ህወሓት እንዴት ሰነበተ?
ተስፋዬ ገብረአብ
የህወሓትን የጓዳ ወግ ማወቅ አስቸጋሪ የነበረበት ዘመን እንደዋዛ አልፎአል። ዛሬ ቀዳዳቸው በዝቶ፤ ቴክኖሎጂውም አግዞ የፈፀሙት ብቻ ሳይሆን ያሰቡትም በቀላሉ ይገኛል። ዘመኑ የመረጃ ዘመን ነው። መረጃ ከሌለ ምንም ነገር የለም። ለችግሮች መፍትሄም አይገኝም። ወያኔ ዛሬ በአስር ሺዎች ኦሮሞዎችን በገፍ የሚያስረው ስለ ቄሮ በቂ መረጃ ስለሌለው መሆኑ ይታወቃል። ተቃዋሚ የፖለቲካ ተንታኞች ወይም የማህበራዊ ድረገፅ ፀሐፊዎች አንዳንድ ጊዜ አስቂኝ ስህተት ይሰራሉ። ማለትም ሳያውቁ ለወያኔ የሚጠቅም መረጃና ምክር ይፅፋሉ።
የወያኔ የፀጥታ ቢሮ መረጃዎችን እየመዘነ ወደ ጥቅም የሚለውጥ የተደራጀ ክፍል አለው። እንዲህ ያለው ማርሽ ቀያሪ ዘመን ብቅ ሲል ጊዜና መረጃን በጥንቃቄ መጠቀም ካልተቻለ ወርቃማ ዕድል ሊያመልጥ ይችላል። በመሆኑም በዚህ አጭር መጣጥፍ አንዳንድ ጠቋሚ ነጥቦችን ብቻ በጨረፍታ አነሳለሁ። ለመሆኑ ኃይለማርያም መንግሥት እንዴት ሰነበተ?
በህወሓት የውስጥ ግምገማ “በኦሮሚያ የተቀሰቀሰው አመፅ በጊዜ ሂደት ተዳክሞ ይቆማል” ብለው ያምናሉ። እጅግ አሳሳቢ የሆነባቸው ጉዳይ የአመፁ መቀጠል ሳይሆን ከዚህ በሁዋላ በOPDO (ኦህዴድ - የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት) በኩል ኦሮሚያን ማስተዳደር አለመቻሉን ማወቃቸው ነው። እናም ለዚህ ችግር መፍትሄ ለማግኘት ቁጭ ብለው ሲመክሩ መሰንበታቸው ታውቋል። ያስጨነቃቸው “OPDO ከድቷል” ተብሎ መታሰቡ አይደለም። የOPDO ቁንጮ እንዳልከዳቸው ያውቃሉ። የኢህአዴግ መዋቅር በቦታው አለ። “መንጥር” በተባለ ግምገማ አጠራጣሪውን አስወግደው፤ አዲስ መልምለው፣ ኦሮምኛ የሚናገር ኦሮሞ ያልሆነ ዜጋም ሰግስገው OPDOን ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ያስባሉ። ችግር የሆነባቸው OPDOን በመወከል ወደ ወረዳ የመሄድ ድፍረት መጥፋቱ ነው። በገጠር ከተሞች ያመፀው ህዝብ የOPDOን ወኪል ልብሱን እያስወለቀ፣ በኦሮሞ ቀጨሞ እየገረፈ ማባረሩ ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጥሮአል። ተማሪዎች ተሰብስበው OLFን የሚያሞግስ ዘፈን ይዘፍናሉ። ለዚህም ይመስላል፣ በግምገማቸው “ተደፈርን! ተደፈርን!” ሲሉ የተሰሙት። “ተደፈርን!” የሚለው አባባል ብዙ ትርጉም አለው። በሌላ አነጋገር “የወያኔ የማድረግ አቅም ተገመተ” ማለት ነው። እንደገና በሌላ አነጋገር “ህዝብ ምን ማድረግ እንደሚችል አወቀ።” ማለት ነው። ኦሮሞ ሲተርት “ብርሌ ከነቃ” እንደሚለው ...
