20210302 adwa

ግርማ ካሳ

በወልቃይት ጠገዴና ቃብቲያ ሁመራ ህዝብ ላይ የታቀደው ድቡቁ የህወሓት ሴራ ሲጋለጥ | ምስጢራዊ መረጃ

በቅርቡ አንድ በትግሪኛ የተዘጋጀ ሚስጥራዊ ሰነድ በአማርኛ ተተርጉሞ ዘሃበሻ ላይ አነበብኩ። ህወሓት በወልቃይት ዙሪያ ያጋጠመውን ፈተና ለመመከት እንዲያስችለው ያዘጋጀው ሰነድ እንደሆነ ነው የተገለጸው።

በወልቃይት ጠገዴ ዙሪያ የተፈጠረውን ቀውስ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ እና ፍትሃዊና በሆነ መንገድ መፍታት፣ ሁሉም አሸናፊ የሆኑበትን መፍትሄ መፈለግ ሲገባው፣ በአቶ አባይ ወልዱ የሚመራው የህወሓት የመቀሌ አስተዳደር ግን ብስለት የጎደለው ተግባራት እየፈጸመ ነው።

ኢሕአዴግ ሥልጣን ከመጨበጡ በፊት, ወልቃይት ጠገዴ ሁመራ ጠለምት በአጠቃላይ የተከዜ በስተምእራብ ያለው አሁን የምእራብ ትግራይ ዞን የሚባለው ግዛት፣ በበጌምድር(ጎንደር) ክፍለ ሃገር በወገራ አወራጃ ውስጥ ሲተዳደር የነበረ ነው። ይሄንን ደግሞ የቀድሞ የህወሓት መስራች ዶር አረጋዊ በርሄ፣ ልኡል ራስ መንገሻ ስዩም የመሳሰሉ የትግራይ ታዋቂ ግለሰቦች በአደባባይ የመሰከሩት ነው።

ወልቃት ጠገዴ “አማራ” ነን የሚሉ ፣ ትግሬ ነን የሚሉ ለዘመናት በሰላም የኖሩበት ነው። ትግሬ አማራ የሚል ድሮ አልነበረም። ወልቃይቶች ሲፈለጉ ጎንደር ሲፈልጉ ሽሬ ሄደው ይነግዳሉ። የሽሬው ሰው ሲፈልግ መቀሌ፣ ሲፈልግ ጎንደር ይመጣል። ሰው እርስ በርስ ተዛምዷል። በወልቃይት ጠገዴ የሚኖሩ “አማራ” ነን የሚሉ ትግሪኛ ይናገራሉ። በዚያ ያለው ህዝብ ከትግሬዎች ጋር ከትግሪኛ ጋር ችግር ኖሮት አያውቅም። ወልቃይቶችን ህወሃቶች አይደለም ትግሪኛ ያስተማሯቸው። ህዝቡ ትግሪኛ የለመደው ከትግራይ ወንድሞቹ ጋር ትስስር ስላለው ነው። ቋንቋ የዘር መገለጫ ሳይሆን መግባቢያ ስለሆነ ነው።

ሲጀመር ህወሓት የጨዋታውን ሕግ የዘር ጨዋታ እንዳደረገው መዘንጋት የለብንም። የወልይቃት ጠገዴ ህዝብ ሲፈልግ አማርኛ፣ ሲፈለግ ትግሪኛ ሲፈለግ አረብኛ ይናገራል። ህወሓት የ”ትግሪኛ ብቻ” ፖሊሲን በህዝቡ ላይ ጫነ። በልማት ስም ህዝቡን ከመሬቱ ማፈናቀል ጀመሩ። ብዙ ወልቃይቶች ተሰደዱ፣ ተገደሉ፣ ታሰሩ። ህዝቡን በታሪኩ አስቦት የማያውቀውን ነገር እንዲያስብ ገፋፉት። በግድ ትግሬ ናችሁ ሲባሉ እነርሱም የዘር ካርድ ጨዋታን ጀምረው “አማራ ነን“ ማለት ጀመሩ። ትግሬ አማራ መባባሉ ጦዘ።

