴግ የወጋውን የሚረሳ ድርጅት አይደለም ኃጢአቱንም አብጠርጥሮ ስለሚያውቅ ለወያኔ ባለሥልጣኖች በሥልጣን መልቀቅና በስቅላት መገደል መካከል ያለውን ልዩነት ማንም አስረድቶ ሊያሳምናቸው አይችልም። ይህ ስርዓት አልሞት ባይ ተጋደይ ከሆነ ሰንብቷል ይህንንም ከመቼውም ግዜ የተሻለ እንደነበር ብዙዎች በሚስማሙበት ምርጫ 97 በደንብ በተወለወለው የጠመንጃው አፈሙዝ አረጋግጦልናል።

በየት በኩል ነው ሌላ ፖርቲ ወደ ኢሕአዴግ ወንበር መንጠልጠል ቀርቶ አጮልቆ የሚያየው፣ እኔ ጥርጣሬ አለኝ፣ የኢሕአዴግ ማሸነፍ የፆታየን ያህል እርግጠኛ ነኝ፣ ጥርጣሬየ ግን የተቃዋሚዎቹ ተቃዋሚነት ላይ ነው፣ አባሎቻቸው እየታፈኑና እየተገደሉ ጋዜጠኞች እንደነፍሰ ገዳይ ሞት እየተፈረደባቸው እነሱ ተወዳድረው ሊያሸንፉ ነው ወይስ ሊያሟሟቁ?! እውነቱን ለመናገር ለምርጫ መንቀሳቀሻ ተብላ የምትበተንላቸው ሳንቲም ላለመግፋት ብለው ይሆናል ከሚለው በስተቀር ለምርጫ የቀረቡበት የተሻለ ምክንያት አይታየኝም።

ሰላማዊ ትግል መልካም ነው ነገር ግን ሰላማዊ ትግልም ትግል ነውና በዚህ እንቅስቃሴ መድረክ ውስጥ እንደማታሸንፍ እርግጠኛ ሆነህ መታገል ግን ትግልን ዋጋ ከማሳጣት ያለፈ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሎ አይጠበቅም፣ ጭራሹን ወያኔ ከ97 በተማረበትና ጠመንጃና ምርጫ ቦርድን ጠበቅ ባደረገበት ሰዓት፣ ጥቅማቸውን እስካስጠበቁ ድረስ አራጅ አሸባሪዎችን እንኳን በማደራጀት ወደ ኋላ የማይሉትን ልዕለ-ኃያላን ከጕኑ በቆሙበት ሁኔታ እናሸንፋለን ብሎ ወደ ምርጫ መግባት ጥቅሙ ለወያኔ በመሆኑ ተቃዋሚነታቸውን ጥያቄ ውስጥ ከቶታል፣ ምን ማለት እንደሆነ ከገባችሁ እሰይ ለእኔ ግን አልገባኝም አይገባኝምም።

ታላቁ መፅሐፍ በነብር የመሰለውን ህዝብ ጅራቱን ይዟል፣ ከሶስት፣ አስርት ዓመታት በላይ በፖለቲካ ስንክሳር ውስጥ ያለፈው ይህ ድርጅት የነብሩን ጅራት እንደለቀቀ ወዲያው ከመቅፅበት ወደ እሱ እንደሚዞር ለማወቅ የምታስችል የሰናፍጭ ቅንጣት የምታከል ዕውቀት አያጣም

እና ምን ይሁን?

እንደኔና እኔ የተሻለ የሚመስለኝ ብሔራዊ ኩርፊያና አለመታዝ ነው። በአደራ እንዳስቀመጡት ዕቃ ፖርላማ ገብቶ ከመጐለት ሁሉ ነገር በአፍንጫየ ይውጣ ብሎ መገለል፣ በአጠቃላይ ወያኔን ከራሱና ከአሻንጉሊት ድርጅቶቹ ጋር እርቃኑን ማስቀረት፣ ከዚህ በፊት የተሞከሩትን ኢሕአዴግን የማሳጣት ዘዴዎችን መጠቀም አዳዲስም መፍጠር ጉልበት ያፈረጠሙትን የወያኔ ድርጅቶችን ማግለል ለደጋፊዎቹ በሶሻል ሚዲያዎች ላይ በጎም ክፉም ምላሽ አለመስጠት የመሳሰሉትን መተግበር

የተሻለ ኃሳብ ያላቸው እንዳሉ አምናለሁ እኔ ባለችኝ ትንሿ ማሰቢያየ ግን ኢሕአዴግ ራሱ ሰርዓት አስከብሮ ራሱ ምርጫ ቦርድ አቋቁሞና ሾሞ ራሱ ታዝቦ፣ በአጠቃላይ ደራሲው አዘጋጁ ተዋናዩ ያው ወያኔ በሆነበት መድረክ መሸነፍ ዘበት ነው።

ሁላችንም ደግሞ ራሳችንን ማታለል ካልፈለግን በስተቀር የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ብሎ ራሱን የሚያሞካሸው ፖርቲ መስከረም ላይ በአራት ኪሎ ፖርላማ ውስጥ እንደሚመነሸነሽበት ጠንቅቀን እናውቃለን።

በተረፈ ግን ገዥው ፖርቲ ምርጫውን ጨርሶ ስለካቢኔው በሚያስብበትና በግልፅ ቋንቋ ማሸነፉን ለመግለጽ ሁለተኛው የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በሚልበት በዚህ ወቅት ከነአፈሙዙ ዘርጥጨ አፈርጠዋለሁ ብሎ የሚያስብ ካለ አንድም አለቅጥ የሆሊውድ አክሽን ፊልሞችን ማየት የሚያበዛ አልያም ደግሞ በሆሜር የጀብድ ተረቶች የተመሰጠ መሆን አለበት።

ከዚህ ይልቅ በሼህ ሁሴን ጅብሪል ትንቢት መሠረት ወያኔ ብን ብሎ እስኪጠፋ ወይ ደግሞ ፈጣሪ እጅግ ራርቶልን በዚህ ዘመን እንደ ቀደምት አባቶቻችን ከመንግሥትም ከእግዚአብሔርም ርስ በርስ የሚያስታርቅ ፃድቅ መጠበቅ ሳይሻል አይቀርም።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