ህወሓት ሀገሪቱን ተቆጣጥሮ የቆየው በጠመንጃ ጡንቻው ብቻ አይደለም። የኢኮኖሚ ምንጮችን ሁሉ በቁጥጥሩ ስር በማዋሉ ጭምር ነበር። ባለፈው ክረምት የኦሮሚያ ገበሬ 25% ቅድሚያ ከፍሎ ከጉና የንግድ ድርጅት ማዳበሪያ በዱቤ ወስዶ ነበር። ያልተከፈለው ቀሪ ገንዘብ ከ150 ሚሊዮን በላይ መሆኑ ታውቆአል። የነቃው ብርሌ ይህንን ዕዳ ይከፍላል ተብሎ አይታሰብም። ይህን የማስፈፀም ሥራ ይሠራ የነበረው የOPDO ካድሬ ዛሬ ውርደት እየተከናነበ ቀየውን ጥሎ በዋና ዋና ከተሞች ተከማችቶአል። ያልተሰደደውም ጠባዩን አሳምሮ ከመቀመጥ በቀር እየደነፋ ማዘዝ የሚችልበት ሁኔታ ላይ አይደለም። ህወሓትን በእግሩ ያቆሙ የንግድ ድርጅቶች ኦሮሚያ ላይ ክንፋቸው እየተሰባበረ ነው። የህወሓት ከፍተኛ ካድሬዎች በር ዘግተው የሚመክሩት OPDOን እንደገና ወደ ወረዳዎች በመላክ መዋቅሩን እንደነበረ ማስቀጠል የሚቻልበትን ዘዴ ነበር። ፌደራል ፖሊስ ወረዳ ወርዶ ማስተዳደር እንደማይችል ያውቃሉ። የፌደራል ፖሊስ የሰባተኛ ክፍል ተማሪዎች መቀለጃ መሆኑን አይተዋል። የነቃው ወጣት ቦታ እየለዋወጠ መንገድ እየዘጋ፣ ገበሬውም ምርቱን በመከልከል፣ የአፋኙ ሥርዓት መጠቀሚያ የሆኑ ተሽከርካሪዎችን በማጋየት፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን በማዳከም፣ ኢኮኖሚውን ከወያኔ ቁጥጥር ውጭ በማድረግ መንግሥትን ማስገደድና መቀየር እንደሚቻል ግንዛቤ አግኝቷል።
በርግጥ አባይ ፀሃዬ እና ስብሃት ነጋ ችግሮችን የመሻገር ልምድ አላቸው። እንዲህ ያለ ቆንጣጭ ፈተና ገጥሞአቸው ግን አያውቅም። ያም ሆኖ በቀላሉ ተስፋ ይቆርጣሉ ተብሎ አይታሰብም። የተቻላቸውን ያህል ይሞክራሉ። ይገድላሉ። ይገርፋሉ። ያስራሉ። ሆኖም ግን “ሚስማር በተመታ ቁጥር ይጠብቃል” እንዲሉ ወያኔ በነቃው ብርሌ ጠጅ ሊጎነጭ አይችልም። ለዚህም ይመስላል ከድብደባው፣ ከግድያው፣ ከእስሩ ጎን ለጎን ሌላ መላ መዘየዳቸው ተሰምቶአል። ይህም OPDOን ማጀገን (ጀግና ማድረግ) የሚል ነው። በዚህ ዘዴ የህወሓት አመራር አባላት የአመፁ ቀስቃሾች የOPDO አባላት መሆናቸውን መናገር ጀምረዋል። የOPDO ቁንጮም ያለ ጠባዩ ከህዝብ ጎን የቆመ መስሎ መታየት ጀምሮአል። በዚህ ቀመር መሰረት የኦሮሚያ አብዮት OPDO እጅ ላይ እንዲወድቅ ይመኛሉ። ከዚያም OPDO የህዝቡን ጥያቄዎች ከአፍ እየቀለበ ያስፈፅማል፣
ማስተር ፕላኑን አስቀረሁልህ!
