“ይቅርታ” ወይም “ሰላም”
ተስፋዬ ገብረአብ
ኃይለማርያም ደሳለኝ ባለፈው ሣምንት ያደረጉት ቃለመጠይቅ አነጋጋሪ ነበር። ከኦሮሞ ህዝብ አመጽ ጋር በተያያዘ የሰነበተውን ችግር ሌላ አካል ላይ ማላከክ እንደማይገባ መናገራቸው ከኢህአዴግ ጠባይ አንፃር ያልተለመደ ነበር። በውስጥ ባለ ችግር ምክንያት የህዝብ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ባለማግኘታቸው ህዝብና መንግሥት ተቃቅረው ጉዳዩ ወደ ግጭት ደረጃ መድረሱን ማመናቸው አንድ እርምጃ ወደፊት ነው። ችግሩ የመልካም አስተዳደር እጦት መሆኑን መግለፅ መቻላቸው ይደነቃል። ኃይለማርያም በዚህ ደረጃ ችግሩን አምነውና ተቀብለው ሲያበቁ፤ በመጨረሻ ለተፈጠረው ችግር በጥቅሉ ህዝብን ይቅርታ ጠይቀዋል። ይቅርታ ጥየቃው ካንገት በላይ ነው ወይስ ካንገት በታች ለጊዜው ባናውቅም፤ ይቅርታ መጠየቅ በራሱ ሥልጣኔ ነው።
እንግዲህ በመቀጠል ወደ ዝርዝር ጉዳይ እንግባ።
ኃይለማርያምይቅርታ ሲጠይቁ በመሰረቱ ምን ማለታቸው ነው? ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ላይ በሕጉ መሰረት ሰላማዊ ተቃውሞ ማካሄድ ተፈቅዶአል ማለት ነው? ከዚህ በኋላ የፌደራል ፖሊስ ሰላማዊ ሰዎችን በየጎዳናው አይገድልም? ባለፉት አራት ወራት እና ከዚያም በፊት በየጎዳናው ለተገደሉት ንፁሃን ዜጎች ወላጆችና ቤተሰብ ካሳ ይሰጣል? ንፁሃን ዜጎችን የገደሉና ያስገደሉ ለፍርድ ይቀርባሉ? የታሰሩት በአስር ሺዎች የሚገመቱ የፖለቲካ እስረኞች ይፈታሉ? መሬታቸው ተነጥቆ ለተፈናቀሉ ገበሬዎች ተገቢው ካሳ ተከፍሎ እንዲቋቋሙ ይደረጋል?ይቅርታውን ተከትሎ ሊወሰድ ስለሚገባው እርምጃ አንዳችም ያሉት ነገር የለም። በደፈናው ሸውዶ ለማለፍ የተደረገ የለበጣ ይቅርታ ከሆነ ቅዳሴና ዳንኪራን እንደመደባለቅ ይቆጠራል።
ከአንድ ሰው ጋር ስለዚሁ ጉዳይ ስንወያይ፣ “ኃይለማርያም ይቅርታ ጠየቀ ለማለት አይቻልም። ይቅርታውን መልሶ አፍርሶታል። ” አለኝ። ሌላው ደግሞ፣ “ኃይለማርያም ከዚህ ቀደም ‘አስመራ ሄጄ ከኢሳይያስ ጋር ለመነጋገር ዝግጁ ነኝ’ ሲል እንደተናገረው፤ አሁንም የግሉን ይቅርታ ደባልቆ ይሆናል። ” አለ። ከዚህ በተጨማሪ “የይቅርታው ቃል በአሜሪካኖች አስገዳጅነት በህወሓት እውቅና የመጣ ነው። ” የሚል የውስጥ አዋቂ መረጃም ሰምቻለሁ። ከአስተያየቶች ሁሉ “ይቅርታ” የምትለው ቃል በአሜሪካኖች ተጽዕኖ የተነገረች ልትሆን መቻሏ ወደ እውነት የሚጠጋ ይመስለኛል። ሲፃፍ እንደሰነበተው ወያኔ ችግር ውስጥ መገኘቱ አከራካሪ አይደለም። አስረጅ ሊሆን ከሚችለው መካከል፣ “ከኦሮሞ ህዝብ አመጽ ጀርባ የኤርትራ እና የግብፅ ተላላኪዎች አሉ” የሚለውን ክስ ለመተው መገደዳቸው አንዱ ነው። የኦሮሞ ህዝብ አመጽ መነሻ የመልካም አስተዳደር እጦት መሆኑን ማመን እስከዛሬ ጌታቸው ረዳ ሲነግረን የነበረውን ይቃረናል።
