Prof. Messay Kebede. ፕ/ር መሳይ ከበደግርማ ካሳ

ማርች 26 እና ማርች 27 ቀን 2016፣ በቪዥን ኢትዮጵያ አማካኝነት አንድ ኮንፍራንስ ተካሄዶ ነበር። በዚህ ኮንፍራንስ ላይ ብዙ ምሁራን ጥናታዊ ጽሁፎች አቅርበዋል (“የኢትዮጵያ ዘውጋዊ ክፍፍሎችና የመፍትሔ ሃሳብ”)። ከነዚህ መካከል ፕ/ር መሳይ ከበደ አንዱ ነበሩ። ንግግራቸውን በሦስት ነበር የከፈሉት። የመጀመሪያው ክፍል ስለዘውግ (ethnicity) አንዳንድ ጽንሰ ሃሳቦች ለማሳየት የሞከሩበት ነው። ብዙም የማያከራክር ለጠቅላላ እውቀት የሚሆን ፍልስፍናዊና ቴዎረቲካል ትንተና በመሆኑ እዚያ ላይ ብዙ ጊዜ አላጠፋም።

ሁለተኛው ክፍል፤ በሀገራችን ስላለው የዘውግ ሥርዓት አመጣጥ በስፋት ገለጻ ያደረጉበት ነው። የፌዴራል አወቃቀሩ ገና ከጅምሩ ሲዘረጋ ያለውን ችግር አሳይተዋል። “ሥርዓቱ (ፌዴራል) የተነደፈው ሰፊ ነጻ ውይይት ተደርጎ በህዝብ ነጻ ምርጫ የጸደቀ ሳይሆን፤ በጥቂት አሸናፊ ነን በሚሉ (ህወሓት እና ኦነግ) የፖለቲካ ቡድኖች ተወጥኖ በግድ ህዝብ እንዲቀበለው የተደረገ ነው” ይላሉ። ያ ብቻ አይደለም “ፌዴራል አወቃቀር ሥርዓቱ በግድ ህዝብ እንዲቀበለው ከመደረጉም በላይ፤ የተቀረጸው ፌደራሊዝም ዘውጋዊ ማንነትን የሚያጠናክርና የህዝብን አንድነት የሚያፋልስ ነው” ሲሉም የአወቃቀሩን ፀረ-ሀገር እና ፀረ-ኢትዮጵያዊነት ይዘት አብራርተዋል።

በሦስተኛ ክፍል፤ ፕ/ር መሳይ በሀገራችን ያለውን የዘውግ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ሊፈጥር የሚችለውን አደጋ አሳይተው፣ የዘውግ ጥያቄን ወደ ጎን ከማድረግ፤ የዘውግ ጥያቄን በመለሰ መልኩ፣ ብሔራዊ አንድነት መገንባት እንደሚበጅ ይከራከራሉ። በዚህ ሃሳብ በመርኅ ደረጃ እስማማለሁ። ሆኖም “በራስ ቋንቋ መናገር፤ በራስ ባህል ተክብሮ መኖር ወዘተ ላይ ብቻ ዘውጋዊ ፖለቲካ አይወሰንም … የግለሰብ መብቶች መከበር ብቻ የዘውግን ጥያቄን አይመለስም” የሚሉት ፕ/ር መሳይ፤ የዘውግ የራስ ገዝ መኖር እንዳለበት ይገልጻሉ። “የዘውግ ፖለቲካ መኖር የለበትም” የሚለውን አስተያየት ፕ/ር መሳይ “ከንቱ” እና “ለሀገር አደገኛ” ሲሉም ይፈርጁታል። እዚህ ላይ ፕ/ሩ ትንሽ የተሻለ ቃለ ቢመርጡ ጥሩ ይሆን ነበር። ዜጎች በተለያዩ ምክንያቶች የተለያዩ አስተያየቶች ሊኖራቸው ይችላል። የሌሎችን አስተያየቶች በአክብሮት መንቀፍና መሟጋት አንድ ነገር ነው። “ከንቱ” ብሎ መፈረጅ ግን ከአንድ ምሁር ብዙ የሚጠበቅ አይመስለኝም።

ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ አይነት ማኅበረሰብ አይደለም ያለው። በመሆኑም የሁሉንም አመለካከቶች ለማቀራረብ መሞከር፤ ፕ/ር መሳይ እንዳሉት ሞደሬት መሆን ተገቢ ነው። በተለያም ያለፈውን 25 ዓመት ከመጠን ባለፈ የተራገበው የጎሣ/ዘውግ ፖለቲካ፣ በብሔራዊ አንድነት እና በኢትዮጵያዊነት ትልቅ አደጋ እንደፈጠረ ይታወቃል። የዘውግ ጥያቄ ከጥያቄዎች ሁሉ በላይ የሆነባቸው የሀገራችን ዜጎች እጅግ በጣም ብዙ ናቸው። በነዚህ ዜጎቸና በሌሎች አብሮነትን እና ኢትዮጵያዊነትን በሚያቀነቅኑ ወገኖች መካከል የሰፋ ልዩነትና ክፍተት አለ። ያንን ልዩነት ማጥበብ ጊዜው የሚጠይቀው ቁልፍ ጉዳይ ነው። ለዚህም ነው ፕ/ር መሳይ “የሀገሪቱን አንድነትና ዘውጋዊ ፖለቲካ እንዲተባበሩ ማድረግ ነው” ሲሉ የሰጡትን በመርኅ ደረጃ የምጋራው።

ሆኖም ግን እነዚህ ሁለት አመለካከቶችን ለማስተባበር ዘውጋዊ አከላለልንም መቀበል ያስፈለጋል ያሉትን ግን ከትልቅ አክብሮት ጋር አልቀበልም። አብዛኛው ህዝብም ይቀበላል ብዬ አላምንም።

በአንደኛ ደረጃ እርሳቸው ራሳቸው፣ አሁን ያለውን አከላለል፣ ህዝቡ ሳይመክርበት፣ በህዝቡ ላዩ በግድ የተጫነ እንደሆነ ገልጸው፤ መልሰው ደግሞ፣ ይሄንን አከላለን ተቀበሉ ማለታቸው ግራ የሚያጋባ ነው። “የ(ፌዴራል) ሥርዓቱ ኢዴሞክራሲያዊ ብቻ ሳይሆን፤ የውሸት ፌደራሊዝም ነው” ያሉትን ለምንድን ነው የምንቀበለው? ውሸትን ለምን እንቀበላለን? በሕግ አንጻር፣ በሎጂክ አንጻር፣ በዴሞክራሲ አንጻር ይሄ አባባላቸው ሚዛን ሊደፋልኝ አልቻለም።

ሌላው አሁን ያለውን ክልል መቀበል አለብን ሲሉ፤ ይህ አሁን ያለው አከላለል፣ በኔ ግምት ከሶማሌ እና አፋር ክልል በስተቀር ዘውጋዊ እንዳልሆነ የተረዱት አልመሰለኝም። በኢትዮጵያ ዘጠኝ ክልሎች አሉ። ከነዚህ ውስጥ የአማራው፣ የደቡብ፣ የቤኔሻንጉል፣ የሐረሪ እና የጋምቤላ ክልሎች መድበለ ዘውግ (multi-ethnic) ናቸው። የትግራይ እና የኦሮሚያ ክልሎችም የዘውግ ክልሎች ተደርገው ቢወሰዱም፣ በተግባር ግን እነዚህ ክልሎችም ብዙ ብሔረሰቦች የሚኖሩባቸው ክልሎች ናቸው። በኦሮሚያ ትላልቅ ከተሞች የሚኖረው ህዝብ multi-ethnic ህዝብ ነው። አቶ ሌንጮ ባቲ እንዳሉት ወደ 11 ሚሊዮን ኦሮሞ ያልሆነ ህዝብ በኦሮሚያ ውስጥ ይኖራል። ኦሮሞዎች በተለይም አማራ ከሚባለው ማኅበረሰብ ጋር የተዛመዱና የተዋለዱ ናቸው። ወደ ትግራይ ከሄድን ደግሞ በምዕራብ ትግራይ ዞን፣ በወልቃይት ጠገዴ ህዝቡ “ትግሬ” አይደለንም እያለ ነው። ያ ደግሞ የሚያሳየው የትግራይ ክልል ዘውጋዊ፣ የአንድ ብሔረሰብ ክልል እንዳልሆነ ነው። ፕሮፌሠሩ ትንሽ በዚህ ረገድ ሰፋ ያለ ጥናት ቢያደርጉ ጥሩ ይሆን ነበር።