ከአዲስ አበባ ማግኘት ያለብህን ጥቅም አስከበርኩልህ!
እስረኞችን አስፈታሁልህ!
የዚህ ዓመት የማዳበሪያ ዕዳ ተሰርዞልሃል!
OPDO እንዲህ ላሉ ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጠ፣ ዋናውን ጉዳይ ወደ ጎን በመተው ወደ ህዝቡ ይቀርባል። እናም ቀስ በቀስ “ጥያቄህ ተመልሶአል። ሌላ ምን ትፈልጋለህ?” ማለት ይጀምራል። እግረ መንገዱንም ቄሮን ያጠናል። የአመፁ መሪዎችን ሲመዘግብ ይቆያል። በመጨረሻ ህዝቡ የወለዳቸውን መሪዎች ያፀዳል። እናም እንደ ገና ሌላ ሃያ አምስት ዓመታት ለመግዛት ሜዳውን ያመቻቻል። አንድ ቀንም ዕድሜ ነው እንዲሉ።
የህወሓትን አመራር በጣም ካስጨነቁት ጉዳዮች ሌላው “አማሮች የኦሮሞን መነሳሳት ሊደግፉ ይችላሉ” የሚለው ስጋት ነበር። አስካሁን አማራውም ሆነ የአንድነት ኃይሉ ሙሉ በሙሉ የኦሮሞን አመፅ ከልቡ አልደገፈም። እርግጥ ነው፤ ለጥሪው አጥጋቢ ምላሽ ተሰጥቷል ማለት ባለመቻሉ እንጂ አርበኞች ግንቦት 7 እና ሰማያዊ ፓርቲ መላ ኢትዮጵያውያን ከኦሮሞ ህዝብ ጎን እንዲሰለፉ የሚያቀርቡት ጥሪ የሚመሰገን ነው። በአማራ ሕብረተሰብ በኩል የታዩ የመነሳሳት ምልክቶች ግን መልሰው ቀዝቅዘዋል። የአማራ ልሂቃንም ግራ የተጋቡ ይመስላሉ። መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆመው ይታያሉ። አምባሳደር እምሩ ዘለቀ ባስነበቡት ጽሑፍ እንዲህ ሲሉ ግራ መጋባታቸውን ገልፀዋል፤
“... በምንም መንገድ ሥልጣን የሚፈልጉ ፖለቲከኞች ‘አብረን ወያኔን እንውጋ ይሉናል፤ ነገር ግን እኛ የምናውቀው አንድነት በሃቅና በእኩልነት ሲመሰረት ነው፤ እኛ የምንመኛት የምንሞትላት ኢትዮጵያ ሁሉም ዜጋ በነጻነት መብቱ በሕግ ተጠብቆ፤ በኢትዮጵያ ጠረፍ ውስጥ የትም ሂዶ፣ የትም ውሎ፤ የትም ሠርቶ፤ የትም አፍርቶ፤ የሚኖርባት ሀገር ስትሆን ነው። ... አሁን ደግም በከተምንበት በኖርንበት ሀገር የፈረንጅ ግርፊት ወሮበሎች ተነስተው ‘ባዕድ ናችሁ፣ ቦታም የላችሁ’ ይሉናል። ዛሬ ደሞ ዙረው እንደሚያርዱን እያወቅን አብረን እንዝመት ይሉናል። ዝምታችን ትግስታችን ሞኝነት መስሏቸዋል።”