ርግጥ ነው፤ ከኃይለማርያም ይቅርታ መጠየቅ ጋር በተያያዘ ከሚሰሙ ጭምጭምታዎች ዋናው የአሜሪካኖች ተጽዕኖ ሚዛን የሚደፋ መስሎ መታየቱ ነው። የፕሮፌሠር ኤፍሬም ይስኃቅ “ሰላም” የተባለው የማሸማገል ሂደትም የቀጠለ በመሆኑ ምን መልክ ይዞ ይፋ እንደሚሆን በቀጣዩ ጊዜያት የምንሰማው ይሆናል። በአንድ ወቅት CUD የተባለውን ቅንጅት ይመሩ የነበሩ ሰዎች በፕሮፌሠር ኤፍሬም አሸማጋይነት ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ የወያኔ ፍላጎት እንደምንም ተያይዘው ከሀገር እንዲወጡለት መንገድ መክፈት ነበር። በርግጥም አብዛኞቹ ባገኙት ዕድል ሁሉ ተጠቅመው የታገሉላትን ሀገር ትተው እንደማይመለሱ ሆነው ርቀው ሄደዋል። ይህ ለህወሓት አገዛዝ ጥሩ ዕድል ነበር። አብዛኞቹ የCUD ሰዎች ከኮበለሉ በኋላ ወያኔ እንደ ብርቱካን ሚደቅሳ ያሉትን ነጥሎ ለመምታት አልተቸገረም።
ህወሓት ቅንጅትን አዳክሞ ባጠፋው መንገድ የኦሮሞ አማጽያንን በዚያው ዘዴ ለማኮላሸት ማሰቡ ገና ያልተፈፀመ በሂደት ላይ ያለ ተግባር ነው። እንደሚሰማው የኢትዮጵያ መንግሥት ህዝቡን ይቅርታ ጠይቆ እስረኞችን ለመፍታት ለአሜሪካኖቹ ቃል ገብቶ ከሰነበተ እንግዲህ ይቅርታዋ እንደምንም ተነግራለች። እስረኞችን መፍታት ግን ገና አልተፈፀመም። እንደ ውስጥ አዋቂዎች ጥቆማ ከሆነ በእስር ቤት ካጎሯቸው በአስር ሺህዎች የሚገመቱ ኦሮሞ እስረኞች መካከል የአመጹ አስተባባሪ ሊሆኑ ይችላሉ ብለው የገመቷቸውን በመለየት ሥራ ተጠምደዋል። አመጹን ያስተባብራሉ ብለው የሚገምቷቸውን ለይተው ካበቁ በኋላ ወደ ስደት የሚሄዱበትን መንገድ ያመቻቻሉ ተብሎ ይታሰባል። ይህን ማድረግ የኦሮሞን ህዝብ ትግል ያዳክማል፤ ሥርዓቱ ትንፋሽ እንዲያገኝም ፋታ ይሰጠዋል ብለው ቢያስቡ ከልምዳቸው አንፃር ስህተት አይሆንም። የነቃው እና የተደራጀው ግለሰብ ከሜዳው ገለል ካለ አመጹ ጠቅልሎ ባይቆም እንኳ ፋታ ሊገኝ ይችላል። በርግጥ እንደ እስክንድር ነጋ፤ እንደ በቀለ ገርባ ለመኮብለል ፈቃደኛ የማይሆኑ ሲገጥሙ ቀመሩ ተገላቢጦሽ ይሆናል።
የኦሮሚያ ወጣቶች ሴራውን ባለመረዳት ለአዲስ ዙር ስደት ከተነሱ ‘በሀገሩ የሌለ - የትም የለም። ’ እንደሚባለው ለህወሓት ድል ይሆናል። ኮብላዮች ድጋፍ ሰጪ ከመሆን ያለፈ አቅም አይኖራቸውም። የኦሮሞ ህዝብ አሁን ከደረሰበት የተሰሚነት አቅም ላይ እንዲደርስ ያደረጉት በግንባር ቀደምትነት ተጋፍጠው መስዋዕትነት የከፈሉት ጥቂት ወጣቶች ናቸው። ድጋፍ ሰጪ ስደተኛ የማድረግ ችሎታው በጣም ውሱን ነው። ሃርቫርድ ከሚገኝ አንድ ተራ ፕሮፌሠር፤ ሐረማያ የሚገኝ አንድ ተራ የገበሬ ልጅ የተሻለ የማድረግ ችሎታ አለው። ህወሓት ከዳያስፖራ ይልቅ አጠገቡ ያሉትን ተራ ዜጎች ይሰጋል። ስለዚህ የማስቸገር ብቃት ያላቸው ይኮበልሉ ዘንድ ተግቶ ይሠራል። ማሰርና መግደል የህወሓት የመጀመሪያ ምርጫ ሆነው አያውቁም። የኮበለለ ሁሉ የወያኔን የመጀመሪያ ምርጫ እንደተቀበለና እንደተሸወደ ማወቅ አለበት።