አንድ ዘውግ በአንድ አካባቢ contiguous በሆነ መልኩ የሚገኝ ከሆነ ዘውጋዊ ራስ ገዝ መመስረቱ ችግር ይኖረዋል ብዬ አላስብም። ሆኖም ኢትዮጵያ ውስጥ ከሰማኒያ በላይ ዘውግ (ብሔረሰብ) እንደመኖሩ፣ ብሔረሰቦችም በተበታተነ ቦታ ያሉ፣ የተዋለዱና የተደባለቁ እንደመሆናቸው፣ በሁሉም አካባቢዎች የአንድን ዘውግ ክልል ወይም ራስ ገዝ ማበጀት እጅግ በጣም ትልቅ ራስ ምታት ነው የሚሆነው። እነ አቶ መለስ ዜናዊም ስለከበዳቸው ነው ከአምሳ በላይ የሚሆኑ ብሔረሰቦችን አንድ ላይ ጨፍልቀው ደቡብ ያሏቸው። አዲስ አበባ ራሷን እንድትችል፣ ድሬዳዋ ቻርተር ከተማ እንድትሆን የተደረገውም የዘውግ አከላለል በነዚህ ከተሞች ያሉ ነዋሪዎችን መወከል ስላልቻለ ነው። ጂማና አዋሳም ተመሳሳይ ነገር በመኖሩ እነርሱንም ቻርተር ከተማ ለማድረግ ታስቦም ነበር።

ፕ/ር መሳይ እንዳሉት የዘውግ ክልሎችን ወደ ማጠናከሩ ከሄድን፣ በዩጎዝላቪያ እንዳየነው የአንድ ዘውግ አባላት በአንድ አካባቢ እንዲኖሩ ለማድረግ ሲባል፤ ህዝብ ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ በገፍ መፈናቀል ይኖርበታል። የዘውግ አከላለል በባህሪው አግላይና ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ነው። ክራዪና ከምትባለው የክሮዬሺያ ግዛት፣ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰርቦች ተባረዋል። በቦስኒያ ሄርዞጎቪና ሰርቦች ከሚቆጣሩበት እንደ ሰብረኒቻ ባሉ ቦታዎች፣ ብዙ ቦስኒያዎችና ክሮዬሺያዎች ተባረዋል። በኮሶቮ ሰርቦችን እና አልቤኒያኖችን እንዳይቀላለቁ የተባበሩት መንግሥት ሠራተኞች በመካከል አሉ። በአርመኒያና በአዘርባጃን መካክል ያለው ጦርነት ዘውግ ወለድ ጦርነት ነው። ይሄ ሁሉ ለምን? ቢባል፤ አንድ አይነት የሆነ ከአንድ ዘውግ የተወጣጣ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ነው የሚል መልስ ነው የሚሰጠው። በሀገራችንም የዚህ ብሔረሰብ መሬት ነው በሚል የዘር ማጽዳት በብዙ ቦታዎች እንደተፈጸመ ፕ/ር መሳይ የሚያወቁት ይመስለኛል።

የበለጠ ይሄንን ሃሳብ ለማስፋት አንድ ምሳሌ ላቅርብ። አዲስ አበባን ጨምሮ በአራቱ የኦሮሚያ የሸዋ ዞኖች 55% የሚሆነው ነዋሪ ነው አፋን ኦሮሞ የሚናገረው። (በኦሮሚያ ዋና ከተማ አዳማ 15% ብቻ የሚሆነው)። ሆኖም የዘውግ አከላለል፣ የአንድን ዘውግ ክብር ለማስመለስ፣ ዘውጉ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር እና ባህሉን በበላይነት ለማስፈን እንዲችል የሚዘረጋ በመሆኑ፣ በኦሮሚያ አፋን ኦሮሞ ብቻ ነው የሥራ ቋንቋ የተደረገው። አማርኛ ተናጋሪዎች ማጆሪቲ (አብዝኀው) በሆኑበትም ቦታ፣ የከተሞች ጽ/ቤቶች ሠራተኞች አማርኛ ተናጋሪ ሆነውም፣ አገልግሎት ለማግኘት ግን የግድ ሁሉም ነገር በአፋን ኦሮሞ ተደርጓል። እንደ ቀለም ወለጋ ዞን ባሉ፣ 97% ነዋሪዎች አፋን ኦሮሞ በሚናገሩበትና የኦሮሞዎች አሰፋፈር contiguous በሆኑባቸው ቦታዎች፣ ሁሉም ነገር በአፋን ኦሮሞ ቢሆን ችግር አይኖርም። ግን ሌሎች ማኅበረሰቦች በስፋት ባሉበት ዘውጋዊ አከላለልን መዘርጋት፣ የሌላውን ማኅበረሰብ መብት ከግምት አለማስገባት ነው። ሌላው ማኅበረሰብ ተፈናቅሎ ይወክለኛል ወደሚለው ሌላ የዘውግ ክልል መሄድ ይኖርበታል፤ ወይንም ደግሞ በዘውጉ አባላት በጎ ፍቃድ የሚኖር “እንግዳ” (በኬንያ እንደሚኖሩ ኢትዮጵያውያን) ወይንም ሁለተኛ ዜጋ ሆኖ መኖርን መቀበል አለበት።