አምባሳደር እምሩ ከላይ ያለውን አንቀጽ ከማስፈራቸው በፊት ቪዥን ኢትዮጵያ እና ኢሳት ባዘጋጁት የፓነል ውይይት ላይ ዶክተር መስፍን አብዲ ODFን ወክሎ ያነበበውን ጽሑፍ ተከታትለው ቢሆን ኖሮ ብዕራቸው ያንቃቸው ነበር ብዬ እገምታለሁ። ማናችንም እንደምናውቀው የኦሮሞ ህዝብ አማራን የማረድ ዝንባሌ ያሳየበት ጊዜ አልነበረም። ጉዲፈቻ እና ሞጋሳ የተባሉ ዝነኛ ባህል ያለው ህዝብ እንደ አውሬ እንዲታይ የቀድሞዎቹ ፊውዳላዊ ሥርዓቶች የሠሩት የፕሮፓጋንዳ ሥራ ዛሬም እንደ እውነት ይታያል። በቀለ ገርባ አማራን ያርዳል ተብሎ ይታመናል? መኩሪያ ቡልቻ አማራን ያርዳል? በያን አሶባ ነው የሚፈራው? አሰፋ ጃለታ፣ መሃመድ ሃሰን፣ ጠሃ አብዲ እነዚህ ናቸው አማራን ያርዳሉ ተብለው የተሰጉት? ወይስ ጃምቦ ጆቴ ይሆን? ምናልባት እስከዛሬ በዓይን ያልታዩ ሹል ቀንድ እና ጩቤ ጥርስ ያላቸው ኦሮሞዎች ይኖሩ ይሆን? አምባሳደር እምሩ፣ “ያርዱናል” ብለው ከሚፈሯቸው የፖለቲካም ሆነ የኮሚኒቲ መሪ ኦሮሞዎች መካከል አንድ ሁለት ስሞችን ቢጠሩልኝ አባባላቸውን ለመመዘን ባስቻለኝ ነበር። መቼም አምባሳደሩ እንዳያርዳቸው የሰጉት መላ የኦሮሞን ህዝብ በጥቅሉ ሊሆን አይችልም። ለመሆኑ “ከኦሮሞ ጋር ተዋልደናል፣ ከኦሮሞ ጋር ተጋብተናል” የሚለው ነባር አባባል፣ “ዞረው ያርዱናል” ከሚለው ጋር እንዴት ሊጣጣም ይችላል? የተዋለደና የተጋባ ይተራረዳል እንዴ?
ነገሩ ወዲህ ነው ...
የአምባሳደር እምሩ የአመለካከት ምንጭ “አማራ ካልመራት ኢትዮጵያ ሀገር ልትሆን አትችልም” ከሚል የትምክህት ኩሬ የሚቀዳ ሳይሆን አልቀረም። ከዓመታት በፊት ሌንጮ ለታ ይህን አመለካከት ደጋግሞ እንደተቸው አስታውሳለሁ። ቃል በቃል ባይሆንም “አማራ ያልሆኑ ዜጎች ኢትዮጵያን ሊመሩ እንደሚችሉ፣ እኩል ኃላፊነት ሊሰማቸው እንደሚችል ማመን ሳይቻል እንዴት የጋራ ሀገር መመስረት ይቻላል?” የሚል መንፈስ ያለው ንግግር ማድረጉ ትዝ ይለኛል።
ያም ሆኖ አምባሳደሩ ያንፀባረቁትን አይነት የስጋት ስሜቶችን በማራገብ ረገድ ወያኔ እየተሳካለት ሳይሆን አይቀርም። በተለይ የአማራውን የሕብረተሰብ ክፍል በሌሎች አጀንዳዎች ለማስጨነቅ በርትቶ በመሥራት ላይ ነው። ‘በአንድ ጥይት - ሁለት ጠላት’ እንዲሉ “ኦሮሚያ ከአዲሳባ የምታገኘው ጥቅም” የሚለውን በሕገመንግሥቱ የፀደቀ መብት ዝርዝሩን ለመፃፍ አሁን ተንቀሳቅሰዋል። በአንድ በኩል ‘ለኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ምላሽ ሰጠሁ’ ለማለት ያስችላቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ለአዲሳባ ነዋሪ አፍ መዝጊያ ማስፈራሪያ ሆኖ ያገለግላል። ኦሮሚያ ከአዲሳባ የምታገኘው ጥቅም ተፈፃሚ እንደማይሆን ግልፅ ነው። ምናልባት አማራ ወይም የአንድነት ኃይሎች ከበረቱ አጀንዳው ከፍ ብሎ ይውለበለባል። በምርጫ 97 አዲሳባ ላይ ሲሸነፉ፤ “የኦሮሚያ ዋና ከተማ ፊንፊኔ ናት” እንዳሉት ማለት ነው። ለነገሩ፣ “አዲሳባ ንፁህ ውሃ ከኦሮሚያ ወስዳ ስታበቃ፤ እጣቢውን እና ቆሻሻዋን መልሳ አሮሚያ ላይ ትደፋለች” የሚለውን ቅስቀሳ የጀመሩት ራሳቸው ወያኔዎች ነበሩ። ዞረም ቀረ የአዲሳባ ጉዳይ ለክፉ ጊዜ ያገለግል ዘንድ ሳጥን ውስጥ የሚቆለፍበት መሳሪያ ሆኖ የሚቆይ ይመስላል። ወያኔ ከሚመካባቸው ፈንጂዎቹ አንዱ “አዲሳባ - ፊንፊኔ” አጀንዳ ነው።
የተቀሰቀሰው የኦሮሞ ህዝብ አመፅ ጣልቃ ገብቶ አደናቀፋቸው እንጂ ከአዲሳባ ማስተር ፕላን በፊት ወያኔ ቀዳሚ አጀንዳ ጎንደርና ጎጃምን ማፈራረስ ነበር። በርግጥ በተለምዶ የህወሓት ቀዳሚና ታሪካዊ ጠላት ተብሎ የሚታወቀው የሸዋ አማራ ነው። የአካባቢያችን ፖለቲካ የመሬት ፖለቲካ እንደመሆኑ ግን በዚህ ወቅት የሸዋ አማራ የሚያጓጓ መሬት አለው ተብሎ አይታሰብም። የሸዋ አማራ ከዘመነ ምኒልክ ጀምሮ መሬት ጠቦት፣ ከሚኖርባቸው ኮረብታማ ቦታዎች እየለቀቀ በአብዛኛው እያረሰ የሚኖረው በኦሮሚያ እና በሲዳማ ነበር። ከትግራይ በቀር በሌሎች ከተሞችም እየነገደም ሆነ እየሸቀለ ኑሮውን ሲገፋ ቆይቷል። በመሆኑም የወያኔ ኢላማ ያተኮረው ጎንደር እና ጎጃም ላይ ሆኖ ቆይቷል። ከእነዚህ የወያኔ አሻጥሮች አንዱ የቅማንት ጉዳይ ነው። ቅማንት በርግጥ አማራ አይደለም። ከአማራ ጋር ደም ወደሚያፋስስ ፀብ የሚያስገባው ልዩ ምክንያት ግን አልነበረም። ክስተቱ ወያኔ ሠራሽ ነው። ከቅማንት ቀጥሎ በዚህ መልኩ እንዲነሳሳ የተዘጋጀው አገው ነው። የአገው የመሬት ጥያቄ ጎጃምን ጎጃም ከመሆን ያስቀራታል ተብሎ ሲሠራበት ቆይቷል።
እንደ ወያኔ አስተሳሰብ የቅማንት መነሳሳት በአብዛኛው የሰሜን ጣና ኃይቅን ክፍል ከአማራ ነፃ ያወጣል። ነገ ደግሞ ዋታ (ወይጦ) በደቡብ የጣና ኃይቅ ይዞታ ላይ ጥያቄ እንዲያነሳ ይቀሰቀስ ይሆናል። ምናልባት ጣና ኃይቅን ከአማራ ቁጥጥር ነፃ የማድረግ ረጅም ግብ ይኖራቸውም ይሆናል። አካሄዳቸው የሚጠቁመኝ ይህንን ነው። ወያኔ ነዳጅ አልቆበት ካልቆመ፤ ዋታ እና ቅማንት በጣና ኃይቅ ባለቤትነት ላይ ከአማራ ጋር በሚያደርጉት ፍልሚያ አሸማጋይ ሆኖ ብቅ ይል ይሆናል። ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ ፈንጂ መቅበር የሚባለው እንዲህ አይነቱ ድርጊት ነው። የዚህ አይነቱ ሴራ ግብ “ትግራይ ሪፖብሊክ” የሚለው የማሌሊት ማኒፌስቶ ተከድኖ በመቀመጡ ሊሆን ይችላል።