ባለፈው ሣምንት “የቅዳሜ ማስታወሻ” ፕሮፌሠር ኤፍሬም ይስኃቅን በጨረፍታም ቢሆን ነካ አድርጌያቸው ነበር። በላኩልኝ ኢሜይል ስለርሳቸው ያለኝ ግንዛቤ ስህተት መሆኑን ጠቁመውኛል። እርሳቸው እንደገመቱት ሳይሆን ስለ ፕሮፌሠሩ ብዙም ባይሆን ጥቂት አውቃለሁ። የት ከማን እንደተወለዱ፣ የት ምን እንደተማሩ፣ የት ምን እንደሚያስተምሩ አውቃለሁ። ደረጀ ደሬሳ በአጤ ኃይለሥላሴ ዘመን በወቅቱ የ31 ዓመት ጎረምሳ ለነበሩት ለአቶ ኤፍሬም ይስኃቅ የፃፈውን መወድስም ኢትዮጵያ ሳለሁ አንብቤያለሁ። በተማሪዎች እንቅስቃሴ ዘመን ለሀገራቸው ብዙ ቁምነገር የሠሩ ሰው መሆናቸውን ቀደም ብዬም አውቅ ነበር። ሽማግሌው ፕሮፌሠር በጎልማሳነታቸው ዘመን ለደቡብ አፍሪቃ ጥቁሮች መብት መከበር መታገላቸውን በርግጥ አላውቅም ነበር። ዞረም ቀረ የተሠራው መልካም ነገር ሁሉ በቦታው አለ። ታሪክ አይረሳውም፤ ታሪክ ያመሰግናቸዋል። ፕሮፌሠሩ የአባት ሀገራቸው ታማኝ ልጅ ቢሆኑም፤ መወለድ ቋንቋ ነውና ልክ እንደኔው እሳቸውም የትውልድ ሀገራቸውን እንደሚወዱ እረዳለሁ።
ፕሮፌሠር ኤፍሬም በደርግ ውድቀት ማግስት የመሸጋገሪያው መንግሥት ምስረታ ላይ፣ ታምራት ላይኔን ለማሞገስ፣ “ተዓምራት ለዓይኔ፣ ተዓምር በዓይኔ አየሁ” ብለው ቅኔ ሲቀኙ በደማቁ ካጨበጨቡላቸው አንዱ እንደነበርኩ አልክድም። በወቅቱ ሁላችንም ተዓምራት በዓይናችን ያየን መስሎን ነበር። ታምራትና መለስ የተሸፈነ ጠባያቸው ሳይገለጥ ጥቂት ዓመታት እንኳ መጓዝ እንደማይችሉ አልገመትንም ነበር። ጃኬትና መኪና ወደ ማማረጥ ይገባሉ ብሎ የጠረጠረ አልነበረም። የሆነው ሆኖ የስካሩ አቧራ ገለል ሲል ፕሮፌሠር ኤፍሬም በዓይናቸው ተዓምራት ሳይሆን መቅሰፍት ነበር ያዩት። ያም ሆኖ ወዳጅነታቸውን ከወያኔ ጋር ቀጥለዋል። እዚህ ላይ እንግዲህ መነጽራችንን ዝቅ አድርገን፣ “ጤና ይስጥልኝ ፕሮፌሠር!” ለማለት እንገደዳለን።
ፕሮፌሠር ኤፍሬም ይስኃቅ የኦሮሞን ህዝብ ከገዢው ግንባር ጋር ለማስታረቅ በሚያደርጉት ሙከራ፣ “ሰላም” የሚለውን ቃል ሲጠቀሙ “የማን ሰላም?” የሚለውንም ጥያቄ ይመልሱት ዘንድ ይጠበቃል። ሰላምን ለማስገኘት ሽምግልና ከመጀመራቸው በፊት “ፀረ ሰላም ማነው? ለሰላም ጠንቅ የሆነው ማነው?” ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ይገባል። የቀድሞ በጎ ሥራ ለዛሬው ስህተት ላጲስ ሆኖ አያገለግልም። “ሰላም ወዳድ” የሚለው ማዕረግ “አሻጥረኛ” ወደሚል ከተለወጠ ለመመለስ ያስቸግራል። የኦሮሞ ህዝብ በሀገሩ ላይ የተረጋገጠ ሰላም ለማግኘት መስዋዕትነት መክፈል እንዳለበት የተረዳበት ጊዜ ላይ ነው። በርግጥም የአዲሱ ትውልድ መሪ መፈክር አንድ ብቻ ሆኖአል። ይህም፣ “ዛሬ አንድ ነገር ማድረግ አለብን። ወይም ደግሞ መሞት አለብን!” የሚል ነው። እና ማገዙ ካልተቻለ ቢያንስ “እንኳን ለዚህ አበቃችሁ!” ማለት ይገባል።