ለዚህ ነው የዘውግ አከላለል ለሀገራችን በጣም አደገኛ ነው የሚል መከራከሪያ የማቀርበው። ምናልባት የዘውግ እንቅስቃሴ አንቀንቃኞች በስፋት ድምጻቸው እየተሰማ ስለሆነ ይሆናል ፕ/ር መሳይ ከወቅቱ ንፋስ ጋር አብሮ ለመሄድ በሚል የዘውግ አከላለልን መቀበል አለብን ወደሚል አስተሳሰብ የመጡት። ሆኖም ድምጹን ያላሰማ የዘውግ አከላለል ሰለባ የሆነ፣ የዘውግ አከላለልን ፕራክቲካል በሆኑ ምክንያቶች የማይቀበል ትልቅ ማኅበረሰብ እንዳለ መርሳት ያለባቸው አይመስለኝም። (በምርጫ ዘጠና ሰባት በሀገሪቷ፣ በአሰላ፣ በጂማ፣ በመቱ፣ በብዙ የሸዋ አካባቢዎች ሳይቀር ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ ያገኘው፣ አሁን ያለውን ፌዴራላዊ አወቃቀር መቀየር አለበት ብሎ ያምን የነበረው፣ ቅንጅት እንደነበረ ላስታውሳቸው እወዳለሁ)

የዘውግ አከላለል ላይ ተቃውሞ ሳነሳ የዘውግ ጥያቄዎችን ማናናቅ ተደረጎ እንደማይወሰድብኝ መቼም ተስፋ አደርጋለሁ። ፕ/ር መሳይ እንዳሉት፣ በመርኅ ደረጃ በዘውግ ፖለቲካ አንቀንቃኞች እና በብሔራዊ አንድነት አቀንቃኞች መካከል መቀራረብ እንዳለበትና ሁሉም አሸናፊ የሆኑበት መፍትሔ ማምጣት መቻል አስፈላጊ እንደሆነ አምናለሁ። ከፕ/ር መሳይ በተለየ ግን፣ ይሄን መቀራረብ ሊያመጣ የሚችለው፣ የዘውግ አከላለል ሳይሆን፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው ባይ ነኝ።

ዴሞክራሲያዊ ስላልሆነ በሂደት አሁን ያለው ፌዴራል አወቅቀር መቀየር አለበት የሚል በጣም ጠንካራ አቋም አለኝ። አዲስ አበባን ጨምሮ ምስራቅ፣ ሰሜን ሸዋ ዞን የመሳሰሉት በአንድ ላይ ሆነው የራሳቸው አንድ ክልል መሆን አለባቸው ባይ ነኝ። ይሄንን አቋም ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ፣ ህዝብን በማስተማር የህዝብን ድጋፍ ማግኝት ይቻላል የሚል እምነት አለኝ። ሆኖም ያንን ለማድረግ መጀመሪያ የዴሞክራሲ ሥርዓት መፈጠር አለበት። የፌዴራል አወቃቀር በአንድ ጊዜ ሊለወጥ አይችልም።

በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲመሰረትና፣ ህዝብ የፈለገውን መምረጥና መሻር እንዲችል፣ ሁሉንም ሊያሰባስብና በጋራ ሊያታግል የሚችል ስምምነት መደረግ አለበት።

በዚህ ረገድ አሁን ያለው አወቃቀር በጊዜያዊነት ከማስቀጠል ውጭ የተሻለ አማራጭ ላይኖር ይችላል የሚል ሃሳብ አለኝ። ይህ አማራጭ በጊዜያዊነትም ቢሆን፤ ተቀባይነት እንዲኖር መጠነኛ ማሻሻሎች መደረግ ግን ይኖርበታል። ይሄንንም እንዲረዳ ባለ ሰባት ነጥብ ሃሳቦችን እንደሚከተለው አቅርቢያለሁ። በ“ጊዜያዊነት” የሚለውን ቃል እንደገና በትልቁ ላሰምርበት እወዳለሁ።