ጎጃም እና ጎንደር ከቅማንት እና ከአገው ጋር ለረጅም የርስበርስ ግጭት ታጭተው ሳለ የዋቀዮ ፈቃድ ሆነና የኦሮሚያ አመፅ ፈነዳ። ይህ ለወያኔ ዱብ እዳ ነበር። ስለዚህ ወያኔ አሮሚያን እስኪያስተኛ ከአማራ እና ከአንድነት ኃይሎች ጋር መጋጨት እንደማያዋጣው ተረዳ። ስለዚህ የቅማንት ጉዳይ ለጊዜው እንዲቀዘቅዝ በፕሮፓጋንዳው ብዙ ጣረ። ለሱዳን ስለተሸጠው መሬትም ‘አላየሁም! አልሰማሁም!’ ሲል ካደ።
እነሆ! የጊዜ ጎማ መሽከርከሩን ቀጥሎአል ...
ከመሬት ጋር በጥብቅ የተቆራኘው የአካባቢያችን ፖለቲካም መጦዙን ቀጥሎአል። ኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ጅቡቲም ቢሆኑ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከዚሁ ቀውስ ጋር ስማቸው መነሳቱ አልቀረም። የአፍሪቃ ቀንድ ሀገራት ህዝቦች በጣም ጥቂት ናቸው። ታሪካቸው ረጅም ነው። የጋራም ሆነ የተናጠል የተያያዘ ታሪክ አላቸው። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ህዝቦቹ የደም ትስስር አላቸው። መሬታቸውም ሆነ ባህራቸው ሃብታም ነው። ህዝባቸው ግን ዝንተዓለም ድሃ ሆኖ ቆይቷል። መተባበር ቢችሉ ለራሳቸው ቀርቶ ለአካባቢያቸውም መትረፍ በቻሉ። የኃያላን ሀገራት አሻንጉሊት ከመሆን ቢቆጠቡ ፊታቸውን ወደ ልማት ማዞር በቻሉ። በተለይ ግን አሁን ላለንበት የአካባቢያችን ቀውስ ነቀርሳው የወያኔ ሥርዓት ነው ብዬ በጥብቅ አምናለሁ። ወያኔ በያዘው መንገድ ጉዞውን ከቀጠለ አካባቢያችን ለከፋ ጦርነት፣ ለከፋ ስደትና ለከፋ እልቂት ሊጋለጥ ይችላል። ይህ እንዳይሆን፣ በሞራልም፣ በእውቀትም ለእውነተኛው እኩልነት፣ ለፍትህ፣ ለዴሞክራሲ በቁርጠኛነት መነሳት ይገባል። “በቃ!” የሚለው ቃል ከቃል ደረጃ አልፎ ወደ ተግባር ሊለወጥ ይገባል። “በቃ!” ስለተባለ አይበቃም። መብቃት ያለበት እንዲያበቃለት ተግባር ያስፈልጋል። በዚህ ዘመን እንደ ኢያሪኮ በጩኸት የሚፈርስ ግንብ የለም። ከኦሮሞ ህዝብ መነሳሳት ጎን መሰለፍ የጊዜው ወሳኝ ጥያቄ ይመስለኛል።
ተስፋዬ ገብረአብ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