ርግጥ ነው፤ “የሰላም መጥፎ፣ የጦርነት ጥሩ የለውም” የሚለው ነባር አባባል በጥቅሉ ተቀባይነት አለው። ልጇ የሞተባት እናት፤ አባቱ የሞተበት ልጅ ኀዘን ላይ ናቸው። ኀዘናቸውን ለመረዳት እግራችንን እነርሱ ጫማ ውስጥ መጨመር ይገባል። ቢሆንም ግን ለሰላም ሲባል ሰላምን ለማደፍረስ፤ ጦርነትን ለማስወገድ ጦርነት መለኮስ ግዴታ ሆኖ ሊመጣ ይችላል። ሲደፈርስ በርግጥ ብዙ ሕይወት ይቀጠፋል። ባይሆን ጥሩ ነበር። ሕይወት ሳይከፈል የብዙኀን ሰላም የማይገኝ ከሆነ ግን መደፍረሱ ግድ ይሆናል። ሕይወት በሚቀጠፍበት መንገድ ብቻ ማለፍ ግድ መሆኑ ያሳዝናል። በጦርነት ድል ቢገኝም እንኳ ከድሉ ባሻገር አሸናፊውም ልክ እንደ ተሸናፊው እኩል ኪሳራ ይቀበላል።
ሰላም አንፃራዊ ነው። በሚዛናዊ መነጽር ስንመለከተው ዚምቧቡዌ ከቀድሞ ሰላሟ ይልቅ የአሁኑ መተራመሷ ይሻላት ይሆናል። በዚህ የዚምቧቤ መተራመስ ውስጥ 300 ሺህ የሀገሬው ሰዎች ከዘበኛነትና ከግርድና ሥራ ተላቀው ባለመሬት መሆናቸውን መዘንጋት አይገባም። የኦሮሞ ወጣቶች በዚህ ዘመን የተተወላቸው ሥራ በተነጠቀ መሬታቸው ላይ ዘበኝነት መቀጠር ሆኖአል። ከመሬታቸው የተፈናቀሉ የገበሬ ልጆች በዘበኛነት የሥራ ዘርፍ አዲሳባን እንደወረሩ፣ በበረንዳ አዳሪነት ከተማዋን እንዳጥለቀለቁ በቂ መረጃ አለ። እነዚህ ወጣቶች ከጥቂት ዓመታት በፊት ባለመሬት ነበሩ። ሃብታም መሬት ያርሱ ነበር። ሳሞራ ማሼል ሥልጣኑን በያዘባት ሌሊት ያንን ዝነኛ አዋጅ ያወጀው የነፃነትን የተሟላ ትርጉም ለወገኖቹ ለማቅመስ ነበር። ነፃነት ሲባል የከበርቴ ሰዎች ዘበኛ ሆነህ መለፍለፍ መቻል ማለት አይደለም። ነፃነት ከመሬት ባለቤትነት ይጀምራል። እና ሞዛምቢካውያን ከነሙሉ ችግራቸው ዛሬም ቢሆን ሳሞራን በበጎ ያስታውሱታል።
የኦሮሞ ህዝብ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሥርዓቱ የጫነበትን የሰቆቃ ሕይወት እየተቃወመ ረጅም ተጉዟል። ሸክሙ ሲበዛበት ግን ቀንበሩን ወረወረና አታላዩን ሰላምና ፀጥታ ክፉኛ አደፈረሰው። የህልውና ጉዳይ ሆነበት። ዓይኑ እያየ የማያውቃቸው ሰዎች መጥተው የአያቱን መሬት ሲሸጡ ሲመለከት የሰላም ትርጉሙ ጠፋበት። መሞትን መረጠ። እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰን ሰው “ለሰላም ሲባል”፤ “ለአንድነት ሲባል” ብለህ ልታግባባው አትችልም። አይሰማህም። በአንድ ወቅት የOPDO ምክትል