ምን ችግር ነበረው ትግሬ፣ አማራ ሳይባባሉ፣ ትግሪኛንም፣ አማርኛም እየተናገሩ፣ ሽሬም፣ ጎንደረም እየሄዱ እየነገዱ እንደ ድሯቸው በሰላም ቢኖሩ? ያ ሊሆን አልቻለም። ህወሓት ለዘመናት በዚያ አካባቢ በፍቅር በሰላም እየተዋለዱ በጋራ የአገራቸውን ዳር ድንበር እየጠበቁ የኖሩ ወንድማማቾችን በዘር ለያይቶ ወደ ጠብ እየወሰዳቸው ነው። ህዝቡን አማረሩት።

“እኛ ጎንደሬ ነን፤ ወደ ጎንደር መቀላቀል አለብን” በሚል የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ኮሚቴ አቋቋመ። ወደ አምሳ ሺህ ፊርማ ተሰብስቦ ጉዳዩ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ተወሰደ። ሕገ መንግሥቱና ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት እንቅሳሴዎች ተደረጉ። ሆኖም የህወሓት ባለሥልጣናት ገመዱን የበለጠ ማክረር ጀመሩ። በህዝቡ ላይ ዛቻ ይናገሩ ጀመር። ሰነድ አዘጋጅተው እነርሱ “ትግሬነት” የሚሉትን በኋይል ለመጫን ከላይ እንደጠቀስኩት ሚስጥራዊና በጣም ዘረኛ የሆነ ሰነድ አዘጋጁ።

በወልቃይት ያለውን ለመቀልበስ መደረግ አለበት ተብለው ከተቀመጡት ነጥቦች መካከል የሚከተለው ይገኝበታል።

“የትግራይ ኪነ-ጥበብ በተለይ የትግርኛ ዘፈኖች ብናያቸው በሁሉም ዘፈኖቹ ሲጠሩ የምንሰማቸው የአካባቢ ስሞች ትግራይ ማለት ከሽሬ የሚመለስ እንደሆነ የሚሰብኩ ናቸው። ይህን ችግር ከመሰረቱ በማረም ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ሁመራ ያካተተ እንዲሆን የትግራይ ጥበበኞች እንዲያስቡበት ማድረግ፤ ምክንያቱም በአማርኛ ቋንቋ የሚዘፈኑ የጎንደር አካባቢ ስም የሚያነሱ ዘፈኖች ሁሉ ብንመለከት አሁንም ያልተዋቸው በሽታ የእነዚህ አካባቢ (ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ሰሜን፣አርማጭሆ፣ጠለምትና ሁመራ) ስም ሳይጠሩ አያልፉም። ስለሆነም የጥበብ ድርሻ በሰው ልጅ ስነ-ልቦና ከፍተኛ ተፅእኖ ስላለው የትግራይ ጥበበኞች ልንሰራበት ይገባል። የቆላው የትግራይ ተወላጅ (ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ሁመራ፣ ቃብቲያና ጠለምት) ከጎንደር ታሪክ በላይ በአክሱምና ይኼ ታሪክ ኩራት እንዲሰማውና የእኔነት ስሜት እንዲያድርበት ማድረግ የግድ ያስፈልጋል። ከአጤ ቴዎድሮስ ታሪክ በላይ የኢትዮጵያን ዳርድንበርን ለማስከበር ላይ እና ታች እያለ ሳለ የሞተውን የአጤ ዮሃንስ አራተኛ ጀግንነት አውቆ እንዲኮራበትና እንዲመካበት ቢደረግ የትምክህተኞቹ የአማራዎቹ ተግባር ማለትም ከድሮ ጀምሮ በተዋረድ የመጣውን ክፋታቸውና ውሸታቸው እንዲሁም የትግራዋይን ስም የማጥፋትና በወሬ በማስተጋባት ብልግና እንደሰሩ በማስተማር በተቃራኒው ደግሞ የትግራይና ትግራዎትን የበላይነትንና ብሔርተኝነትን ከፍ በማድረግ በውስጣዊ ስብከት እንዲያስተጋባ በማድረግ ጫና መፍጠር”

እንግዲህ አስቡት ምን ያህል መቀሌ ያሉ የህወሓት ባለሥልጣናት ጠባብ መሆናቸውን? አጼ ዮሐንስ፣ አጼ ቴዎድሮስ፣ ጎንደር ፣ አክሱም እያሉ መርዝ ከሚረጩ፣ አክሱም የትግሬዎች ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊያን፣ ጎንደር የጎንደሬዎች ብቻ ሳትሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ቅርሶች መሆናቸውን ለምን መረዳት አቃታቸው?