1. በፌዴራል አወቃቀር ዙሪያ የተለያዩ ልዩነቶችና አለመስማማቶች አሉ። ሆኖም ወደፊት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተገንብቶ፤ ፓርቲዎች ያሏቸውን አቋም በግልጽና ያለፍርሃት ለህዝብ አስተዋውቀው፤ ህዝብ ከፈለገ የአስተዳደር መዋቅሩ እንዲቀጥል ማድረግም ሆነ መቀየር መብቱ እንደሆነ በማረጋገጥ በጊዜያዊነት ግን አሁን ያላቸው አወቃቀር መጠነኛ ማሻሻያዎች ተደርገውበት ይቀጥላል። በኦሮሚያ፣ በአማራው እና በደቡብ ክልሎች ለአስተዳደር አመችነት እንዲኖር ለዞኖች የበለጠ ሥልጣን ይሰጣል።

2. አዲስ አበባ ለብቻዋ የፌዴራል ክልል መሆኗ ቀርቶ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉትን አካባቢዎች በማካተት ወይንም ከምስራቅ ሸዋ ወይንም ሰሜን ሸዋ ዞን ጋር በመቀላቀል የራሷ ዞን ሆና፣ ሙሉ በሙሉ በኦሮሚያ ክልል ስር ትሆናለች። አዲስ አበባን ያካተተው ዞን የፊንፊኔ ዞን ተብሎ ሊጠራ ይችላል።

3. የሐረሪ ክልል ከኦሮሚያ ክልል ጋር ይዋሃዳል። ድሬዳዋ ከተማ ከሶማሌ ክልል ጋር ትዋሃዳለች። አማርኛ የሶማሌ ክልል የሥራ ቋንቋ ይሆናል።

4. የምዕራብ ትግራይ ዞን (ወልቃይት ጠገዴ) ትልቅ ሥልጣን ያለው ልዩ ዞን ሆኖ በትግራይ ውስጥ በጊዜያዊነት እንዲቀጥል ይደረጋል። አማርኛ በትግራይ ከትግሪኛ ጋር የሥራ ቋንቋ ይሆናል።

5. ማንም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የሀገሪቷ ክፍል የመኖር፣ የመነገድ፣ ኢንቨስት የማድረግ፣ የመምረጥ፣ የመመረጥ ሙሉ መብት አለው። ማንም ኢትዮጵያዊ በኃይማኖቱ፣ በጾታው፣ በብሔር ብሔረሰብ ማንነቱ አድሎና ልዩነት አይደረግበትም። ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች ሳይሆን የዜጓቿ ናት።

6. የኢትዮጵያ ህዝብ ወይንም የክልሎ ህዝቦች አሥር በመቶ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን እንደ አንደኛ ቋንቋ የሚናገሯቸው ቋንቋዎች የኢትዮጵያ ፌዴራል እና የክልል የሥራ ቋንቋ ይሆናሉ። በዚህ መሰረት አፋን ኦሮሞ እና አማርኛ የፌዴራል ቋንቋ ይሆናሉ። አማርኛ እና አፋን ኦሮሞ የኦሮሚያ ክልል የሥራ ቋንቋ ይሆናሉ።

7. በኦሮሚያ (አዲስ አበባን ጨመሮ) አማርኛ፣ እንግሊዘኛ፣ አፋን ኦሮሞ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ይሰጣል። በሌሎች ክልሎች ከእንግሊዘኛ እና ከአማርኛ በተጨማሪ ሌላ ሦስተኛ የኢትዮጵያ ቋንቋ በትምህርት ቤቶች ይሰጣል። በደቡብ፣ በሶማሌ፣ በአፋር በመሳሰሉ ክልሎች ኦሮምኛ ትምህርት ባይሰጥም፣ በአማራው ክልል ከዘጠና በላይ በሚሆኑት አካባቢዎች (በጎጃም፣ በአብዛኛው ወሎ፣ በሸዋ) አፋን ኦሮሞ ትምህርት ይሰጣል። በሰሜን ጎንደር እና ሰሜን ወሎ ምናልባት ትግሪኛ መማር ህዝቡ ሊመርጥ ይችላል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