ሊቀመንበር እንደነበረው እንደ ኢብራሂም መልካ ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “ለኦሮሞ ያልሆነች ኢትዮጵያ አስር ቦታ ትበጣጠስ!!” ሊልህ ይችላል። በመሆኑም ፕሮፌሠር ኤፍሬም ለማን ጥቅም እየሠሩ እንዳሉ ማወቅ አለባቸው። ለኢትዮጵያ አንድነት? ለተጨቆኑ ህዝቦች ሰላም? ወይስ ለአንድ ቡድን ሥልጣን? ምላሹ ለህሊናቸው ይሁን።
የጃዋር መሐመድን መረጃ ከያዝን ሌላው ይቆይልንና ባለፉት አራት ወራት በኦሮሚያ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ወደ 500 አሻቅቦአል። ይህ ብቻውን እንኳ ለወያኔ ትልቅ ዕዳ ነው። ክፍያው ሊቸግር ይችላል። የሕይወት ዕዳ ወለዱ ውድ ነው። ኃይለማርያም በቅርቡ ሴት ልጃቸውን በሞቀ ሠርግ ድረዋል። ሟቾቹ ወጣቶች በተመሳሳይ ለወግ ለማዕረግ እንዲበቁ ወላጆቻቸው ይመኙ ነበር። ልጆቻቸውን ያጡ፣ አባታቸውን የተነጠቁ ወገኖች ኀዘኑን አይችሉትም። ኃይለማርያም ይቅርታ የጠየቁት በራሳቸው ተነሳሽነት ከሆነ፤ ከዚያም በላይ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ርግጥ ነው፤ “የኦሮሚያ አመጽ” የሚለው የጨዋታ ካርድ ላለፉት አራት ወራት ከፖለቲካ ሜዳው ላይ ሊወርድ አልቻለም። ከቀዳሚ ዜናነቱ ሊገፈተር አልቻለም። ሰበር ዜና ከመሆን ሊታቀብ አልቻለም። ኃይለማርያም የበታች አለቆቻቸውን ሥነልቦና መረዳት ይጠበቅባቸዋል። አባይ ፀሐዬ እና ስብሃት ነጋ “ጥቂት ታገስ! ከዚያም ጊዜ ጠብቀህ የጨዋታውን ካርድ ቀይረው” የሚለውን የሰርቫንቴስ አባባል ደጋግመውም ይጠቀሙበታል። የ“ይቅርታ” እና የ“ሰላም” ወጎች የትዕግስት ምዕራፍ ሲሆኑ፤ ከረምረም ብለው የጨዋታውን ካርድ ለመቀየር መሸጋገሪያ ይሆናሉ። ያን ጊዜ ጊሎቲን አንገት ቆረጣውን እንዳዲስ ይጀምራል።
በመጨረሻ አንድ ነጥብ ላይ ላስምር። የኦሮሞ ህዝብ እየከፈለ ያለው የሕይወት መስዋዕትነት ኪሳራ አይደለም። ግብና ዓላማ አለው። ለመጪው ትውልድ እየተከፈለ ያለ የክብር ዋጋ ነው። እና የኦሮሞ ህዝብ ጨክኖ እንደጀመረ ከመግፋት በቀር አማራጭ የለውም። ወደኋላ ማየት እንደገና መቶ ዓመታት ሊያስተኛ ይችላል። መስዋዕትነቱን አያስቀረውም። ከመሬት መፈናቀሉን፣ ስደቱን አያስቀረውም። የኦሮሞ ህዝብ ትልቅ ህዝብ እንደመሆኑ ሌሎችንም ኢትዮጵያውያን አስተባብሮ፣ አቅፎ ወደ ተሻለው ዘመን የመጓዝ ብቃቱና ችሎታው አለው። ያለ ኦሮሞ ህዝብ ኢትዮጵያ ምትባል ሀገር የለችም። እና የኦሮሞ ህዝብ ራሱን ነፃ ከማውጣት ባሻገር ከባድ ኃላፊነት አለበት። የተረጋገጠውን ሰላም ለማግኘትና በረጅሙ ለማረፍ ጨለማውን ጫካ በድፍረት ማለፍ ይገባዋል። ይቻለዋልም። አሳምሮ ይቻለዋል። ታግለው ነፃ የወጡ የዓለም ህዝቦች ታሪክ የሚነግረን ይህንኑ ነው።