በበጋው ወር ፍራንክፈርት ትጣራለች
ዮሃንስ ደሳለኝ (ፍራንክፈርት - ጀርመን)
መቼም ማንም ልብ እንደሚለው ሞቃታማው የሐምሌ ወር ገና ብቅ ሲል ነው ጀርመናውያን በበጋ አለባበስ ደምቀው የሚታዮት።
የዘንድሮው በጋ (sommer, auf Deutsch) ወር ገና ሰኔ አጋማሽ ለይ ነበር ወበቁን የጀመረው ፣ ቀኑ እየጨመረ ወደ ዋናው በጋ ሲገባ ነዋሪውም የአለባበስ ሁኔታውን ከዕለቱ አየር ሁኔታ ጋር እየቃኘ ስያስኬደው አጀብ ያሰኛል ፣ አንዳንዶቹማ ከወገብ በታች ለመከለል ሲባል ብቻ ከሚጠለቅ አልባሳት ውጭ የላይኛውን የሰውነት ክፍል ማራቆት የለመዱትና የግድ የሆነ ድርጊት ነው፣ አሊያ ግለቱ እንኩዋን በልብስ በእርቃንም አቅል ያስታል።
ታዲያ እንግዲህ በዚሁ ወር ላይ ነበር ኢትዮጵያውያን ሰማይ ጠቀስና አሰራራቸው በሚያማልሉት ሕንፃዎችዋ በታጀበችው ፍራንክፈርት 13ኛውን የመላው አውሮፓ ከተሞች እግር ኳስ ውድድር ለመታደም ሳምንቱን የከተሙት።
ሳምንቱን በተለያዬ መርሃ ግብሮች የተጓዘው ይህ ውድድር ቅዳሜ July 18,2015 በአማረና በደመቀ ሁኔታ ፍጻሜ አግኝቷል ፣ በዕለቱ የነበረው ትዕይንተ በጣም መሳጭና ያማረ ሆኖ አልፏል ፣እንደው ድንገትእግር ጥሎት ለመጣ ሰው ትንሿን ኢትዮጵያ በተለይ አዲስ አበባን እዚያው ሜዳ ላይ ያገኛት ነበር የሚመስለው።
የተለያዩ የአገር ቤት ስያሜ ያላቸው ምግብ ቤቶች በሜዳው ላይ ተንሰራፍተው ሲታዩና በተለይ ደግሞ ቀጠና ሁለት ምግብ ቤትና ቅዱስ ገብርኤል ስጋ ቤት ያየ
ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ
አገርም እንደ ሰው ይናፍቃል ወይ
ሳይቀኝ አይቀርም ፣እናም በአጠቃላይ የነበረው ድባብ ተነፋፍቆ የቆየውን ኢትዮጵያዊ ያገናኘና ፈታ ዘና ያለ ስሜት እንዲጭር አድርጓል።
በመዝጊያው ውድድር ኢትዮ ለንደንና ኢትዮ ኖርዌይ ለዋንጫ ደርሰው በ 90 ደቂቃ ሳይሸናነፋ ቀርተው በመለያ ምት ኢትዮ ለንደን 5ለ4 አሸንፎ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል።
ሌላው ከዚሁ ዝግጅት ጐን ለጐን ESAT ቴሌቪዥን የተመሰረተበትን 5ኛ ዓመት በማስመልከት የተደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ ብዙዎችን አሳትፏል፣ በተለይ ደግሞ አንድ ቀደም ብሎ (አርብ ዕለት) ባማረውና በተንጣለለው የዛልባው ግሪሻይም አዳራሽ የተደረገው የ ESAT ገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ልዩ ድባብ የነበረውና አመርቂ ውጤት ያሰረመዘገበ ነበር።
በዚህ ዕለት ተጋባዥ እንግዶች ሆነው ከመጡት መካከል አርቲስትና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ታማኝ በየነና ጋዜጠኛ አፈወርቅ አግደው የዝግጅቱ ፈርጦች ሆነው አምሽተዋል።
ጋዜጠኛ አፈወርቅ አግደው በርዕቱ አንደበቱና በእነዚያ ሁሌም በአድማጭ ጀሮ ኩልል እያሉ በሚገቡት ጨዋታ አዘል ቁም ነገሮቹ እያዋዛ ያስተላለፈው መልዕክት ለነፃ ሚዲያ መጐልበት ለሚታገሉ ፣ ግዜና ገንዘባቸው ለሚሰው የነፃው ፕሬስ ቤተሰቦችና ለመላው የ ESAT ደጋፊዎች መነቃቃትን ፈጥሯል።
ከእሱ ቀጥሎ ታማኝ መድረኩን ተረክቦ በፍራንክፈርት ሰዓት አቆጣጠር ከ 5pm - 10pm (17:00 - 22:09) ያለ ምንም ዕረፍት መርቷል ፣ በዕለቱ ከነበረው ክስተት ግንባር ቀደሙን ሥፍራ ይዞ ያመሸው ለ ESAT ገቢ ማሰባሰቢያ የተደረገው ጨረታ የሚገርሙና የሚያስደስቱ ኩነቶችችን አስተናግዷል። ሁሉም በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለዚህ የህዝብ ዓይንና ጆሮ ለሆነ ሚዲያ ቀጣይነት በጋለ ስሜትና ከልብ በሆነ ቁርጠኝነት አጋርነታቸውን አሳይተዋል።
አዎ!!! እንዲህ ነው ኢትዮጵያዊነት
ESAT የብዙሃን ድምፅ ነው ካለ በኋላ ታማኝ አያይዞም አንዳንዶቹ ሁሉንም ያማከለ ስራ ሥሩ የአንድ ወገንን ብቻ አታስተጋቡ ለሚሉን መልሳችን ማን ነው የጋምቤላን ህዝብ መከራ የዘገበው ፣ ማነው የአርባምንጭ ወጣቶችን ተጋድሎ ፣ የወልቃይት ጠገዴን ፣ የአርማጭሆንና የመተማን ህዝብ ስቃይ ያጋለጠው በማለት ሁሉንም ወደ አንድ ዕይታ እንዲመጣ አድርጓል ወደ ህዝብና ነፃ ሚዲያ!!
ታማኝ በነበረው ቆይታ አዝናኝና ስሜት ኮርኳሪ እውነታዎችን አንስቶ ሁሌም ከውስጡ በሚቀጣጠለው ኢትዮጵያዊነት ማንነቱ አንዴ ከፍና ጐላ አንዴ ደግሞ ረገብ እያረገ በሚያወጣው ድምፁ ታዳሚው ኪሱን እየፈተሸ ESAT ን እንዲደግፉ አድርጓል
በተለይ በተለይ ደግሞ በአውሮፓ ከተሞች መካከል የጨረታ ፋክክሩ የሚያጓጓና ኢትዮጵያዊ አንድነት እንዲፀባረቅ ያበረከተው አስተዋፆ ይበል የሚባልና የሚያስመሰግነው ነው ፣ በመጨረሻም በዕለቱ ለጨረታ የቀረበውን Galaxy Tablet በርሊኖች አሸንፈው መልሰው ESAT ገቢ አድርገዋል ጨረታው ተዘግቷል።