የትግራይ ህዝብ በአጼ ዮሐንስ እንደሚኮራው በአጼ ቴዎድሮስም ይኮራል። ለዚህም ነው ትግራይ ብትሄዱ እጅግ በጣም ብዙ የትግራይ ልጆች ቴዎድሮስ የሚል ስም ያላቸው። ዶር ቴዎድሮስ አዳኖም፣ አቶ ቴዎድሮስ ሃጎስ ያሉ ከፍተኛ የህወሓት ባለሥልጣናትን መጥቀሱ ይበቃል። ታዲያ ከአሁን ለአሁን የወልቃይት ህዝብ ጎንደሬዎች ነን አለና ቴዎድሮስን ጥሉ ዮሐንስን ውደዱ አይነት ዘመቻ በህወሓት መደረጉ ምን ይባላል?

በወልቃይት ጠገዴ እርግጥ ነው ድሮም ሲኖሩ የነበሩ፣ በቅርቡም የሰፈሩ ብዙ ትግሬ ነን ባዮች አሉ። ወልቃይት ጠገዴ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ክልሎችም ብዙ ትግሬዎች አሉ። ለትግሬዎች ወልቃይት ጠገዴ ብቻ ሳይሆን ሁሉም የኢትዮጵያ ግዛት መሬታቸው ነው። የኢትዮጵያ የሁሉም ግዛት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ነውና።

ነገር ግን ለጊዜው ጡንቻ ያላቸው ህወሓቶች ስለሆኑ ህዝቡን በግድ “ትግሬ ነህ” ብለው ሊያስገድዱት መሞከራቸው ግን አያዛልቃቸውም። ይህ አይነቱ የኃይል እርምጃ ዘላቂ መፍትሄ አያመጣም። እንደው የዘር መካረሩን በጣም ያባብሰዋል። የዘር ነገር ደግሞ እንደሚታወቀው ሰውን በስሜት እላይ የማድረስ አቅም አለው። የዘር ክርክር፣ የዘር ፉክክር፣ በዘር ሂሳቦችን ማወራረድ እጅግ በጣም አደገኛ ነው። መሪዎች ጠባብ ከሆኑ በቀላሉ ብዙዎችን በጠባብነት መበከል ይችላሉ። በአጭሩ ከወዲሁ በብስለትና በጥንካሬ የጠባብ መሪዎች ፖለቲካ ካልተመከተና ካልተሸንፈ፣ ብዙዎችን በክሎ፣ ህዝብን እና አገርን ገደል ውስጥ ሊከት ይችላል።

ነገሮች ረገብ ይበሉ ባይ ነኝ። ህወሓት ሁሉም አሸናፊ የሆኑበት መፍትሄ ይፈለግ ባይ ነኝ። ቢቻል እንደውም እንደ ሩዋንዳና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች የዘውግ/የዘር ነገርን ከፖለቲካው ሙሉ ለሙሉ ማውጣት ቢቻል ጥሩ ነው። አጼ ቴዎድሮስ አገር የጋራ ኃይማኖት የግድ እንዳሉት፣ አገር የጋራ ዘውግ/ዘር የግል ነው ይባል። ትግሬ ነኝ፣ ኦሮሞ ነኝ፣ ጉራጌ ነኝ የምንል፣ ከፈለገን በግል ከፈለግን በቡድን ትግረነታችንን፣ ኦሮሞነታችንን እንዘርክ። የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት ግን፣ ከኃይማኖትና ከዘውግ/ዘር የጸዱ ይሁኑ። ሰው በሕግ ፊትም ሆነ በማንኛውም የመንግሥት አገልግሎት ዘርፍ በዘሩ ሳይሆን በስብዕናው ይታይ። በዘሩና በሚናገረው ቋንቋ ሳይሆን በሥራው ይመዘን።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!